ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 1 ዘፍ. 8:22፣ መዝ. 90:10፣ ኢዮ. 1:13–19፣ ሐዋ. 9:1–22፣ ፊልጵ. 1:6፣ ሮሜ 8:1።
መታሰቢያ ጥቅስ:- “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው” (መክ. 3፡1)።
በ
ንጉሥ ሰሎሞን የተጻፉት ስንኞች በሥነ ግጥሙ ዓለም እጅግ ውብና ዘመን አይሽሬ
ከሚባሉ ጎራ ይመደባሉ፡ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው
ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው፤ ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው፤
ለመትከል ጊዜ አለው፤ ለመንቀልም ጊዜ አለው፤ ለመግደል ጊዜ አለው፤ ለማዳንም
ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፤ ለመገንባትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፤
ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ ለሐዘን ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመጣል
ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፤ ለመለያየትም
ጊዜ አለው፤ ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ለመተውም ጊዜ አለው፤ ለማስቀመጥ ጊዜ አለው፤
አውጥቶ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ ለመቅደድ ጊዜ አለው፤ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤
ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ
አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፤ ለሰላምም ጊዜ አለው።” (መክ. 3፡1-8)።
እነዚህ ቃላት የሰብዓዊው የህይወት ጊዜያት ህልውና መሰረት የሆኑትን የለውጥ
ምዕራፎች አብልጠው ይዘዋል። እርግጥ ነው ህይወታችን ከተወለድንባት ጊዜ አንስቶ
በፈርጅ በፈርጁ ገቢራዊ በሚሆኑ ተለዋዋጭ ሂደቶች ውስጥ ያልፋል። አንዳንዴ
ለውጦቹ መልካምና በቁጥጥራችን የሚገኙ ሲሆኑ፤ ሌላ ጊዜ ግን ከዚህ በተቃራኒ
ልናገኛቸው የምንገደድበት ሁናቴ ይፈጠራል። በዚህ ሣምንት በተለይ በራሳችንም ሆነ
በቤተሰባችን ሕይወት ላይ ተጽእኖ ሊኖራቸው በሚችሉ ፈርጀ ብዙ የሕይወት ቀናትና
የለውጥ ሂደቶች ዙሪያ ምልከታ እናደርጋለን።
መጽሐፍ ቅዱስ “በመጀመሪያ…” (ዘፍ. 1፡1) የሚለውን ቃል በማስቀደም ይጀምራል።
በእርግጥ ይህ ቃል ለመግቢያነት ጥቅም ላይ የዋለበትን ምክንያት ለማወቅ እምብዛም
አይገድም። ምክንያቱም ምድር “ቅርጽ የለሽና ባዶ” (ዘፍ. 1፡2) ከነበረ ሁናቴ-እግዚአብሔር ራሱ በስድስተኛው ቀን “እጅግ መልካም” (ዘፍ. 1፡31) ብሎ የጠራውን
ገጽታ ይዛ መለወጧ ዐበይት የምዕራፉ ትኩረት በመሆኑ ነው። በመጀመሪያ በሚል
የተጠቀሰው ቃል በአጭሩ ምድራችን እንዴት እንደተጀመረች ያመለክታል።
ከዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ያንብቡ። በምዕራፉ መጠነ ሰፊ
ክስተቶች ገቢራዊ ከመሆናቸው አኳያ ይህ ሁሉ ነገር በዘፈቀደ ወይም እንደ አጋጣሚ
መሆኑን የሚያሳይ አንዳች ፍንጭ ማግኘት ይቻላል--ወይስ እያንዳንዱ ነገር ትክክለኛ
ጊዜና ቦታውን ጠብቆ ተፈጻሚ ሆኖአል? መልስዎ ስለ እግዚአብሔር ባህሪ ምን
ይናገራል?
“ሥርዓት ተቀዳሚው የሰማይ ሕግ ነው” በማለት ኤለን ጂ. ኋይት (Signs
of the Times, June 8, 1908) ትናገራለች። ለነገሩ ጉዳዩ በሰማይ ሳይወሰን
ምድርን ማካተቱም በግልጽ ይታያል። ምንም እንኳ ኃጢአት የምድርን ተፈጥሮ
ቢያመሳቅልም--ሥርዓት፣ ለዛ ያለው የሁናቴዎች መፈራረቅና መደበኛነት እነሆ
ዛሬም አለ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 8፡22። ሥርዓትና መደበኝነት በዚህ መልእክት የቀረበበት
መንገድ ምን ይመስላል?
በኃጢአት መውደቅ ከተከሰተ በኋላም እንኳ በአጠቃላይ ሲታይ ወቅቶች
ሥርዓታቸውን ጠብቀው ይፈራረቃሉ። የሰማይ ብርሃናትን ማለትም ፀሐይና
ጨረቃን ጨምሮ “ቀኑን ከሌሊት እንዲለዩ፣ የዓመት ወቅቶች፣ ቀናትና ዓመታት
የሚጀምሩበትንም እንዲያመለክቱ…” (ዘፍ. 1፡14) ሁሉንም የተፈጥሮአዊ መፈራረቆች
ፈጠረ። በእርግጥ ዛሬ በድንግዝግዝ ብናይም ነገር ግን በአዲሱ ሰማይና ምድርም
እንዲሁ ለዛ ያለው መፈራረቅ እንደሚኖር እንደ ኢሳ. 66፡23 ዓይነቶቹ ጥቅሶች
ያመለክቱናል።
ሰንበት በእርስዎ በተለይ ደግሞ በቤተሰብዎ ህይወት ላይ ምን
ያህል እጅግ ብርቱ መደበኛ ተጽእኖ እንዳለው አሰብ ያድርጉ። ከላይ
ከተመለከትነው መደበኛነት አኳያ ከሰንበት ምን የተለዩ መወሳት
የሚችሉት ጥቅሞች ይገኛሉ?
ሳይንቲስቶች ሲርካዲያን ሪትም ብለው ስለሚጠሩት ነገር ሲናገሩ ይደመጣሉ።
ይህ ጽንሰ ሃሳብ አንዳንዴ አካላዊ ሰዓት በመባል የሚታወቅ ሲሆን--የውስጠኛው
አካላችን ዑደት ተስተካክሎ እንዲቀላጠፍ ያደርጋል። በሌላ አነጋገር በራሱ በአካላችን
ውስጥ ሳይቀር ሕግና ሥርዓትን የተከተለ የለውጥ ሂደት ወይም ዑደት አለ። በዚህ
የተነሳ አግባብ ያለው መፈራረቅ በገዛ ራሳችን ውስጥ ስለ መኖሩ አፋችንን ሞልተን
መናገር እንችላለን።
በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ የተጠቀሱ አስቀድመው መገመት የሚችሉ የሕይወት
ቀናት የትኞቹ ናቸው? ከቤተሰብ ሕይወት ጋር ያላቸው ቀጥተኛ ቁርኝትስ ምን
ይመስላል?
መክ. 3:2
ዘፍ. 21:8፣ መሣፍ. 13:24
መዝ. 71:5፣ ምሳ. 5:18
ዘፍ. 15:15፣ መሣፍ. 8:32
ምሳ. 90:10
እያንዳንዱ ሰው በሁለቱ የሕይወት ጫፎች ማለትም በመወለድና ሞት መሃል-አስቸጋሪ በሆኑ ፈርጀ ብዙ ምዕራፎች ያልፋል። አንዳንዶች ተወልደው ብዙም
ሳይቆዩ ገና በለጋነታቸው ሲቀጬ ሌሎች ደግሞ እስከ ሽምግልና ዕድሜ ይዘልቃሉ።
ልጆች በየራሳቸው ፍጥነት ያድጋሉ፣ ይጎለብታሉም። አንዳንዶች ከሌሎች ቀድመው
ይራመዳሉ ወይም ይናገራሉ። የተወሰኑት ትምህርት ቤት ገብተው እስከ ከፍተኛ
ባለሙያነት የሚያበቃቸው ደረጃ ሲደርሱ ሌሎች ደግሞ ጊዜያቸውን ለሌላ የሥራ
ዓይነት ያውላሉ። አንዳንዶች ቤተሰብ ሲያፈሩ ሌሎች ግን ሳያገቡ ወይም ልጅ
ሳይወልዱ ይቀራሉ።
ዛሬ በምድራችን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች ይኖራሉ። ምንም እንኳ ሁላችንም
በተመሳሳይ የምንጋራቸው ነገሮች ቢኖሩንም (ሐዋ. 17፡26) ግላዊ ማንነትም አለን።
ይህን ተከትሎ በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ ልዩነቶች አሉ።
እነዚህ ልዩነቶች እያንዳንዳችንን ልዩ ስለሚያደርጉንና አንዳችን ያለንን ለሌላው
የምናጋራበትን መንገድ ስለሚከፍቱልን አስፈላጊነታቸው አንድና ሁለት የለውም።
በአጭሩ ልዩነቶቻችን አንዳችን ለሌላው በረከት እንድንሆን ይፈቅዱልናል።
ለምሳሌ ጎልማሳና አዛውንት አንዱ ለሌላው ሊያበረክት በሚችለው ነገር ሁለቱም
ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፡ “የጎልማሶች ክብር ብርታታቸው፣ የሽማግሌዎችም ሞገስ
ሽበታቸው ነው” (ምሳ. 20፡29)። በየትኛውም የህይወት ርካብ ላይ ልንገኝ ብንችልና
ልዩነቶቻችን የቱንም ያህል ቢሰፉ ለጌታ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም እርስ በርስ ልንለጋገስ
የምንችላቸው ነገሮች አሉን።
እርስዎ በየትኛውም የህይወት ሁናቴ ላይ ቢገኙም፤ ለሌላው በረከት
ለመሆን ምን ማድረግ ይችላሉ? በተለይ የቤተሰብዎ አካል ለሆነ ሰው
እንዲህ ያለው በረከት ይሆኑ ዘንድ ለምን ብርቱ ጥረት አያደርጉም?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢዮ. 1:13–19፣ 2:7–9። በኢዮብ ላይ ምን ደረሰ? እርሱ ያለፈበት ተሞክሮ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በእያንዳንዱ ላይ ሊደርስ ስለሚችል ነገር በምን መልኩ ነጸብራቅ መሆን ይችላል ?
ታዋቂው የግሪክ ፈላስፋ ሔራክሊተስ “ከለውጥ በቀር በቋሚነት የሚዘልቅ ነገር
የለም” በማለት ተናግሮአል። ሁሉም ነገር በመልካም ሁኔታ ላይ ያለ እየመሰለ
ያልተጠበቀ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። ሥራ ወይም አካል ማጣት፣ ሆስፒታል
የሚያስተኛ ህመም ወይም ያልተገመተ ሞት፣ የቤት ቃጠሎ ወይም የመኪና ግጭት
በማንም ላይ ሊደርስ የሚችልበት አጋጣሚ ይከሰታል።
በእርግጥ ለውጦች ሁሉ አሉታዊ እንዲሆኑ አይጠበቁም። ወደ ተሻለ የኤኮኖሚ
ሁኔታ ሊያደላድል የሚችል የሥራ ዕድገት ሊመጣ ይችላል። ወይም ደግሞ አንድ
ሰው በሕይወቱ ላይ ሊመጣ የሚችለውን ለውጥ በደስታ የሚቀበልበት፣ የወደፊት
የትዳር አጋሩን የሚተዋወቅበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።
ወይም ደግሞ ነገሮች ባልተጠበቀ መልኩ ምስቅልቅላቸው ይወጣና አንዳንዶች
በከባድ ሁኔታ ውስጥ ለማለፍ የሚገደዱባቸው ወቅቶች ሊመጡ ይችላሉ።
ኢዮብ በእርግጠኝነት እነዚያ አዳዲስ ወቅቶች የህይወቱ አካል ሊሆኑ እንደሚችሉ
አድርጎ ሊጠብቅ አይችልም።
መጽሐፍ ቅዱስ ኢዮብን “ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣
እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ” (ኢዮ. 1፡1) ሲል ይገልጸዋል። መጽሐፉ
አጋማሽ ላይ ስንደርስ ዋንኛ የሚባሉ ቢያንስ ስድስት እጦቶች እንደ ደረሱበት
እንመለከታለን፡ ሐብትና ንብረቱ፣ ሠራተኞቹ፣ ልጆቹ፣ ጤናው፣ የባለቤቱ ድጋፍ እና
የጓደኞቹ አይዞነት። ዓለም ተገለባበጠችበት፣ የቤተሰብ ህይወቱም አሰቃቂ ሆነ።
ምንም እንኳ በኢዮብ ላይ የደረሰው እጅግ ከመጠን ያለፈ ቢሆንም ለመሆኑ ከእኛ
መሃል ፍጹም ያልጠበቀው አሉታዊ ነገር ያልገጠመው ማን ነው? ነገሮች ሳይታሰብ
ያለ አንዳች ማስጠንቀቂያ ሲለዋወጡ የእኛም ሆነ የቤተሰባችን ህይወት ተመልሶ
እንደቀድሞው ላይሆን ይችላል።
ይህ በእርግጥ አዲስ ነገር አይደለም። ምናልባት አቤል በወንድሙ እንደሚገደል
እንዲሁም ዮሴፍ በገዛ ወንድሞቹ በባርነት ወደ ግብፅ እንደሚሸጥ--ሁለቱም
አልጠበቁም። በሁለቱም ታሪኮች ክህደት ፈጻሚዎቹ የቤተሰብ አባላት ሲሆኑ
በሁለቱም የጉዳት ሰለባዎች በደረሰው ነገር ግዙፍ ተጽእኖ የተፈጠረውም
በቤተሰባቸው ላይ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የግለሰብም ሆነ የቤተሰብ ህይወት ፍጹም
ሳይጠበቅ በከፍተኛ ሁኔታ በተለወጠ--ሰዎች ምሳሌ የተሞላ ነው።
የተረጋጋውን የህይወት ዑደት ሳይታሰብ ከሚያምሱ ያልተጠበቁ አስቸጋሪ
ሁናቴዎች ጋር በተላተሙበት ወቅት እምነትዎ እንዴት ረዳዎት?
ብዙውን ጊዜ ሰዎች የልማዳቸው ፍጥረቶች ናቸው ሲባል ቢደመጥም ነገሩ እውነትነት
አለው። አንድ ሰው በተደጋጋሚ አንድ ነገር እያደረገ ብዙ ዘመናት ባስቆጠረ መጠን
እንዲህ በቀላሉ ያን የቆየ አካሄድ መቀየር አይሆንለትም።
በእርግጥ--እንዲህ በቀላሉ አንለወጥም። ለመሆኑ ስንት ሚስቶች ናቸው “ባሌን
ለመለወጥ ሞክሬአለሁ፤ ግን …” እያሉ ያማረሩ? ሆኖም በተለይ ስብዕናችንንም
ባይሆን እግዚአብሔር ባህሪያችንን የመለወጥ ሥራ እየሠራ ይገኛል። እግዚአብሔር
እኛን በእርሱ አዲስ ፍጥረቶች እያደረገ የመሆኑ እውነታ የደኅንነትን እቅድ አብልጦ
ይገልጣል።
በተርሴሱ ሳውል ላይ ምን ዓይነት ታላቅ ለውጥ ታየ? እንዴትስ ተከሰተ? ሐዋ.
8:1፣ 3፣ 9:1–22፣ ገላ. 1:15–17
“ሳኦል ስለ ኃጢአት ለሚወቅሰው መንፈስ ቅዱስ ሙሉ ለሙሉ እጁን በሰጠ ጊዜ
በህይወቱ የሠራቸውን ስህተቶች ለመመልከት ቻለ። አምላካዊው ሕግ የሚጠይቀው
ነገር ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነና በደለኛውን በዋዛ እንደማያልፍ ተገነዘበ። ኩሩ
ፈሪሳዊ የነበረው ሳኦል በመልካም ሥራው ለመጽደቁ ልበ ሙሉ የነበረ ቢሆንም፤
አሁን ግን በትህትና ራሱን በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ አደረገ። ከንቱ ሆኖ ያገኘውን
ተመጻዳቂነት በመናዘዝ የተሰቀለውንና ከሞት የተነሳውን አዳኝ የጽድቅ ሥራ
የሚማጸን ሆነ። ከአብ እና ከወልድ ጋር ፍጹም ሰላም ወዳለው ህብረት ለመምጣት
የናፈቀው ሳኦል ይቅርታና ተቀባይነት ለማግኘት በነበረው የማያባራ ምኞት ከልብ
የመነጨ ልመና አቀረበ…
“የታጋሹ ፈሪሳዊ ጸሎት ከንቱ ሆኖ አልቀረም። የልቡ ሃሳብና ውስጠኛው ስሜቱ
በመለኮታዊው ጸጋ በመለወጡ፤ ያ የሚደነቅ የአእምሮ ሰጦታው ከአምላካዊው
ዘላለማዊ ዓላማና እቅድ ጋር ስምምነት መፍጠር ቻለ። ዓለም ሁሉ በአንድነት
ቢደመር ለእርሱ እጅግ የከበረው ክርስቶስና የእርሱ ጽድቅ ብቻ ሆኖ ተገኘ”—Ellen
G. White, The Acts of the Apostles, pp. 119, 120.
የገዛ ራሳችን የመለወጥ ታሪኮች እጅግ አስደናቂ ከሆነው የጳውሎስ ታሪክ ጋር
ባይቀራረቡም፤ መሆን አለብን ብለን የምንገነዘበው ዓይነት ሰዎች እንሆን ዘንድ
ጌታ እኛን ለመለወጥ እንዴት በህይወታችን እንደሠራ የሚናገሩ የየራሳችን ታሪኮች
አሉን። በእርግጥ ሂደቱ ረጅም ሊሆን ስለሚችል እንደውም አልፎ አልፎ እንዴት
መለወጥ እንችላለን ብለን ብንደነቅ እምብዛም ላይገርም ይችላል። አንዳንዴ እንዲህ
ዓይነት ሁናቴዎች ሲገጥሙ ለመንፈሳዊ ማሰላሰል ወሳኝ የሆኑና የየግላችን አድርገን
ልንቆጥራቸው የሚገቡ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ፊልጵ. 1፡6፣ ሮሜ 8፡1። በጥቅሶቹ የምናገኛቸው
ሁለት ታላላቅ የተስፋ ቃሎች ምንድን ናቸው? በክርስትና ተሞክሮ
የጥቅሶቹ ጥምረት ያለው ተገቢነት ምን ይመስላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰብዓዊው የእርስ በርስ መስተጋብር የሚያወሳ መጽሐፍ ነው።
እኛ ከሌሎች ጋር ግንኙነት እንድንመሰርት ሆነን እነሆ በእግዚአብሔር ተፈጥረናል።
በእርግጥ ፍጹም ከሰዎች ተገልለን የምንኖር አንዳንዶች መኖራችን እሙን ነው።
ሲጀመር በሌሎች የተነሳ ካልሆነ በቀር መጠንሰሳችን ፈጽሞ የማይታሰብ በሆነ
ነበር። በመቀጠል ከተወለድን በኋላም፣ ቢያንስ በመርኅ ደረጃ የተወሰነ ዕድሜ ላይ
ደርሰን በራሳችን መቆም እስክንችል የሌሎች ድጋፍና እንክብካቤ ያሻናል።
ከዚያ
በኋላስ--ከቤተሰብ መራቁን ማን ይሻዋል? አብዛኞቻችን የሌላውን አብሮነትና
ጓደኝነት እንፈልጋለን። ምንም እንኳ በተለይ እንደ ውሻ ካሉት የቤት እንስሳት ጋር
ባለን አብሮነት ደስተኞች ልንሆን ብንችልም፤ ነገር ግን እጅግ ጥልቅና ትርጉም ያለው
ህይወት የሚለውጥ መስተጋብር ሊመጣ የሚችለው ከሰዎች ነው። ከዚህ አኳያ
ከቤተሰብና ከቤተሰብ አባላት ጋር የሚኖር ግንኙነት በእጅጉ ወሳኝ መሆኑ ብዙም
ሊያስገርም አይችልም።
አብዛኞቻችን ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ጋር ግንኙነት የምንፈጥር እንደመሆናችን፤
ግንኙነቶቹ በህይወታችን ሊኖሩ በሚችሉ ለውጦች እና የለውጥ ሂደቶች ላይ ተጽእኖ
ይኖራቸዋል። ሆኖም ጉዳዩ በሁለት መንገዶች ይሠራል። አንደኛው፡ ሌሎች ከእኛ
ጋር ባላቸው መስተጋብር በህይወታችን ላይ ተጽእኖ ማሳረፋቸው ሲሆን ሁለተኛው
ደግሞ እኛ ከሌሎች ጋር ባለን መስተጋብር በህይወታቸው ላይ የምናሳድረው ተጽእኖ
ነው። ጉዳዩን አስተዋልነው ወይም አላስተዋልነው (ብዙውን ጊዜ አናስተውለውም)
በሁለቱም አቅጣጫ ያሉት ግንኙነቶች በጎ ወይም ክፉ ውጤት ይዘው ሊመጡ
ይችላሉ። ታዲያ ሁሌም ሊመጣ ላለው ለውጥ ወይም አስቸጋሪ ሁኔታ አስቀድሞ
መወሰን መቻል በእጅጉ ወሳኝ እንደሆነ ልብ ይሏል። እንዲህ ሲሆን በአብዛኛው
የቤተሰባችን አካል ሊሆኑ በሚችሉ በጣም በምንቀርባቸው ወገኖች ላይ የሚኖረን
ተጽእኖ ሁሌም ሊጠበቅ የሚችል በጎ ውጤት ይኖረዋል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 15:7፣ ኤፌ. 4:2-32፣ 1ተሰ. 3:12፣ ያዕ. 5:16። ከሌሎች ጋር
በሚኖረን መስተጋብር ምን እንድናደርግ ይነግሩናል?
የምንከተለው መርኅ በአመዛኙ ከባድ የሚባል አይደለም። እኛነታችን በበጎ
ምግባር፣ በደግነትና በርኅራኄ የበለጸገ እስከሆነ ድረስ የሌሎችን ህይወት በአዎንታዊ
መንገድ ለመቀየር የሚያስችል ተጽእኖ ፈጣሪ ስብዕና ባለቤቶች እንሆናለን። የሱስ
የሰዎችን ህይወት አዎንታዊ በሆነ መልኩ እንደ ቀየረ እኛም በተመሳሳይ ለሌሎች
ማድረግ መቻላችን እንዴት ጸጋ ነው! ተጽእኖአችን ለበጎ ወይም በረቀቀ መንገድ
ተጠልፎ ለክፉ ሊውል እንደሚችል ሁሌም ማስታወስ ይኖርብናል። ደግሞም አጉል
የሆነው ተጽእኖ የረቀቀ ሆነ ወይም አልሆነ ከቤተሰባችን ይልቅ ግልጽና የማያወላዳ
ሆኖ የትም ቦታ አለ።
የሱስ የተናገራቸውን የሚከተሉትን መልእክቶች ልብ ይበሉ፡ ሉቃ.
11:34፣ ማር. 4:24-25። ከሌሎች ጋር ግንኙነት ስለ መፍጠር
አስፈላጊነት ምን ይላሉ?
የየሱስ ደቀ መዛሙርት ከእርሱ ጋር በነበራቸው ግኝኙነት
በህይወታቸው ገቢራዊ የሆኑትን ለውጦች በዐይነ ህሊና መመልከት ይቻላል።
ደቀ መዛሙርቱ በአብዛኛው የዘመኑን ትምህርት ያልተማሩ፣ ቀለል ያለ ስብዕና
የነበራቸው እና ከአይሁድ እምነት አስተምህሮዎችና ልማዶች የወጡ ሆነው ሳለ፤
አሁን ግን በገሊላው ረቢ ብርቱ ተግዳሮት ገጠማቸው።
እነርሱ ምቀኝነት (ማቴ.
20፡20-24) እና ግጭት (ዮሐ. 3፡25) ይስተዋልባቸው የነበረ፣ እምነት የጎደላቸው
(ማር. 9፡28-29) ከዚያም አልፎ የሱስን እስከ መተው የደረሱ (ማቴ. 26፡56) እና
ክህደት የፈጸሙበት (ማቴ. 26፡69-74) መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።
የሚገርመው ከዚህ በተጓዳኝ መንፈሳዊ ህይወታቸው እያደገ ስለ ነበር ጴጥሮስ
ከየሱስ ጋር እንደነበር ሰዎች ለመገንዘብ አልተቸገሩም (ማቴ. 26፡73)። ይባስ
ብሎ የአይሁድ ሸንጎ ሳንኸድሪን አባላት ጴጥሮስና ዮሐንስ “ያልተማሩ ተራ ሰዎች
መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ” (ሐዋ. 4፡13)።
የቤተሰባችን አባላት በዚህ ዓይነት መልኩ እየተመላለስን የሚመለከቱን ከሆነ
በእርግጥም “ከየሱስ ጋር እንደነበርን” ስለሚገነዘቡ በእነርሱ ላይ አስደናቂ የሆነ
አዎንታዊ ተጽእኖ ሊኖረን እንደሚችል ያስቡ።
በቤታችን ሊኖረን ስለሚገባ ተጽእኖ ኤለን ጂ. ኋይት የሚከተለውን ምክረ
ሃሳብ ትለግሳለች፡ “ቤታችንን በግልጽ የምናስተውል ቢሆንም ነገር ግን መልካም
እርዳታና ፍቅር ከእኛ የማይለዩ እንግዶች ከሆኑ ሁሌም አስደሳችና ፍልቅልቅ ቃላት
የሚነገሩበትና በበጎ ተግባራት የተሞላ መሆን ይችላል።”—The Adventist Home,
p. 18.
1.በመክ. 3፡1-8 የቀረቡት ጥቅሶች ምን ይላሉ? እነዚህን መርኅዎች
በህይወትዎና በተሞክሮዎ መተግበር የሚችሉት እንዴት ነው?
2.እስርዎ ባለፉባቸው አንዳንድ ህይወት የሚቀይሩ ተሞክሮዎችና
በትምህርቱ ባጠኑአቸው ነጥቦች ዙሪያ ተነጋገሩ። ደግሞም እንደ
ትምህርት ሊወስዷቸው ሲገቡ ነገር ግን ያ ሳይሆን የቀረበት አጋጣሚ
ይኖር ይሆን? ከዚህ ቀደም ያላስተዋሉት ነገር ግን በዚህ ትምህርት
የተማሩት አንዳች ነገር ይኖር ይሆን? በተጨማሪ እነዚህ ህይወት
የሚቀይሩ ተሞክሮዎች በህይወትዎ ስላሳደሩት ተጽእኖ ተነጋገሩ።
ከእነዚህ ሁናቴዎች ምን ተማሩ?
3.ክርስቶስ በህይወትዎ ባይኖር ኖሮ የዛሬው የህይወትዎ አቅጣጫ ምን
ያህል ፍጹም የተለየ ሊሆን ይችል ነበር? መልስዎ እኛን መለወጥ
ስለሚችለው የክርስቶስ ኃይል ምን ይነግሮታል?