የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከጥቅምት 14 - 20

5ኛ ትምህርት

Oct 24 - Oct 30




የሱስ እንደ ታላቅ መምህር



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዕብ. 1:1–4፣ 2ቆሮ. 4:1–6፣ ዮሐ. 1:14፣ 18፣ 14:1–14፣ ፊልጵ. 2:1–11፣ 2ቆሮ. 5:16–21።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “በክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ ‘በጨለማ ብርሃን ይብራ’ ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን አብርቶአልና” (2ቆሮ. 4፡6)፡፡

የ ወንጌል ሰባኪው ቢሊ ግርሃም በአንድ ወቅት በዐውደ ውጊያ ጉዳት የደረሰባቸውን ወታደሮች ለመጎብኘት ከግንባሩ አዋጊ ጀነራል ጋር በመሆን ከጦር ሜዳው ብዙም ባልራቀ ጊዜያዊ የህክምና መስጫ ጣቢያ ተገኝተው ነበር። “በተፋፋመ ውጊያ መሃል በደረሰበት ከባድ መቁሰል አደጋ አካሉ የተጠማዘዘና መላወስ የማይችል አንድ ወጣት ወታደር፤ ፊቱ በወለሉ ትይዩ ሆኖ በብረቶች በተወጠረ ቃሬዛ ላይ በደረቱ እንዲተኛ ተደርጎ ነበር።” ዶክተሩ ወደ ቢሊ ግርሃም ጆሮ ጠጋ አሉና “ዳግም በሁለት እግሮቹ ቆሞ ይሄዳል የሚል ግምት የለኝም” ሲሉ አንሾካሾኩ። ጀርባው እንጂ ፊቱ የማይታየው ወታደር እንዲህ የሚል ጥያቄ ለጀነራሉ አቀረበ፡ “ጌታዬ… ለእርሶ ብዋጋም ነገር ግን ፈጽሞ አይቾት አላውቅም። ፊትዎን ማየት እችላለሁ?” በዚህ ጊዜ ጀነራሉ በብረቶች በተወጠረው ቃሬዛ ስር ተንሸራትተው በመግባት ሽቅብ ወታደሩን እያዩ አወሩት። ቢሊ ግርሃም ይህን ትእይንት እየተመለከቱ እያለ፤ የዕንባ ዘለላ ከወታደሩ ዐይኖች ቁልቁል ጀነራሉ ጉንጭ ላይ ጠብ አለ።

የሱስ በተወለደ ጊዜ ሰብዓዊው ፍጡር መላወስ የተሳነው፣ በብርቱ የቆሰለና የደማ ከመሆኑ አኳያ አምላካዊው የፈውስ ዐይኖች አጥብቀው ያስፈልጉት ነበር። ይህን ተከትሎ “አቤቱ አምላክ ሆይ፤ ፊትህን ልናይ እንችላለን?” የሚል ተማጽኖ ያቀረበ መሰለ። አብ ፊቱን ለሰብዓዊው ፍጡር ይገልጥ ዘንድ እነሆ ጌታና መምህር የሆነውን ልጁን ወደዚህ ምድር ላከ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ “በክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን” (2ቆሮ. 4፡6) ለእኛ የገለጠበትን አስደናቂ ልዩ መብትና ጥቅም ሰጠን።

ጥቅምት 15
Oct 25

አብን መግለጥ


ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ መግቢያ ላይ ስለ የሱስ የሚያነሳቸው እጅግ አስፈላጊ ነጥቦች ምንድን ናቸው? (ዕብ. 1፡ 1-2)።



የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ለአንድ ትርጉም አዘል ላቅ ያለ ጽንሰ ሀሳብ ተደጋጋሚ አጽንኦት ይሰጣሉ--የሱስ አብ ማን እንደሆነ ለሰብዓዊው ፍጡር ለማሳየት ወደ ምድር መምጣቱን! በቀደሙት ጊዜያቶች በነቢያት አማካይነት እግዚአብሔርን ለማሳየት የተሄደበት መንገድ ብጥስጣሽ ምስሎች ከመስጠት ባሻገር እርሱን ፍጹም አድርጎ የሚገልጥ አልነበረም። ስለዚህ የየሱስ መገለጥ የመጨረሻውንና የተሟላውን አምላካዊ ማንነት በገሃድ ማሳየት ቻለ።

ደግሞም የሱስ በራሱ “የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ ነው” (ዕብ. 1፡3)። ኃጢአተኞች በመሆናችን በእግዚአብሔር ክብር ፊት መቅረብ አልቻልንም። ሆኖም ሰብዓዊውን ሥጋ የለበሰው ወልድ ያንን ክብር ያንጸባርቃል። የእግዚአብሔርን ባህሪ በግልጽ እናስተውልና እንመለከት ዘንድ እነሆ እርሱ በክርስቶስ ስብዕና ውስጥ ድምፀ-ከል ሆኖ ቀረበ።

እንዲሁም የሱስ “የባሕሪው ትክክለኛ ምሳሌ” ነው (ዕብ. 1፡3)። በጥቅሱ ባሕሪ በሚል ጥቅም ላይ የዋለው የግሪክ ቃል፤ ከሰም እንደሚሠራ ወይም በሳንቲም ላይ እንደሚቀረጽ ማኅተም ዓይነት አንደምታ ሊኖረው ይችላል። ስለዚህ የሱስ የባሕሪው ትክክለኛ ቅርጽ ወይም ዱካ ነው።

አብን ማወቅ ከፈለግን መምህሩ ስለ እሱ የሚናገረውን በጥሞና ማዳመጥ፤ ዐይኖቻችንንም እንዲሁ በእርሱ ላይ መትከል ይኖርብናል። አብ በወልድ ውስጥ ታይቶአልና።

ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዕብ. 1:1–4፣ 2ቆሮ. 4:1–6፣ 2ቆሮ. 4:1–6። የሱስ ማን ነው? ከእርሱ ምን እንማራለን?



ጳውሎስ እና የአገልግሎት አጋሮቹ ስለ እግዚአብሔር ሲያስተምሩ፤ የሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ስለ አብ ሲናገር የተጠቀማቸውን መንገዶች የማንጸባረቅ መሻት ነበራቸው። የሱስ እንደ እግዚአብሔር አምሳልነቱ (2ቆሮ. 4፡4) ስለ እግዚአብሔር አብ ዕውቀት ሰጥቶናል። በተመሳሳይ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል ከአሳችና የተዛባ አቀራረብ ጠብቆ እውነትን በግልጽ ሲያቀርብ ይስተዋላል (2ቆሮ. 4፡2)። እግዚአብሔር በፍጥረት ወቅት ጨለማውን ለማስወገድ ብርሃን እንደ ተጠቀመ ሁሉ፤ ስለ እርሱ የሚቀርብ ማንኛውንም ሐሰተኛ አመለካከት ለማስወገድ እና ስለ እግዚአብሔር እውነት የሆነውን ለማሳየት ልጁን የሱስ ሰጠን። ስለ እግዚአብሔር ግልጽ እና ጥርት ያለ ዕውቀት የምናገኘው “በክርስቶስ ፊት” (2ቆሮ. 4፡6) ነው። የሱስ አብን በትክክለኛ መንገድ እንዳንጸባረቀው ሁሉ እኛም “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ” (ኤፌ. 5፡1) የሚል ጥሪ ቀርቦልናል። ለመሆኑ ይህ ምን ማለት ነው? እርሱን እንዴት መምሰል እንዳለብን አስመልክቶ ከየሱስ ምን መማር እንችላለን?

ጥቅምት 16
Oct 26

አብን መግለጥ (የቀጠለ…)


ዮሐንስ ልብን በሚነካው የወንጌል መግቢያ መልእክቱ (ዮሐ. 1፡1-18) የሱስ ዘላለማዊ “ቃል” ነው ሲል ይሞግታል። ዮሐንስ በድፍረት የተሞሉና የአጽናፈ ሰማያት ስፋትና ጥልቀት ያላቸውን አገላለጾች ተጠቀመ እንጂ፤ ሲፈራ ሲቸር ወይም ዉሱን አድርጎ እነዚህን መንገዶች ተጠቅሞ የሱስን አልገለጸውም። ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ፣ እንደውም ከዘላም አንስቶ የሱስ ነበር። የፍጥረትን ሥራ ያከናወነው የሱስ (ዮሐ. 1፡ 2-3) ወደ ዓለም የመጣው ቃል እንደ መሆኑ እርሱ “ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጪ” ነበር (ዮሐ. 1፡9)።

እንደ ዮሐንስ ገለጻ፤ የክርስቶስ ሰብዓዊውን አካል መውሰድ ምን ዓይነት ውጤት አስከተለ? እንደ ቃልነቱ ምን ዓይነት ብርሃን አመጣ? ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ምን ዓይነት ብቃቶች ነበሩት? ዮሐ. 1፡14፣18።



“ምድር በብርቱ ድቅድቅ ጨለማ ተውጣ በነበረበት ወቅት ብርሃን ፈነጠቀ… “ሰብዓዊው ዘር አንድ ብቻ ተስፋ ነበረው… ዓለም ዳግመኛ የእግዚአብሔርን ማንነት ዕውቀት እንዲያገኝ ማድረግ ነበር።

“ክርስቶስ ይህን ዕውቀት በሰብዓዊው ልብ ሊያድስ መጣ። እግዚአብሔርን እናውቀዋለን የሚሉ ስለ እርሱ ያቀረቡትን ሐሰተኛ አስተምህሮ እርቃኑን ለማስቀረት፣ የሕጉን ተፈጥሮ ለመግለጥ እና የቅድስናን ውበት በራሱ ባህሪ ለመግለጥ ወደዚህ ምድር መጣ።”—Education, p. 82.

የሱስ ራሱ “‘እኔን ያየ አብን አይቶአል’ ” (ዮሐ. 14፡9) በማለት ይናገራል። የሱስ ይህን አባባል ጥቅም ላይ ያዋለበት መቼት ምን ነበር? ለምን እንዲህ አለ? (ዮሐ. 14፡1-14)



የፊልጶስን የተሳሳተ አነጋገር ተከትሎ ብዙውን ጊዜ እርሱን ለመተቸት እንፈተናለን (ዮሐ. 14፡8)። ምንም እንኳ ይህ ደቀ መዝሙር ከየሱስ ጋር ለዓመታት የዘለቀ ቅርበት ያለው ህብረት ቢመሰርትም--የሱስ የአብን ባህሪ ለማሳየት ሥጋ ለብሶ የመምጣቱን መሰረታዊ ነጥብ ግን ስቶ ነበር። ከጌታና መምህሩ ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው፤ እንዲህ ዓይነቱን ስህተት መሥራቱ ምናልባት ለዛሬዎቹ መምህራን-አያችሁት! የሚል ዓይነት ምቾት ቢጤ ይሰጥ ይሆናል። ሆኖም ይህ የፊልጶስ አነጋገር የወንጌል አካል እንዲሆን የተደረገበት ምክንያት፤ እርሱን እንድንተችበት ሳይሆን ራሳችንን የምንመረምርበት ዕድል እንድናገኝ ሊሆን ይችላል። ለምን ያህል ጊዜ ከየሱስ ጋር ተጉዘናል? ከፊልጶስ ይልቅ የሱስን በተሻለ አስተውለነዋል? “‘እኔን ያየ አብን አይቶአል’ ”

ጥቅምት 17
Oct 27

የታላቁን መምህር አእምሮ ማንበብ


ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ሲጽፍ በዚያ ስለነበረው ክርስቲያን ማኅበረሰብ ያሳሰበውና በልቡ ውስጥ የነበረው ነገር ምን ነበር? ፊልጵ. 2:1–4፣ 4:2-3።



በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ከሚገኙ እጅግ ጥልቀት ያላቸው መልእክቶች አንዱ ፊልጵ. 2፡1-11 ሲሆን፤ መልእክቱ ክርስቶስ አስቀድሞ ስለ መኖሩ፣ ስለ መለኮትነቱ፣ ሥጋ ስለ መልበሱ፣ ሰው ስለ መሆኑ እንዲሁም የመስቀል ላይ ሞትን ስለ መቀበሉ ጥሩ አድርጎ ያብራራል። የሱስ ከሰማያ ሰማያት ወደ ምድር ወርዶ እስከ ቀራኒዮ የሄደበትን ረጅሙንና አስቸጋሪውን ጉዞ ያብራራል (ፊልጵ. 2፡5-8)። እንዲሁም መላው ዩኒቨርስ ለእርሱ ስግደት ያቀርብ ዘንድ ምን ያህል አብ ከፍ ከፍ እንዳደረገውም ይገልጻል (ፊልጵ. 2፡9-11)። በእነዚህ ቁጥሮች አያሌ አስደናቂ እውነቶች ታጭቀው ቀርበዋል። ጳውሎስ እንዴት ነበር ፊልጵ. 2፡5-11 ያስተዋወቀው? ሐዋርያው ከሚያሞግሳቸውና ከሚያከብራቸው--በየሱስ ህይወት ገቢራዊ የሆኑ ክስተቶች መሃል፤ አማኞች በህይወታቸው እንዲያንጸባርቋቸው ተስፋ የሚያደርጋቸው የትኞቹን ይመስሎታል? (ፊልጵ. 2፡6-11)።



የክርክር ሀሳብ ሊያነሱ የሚችሉ አንዳንድ የፊልጵስዩስ አማኞች ከየሱስ እና ሥጋ ከመልበሱ--ትምህርት ይወስዳሉ ብሎ ጳውሎስ ተስፋ አድርጎአል። የሱስ ሰብዓዊውን አካል መልበስ ከቻለና “የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም አምሳል ተገኝቶ” እስከ መስቀል ሞት ራሱን አሳልፎ ከሰጠ--ለፍቅር ሲባል ምን ያህል አንዱ ለሌላው ራሱን ማስገዛት ይኖርበታል?

ከታላቁ መምህር ከየሱስ ብዙ የምንማረው ነገር መኖሩን እንድናስታውስ ተነግሮናል። በምድራዊ አገልግሎቱ ከሚያካፍለን መልእክቶቹ፣ ከታምራቶቹና ለሌሎች ከነበረው በጎ ምላሾቹ ትምህርት እናገኛለን። የሰማይን ክብር በከብት በረት ለመለወጥ ፈቃደኛ የነበረውንና እጅግ አድርጎ ራሱን ዝቅ ያደረገውን ህይወት በመኖር፤ ከሌሎች ጋር ላለን ግንኙነት እርሱን ምሳሌያችን የማድረግ ብርቱ ምኞት ሊያድርብን ይችላል። (ምንኛ ታላቅ ትምህርት ነው!)

በተቃራኒው፤ ዓለም ራሳችንን ከፍ ከፍ እንድናደርግና ባገኘነው ስኬት እንድንኩራራ አጥብቆ ይጋብዘናል። ሆኖም ከቤተልሔሙ የከብት ግርግም ብሎም ከጌታና መምህሩ የምንማረው ትምህርት ግን ከዚህ የተለየ ነው። የእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ ውጤት የሆነው ሥነ ትምህርት እና የደኅንነት እቅድ ክንዋኔ የሚያገኘው ራሳችንን በማመጻደቅ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት ትሁታን ሆነን ስንገኝና ሌሎችን ስናገለግል ነው።

ራስዎን በትህትና ዝቅ አድርገው ከርስቶስን በብርቱ ለሌሎች የሚያንጸባርቁበትን ዕድል እንዳያገኙ ፈታኝ የሆነቦት ነገር ምንድን ነው?

ጥቅምት 18
Oct 28

ታላቁ መምህር እና እርቅ


ሁሉም ዓይነት ሰብዓዊ ግንኙነቶች እንከን ስለማያጣቸው ለመፍረስ ጊዜ አይወስድባቸውም። አንዳችን ከሌላችን እንነጠላለን። በአንድ ወቅት የልብ ጓደኛችን የነበረ ሰው የሆነ ጊዜ ላይ ባይተዋር ይሆናል። ለነገሩ እንዲህ ያለ እንከን የሚገጥመው ግንኙነት ዳግም መጠገን ይችላል። ይህ ሲሆን በአስገራሚው የእርቅ ሂደት ልምድ ውስጥ እናልፋለን። ጥቂት የሚባሉ ሰብዓዊ ግንኙነቶች የእንዲህ ያለ ጣፋጭ ተሞክሮ ባለቤት ናቸው።

እርቅ ከክርስቶስ ሥጋ መልበስ እና ከታላቅ መምህርነቱ አኳያ የነበረው ሚና ምን ነበር? 2ቆሮ. 5፡16-21።



ከሰብዓዊ ወዳጃችን ጋር የነበረን ልዩነት ተፈትቶ ግንኙነታችን ሲታደስ የመባረክ ስሜት የሚሰማን ከሆነ፤ ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ ስንፈጥር እንዴት ያለ ታላቅ ስሜት ሊሰማን ይገባል? ጳውሎስ በ2 ቆሮ. 5፡16-21 ግልጽ አድርጎ እንዳስቀመጠው-ከእግዚአብሔር ጋር የነበረንን የተበጠሰ ግንኙነት በመቀጠል ቀዳሚውን የእርቅ ተነሳሽነት የወሰደው አብ እራሱ ነው። በዚህም ይህን የማስታረቅ ሥራ “በክርስቶስ አማካይነት” ተፈጻሚ አደረገ። “እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር” አስታረቀ (2ቆሮ. 5፡19)።

ይህም ቢሆን እንደው በደፈናው እርቅ የሚያስገኘው ደስታ ተጠቃሚዎች እንድንሆን ብቻ ዕድሉ አልተሰጠንም። ይልቁንም ከታላቁ መምህር መማር ይጠበቅብናል። ሰብዓዊውን ሥጋ የለበሰው የሱስ በእርቅ ሥራ ተሳትፎ ነበረው። እኛም በዚህ ተሳታፊ እንሆን ዘንድ ግብዣ ቀርቦልናል። እግዚአብሔር በክርስቶስ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታረቀን። ስለዚህ ከጳውሎስ ጋር “የማስታረቅ አገልግሎት” (2ቆሮ. 5፡ 18) ተሰጥቶናል።

የክርስቶስን ሥጋ መልበስ አስመልክቶ የተሰጠው ሌላው የአዲስ ኪዳን ታላቅ መልእክት በቆለ. 1፡15-20 ይገኛል። መልእክቱ ብዙውን ጊዜ በመዝሙር መልክ ሲቀርብ ቢስተዋልም፤ የዚህ መልእክት የመጀመሪያ ክፍል በክርስቶስ ሥጋ መልበስ ሚና ዙሪያ ዳሰሳ (ቆለ. 1፡15-17) ሲያደርግ--የመጨረሻው አጋማሽ ክፍል ደግሞ ክርስቶስ ቤዛ በመሆን በነበረው ሚና ላይ ትኩረት ያደርጋል (ቆለ. 1፡18-20)። ክርስቶስ የፈጣሪ--አዳኝነት ሚና ቢኖረውም፤ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ከራሱ ጋር ያስታረቀው በእርሱ ነው። ዩኒቨርስ አቀፍ ተጽእኖ ያለው እግዚአብሔር በክርስቶስ አማካይነት ያከናወነው የእርቅ ሥራ “በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን በማድረግ በምድርም ሆነ በሰማይ ያለውን ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል ከራሱ ጋር አስታረቀ”(ቆለ. 1፡20)።

የታላቁን መምህር ዩኒቨርስ አቀፍ የአስታራቂነት ሥራ ስፋትና ጥልቀት ፈጽሞ ማስተዋል ባንችልም፤ በዙሪያችን “የማስታረቅ አገልግሎት” (2ቆሮ. 5፡18) በመስጠት ተሳትፎ እንድናደርግ ግን ግብዣ ቀርቦልናል። የሱስ “ ‘አንተ ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ፤ እኔም ወደ ዓለም ልኬአቸዋለሁ’ ” (ዮሐ. 17፡18) ብሎ ሲጸልይ ይህ በአእምሮው ነበር ብለን ማሰብ እንችላለን?

እንደ አስታራቂነት፤ የእግዚአብሔርን ሚና ማንጸባረቅ የምንችልባቸው ተግባራዊ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ይህ ማለት--ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥ ችግር ያለባቸው ሰዎች ካሉ እርስ በእርስ እንዲታረቁና ይቅር እንዲባባሉ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

ጥቅምት 19
Oct 29

የታላቁ መምህር የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች


በአንድ ወቅት እዚህ ግባ ከማይባል አነስተኛ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ መጠነኛ የበግ መንጋ ያግዱ የነበሩ እፍኝ የማይሞሉ ተራ እረኞች የዘወትር ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ነበሩ። ታዲያ በአንድ ወቅት፣ ፍጹም ባልጠበቁት ሁኔታ ድንገት መላእክት አስደናቂና እጹብ ድንቅ የሆነ የምሥራች ይዘው በመገስገስ፤ የዓለም ቁጥር አንድ የሆነውን ምርጥ ሰበር ዜና አበሰሯቸው! በመላእክቱ መገለጥና ሰናይ ብሥራት ጉልበት ያገኙት እረኞች፤ ይህን ስለ እርሱ የተነገረለትን ህፃን ፍለጋ ለመንቀሳቀስ ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር።

ከእረኞቹ መሃል ቆመው ወደ ግርግሙ እየተመለከቱ አድርገው ራስዎን በዐይነ ህሊናዎ ይሳሉ። ምን ይታዮታል? ሉቃ. 2፡8-20።



የታላቁ መምህር የመጀመሪያ ተማሪዎች የሆኑትን--ዮሴፍ፣ ማርያም እና እነዚያን የበግ እረኞች ማድነቃችን የግድ ይሆናል። ከመጠን በላይ ራስን ዝቅ በማድረግና ፍጹም በሆነ ትህትና የተገለጠው ይህ የሱስ የተወለደበት ሁናቴ፤ እግዚአብሔር በዚህ ህፃን ማንነት ከሰብዓዊው ፍጡር ጋር አንድ ስለ ሆነበት ሥጋ የመልበሱ አስደናቂ ክስተት የሚሰጠው አንዳች ፍንጭ የለም። ሆኖም እነዚህ የመጀመሪያ ተማሪዎቹ በራእዮች፣ ሕልሞች እንዲሁም የመላእክት መገለጦች አማካይነት ከየሱስ መወለድ ውጪያዊ እይታ ባሻገር መመልከት ችለው ነበር። እረኞች ስለዚህ ሕፃን ማንነት ማለትም እርሱ “‘ መድኅን… ጌታ ክርስቶስ’ ” (ሉቃ. 2፡11፣ 2፡17)መሆኑን ለሌሎች አካፍለው ነበር። ከምሥራቅ የመጡት ጠቢባን ስለ የሱስ መወለድ የምሥራች የሰጡት ምላሽ ምን ይመስላል? የሄሮድስስ? ማቴ. 2፡1-12



ታላቁ መምህር ገና የመጀመሪያውን ምሳሌያዊ ንግግር ከመናገሩ ወይም ታምራት ከማድረጉ አስቀድሞ የእኛን አምልኮ ለመቀበል የተገባው ነው። ለምን ቢባል-በማንነቱ የተነሳ! በቀጣዮቹ የየሱስ የማስተማር አገልግሎት በሙላት ሐሴት ማድረግ ከተፈለገ፤ እነዚህ የቀደሙ ተማሪዎቹ--ጠቢባን ለታላቁ መምህር ያቀረቡትን አምልኮ በአንድ ላይ ማካተት ይኖርብናል። ለአስተምህሮዎቹ ልዩ አንድናቆት ያለን--እርሱ ከጠቢብ መምህርም የላቀ ምርጥ ነው። እርሱ ከሰው ልጆች ጋር አብሮ ለመኖር የመጣ አምላክ ነው። ለክርስቶስ ስግደት ማቅረብ እና እርሱን ማምለክ የከርስቲያናዊው ሥርአተ ትምህርት ጥልቅ መሰረት ነው።

ከምሥራቅ ከመጡ ጠቢባን፣ እረኞች እና መላእክት ጋር በአንድነት አዲስ የተወለደውን ንጉሥ ይኸውም ክርስቶስን እንድናመልክና፤ በህፃኑ የሱስ ውስጥ በተጨባጭ የቀረበውን ራሱን አግዚአብሔርን እንድናይ ተጠርተናል። የየሱስ ሥጋ መልበስ ከእግዚአብሔር ባህሪ አኳያ ያለውን አንደምታ ለማሰብ ይሞክሩ። ልንገነዘብ ከምንችለው በላይ የሆነው የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ አምላክ ሰብዓዊውን ሥጋ በመልበስ “ራሱን ዝቅ አደረገ”፣ እንደ የሱስ ኖረ፣ የኃጢአታችንን ቅጣት ራሱ ተሸክሞ በመስቀል ላይ ሞተ። ታዲያ ይህ የምሥራች መሆን የቻለው እንዴት ነው?

ጥቅምት 20
Oct 30


ተጨማሪ ሀሳብ


Read Ellen G. White, “The Teacher Sent From God,” pp. 73–83, in Education. “የሁሉም እውነተኛ ሥርዓተ ትምህርት የሥራው ማዕከል ከእግዚአብሔር የተላከው መምህር ነው። አዳኙ ከሺ ስምንት መቶ ዓመታት በፊት የዛሬውን ሥራ መሰረት ሲጥል የሚከተሉትን ቃላት ተናግሮ ነበር፡ “‘ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤ እኔ ሕያው ነኝ’ “‘አልፋና ኦሜጋ፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ’” (ራእ. 1፡17-18፣ 21፡6)። “ከእንዲህ ያለው መለኮታዊ ሥርዓተ ትምህርት ዕድል እና መምህር አብሮነት አፈንግጦ ሌላ ከመሻት--ከጥበብ ውጪ ጥበበኛ ለመሆን ከመፈለግ--እውነትን እየካዱ እውነተኛ ለመሆን ከመጣር--ከብርሃን ውጪ ብርሃን ከመፈለግ፣ ያለ ህይወት--በህይወት ለመኖር ከማሰብ፣ ፊትን ከሕይወት ምንጭ እየመለሱ ውሃ መያዝ ከማይችል የሚያፈስ ማጠራቀሚያ ውሃን ከመሻት የከፋ ምን ከንቱነት አለ! “ጌታ ዛሬም እንዲህ ሲል ይጋብዘናል፡ ‘ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።’ ‘እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል’ (ዮሐ. 7፡37-38፣ 4፡14)” —Ellen G. White, Education, p. 83. “ውድ መምህር… “ለሥራዎ ለሚያደርጉት ከፍተኛ ዝግጅት፤ የመምህራን አለቃ የተጠቀመባቸውን-ህይወት፣ ዘዴና ብልሃት ወደ ተሞሉት ቃላት አመላክትዎታለሁ። እርሱን በአጽንኦት ይመለከቱ ዘንድ አቀርብልዎታለሁ። ለእርስዎ እውነተኛውና ተስማሚው እርሱ ነውና። የመለኮታዊው መምህር መንፈስ የልብዎን ማኅደር ብሎም መላው ህይወትዎን እርስቱ ያደርግ ዘንድ ወደ እርሱ መመልከትዎንም ሆነ በእርሱ ውስጥ መኖርዎን አያቋርጡ።

“‘ የጌታን ክብር እንደ መስታወት እያንጸባረቅን የእርሱን መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን’” (2ቆሮ. 3፡18)። “ይህ በተማሪዎችዎ ላይ ሥልጣን የሚያገኙበት ምስጢር ነው። እርሱን ያንጸባርቁ”— Education, p. 282.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ሰብዓዊውን ሥጋ ከለበሰው ታላቁ መምህር የመማርን ጽንሰ ሀሳብ ከልባቸው ለሚቀበሉ ክርስቲያን መምህራን እና ተማሪዎች ምን ዓይነት እሴቶች እና ተግባራት ይበልጥ ጠቃሚ ይሆናሉ?

2.የእግዚአብሔር ባህሪ ሥጋ በለበሰው የሱስ እንደተንጸባረቀ ሁሉ ክርስቲያን ወላጆች እና መምህራንም ይህን የማሳየት ኃይል የሚሆናቸውን ከፍ ያለ ማንነት ተላብሰዋል። በዚህ ከፍ ያለ ደረጃ መሰረት መንቀሳቀስ ሳይሆንልን ሲቀር ምን ማድረግ አለብን?

3.በሐሙስ ጥናት መጨረሻ ላይ በቀረበው ጥያቄ ዙሪያ ተወያዩ። የየሱስ መወለድ፣ ምድራዊ ህይወት እና ሞት ስለ እግዚአብሔር ባህሪ ምን ያስተምረናል? በተለይ ብርቱ ፈተና በገጠመን ጊዜ ይህ መጽናኛችን መሆን የሚገባው ለምንድን ነው?