የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 55:1– 7፣ ኢሳ. 55:6–13፣ ኢሳ. 58:1–12፣ ኢሳ. 58:13-14።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ለተራበው ብትራራለት፣ የተገፉት እንዲጠግቡ ብታደርግ፣ ብርሃንህ በጨለማ ይበራል፤ ሌሊትህም እንደ ቀትር ፀሐይ ይሆናል” (ኢሳ. 58፡10)
በ
ነብራስካ ሊንከን የሚኖሩ አንድ የአይሁድ ቤተ አምልኮ መሪ እና
ባለቤታቸው ጸያፍ የማስፈራሪያ የስልክ ጥሪዎች መቀበል ጀመሩ። ጥሪዎቹ
የመጡት ኩ ክሉክስ ክላን በመባል ከሚታወቅ፣ በአሜሪካ የነጭ የበላይነትን
ከሚያቀነቅን አንድ የጥላቻ ቡድን መሪ መሆኑን ደረሱበት። የግለሰቡን ማንነት
በማወቃቸው ለፖሊስ አሳልፈው ሊሰጡት ይችሉ ነበር። ሆኖም የተሻለ መሰረታዊ
አቀራረብ መፍጠር እንዳለባቸው አሰቡ። ሰውየው እግሮቹ የማይራመዱለት
(ሽባ) መሆኑን ሲገነዘቡ፤ ሽክን ያለ ዶሮ ሠርተው በእራት ሠዓት በራፉን አንኳኩ።
ግለሰቡ በተመለከተው ነገር ተደመመ። ጥላቻው በፊታቸው ፍቅር ቀለጠ። ባልና
ሚስቱ ጉብኝታቸውን ስለ ቀጠሉ ጓደኝነታቸው ማደግ ጀመረ። ግለሰቡ ይባስ ብሎ
የአይሁድ እምነት ተከታይ እስከ መሆን ማሰብ ጀመረ!
“እንግዲህ እኔ የመረጥሁት ጾም፣ የጭቆናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣ የቀንበርን
ገመድ እንድትፈቱ፣ የተጨቆኑትን ነጻ እንድታወጡ፣ ቀንበርን ሁሉ እንድትሰብሩ
አይደለምን? ምግብህን ለተራበ እንድታካፍለው... አይደለምን? (ኢሳ. 58፡6-7)።
የሚገርመው በሊንከን ይኖሩ የነበሩት እነዚህ ባልና ሚስት እንዲህ ዓይነቱን ጾም
በመጾምና ምግባቸውን ለተራበው በማካፈል፣ ግለሰቡ ከተተበተበበት ኢፍትሐዊ
ጭፍን የጥላቻ ሰንሰለት በጣጥሰው ነጻ አወጡት!
በነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ተመለከተው ስለዚህ አስፈላጊ መንፈሳዊ መርህ የበለጠ
መማራችንን እንቀጥል።
ጥቅሱን ያንብቡ፡ “እናንት የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፤ እናንት ገንዘብ የሌላችሁ፣ ወደ ውሆች ኑ፤ ኑና ግዙ፤ ብሉም” (ኢሳ. 55፡1)። እዚህ ላይ የሚመለከቱት ተቃርኖ ምን ይመስላል?
ለምሳሌ አንድ ሰው በአንድ ትልቅ ከተማ አውራ ጎዳና ቆም ብሎ “እናንት ገንዘብ
የሌላችሁ ምስኪኖች፤ ኑና ይህን ምግብ እየገዛችሁ ብሉ!” ቢል፤ ገንዘብ ከሌላቸው
እንዴት ገዝተው መብላት ይችላሉ?
ሆኖም እንደ ኢሳይያስ “ያለ ገንዘብ፣ ያለ ዋጋ” (ኢሳ. 55፡1) የሚሉትን ቀጣይ ቃላት
ካካተትን፤ እንዲያመለክት የተፈለገው ነጥብ ግልጽ ይሆናል። ሰዎች በነጻ ይቅርታ
ይቀበሉ ዘንድ ኢሳይያስ ተማጽኖ ያቀርባል (ኢሳ. 55፡7)። ሆኖም መግዛት የሚለው
ቃል--ሰዎች የሚያስፈልጓቸው እና እንዲኖራቸው የሚመኟቸው ነገሮች መሟላት
እንዲችሉ እግዚአብሔር የሚሰጣቸው ነገሮች ዋጋ እንዳላቸው ያሳያል። ስለዚህ
ይህን ለመቀበል ግብይት ማድረግ የግድ ይላል።
እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር በገባው
የቀደመ ኪዳናዊ መዋቅር ግንኙነት ለሕዝቡ ይቅርታን በነፃ ይሰጣል። ሆኖም በነፃ
የሚሰጠው እርሱ ነፃ ሆኖ አግኝቶት ሳይሆን፡ የገዛ ባሪያው በአሰቃቂ ሁኔታ በደም
ተነክሮ በከፈለው ዋጋ ነው። ነጻ ቢሆንም፤ አስገራሚ ዋጋ አስከፍሎታል።
ለመዳናችን የተከፈለው ዋጋ ምን ነበር? 1ጴጥ. 1:18-19።
ኢሳይያስ ስለ መዳን ያለው አቋም ከአዲስ ኪዳን ጋር እንዴት ይነጻጸራል? ኤፌ. 2:8-9
ኢሳይያስ ጠቅለል አድርጎ የሚያቀርበው የብሉይ ኪዳን ወንጌል፣ ከአዲስ ኪዳን
ወንጌል ጋር አንድ ነው። በ “አዲስ ኪዳን” ጸጋ የሚሻር--በሥራ ደኅንነት የሚገኝበት
“አሮጌ ኪዳን” አልነበረም። እግዚአብሔር ለአዳምና ሔዋን የደኅንነት ተስፋ ቃል
ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮ (ዘፍ. 3፡15) ለመዳን አንድ ብቻ መንገድ አለ፡ በጸጋ በእምነት
(ኤፌ. 2፡8)፤ “የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላም
ሕይወት ነው” (ሮሜ. 6፡23)። ዘላለማዊ ሕይወት ለማግኘት በጀግንነት የተሞላ
ከንቱ ፍለጋ ካደረገው ጥንታዊው ጊልጋሜሽ--ከሞት በኋላ ነፍስ በሌላ መልክ ወደ
መሬት ትመለሳለች ብለው እስከሚያምኑ ዘመናዊ አርቲስቶች--ሰዎች የተለያዩ የመዳን
መንገዶችን ሞክረዋል፤ ግን ሁሉም ፍሬ አልባ ናቸው። ስለ የሱስ እና በመስቀል ላይ
ስላከናወናቸው ሥራዎች ማወቅ የሚያስፈልጋቸው በዚህ የተነሣ ነው።
ደኅንነት በነጻ የተሰጠ በመሆኑ የግላችን ለማድረግ ምንም የምናደርገው
ነገር የለም። ሥራችን እኛን ለማዳን ፈጽሞ ብቁ ሊሆን አይችልም።
ሆኖም በተመሳሳይ፤ ማንኛውንም ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል። ይህ
ምን ማለት ነው? ለምሳሌ፣ ማቴ. 10፡39፣ ሉቃ. 9፡23፣ 14፡26፣
ፊልጵ. 3፡8።
እግዚአብሔር “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ” የእርሱ አስተሳሰቦችና መንገዶች ከእኛ ከፍ ያሉ መሆናቸውን የሚናገረው ለምንድን ነው? (ኢሳ. 55፡8-9) ያ ምን ማለት ይመስሎታል?
አእምሯችን ሊገነዘባቸው የማይችላቸውን አንዳንድ ምስጢራዊ ባህሪያት የተላበሱ ቀላል ነገሮችን ብቻ ሳይሆን፣ መላውን አጽናፈ ሰማይ (ዩኒቨርስ) የሠራውን አምላክ መንገዶች ፈጽሞ ማስተዋል የማንችል መሆኑ ጥርጥር የለውም። ማብቂያ የሌለውን ይህን ታላቅነቱን መገንዘባችን እርዳታውን በቀላሉ በትህትና መቀበል እንድንችል ያደርገናል (ኢሳ. 57፡15)። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኢሳ. 55፡6-9። የጌታ መንገዶች እና ሀሳቦች እኛ ማሰብ ከምንችለው በላይ የላቁ ስለ መሆናቸው የሚናገርበት ዐውድ ምን ይመስላል? እርሱ የሚያደርገውን ነገር መገንዘብ ለእኛ አዳጋች መሆኑን ሲናገር ምን ማለቱ ነው?
በመላው አጽናፈ ሰማይ ከሚገኙ ታላላቅ ምስጢሮች ሁሉ በእጅጉ የላቀው--ላመል
ያህል ለማስተዋል እየተፍጨረጨርን የምንገኝበት የደኅንነት እቅድ ለመሆኑ ጥርጥር
የለውም (ኤፌ. 6፡19)። የአጽናፈ ሰማይ ፈጣሪ ራሱን እጅግ ዝቅ አድርጎ ሰብዓዊውን
ሥጋ መልበሱ፣ ብርቱ ድካምና ሥቃይ የተሞላው ህይወት መኖሩ፣ እኛን ይቅር
ማለት ይችልና ምኅረት ያሳየን ዘንድ የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ስለኛ የመሞቱ
ይህ እውነታ፤ ሕያው ሆነው የሚኖሩ የእግዚአብሔር ፍጥረታትን ልብ ለዘላለም
ሲያስገርም የሚኖር ጉዳይ ነው።
“የመቤዠት ጭብጥ መላእክት በጥልቅ ሊመረምሩት የሚመኙት ጉዳይ ነው። የዳኑት
ፍጻሜ በሌለው ዘላለማዊነት የሚማሩት ሳይንስ እና የሚያዜሙት መዝሙር ይሆናል።
አሁንስ ቢሆን ጥንቃቄ የተሞላው እሳቤ እና ጥናት የሚሻ ጉዳይ አይደለምን? . . .
“የማያልቅ ርዕሰ ጉዳይ ነው። የክርስቶስ ሥጋ መልበስ፣ የሥርየት መሥዋዕትነቱና
የማማለድ ሥራው፣ ትጉ ተማሪ ማብቂያ ለሌላቸው ዘመናት የሚማረው ትምህርት
ይሆናል። ፍጻሜ ወደማያውቃቸው ሰማያት ይመለከትና ‘የእውነተኛ መንፈሳዊ
ሕይወት ምስጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው’ ሲል በደስታና በአድናቆት ይናገራል።”—
Ellen G. White, My Life Today, p. 360.
መጥፎ ድርጊቶችዎን ይመልከቱ። የጎዷቸውን ሰዎች፣ የተናገሯቸውን
ደግነት የጎደላቸው ቃላት፣ ሌሎችን ያሳዘኑባቸውን አካሄዶች…።
ይህም ቢሆን፤ እነዚህ ነገሮች በሙሉ በየሱስ ይቅር ተብለው፣ ፍጹም
እና ጻድቅ ሆነው በእግዚአብሔር ፊት መቆም ይችላሉ። እንግዲህ ይህ
ምስጢር ካልሆነ፣ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?
“ጾም” በኢሳ. 58፡3 የተጠቀሰበት ዐውድ ምን ይመስላል?
ይህ በእግዚአብሔር የታዘዘው ብቸኛ የሥርየት ቀን ጾም ሳይሆን እንደማይቀር
ይታመናል (ዘሌዋ. 16:29፣ 31፣ ዘሌዋ. 23:27–32)። ልብን ትሁት ስለ ማድረግና
ራስን ስለማዋረድ የሚናገረው በኢሳ. 58፡3 የቀረበው አገላለጽ ከዘሌዋውያኑ
መልእክት ጋር ትይዩ ሆኖ እናገኘዋለን። ራስን ትሁት ማድረግ ወይም ዝቅ ማድረግ
ጾምን ጨምሮ የተለያዩ ራስን የመካድ መንፈሳዊ ቅርጾች ጋር ይወሳል (መዝ. 35፡13፣
ዳን. 10፡2-3፣ 12)።
የሥርየት ቀን “ድምፅህን እንደ መለከት አሰማ” (ኢሳ. 58፡1) የሚለውን የእግዚአብሔር
ትእዛዝ ያብራራል። ይህ ዓይነቱ ከበግ ቀንድ የተሠራ ቀንደ መለከት የሥርየት ቀን
ከመድረስ አስር ቀን በፊት ይነፋ ነበር (ዘሌዋ. 23፡24)። በተጨማሪ በየአምሳኛው
ዓመት የሥርየት ቀን፣ አዲሱ የኢዮቤልዩ የነፃነት ዓመት--መታወጅ ነበረበት (ዘሌዋ.
25፡9-10፣ ኢሳ. 27፡ 13)።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 58፡3-7። ጌታ ምን ዓይነት ምሬት
እያቀረበባቸው ነበር? የእነርሱ “ጾም” ምን ችግር ነበረበት?
ሰዎቹ ስላሳዩት “ቅድስና” ጌታ እንዲያመሰግናቸው የፈለጉ ይመስላል። እርግጥ
ነው፣ የተጓዙት የኋሊት ነበር። በሥርየት ቀን ሊቀ ካህናቱ ቤተ መቅደሱን ለማንጻት
ማለትም ይቅር ከተባሉት ኃጢአት (ዘሌዋ. 16 ከምዕ. 4 ጋር ያስተያዩ) እነርሱን
ለማንጻት በእግዚአብሔር ፊት ሲያልፍ፣ ራሳቸውን የሚክዱትና የሚያዋርዱት
ለእርሱ ምስጋና ለማቅረብና ታማኝነታቸውን ለመግለጽ ነበር። ይህ ተግባራቸው
ከፍርድ ቀን ላዳናቸው አምላክ ምስጋና የሚያቀርቡበት እንጂ ስለ “ቅድስናቸው”
እና “አምልኮአቸው” የእግዚአብሔርን አድናቆት የሚቀበሉበት አልነበረም። ደግሞስ
የእግዚአብሔርን መቅደስ ያረከሰው የሕዝቡ ኃጢአት አልነበር? ስለዚህ ስለ እነርሱ
ድርጊት በፈሰሰ ደም መንጻት ነበረበት።
በእነዚህ ጥቅሶች ከምናገኛቸው ወሳኝ ትምህርቶች አንዱ፣
በኃይማኖተኝነት እና በእውነተኛ የክርስቶስ ተከታይነት መካከል
ያለውን ልዩነት ያመለክታል። በዚህ መሃል ያለውን ልዩነት እንዴት
እንመለከተዋለን? እኛ፣ እንደ ግለሰብ በዚህ ከቀረቡት ተመሳሳይ
አደጋዎች ጋር የምንጋፈጠው እንዴት ነው? ኃይማኖታዊ ትውፊቶቻችንን
መጠበቃችን ጌታ እንደሚጠይቀን በእውነት እየተከተልነው እንደሆነ
ምን ያህል ያሳያሉ?
በሥርየት ቀን ጌታ እንደዚህ ሕዝብ ንጉሥነቱ ከፍተኛ ክብርና ምስጋና ይቀበላል።
እነዚህ ሕዝቦች ራሳቸውን በመካድ ለእርሱ ያላቸውን ታማኝነት ያጸኑ ዘንድ፤ ቀንደ
መለከቱ ለተከታታይ አሥር ቀናት እየተነፋ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያሳስባል። ነቢዩ
ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ ማመጹን ለመንገር ድምፁን እንደ መለከት ከፍ አድርጎ
ያሰማል (ኢሳ. 58፡1)።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 58፡6-12። እግዚአብሔር እንደ እውነተኛ
ራስን የመካድ እርምጃ የሚቆጥራቸው ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው?
ጥቂት የምግብ ሰዓቶችን ከመዝለል እና ጊዜና ገንዘብን ተጠቅሞ
በከተማዎ የሚገኙ ቤት የሌላቸውን ወገኖች ከመመገብ የቱ ይከብዳል?
ከእነዚህ ድርጊቶች በስተጀርባ መታየት ያለበት መርኅ ምንድን ነው?
እነዚህ ድርጊቶች እውነተኛ ኃይማኖትን የሚያካትቱት እንዴት ነው?
ማንኛውም ሰው ኃይማኖተኛ ሊሆን ይችላል። ማንኛውም ሰው ሁሉንም ትክክለኛ
ቀመሮች ባካተቱ ኃይማታዊ ሥርዓቶች ውስጥ ሊያልፍ ይችላል። ነገር ግን ጌታ
የሚፈልገው ያን ብቻ አይደለም። ወደ የሱስ ሕይወት ይመልከቱ። እርሱ ለነበረበት
ኃይማኖታዊ ሥርዓት የቱንም ያህል ታማኝ የነበረ ቢሆንም፤ የወንጌል ጸሐፊዎች
አብልጠው ትኩረት ያደረጉት ከዚህ ይልቅ--ምኅረቱ፣ ፈውሱ፣ መመገቡ እና
ይቅርታው አጥብቆ በሚያስፈልጋቸው ወገኖች ዙሪያ ነበር።
ጌታ እውነትን ለዓለም የምትሰብክ ቤተክርስቲያን፣ ሕዝብ ይፈልጋል። ነገር ግን
በየሱስ እንደ ሆነው ሕዝቦችን በተሻለ ወደ እውነት የሚስበው--አምላካዊውን
ሕግጋት በጥብቅ መታዘዝ ነው ወይስ የተራበውን የመመገብ ፈቃደኝነት? ሳያወላዱ
በሰንበት ማረፍ ወይስ ጊዜዎንና ጉልበትዎን ችግረኞችን ለመርዳት ለማዋል ፈቃደኛ
መሆን?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 25፡40፣ ያዕ. 1፡27። ምን ይነግሩናል?›
በችግር ውስጥ ያሉ ምስኪኖችን ማገልገል ለሚሹ እግዚአብሔር
ያዘጋጀላቸውን በረከቶች በኢሳ. 58 ይመልከቱ። ጌታ በዚህ ቦታ ምን
እያለ ይመስሎታል? የተባሉትን የምናደርግ ከሆነ እነዚህ የመለኮታዊ
ጣልቃ ገብነት የተስፋ ቃሎች ሕይወታችንን ይጎበኛሉ? ወይስ
ከስግብግብነት፣ ከስስትና ከራስወዳድነት በተቃራኒ ራሳችንን ለሌሎች
በመስጠት ስለምንቀበለው ተፈጥሮአዊ በረከት እየተናገረ ነው?
መልስዎን ያብራሩ።
ኢሳይያስ በእነዚህ ጥቅሶች ስለ ሰንበት ያነሣው ለምንድን ነው፡ ኢሳ. 58፡13-14? ቀደም ካሉት የሥርየት ቀን ቁጥሮች መቼት ወይም መነሻ ቦታ ጋር ምን ግንኙነት አለው?
ዓመታዊው የሥርየት ቀን የሰንበት ቀን ነበር። ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሥርዓታዊ
ሰንበት ቀን እንደ ማንኛውም ሣምንታዊ የሰንበት ቀን ምንም ዓይነት ሥራ
እንዳይሠራበት የተከለከለ ነበር (ዘሌዋ. 23፡27-32)። ስለዚህ ቀደም ባሉት ሰባተኛ
ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች (አድቬንቲስቶች) ተለይቶ እንደተቀመጠው፣
ከምሽት እስከ ምሽት (ዘሌዋ. 23፡32) የሚቆየው የሥርየት ቀን የሚያርፍበት ጊዜ
ከሣምንቱ ሰንበት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ይጠቁመናል። በተመሳሳይ ምንም እንኳን
የኢሳ. 58፡13-14 ቀዳሚ ዐውድ ሥርዓታዊው የሥርየት ቀን ቢሆንም፤ መልእክቱ
ሣምንታዊውን ሰንበትም ይመለከታል።
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኢሳ. 58፡13። ሰንበት ምን ዓይነት ቀን መሆን
አለበት? የሰንበት ልምዳችንን እዚህ ላይ እንደተገለጸው ማድረግ
የምንችለው እንዴት ነው? ደግሞም ሰንበት ስለሚወክለው ነገር
ሲያስቡ፤ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተገለጸው ዓይነት ቀን መሆን ያለበት
ለምንድን ነው?
ኢሳ. 58 ስለ ሦስት ዋና ዋና ጭብጦች ይናገራል፡ ራስን ስለመካድ፣ ስለ
ማኅበራዊ በጎነት እና ስለ ሰንበት።
በመካከላቸው ያሉ ግንኙነቶች ምንድናቸው?
በመጀመሪያ ሦስቱም በእግዚአብሔር ላይ በማተኮር እርሱ ቅድሚያ በሚሰጣቸው
ነገሮች እና በእርሱ ላይ ጥገኞች መሆናችንን ማወቅንና መቀበልን ያካትታሉ። ሰዎች
እነዚህን ሦስቱንም በተግባር ላይ እያዋሉ፣ በክርስቶስ መልክ ራሱን ዝቅ ያደረገውን
(ፊልጵ. 2፡8)፣ ራስን መሥዋዕት አድርጎ የመስጠት ደግነት ያሳየውን (ዮሐ. 3፡16)
እና በፍጥረት ሣምንት መጨረሻ ላይ በሰንበት ከሥራው ያረፈውን (ዘፍ. 2፡2-3፣
ዘፀ. 20፡11) እግዚአብሔርን እየመሰሉ የቅድስናን መንገድ ይከተላሉ (ዘሌዋ. 19፡2)።
በኢሳ. 58 እንደ ቀረበው--ራስን በመካድ፣ በማኅበራዊ ደግነት እና
በሰንበት ጭብጦች መካከል ያሉትን የሚከተሉትን ሌሎች ትስስሮች
ይመልከቱ፡ የሰንበት ነጻነት ሰዎች ከሣምንታዊው ድካም እረፍት
እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው መልካም ነው (ዘፀ. 23፡12፣ ማር. 2፡
27)፣ በሰንበት ቀን መልካም ማድረግ ተገቢ መሆኑን የሱስ አሳይቷል
(ማር. 3፡1-5፣ ዮሐ. 5፡1-17)፣ ሌሎችን መርዳት የሚያካትተው
(ኢሳ. 58፡10-11) እውነተኛ የሰንበት እረፍት ደስታ ያስገኛል
(ኢሳ. 58፡14)። እነዚህን በረከቶች በግል ለመለማመድ በሕይወትዎ
ሊለውጡት የሚገባ ነገር ምንድን ነው?
“አንድ ሰው ራሱን ካልካደ በቀር እውነተኛ ቸርነትና ፍቅር
ማሳየት አይችልም። ያልተወሳሰበ ህይወት በመምራት፣ ራስን በመካድ እና ራስን
በመቻል--እንደ ክርስቶስ ተወካይነታችን የተሰጠንን ተግር ማከናወን እንችላለን።
ትዕቢት እና ዓለማዊ ምኞት ከልባችን መወገድ አለባቸው። በክርስቶስ ሕይወት
የተገለጠው ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ መርኅ በእኛም ውስጥ ክንውን ሊያገኝ ይገባል።
በቤታችን ግድግዳ፣ በሥዕሎች እና ቁሳቁሶች ላይ ‘ተንከራታቹን ድኻ ወደ ቤትህ
እንድታስገባው’ የሚለው ጥቅስ ሊነበብ ይገባል። የልብስ ማስቀመጫ ቁምሳጥናችን
ላይ ‘የተራቆተውን ስታይ እንድታለብሰው’ የሚሉትን በጌታ ጣቶች የተጻፉ
መልእክቶች እንመልከት። በቂ ምግብ በሚቀርብበት መመገቢያ (ሳሎን) ቤታችን
‘ምግብህን ለተራበ እንድታካፍለው’ የሚለውን ጽሑፍ መፈለግ የለብንምን?’ Isaiah
58:7”—Ellen G. White, The Ministry of Healing, p. 206.
1. ኢሳይያስ ለእርሱ ዘመን ሕዝብ ያቀረበውን ጥያቄ ይመልከቱ፡
“ገንዘባችሁን እንጀራ ባልሆነ ነገር ላይ ለምን ታጠፋላችሁ?
በማያጠግብስ ነገር ላይ ለምን ጉልበታችሁን ታጠፋላችሁ? (ኢሳ.
55፡2)። እኛም በተመሳሳይ በምን መልኩ በማያጠግበን ነገር ላይ
ጉልበታችንን እያጠፋን እንደሆነ ራስዎን ይጠይቁ። በዚያች ወጥመድ
ውስጥ መውደቅ በጣም ቀላል የሆነው ለምንድነው?
2. ራስን መካድ፣ ማሕበራዊ ደግነት እና ሰንበት ለኢሳይያስ ዘመኑ
የሥርየት ቀን አስፈላጊ እንደ ነበሩ ሁሉ፤ የእግዚአብሔር ኢዮቤልዩ
መለከት የክርስቶስን ዳግም ምጽአት (1ቆሮ. 15፡52፣ ዘሌዋ. 25፡
9-10) ነጻነት በሚያውጅበት በመጨረሻው ዘመን የሥርየት ቀንም
እንዲሁ (ዳን. 8፡14) አስፈላጊ ይሆናሉ ወይ? መልስዎን ያብራሩ።
3. በክፍል ውስጥ ስለ ሰንበት አጠባበቅ ተወያዩ። በሰንበት ቀን
ራሳችንን ከሚያስደስተን መታቀብ እንዳለብን የሚናገረው ኢሳይያስ፤
በተመሳሳይ ሰንበትን “ደስታ” (ኢሳ. 58፡13) ብለን እንድንጠራው
ጥሪ ሲያቀርብ ምን ማለቱ ነው ብለው ያስባሉ? ሁለቱንም ማድረግ
የምንችለው እንዴት ነው? አጠቃላዩን የኢሳ. 58 ዐውድ ከግምት
ማስገባት አይዘንጉ።
ማጠቃለያ፡ ሕዝቡ የገዛ ራሱን አስተሳሰብና አካሄድ ትቶ አብልጦ የከበረ የሆነው
ደስታ ባለቤት ወደሚያደርገው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ ነቢዩ በኢሳ.
55 እና 58 ተማጽኖ ያቀርባል። እርሱ ከሥርየት ቀን እና ከሰንበት መንፈስ ጋር
ኅብር በሚፈጥር በሙሉ ምኅረት ይቅር እንዳላቸው ሁሉ፤ እነርሱም ሌሎችን
ይቅር እንዲሉ አጥብቆ ይመክራል። ምክንያቱም የእግዚአብሔርን የይቅርታ
ስጦታ በእውነት መቀበል ልብን ይለውጣል።