የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 59፣ ኢሳ. 59:15–21፣ ኢሳ. 60:1-2፣ ኢሳ. 61፣ ኢሳ. 61:2።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “ሕዝቦች ወደ ብርሃንሽ፣ ነገሥታትም ወደ ብርሃንሽ ጸዳል ይመጣሉ” (ኢሳ. 60፡3)።
በ
ክርስቶስ ትምህርት ቤት መማር አለብን። የጸጋው ኪዳን በረከት ባለመብት
የሚያደርገን ሌላ ሳይሆን የእርሱ ጽድቅ ነው። እነዚህን በረከቶች እየናፈቅንና
ለማግኘት እየሞከርን ረጅም ጊዜ ብንቆይም ነገር ግን ልንቀበላቸው
አልቻልንም። ለዚህ መንስዔው ራሳችንን ለእነዚህ ነገሮች ብቁ ለማድረግ በራሳችን
ማድረግ የምንችለው ይኖራል የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ከፍ አድርገን በመመልከታችን
ነው። የሱስ ሕያው አዳኝ መሆኑን ብናምንም ዐይኖቻችንን ከራሳችን ላይ
አላነሣንም። የገዛ ሞገሳችንና በጎ ሥራችን ያድነናል ብለን አናስብ። ብቸኛው የመዳን
ተስፋችን የክርስቶስ ጸጋ ነው። ጌታ በነቢዩ አማካይነት የሚከተለውን የተስፋ ቃል
ሰጥቶናል፡ ‘ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም ሐሳቡን ይተው።
ወደ እግዚአብሔር
ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው
ብዙ ነውና’ (ኢሳ. 55:7)። እምነትን አስመልክቶ በገሃድ የቀረበውን የተስፋ ቃል
እንጂ ስሜትን አንቀበል። ሙሉ ለሙሉ በእግዚአብሔር ስንታመን፣ ኃጢአትን ይቅር
ባለው አዳኝነቱ--በየሱስ የጽድቅ ሥራዎች ላይ ስንመካ፣ የምንናፍቀውን እርዳታ
ሁሉ እንቀበላለን”—Ellen G. White, Faith and Works, p. 36.
በነቢዩ ኢሳይያስ ጽሑፎች የተገለጠውን ይህን ታላቅ እውነት ይበልጥ ጠለቅ ብለን
በዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን እንመለከታለን።
በኢሳ. 58፡3 ሕዝቡ እንዲህ ሲል እግዚአብሔርን ጠይቆ ነበር፡ “ ‘አንተ
ካልተቀበልኸው፣ ስለ ምን ብለን ጾምን? አንተ ከጉዳይ ካልቆጠርኸው፣ ስለ ምን
ራሳችንን አዋረድን?’ ”
በተቃራኒው፣ ኢሳ. 59፡1--እነሆ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን መች አጠረች፤ ጆሮውስ
መች መስማት ተሳናት? ሲል እግዚአብሔር ለማዳን እና ለመስማት የሚችል አምላክ
መሆኑን በመናገር ኢሳይያስ ይመልሳል (ኢሳ. 59፡1)። ሆኖም ያን ሳያደርግ ከቀረ ግን
ነገሩ ሙሉ በሙሉ ሌላ ጉዳይ ነው።
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኢሳ. 59፡2። በኢሳ. 59:1 የቀረበውን ጥያቄ
መመለስ የሚችል ምን ዓይነት መልእክት ተሰጥቶአል?
እግዚአብሔር ሕዝቡን ችላ ማለት የሚመርጠው ያን ማድረግ ምኞቱ ሆኖ አይደለም። ይልቁንም “በደላችሁ ከአምላካችሁ ለይቷችኋል” (ኢሳ. 59፡2) ሲል ኢሳይያስ ይናገራል። ኃጢአት በመለኮት እና በሰው ግንኙነት መካከል የሚያስከትላቸውን ውጤቶች አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ከቀረቡ ግልጽ መግለጫዎች አንዱን በዚህ ስፍራ መመልከት ይቻላል። ኢሳይያስ በመላው ሰብዓዊ ታሪክ የሚታየውን ይህን ነጥብ ማለትም፡ ኃጢአት ከጌታ ጋር ያለንን ግንኙነት አበላሽቶ ወደ ዘላለማዊ ውድመት ሊመራን የመቻሉን እውነታ በተቀረው ምዕ. 59 ያብራራል። ይህ የሆነው ኃጢአት እግዚአብሔርን ከእኛ በማራቁ አይደለም--እኛን ከእርሱ በማራቁ እንጂ! ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡8። ይህ ምሣሌ ከላይ በቀረበው አንቀጽ የተገለጸውን መርኅ እንዴት ያሳያል?
በመጀመሪያ--ኃጢአት እግዚአብሔርን አለመቀበል፣ ከእርሱ መራቅ ነው።
የኃጢአት ድርጊት ብቻ ከእግዚአብሔር አያርቅም። ነገር ግን የድርጊቱ ውጤት
ኃጢአተኛውን ይበልጥ ከጌታ እንዲርቅ ያደርገዋል። ኃጢአት ከእግዚአብሔር
የሚለየን እግዚአብሔር ወደ ኃጢአተኛው መድረስ ስለማይችል ሳይሆን፤ ኃጢአት
መለኮታዊ እቅዱን እንድንቃወም ስለሚያደርገን ነው (መላው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች
እግዚአብሔር ወደ ኃጢአተኞች ለመድረስና እነርሱን ለማዳን የሚያደርገውን ጥረት
ማሳየታቸው እሙን ነው)። በሕይወታችን ምንም ዓይነት ኃጢአት አለማድረጋችን
በእጅጉ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ይኸው ነው።
ኃጢአት ከእግዚአብሔር ጋር መለያየት እንዲፈጠር የሚያደርግበትን
እውነታ የተገነዘቡበት መንገድ ምን ይመስላል? በእርስዎ ልምድ
ለችግሩ ብቸኛው መፍትሔ ምንድነው?
ኢሳ. 59 የኃጢአትን ችግር አስመልክቶ አስገራሚ መግለጫ ይሰጣል። የተቀረው
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም እንዲሁ የመዋጀትን ተስፋ ሲሰጥ መመልከት እጅግ ደስ
ያሰኛል።
ለመጀመር--ቀዳሚው ጥያቄ፡ ስንቶቻችን ኃጢአት ሠርተናል? የሚል ሲሆን-ሁላችንም! ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ቁርጥ ያለ መልስ ይሰጠናል። ስለዚህ መቤዠት
በይቅርታ ላይ እንጂ (ኤር. 31፡34) በኃጢአት ማነስ ላይ መመስረት አይችልም። በዚህ
ጳውሎስ ይስማማል። ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል (ሮሜ 3፡9-20፣ 23)። ስለዚህ
በዚህ ረገድ ምንም ልዩነት ሊኖር አይችልም (ሮሜ 3፡22)። የጸደቁት እንደ ጻድቅ
የተቆጠሩበትን ፍትሕ ሊያገኙ የቻሉት በክርስቶስ መሥዋዕትነት የእግዚአብሔርን
የጽድቅ ስጦታ በመቀበላቸው ብቻ ነው።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 3፡21-24። እንዴት እንደዳንን አስመልክቶ
ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል? ስለ ፍርዱ ሂደት ምን ዓይነት ተስፋ ሊሰጡን
ይገባል?
በፍርድ ወቅት የሚቀርበው ጥያቄ፡ ኃጢአት የሠራው ማን ነው? የሚል ይሆናል
ብለው ብዙዎች ያስባሉ። ነገር ግን ይህ በጥያቄነት ሊቀርብ አይችልም፤ ምክንያቱም
ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል። ይልቁንም ጥያቄው፡ ይቅር የተባለው ማን ነው? የሚል
ይሆናል። እግዚአብሔር “በኢየሱስ የሚያምነውን” (ሮሜ 3፡26) ሲያጸድቅ ፍርዱ
ጻድቅ ይሆናል። በፍርዱ ውስጥ ወሳኙ ጉዳይ--በየሱስ በማመን ይቅርታን የተቀበለና
በመቀበሉ የቀጠለ ማን ነው? የሚለው ነው።
በሥራችን ፍርድ መቀበላችን እውነት ቢሆንም፤ የምንድንበት መንገድ በመሆኑ ግን
አይደለም። ይህማ ቢሆን እምነት ከንቱ በሆነ ነበር (ሮሜ 4፡14)። ይልቁንም ሥራችን
በእውነት የዳንን መሆናችንን ገልጦ ያሳያል (ያዕ. 2፡18)።
ሥራችን አሁንም ሆነ በፍርድ ወቅት ሊያድነን የማይችለው ለምንድን
ነው? ሮሜ 3፡20፣ 23።
መልካም ሥራ መሥራት ወይም ሕጉን መታዘዝ ማንንም አያድንም። ኃጢአተኛ
በሆነው ዓለም የሕጉ ዓላማ ማዳን ሳይሆን ኃጢአትን መጠቆም ነው። በእግዚአብሔር
መንፈስ በልባችን በፈሰሰው ፍቅር (ሮሜ 5፡5) “በፍቅር የሚገለጽ እምነት” (ገላ. 5፡
6) ግለሰቡ በየሱስ ሕያው እምነት እንዳለው ያሳያል (ያዕ. 2፡26)።
ሥራ አንድ ግለሰብ የሚያድን እምነት ባለቤት መሆኑን የሚጠቁም ውጪያዊ
መገለጫ ነው። ስለሆነም እውነተኛ ክርስቲያናዊ ተሞክሮ ሕጉን በመታዘዝ ለጌታ
የሚኖር የየዕለት ሕይወት ቁርጠኛ እምነት የሚገለጥበት መንገድ ነው።
በፍርድ
ወቅት እግዚአብሔር እንደ እርሱ የእምነት ሀሳቦችን ማንበብ ለማይችሉ ፍጥረታቱ
ሥራን እንደ ማስረጃ ይጠቀማል። ሥራ የተለወጠውን ሰው ተከትሎ የሚመጣ
ሲሆን፤ ህይወት በክርስቶስ እና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተሞላ ሲሆን ብቻ ከፍርዱ
ጋር አግባብ ይኖረዋል። ግለሰቡ ከመለወጡ አስቀድሞ ሲመራ የኖረው የኃጢአት
ህይወት በበጉ ደም ታጥቧል (ሮሜ 6)።
ይህ ጥቅስ ስለ ምን ይናገራል--ኢሳ. 60፡1-2? በመላው መጽሐፍ ቅዱስ የታየ ምን ዓይነት መርኅ በዚህ ስፍራ በሥራ ላይ ውሎ ይመለከታሉ? ምን ተስፋ ይሰጣል?
እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚያድንበት ሥዕል በኢሳ. 60፡1-2 ተሰጥቶናል። የግዞት ዘመንን ተከትሎ ገቢራዊ የሚሆነው እርሱ በጨለማ ውስጥ ብርሃን በሚፈነጥቅበት ተምሳሌታዊ አገላለጽ--የመጨረሻ ፍጻሜ የሆነውን የክርስቶስ ማዳን ያመላክተናል። በኢሳ. 60፡3--ብሔራትና ነገሥታት ወደ የትኛው የብርሃን ጸዳል ይመጣሉ?
በዕብራይስጥ በተጻፈው በዚህ መልእክት--እንስት ጾታ ያላት በነጠላ የቀረበች ሴት
እንመለከታለን (በተጨማሪ፡ ኢሳ. 60፡1-2 ይመልከቱ)። ይህች ሴት ቀደም ሲል
በቀረበው ምዕራፍ መጨረሻ አካባቢ (ኢሳ. 59፡20) በእንስት ጾታ የቀረበችው
“ጽዮን” እንደምትሆነ ይታመናል። ስለዚህ ጨለማ የሸፈናቸው የምድር ሕዝቦች ወደ
ጽዮን ይመጣሉ። እርሷ ላይ በፈነጠቀው አምላካዊ ክብር ብርሃን ይሳባሉ (ኢሳ. 60፡
2)። “ጽዮን የእርሷ ወደ ሆነው ብርሃን እንድትገባ፣ እንድትመለከትና በተመሳሳይ
ብርሃን ለተሰባሰቡ ሕዝቦች አጸፋዋን እንድትገልጽ ተጠርታለች”—J. Alec Motyer,
The Prophecy of Isaiah: An Introduction and Commentary, p. 494.
ጽዮን፣ የሩሳሌም ብትሆንም ጥልቅ ትኩረት የተሰጠው ለሕዝቡ እንጂ ለመልክአ
ምድሩ አለመሆኑን ልብ ይሏል።
ቀሪው የኢሳ. 60 ክፍል በቁ. 1-3 የቀረበውን ጭብጥ ያዳብራል፡ የሩሳሌም በክብር
በተሞላው አምላካዊ ሕልዎት ምክንያት በመባረኳ የዓለም ሕዝቦች ወደ እርሷ
ይሳባሉ።
ይህ ትንቢት እግዚአብሔር ለአብርሃም ከገባው ኪዳን ጋር እንዴት
ይነጻጸራል? ዘፍ 12:2-3 የሚናገረው አንድ ዓይነት ነገር አይደለም?
እግዚአብሔር አብርሃምንና ዘሩን ሲመርጥ ዩኒቨርስ ዓቀፍ ዓላማ ነበረው፡ የምድር
ወገኖች ሁሉ በአብርሃም በኩል ይባረካሉ (ዘፍ. 12፡3፣ ዘፍ. 18፡18፣ ዘፍ. 22፡18)።
ስለዚህ፣ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባው ኪዳን ውሎ አድሮ በአብርሃም
በኩል ከመላው ሰብዓዊ ዘር ጋር ኪዳን እንዲሆን የታቀደ ነበር። እርሱ እና ዘሩ
የእግዚአብሔር ለዓለም መገለጫ መንገድ ይሆናሉ።
ኢሳይያስ ሕዝቡን ወደ ቀደመው ጥንታዊ ዩኒቨርስ አቀፍ ማንነት ለመመለስ ተመኘ።
የእውነተኛው አምላክ ተወካዮች እንደመሆናቸው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለዓለምም
ኃላፊነት ነበረባቸው። እግዚአብሔርን ይሹ የነበሩ መጻተኞች መልካም አቀባበል
ማድረግ ነበረባቸው (ኢሳ. 56፡3-8)፡--“ቤቴ፣ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ተብሎ
ይጠራል” (ኢሳ. 56፡7)።
ከዚሁ ዐውድ ሳንወጣ፣ የሰባተኛ-ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ
ቤተክርስቲያንን ወይም በተለይ እርስዎ በዚህች ቤተክርስቲያን ውስጥ
ያሎትን ሚና እንዴት ይረዱታል?
በኢሳ. 61፡1 ላይ እየተናገረ ያለው ማን ነው?
የእግዚአብሔር መንፈስ በዚህ የተቀባ ሰው ላይ ነው፣ ይህም ማለት እርሱ መሲህ ነው
ማለት ነው። “ለድኾች የምሥራች እንድሰብክ… ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣
ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል” (ኢሳ. 6፡11)።
ስለ ማን እየተናገረ ያለ ይመስላል? የእግዚአብሔር ባሪያ በእጅጉ ተመሳሳይ በሆነ
አገላለጽ ከቀረበበት ኢሳ. 42፡61፡1 ጋር ያስተያዩ።
ኢሳ. 61፡2 ስለ “ተወደደው የእግዚአብሔር ዓመት” ይናገራል። በዳዊታዊ ንግሥና
እና አዳኝነት የተቀባው መሲህ ነጻነትን ሲያውጅ ስለ ተወደደው የእግዚአብሔር
ዓመት በይፋ ይናገራል። እስራኤላውያን በተቀደሰው ሃምሳኛ ዓመት ነጻነትን
እንዲያውጁ እግዚአብሔር ካዘዛቸው ዘሌዋ. 25፡10 ጋር ያስተያዩ፡ “ይህም ኢዮቤልዩ
ይሁንላችሁ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደ ቤተሰቡ ርስት፣ ወደ ወገኑም ይመለስ።”
ይህ ማለት የገጠማቸውን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ብለው ከአባቶቻቸው የወረሱትን
መሬት ለመሸጥ የተገደዱ ወይም በባርነት ቀንበር ስር የወደቁ (ዘሌዋ. 25፡ 5-55)
ሰዎች፤ መሬታቸው እና ነጻነታቸው ይመለስላቸዋል። የኢዮቤልዩ ዓመት ይጀምር
የነበረው በሥርየት ቀን የሚነፋውን መለከት (ዘሌዋ. 25፡9) ተከትሎ እንደ ነበር
የሚያመለክተውን ይህንን ክፍል ከኢሳ. 58 ጥናታችን ጋር በተያያዘ ቀደም ብለን
ጠቅሰነዋል።
በኢሳ. 61፡2 የቀረበው “የተወደደው የእግዚአብሔር ዓመት” የሆነው ኢዮቤልዩን
የሚመስል ዓመት፣ በዘሌዋ. 25 የቀረበውን መልእክት ስለ ማክበር የቀረበ ብቻ
አይደለም። ይህ ዓመት መሲህ እና ንጉሥ በሆነው ጌታ የታወጀው፣ ሕዝቡን
ሊያገለግልና ወደ ቀደመ ንጽህና ሊመልስ ራሱን በገለጠ ጊዜ ነበር። ይህ ክስተት
በንግሥናቸው መጀመሪያ አካባቢ--በዕዳ የተያዙ ግለሰቦችን ነጻነት እያወጁ ማኅበራዊ
በጎነትን ከፍ ከፍ ያደርጉ ከነበሩ አንዳንድ የጥንት ሞሶፓታሚያ ነገሥታት ጋር
ተመሳሳይነት ነበረው። ነገር ግን የመሲህ አገልግሎት በዘሌዋ. 25 የቀረበውን ወሰን
አልፎ የሚጓዝ ነበር። እርሱ “ለምርኮኞች ነጻነትን” ማወጅ ብቻ ሳይሆን የተሰበረውን
ልብ ይጠግናል፣ ያዘኑትን ያጽናናል እንዲሁም ወደ ቀደመ ደኅንነታቸው ይመልሳል
(ኢሳ. 61፡1-11)። ከዚያ አልፎ፣ “ከተወደደው የእግዚአብሔር ዓመት” በተጨማሪ
“የአምላካችንንም የበቀል ቀን” ያውጃል” (ኢሳ. 61፡2)።
የኢሳይያስ ትንቢት መቼ ተፈጸመ--ሉቃ. 4፡16–21?
የየሱስ
አገልግሎት ይህን ያከናወነው እንዴት ነበር? ደግሞም ይህን አስፈላጊ
ጥያቄ ራስዎን ይጠይቁ፡ እኛ የሱስ አለመሆናችን እርግጥ ነው። ነገር
ግን በዚህ ምድር እነርሱን መወከል ደግሞ ይኖርብናል። በኢሳ. 61፡
1-3 በተገለጠው መሰረት ውሱን በሆነው ችሎታችን እኛ ማድረግ
የሚኖርብን እና መሲህ የሚያደርጋቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
እነዚህን ነገሮች ማድረግ የምንችልባቸው አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች
የትኞቹ ናቸው?
በኢሳ. 61 እንደተመለከተው በዚህ ሁሉ የምሥራች መሃል መሲህ የእግዚአብሔርን የበቀል እርምጃ ለምን ያውጃል? ይህ ትንቢት የሚፈጸመው መቼ ነው?
መሲሁ የሱስ በናዝሬት ወደ ምኩራብ ገብቶ ከኢሳይያስ ጥቅልል መጽሐፍ ምዕ. 61
በመግለጥ “የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል” (ኢሳ. 61፡2፣ ሉቃ.
4፡19) የሚለውን ክፍል አነበበ።
ከዚያም “ይህ በጆሮአችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” (ሉቃ. 4፡21)
አላቸው። ነገር ግን የዚያው ጥቅስ አካል የነበሩትን “የአምላካችንንም የበቀል ቀን
እንዳውጅ” (ኢሳ. 61፡2) የሚሉትን ቃላት ሳያነባቸው ቀረ። የመልካም የምሥራች፣
የነጻነት እና የመጽናናት አገልግሎቱ ወገኖችን ከሰይጣን የጭቆና ቀንበር ነጻ
ማውጣት የጀመረበት እንደመሆኑ፤ የበቀል ቀን ገና አልመጣም ነበር። በማቴዎስ
24 (ማር. 13፣ ሉቃ. 21) መለኮታዊ ፍርድ ወደፊት እንደሚመጣ ለደቀ መዛሙርቱ
ተንብዮአል።
በኢሳ. 61 የቀረበው የጌታ የበቀል ቀን የሆነው “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር
ቀን” (ኢዮ. 2፡31፣ ሚልክ. 4፡5) ፍጻሜ የሚያገኘው ክርስቶስ ዳግም ተገልጦ ጠላቶቹን
ድል በማድረግ የተጨቆኑ ትሩፋን ሕዝቦቹንና ምድርን ከኢፍትሐዊነት ነጻ ሲያወጣ
ነው (ራእ. 19፣ ዳን. 2፡44-45)። ስለዚህ ምንም እንኳ ክርስቶስ “የተወደደችው የጌታ
ዓመት” መጀመሯን ቢያበስርም፤ ድምዳሜ የምታገኘው በዳግም ምጽአቱ ነው።
አፍቃሪ ስለሆነው አምላክ ያሎትን አስተሳሰብ በቀል እንደሚኖር ከገባው
ቃል ጋር እንዴት ያስታርቁታል? ሀሳቦቹ ይጣጣማሉ? ወይስ በቀልን
እንደ ፍቅር መገለጫ አድርገው ያስተውሉታል? እንዴት? መልስዎን
ያብራሩ።
ምንም እንኳ የሱስ ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላኛውንም አዙርለት (ማቴ. 39) ብሎ
ቢነግረንም፤ በሌላ ስፍራ ግን ፍትሕ እና ቅጣት ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸው
በግልጽ አስቀምጦአል (ማቴ. 8፡12)። በተመሳሳይ ጳውሎስ “ማንም በክፉ ፋንታ
ክፉ እንዳይመልስ” (1ተሰ. 5፡15) ብሎ ቢናገርም፤ ነገር ግን ጌታ በሚንበለበል እሳት
በሰማይ ሲገለጥ “እግዚአብሔርን የማያውቁትን ይበቀላል” (2ተሰ. 1፡8) ይለናል።
ልዩነቱ፣ ጌታ ወሰን በሌለው ጥበቡና ምኅረቱ እርሱ ብቻ ፍትሕ እና በቀልን ሙሉ
በሙሉ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማምጣት የሚችል አምላክ መሆኑ ነው። ሰብዓዊ
ፍትሕ እና ሰብዓዊ በቀል ከሁሉም ሰብዓዊ ድክመቶች፣ ጉድለቶች፣ እና አለመጣሞች
ጋር አብሮ ይከሰታል። የእግዚአብሔር ፍትሕ ግን ከእነዚህ አንዱንም ውስንነት
አያካትትም።
ክፉ ድርጊት በፈጸመ ሰው ላይ የበቀል እርምጃ ሲወሰድ ማየት የሚሹት
በየትኛው ላይ ነው? (1) እርስዎ የማይወዱትን ሰው በጎዳው ላይ? (2)
እርስዎ በሚወዱት ሰው ላይ ጉዳት ባደረሰው ላይ? እግዚአብሔር ለእኛ
ባለው ፍቅር እና በበቀል ማስጠንቀቂያዎች መካከል ያለውን ግንኙነት
በተሻለ መረዳት እንችል ዘንድ ይህ እንዴት ይረዳናል?
በተጨማሪ የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት በሚለው
መጽሐፍ “ከሲና እስከ ቃዴስ” በሚለው ምዕራፍ ስር ከገጽ 427 – 428
ያንብቡ። እንዲሁም የዘመናት ምኞት መጽሐፍ ከገጽ 226-233 ያንብቡ።
“የሱስ ስለ እርሱ የተነገሩትን ትንቢቶች በሕዝቡ ፊት በአካል ተገኝቶ ተረጎመ።
ያነበበውን ሲያብራራ መሲሑ ጭቁኖችን ከጭቆናቸው እንደሚያላቅቅ፣ ምርኮኞችን
ነጻ እንደሚያወጣ፣ ሕሙማንን እንደሚፈውስ፣ ዐይነ ሥውራንን እንዲያዩ
እንደሚያደርግና ለዓለም እውነትን እንደሚያሳውቅ ተናገረ። ንግግሩ አድማጮችን
ከዚያ በፊት ተሰምቷቸው በማያውቅ ኃይል አነቃቃቸው። የመለኮታዊ በጎ ተጽዕኖ
ማዕበል እንቅፋቱን ሁሉ ስለ ደመሰሰው እንደ ሙሴ ሊታይ የማይቻለውን አምላክ
አዩ። ልባቸው በመንፈስ ቅዱ ስለተነካ በጋለ ስሜት አሜን በማለት እግዚአብሔርን
አወደሱ።” የዘመናት ምኞት፡ ገጽ 228።
“የእግዚአብሔር የበቀል ቀን--የእርሱ ቁጣ ቀን ይመጣል። እርሱ በሚገለጥበት ቀን
ጸንቶ የሚቆም ማን ነው? ሰዎች ልባቸውን በእግዚአብሔር መንፈስ ላይ አደንድነዋል።
የእምነት ፍላጻ ሊበሳው ያልቻለውን፣ የቁጣው ፍላጻ ግን ይበሳዋል። ስለዚህ ጌታ
ኃጢአተኛውን ሊማጸን አይገለጥም። በዚያ ቀን ሐሰተኛ እረኞች ለተላላፊው ጋሻ
ይሆኑታል? ከብዙሃን ጋር በአመጽ ጎዳና የተጓዘው ይቅርታ ሊደረግለት ይችላል? ዝና
ወይም የቁጥር ብዛት ከጥፋተኝነት ነጻ ያደርጋል? እነዚህ፤ ግዴለሾች እና ግዴለም
የሚሉ አጥብቀው ሊያጤኗቸውና ለራሳቸው መፍትሔ ሊፈልጉላቸው የሚገቡ
ጥያቄዎች ናቸው።”—Ellen G. White, Faith and Works, p. 33.
1. አንድ ብልህ የሰባተኛው ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ፓስተር
እንዳሉት የእርሳቸው ቁጥር አንድ ችግር፡ የቤተ ክርስቲያን አባላት
ሌሎች እንዲቀላቀሏቸው አለመፈለጋቸው ነው። አባላት ወደ ቤተ
ክርስቲያናቸው የሚመጡትን ሰዎች ለመቀበል የማይፈልጉ ከሆነ፤
ለመሆኑ ከዳግም ምጽአቱ አስቀድሞ (ማቴ. 24፡14) ሌሎች የመዳን
ዕድል የሚያገኙትና “ክርስቲያኖች” የክርስቶስን መንግሥት ፍቅር፣
ተስፋና የምሥራች ለዓለም ማድረስ የሚችሉት እንዴት ነው?
ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር አመጸኞችን በማስወገድና ከእርሱ እንዲለዩ
ካደረጋቸው ኃጢአቶች የተመለሱ ትሩፋኑን መልሶ በማቋቋም ኢፍትሐዊውን
ማሕበረሰብ ያጸዳል። ከአምላካዊው ሕልዎት በረከት የተነሳ--ከሌሎች
ብሔራት የተውጣጡ ሕዝቦችም በመሲህ በታወጀው እና በተሰጠው፣
በተወደደው የእግዚአብሔር ዘመን ሐሴት ያደርጉ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር
እና ሕዝቡ ይፈልሳሉ።