የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከጥቅምት 7 - 13

4ኛ ትምህርት

Oct 17 - Oct 23




የጌታ ዐይኖች፡ መጽሐፍ ቅዱስ ዓለምን የሚቃኝበት መነጽር



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ምሳ. 15:3፣ ኢዮ. 12:7–10፣ ኤፌ. 6:12፣ ራእ. 20:5፣ 6፣ ዮሐ. 1:1–14፣ ማር. 12:29–31።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡“የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉም ስፍራ ናቸው፤ ክፉዎችንም ደጎችንም ነቅተው ይመለከታሉ” (ምሳ. 15፡3)።

ፖ ላንዳዊው ገጣሚና ባለ ቅኔ ዜስላው ሚሎዝ ምናባዊውን እይታ ተጠቅሞ እንስሳትን የተመለከተ አንድ ግጥም ጽፎ ነበር። የሚናገሩ ጥንቸሎች፣ ሽኮኮዎች ወዘተ የምናባዊ ግጥም ሥራው አካል ሆነው ቀርበዋል። “እኛ ስለ ገሀዱ ዓለም የራሳችን ጽንሰ ሀሳብም ሆነ እምነት እንዳለን ሁሉ፤ እንስሳቱም በተመሳሳይ የሚጋሩት አላቸው” ይላል ባለ ቅኔው ዜስላው። በመጨረሻ “ስለዚህ ነገር እያሰላሰላችሁ በፍርሃት ራዱ” በሚል ስንኝ ግጥሙን ይቋጫል።

በእርግጥ “በፍርሃት ራዱ” የተሰኙት ቃላት ጥብቅ ሊሆኑ ቢችሉም ነገር ግን ሰዎች ስለዚህች ዓለም ካላቸው አስተሳሰብ በአመዛኙ ሙሉ ለሙሉ የተሳሳተ መሆኑ እውነት ነው። ለአብነት ያህል የዓለማችን ብልህ እና በዘመናቸው ብዙ ምርምር አድርገዋል የተባሉ ሊቃውንት ላለፉት 2,000 ዓመታት ምድርን የሳሏት--በዩኒቨርስ መሃል ያለ እንቅስቃሴ ደርቃ እንደተቀመጠች አካል ነበር። ዛሬ በዚህ ዘመን ደግሞ ጊዜው የደረሰበትን ምርጥ ትምህርት ቀስመዋል የሚባሉ የሳይንስ ጠበብት--ሰው የመጣው ከአንዲት ቅንጣት ዘረ መል ነው ብለው ያስባሉ።

እንደ ሰብዓዊ ፍጡርነታችን ይህን ዓለም በገለልተኛ አቋም የምንመለከትበት ሁናቴ ፈጽሞ አይስተዋልም። እኛ ሁሌም ቢሆን የምናየው በዙሪያችን ያለውን ዓለም እንዴት መተርጎምና ማስተዋል እንዳለብን ተጽእኖ በሚያደርጉብን ማጣሪያዎች አማካይነት ብቻ ነው። ይህ ማጣሪያ ዓለምን የምንመለከትበት መነጽር ወይም የምንቃኝበት መንገድ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ መጽሐፍ ቅዱስ ዓለምን የሚቃኝበትን መንገድ ለታዳጊ ወጣቶቻችንም ሆነ ለጎልማሶች የቤተ ክርስቲያን አባላት ማስተማራችን አጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ነው።

ጥቅምት 8
Oct 18

የጌታ ዐይኖች


እኛ፣ ይህ ዓለም እንዲሁም በዙሪያችን ያለው ማንኛውም ነገር እውነተኛና ተጨባጭ አይደለም። ይልቁንም እጅግ ግዙፍና የመጠቁ ኮምፒውተሮች ባለቤት የሆኑ ኤልየንስ ዝርያዎች ዲጂታል ፍጡሮች ነን--የሚል ንድፈ ሀሳብ በአንድ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ቀርቦ ነበር።

ምንም እንኳ እንደ ጽንሰ ሀሳብ መሳጭ ይዘት ቢኖረውም--የእውነት ተፈጥሮው ምንድን ነው? ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ ግን አንዳች የሚለው ነገር የለም። ምናልባት ሁለት መልስ መሆን የሚችሉ በጣም ሰፊ ይዘት ያላቸው አስተሳሰቦች አሉ-አንዱ ብቻ ምክንያታዊ ሊሆን ቢችልም። የመጀመሪያው--ዩኒቨርስ እና እኛን ጨምሮ በውስጡ ያሉት ነገሮች ሁሉ እንዳሉ አሉ እንጂ አንዳች የፈጠራቸው ነገር የለም፤ የአሁኑን ቅርጽና ይዘት እንዲይዝ ያደረገውም ምንም አካል የለም። በቃ አሁን እንዳለ አለ። ፈጣሪ የሚባል የለም፣ አማልክት የሉም፣ መለኮትም እንዲሁ የለም። እውነት ፍጹም ቁስ አካላዊና ፍጹም ተፈጥሮአዊ ባህሪ የተላበሰ ነው። አንድ ሰው ከ2,500 ዓመታት በፊት እንደ ተናገረው (ይህ አዲስ ጽንሰ ሀሳብ አይደለም) “አቶሞች እና ባዶነት” ብቻ አሉ። ሌላው እይታ ዩኒቨርስ በአንድ የሆነ መለኮታዊ ኃይል (ወይም ኃይላት) ተፈጠረ የሚል ነው። በእርግጥ ይህኛው ጽንሰ ሀሳብ በቂ ትንታኔ ሊቀርብበት ካልቻለው ቀደም ሲል ከቀረበው የላቀ ምክንያታዊና አሳማኝ ነው። ምንም እንኳ ይሄኛው አቋም “አተሞችን እና ባዶ” የሆነውን ተፈጥሮአዊ ዓለም ቢያካትትም፤ በዚያ ብቻ የተወሰነ ግን አይደለም። ይልቁንም ዛሬ ከምንሰማው የዝግመተ ለውጥ ቁሳ አካላዊ ንድፈ ሀሳብ እጅግ የሰፋ፣ ጥልቅ እና ዘርፈ ብዙ እውነት ይጠቁማል።

የሚከተሉት ጥቅሶች በዛሬው ትምህርት ስለ ተነሱት ጽንሰ ሀሳቦች ምን ይነግሩናል? መዝ. 53:1፣ መዝ. 15:3፣ ዮሐ. 3:16፣ ኢሳ. 45:21፣ ሉቃ. 1:26–35።



የማንኛውም ክርስቲያናዊ ሥርዓተ ትምህርት ማዕከላዊ ክፍል የእግዚአብሔር ህልዎት ብቻ ሳይሆን--እርሱ እያንዳንዳችንን የሚወድ እና በግል ከእያንዳንዳችን ጋር ግንኙነት የሚፈጥር አምላክ ስለ መሆኑም አጽንኦት ሊሰጥ ይገባል። እግዚአብሔር የታምራት አምላክ ነው። ምንም እንኳ እርሱ በተፈጥሮ ሕግጋት የተገደበ አምላክ ባይሆንም ነገር ግን በፈቀደ ጊዜ ከተፈጥሮ ሕጎች ባሻገር ይሠራል (ለምሳሌ የየሱስ በድንግል ማህጸን መጸነስ)። የዚህ ዓይነቱ አመለካከት አስተምህሮ በተለይ ለዘመናችን እጅግ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም አብዛኛው በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ አልፌአለሁ የሚለው አካል የሣይንስ (የተሳሳተው) ድጋፍ አለው የሚለውን የዝግመተ ለውጥ እና ቁስ አካላዊ ዓለማቀፋዊ አመለካከት ዐይኑን በጨው አጥቦ እያስተማረ በመሆኑ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ዓለምን የሚመለከትበት መነጽር (ከላይ እንደ ተጠቀሰው) ቁስ አካላዊውን ዓለም የሚያካትት--ነገር ግን በዚያ ብቻ ያልተገደበ ከመሆኑ አኳያ፤ ሰው ከጦጣ መሰል እንስሳ መጣ የሚለው የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሀሳብ ምን ያህል ጠባብ እና ውሱን ስለ መሆኑ አሰብ ያድርጉ። በስተመጨረሻ--መጽሐፍ ቅዱሳዊው እና ሥነ መለኮታዊው የዓለም አተያይ ከዝግመታዊው ይልቅ እጅግ ምክንያታዊና አሳማኝ የሆነው ለምንድን ነው?

ጥቅምት 9
Oct 19

የ--ሌብኒዝ ጥያቄ


ጎትፍራይድ ዊልኸልም ሌብኒዝ በመባል የሚታወቀውና ከበርካታ ዓመታት በፊት የኖረው የጀርመን ተመራማሪና ፈላስፋ ምናልባትም በጣም መሰረታዊ እና ዋና የሚባለውን ጥያቄ ጠይቆአል፡ “በባዶ ፋንታ--አንዳች ነገር ለምን ኖረ?”--የሚል። የሚከተሉት ጥቅሶች የ--ሌብኒዝን ጥያቄ እንዴት ይመልሱልናል? ዘፍ. 1:1፣ ዮሐ. 1:1–4፣ ዘፀ. 20:8–11፣ ራእ. 14:6-7፣ ኢዮ. 12:7– 10።



የእግዚአብሔር ሕልዎት በመጽሐፍ ቅዱስ በውስጠ ታዋቂነት የቀረበበት መንገድ እጅግ አስገራሚ ነው። ዘፍ. 1፡1 የእግዚአብሔርን ሕልዎት አስመልክቶ አመክንዮአዊ አተካሮ ውስጥ አይገባም። ይልቁንም አምላካዊውን ሕልዎት ብቻ በውስጠ ታዋቂነት የሚያስቀምጥ ሲሆን (ዘፀ. 3፡13-14) በዚያ መነሾ--እግዚአብሔር በፈጣሪነቱ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እና ሁሉም እውነት ባልተከደኑ ገጾች ወለል ብሎ ቀርቦአል። የፍጥረት ኃይማኖታዊ አስተምህሮ የማንኛውም ክርስቲያናዊ ሥርዓተ ትምህርት መሰረት ጭምር ነው። እንደ ክርስቲያን ማንኛውም የምናምነው ነገር ስድስት ቀናት በፈጀው የፍጥረት ሥራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ላይ የተመሰረተ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥርየት፣ ስለ ሕግ፣ ስለ መስቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው ወይም ስለ ዳግም ምጽአቱ በመናገር አልጀመረም።

ይልቁንም ስለ እግዚአብሔር ፈጣሪነት በመናገር ይጀምራል። ምክንያቱም ከላይ ከቀረቡት አስተምህሮዎች አንዱ እንኳ እግዚአብሔር ፈጣሪያችን ከመሆኑ እውነታ ውጪ ትርጉም አይሰጥም።

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊው የዓለም ዕይታ--ስለ ፍጥረት ኃይማኖታዊ አስተምህሮ አስፈላጊነት ብርቱ አጽንኦት መስጠቱ የግድ ይሆናል። ይህ አጽንኦት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም በስመ ሳይንሳዊ አስተምህሮ ፊት ለፊት እየተሰነዘረ ያለው ጥቃት መጠነ ሰፊ ነው። ህይወት በቢሊዮን በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ በዝግታ፣ እንደ አጋጣሚ በራሱ መጀመር ቻለ የሚለው የዝግመተ ለውጥ አስተምህሮ፤ ይህን ያህል ብሎ ለመግለጽ አዳጋች የሆኑ ሚሊዮኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው አድርጎአል። ከዝግመተ ለውጥ አስተምህሮ ይልቅ ለመጽሐፍ ቅዱስ እና ለክርስትና እምነት አብልጦ ጠላት የሆነ ትምህርት አለ ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው። የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሀሳብ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው የፍጥረት አስተምህሮ ጋር ስምምነት እንዲፈጥር መሞከር--እግዚአብሔር የለም ብሎ ከሚያምነውም የባሰ የከፋ ነው የሚባለው ለዚህ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ እና በአጠቃላይ በክርስትና እምነት ላይ መሳለቅ ካልሆነ በቀር ይህ ፍጹም ሊሆን አይችልም።

እግዚአብሔር በየሣምንቱ፣ ከህይወታችን አንድ ሰባተኛውን--ስድስቱን የፍጥረት ቀናት እንድናስታውስበት ይጠይቀናል። ይህ ጥያቄ በየትኞቹም ሌሎች አስተምህሮዎች የለም። ለክርስቲያናዊው የዓለም ዕይታ--ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ምን ያህል መሠረታዊና አስፈላጊ ስለመሆኑ ከዚህ ምን እንረዳለን?

ጥቅምት 10
Oct 20

መጽሐፍ ቅዱስ ዓለምን የሚያይበት መንገድ


በመግቢያው ላይ እንደ ተጠቀሰው አንዳችንም ብንሆን ዓለምን ገለልተኛ አቋም ይዘን አንመለከታትም። ለምሳሌ በዝግመተ ለውጥ የሚያምን ሰው በሰማዩ ላይ ቀስተ ደመና ወጥቶ ቢመለከት በቀጥታ የሚያያይዘው ከተፈጥሮአዊ ክስተት አኳያ ብቻ ነው። ሰው ሊሰጠው ከወሰነው ትርጉም ውጪ ሌላ ፍቺ የለውም። በተቃራኒው ጉዳዩን መጽሐፍ ቅዱስ ዓለምን ከሚያይበት መንገድ አኳያ የሚመለከት ሰው--የሚያየው በውሃ እና ብርሃን መካከል የተፈጠረውን መስተጋብር ማለትም ተፈጥሮአዊውን ክስተት ብቻ ሳይሆን፤ እግዚአብሔር ምድርን ዳግመኛ በውሃ እንደማያጠፋት የገባውን ኪዳን ጭምር ነው (ዘፍ. 9፡13-16)። “ርኅሩኁ አምላክ በኃጢአት ለወደቀው ሰብዓዊ ፍጡር ካለው አዘኔታና ፍቅር የተነሳ ክብሩን ወደጎን ትቶ ከሰው ጋር ቃል ኪዳን ገባ። ለቃል ኪዳኑ ማሰሪያ እንደ ምልክት አድርጎ ውብ የሆነውን ቀስተ ደመና አቆመ! ጌታ እንደተናገረው-ቀስተ ደመናውን በተመለከተ ጊዜ፤ ቃል ኪዳኑን ያስታውሳል። … አንዱ ትውልድ አልፎ ሌላው በተተካ ቁጥር ልጆች ሰማይን ያሰመረውን የውቡን ቀስተ ደመና ምንነት ወላጆቻቸውን ሲጠይቁ፤ ያን የቀደመ የጥፋት ውሃ ታሪክና የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ይተርኩላቸዋል። ይህም መለኮታዊውን ፍቅር ከአንዱ ትውልድ ወደ ሌላው የሚመሰክርና ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት የሚያጠነክር ይሆናል።” (የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት ገጸ፡ 111)

መጽሐፍ ቅዱስ ለሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ጽኑ የእምነታቸው መሰረታዊ መልእክት ነው። እጅግ ተስፋ አስቆራጭና ውስብስብ ሊሆን የሚችለውን ዓለም እንዴት ባለ ማጣሪያ መመልከትና መረዳት እንዳለብን ያስተምረናል። መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ ግራ ስለሚያጋባን ራሳችን የምንገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ በተሻለ እንድናስተውል የሚረዳንን ንድፍ ይሰጠናል::

የምንገኝበትን ተጨባጭ ሁናቴ በተሻለ ማስተዋል እንድንችል የሚረዱን ምን ዓይነት እውነቶች በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ ይገኛሉ? ኤፌ. 6:12፣ ማር. 13:7፣ ሮሜ 5:8፣ ሮሜ 8:28፣ መክ. 9:5፣ ራእ. 20:5-6።



እንደ ሰባተኛው ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነታችን--እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የገለጠውን እውነት ይኸውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን አጥብቀን መያዝ አለብን። ምክንያቱም እርሱ ስለ ዓለም የቀረቡትን እነዚህን እጅግ ብዙ ነገሮች ባይገልጥልን ኖሮ በራሳችን ልናውቃቸው ወይም ልንረዳቸው ባልቻልን ነበር። ስለዚህ ሁሉም ክርስቲያናዊ ሥርዓተ ትምህርቶች በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረቱ ሊሆን ይገባል። ይህን የሚቃረን ማንኛውም አስተምህሮ ውድቅ መሆን አለበት።

ሰዎች ከሚያምኑባቸው ሌሎች እምነቶች ጋር የሚቃረኑ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? የእግዚአብሔርን ቃል በታማኝነት አጥብቆ መያዝ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስመልክቶ ይህ ልዩነት ምን ሊያስተምረን ይገባል?

ጥቅምት 11
Oct 21

ቤዛ የሆነውን ማምለክ


የሥነ ፍጥረት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ለእምነታችን አስፈላጊ የሆነውን ያህል ብቻውን ግን አናገኘውም--በተለይ በአዲስ ኪዳን። ሥነ ፍጥረት ከመዋጀት አስተምህሮ ጋር ጥንድ ሆኖ፤ እንደውም ጥምረት ፈጥሮ በተደጋጋሚ እንመለከታለን። ይህ የሆነበት ምክንያት፤ እንደ እውነቱ ከሆነ፤ በኃጢአት ለወደቀውና የሞት ሰለባ ለሆነው ዓለም የሥነ ፍጥረት አስተምህሮ ብቻውን በቂ አይደለም። እንኖራለን፣ እንታገላለን፣ በአስቸጋሪ ሁናቴዎች ውስጥ እናልፋለን--ከዚያስ? አይቀሬው ሞት ሲመጣ በጎዳና ዳር ወድቀው ከምንመለከታቸው የሞቱ እንስሳት ቅሪቶች የተለየን አንሆንም። ለመሆኑ ያ ምን ያህል ታላቅ ነው?

ዓለምን የምናይበት መነጽር በጣም ወሳኝ እንደመሆኑ ሁሉ የመቤዠት አስተምህሮም በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት የተሰቀለልን እና ከሞት የተነሳው--የእምነታችን ሁሉ አስኳል የሆነው የሱስ ክርስቶስ አለን!

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 1፡1-14። ስለ የሱስ ማንነትና እርሱ ስላደረገልን ነገር ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?



በተጨማሪ የሦስቱን መላእክት መልእክት ይመልከቱ፡ “ከዚያም ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰበከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር፤ በታላቅ ድምፅም ‘እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል፤ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ’ አለ” (ራእ. 14፡6-7)። እዚህ ላይ--“የዘላለም ወንጌል” እንደ ፈጣሪነቱ ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳለው ልብ ይሏል። የፈጠረን አምላክ ሰብዓዊውን ሥጋ ለብሶ የእኛን የኃጢአት መቀጮ ለራሱ የወሰደ መሆኑን ስንገነዘብ--እናመልከው ዘንድ መጠራታችን ብዙም አስገራሚ አይሆንም። አምላካችን በእርግጥ እንዴት ያለ አምላክ መሆኑን መገንዘብ ስንችል ምን ዓይነት ተጨማሪ ምላሽ ይኖረናል?

በዚህ ምክንያት ክርስቶስ እና የተሰቀለው እርሱ--የትምህርቶቻችን ሁሉ ተቀዳሚ እና ማዕከል ሆኖ መጽናት ይኖርበታል። የክርስቶስ የመጀመሪያ ምጽአት ከዳግም ምጽአቱ ከተነጠለ መልካም የሆነውን ሁሉ የተሟላ ስለማያደርግልን አስተምህሮው በእርግጠኝነት ዳግም ምጽአቱንም ማካተቱ የግድ ይሆናል። ምናልባት አንድ ሰው--የክርስቶስ የመጀመሪያውና ሁለተኛው ምጽአት የአንድ ክስተት ሁለት ክፍሎች (የደኅንነት እቅድ አካል) ናቸው ብሎ መጽሐፍ ቅዱስን ተንተርሶ ሊሞግት ይችላል።

በመስቀል ላይ በሞተልን “ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል” (ዮሐ. 1፡ 3) በሚል ከቀረበው መልእክት በቂ ሃሳብ ለመጨበጥ ይሞክሩ። አምልኮ ከሁሉ የላቀ ተፈጥሮአዊ ምላሽ የሆነው ለምንድን ነው?

ጥቅምት 12
Oct 22

የእግዚአብሔር ሕግ


ከዓመታት በፊት በፈረንሳይ አገር የሞት ቅጣት ውሳኔ ይሻር የሚሉ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች ያነሱትን ሙግት ተከትሎ ሰፊ ክርክር ተካሂዶ ነበር። ሕጉ እንዲሻር የሚሞግቱ ወገኖች ሚሸል ፎካልት ከሚባሉ ዝነኛ ደራሲና ፈላስፋ ጋር ግንኙነት በመፍጠር አቋማቸውን የሚያራምድ ጽሑፍ በስማቸው እያዘጋጁ እንዲያወጡ ጠየቋቸው። ከስምምነታቸው ብዙ አልፈው የተጓዙት ሚሸል ፎካልት ግን፤ የሞት ቅጣት ይሻር ብቻ ሳይሆን አጠቃላዩ የወህኒ ቤት መዋቅር ፈራርሶ አንድም ታራሚ ሳይቀር በሙሉ ነፃ ይውጡ የሚል ሙግት ይዘው ቀረቡ።

ለምን? ምክንያቱም ለ--ሚሸል ፎካልት ግብረገባዊ ደንብና ሥርዓቶች ሁሉ የተዋቀሩትና የተደራጁት በሰው ነው፤ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች ሰፊውን ሕዝብ ለመቆጣጠር የቀየሷቸው ሰብዓዊ ጽንሰ ሀሳቦች ናቸው። ስለዚህ እነዚህ የሥነ ምግባር መተዳደሪያዎች እውነተኛ ሕጋዊነት የላቸውም።

ምንም እንኳ የሚሸል ፎካልት አቋም ጽንፍ የያዘ ቢመስልም፤ ሆኖም በዓይነቱ አዲስ ያልሆነው ይህ ችግር ያስከተለውን አመክንዮአዊ መዘዝ ግን እንመለከታለን። ሙሴ በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት አስቀድሞ ለዚህ ጉዳይ ይበጃል ያለውን የመፍትሔ ሀሳብ ለጥንት እስራኤላውያን አቅርቦ ነበር፡ “ዛሬ እንደምናደርገው ሁሉ፣ እያንዳንዱ የሚመስለውን እንዳደረገ አታድርጉ” (ዘዳ. 12፡8። [በተጨማሪ፡ መሳ. 17፡6፣ ምሳ. 12፡ 15])።

ሆኖም በገዛ ዓይኖቻችን ቀና መስለው የታዩንን ካላደረግን--ከሥነ ምግባር አኳያ ትክክል የሆነውን ለማወቅ እኛ ራሳችን ጽድቅ፣ ቅድስና እና ዓላማ መር ማንነት የለንም ማለት ነው--ታዲያ ምን ማድረግ እንዳለብን እንዴት እናውቃለን? መልሱ ወይም አካሄዱ-እኛን የፈጠረው ጌታ የምንኖርበትንም የግብረገብ ሕግ ሰጥቶናል--የሚል ይሆናል። ምናልባት ለዐይኖቻችን ሙሉ ሆነው ባይታዩን እንኳ ጌታ ግን ሁሌም ትክክል ነው። የሚከተሉት ጥቅሶች ስለ ግብረገባዊው ሕግ ምን ይነግሩናል? ዘዳ. 6:5፣ ማር. 12:29–31፣ ራእ. 14:12።



ባለፈው ሣምንት ጥናታችን እንደ ተመለከትነው መቤዠታችንን ዓለምን የምናይበት የክርስትና መነጽር አስኳል የምናደርግ ከሆነ--የእግዚአብሔር ሕግ የሆነው አሥርቱ ትእዛዛትም ተመሳሳይ ማዕከላዊነትን ይወስዳል ማለት ነው። ለነገሩ አምላካዊውን ሕግ መጣስ (ሮሜ 3፡20) ከሆነው ከኃጢአት ሌላ ከምን ተዋጀን? ሕጉ የማያድነን ሆኖም እንኳ ወንጌል ከእግዚአብሔር ሕግ ከተነጠለ ምንም ትርጉም አይሰጥም።

ስለዚህ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ሥርዓተ ትምህርት ሁሉ ኤለን ኋይት “ዘላለማዊነት የተላበሰው ሕግ” (The Great Controversy, p. 63) ብላ ለጠራችውና ሰንበትን ጭምር ለሚያካትተው ለዚህ ሕግ አጽንኦት ሊሰጥ ይገባል። በዚህ ምድራዊ ህይወት፤ ሥነ ትምህርት አምላካዊውን አምሳል በተቻለ በውስጣችን እንዲሰርጽ ያደርጋል ካልን፤ የክርስቶስ ምሳሌነት ከሚፈነጥቅልን ብርሃን አኳያ እጅግ መሰረታዊ በሚባል ደረጃ መጠበቅ ይኖርበታል። ግብረገባዊው ሕግ በእግዚአብሔር ፊት በእውነት ቀና የሆነውን ሁሉ ፍንትው አድርጎ ያሳየናል።

ጥቅምት 13
Oct 23


ተጨማሪ ሀሳብ


“የሥነ ትምህርት እውነተኛ ዓላማ የእግዚአብሔርን አምሳል በነፍስ ውስጥ ማስቀመጥ ነው።”—የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ክፍል 2፡ ገጽ 259። ይህን ጽንሰ ሀሳብ በአእምሮአችን እንደ ያዝን--ክርስትና ዓለምን የሚመለከትበት ጽኑ መንገድ ለአድቬንቲስት ሥነ ትምህርት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ማየት እንችላለን። ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው ሥነ ትምህርት በራሱ አንዳች በጎ ብለን ልንጠራው የምንችለውን ነገር አጠቃሎ አልያዘም። ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ጽንሰ ሀሳብ በተቃራኒ ያሉ አመለካከቶችን በሚያራምዱ፣ እጅግ ከፍ ባሉና በመጠቁ የትምህርትና ዕውቀት ዘርፎች ሊያልፉ ይችላሉ። እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት፤ የሥነ ትምህርት ሥርዓታችን የክርስትና እምነት ዓለምን ከሚያይበት መነጽር አኳያ የተዋቀረ መሆን አለበት የምንለው ከዚህ የተነሳ ነው። ይህ ማለት እንደ ሳይንስ፣ ታሪክ፣ ግብረገብ፣ ባህል እና የመሳሰሉት አጠቃላይ የትምህርት ዘርፎች በተቃራኒ ሳይሆን ከዚህ አኳያ ለተማሪው ይቀርባሉ። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው--ነገር ግን ለመድገም ያህል፡ ገለልተኛ አመለካከት የሚባል አቋም የለም። ማንም ቢሆን ህይወትንም ሆነ እውነትን የሚመለከተው ዓለምን አጣርቶ በሚያይበት በገዛ ራሱ መነጽር ነው። እርግጥ ነው-ይህ መነጽር በሥርዓት የተቀረጸ፣ ምክንያታዊና አሳማኝ ሊሆን ወይም ላይሆን ይችላል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ዓለምን የሚያይበት መንገድ ለሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ሥርዓተ ትምህርት እጅግ አስፈላጊና መሰረት ነው።


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ከታሪክ አኳያ በአጠቃላዩ የትምህርት ሥርዓት ላይ ውድመት የደረሰበት ዘመን ብለው የሚያስቡትና በምሳሌ ሊያቀርቡ የሚችሉት የትኛውን ነው? የት አካባቢ? ምን ዓይነት ትምህርት ለተማሪዎች ቀረበ? ከዚያ ምን እንማራለን? የትምህርት ሥርዓታችንን ከእነዚህ አውዳሚ ተጽእኖዎች እንዴት መከላከልና መጠበቅ እንችላለን?

2.በዚህ ሣምንት ክርስትና ዓለምን የሚመለከትባቸውን አንዳንድ ቁልፍ ነጥቦች ማለትም--የእግዚአብሔር ሕልዎት፣ ሥነ ፍጥረት፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የደኅንነት ዕቅድ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ሕግ ለመቃኘት ሞክረናል። ክርስትና ዓለምን የሚመለከትበት መነጽር የተሟላ ቀመር ይኖረው ዘንድ ምን ዓይነት ተጨማሪ ወሳኝ ባህሪያት መካተት ይኖርባቸዋል?

3.የዐሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ፈላስፋና ተመራማሪ የነበረ አንድ ግለሰብ እንዲህ ብሎ ነበር፡ “ህሊና! ህሊና! አንቺ መለኮታዊ ባህሪ፣ አንቺ የአላዋቂውና የታሰረው አእምሮ ያልተገደብሽ መሪ፣ አንቺ ብልህ እና ነፃ፣ ለሰው ልጅ የአምላኩን አምሳል ያጎናጸፍሽ--የመልካም እና የክፉ አስተማማኝ ዳኛ።” ከፈላስፋው ሀሳብ አኳያ ትክክለኛው የቱ ነው? የተሳሳተውስ?

4.ይህን የኤለን ኋይት ጽሑፍ እንደ ገና ይመልከቱ፡ “የሥነ ትምህርት እውነተኛ ዓላማ የእግዚአብሔርን አምሳል በነፍስ ውስጥ ማስቀመጥ ነው” ይህ ምን ማለት ነው? የአድቬንቲስት ሥርዓተ ትምህርት ዓለም ሥነ ትምህርትን ከሚመለከትበት መነጽር ለምን የተለየ ሊሆን እንደሚገባ ይህ እንዴት ያሳየናል?