ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኤፌ. 1:1–4፣ ማቴ. 22:35–37፣ ማቴ. 7:24-25፣ ምሳ. 18:24፣ 1ቆሮ. 15:33፣ መክ. 2:1–11።
መታሰቢያ ጥቅስ:- “እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” (ኢያ. 24፡15)።
ህ
ይወት በምርጫ የተሞላች መሆኗን ሁሌም ልብ ይሉ ይሆን? ጠኋት
ከመኝታ ከተነሳን አንስቶ ተመልሰን እስክንተኛ ምርጫዎቻችንን ስናደርግ
ውለን እናመሻለን ብሎ ምናልባት አንድ ሰው ሊሞግት ይችላል። እንደውም ልብ
የማንላቸውን አያሌ ምርጫዎች እናደርጋለን።
አንዳንድ ምርጫዎች ቀላልና በዘልማድ የምናደርጋቸው ዓይነት ሲሆኑ ሌሎቹ
ደግሞ ህይወትን የሚለውጡና በእኛ ላይ ብቻ ሳይወሰኑ በቤተሰባችን ጭምር
ዘላለማዊ ውጤት ያላቸው ናቸው።
ነገሩ እንዲህ ከሆነ በምናደርጋቸው ምርጫዎች ላይ በጽሞና ማሰባችን ምን ይህል
ወሳኝ እንደሆነ ልብ ይሏል። በተለይ ደግሞ ትላልቅ ውሳኔ የሚጠይቁ ሆነው በቀረው
የህይወታችን ዘመንም ሆነ በቤተሰባችን ህይወት ላይ ብርቱ ተጽእኖ ሊፈጥሩ
የሚችሉ ሲሆኑ።
በአንድ ወቅት ባደረግነው ምርጫ ዛሬ ድረስ የምንጸጸት ስንቶቻችን ነን? ከብዙ
ጊዜ በፊትም ቢሆን ባደረግነው የተሳሳተ ምርጫ ዛሬ ድረስ ተጨብጠን የምንኖር
ስንቶቻችን ነን? ሆኖም የቱንም ዓይነት የከፋ ውሳኔ ብናሳልፍ እንደ መታደል ሆኖ-ይቅር መባል፣ መዋጀት፣ መፈወስ የሚባል ነገር አለ!
በዚህ ሣምንት በምርጫዎቻችን ዙሪያ ሊነሱ በሚችሉ ጥያቄዎች ላይ ሰፊ ምልከታ
እናደርጋለን። ምርጫ እንዴት ማድረግ እንዳለብን እንዲሁም ምርጫዎቻችን በእኛም
ሆነ በቤተሰቦቻችን ላይ ስለሚያሳድሯቸው ተጽእኖዎች ፍተሻ እናደርጋለን።
አንድ ሰው ገና ከመወለዱ አስቀድሞ መጻኢ ምድራዊ ህይወቱም ሆነ ከክርስቶስ
ዳግም ምጽአት በኋላ ያለው መዳኑ ወይም መጥፋቱ አስቀድሞ በእግዚአብሔር
ተወስኖ ያበቃለት ጉዳይ ነው ብለው አንዳንድ ክርስቲያኖች ያምናሉ። በመጨረሻ
ለዘላም የሚጠፋው ሰው እንዲጠፋ የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር በጥበቡ
(ይህ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ እንደሚለው) ግለሰቡ እንዲጠፋ ስለወሰነበት ወይም
ስለመረጠለት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ማለት ግለሰቡ የመምረጥ ነፃነት ቢኖረውም
አንዴ ተኮንኖአል።
እኛ እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነታችን እነሆ በጌታ እርዳታ
ከእንዲህ ዓይነቱ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ የተጠበቅን ነን። በዚህ ፋንታ ዓለም
ከመፈጠሩ አስቀድሞ የዘላለም ህይወት ባለቤቶች እንድንሆን በእርሱ የተመረጥንና
ሁላችንም እንድን ዘንድ የእግዚአብሔር ምርጫ መሆኑን እናምናለን።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 1፡1-4፣ ቲቶ. 1፡1-2፣ 2ጢሞቴ. 1፡8-9። ጥቅሶቹ
በእግዚአብሔር ስለ መመረጥና መቼ እንደተመረጥን ምን ይነግሩናል?
ይህ የምስራች የቱንም ያህል መልካም ሊሆን ቢችል አንዳንዶች መጥፋታቸው ግን
እውነት ነው (ማቴ. 25፡41)። ይህ የሆነበት ምክንያት ምንም እንኳ እግዚአብሔር
ሁላችንንም ቢመርጠንም እርሱ ለመላው ሰብዓዊ ዘር እጅግ የተቀደሰውን ስጦታ
ይኸውም የመምረጥ ነጻነትን በመስጠቱ ነው።
በማቴ. 22፡35-37 የምናገኘው ጥቅስ ስለ መምረጥ ነፃነት ምን ያስተምረናል?
ጌታ እንድንወደው የሚያስገድደን አምላክ አይደለም። ፍቅር፣ ፍቅር መሆን ይችል
ዘንድ በነፃ ሊሰጥ የግድ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ወደ ጠፋው ሰብዓዊ
ዘር በመድረስ ያለ አንዳች ማስገደድ የሰዎችን ልብ ወደ ራሱ ለማሸነፍ ያደረገውን
ብርቱ ጥረት የሚተርክ ሰነድ ነው ሲሉ አንዳንዶች ይሞግታሉ። ይህ እውነታ በየሱስ
ህይወትና አገልግሎት ምርጥ ሆኖ መታየት ችሎአል። ምክንያቱም ሰዎች የመምረጥ
ነፃነታቸውን ተጠቅመው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። የመረጡት ወደ እርሱ ሲሳቡ
ሌሎች በተቃራኒው ሞቱን ይሹ ነበር።
አዎ እግዚአብሔር እንድንድን የመረጠን ቢሆንም ነገር ግን በስተመጨረሻ
ይህን ደኅንነት ለመቀበል መምረጥ ይኖርብናል። ከምናደርገው ምርጫ ሁሉ ጌታን
ለማገልገል መምረጣችን በራሳችንም ሆነ ተጽእኖአችን በሚያርፍባቸው ወገኖች
(በቅርብ ቤተሰባችን) ላይ የሚያስከትለው ውጤት የትዬለሌ መሆኑ አንድና ሁለት
የለውም።
አንዱን ከሌላው የመምረጣችንን አስፈላጊነት ሁላችንም ጠንቅቀን እንረዳለን።
ደግሞም የተሳሳቱ ምርጫዎች የእኛንም ሆነ የሌሎችን ህይወት ምን ያህል አሉታዊ
በሆነ መልኩ ሊያመሳቅሉ እንደሚችሉ እንገነዘባለን። በመሆኑም ጥያቄው--ትክክለኛ
ምርጫ ማድረጋችንን እንዴት ማወቅ እንችላለን? የሚል ይሆናል።
ትክክለኛው ውሳኔ ላይ ለመድረስ በምናደርገው ጥረት የሚከተሉት ጥቅሶች
አጠቃላይ የአካሄድ ቅደም ተከተሎችን ይሰጡናል።
1. 1ተሰ. 5:17፣ ያዕ. 1:5
2. ኢሳ. 1:19፣ ማቴ. 7:24-25
3. መዝ. 119:105፣ 2ጢሞቴ. 3:16
4. ምሳ. 3:5-6፣ ኢሳ. 58:11
5. ምሳ. 15:22፣ 24:6
እያንዳንዱ አስፈላጊ ውሳኔ ላይ ከመድረሳችን አስቀድመን ወደ ጌታ የምንቀርብ ከሆነ
ምርጫችን በቃሉ ከቀረበው አምላካዊው ፈቃድ እና መርኅዎች ጋር ተቃርኖ ውስጥ
እንደማይከተን እርግጠኞች እንሆናለን።
በእግዚአብሔር ታምነን ምርጫዎቻችንን
ለእርሱ ማስገዛታችን በእጅጉ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ይህም ምርጫዎቻችን ለእርሱ
ክብር የሚሰጡ እንዲሆኑ በመጸለይ ምኞቶቻችን እርሱ ለእኛ ህይወት ካለው ዕቅድ
በተቃራኒ የሚጓዙ ከሆነ በእግሮቹ ስር ለማስገዛት ዝግጁ መሆን ነው። ብዙውን ጊዜ
እንደሚታወቀው ትክክለኛዎቹን ምርጫዎች ለማድረግ በሳል የምክር አገልግሎት
የሚሰጡ ባለሙያዎች ጋር መገናኘት ጉልህ ጠቀሜታ አለው። በመጨረሻ--በእምነትና
በትህትና ራሳችንን ዝቅ አድርገን ህይወታችንን ለእርሱ የምናስገዛ ከሆነ በምርጫችን
ወደፊት መራመድ እንችላለን። በዚህም እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚወደንና
ለእኛ ምርጥ የሆነውን አጥብቆ እንደሚሻ እንገነዘባለን።
በህይወትዎ የሚገጥሞትን ግዙፍ ምርጫዎች የሚያደርጉት እንዴት
ነው? ትክክለኛውን ምርጫ ለመምረጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ
መንፈሳዊ ቅደም ተከተሎችን ጥቅም ላይ ቢያውሉስ?
በእጅጉ ወሳኝ ሊሆኑ ከሚችሉ ምርጫዎቻችን አንዱና ዋንኛው ጓደኛን መምረጥ
ነው። ብዙውን ጊዜ ጓደኝነትን ለመመስረት ይሄ ነው የሚባል ምክንያት ወይም
ትክክለኛ መግለጫ አይኖረንም። ይልቁንም ባመዛኙ ጓደኝነት እኛ የምናደርጋቸውን
አንዳንድ ነገሮች ከሚጋሩን ወገኖች ጋር ያለን ተፈጥሮአዊ የግንኙነት ዕድገት ሲሆን
ይስተዋላል።
ጓደኛን በመምረጡ ረገድ በሚከተሉት ጥቅሶች ምን ዓይነት መርኅዎችን እናገኛለን?
ምሳ. 12:26፣ 17:17፣ 18:24፣ 22:24-25።
ጓደኛ እንዲኖረን የምንፈልግ እስከሆነ ድረስ ወዳጃዊ ስብዕና ሊኖረን የግድ
ነው ሲል ምሳ. 18፡24 ይነገረናል። ሰዎች አንዳንዴ ራሳቸውን በብቸኝነት ውስጥ
ሊያገኙት ቢችሉም የሚከፋና ግልፍተኛ ባህሪ ካላቸው ሌላው ሰው ይርቃቸዋል።
“ምርጥ የምንባል ሰዎች ሳንቀር እነዚህን የማይወደዱ ባህሪዎች የማናጣ ቢሆንም
ጓደኞችን ስንመርጥ እንከን የማያጣን መሆናችንን ሲመለከቱ ከእኛ ተገፍተው
የማይሄዱ ዓይነት ሊሆኑ ይገባል።
በሁሉም ወገን የጋራ ትዕግሥት አጥብቆ ሊኖር
የግድ ነው። ምንም እንኳ ለመታገስ የሚፈትኑ ጉድለቶች ሊኖሩ ቢችሉም አንዱ
ሌላውን ሊወድና ሊያከብር ይገባል--ምክንያቱም ይህ የማንም ሳይሆን የክርስቶስ
መንፈስ ነውና። ትህትናና መተማመን በእንክብካቤ ሊያዙ፣ ጉድለቶችም በትዕግሥት
ሊታለፉ ይገባል። እንዲህ ያለው አካሄድ ጠባቡን ራስ ወዳድነት ገድሎ የሆደ ሰፊና
ለጋስ ስብዕና ባለቤት ያደርጋል።”—Ellen G. White, Pastoral Ministry, p. 95.
በዳዊትና በዮናታን መሃል የነበረው ግንኙነት አብልጠው ከሚታወቁ የጓደኝነት
ታሪኮች አንዱ ነው። የእስራኤል የመጀመሪያው ንጉሥና የዮናታን አባት የነበረው
ሳኦል ታማኝና ታዛዥ ቢሆን ኖሮ መንግሥቱ ለአያሌ ዐሥርተ ዓመታት በዘለቀና
የዙፋኑ ተተኪ ወራሽም ልጁ ዮናታን በሆነ ነበር። ሳኦል የተጠራበትን ኃላፊነት
የማይመጥን ከንቱ መሆኑን ሲያስመሰክርና እግዚአብሔር ዳዊትን አዲሱ የእስራኤል
ንጉሥ አድርጎ ሲመርጠው ዮናታን ከሕጋዊ የዙፋን ወራሽነት መስመር ውጪ
ሆነ። የአንደኛው የቤተሰብ አባል (ሳኦል) የተሳሳተ ምርጫ ሌላኛው የቤተሰብ
አባል (ዮናታን) ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ የሚያሳየውን ብርቱ ምሳሌ በታሪኩ
እንመለከታለን።
ነገር ግን ዮናታን በዳዊት ላይ አልተበሳጨም ወይም አልተመቀኘውም ነበር።
ይልቁንም ዳዊትን ከገዛ አባቱ ቁጣ ለመከላከል መረጠ። “የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ
ጋር ተቆራኘች፤ እንደ ራሱም አድርጎ ወደደው” (1ሳሙ. 18፡1)። ታሪኩ የእውነተኛ
ጓደኝነት ብርቱ ምሳሌ ነው።
“አትሳሳቱ ‘መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል’” (1ቆሮ.
15፡33)። ባለኝ በጎ ነገር ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ተጽእኖ
ሊያደርሱ አይችሉም ብለው ቢያስቡም ነገር ግን ከዚያ ተቃራኒ የሆነ
አጋጣሚ የተከሰተበት ሁናቴ ሊኖር ከመቻሉ አኳያ ከገዛ ጓደኞችዎ
ጋር ያሎት ተሞክሮ ምን ይመስላል? የተሳሳቱ የጓደኝነት ምርጫዎች
በቤተሰባዊ ግንኙነት ላይ ጉዳት የሚያደርሱት እንዴት ነው?
ጓደኛ ሲመርጡ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ካለቦት የወደፊት የህይወት አጋርዎን
በዕጮኝነት ሲመርጡ ከዚያ የላቀ ጥንቃቄ ከእርስዎ ይጠበቃል። እግዚአብሔር
የአዳምን የህይወት ጓደኛ ከራሱ አካል ወስዶ ሲያበቃ በእጆቹ አበጃጅቶና ባርኮ
ሰጠው። በእርግጥ በወቅቱ በምድር ላይ የነበረችው እንስትና ፍጹም ሴት ሔዋን
ብቻ ከመሆኗ አኳያ ለአዳም ምርጫ ከባድ አልነበረም። ጉዳዩ ወዲህ ሲመጣ፤ እኛ
ፍጽምና የጎደለን ሆነን ከመገኘታችን በተጨማሪ የምንመርጠውም ከብዙ ሰዎች
መሃል መሆኑ ነገሩን አክብዶታል።
ይህ ውሳኔ እጅግ ወሳኝ ከመሆኑ አኳያ እግዚአብሔር በዚህ የህይወታችን ክፍል ያለ
ምሪት አልተወንም። አስፈላጊ የተባሉትን ቅደም ተከተሎች በሰኞው ትምህርታችን
ከመመልከታችን ጎን ለጎን ካጠቃላዩ የጋብቻ ጽንሰ ሃሳብ አኳያ በተጨማሪ
የምንመለከታቸው የተወሰኑ ነጥቦች ይኖራሉ (በስድስተኛው ትምህርት ከጋብቻ
ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን በሙሉ እንመለከታለን)። እርግጥ ነው--ከጌታ ቤት
ውጪ የሚደረግ የህይወት ጓደኛ ምርጫና ውሳኔ ውሎ አድሮ መዘዝ ማስከተሉና
ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ ነው።
የህይወት ጓደኛ ፍለጋ ላይ ላለ ሰው መተግበር የሚችል ምን ዓይነት ጠቅለል ያለ
ምሪት በሚከተሉት ጥቅሶች እናገኛለን? መዝ. 37:27, 119:97, 1ኛ ቆሮ. 15:33, ያዕቆብ
1:23–25.
ለጋብቻ ትክክለኛውን ሰው ከመፈለግ ጎን ለጎን በቅድሚያ እኛ ራሳችን ትክክለኛ
ሰው መሆን ይጠበቅብናል። “‘ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር
እናንተም አድርጉላቸው፤ ኦሪትም ነቢያትም በዚህ ይጠቃለላሉና’” (ማቴ. 7፡22)።
አንድ ሰው የሚፈልገውን ሁሉ የምታሟላ /የሚያሟላ ገራሚ የህይወት ጓደኛ ሊያገኝ
ቢችልም ነገር ግን መራጩ ያሉት መልካም ነገሮች በዚያኛው ሰው ዐይን የማይሞሉ
ሆነው ከተገኙ ሁነኛ ችግር መፈጠሩ አይቀሬ ነው።
ይህ እንደውም በትዳር ብቻ ሳይሆን በአጠቃላዩ የህይወት ፈርጅ ጭምር የሚታይ
እንደ መሆኑ አዲስ ነገር አይደለም። በሮሜ መጽሐፍ መግቢያ ላይ አንዳንዶች
ራሳቸው ጥፋተኞች በሆኑበት ነገር ሌሎችን ስለ መኮነናቸው ጳውሎስ ሰፋ ያለ
ጊዜ ወስዶ ሲናገር ይደመጣል። ወይም የሱስ እንዲህ ሲል የተናገረውን ልብ ይሏል
“‘በዐይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ ሳትመለከት፣ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ
ለምን ታያለህ?’ ”
እርስዎ ራስዎ ጉድለት እያለቦት የሌሎችን ባህሪ የመንቀፍ ችግር ምን
ያህል ይስተዋልቦታል? በጉዳዩ ያስቡበት።
ሙያን ወይም ሥራን አስመልክቶ በህይወታችን አንድ የሆነ ነጥብ ላይ ስንደርስ
ውስጣችን ወደሚያዘነብለው ዘርፍ ምርጫ ማድረጋችን የግድ ይሆናል። በሀብት
ራሳችንን ችለን የደረጀን ወይም ቤተሰባችንን በመንከባከብ ሙሉ ጊዜያችንን በቤት
ውስጥ የምናውል (እጅግ የከበረው ሥራ) ካልሆንን በቀር ብዙዎች ገቢ ሊያገኙ
የሚችሉበትን የሥራ ዘርፍ መምረጥ ይኖርባቸዋል።
ሥራን በተመለከተ እርግጥ ነው እኛ ሁላችንም ምርጫችንን በከፍተኛ መጠን
ሊገድብ በሚችል ዉሱን ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። ነገር ግን በየትኛውም ሁናቴ
ውስጥ ልንገኝ ብንችልም፣ በተለይ ለህይወታችን ተጨማሪ ትርጉምና ዓላማ መስጠት
በሚችለው በየሱስ ክርስቶስ ደኅንነት ማግኘታችንን የምናስተውል ከሆነ ሥራችንን
መምረጥ እንችላለን። በአጭሩ--ምንም ዓይነት ሥራ ብንሠራ ለእግዚአብሔር ክብር
ልናውለው እንችላለን።
የሰሎሞን ስህተት ምን ነበር? እኛም ተመሳሳይ ስህተት እንዳንሠራ እንዴት መጠንቀቅ
እንችላለን? (መክ. 2፡1-11)።
ሰሎሞን በተያዘበት ተመሳሳይ ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ አፍቅሮተ ንዋይ
ጠምዝዞ ምርኮኛው እንዳያደርገን መጠንቀቅ ይኖርብናል። “ምክንያቱም የገንዘብ
ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው፤ አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጉጉት የተነሣ
ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል” (1ጢሞቴ.
6፡10)። ባለ ሀብት ሆኖ ገንዘብ ከሚወደው ሰው በተመሳሳይ ድኻ ሆኖ ብርቱ
የገንዘብ ፍቅር ያለውም አለ።
እርግጥ ነው--ለመተዳደሪያ የሚሆን የገቢ ምንጭ ያስፈልገናል። ነገር ግን
በየትኛውም ዓይነት የሥራ መስክ ብንሰማራና ገቢ ሊኖረን ቢችል፤ ሀብትን እንደ
ጣኦት ልናመልክና ልናሳድድ አይገባም። አባት ነጋ ጠባ የሚያሰላስለው ስለ
ተጨማሪ ገቢና ገንዘብ ብቻ በሆነባቸው ቤቶች የቤተሰብ አባላት አባወራውን እንደ
ልቡ ለማግኘት ስለሚቸገር ውሎ አድሮ ቸል የመባልና የመተው ስሜት ይመጣል።
ድሃ ውሃውን ጠጥቶ እሳቱን ይሞቃል ሐብታም ግን ስለ ገንዘቡ ይጨነቃል እንዲሉየሕይወት ምዕራፎች
-ምናለ እጥር ምጥን ያለ ኑሮ እየኖርን ከአባታችን ጋር እንደልባችን ቦርቀን ባደግን
የሚሉ ልጆች ወይም ሚስቶች መኖራቸው እሙን ነው።
ሥራ ገና ከፍጥረት አንስቶ የሰብዓዊው የህይወት አካል እንዲሆን የእግዚአብሔር
እቅድ ነበር (ዘፍ. 2፡15)። ሆኖም ሥራችንን እንደ ህይወታችን ፈርጥ አድርገን
መቁጠር ስንጀምር አደጋ መከሰቱ አይቀሬ ይሆናል። ይህ ሰሎሞን የሠራው ስህተት
ነው። እርሱ በአብዛኞቹ የሥራ ዕቅዶቹ ትርጉም ያለው ነገር ለማግኘት ፍለጋ አድርጎ
የነበረና እንደውም ከነዚያ ውስጥ ከፍ ያለ ቁጥር የነበራቸው የተወሰነ እርካታ
አምጥተውለት የነበረ ቢሆንም፤ ሆኖም በመጨረሻ የተገነዘበው ሁሉም ትርጉም
የለሽና ከንቱ መሆኑን ነበር።
“ሰዎች አብዛኛውን የህይወታቸውን ዘመን ለቢሮአቸው ከዚያ ያነሰውን
ግን ለቤታቸው ማዋላቸውን በመጨረሻ የሚገነዘቡ ስንት ሰዎች
ናቸው?” ሲል አንድ ጸሐፊ ይጠይቃል። አባባሉ የያዘው ጠቃሚ
መልእክት ምን ይመስላል?
የሰብዓዊውን የመምረጥ ነፃነት ተጨባጭ እውነታ በሁሉም
የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች እንመለከታለን። በኃጢአት ያልወደቁት አዳምና ሔዋንም
(ዘፍ. 3) ተመሳሳይ የመምረጥ ነፃነት የነበራቸው ቢሆንም፤ በሚያሳዝን መልኩ
ይህንን ነፃነታቸውን ለተሳሳተ ምርጫ አዋሉት። እነዚያ በፍጽምና ይኖሩ የነበሩ
በኃጢአት ያልወደቁ ፍጡራን እጃቸው ላይ የነበረውን ነፃነት በተሳሳተ መንገድ
ጥቅም ላይ ካዋሉ፤ እኛ በመተላለፍ አዘቅት የወደቅን ይህን ልዩ መብትና ጥቅም ምን
ያህል በተሳሳተ መንገድ እናውለው ይሆን?
የመምረጥ ነፃነት ስንል ምንም ዓይነት ገደብ አለመኖሩን ልብ ይሏል። በእርግጥ
ከውስጥም ሆነ ከውጭ ተጽእኖ ቢኖርብንም ነገር ግን የተሳሳተውን መምረጥ
አይጠበቅብንም። ጌታ የሰጠንን የመምረጥ ነፃነት ተጠቅመን በእኛ ውስጥ
በሚኖረው በእግዚአብሔር ኃይል ትክክለኛውን ምርጫ መምረጥ እንችላለን።
በተለይ ውሳኔዎቻችን ከእኛ አልፎ ምን ያህል በቤተሰባችን ህይወት ላይ ተጽእኖ
ሊኖራቸው እንደሚችል ስናስብ፤ ምርጫችንን ደግመን ደጋግመን በጥንቃቄ ማጤን
በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ መመልከት እንችላለን። ቃየን የመምረጥ ነፃነቱን ተጠቅሞ
የወንድሙን ህይወት መቅጠፉ በቤተሰቡ ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ውድመት
ለመገመት አይከብድም። የዮሴፍ ወንድሞች የመምረጥ ነፃነታቸውን ተጠቅመው
የገዛ ወንድማቸውን በባርነት መሸጣቸው የአባታቸውን ልብ ሰበረ፣ ህይወቱንም
ክፉኛ አመሳቀለ። “እርሱም ልብሱን ዐውቆት፣ ‘ይህማ የልጄ እጀ ጠባብ ነው፤ ክፉ
አውሬ በልቶታል፣ በእርግጥም ዮሴፍ ተቦጫጭቆአል’ አለ።
ከዚህ በኋላ ያዕቆብ
ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለብሶ ስለ ልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ፤ ወንድሞቹና ሴቶች ልጆቹም
ሁሉ ሊያጽናኑት መጡ፤ እርሱ ግን ሊጽናና ባለመቻሉ ‘በሐዘን እንደ ተቆራመድኩ
ልጄ ወዳለበት መቃብር እውርዳለሁ’ አለ። ሰለ ልጁም አለቀሰ።” (ዘፍ. 37፡33-35)
ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን ምርጫ እንዳደረጉ ሁሉ (ዘኁ. 16፡1-32፣ ዳን. 6፡23-24፣
ዘፍ. 18፡19) የቤተሰብ አባላት የመምረጥ ነፃነት ለመልካምም ሆነ ለክፉ በሌሎች
ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ስለ መሆኑ በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች መመልከት
እንችላለን።
1.የመምረጥ ነፃነትዎን ተጠቅመው ዛሬ ካሳለፏቸው ውሳኔዎች መሃል
አንዳንዶቹ ምን ይመስላሉ? ስለ ራስዎ እና ከእግዚአብሔርም ሆነ ከሌሎች
ጋር ስላሎት ግንኙነት ምን ይነግሮታል? ከምርጫዎ መሃል ለመወሰን
አስቸጋሪ የሆነብዎ የትኛው ነበር?
2.ከመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ባህሪያት መካከል የተሳሳተ ምርጫ ያደረጉ የትኞቹ
ነበሩ--ከስህተታቸው ምን መማር እንችላለን? የተሳሳቱ ምርጫዎቻቸው
በምን መልኩ ነበር በቤተሰቦቻቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖዎች ያሳደሩት?
3.መቼም ሁላችንም ብንሆን በሠራናቸው ስህተቶች መጸጸታችን
አያጠያይቅም። በእነዚህ የጸጸት ጊዜያቶች ወንጌል መልካም የምሥራች
የሆነው ለምንድን ነው? የተሳሳቱ ምርጫዎች በሚያመጧቸው በእንደነዚህ
ዓይነቶቹ የሐዘንና የጸጸት ጊዜያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች መሃል ወደ
አእምሮዎ የሚመጡት የትኞቹ ናቸው?
4.ሰዎች ወደ እርስዎ ቀርበው ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ሊያወሮት ቢሞክሩ
ምን ዓይነት ምክረ ሃሳብ ሊሰጧቸው ይችላሉ? ለምን? በእጅጉ አስፈላጊ
ውሳኔ በሚጠይቀው በዚህ ጉዳይ ውጤታማ መሆን ይችሉ ዘንድ
ከእግዚአብሔር ቃል የትኞቹን መርኅዎች ሊያመላክቷቸው ይችላሉ?