የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ኢሳይያስ፡ “ሕዝቤን አጽናኑ”


1ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከየካቲት 20 – 26

10ኛ ትምህርት

Feb 27 - Mar 05




ሊታሰብ የማይችለውን ማድረግ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 50:4– 10፣ ኢሳ. 52:13–53:12፣ ኢሳ. 53:3–9፣ ኢሳ. 53:10–12።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን” (ኢሳ. 53፡5)።

ቻ ይናዊው ሎው ፉክ በአፍሪካ የማዕድን ማውጫ በባርነት ያገለግሉ ለነበሩ የአገሩ ልጆች ልቡ ተነክቷል። የወንጌልን ተስፋ ሊሰጣቸው ቢፈልግም ግን እንዴት እነርሱ ያሉበት ስፍራ መድረስ ይችላል? የመጣለት መፍትሔ ራሱን ለአምስት ዓመት በባርነት መሸጥ ነበር። ከዚያም በማዕድን ቁፋሮ በሚሠራበትና ለሥራ ባልደረቦቹ ስለ የሱስ ወደሚነግርበት ስፍራ ተወሰደ። አንድ ቀን ሎው ፉክ በዚያ ከባድ የማዕድን ማውጫ ስፍራ እንዳለ ሞተ። ሆኖም ይህ የሆነው 200 ሰዎች ከተስፋ መቁረጥ ወጥተው የሱስን የግል አዳኛቸው አድርገው ከተቀበሉ በኋላ ነበር።

ስለ ሌሎች መልካም ሲባል የተከፈለ አስደናቂ መሥዋዕትነት! እንዴት ያለ ታላቅ ምሣሌ ነው! ፈጽሞ የማይታሰበውን በማድረግ፤ “የባሪያን መልክ ይዞ” (ፊልጵ. 2፡7) በትህትና የመጣው የሱስ፤ እርስዎ እና እኔ እንዲሁም መላው ዓለም ሰጥሞ ከጠፋበት የኃጢአት አዘቅት ለማውጣት--እነሆ ሊደረስ ወደማይችለው ደረሰ። ይህ አስደናቂ ክስተት እውን ከመሆኑ መቶ ዓመታት በፊት በትንቢት መነገሩን በዚህ ሣምንት ጥናታችን እንመለከታለን።

የካቲት 21
Feb 28

የኢሳይያስ ፈታኝ እውነት (ኢሳ. 50፡4-10)


የኢሳይያስ እቅድ መረጃ ማስተላለፍ ብቻ ቢሆን ኖሮ፤ መሲሑን የተመለከቱ ዝርዝሮችን በሙሉ አብራርቶ ባለፈ ነበር። ነገር ግን ተደራሲውን ለማስተማር፣ ለማሳመንና ከጌታ ባሪያ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥር ለማድረግ ተምሳሌታዊ አቀራረብ ተጠቅሞ ተደጋጋፊ ጭብጦችን ያዳብራል። እያንዳንዱ ሁናቴ ከተቀረው ምስል ጋር ከሚኖረው ግንኙነት አኳያ መስተዋል ይችል ዘንድ፤ አምላካዊውን መልእክት ደረጃ በደረጃ ይገልጣል። ኢሳይያስ ሠዓሊ--ቡሩሹ የሚያርፍበት ሸራ ደግሞ የአድማጮቹ ነፍስ ነው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 50፡4-10። ጥቅሶቹ የሚሉትን ጠቅለል አድርገው ሲመለከቱ፤ በመልእክቱ ውስጥ የሱስን እንዴት ያዩታል?



የእግዚአብሔር ባሪያ የተናቀ፣ የተጠላ እና “የገዦች አገልጋይ” ሆኖ በኢሳ. 49፡7 የምናገኘው ቢሆንም፤ ነገር ግን “ነገሥታት አይተውህ ይነሣሉ፣ ልዑላንም አይተው ይሰግዳሉ” በማለት ያው ቁጥር ስለ እርሱ ይናገራል። በኢሳ. 50 ደግሞ ቃላቶቹ የደከመውን ደግፈው የሚይዙት ይህ በጣም ገር መምህር የሚያልፍበት ሸለቆ እጅግ ጥልቅ እንደሆነ እንረዳለን (ኢሳ. 50፡4)። የጽድቅ መንገድ በአካላዊ በደል ውስጥ ይመራዋል (ኢሳ. 50፡6)። ይህ በደል በተለይ በዘመናዊው የምዕራብ ዓለም እንደ ጸያፍ ይታያል። በጥንታዊው የቅርብ ምሥራቅ ባህል፤ ክብር ለአንድ ሰው እና ቡድኑ የሞት ሽረት ጉዳይ ነበር። እንዲህ ዓይነቱን ሰው የሚዘልፍና የሚያጎሳቁል የተሻለ ጥበቃና ከለላ ያገኛል። ነገር ግን የጉዳት ሰለባው ወይም ጎሳው ግማሽ ዕድል የሚያገኝ ከሆነ መበቀላቸው አይቀሬ ነው።

የአሞን ንጉሥ የነበረው “ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ፣ የእያንዳንዳቸውን ጢም በከፊል ላጨ፣ ልብሳቸውንም ወገባቸው ድረስ አሳጥሮ በመቁረጥ መልሶ ሰደዳቸው” (2ሳሙ. 10፡4)። በዚህ ምክንያት ንጉሥ ዳዊት የአሞንን ምድር ድል አድርጎ ተቆጣጠረ (2ሳሙ. 10፡ 1-12)። ነገር ግን በኢሳ. 50 ሰዎች ባሪያውን ይመቱታል፣ ጢሙን ይነጩታል፣ ይተፉበታልም። እነዚህን ድርጊቶች ዓለማቀፋዊ የሚያደርጋቸው ብሎም በዩኒቨርስ ደረጃ የሚያገዝፋቸው፤ ተጠቂው የመለኮታዊው የነገሥታት ንጉሥ መልእክተኛ መሆኑ ነው። እርግጥ ነው--ኢሳ. 9፡6-7 እና ኢሳ. 11፡1-16 ከሌላው “ባሪያ” ጥቅሶች ጋር በማነጻጸር፤ ባሪያው ኃያል የሆነው አዳኝ ንጉሥ መሆኑን ተመልክተናል። ነገር ግን ይህ ሁሉ ኃይል እና ክብር እያለው--በአንድ ለማሰብ አዳጋች በሆነ ምክንያት ራሱን አያድንም! ሰዎች ሳያምኑ መቅረታቸው በጣም እንግዳ ነገር ነው። መሪዎች በመስቀል በተቸነከረው የሱስ አፌዙ፡

“ ‘ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፤ እስቲ ራሱን ያድን’ ”(ሉቃ. 23:35)። “ ‘ ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም’ ” (ማቴ. 27:42) ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 50፡4-10። በገዛ ህይወታችን ተግባራዊ ሊሆኑ የሚገቡ እዚህ ላይ የቀረቡ መንፈሳዊ መርኅዎችን ይፃፉ። በጽሑፍ ባቀረቧቸው ነጥቦች ብርሃን ራስዎን ይመልከቱ። በየትኞቹ መስኮች በተሻለ መሥራት ይችላሉ?

የካቲት 22
Mar 01

የባሪያው ሥቃይ ስንኝ (ኢሳ. 52፡13-53፡12)


“የባሪያው ሥቃይ ስንኝ” በሚል የሚታወቀው ኢሳ. 52፡13-53፡12--ኢሳይያስን “የወንጌል ነቢይ” የሚል ዝና አጎናጽፎታል። የስንኞቹ ከወንጌል ልህቀት ጋር ኅብር መፍጠር፤ ከሌሎች ሥነ ጽሑፎች በላይ አድርጓቸዋል። ምንም እንኳ እነዚህ አግራሞት የሚያጭሩ ስንኞች አጭር ቢሆኑም፤ እያንዳንዱ ሀረግ በኃጢአት የጠለቀውንና ጭልጥ ብሎ የጠፋውን ዘር ለማዳን የእግዚአብሔርን ሊታሰብ የማይችል የፍለጋ ተልዕኮ በሚገልጽ ጥልቅ ትርጉም የተሞላ ነው። የኢሳይያስ መጽሐፍ በመጀመሪያው ክፍል መሲህን የተመለከቱ ጭብጦችን በማጎልበት አንባቢዎቹን አዘጋጅቷል።

መሲሁ በዚህ ምድር የሚኖረውን አጠቃላይ ህይወት ጎዳና ተከትሎ፤ ከመጸነሱ እና ከውልደቱ ይጀምርና (ኢሳ. 7፡14) መለኮታዊ ባህሪ ያለውን የዳዊታዊ ስርወ ንግሥና ማንነቱን ያስተዋውቃል (ኢሳ. 9፡6-7)፣ እስራኤልን መልሶ በማቋቋም የሚሠራውን ሥራ (ኢሳ. 11፡1-6)፣ እንዲሁም በኢፍትሐዊነት እና ሥቃይ ዙሪያ የሚሰጠውን ጸጥተኛ አገልግሎት (ኢሳ. 42፡1-7) ያቀርባል። በመሲህ የሚተገበረውን ታላቅ ትርዒት--እርሱ ከመክበሩ አስቀድሞ (ኢሳ. 49:1–12፣ ኢሳ. 50:6–10) ተግባራዊ ከሚሆነው አሳዛኝ ክስተት ጋር በማነጻጸር ኢሳይያስ ገልጦታል። አሁን መከራ የደረሰበት ባሪያ ስንኝ የአሳዛኙን ክስተት ጥልቀት ይመረምራል።

ከላይ በቀረበው አንቀፅ ወደ ተዘረዘሩት ክፍሎች ይመለሱ። ስለ መሲሁ የሱስ የሚነግሩንን ይከልሱ። በኢሳ. 52 እና 53 ለሚመጣው እንድንዘጋጅ እንዴት ይረዱናል? ወይስ በኢሳ. 52 እና 53 ገቢራዊ የሚሆነውን ክስተት ይበልጥ ደማቅ ያደርጉታል?



ኢሳ. 52፡13-53፡1--በመግቢያው አስገራሚ ንጽጽር ከያዘ የስንኝ ቋጠሮ ጋር ያስተዋውቀናል፡ ባሪያው ገናና፤ ብሎም ከፍ ከፍ የሚል ቢሆንም፤ ነገር ግን ገጽታው ማንነቱን ለመለየት እስኪያስቸግር የታወከ ይሆናል። ይህን ማን ያምናል? ኢሳ. 53፡2-3--በህመም የተሞላውን የባሪያውን አመጣጥ እና በሐዘንና ነቀፌታ የታጀበውን ተራ ገጽታውን በመንገር ይጀምራል። የእርሱ ሥቃይ እኛን ለመፈወስ የተሸከመው--በተጨባጭ የእኛ ቅጣት እንደ ነበር ለመግለጽ ኢሳ. 53፡4-6 ቆም ይላል። ኢሳ. 53፡7-9--ይህ ንጹህ፣ ያልበደለ ባሪያ ትውልድ እስከ መቃብር የሚያደርገውን ጉዞ መግለጹን ይቀጥላል።

በኢሳ. 53፡10-12--በስንኙ መግቢያ (ቀደም ሲል ከኢሳ. 52፡13 ጀምሮ) በተተነበየው የከበረ ወሮታ መሰረት ባሪያው ከፍ ከፍ ይላል፤ ይኸውም ሌሎችን የማዳን መሥዋዕትነቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን አክሎ ብርሃን በመፈንጠቅ። የሱስ አምላካዊውን ቅርጽ ይዞ በመጀመር፣ በግዞት ያለውን ሰብዓዊ ገጽታ ለመውሰድ ራሱን ባዶ አድርጎ የወረደበትን እና ከሞት ሁሉ የከፋ የሆነውን የመስቀል ላይ ሞት ለመቀበል ራሱን ዝቅ ያደረገበትን ትዕይንት--በፊልጵ. 2፡5-11 ከቀረበው “ሸለቆ” ቅርጽ ጋር ይህን ስንኝ ያስተያዩ። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው እርሱ በእርግጥ ጌታ መሆኑን ይገነዘብ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አደረገው (ኢሳ. 49፡7)።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 52፡13-53፡12። የሱስ ስላደረገልን ነገር አስመልክቶ በስንኙ የቀረበውን ማንኛውንም ነገር ለመጻፍ ይሞክሩ። እነዚህ የተከፈሉልን ክንውኖች፤ ለእኛ ምን ማለት እንደሆኑ ያሰላስሉ።

የካቲት 23
Mar 02

ማን አመነ? (ኢሳ. 52፡13-53፡12)


በኢሳ. 52፡13--የእግዚአብሔር ባሪያ በከፍተኛ ደረጃ ገናና፣ ከፍ ከፍ ያለና የከበረ ሆኖ ይቀርብና፤ ቀጣዩ ቁጥር “ከሰው ልጆች” በተለየ አብልጦ የተጎሳቆለና እንደ አንዱ ሊታወቅ እንደማይችል ይገልጻል። የሱስ ያለፈበት የማያቋርጥ ህመምና ሥቃይ፣ የእሾህ አክሊል፣ ሥቅላት--ከሁሉም በላይ ግን የሰብዓዊውን ዘር ኃጢአት መሸከሙ-አዲስ ኪዳን ለየሱስ ገጽታ መታወክ መንስዔ ካላቸው ውስጥ ይካተታሉ። ኃጢአት የሰብዓዊው ተፈጥሮ አካል ይሆን ዘንድ ፈጽሞ አልታቀደም። ይህን መሸከሙ “የሰውን ልጅ” ከሰው ተራ የወጣ መልስ አሰጠው።

ይህን ሀሳብ ከከፍተኛ የብልጽግና፣ የክብርና የኃይል ማማ በድንገት ቁልቁል ወርዶ ሲያበቃ፤ ዐመድ ላይ ተቀምጦ ህመም ያለውን ቁስሉን በሸክላ ስባሪ ገል ያክክ ከነበረው ከኢዮብ ታሪክ ጋር ያስተያዩ (ኢዮ. 1-2)። ንጽጽሩ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ ራሳቸው የኢዮብ ወዳጆች ሳይቀሩ በመጀመሪያ አላወቁትም ነበር (ኢዮ. 2፡ 12)። ጥያቄው፡ ኢዮብ ለምን ተሠቃየ? የእግዚአብሔር መሲህ ለምን መሰቃየት አስፈለገው? አንዳቸውም ቢሆኑ ይህ አይገባቸውም ነበር። ሁለቱም ንጹሐን ነበሩ። ታዲያ መከራው ለምን አስፈለገ? የዛሬ ጥናት ጥቅሶችን ካነበቡ በኋላ ስለ በደለኛው የቀረቡ የንጹሐን ሥቃይ ጭብጦችን በጽሑፍ ያስፍሩ። ለእኛ አስፈላጊ የሆነው መልእክት ምንድነው?



በኢሳ. 53፡1 የቀረቡትን ጥያቄዎች ይመልከቱ። እነዚህ ጥያቄዎች ሊታመን የማይችለውን ማመን ተግዳሮት እንዳለው አጥብቀው በመናገር (ያስተያዩ፡ ዮሐ. 12፡37-41) የተቀረውን ታሪክ በትዕግሥት መጠባበቀቅ እንዳለብን ያስጠነቅቃሉ። ደግሞም ራሳቸው ጥያቄዎቹ ተማጽኖ ያቀርባሉ። በዚህ ዐውደ ጽሑፍ--በሁለቱ ጥያቄዎች መካከል ያለው መመሳሰል የጌታ ማዳን ክንድ (ኢሳ. 52፡10) ዘገባውን ለሚያምኑ መገለጡን ያመለክታል። የእግዚአብሔርን የማዳን ኃይል መለማመድ ይፈልጋሉ? እንግዲያውስ ዘገባውን አምነው ይቀበሉ።

ጥቅሱን በጥንቃቄ ይመልከቱ፡ ኢሳ. 53፡6፣ በዚህ ቦታ የቀረበው መልእክት ምንድን ነው? ቀደም ሲል ኃጢአትና ውድቀት ቢጎበኞትም፤ ጥቅሱ ምን ዓይነት ተስፋ ሊሰጦት ይገባል? ለእርስዎ በግል ምን የሚል መልእክት አለው?

የካቲት 24
Mar 03

የማይደረስበት እኛ ነን! (ኢሳ. 53:3–9)


እየተሰቃየ ስላው ባሪያ በዚህ ስፍራ የተሰጠን መግለጫ--በቀላሉ ሊጎዳ እንደሚችልና ምንም የተለየ ዋጋ እንደሌለው የተናቀ ቡቃያ (ኢሳ. 53፡2-3) ሆኖ ቀርቧል። ኢሳይያስ ንጹህ በሆነ ወጣት አማካይነት አጣድፎ ወደ አንድ ጥልቅ ጉድጓድ አፋፍ ያመጣናል። ቀደም ሲል የኋላ ታሪኩ ቢቀርብልንም፤ በዚህ መልኩ ባሪያው ላይ የሚደርስበትን ለመቀበል ግን አልተዘጋጀንም። በተቃራኒው--ታላቁ የሰላም ልዑል ለሆነው፣ ለተወለደልን ህፃን የከበረ ዋጋ እንድንሰጥ ኢሳይያስ አስተምሮናል። ሌሎች ቢንቁትም፤ እኛ ግን እርሱ በእርግጥ ማን እንደሆነ እናውቃለን።

“ጠላታችንን አግኝተነዋል፤ እርሱም እኛው ነን” ሲል አንድ ሰው ተናግሯል። የንቀት፣ የጥላቻ፣ የነቀፌታ ወይም የሥቃይ ሰው ለመሆን ባሪያው የመጀመሪያ አልነበረም። ንጉሥ ዳዊት ከልጁ አቤሴሎም በሸሸ ጊዜ ይህ ሁሉ ደርሶበታል (2ሳሙ. 15፡30)። ነገር ግን ይህ ባሪያ የተሸከመው ሥቃይ በራሱ ኃጢአት ምክንያት የደረሰበት አልነበረም። ወይም ለሌላ ግለሰብ ሲል አልተሸከመውም፡ “እግዚአብሔርም የሁላችንንም በደል በእርሱ ላይ ጫነው” (ኢሳ. 53፡6)። “ለምን?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ የኢሳይያስ ፈታኝ እውነት ነው፡ በእግዚአብሔር ፍቅር ምክንያት መሲሕ ሥቃይ ይቀበል ዘንድ ይመርጣል። ግን ለምን? ኢሳይያስ በሰው አእምሮ ሊታሰብ የማይችለውን እውነት ማስረዳቱን ይቀጥላል፡ ወደ ማይደረሱበት ለመድረስ መከራን ይመርጣል፣ የማይደረስበት ደግሞ እኛ ነን! ነገሩን ያልተረዱ “በእግዚአብሔር እንደ ተመታ” (ኢሳ. 53፡4) አድርገው ቆጠሩ። የኢዮብ ጓደኞች--ኃጢአቱ ለደረሰበት ሥቃይ መንስዔ ሳይሆን አይቀርም ብለው እንዳሰቡ፤ ወይም የየሱስ ደቀ መዛሙርት “ ‘ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ራሱ ወይስ ወላጆቹ?’ ” (ዮሐ. 9:2) ብለው እንደጠየቁ፤

የሱስን በመስቀል ላይ የተመለከቱ፣ ስለ እርሱ የነበራቸው ግምት የከፋ ነበር። ደግሞስ “በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነው” በማለት ሙሴ ተናግሮ የለ? (ዘዳ. 21፡23፣ ዘኁ. 25፡4) ሆኖም፣ ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር (ኢሳ. 53፡10)። እንዴት? ምክንያቱም “ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል” (ገላ. 3፡13)። ምክንያቱም “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኃጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው” (2ቆሮ. 5፡21)።

“እንዴት ያለ ዋጋ ተከፍሎልናል! እነሆ ወደ መስቀሉና በላዩ ከፍ ወዳለው ተሰዊ ተመልከቱ። በጨካኝ ምስማሮች የተበሱ እጆቹን ተመልከቱ። ከግንዱ ጋር ተጠፍረው በምስማር የተጣበቁትን እግሮቹን ተመልከቱ። ክርስቶስ ኃጢአታችንን በገዛ ራሱ ሥጋ ተሸከመ። የደረሰበት ሥቃይ፣ ህማም፣ እርስዎን ለመዋጀት የከፈለው ዋጋ ነው።”—Ellen G. White, God’s Amazing Grace, p. 172. እርሱ የመላውን ዓለም ኃጢአት ተሸከመ፣ እንደ ጥፋተኛ ተቆጥሮም ቅጣት ተቀበለ። በእያንዳንዱ ኃጢአተኛ የተፈጸመ እያንዳንዱ ኃጢአት እኛን ለማዳን ብቸኛ መፍትሔ በሆነውና በመስቀል ላይ በዋለው ክርስቶስ ላይ በአንዴ ወደቀ! እኛን መዋጀት እንዲህ ያለ ታላቅ ዋጋ ማስከፈሉ--ኃጢአት ምን ያህል የከፋ ነገር እንደሆነ ከዚህ ምን እንረዳለን? እርሱ እንዲህ ያለውን ታላቅ ዋጋ ከፍሎ ይህን ለእኛ ማድረጉ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ምን ይነግረናል?

የካቲት 25
Mar 04

የሚለውጠው የበደል መሥዋዕት (ኢሳ. 53:10–12)


የባሪያው ህይወት “የኃጢአት መሥዋዕት” ነው ሲል ምን ማለቱ ነው? (ኢሳ. 53፡10)



“የበደል መሥዋዕት” (ዘሌዋ. 5:14–6:7፣ ዘሌዋ. 7:1–7) በሚል የቀረበው የዕብራስጡ ቃል፤ ሆነ ተብሎ በሌላ ሰው ላይ የሚፈጸምን በደል ማስተሰረይ የሚችል ነው (ዘሌዋ. 6፡2-3)። እንደዚህ ያሉ ኃጢአቶች በኢሳይያስ ተመርጠው ወጥተዋል (ኢሳ. 1–3፣ ኢሳ. 10:1-2፣ ኢሳ. 58)። ደግሞም ኃጢአተኛው ከእግዚአብሔር ይቅርታ ለመቀበል የሚያስችለውን መሥዋዕት ከማቅረቡ በፊት፤ ከበደለው ሰው የወሰደውን ነገር ከነመቀጮው መመለስ አለበት (ዘሌዋ. 6፡4-7፣ ማቴ. 5፡23-24)። የእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ሳያውቁ በተሳሳተ መንገድ ጥቅም ላይ ሲያውሉ ካሳው ወደ እርሱ ይሄዳል (ዘሌዋ. 5፡16)።

እግዚአብሔር ለኃጢአታቸው በቂ ዋጋ እንደ ከፈሉ በመንገር በግዞት ያሉ ሕዝቦቹን የሚያጽናናበትን ኢሳ. 40፡2 አሁን ማስተዋል እንችላለን። ነገር ግን የሚከፈለውን ካሳ ተከትሎ የሚቀርብ መሥዋዕት አለ። በዚህ በኢሳ. 53--ተቅበዝብዘው ስለ ጠፉ ሕዝቦች (ኢሳ. 53፡6) መሥዋዕት ሆኖ በሚቀርበው የበግ ጠቦት ምትክ ወደ እርድ የሚነዳው (ኢሳ. 53፡7) የእግዚአብሔር ባሪያ ነው። ምንም እንኳን ሙሉ ለሙሉ ከሕያዋን ምድር ተወግዶ (ኢሳ. 53፡8፣ ዳን. 9፡26) እና መሥዋዕት ሆኖ ለእኛ የተስፋ ነበልባል ቢለኩስልንም--እርሱ ከፍ ከፍ ማለቱን ይቀበል፣ “ዘሩን” ያይና ዕድሜው መርዘሙን ይመለከት ዘንድ እነሆ ባሪያው መመለሻ ወደ ሌለው ወደዚህ ምድር ሊሞት መጣ።

የሚከተሉትን ጥቅሶች ይመልከቱ። እነዚህ እያንዳንዳቸው ከኢሳ. 53 ጋር ተመሳሳይ መሰረታዊ መልእክት የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው? መዝ. 32:1-2



ሮሜ 5:8



ገላ. 2:16



ፊልጵ. 3:9



ዕብ. 2:9



1ጴጥ. 2:24



አንድ ሰው በኢሳ. 52፡13-53፡12 የቀረበውን መልካም የምሥራች በአንድ አንቀጽ አሳጥረው እንዲጽፉ ቢጠይቆት እንዴት ያቀርቡታል?

የካቲት 26
Mar 05


ተጨማሪ ጥናት


“ክርስቶስ ኃጢአታችንን በመስቀል፣ በገዛ አካሉ ተሸከመ… ዘላለማዊው ማንነት ሥርየት ማምጣት ባይችል ኖሮ ኃጢአት ምን መሆን ይችል ነበር? የኃጢአት ቅጣት ሞት መሆኑን የክርስቶስ መስቀል ለሁሉም ይመሰክራል… ሰዎችን ከእግዚአብሔር መንፈስ ዱካ እየሰረቀ ሥነ ምግባራዊ ስሜቶችን ጠፍንጎ የሚይዝ ጠንካራ አፍዝ አደንግዝ ኃይል መኖሩ እርግጥ አይደል?”—Ellen G. White, Our High Calling, p. 44.

“የአምላካዊው መንግሥት ሕግ በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ሞት ጎልቶ መታየት ነበረበት። ክርስቶስ የዓለምን በደል ተሸከመ። ብቃታችን የተገኘው በእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ መልበስና ሞት ብቻ ነው። የአለመታመን ወይም የኃጢአት እርክስና የማያውቀው እርሱ በሥቃይ ውስጥ አለፈ። የቅጣትን ፍርድ የተሸከመው ክርስቶስ ስለ ሰው ዘር ድል አደረገ። ሕጉን ከፍ በማድረግና ክብር በመስጠት ለሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት አስገኘ።”—Ellen G. White, Selected Messages, book 1, p. 302.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ኢሳ. 53፡7-9 የአዳኙን ሞት እና ቀብር ወደሚያመለክተው ጥልቁ ይወርዳል። ከእነዚህ ጥቅሶች ስንቶቹ በየሱስ ምድራዊ ህይወት መጨረሻ ፍጻሜ አግኝተዋል? ማቴ. 26:57–27:60፣ ማር. 14:53–15:46፣ ሉቃ. 22:54–23:53፣ ዮሐ. 18:12–19:42።

2.ኤለን ኋይት በክርስቶስ ሞት ስለ ጎላው ሕግ አስመልክታ የጻፈችውን (ከላይ) ይመልከቱ። ምን ማለቷ ነው? የእርሱን ሞት የሕጉ ዘላለማዊነት ማረጋገጫ አድርገን የምናስተውለው እንዴት ነው? ማጠቃለያ፡

ስለ እግዚአብሔር አዳኝ--መወለድ፣ ማንነት እና ሥራ የሚነግረን ኢሳይያስ፤ በመጨረሻ፣ ተስፋ የሚሰጠንንና ከሁሉ የላቀውን አሳዛኝ ክስተት ይገልጥልናል፡ ሊያስተምር፣ ሊያድን፣ የጠፋውን ሕዝብ ሊፈውስ የመጣው የእግዚአብሔር ባሪያ የእኛን ሥቃይና ቅጣት በፈቃደኝነት ወሰደ።