የሕይወት ምዕራፎች
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከሰኔ 1–7

11ኛ ትምህርት

Jun 08 - Jun 14




የእምነት ቤተሰቦች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሐዋ. 10:1– 28፣ 34-35፣ 1ቆሮ. 2:2፣ 1ተሰ. 5:21-22፣ ዮሐ. 1:12-13፣ 3:7፣ 1ዮሐ. 5:1።


መታሰቢያ ጥቅስ:-“እንግዲህ… በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ፡፡ የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ተቀምጦአል” (ዕብ. 12፡1-2)፡፡

በ የትኛውም የዕድሜ ክልል ብንገኝ ወይም በማናቸውም ሁናቴ ውስጥ አልፈን ቢሆን ወይም ማለፍ ቢጠበቅብን እንኳ ከባህላችን ታሪካዊ ዳራ አኳያ እንኖራለን። ወላጆቻችን፣ ልጆቻችን፣ ቤታችን፣ ቤተሰባችን እንዲሁም ቤተ ክርስቲያናችን ሳይቀር ሁሉም በሚኖሩበት ባህል ተጽእኖ ስር ይመላለሳሉ። ለአብነት ያህል የቅዳሜ ሰንበት ወደ እሁድ መለወጥ ላይ ሌሎች መንስዔዎች ተዋናይ ቢሆኑም፤ በዘመኑ የነበረው ባህል ቤተ ክርስቲያንን በብርቱ ኃይል እና አሉታዊ በሆነ አካሄድ እንዴት ተጽእኖ እንዳሳደረባት የሚያሳይ ኃይለኛ ምሳሌ ነው።

በየመንገዱ ዳር ተለጥፈው የምንመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን እሁድ ቀን አገልግሎት ማስታወቂያ ሰሌዳዎች፤ የባህል ተጽእኖ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ በተጨባጭ ያስታውሰናል። ክርስቲያን ቤተሰቦች ከባህል ተግዳሮቶች ጋር በየጊዜው ይላተማሉ። በእርግጥ አንዳንዴ ባህላዊው ተጽእኖ መልካም ሊሆን ቢችልም ነገር ግን ባብዛኛው አሉታዊ ተጽእኖው የትዬለሌ ነው።

የወንጌል ኃይል ብርሃንና መጽናናት እንዲሁም ባህል ሊያመጣው የሚችለውን ተግዳሮት ለመጋፈጥ የሚያስችል ጥንካሬ መስጠቱ ታላቅ የምስራች ነው። በዚህ ሣምንት እንዴት “የእምነት ቤተሰቦች” መሆን እንደምንችል እንመለከታለን፡ “ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው” (ፊልጵ. 2፡15)።

ሰኔ 2
Jun 09

መልካም የሆነውን ፈጥኖ መያዝ


ወንጌል ዓለምን እንደሚያካልል ሁሉ ክርስቲያኖችም በዚያው አንጻር ከተለያዩ ባህሎችና ልምዶች ጋር ይገናኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ከቤተሰብ እና ማኅበራዊ ግንኙነት ጋር አግባብ አላቸው። በወንጌል ሥራ ርቀው የሚጓዙ ሚሽነሪዎች ከአካባቢው ባህልና ልማድ ጋር እንዴት ራሳቸውን ማዛመድ እንዳለባቸው ከሚያነሷቸው ውሃ የሚቋጥሩ ጥያቄዎች አንዱና ብዙም ምቾት የማይሰጣቸው ቤተሰባዊ ግንኙነቶች ናቸው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 10፡1-28፣ 34-35። ከሌሎች ባህሎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት የገዛ ራሳችንን አጥሮችና ጭፍን አስተሳሰቦች ማሸነፍ መማር የምንችለው እንዴት ነው?



ክርስቶስ የሞተው በማንኛውም ስፍራ ለሚገኝ እያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር ነው። ሆኖም አያሌ ሕዝቦች ይህን ታላቅ እውነት ገና እያስተዋሉ አይደለም ለማለት ያስደፍራል። እግዚአብሔር የማያዳላ አምላክ እንደመሆኑ ክርስቲያኖች ማንኛውም ሰው ይህን መልካም የምሥራች የራሱ የሚያደርግበትን ዕድል በአክብሮትና በሐቅ እንዲያቀርቡ ተጠርተዋል።

ወንጌልን ለሌሎች ባህሎች በማቅረቡ ረገድ የቀደሙ ክርስቲያን ወንጌላውያን ምን ዓይነት ድምዳሜ ላይ ደርሰው ነበር? ከጥቅሶቹ ምን ዓይነት መርኅ ማውጣት እንችላለን? ሐዋ. 15:19-20፣ 28-29፣ 1ቆሮ. 2:2፣ 1ተሰ. 5:21- 22።



ምንም እንኳ እያንዳንዱ ባህል የወደቀውን ሰብዓዊ ሁናቴ በራሱ ውስጥ የሚያሳይ ቢሆንም፤ በተጨማሪ ባህሎች ለወንጌል ዓላማ ጠቃሚነት ያላቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ስምሙ እምነት አላቸው። በአብዛኛው የዓለም ክፍል እንደሚስተዋለው-በቤተሰብና በማኅበረሰብ መሃል ለሚኖር የቀረበ ግንኙነት የሚሰጥ ዋጋ እንደ ምሳሌ መቅረብ ይችላል። ክርስቲያኖች መልካም የሆነውንና ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው መርኅ ጋር የሚሄደውን አጥብቀው ሊይዙና ሊያጸኑ ይችላሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ አምላካዊ እውነት ፈጽሞ ለድርድር መቅረብ የለበትም። ከባህል ጋር ለድርድር መቀመጥ ብሎም ወደ መስማማቱ ማዘንበል የሐሰት ክርስትናን የፈጠረና የይስሙላ ሐቀኝነትን ክርስትና ላይ የጣፈ ፍሬ ያፈራ እንደ ነበር አሳዛኙ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል።

ራሱን የዚህ ዓለም አምላክ አድርጎ የሚቆጥረው ሰይጣን ይህን ማደናገሪያውን እጅግ በደስታ ቢነዛም፤ ነገር ግን የሱስ ይህን ዓለም ዋጅቶአል፣ መንፈሱም ተከታዮቹን ወደ እውነት ሁሉ ይመራል (ዮሐ. 16፡13) ባህልዎ ከእምነትዎ ምን ያህሉን ክፍል የራሱን ቅርጽ እንዲይዝ አድርጎአል? መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነትስ? በሁለቱ መካከል ባሉ ልዩነቶች ላይ ያሎትን ግንዛቤ ማጎልበት የሚችሉት እንዴት ነው? መልስዎን በሰንበት ትምህርት ጥናት ክፍለ ጊዜ ይዘው ለመቅረብ ይሞክሩ።

ሰኔ 3
Jun 10

ባህል በቤተሰብ ላይ ያለው ጉልበት


“ትክክለኛና ቀና የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤተ ሰቦቹን እንዲያዝ መርጬዋለሁ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ሁሉ እንዲፈጸም ነው” (ዘፍ. 18፡19)። ምንም እንኳ ቤተሰብ ከተለያየ አመወቃቀር ቢመጣም፤ ማኅበረሰብ የሚገነባበት ጡብ አካል ነው።

በዚህ የተነሳ ብዛት ያላቸው በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ የአያሌ ማኅበረሰብ ባህሎችና ባህሪዎች ከቤተሰብ ጋር ቀጥተኛ ትስስር አላቸው። ለአብነት ያህል በአንድ ጥንታዊ ባህል ወንድ ልጅ በሞት የተለዩ ወላጆቹን ሙት አካል እንዲበላ ይገደድ ነበር። በሌላ ባህል ደግሞ አንድ ወንድ ለአካለ መጠን ደርሶ ሚስት ለማጨት ሲፈልግ ለማኅበረሰቡ በጠላትነት ከተፈረጀ ጎሳ የአንዱን ራስ ቆርጦ ለልጅቷ አባት በጥሎሽ ማቅረብ ነበረበት።

በዚህ ዘመናዊ በሚባል ዘመንም ቢሆን ከልጆች፣ ከመተጫጨት፣ ከፍቺ፣ ከጋብቻ፣ ከወላጅነትና ከመሳሰሉት ጋር ያሉ አስተሳሰቦች ሰፊ ልዩነት አላቸው። መልእክታችንን ለእነዚህ የተለያዩ ባህሎች ስናሰራጭ አንዱንም የእምነታችንን አንጓ ለድርድር ሳናቀርብና አላስፈላጊ ችግሮችን ሳንፈጥር ራሳችንን እንዴት ከማኅበረሰቡ ጋር ማዛመድ እንደምንችል መማር ይኖርብናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቤታችን ጋር በተያያዘ በቤተሰባችን ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ስለሚችለው ባህል ንቁ ልንሆን ይገባል። በመቀጠል ከቀረቡት ምሳሌዎች ባህል በቤተሰባዊው ህይወት ላይ ተጽእኖ ያሳደረባቸው አካሄዶች የትኞቹ ነበሩ? ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን ዓይነት መርኅዎች መማር እንችላለን? ዘፍ. 16:1–3፡



ዘፍ. 35:1–4፡



እዝ. 10፡



1ነገሥ. 11:1 ፡



አንዳችንም ብንሆን ከሰው ተለይተን እንደማንኖር ሁሉ፤ እኛም ሆንን ቤተሰባችን በምንኖርበት ባህል ተጽእኖ ውስጥ ነን። እንደ ክርስቲያን ውዝግብ ከሚፈጥሩ ነገሮች እየራቅን፣ በተቻለን በየባህላችን ውስጥ እምነታችንን እንደ ጠበቅን በንጽህና የመመላለስ ኃላፊነት አለብን።

በእርስዎ ባህል በተለይ ለቤተሰባዊው ህይወትና ለመጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ አላባዎች የትኞቹ ናቸው? ጠቃሚ ያልሆኑትስ? መሰረታዊ እውነቶችን ለድርድር ሳያቀርቡ እምነትዎን ምርጥ በሆነ አግባብ ከባህልዎ አኳያ በሥራ ላይ ማዋል የሚችሉት እንዴ ነው?

ሰኔ 4
Jun 11

በለውጥ ዑደት ቤተሰብን ጠብቆ ማቆየት


ሰዎች በየትኛውም ባህል ውስጥ ቢኖሩ በቤተሰብ ውስጥ ከሚከሰት ለውጥ ማምለጥ አይችሉም። አንዳንድ ለውጦች የህይወትን ዑደቶች ተከትለው ስለሚመጡ የሚጠበቁ ዓይነት ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ እንደ ሞት፣ መቅሰፍት፣ ጦርነት፣ ህመም፣ የቤተሰብ መኖሪያ አካባቢን መቀየር ወይም ከሥራ መባረር ዓይነቱ ለውጥ መቼ ሊከሰት እንደሚችል አይታወቅም። ብዙ ቤተሰቦች በማኅበረሰባቸውም ሆነ በአገራቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦች ይገጥሟቸዋል። ሌሎች ለውጦች ከባህል ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ ይኖራቸዋል።

በሰዎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ እጅግ አሰቃቂ ጥቂት ምሳሌያዊ ገጠመኞች ከዚህ በታች ቀርበዋል። ሁኔታውን በዐይነ ህሊናዎ ለመመልከት ይሞክሩ። ለውጦቹ በቤተሰባቸው ህይወት ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖዎች አስከተሉ? እርስዎ ቢሆኑ ምን ዓይነት እገዛ ሊያደርግ የሚችል ዘዴ ሊጠቀሙ ይችሉ ነበር? ከዚያ በተለየ ምን ዓይነት አካሄድ ሊከተሉ ይችሉ ነበር? • አብርሃም፣ ሣራ፣ ሎጥ (ዘፍ. 12፡1-5)



• ሀደሳ (አስቴ. 2:7–9)



• ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤል፣ አዛርያስ (ዳን. 1)



ለውጥ ለእጦትና ስጋት ተሞክሮዎች እምብዛም ሩቅ አይደለም። እነዚህ ተሞክሮዎች ቤተሰብ ለውጥን ከራሱ ጋር ለማስማማት እንዳለው የክህሎት ደረጃ ወደ አዲስ የእድገት ከፍታና መንፈሳዊ ልቀት ሊያሸጋግሩ ወይም በተቃራኒው ጭንቀትና ጥበት ውስጥ ሊከቱ ይችላሉ። በእግዚአብሔር ላይ ጥርጣሬና አለመተማመን እንዲሰፍን የሚሠራው ሰይጣን--ለውጥ፣ ነውጥ እንዲሆን ይጠቀምበታል።

አያሌ የእምነት ጀግኖች ህይወታቸው ፈታኝ ሁኔታ በገጠመው ወቅት--የአምላካዊው ቃል ተስፋ፣ የቤተሰብና የጓደኞች ድጋፍ እንዲሁም ህይወታቸው በእግዚአብሔር እጅ የመሆኑ ማረጋገጫ ችግሩን በስኬት እንዲጋፈጡ አስችሏቸዋል። አሰቃቂ ዓይነት ለውጥ ለመጋፈጥ የተገደደን ሰው (ወይም ቤተሰብ) የሚያውቁ ከሆነ የተለየ እርዳታና ማበረታታት ያድርጉ።

ሰኔ 5
Jun 12

ወደ ቀደመው ትውልድ እምነት


ኢያሱና የእርሱ ዘመን ሰዎች ከሞቱ በኋላ ምን ዓይነት የእምነት ቀውስ መጎልበት ጀመረ? Judg. 2:7–13



እንደ ቤተ ክርስቲያን ያሉ ተቋማት ወደ ቀጣይ ትውልድ ሲተላለፉ፤ የቀደሙት የነበራቸው የእምነትና የቁርጠኝነት ደረጃ ከተከታዮቹ ይልቅ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ጥናቶች ያመለክታሉ። እነዚያ የቀደሙት ወደር ያልተገኘላቸው ሰዎች ነበሩ። በአንድ ወይም በሁለት ትውልድ ውስጥ ለመርኅና ለእሴቶች ልል መሆን ይከሰታል። ትውልዱ ከተቋሙ ጋር ያለውን ግንኙነት ላያቋርጥ ቢችልም እንኳ አብዛኛው አካሄዱ ልማዳዊ ነው። ልማድ ደግሞ ወደ ተከታይ ትውልዶች ሲደርስ ከባህል ጋር የመቆራኘት አዝማሚያ አለው። ስለዚህ የመሥራቾች ጥልቅ ፍቅርና ቀናኤ እያከተመለት ይሄዳል። እግዚአብሔር ልጆች እንጂ የልጅ ልጆች የሉትም የሚል አባባል አለ። ለመሆኑ የአባባሉ ትርጉም ምንድን ነው? ዮሐ. 1:12-13፣ 3:7፣ 1ዮሐ. 5:1።



ጎልማሶች የሚያምኑትን ለወጣቶች እየነገሩ የክርስትና እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፋቸው ይታወቃል። ይህ የተለመደው አሠራር ነበር። ለነገሩ ወላጆች የሚያምኑትን ወይም ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን መስማት ብቻውን ግላዊ እምነት መሆን አይችልም።

ክርስቲያን መሆን ታሪክና ቀኖና ካለው ተቋም የላቀ ነው። እውነተኛ እምነት ከአንደኛው ትውልድ ወደ ቀጣዩ በዘር ሃረግ የሚወራረስ ነገር አይደለም። ይልቁንም እያንዳንዱ ሰው ክርስቶስን በግሉ፣ ለራሱ ሊያውቅ ይገባል። ወላጆች ሊያደርጉ የሚችሉት ይህን ያህል ብቻ ነው። በአጠቃላይ እንደ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በተለይ ወላጆች--ወጣቶች ትክክለኛውን ምርጫ መምረጥ የሚሹበትን ድባብ መፍጠር ይኖርባቸዋል።

በእግዚአብሔር ሕልዎት እምነት ያልነበረውና የዝግመተ ለውጥ አስተሳሰብ አራማጁ ጆ ከኃይለኛ ተግዳሮት በኋላ በጉልምስና ዕድሜው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን በቃ። ከአንዲት አድቬንቲስት ሴት ጋር ትዳር መስርቶም ልጆች ወለዱ። ታዲያ አንድ ቀን ስለ ልጆቹ መንፈሳዊነት እያሰበ “ምናለ ልጆቼ ያለፍኩበትን ተሞክሮ ተጋርተው ቢሆን!” ሲል ተናገረ። እርስዎ በዚያ ቢኖሩ ምን ይመልሱለት ነበር?

ሰኔ 6
Jun 13

የሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሯጮች


ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በተውጣጣው ዘ ሜሴጅ በሚል ስያሜ በሚታወቀው ሥራው የሚታወቀው ኢዩጌን ፔተርሰን፤ በመጽሐፍ ቅዱስ “ወንጌል” በሚል በየትኛውም ጥቅስ የሚገኝን ቃል “መልእክት” እያለ ሰይሞታል። ስለ የሱስ የቀረበው መልካም የምስራች በእርግጥም ዛሬም ዓለም የሚሻው እውነተኛ መልእክት ነው። ክርስቲያን ቤተሰቦች በአንድነት ሊለማመዱትና ለሚኖሩበት የትኛውም ባህል እንዲያካፍሉ ተጠርተዋል።

“መልእክቱ” (ዘ ሜሴጅ) የተሰኘውን ቃል የሚከተሉትን ጥቅሶች ተጠቅመው እንዴት አጠር ባለ መንገድ ያስቀምጡታል? ማቴ. 28:5–7፣ ዮሐ. 3:16፣ ሮሜ. 1:16-17። 1ቆሮ. 2:2፣ 2ቆሮ. 5:18–21።



ደቀ መዛሙርቱን በየአቅጣጫው ያሯሯጣቸው የቀደመው የምሥራች የየሱስ ትንሳዔ ነበር። ዛሬ ክርስቲያን ሯጮች እርሱ እንዳለው “‘ከሙታን ተነስቶአል’ ” (ማቴ. 28፡7) እያሉ ረጅሙን የሩጫ ሰልፍ ተቀላቅለዋል። የትንሳኤው እውነታ የሱስ ማንኛውንም ስለ ራሱ፣ ስለ እግዚአብሔርና ለኃጢአተኞች ስላለው ፍቅር፣ ስለ ምህረት እንዲሁም በእርሱ በማመን ስለሚገኝ የዘላለም ሕይወት የተናገረውን ሁሉ ተአማኒ ያደርገዋል።

ወንጌል በቀደሙት የየሱስ ተከታዮች ህይወት ያስከተለውን አስገራሚ ውጤት አምላካዊው ቃል ይነግረናል። ቤታቸውን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍት አድርገው ነበር፣ ይፀልዩና አብረው ይመገቡ ነበር፣ ገንዘባቸውንና ንብረታቸውን በአንድነት ይጋሩ ነበር፣ ደግሞም አንዱ ለሌላው ጥንቃቄ ያደርግ ነበር። የቤተሰብ አባላት በሙሉ መልእክቱን በደስታ ተቀብለው ነበር።

ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ባንዴ ወደ እንከን የለሽነት ተለውጠው ነበር? በፍጹም! በመሀላቸው ግጭትና አለመስማማት ነበር? አዎ! ሆኖም ግን እነዚህ የክርስቶስ ተከታዮች ለየት ያሉ ሰዎች ነበሩ። በጋራም ሆነ በግል የሚያስፈልጓቸውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ያሳውቁ ነበር። የሱስ በጌተሰማኔ የጸለየው ጸሎት (ዮሐ. 17፡20-23) ይፈጸም ዘንድ በቤትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ለህብረታቸውና ለዛ ላለው ውህደታቸው ቅድሚያ ይሰጡ ነበር። ለእምነታቸው ሲሉ ህይወታቸውን አደጋ ላይ እስከ መጣል በደረሰ ቅንአት--አንዳቸው ለሌላቸውም ሆነ አማኝ ላልሆኑ በድፍረት ይመሰክሩ ነበር። ቅንአት ለወንጌል፡ ይህ በእኛም ሊተገበር የግድ ይሆናል። ይህ ትውልድ ለአምላካዊው ነገሮች ተጠራጣሪ ቢሆንም ልባቸው ደስ የተሰኘ ሰዎች በተሻለ ይደመጣሉ። መንፈስ ሰብዓዊውን ልብ በወንጌል ደስታ ለመሙላት ይናፍቃል። ወንጌል ልክ እንደ ቃሉ በልባችንም የምሥራች ሆኖ ተቀባይነት ሲያገኝ፤ ይህን እውነት ለሌሎች ማካፈል--ድንገት ውስጣችንን ፈንቅሎ ገቢራዊ የሚሆን፣ ማንም ሊያቆመው የማይችል ክስተት ነው። የተሻለ ጥሩ ወሬ አብሳሪ ሆነው የተጠሩበትን “መልእክት” ለሌሎች ማጋራት ይችሉ ዘንድ በገዛ ቤተሰብዎ ምን ዓይነት ለውጥ ማድረግ ያስፈልጎታል?

ሰኔ 7
Jun 14

ተጨማሪ ሀሳብ


Ellen G. White, “In the Court of Babylon,” pp. 479– 490, in Prophets and Kings; “Words of Caution,” pp. 324, 329; “No Respect of Persons With God,” pp. 330, 331, in Gospel W- orkers; “Rejoicing in the Lord,” pp. 115–126, in Steps to Christ. ለእግዚአብሔር ሰዎች ክብር አለመስጠት፡ “የክርስቶስ ኃይማኖት ተቀባዩን ከፍ ወዳለ የአስተሳሰብና የድርጊት ልቀት ያሸጋግራል።

በተመሳሳይ መላውን ሰብዓዊ ዘር በልጁ መሥዋዕትነት እንደ ተገዛ የአምላካዊው ፍቅር ባህሪ አድርጎ ያቀርባል። ሐብታም ወይም ደኻ፣ ፊደል የቆጠረ ወይም መሐይም ያለ አንዳች የመደብ ወይም የምድራዊ አለቅነት ሃሳብ ሁሉም በአንድነት በየሱስ እግሮች ስር ይገናኛሉ። ኃጢአታችን የቸነከረውን እርሱን ስንመለከት ሁሉም ምድራዊ ልዩነቶች ይረሳሉ።

ራሱን የካደው፣ ያዋረደውና እጅግ አድርጎ በሰማይ የከበረው፤ የወሰን ዐልባ ርኅራኄ ባለቤት የሆነው እርሱ--ሰብዓዊውን መታበይ፣ መመጻደቅና የመደብ ልዩነትን ያሳፍራል። ንጹህና ያልረከሰ ኃይማኖት በእውነት የተቀደሱትን ወደ አንድነት በማምጣቱ ረገድ ሰማያዊ መርኅዎችን ገልጦ ያሳያል። መተማመናቸውን በእርሱ አድርገው፣ ለእግዚአብሔር የዋጃቸውና በደሙ የተገዙ ነፍሳት በሙሉ በአንድነት ይገናኛሉ።”—Ellen G. White, Gospel Workers, p. 330.


የመወያያ ጥያቄዎች




፡ 1.በእሁድ መልስ ላይ ተወያዩ።

2.…በጥቅም ላይ መዋል ከቻለ በቤተሰባችን ህይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል በሚል በትምህርተ ጥቅስ ከቀረበው የኤለን ጂ. ኋይት መልእክት ምን ዓይነት መርኅዎች ማግኘት እንችላለን?

3.አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ ወጣቱን አማኝ ትውልድ በማበረታታትና በማሳደግ ረገድ ምን ያህል ውጤታማ ሥራ እየሠራች ነው? እንደ ሰንበት ትምህርት ጥናት አባልነታችሁ ለዚህ አስፈላጊ ተግባር ምን ዓይነት እገዛ ማድረግ ትችላላችሁ?

4.እምነትን ወደ ተከታዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ያሉት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?

5.የእርስዎ ባህል በቤተሰቦ ህይወት ላይ ያለው መልካም ተጽእኖ ምን ይመስላል? ክፉው ተጽእኖስ?