
ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘዳ. 6:5፣ ዘዳ. 31:9–27፣ ሮሜ 3:19–23፣ ራእ. 12:17፣ 14:12፣ ማር. 6:25–27፣ ዕብ. 5:8።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ ጥቅስ፡ “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ” (ዘዳ. 6፡5)፡፡
ጳ
ውሎስ ሕግን በመጠበቅ ለመዳን የሚያስቡትን ሕጋውያን የገላትያ ሰዎች
በማስጠንቀቅ እንዲህ ጽፎአል፡ “ሕግ የተሰጠው ሕይወትን ለማስገኘት ቢሆን
ኖሮ፣ በእርግጥ ጽድቅ በሕግ በኩል በተገኘ ነበር” (ገላ. 3፡21)። እርግጥ ነው-የሆነ ዓይነት ሕግ በመጠበቅ ሕይወት የሚገኝ ቢሆን ኖሮ ያ ሕግ ሌላ ሳይሆን
የእግዚአብሔር ሕግ በሆነ ነበር። ጳውሎስ ሊዳስስ ያሰበው ነጥብ--ኃጢአተኞች
ለሆንነው ለእኛ የእግዚአብሔር ሕግ እንኳ ህይወት ሊሰጥ አልቻለም የሚል
አንደምታ አለው። ለምን? “መጽሐፍ ግን ዓለም ሁሉ የኃጢአት እስረኛ መሆኑን
ያውጃል፤ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው ተስፋ ለሚያምኑት ሁሉ
ይሰጥ ዘንድ ነው” (ገላ. 3፡22)።
ሆኖም ሕጉ ለኃጢአተኞች ሕይወት መስጠት ካልቻለ፤ ጸጋ እንደሚያስፈልገን
ከማሳየት ባለፈ ፋይዳው ምንድን ነው? ኃጢአታችንን የማሳየት አሉታዊ ተግባር
ብቻ ነው ያለው?
አይደለም፡ ይልቁንም ሕጉ በየሱስ ብቻ የሚገኘውን የሕይወት መንገድ ሊያመላክተን
ተሰይሞአል። በተጨማሪ እውነተኛ ሥነ ትምህርት እኛን ወደ ጸጋ ሕይወት፣ ወደ
እምነትና ክርስቶስን ወደ መታዘዝ ይመራል። በዚህ የተነሳ የዚህ ሣምንት ጥናታችን
የእግዚአብሔር ሕግ በአጠቃላዩ ክርስቲያናዊ ሥነ ትምህርት ላይ ባለው ሚና ዙሪያ
ትኩረት ያደርጋል። ይህን ስናደርግ፤ ሕጉ ሊያድነን ባይችልም እንኳ ነገር ግን ስለ
እምነት፣ ስለ ጸጋ እና አምላካችን እግዚአብሔር ለወደቀው ሰብዓዊ ፍጡር ስላለው
ፍቅር ሊያስተምረን የሚችለውን እንመልከት።
የኦሪት ዘዳግም መጽሐፍ ሙሴ በመጨረሻ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከሚገባው
ከአዲሱ ትውልድ አስቀድሞ ለነበሩት እስራኤላውያን የጻፋቸውን የመጨረሻ
መልእክቶች ይዞአል። እነዚህ ሕዝቦች ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደሚወርሷት
ምድር ከመግባታቸው አስቀድሞ ልብ ሊሏቸው የሚገቡ አንዳንድ ግልጽ ቃላቶችና
መመሪያዎች ተሰጥተዋቸው ነበር።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 31፡9-13። ጌታን መፍራት ምን ማለት ነው?
እግዚአብሔር የገዛ ሕጉን ለእስራኤል የሰጠባቸው መንገዶች በእቅድና በዓላማ
የተሞሉ ነበሩ። እርሱ ሕጎቹ እንዳይረሱ ሊረዱ የሚችሉ ማናቸውንም ነገሮች
ከመስጠት ወደ ኋላ አላለም። እግዚአብሔር ምን ያህል በትዕግሥት የተሞላ መምህር
እንደሆነ ይህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ጌታ መልእክቱን ለማስተላለፍ ነቢያትን
ደጋግሞ በማስተማርና በመላክ በአገልጋዮቹ የተጠቀመ ሲሆን፤ ይህን በተደጋጋሚ
አድርጎአል። ከብሉይ ኪዳን መልእክቶች አብዛኞቹ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቦቹ
የሕይወትን መንገድ እንዲከተሉ ሊያስተምራቸው የፈለገባቸው መንገዶች ከመሆን
ውጪ ሌላ መሆን ይችላሉ?
ሙሴ አምላካዊውን ሕግ ለቀጣዩ ትውልድ ስለ ማስተማር አስፈላጊነት የሰጠውን
አጽንኦት በጥቅሶቹ ይመልከቱ። ሙሴ ይህን ሁኔታ በሁለት ቅደም ተከተላዊ ሂደቶች
ይገልጸዋል። በመጀመሪያ ልጆች ስለ ሕጉ ሊሰሙ፤ በመቀጠል አምላካቸውን
“እግዚአብሔርን መፍራት ሊማሩ ይገባቸዋል” (ዘዳ. 31፡13)--በሚል።
መጀመሪያ ይሰማሉ፤ በመቀጠል ፈሪሐ እግዚአብሔርን ይማራሉ። ይህ ማለት
ፍርሐት ስለ ሕጉ ማወቅን ተከትሎ የሚመጣ ተፈጥሮአዊ ውጤት አለመሆኑን
ያሳያል። የፈሪሐ እግዚአብሔርን ሂደት መማር የግድ ይሆናል። ዕውቀት እና
ፍርሐት ሂደት እንጂ ከመንስኤና ውጤት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌላቸው ሙሴ
በተዘዋዋሪ ይጠቅስልናል።
እንዲሁም “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣
በፍጹም ኀይልህ ውደድ” (ዘዳ. 6፡5) ተብሎ ለሕዝቡ ከተሰጠው መልእክት አኳያ
“እግዚአብሔርን መፍራት” ምን ማለት ነው? ምናልባት ይህን አባባል ልጅ መልካም
የሆነውን አባት ከሚወድበትና ከሚፈራበት ሁኔታ አኳያ ልናስተያየው እንችላለን-የሚለውን እየተናገረና የሚናገረውን እያለ ፍቅርና እንክብካቤውን ከሚገልጸው አባት
ጋር! እንዲህ ያለ አባት ያለው ልጅ ጥፋት ሲሠራ ጥፋቱ ሊያስከትል የሚችለውን
መዘዝ በሚገባ ይገነዘባል። ስለዚህ በተመሳሳይ ጊዜ--እግዚአብሔርን ልንወደውም
ሆነ ልንፈራው መቻላችን እርግጥ ነው። እነዚህ ሁለቱ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ
ጽንሰ ሀሳቦች አይደሉም። እግዚአብሔር መልካም በመሆኑ የተነሳ አብልጠን ስለ
እርሱ ባወቅን ቁጥር አብልጠን እንወደዋለን። ይህ አምላክ ምን ያህል ቅዱስና ጻድቅ
እንደሆነ መመልከታችን በተቃራኒው የሚገኘውን የእኛን ኃጢአተኝነትና የረከሰ
ማንነት በጥልቀት እንድናይ እና ያልጠፋነው ለእኛ በተቆጠረው የእርሱ ጽድቅ ሥራና
ቤዛነት ይኸውም እንዲያው በጸጋው ብቻ መሆኑን እንድንገነዘብ ያስችለናል።
እግዚአብሔርን በተመሳሳይ ጊዜ መውደድና መፍራት የሚለውን ጽንሰ
ሀሳብ እንዴት ያስተውሉታል?
ሙሴ የመሞቻው ጊዜ ሲቃረብ ከኋላው ትቶት ስለሚሄደው ሁናቴ በቂ ግንዛቤ
ነበረው። እርሱ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን የተስፋይቱ ምድር ወደ ሆነችው ከነዓን
እንደሚገቡ ያውቅ ነበር። እነዚህ ሕዝቦች ለረጅም ዘመናት ተስፋ ሲያደርጉ ወደ
ኖሩት መዳረሻቸው ሲደርሱ የአመጻ ተግባር እንዲሚፈጽሙም እንዲሁ በሚገባ
ይረዳ ነበር።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 31፡14-27። ሙሴ ከመሞቱ አስቀድሞ ምን
ዓይነት ዝግጅቶች አድርጎ ነበር? እርሱን አብልጠው ያሳሰቡት ጉዳዮች
ምን ነበሩ? እነዚህን ጉዳዮች እንዴት ይገልጻቸዋል?
እዚህ ላይ የቀረበው የሙሴ ሁኔታ ሌላው መምህር ተተክቶ የሚገባበትን ሁኔታ
እያመቻቸ የሚመስል ድምፀት ያለው ይመስላል። እርሱ በክፍል ውስጥ እያለ
ተማሪዎቹ በፊቱ አጓጉል ጸባይ ያሳዩት እንደነበር ያውቃል። ሰለዚህ እርሱ
በማይኖርበት ወቅት ተማሪዎቹ እንደማይረብሹ አድርጎ በማሰብ ራሱን ማሞኘት
አልፈለገም። የእግዚአብሔርን የምስክሩን ኪዳን ታቦት ተሸክመው ከቦታ ቦታ
ይዘዋወሩ የነበሩ ሌዋውያን፤ የሕጉ መጽሐፍ በእነርሱ ላይ “ምስክር” ሆኖ በዚያ ይኖር
ዘንድ ከምስክሩ ኪዳን ታቦት አጠገብ እንዲያስቀምጡት ሙሴ አዞአቸው ነበር።
ሙሴ የተጠቀመበትን የትምህርት ዕቅድ ሰነድ እንደው በዋዛ እርሱን ለሚተካው
መምህር እያስተላለፈ አልነበረም--ይልቁንም በምስክር አስተላለፈው! ሙሴ ስለ ሕጉ
መጽሐፍ ሲናገር የሰዎችን ልብ ለመገሰጽ የሚያስችል ሕያው ኃይል እንዳለው አድርጎ
ያቀርበዋል።
በእነርሱ ላይ “ምስክር ሆኖ” በዚያ እንዲኖር ስለ ተደረገው ሕግ
አሰብ ያድርጉ። ይህን ጽንሰ ሀሳብ ከአዲስ ኪዳን አኳያ እንዴት
እናስተውለዋለን? ሮሜ 3፡19-23--ይመልከቱ። ጸጋ እንደሚያስፈልገን
ሕጉ እንዴት ያመለክተናል?
ጌታ ለሙሴ ያስተማረውን መዝሙር በጽሑፍ እንዲያሰፍር እግዚአብሔር ሙሴን
እንዳዘዘው በዘዳ. 31 እንመለከታለን። ከዚያም “ስለ እኔ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ”
(ቁ. 19) በሚል በተጠቀሰው መሰረት እነሆ ሙሴ መዝሙሩን ለእስራኤል ልጆች
አስተማረ። በዚህም መልካም አርአያ የሆኑት አምላካዊ መመሪያዎች በድጋሚ
ቀርበው እንመለከታለን። መዝሙር በሚዘመርበት ጊዜ በቀላሉ አንዱ ለሌላው
እያካፈለ ወደ ብዙዎች ሊዛመት ይችላል። መዝሙር ምስክር ሲሆን ሰዎች ወደ
ራሳቸው እንዲመለከቱና ስለ ራሳቸው ምን እንደሚል እንዲያጤኑ ያስችላቸዋል።
እግዚአብሔር በሚሰጠን በሙሉ ኃይላችን ትእዛዛቱን ለመፈጸም ባለን
ምኞት እንኳ--ሕጉ በምን ዓይነት መንገዶች በእኛ ላይ “ምስክር ሆኖ”
ይሠራል? ወንጌል በሕይወታችን እንደሚያስፈልገን አስመልክቶ ይህ
ምስክር ምን ያስተምረናል?
የእግዚአብሔርን ሕግ ማወቅና መታዘዝ ተከትሎ የተገኙ ሌሎች ውጤቶች በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ቀርበው እንመለከታለን። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢያ. 1፡7-8። ጌታ ለኢያሱ ምን እያለው ነበር? በዚህ ስፍራ የምናገኛቸውን መርኅዎች ዛሬ ጥቅም ላይ የምናውላቸው እንዴት ነው?
ኢያሱ ከነዓን ለመግባት ጥቂት ሲቀረው ጌታ እንዲህ ሲል ነገረው፡ “አይዞህ፤ ብቻ
አንተ በርታ፤ ባርያዬ ሙሴ የሰጠህን ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቅ፤ በምትሄድበትም
ሁሉ እንዲሳካልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል” (ኢያ. 1፡7)።
ይህ መታዘዝን ተከትሎ ከሚገኙ ውጤቶች አንዱ ሆኖ የቀረበ የስኬት ጽንሰ ሀሳብ፤
ዛሬ ስኬት በዓለማችን ከሚለካበት መንገድ በተቃራኒ የተቀመጠ ይመስላል። ዛሬ
ብዙዎች እንደሚያምኑት እንደ ሰኬት ምልክት ሆነው የሚቀርቡት--አዳዲስ ሀሳቦችና
የፈጠራ ሥራዎችን ማመንጨት እንዲሁም ራስን መቻልና በራስ ሀሳብ መመራት
ናቸው። በአንድ የግል የሥራ ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን--ብቃት እና ኪሳራ ሊመጣ
ቢችል እንኳ ያን ለመቀበል ዝግጁ ወኔ ይጠይቃል። ሆኖም ስኬት በአምላካዊው
ዐይን ከዚህ የተለዩ የእሴት ስብስቦችን ይዞአል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 12:17፣ 14:12፣ ሮሜ 1:5፣ 16:26፣ ያዕ.
2:10–12። ጥቅሶቹ ዛሬ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ እንዳለብን
አስመልክቶ ምን ይነግሩናል? ምንም እንኳ የዳንነው የእግዚአብሔርን
ትእዛዛት በመጠበቃችን ባይሆንም፤ ዛሬም ትእዛዛቱን መጠበቃችን
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ብሉይ ኪዳን፣ አዲስ ኪዳን፣ አሮጌው ኪዳን፣ አዲሱ ኪዳን--የቱንም ዓይነት
አንደምታ ሊኖራቸው ቢችልም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አማኝ ክርስቲያንነታችን
የእግዚአብሔርን ሕግ እንድንታዘዝ ተጠርተናል። ሕጉን መተላለፍ ወይም በሌላ
አነጋገር ኃጢአት መሥራት የሚያመራው ወደ ህመም፣ ሥቃይና ዘላለማዊ ሞት
ብቻ ነው። የእግዚአብሔርን ሕግ የመጣስ ውጤት የሆነውን የኃጢአት ውጤት-ለራሳቸው ያልተማሩ ወይም ያልተገነዘቡ ከቶ ሊኖሩ ይችላሉ? የጥንት እስራኤላውያን
የእግዚአብሔርን ሕግ ሲጠብቁ (ምንም እንኳ ጸጋ ቢያስፈልጋቸውም) ብልጽግና
ከማግኘታቸው አኳያ፤ የዛሬውም የእኛ ሁኔታ ከእነርሱ የተለየ አይደለም። ስለዚህ
የክርስቲያናዊ ትምህርት አካል የሆነውን የእግዚአብሔር ሕግ፤ በእምነት ከመኖርና
በአምላካዊው ጸጋ ከመታመን ዓይነተኛ ፍቺ አኳያ እንደ ማዕከላዊ ክፍል ልንጠብቀው
ይገባል።
ኃጢአት ካስከተለው መዘዝ አኳያ የግል ተሞክሮዎ ምን ይመስላል?
ምናልባት ሌሎች በተመሳሳይ ስህተቶች እንዳይወድቁ ሊያካፍሉ
የሚችሉት ምን ዓይነት ትምህርት ተማሩ?
አምላካዊውን ሕግ መጠበቅ ታላላቅ ጥቅሞች ማስገኘቱን አስመልክቶ እግዚአብሔር
ያበለጸጋቸውን ሕዝቦች እንደ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል። ኢያሱ የእግዚአብሔርን
መርኅዎች በቅርብ በመከተሉ የእስራኤልን ሕዝቦች በአግባቡ መምራት ቻለ። ሕጉን
ከታዘዙ ብልጽግና እንደሚያገኙ ጌታ በተደጋጋሚ ለእስራኤላውያን ነግሮአቸው
ነበር።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ዜና 31፡20-21። ሕዝቅያስ ብልጽግና እንዲያገኝ
መንስዔ የሆኑት ቁልፍ ምክንያቶች ምን ነበሩ?
የቱንም ዓይነት የትምህርት ጎዳና ላይ ብንሆንም ለመታዘዝ አስፈላጊነት ብርቱ
አጽንኦት ልንሰጥ ይገባል። ለነገሩ ተማሪዎቻችን አስተዋዮች በመሆናቸው አንዳንዶች
በታማኝነታቸው፣ በአፍቃሪነታቸውና በታዛዥነታቸው የተነሳ የተጋፈጡትን መራራ
እውነታ ውሎ አድሮ ይደርሱበታል። እሺ--ከዚያስ? ከዚያማ እነዚህ በጎ ሰዎችም
ውድመት ሊያደርስ የሚችል ሰቆቃ ሊገጥማቸው ይችላል። ለመሆኑ እንዴት
አድርገን ነው ይህን የምንገልጸው?
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህን መግለጽ አንችልም። በታላቁ ተጋድሎ እየተናጠች በምትገኝ
ኃጢአተኛና ክፉ ዓለም ውስጥ እየኖርን እንደመሆናችን አንዳችንም ከዚህ አስቸጋሪ
ቅጥር ውጪ አይደለንም።
የሚከተሉት ጥቅሶች ስለዚህ አስቸጋሪ ጥያቄ ምን ይነግሩናል? ማር.
6:25–27፣ ኢዮ. 1፣ 2፣ 2ቆሮ. 11:23–29።
ሕጉን የሚታዘዙ፣ መልካምና ታማኝ ሰዎች ቢያንስ ዓለም የሚያስተውለው ዓይነት
ብልጽግና ባለቤት አለመሆናቸው ብዙም አያጠያይቅም። ስለ ሕጉ አስፈላጊነት
ለማስተማር በምናደርገው ጥረት እንዲህ ያለው ጥያቄ ያለ ምንም ጥርጥር መነሳቱ
አይቀርም። ለመሆኑ ስኬት ወይም “ብልጽግና” ስንል ምን ማለታችን ነው? ይህን
አስመልክቶ ባለ መዝሙሩ ምን ይላል? “በክፉዎች ድንኳን ከመቀመጥ ይልቅ፤
በአምላኬ ቤት ደጅ መቆም እመርጣለሁ” (መዝ. 84፡10)። ለእግዚአብሔር ታማኝ
የሆኑትና ሕጉን የሚታዘዙ ሁሌም ቢሆን በዚህ ዓለም መስፈርት የተቀመጠው
“ብልጽግና” ባለቤት አለመሆናቸው እሙን ነው። ከዚህ ውጪ የምንናገር ከሆነ
በተማሪዎቻችን ላይ ጉዳት እናደርሳለን።
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዕብ. 11፡13-16። ታማኝ የሆኑ ዛሬ በምድራዊው
ህይወት የሥቃይ ገፈት የሚቀምሱበትን ምክንያት ማስተዋል እንድንችል
ጥቅሶቹ እንዴት ይረዱናል?
የሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ፤ አባቱን ፍጹም በመታዘዝ ብቸኛውን ሰብዓዊ ህይወት ኖረ፤ የእግዚአብሔርን ሕግ ፍጹም አድርጎ ጠበቀ። እርሱ ይህን ያደረገው የእኛ ቤዛ ለመሆን ብቻ ሳይሆን ምሳሌያችን መሆኑንም ለማሳየት ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 2:51-52፣ ፊልጵ. 2:8፣ ዕብ. 5:8፣ ዮሐ. 8:28-29። ክርስቶስ ህይወቱን ሙሉ ታዛዥ ሆኖ መኖሩን ጥቅሶቹ እንዴት ያስታውሱናል?
ምናልባት ዮሐንስ በዚህ ዙሪያ ስለ እርሱ የተናገረው እንደ ምርጥ አባባል ሊወሰድ
ይችላል፡ “ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ
ይገባዋል” (1ዮሐ. 2፡6)። ዐይኖቻችንን በክርስቶስ ህይወትና በምድር አገልግሎቱ ላይ
ስንተክል፤ በመታዘዙ ምን ያህል አብን እንዳስደሰተ ለመመልከት ብዙ አንቸገርም።
ክርስቶስ ትንቢቶችን ወደ ፍጻሜ አምጥቶአል፤ ህይወቱን ሙሉ አምላካዊውን
ሕግጋትም ጠብቆአል።
ሕጉ ለእስራኤላውያን ምስክር ይሆን ዘንድ ሙሴ አምላካዊውን ሕግ እንዲጽፍ
እግዚአብሔር እንደነገረው ሁሉ፤ በተመሳሳይ ክርስቶስ--ለሐዋርያት፣ ለኃጢአተኞችና
ለቅዱሳን ህያው ምሳሌና ምስክር ነበር። አሁን ግን ከሕግ ስብስብ ይልቅ እንከተለው
ዘንድ እነሆ ሰብዓዊ ሥጋና ደም የለበሰው የሱስ ምሳሌያችን አለን።
እንደ መምህራን፤ ከየሱስ እና እርሱ አብን እንዴት እንደታዘዘ ከሚያሳየው ምሳሌ
ሌላ ምን የተሻለ ነገር ለተማሪዎቻችን ማቅረብ እንችላለን?
“ሰዎች እግዚአብሔርን መታዘዝ ካለባቸው ግዴታ ነጻ የሚያደርግ እምነት ተብዬ-የእውነት መሰረት የሌለው እምነት ነው። ‘በእምነት በጸጋ ድናችኋልና’ ‘እንዲሁም
ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው’ (ኤፌ. 2፡8፣ ያዕ. 2፡17)። የሱስ ወደ ምድር
ከመምጣቱ አስቀድሞ ‘አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ ሕግህም በልቤ ውስጥ
አለ’ (መዝ. 40፡8) ሲል ስለ ራሱ ተናግሮ ነበር። ደግሞም ወደ ሰማይ ከመመለሱ
በፊት ‘የአባቴን ትእዛዝ’ ጠብቄአለሁ ሲል አወጀ (ዮሐ. 15፡10)። እላካዊው
ቃል እንዲህ ይላል ‘ትእዛዙን ብንፈጽም እርሱን ማወቃችንን በዚህ እርግጠኞች
እንሆናለን… ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ
ይገባዋል’ (1ዮሐ. 2፡3-6) —Ellen G. White, Steps to Christ, p. 61.
ለገዛ ራስዎ ህይወትም ሆነ ለሌሎች የተሻለ መምህር ይሆኑ ዘንድ የሱስን በሁሉም
የህይወትዎ ክፍል ምሳሌ አድርገው ለመከተል አብልጠው ሊያደርጉ የሚገባው ነገር
ምንድን ነው? ምንም እንኳ የተለመደ አባባል ቢሆንም--ድርጊታችን ከምንናገረው
በላይ መናገር የሚችለው ለምንድን ነው?
“የፍጥረትና የቤዛነት መሰረት የሆነው ፍቅር የእውነተኛ ሥነ
ትምህርት መሰረት ነው። ይህ እግዚአብሔር የሕይወት መመሪያ አድርጎ በሰጠን
ሕግ ግልጽ ሆኖ ቀርቦአል። የመጀመሪያውና ታላቁ ትእዛዝ እንዲህ ይላል፡ ‘ጌታ
አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ
ውደድ፤ ባልጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ (ሉቃ. 10፡27)። የማይወሰነውንና ሁሉን
የሚያውቀውን አምላክ በፍጹም ልብ፣ ነፍስ፣ ኀይልና ሐሳብ መውደድ ማለት
እያንዳንዱን ሰብዓዊ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማጎልበት ነው። የቀደመውን አምላካዊ
አምሳል--በአካል፣ በአእምሮ እንዲሁም በነፍስ ውስጥ ማኖር ነው።
“ሁለተኛውም ትእዛዝ የመጀመሪያውን ይመስላል--‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ
ውደድ’ (ማቴ. 22፡39)። የፍቅር ሕግ አካል፣ አእምሮ እና ነፍስ ለእግዚአብሔር እና
ለባልንጀራችን አገልግሎት እንዲሰጥ ጥሪ ያቀርባል። ይህ አገልግሎት እኛን ለሌሎች
በረከት ከማድረግ ባሻገር ለገዛ ራሳችንም ታላቅ በረከት ያስገኝልናል። ከራስ ወዳድነት
የጸዳ ስብእና የሁሉም እውነተኛ እድገትና ግስጋሴ መሰረት ነው። ስስት የማያውቀውን
አገልግሎት በመስጠታችን አካላችንን፣ አእምሮአችንንና ነፍሳችንን በከፍተኛ ደረጃ
እናበለጽጋለን። የመለኮታዊው ባህሪ ተጋሪነታችን እያደር በሙላት እያደገ ይሄዳል።
ሰማይን በልባችን በመቀበላችን እነሆ ለሰማይ ገጣሚዎች ሆነናል”—Ellen G.
White, Education, p. 16.
1.እንደ ጥንት እስራኤላውያን ሁሉ እኛም ዛሬ እግዚአብሔርን
እንወደዋለን፣ እንፈራውማለን (ማቴ. 22፡37፣ ራእ. 14፡7)። እነዚህን
ሁለቱን እንዴት በአንድ ጊዜ ማድረግ እንደምንችል ተወያዩ። ደግሞም
ይህን ጥያቄ መልሱ፡ እነዚህ ሁለት ትእዛዞች እርስ በርስ የማይጣረሱት
ለምንድን ነው?
2.ደረጃ ወይም መለኪያ በማስቀመጥና ደንብ በማውጣት መካከል
ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ከእርስዎ ተሞክሮ አኳያ ቤተ ክርስቲያንን
የሚያሳስባት በአማኝ ማኅበረሰብ መሃል ከፍ ያለውን ደረጃ ወይም ሥነ
ሥርዓት ማስቀመጥ ነው ወይስ በማኅበረሰቧ መሃል ህብረት ለመፍጠር
የሚያስችሉ ደንቦች ማውጣት?
3.የእግዚአብሔርን ሕግ መታዘዝ አስፈላጊ በመሆኑ እና በተመሳሳይ
ይኸው መታዘዛችንን ማሳየታችን የመዳናችን ምንጭ ባለመሆኑ መካከል
ያለውን ትክክለኛ ሚዛን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
4.መዝ. 119 ያንብቡ። በዚህ ምዕራፍ--መታዘዝ፣ ነጻነት፣ ሕጎች፣
ደንቦችና ትእዛዞች ምን ያህል ጊዜ እንደ ተጠቀሱ ልብ ይበሉ።
የመዝሙር 119 ጸሐፊ ሰለነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ሊያስተላልፍልን የፈለገው
መልእክት ምንድን ነው?