የሕይወት ምዕራፎች
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከሚያዝያ 5-11

3ኛ ትምህርት

Apr 13 - Apr 19




ለለውጥ መዘጋጀት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 2፡8-11፣ 3:7–11፣ 2:12–17፣ 14:12፣ 2:18–29፣ 3:1–6፣ 3:14–22፣ ኢሳ. 61:10።


መታሰቢያ ጥቅስ:- “ጻድቅ በፊቴ ይሄዳል፤ ለአረማመዱም መንገድ ያዘጋጃል” (መዝ. 85፡13)።

ሕ ይወት በለውጦች የተሞላች ናት። ነገሮች ሁሌም ተለዋዋጭ ገጽታ አላቸው። በብቸኝነት የማይለዋወጥ ነገር ቢኖር ራሱ ለውጥ ብቻ ነው። በእርግጥ ለውጥ የህልውናችን አንዱ አካል ነው። ለውጥ የአንድ ተጨባጭ መዋቅር አካል ሆኖ መከሰት እንደሚችል የሚጠቁም አስተምህሮ የፊዚክስ ሕግ ሳይቀር ያለው ይመስላል።

ብዙውን ጊዜ ለውጥ ሳይታሰብ ከተፍ ይላል። በተለመደው አካሄድ እየተመላለስን እያለ ነገሮች በድንገት ተለዋውጠው ራሳችንን ፍጹም ባልተለመደ ሁናቴ ውስጥ ልናገኘው እንችላለን።

በሌላ በኩል አንዳንዴ ለውጥ እየመጣ እንደሆነ የምንመለከትበት ሁናቴ--ይኸውም ነገሮች የተለየ ገጽታ ሊኖራቸው እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጡና ሊመጡ ያሉትን ነገሮች የሚጠቁሙ ምልክቶች ይኖራሉ። ይህ ሲሆን ሊመጣ እንደሆነ እየተመለከትነው ላለ ነገር አነሰም በዛም ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ መጀመር ብልህነት ነው።ከእነዚህ ለውጦች መሃል አብዛኞቹ ግዙፍ የሚባሉ ዓይነት ሲሆኑ እንደ ጋብቻ መመስረት፣ ልጅ መውለድ፣ በዕድሜ መግፋት እንዲሁም ሞት በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው።

እርግጥ ነው ሁላችንም ብንሆን ከሰው ተነጥለን ስለማንኖር፤ የሚመጡት ለውጦች ተጽእኖ በእኛ ብቻ ሳይወሰኑ እስከ ቤተሰባችን የሚዘልቁና ምናልባትም እነርሱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚነኩበት አጋጣሚ ይኖራል። በተመሳሳይ በቤተሰባችን መሃል የሚከሰቱ ለውጦች በእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ላይ ተጽእኖ የሚኖራቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ሣምንት ጥናታችን ብዙም ሳይቆይ ወይም ዘግየት ብሎ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ አብዛኞቻችን ልንጋፈጥ በምንችላቸው ለውጦች ዙሪያ ምልከታ የምናደርግ ሲሆን፤ እነዚህ ለውጦች ምን ያህል በህይወታችን ላይ ተጽእኖ ሊኖራቸው እንደሚችልም ቅኝት እናደርጋለን።

ሚያዝያ 6
Apr 14

ያልተጠበቀ


በአምላካዊው ቃል ዙሪያ አንድ ሊዘነጋ የማይገባ ነጥብ ያለ ሲሆን ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ የሰብዓዊውን ህይወት ተጨባጭ እውነታ ሸፋፍኖ የማያልፍ መሆኑ ነው። በተቃራኒው ገር ያልሆነውንና ያልለዘበውን፣ ስስነቱን፣ አናዳጅነቱን ብሎም ተስፋ ቢስነቱን ሳይሸሽግ ይገልጣል።

በእርግጥ በተለየ ከቀረቡት የመጀመሪያዎቹና የመጨረሻዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ገጾች ውጪ የምናገኘው የእግዚአብሔር ቃል የሰብአዊውን ዘር አሳዛኝ ገጽታ በጉልህ ያሳያል። ጳውሎስ “ሁሉም ኃጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” (ሮሜ. 3፡22) ብሎ ሲጽፍ እያጋነነ አልነበረም።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 10፡1-13። ምን ዓይነት ማስጠንቀቂያዎች እንዲሁም የተስፋ ቃሎች ቀርበዋል?



ከህይወት እርምጃዎቻችን አብዛኞቹ ለለውጥ በምንሰጣቸው ምላሾች ዙሪያ ያጠነጥናሉ። ለውጦችን አዘውትረን መጋፈጣችን ያለ ቢሆንም፤ እንደ ክርስቲያን የለውጥ ተግዳሮቶችን በእግዚአብሔር ታምነንና ፈተናም ቢኖር--እምነታችንን በመታዘዝ እየገለጥን ጉዳዩን ከእምነት አኳያ ልንመረምርና ከዚያ አግባብ ልናይ የተገባ ነው።

“ዓለም በእጅጉ የጎደለውና የሚያሻው ነገር ቢኖር ሰዎች ናቸው--የማይገዙ ወይም የማይሸጡ ሰዎች፣ በውስጠኛው ነፍሳቸው እውነተኞችና ታማኞች፣ ኃጢአትን በትክክለኛ ስሙ ለመጥራት የማይፈሩ፣ ለተጠሩበት ሐቅ የማያወላዳ ኅሊና ያላቸው፣ ሰማይ ቢደፋ--ለእውነት ጸንተው ከመቆም ፍንክች የማይሉ ሰዎች--ዓለም አጥብቆ ያስፈልገዋል”—Ellen G. White, Education, p. 57. እነዚህ ቃላት ለጥንት እስራኤላውያን፣ ለኤለን ጂ. ኋይት ትውልድም ሆነ ለእኛ ዘመን እነሆ ገጣሚ ናቸው። ከዚህ በታች በቀረቡት ጥቅሶች እንደ ተመለከተው ሰዎች ከለውጥ ጋር በተጋፈጡበት ወቅት የሠሯቸው ስህተቶች ምን ነበሩ? እኛስ ከእነርሱ ስህተቶች ምን እንማራለን? ሐዋ. 5:1–10



ዘፍ. 16:1-2፣ 5-6



ማቴ. 20:20–22



ለውጥ--ብዙውን ጊዜ ፈተና እና ተግዳሮት አልፎ አልፎም ስጋት ይዞ ይመጣል። ነገሩ እንዲህ ከሆነ መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችንን ታጥቀን ጉዳዩን ባግባቡ መጋፈጥ ወሳኝ ይሆናል። ለውጦቹ ያልተጠበቁ ወይም የተለመዱ የህይወት አካል ሊሆኑ ቢችሉም እንኳ--ሊመጣ ላለው የሚታይም ሆነ የማይታይ ነገር ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ነው።

ሚያዝያ 7
Apr 15

ለጋብቻ የሚደረግ ዝግጅት


አንድ ሰው በህይወቱ ብርቱ ለውጥ ከሚመለከትባቸው ክስተቶች አንዱ ጋብቻ ነው። በእርግጥ ሁሉም ሰው ትዳር መስርቶ አይኖርም። ለነገሩ ታላቁ ምሳሌያችን የሆነው የሱስን ጨምሮ አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ባህሪያት በትዳር ደጃፍ አላለፉም። የሆነው ሆኖ ብዙ ሰዎች ማግባታቸውን ተከትሎ መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ከሚያስከትሉ አንዱ ስለ ሆነው ትዳር ሳይናገር ማለፍ አልመረጠም። በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰው ቀዳሚ ማኅበረሰባዊ አደረጃጀት ጋብቻ ነው።

ጋብቻ ለእግዚአብሔር እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ፈጣሪ በኤድን የአትክልት ስፍራ ለአዳምና ሔዋን ስለ ጋብቻ የተናገራቸው ቃላት በሌሎች ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በድጋሚ ተጠቅሰዋል። “ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” (ዘፍ. 2፡24፣ ማቴ. 19፡5፣ ማር. 10፡7፣ ኤፌ. 5፡31)። ጥንዶች አንዴ ወደ ጋብቻ ከገቡ በኋላ እንደ ባልና ሚስት-ከወላጆቻቸው ሳይቀር በላቀ አኳኋን በህይወታቸው እጅግ ልዩና ወሳኝ ግንኙነት እንደሚኖራቸው ጥቅሶቹ ይነግሩናል። በወንድ እና በሴት መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ አስፈላጊ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ--ጥምረቱ የእግዚአብሔር አብ ልጅ በሆነው በየሱስና ሙሽራው በሆነችው ቤተ ክርስቲያን መካከል ላለው ግንኙነት ምሳሌ በመሆኑ ነው። (ኤፌ. 5፡32)። አንድ ሰው ቤት መሥራት ከመጀመሩ አስቀድሞ ቆም ብሎ ወጪውን ማስላቱ የግድ (ሉቃ. 14፡28-30) እንደሆነ ሁሉ፤ ቤት የሚመሠርተው ምን ያህል ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበት ይሆን? የቤት ግንባታ ለማካሄድ እንደ አሸዋ፣ ሲሚንቶ፣ ድንጋይ፣ ብረት፣ ብሎኬት፣ እንጨት ወዘተ ማስፈለጋቸው ሲሆን፤ ቤት ለመመስረት ግን የግድ እነዚህ ቁሳቁሶች መኖር አይጠበቅባቸውም።

ለሁሉም የሕይወት ገጽታዎች ወሳኝ የምንላቸው ባህሪያት የትኞቹ ናቸው--በተለይ ደግሞ ለጋብቻ በሚደረግ ዝግጅት? 1ቆሮ. 13፡4-8፣ ገላ. 22፡-23።



ለጋብቻ የሚደረግ ዝግጅት እንደ ግለሰብ በግል ሊጀምር የግድ ይሆናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የነገ የትዳር ተጓዳኛችንን ለእኛ ተመጣጣኝ መሆን በጥንቃቄ ልንመለከት ይገባል።

ጠንካራ ሠራተኛ ነው/ናት? (ምሳ. 24፡30-34)፣ ምን ያህል ትዕግሥተኛ ነው/ናት? (ምሳ. 22፡24)፣ አንድ ዓይነት እምነት (ኃይማኖት) እንጋራለን? (2ቆሮ. 6፡14-15)፣ ስለ ወደፊት የትዳር ጓደኛዬ ቤተሰቦቼ ወይም ጓደኞቼ ምን ሊሰማቸው ይችላል? (ምሳ. 11፡14)፣ ምርጫዬ በእምነት ላይ ወይስ በስሜት ላይ የተመሰረተ ነው? (ምሳ. 3፡5-6)--ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጣቸው መልሶች የወደፊቱን የትዳር ህይወት ደስታ ወይም ኀዘን ከወዲሁ ሊናገሩ ይችላሉ።

ስለሚያውቋቸው አንዳንድ መልካም ትዳሮች አሰብ ያድርጉ። ትስስሮቹ ለትዳር ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ሰብዓዊ መስተጋብሮች መዋል የሚችሉ ምን ዓይነት መርኅዎችን ይዘዋል?

ሚያዝያ 8
Apr 16

ወላጅ ለመሆን የሚደረግ ዝግጅት


ልጅ ከማግኘት በበለጠ ጥቂት ነገሮች ህይወታችንን መለወጥ ይችላሉ። በቤተሰብ ውስጥ ሳይለወጥ እንዳለ የሚቀር ምንም ነገር የለም። “በወጣትነት የተገኙ ወንዶች ልጆች፣ በጦረኛ እጅ እንዳሉ ፍላጻዎች ናቸው። ኮረጆዎቹ በእነዚህ የተሞሉ፣ የተባረከ ሰው ነው” (መዝ. 127፡4-5)። በተመሳሳይ ልጆች እንደተወለዱ ወላጆች እንዴት ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገውና ማንኛውንም ሊፈጠር የሚችል ችግር ፈትተው ማሳደግ እንዳለባቸው የሚመራ የባለቤትነት አነስተኛ መጽሐፍ ወይም ማንዋል አብሮ እጃቸው አይገባም።

በመሆኑም አልፎ አልፎ ልምድ ያላቸው ወላጆችም እንኳ ቢሆኑ በልጆቻቸው ድርጊቶች፣ በሚናገሯቸው ቃላት ወይም በሚያሳዩት ጠባይ ግራ መጋባታቸው አይቀሬ ነው። ከጋብቻ በፊት ተገቢውን ጥናትና ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ የሆነውን ያህል ወላጅ ለመሆን ተስፋ የሚያደርጉ ጥንዶችም ለዚያ ታላቅ ኃላፊነት ከወዲሁ ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል።

ከዚህ በመቀጠል የቀረቡት ልጅ ከማግኘት ጋር የተያያዙ ታሪኮች የቱንም ያህል ያልተለመዱ ቢሆኑም፤ ወላጅ ለመሆን ዝግጅት እያደረጉ ያሉ ባልና ሚስት ከነዚህ መርኅዎች የትኞቹን መቅሰም ይችላሉ? 1ሳሙ. 1:27፣ መሳፍ.13:7፣ ሉቃ. 1:6፣ 13–17፣ 39–45፣ 46–55፣ 76–79።



እነዚህ ወላጆች እንዴት ያለ ግሩም ኃላፊነትና መልካም ዕድል ባለቤቶች እንደነበሩ ልብ ይሏል። በጥቅሶቹ እንደ ተመለከተው እነዚህ ሦስት ጥንድ ወላጆች ካፈሯቸው ልጆች መሃል የእስራኤል ነብያትና መሪዎች፣ የመሲህን መንገድ ጠራጊ እና ክርስቶስን እናገኛለን።

ምንም እንኳ የልጆቻችን መጨረሻ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሱት ነቢያት ባይሆንም ወላጆች ህይወታቸውን ሙሉ ለዚህ ስር ነቀል ለውጥ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። “ልጅ ከመወለዱ አስቀድሞ ውሎ አድሮ ህፃኑ ከክፉው ጋር በሚኖረው ውጊያ በስኬት እንዲወጣ የሚያስችለው ዓይነት ዝግጅት ሊደረግ ይገባል።

“እናት ከወሊድ አስቀድሞ ባሉት ጊዜያት ልል ስብዕና የሚስተዋልባት፣ ስስታም፣ ትዕግሥት የለሽና ጥንቁቅነት የሚጎድላት ከሆነች እነዚህ አጉል ባህሪያት በሽሉ ተፈጥሮ ላይ መንጸባረቃቸው አይቀርም። በዚህ የተነሳ በአዎንታዊው አካሄድ ብዙ ልጆች ለክፉው የማይሸነፈውን ዝንባሌ በቅርስነት ተቀብለዋል።”—Ellen G. White, The Adventist Home, p. 256. ጥንቃቄያችንን በሚሹ ህፃናትም በሌሎች ላይ ባለን ኃላፊነት እነዚህን ኃላፊነቶች ለመከወን ልናደርጋቸው የምንችላቸው በጎ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሚያዝያ 9
Apr 17

ለእርጅና ዘመን መዘጋጀት


“የዕድሜአችን ዘመን ሰባ ዓመት፣ ቢበዛም ሰማንያ ነው፤ ከዚያ በላይ ከሆነም ድካምና መከራ ብቻ ነው፤ ቶሎ ያልፋልና፤ እኛም ወዲያው እንነጉዳለን።” (መዝ. 90፡10)። እነዚህ በሙሴ የተነገሩ ቃላት የጊዜን አይበገሬ ገስጋሽነት ያስታውሱናል።

ዓመታት በመጡና በሄዱ ቁጥር በገዛ አካላችን ላይ ለውጦችና ስሜቶች እናያለን። ጸጉራችን መሸበት ወይም መነቃቀል ይጀምራል። አረማመዳችን ዝግ ይላል። ህመምና ድካም የዕለት ከዕለት ባልንጀሮቻችን ይሆናሉ። ያገባንና ልጆች ያሉን ከሆንን፣ ልጆቻችን የገዛ ልጆቻቸውን ይዘው ይመጡና በልጅ ልጆቻችን ሔሰት ማድረግ እንጀምራለን። የቀደሙት የህይወት ዘመኖቻችን ለመጨረሻዎቹ መዘጋጀት እንድንችል ብርቱ ድጋፍ ይሆኑናል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 71። ለእርጅና ዘመናችን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በአጠቃላይ በህይወታችን ማድረግ ስለሚኖርብን ዝግጅት ጥቅሶቹ ምን ያስተምሩናል?



የሽማግሌ ጸሎት በሚል ርዕስ የቀረበው ይህ ምዕራፍ (መዝ. 71) አንዳንዶች በህይወታቸው ሊገጥሟቸው የሚችሉትን ተግዳሮቶች ቢያመላክትም ነገር ግን መታመናቸውን በእግዚአብሔር ላይ እስካደረጉ ድረስ ደስተኛ መሆናቸውን ያረጋግጣል። አንድ ሰው በወጣትነት ዘመኑ በእግዚአብሔር የሚታመን ከሆነ ከሸመገለ በኋላ ነገሮች መልካም ገጽታ ይኖራቸዋል። ነገሩን ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው የዚህ ምዕራፍ ጸሐፊ ወደ ሽምግልና የህይወቱ ምዕራፍ በሚኖረው ጉዞ የተማራቸውን ሦስት አስፈላጊ ትምህርቶች ለአንባቢው ሲያካፍል ይስተዋላል።

1.እግዚአብሔርን በግል ጠለቅ ብሎ የማወቅ ፍላጎት ማሳደግ። ከወጣትነት ዘመኑ አንስቶ እግዚአብሔር ብርቱ መሸሸጊያው (መዝ. 71-1፣ 7) እና አዳኙ ነበር (መዝ. 71፡2)። እግዚአብሔር መጠጊያ ዐለቱ (መዝ. 71፡3) ተስፋውና መታመኛው ነው (መዝ. 71፡5)። የእግዚአብሔርን ብርቱና ድንቅ ሥራ (መዝ. 71፡1617)፣ ክንዱንና ኃያልነቱን (71፡18) እንዲሁም ያደረጋቸውን ታላላቅ ነገሮች ያውጅና (71፡19) በመጨረሻ “አምላክ ሆይ፤ እንዳንተ ያለ ማነው?” ሲል ይጮኻል።

2.መልካም ልምዶችን ማጎልበት። ንጹህና የተመጣጠነ ምግብ፣ ውሃ፣ የጸሐይ ብርሃን፣ ዕረፍት የመሳሰሉት ረጅም ዕድሜ ከመልካም ጤንነት ጋር እንዲኖረን ያስችሉናል። ባለ መዝሙሩ የመታመን (መዝ. 71፡3)፣ የምስጋና (71፡6)፣ እና የተስፋ (መዝ. 71፡14) ልምዶቹን ሲጠቅስ እንደሚስተዋል ሁሉ እርስዎም የተለየ ግንዛቤ ይኑርዎ።

3.ለአምላካዊው ተልዕኮ ጥልቅ ስሜት ማዳበር። በመዝሙረ ዳዊት የቀረበው ሰው በእርጅና ዘመኑ እጆቹን አጣጥፎ የመቀመጥ ፍላጎት አይታይበትም። በጡረታ ዘመኑም ለእግዚአብሔር ምስጋና እያቀረበና (መዝ. 71፡8) ስለ እርሱ ለሌሎች እየነገረ መቀጠል ፍላጎቱ ነበር (መዝ. 71፡15-18)። በሽምግልና ዕድሜ ላሉ--የሽምግልና ዕድሜ አንዳንዶቹ ጥቅሞች ምንድን ናቸው? በወጣትነት ዘመንዎ የማያውቋቸው አሁን ግን የሚያውቋቸው-ለወጣቶች የሚያካፍሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሚያዝያ 10
Apr 18

ለአይቀሬው ሞት መዘጋጀት


በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ወቅት በህይወት ካልተገኘን በቀር ይህ ከለውጦች ሁሉ የገዘፈ ለውጥ በሁላችንም ገቢራዊ ይሆናል ብለን መጠበቃችን እውነትነት አለው። ከጋብቻ እና ልጅ ከመውለድ በተጓዳኝ በቤተሰብ መሃል ሊከሰት ከሚችል የተወዳጅ ህልፈተ ህይወት የላቀ ብርቱ ተጽእኖ ሊኖረው የሚችል ለውጥ ምን ሊሆን ይችላል? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 15፡24-26። ጥቅሶቹ ስለ ሞት ምን ያስተምሩናል?



በእርግጥ ብዙውን ጊዜ ሞት ባልታሰበና አሳዛኝ በሆነ ሁናቴ ይከሰታል። ሲመሽ ዐይኖቻቸውን ከድነው የጠኋቱን ብርሃን ሳያዩ በዚያው እንዳሸለቡ የቀሩ ስንት ወንዶች፣ ሴቶች እንዲሁም ህፃናት ይሆኑ? ወይም ጠኋት ነቅተው ሲያበቁ ጸሐይ ከመግባቷ አስቀድሞ ተወዳጅ ቤተሰቦቻቸውን ዳግም ላያገኙ ያሸለቡስ? አንድ ሰው ከጌታ ጋር በእምነት ከመተሳሰርና በየጊዜው በጽድቁ ተሸፍኖ ከመመላለስ ውጪ (ሮሜ 3፡22) ሲመጣ ሊያየው ለማይችለው ሞት እራሱንም ሆነ ሌሎች ተወዳጅ የቤተሰብ አባላትን ማዘጋጀት አይችልም።

በሌላ በኩል እርስዎ ከዚህ በኋላ የሚኖርዎት የጥቂት ወራት ዕድሜ ብቻ መሆኑን ቢያውቁ ምን ያደርጉ ነበር? ለነገሩ ሞት የሚመጣበትን ጊዜ በእርግጠኝነት መተንበይ ባንችልም ነገር ግን ወደ ህይወታችን መጨረሻ ስንቃረብ ልናውቅ እንችላለን። ለዚህ አይቀሬ ቁርጠኛ ወቅት ራሳችንንም ሆነ የቤተሰብ አባላትን ማዘጋጀት በእጅጉ ወሳኝ ይሆናል።

ንጉሥ ዳዊት ለልጁ ለሰሎሞን የተናገራቸውን አንዳንድ የመጨረሻ ቃላት ይመልከቱ፡ 1ነገሥ. 2፡1-4። ለሞት መዘጋጀትን አስመልክቶ ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰብ አባላቶቻችን ከዚህ ምን ዓይነት ትምህርቶች መውሰድ እንችላለን?



ምናልባት አንባቢው ምክረ ሀሳቡን ሲመለከት ይህ በኦርዮን ሚስት ላይ ዝሙት ፈጽሞና አስረግዞ ሲያበቃ ይባስ ብሎ ባሏን ያስገደለ (2ሳሙ. 11) ሰው ልጁ በቀናው የጌታ መንገድ እንዲሄድ ይነግራል? ብሎ ሊያስብ ይችላል። ምናልባት ዳዊት የተናገራቸው ቃላት ጠጣር የሆኑበት ምክንያት ይህን ኃጢአትና ይዞ የመጣውን አስከፊ ውጤት ከግምት በማስገባት ሊሆን ይችላል። ልቡ ክፉኛ እንዲሰበርና ሐዘኑ እንዲበረታ ካደረገበት ከንቱ ስህተት በራሱ መንገድ የገዛ ልጁን እያስጠነቀቀ እንደ ነበር እርግጥ ነው። ኃጢአት የሚያስከፍላቸውን አንዳንድ ብርቱ ዋጋዎች ለመክፈልና ከዚያ ለመማር የተገደደው ዳዊት እርሱ ካለፈባቸው አስከፊ መንገዶች ልጁ ይጠበቅ ዘንድ ጽኑ ምኞቱ ነበር።

ሚያዝያ 11
Apr 19

ተጨማሪ ሀሳብ


በምድረ በዳ የተጓዙትን የጥንት እስራኤላውያን ታሪክ ስናነብ አምላካዊው ፍቅርና ኃይል በአስደናቂ ሁኔታ እየተገለጠላቸውና ታላቅ ለውጥ ከፊታቸው ተደቅኖ እያለ እነርሱ ግን በስህተት ላይ ስህተት እየሠሩ መቀጠላቸውን መመልከት እንችላለን። በእርግጥ እስራኤላውያን በስተመጨረሻ ወደ ተስፋው ምድር ሊገቡ ሲቃረቡ ሌላ ብርቱ የለውጥ ተግዳሮት ገጥሟቸው ነበር።

ሙሴ የሚከተለውን መልእክት ለጥንት እስራኤላውያን ሰጠ፡ “እግዚአብሔር በብዔልፌጎር ላይ ምን እንዳደረገ በዐይናችሁ አይታችኋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከመካከላችሁ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሁሉ አጥፍቶአቸዋል፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን የተከተላችሁት እናንተ ሁላችሁ ግን ይኸው እስከ ዛሬ በሕይወት አላችሁ። ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ። በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙና ‘በእውነቱ ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው’ ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና።

በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ ቅርብ እንደ ሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው? ዛሬ እኔ በፊታችሁ እንዳስቀመጥሁት ሕግ ያለ ጽድቅ የሆነ ሥርዐትና ሕግ ያሉት ሌላ ታላቅ ሕዝብስ ማነው? ዐይኖቻችሁ ያዩዋቸውን ነገሮች እንዳትረሱ፣ ደግሞም በሕይወት እስካላችሁ ድረስ ከልባችሁ እንዳይጠፉ ብቻ ተጠንቀቁ፣ ነቅታችሁም ራሳችሁን ጠብቁ። እነዚህን ለልጆቻችሁና ከእነርሱ በኋላ ለሚወለዱት ልጆቻቸው አስተምሯቸው።” (ዘዳ. 4፡3-9)። ጌታ ለእኛ ያደረገልንን ነገር አለመርሳታችን እጅግ ወሳኝና መሰረታዊ ጉዳይ ነው። አምላካዊውን በጎነት ለሌሎች ብሎም ዱካችንን ለሚከተሉ ማስተማርና መንገር ይህን ታላቅ ውለታ እንዳንዘነጋ ያስችለናል። በዚህ ሁሉ ጉዳይ ቤተሰብ ምን ያህል ማዕከላዊ እንደሆነና ወላጆች እነዚህን ነገሮች ለተተኪዎቻቸው ማስተማራቸውን ማጤን ተገቢ ነው።

እስራኤላውያን በሰጢም በነበሩበት ወቅት የሠሩት ኃጢአት በቤተሰባዊው ህይወት ላይ ውድመት የሚያስከትል ነበር። “አምላካዊውን ፍርድ በእስራኤላውያን ላይ ያመጣው ወንጀል ምንዝርና ሴሰኝነት ነበር። የሞአብ ሴቶች ወጥመድ መሆን በብዔልፌጎር ተቋጭቶ የሚያበቃ አልነበረም።”—Ellen G. White, The Adventist Home, p. 326.


የመወያያ ጥያቄዎች




፡ 1.በህይወትዎ እጅግ ታላቅ የሚባለውን ምዕራፍ የተቀዳጁበትን ማለትም እንደ ጋብቻ፣ ወላጅነት፣ ከአረጋውያን ተርታ መሰለፍ ወዘተ ባላደረጓቸው ዝግጅቶች ዙሪያ ለሰንበት ትምህርት ጥናት አባላት ያካፍሉ። ለውጡ ቤተሰብዎ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ምን ይመስል ነበር? በተመሳሳይ የህይወት ምዕራፍ ለሚገኙ ወገኖች ሊያካፍሏቸው የሚችሏቸው ምን የተማሩአቸው ነገሮች አሉ?

2.ዳዊት ለሰሎሞን የሰጣቸውን ምክረ ሃሳቦች በመላው የንግሥና ዘመኑ ላይ አሳዛኝ ጥላ ባጠላውና በቤተሰቡ ላይ አስከፊ ተጽእኖ ባሳደረው-ከቤርሳቤህ ጋር ካደረገው ኃጢአት ዐውድ ለማሰብ ይሞክሩ። በዚህ ሁሉ መሀል አምላካዊው ጸጋ በሥራ ላይ መሆኑን የምንመለከትባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?