የሕይወት ምዕራፎች
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከሰኔ 8 –14

12ኛ ትምህርት

Jun 15 - Jun 21




ሰዎች በቤትዎ ያዩት ምንድን ነው?



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 38፣ 39፣ 1ቆሮ. 7:12–15፣ 1ጴጥ. 3:1- 2፣ ዕብ. 6:12፣ 13:7፣ 3ዮሐ. 11፣ ኢሳ. 58:6-7፣ 10-12።


መታሰቢያ ጥቅስ:-“እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ፡፡” (1ጴጥ. 2፡9)

ም ናልባት ቤተሰባችን በመልካም ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ፣ ሥራችን የተቃና፣ የጤናችንና የገቢያችንም ነገር እንዲሁ አስተማማኝ መሆኑን ተከትሎ በመልካም ሁኔታ ላይ ስለሚገኘው ማንነታችን ዘወትር ለጌታ ምስጋና የምናቀርብበት ከፍታ ላይ እንገኝ ይሆናል። ወይስ ከዚህ በተቃራኒ ነን? ምናልባት ቤትዎ ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ይገኝ ይሆን? ምናልባት ንጉሥ ሕዝቅያስን ለመጎብኘት ከባቢሎን እንደ መጡት መልእክተኞች አንድ ሰው ቤትዎን ሲጎበኝና ነቢዩ ኢሳይያስ “ ‘በቤተ መንግሥትህ ያዩት ምንድን ነው?’ ” (ኢሳ. 39:4) ብሎ ንጉሡን ለጠየቀው ዓይነት ጥያቄ የእርስዎ መልስ ምን ሊሆን ይችላል?

ሰዎች በቤትዎ ያዩት ምንድን ነው? የሰማይ መላእከትስ ምን ተመለከቱ? ወደ ቤታችን ዘልቆ የገባው ምን ዓይነት መንፈስ ነው? የጸሎታችን መዓዛ ያውድ ይሆን? ደግነት፣ ቸርነት፣ ፍቅር የሰፈነበት ነው? ወይስ ውጥረት፣ ብስጩነት፣ ቅሬታ፣ ምሬትና ብጥብጥ የሞላበት?

እነዚህ--የፈጠርነው ምን ዓይነት ቤት እንደሆነ ራሳችንን የምንጠይቅባቸው ለሁላችንም አስፈላጊ ጥያቄዎች ናቸው። ምንም እንኳ ዛሬ ቤት ውጥረትና ትግል የማያጣው ቢሆንም በዚህ ሣምንት ቤትን ግሩምና አስደናቂ የሚያደርጉትን አንዳድ ነጥቦች እንመለከታለን።

ሰኔ 9
Jun 16

ከንጉሡ ስህተት መማር


ስለ ሕዝቅኤል መታመንና ፈውስ እንዲሁም ስለ ባቢሎናውያን መልእክተኞች ጉብኝት ያንብቡ። 2ዜና 32፡25-31፣ ኢሳ. 38፣39። መልእክተኞቹ ስለ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታምራዊ ፈውስ ለማወቅ የመፈለግ ስሜት እንደ ነበራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ሆኖም ሕዝቅያስ ስላገኘው ፈውስ ለእነርሱ ከመንገር ይልቅ ዝምታን እንደ መረጠ ይታያል። መልእክተኞቹ ስለ እውነተኛው አምላክ እንዲጠይቁ ልባቸውን ሊከፍቱ ይችሉ ለነበሩ ነገሮች አጽንኦት አልሰጠም። በምዕራፍ 38 ስለ መፈወሱ ያቀረባቸው የምስጋና ቃላት በምዕራፍ 39 ከተስተዋለው ዝምታው ጋር ሲነጻጸሩ ግራ ያጋባሉ።

“እግዚአብሔር ሊፈትነው…ተወው።” ይህ በባቢሎን መንግሥት ልዑካን የተደረገ ጉብኝት ከፍተኛ አጽንኦት የሚሰጠው ዓይነት ቢሆንም፤ ነገር ግን በዚህ ዙሪያ ሕዝቅያስ ከነቢያቱ ወይም ከካህናቱ በጸሎት የተለየ ምሪት ለማግኘት ስለ መሞከሩ የተጻፈ ነገር አናገኝም። እግዚአብሔርም ቢሆን ጣልቃ ሲገባ አንመለከትም። ከሕዝብ ዐይንም ሆነ ከመንፈሳዊ አማካሪዎቹ የተነጠለው ሕዝቅያስ እግዚአብሔር በአገሩም ሆነ በእርሱ ህይወት የሠራው ሥራ ከአእምሮው ገሸሽ እንዲል ፈቀደ። በ2ዜና 32፡ 31 የቀረበው መልእክት ዓላማ አምላካዊው በረከት ሁሌም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚቀጥል ሆኖ መታሰቡንና፤ የምህረቱ ተቀባዮች ነገሮች በራሳቸው ብርታት የተፈለገውን መልክ እንደያዙ አድርገው በቀላሉ የመውሰድ ዝንባሌ እንዳላቸው ያሳያል።

በመቀጠል ከሕዝቅያስ ልምድ በመነሳት ለቤታችን ህይወት ታማኝ ልንሆንባቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች አንዳንድ ትምህርቶች ቀርበዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ወደ አእምሮዎ ሊመጡ የሚችሉ ነገሮች አሉ?



ወደ ክርስቲያን ቤት የሚደረግ እያንዳንዱ ጉብኝት የክርስቶስን ተከታዮች የመገናኘት ዕድል ይሰጣል። ከጎብኚዎች መሃል በመንፈሳዊ ነገሮች ዙሪያ ንግግር የሚከፍቱ ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ክርስቲያኖች መልካሙን የምሥራች ለሌሎች ማካፈል የሚያስችላቸውን እያንዳንዱን አጋጣሚ በአንክሮ ሊከታተሉ ይገባል። ክርስቲያኖች ቁሳዊ ሀብታቸውም ሆነ ስኬታቸው ከእግዚአብሔር የተቀበሉት በረከት ቢሆንም፤ ለጉራ ግን አልተጠሩም። ይልቁንም “ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ” ነው--(1ጴጥ. 2፡ 9)። ወይም የሕዝቅያስን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ በመጠቀም፤ እየሞቱ የነበረ ቢሆንም ክርስቶስ ግን እንደ ፈወሳቸው ለማወጅ፣ በኃጢአታቸው ሞተው ሳለ በክርስቶስ ሕያው ሆነው በሰማያዊ ስፍራ መቀጣቸውን ለማብሰር ነው (ኤፌ. 2፡4-6)። ቤትዎን ለሌሎች ለመመስከር መጠቀም የሚችሉት በምን መልኩ ነው? በክርስቶስ ያሎትን እምነት ቤትዎ ለመጡ እንግዶች ጊዜ ሳይወስዱ በቀጥታ ማካፈል የሚችሉት እንዴት ነው?

ሰኔ 10
Jun 17

ቤተሰብን ማስቀደም


ቤተሰባችን ወንጌልን ከምናካፍላቸው ወገኖች መሃል ቅድሚያውን መውሰዱ ተፈጥሮአዊ ነው። ከዚህ የላቀ አስፈላጊ የወንጌል ዘር መዝሪያ ስፍራ የለምና። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 1፡40-42 እምነታችንን ለቤታችን አባል ስለ ማካፈል አስመልክቶ ከዚህ ምን ዓይነት ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን? በተጨማሪ እነዚህን ጥቅሶች ይመልከቱ፡ ዘዳ. 6፡6-7፣ ሩት 1፡14-18።



አጓጊ ዘገባ፡ እንድርያስ ከዘገባም የላቀውን የዘገባ አቀራረብ ተከትሎ ወንድሙ ስምዖን የሱስን የሚገናኝበትን መንገድ ቀየሰ። ስለ የሱስ አጓጊ ዘገባ አቅርቦ እርሱን እንደ ግለሰብ ማስተዋወቅ--ወንጌልን ለቤተሰባችን አባል ለማካፈል የሚያስችል እንዴት ያለ ቀላል ቀመር ነው! ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም እንዲሉ እንድርያስ ወንድሙን ከየሱስ ጋር ካስተዋወቀ በኋላ የተቀረውን ለራሱ ተወለት። ጴጥሮስና የሱስ ከዚያን ጊዜ አንስቶ የራሳቸውን ግንኙነት መሰረቱ።

ለልጆች እምነት መጎልበት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ፡ ብዙውን ጊዜ ወንጌልን በቤታችን ላሉ ልጆችን ለማካፈል ቸል እንላለን። ወላጆች ልጆቻቸው የቤተሰባቸውን መንፈሳዊነት በቀላሉ እንደሚይዙ አድርገው በማሰብ የተሳሳተ ግምት ይወስዳሉ። ይህ አስተሳሰብ ሁሌም እንደሚሠራ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ልጆች የሚመለከቱትን ነገር ለራሳቸው የሚወስዱና ከዚያ የሚማሩ ቢሆንም፤ እነዚህ ታዳጊ የጌታ ቤተሰብ አባላት የግል ትኩረት ሊደረግላቸውና ከጌታ ጋር በግል የሚተዋወቁበት ሁኔታ ሊመቻች የሚገባ መሆኑ እውነት ነው። እጅግ ውጤታማ ለሆነው ኃይማኖታዊ አስተምህሮ ትኩረት መስጠት የግድ መሆኑን ዘዳ. 6 አጥብቆ ያስገነዝባል። በቤት ወስጥ የሚደረጉ መደበኞቹ የግልና የቤተሰብ አምልኮ ልማዶች ሊበረታቱ ይገባል። ጊዜን መሥዋዕት ያደረገና ቅን ጥረት የታከለበት ያላሰለሰ ጥረት ለልጆችና ለወጣቶች ሊደረግ ይገባል።

ኑኃሚን ካደረገቻቸው የወንጌል ጥረቶች ምን መማር እንችላለን? ሩት 1:8–22



የኑኃሚን ልብ በሐዘን መሰበሩን ሩት ተመልክታለች። ምራቷ ትታት እንድትሄድ ስትጎተጉታት የነበረችው ኑኃሚን የደረሰባትን እጦት እያስታወሰች በቁጣና በጭንቀት እግዚአብሔርን አጥብቃ አማረረች (ሩት 1፡15፣ 20-21)። ልጆች ምንም እንኳ ፍጽምና በጎደላቸው ወላጆች አማካኝት ከእርሱ ጋር ቢተዋወቁም--ወጣቶች ፍጹም ለሆነው አምላክ ሊኖራቸው የሚገባውን ቁርጠኝነት አስመልክቶ ሩት ከሰጠችው የሚልቅ ልብ የሚነካ ምስክርነት የለም።

ቤትን እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የወንጌል ዘር መዝሪያ ስፍራ የመመልከቱ ጽንሰ ሃሳብ በቤትዎ ነፍሳት ዙሪያ ባሎት አመለካከት ላይ ተጽእኖ የሚያደርገው እንዴት ነው? ያልዳኑ ዘመዶችዎን ወደ ክርስቶስ ለማጣት ከቤተሰቦ ጋር የተቀናጀ ጥረት ለማድረግ የሚያስችሎትን ዝግጅት ያድርጉ።

ሰኔ 11
Jun 18

አሸናፊው ሰላም


አዲስ ኪዳን በኃይማኖት ለተከፋፈለ ጋብቻ ምን ዓይነት ምክረ ሃሳብ ይሰጣል? 1ቆሮ. 7:12–15፣ 1ጴጥ. 3:1-2።



ክርስቲያን የትዳር አጋር የመሆን በረከት፡ ከማያምን ሰው ጋር በጋብቻ መቀጠል እግዚአብሔር የሚጸየፈው ወይም እነርሱንና ልጆቻቸውን ያሚያረክስ ይሆን--በሚል ሀሳብ ለገባቸው ወገኖች ጳውሎስ በአንድኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ምላሽ ይሰጣል። ጳውሎስ ነገሩ እንደዚያ አለመሆኑን ይናገራል። ጋብቻ የተቀደሰ እንደመሆኑ ከባልና ሚስት አንዳቸው ከተለወጡም በኋላ እንደ ቀድሞው ትሰስሩ መቀጠል ይኖርበታል።

አንዳቸው ክርስቲያን መሆናቸው ሌላኛውን የትዳር ጓደኛ እንዲሁም ልጆቻቸውን “ይቀድሳል”። “መቀደስ” የተሰኘው ቃል ትርጉም የማያምነው ባል ወይም የማታምነው ሚስት ከክርስቲያን ተጣማሪ ጋር አብሮ በመኖር የአምላካዊው ጸጋ በረከት ተቋዳሽ ይሆናሉ ከሚለው አኳያ ሊስተዋል ይገባል።

በእርግጥ ልብ የሚሰብር ቢሆንም አማኝ ያልሆነው የትዳር ተጣማሪ ፍቺ ለመፈጸም ሊወስን ይችላል። ምንም እንኳ ውጤቱ የከፋ ሊሆን ቢችልም ሁሌም ከሰብዓዊው የመምረጥ ነፃነት ጎን የሚቆመውና በምህረት የተሞላው አምላካዊ ቃል--“መለየት ከፈለገ ይለይ” ይላል። “አንድ ወንድም ወይም እህት በዚህ ሁኔታ የታሰሩ አይደሉም” (1ቆሮ. 7፡15)።

በሰላም ለመኖር መጠራት፡ ቤት በመንፈሳዊ ይዘቱ የመከፋፈል ተግዳሮት ቢገጥመው የክርስቶስ ሰላም ሊሰፍን የሚችልበት መንገድ ስለ መኖሩ ግልጽ የሆነ ምርጫ የእግዚአብሔር ቃል ያስቀምጣል። የትዳር አጋር አማኝ ባይሆንም ወይም ባትሆንም ጋብቻቸው ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስበት እንዲዘልቅ ተስፋ ማድረግ ተገቢ ነው። በአስቸጋሪ ወቅት ወንጌል የበላይነቱን እንዲወስድ መፍቀድና አማኙ አንድ ሥጋ የሆነችውን ወይም የሆናትን የትዳር አጋር ምቾትን መጠበቅ የግድ ነው። የትዳር ጓደኞች አማኝ ላልሆኑ ተጣማሪዎች የሚኖራቸው ኃላፊነት የት ድረስ ነው?



በአማኙ በኩል የሚገለጽ በፍቅር የተሞላ ደግነት፣ የማያወላዳ ታማኝነት፣ ትህትና የተሞላው አገልግሎትና ቆንጆ ምስክርነት--ክርስቲያን ያልሆኑትን የትዳር ተጣማሪዎች ልብ ለመንካት ታላቅ ዕድል ይፈጥራል። ክርስቲያን የትዳር ተጣማሪ ለክርስቶስ ካለው አክብሮት የተነሳ ራሱን ለትዳር ጓደኛው ያስገዛል (ኤፌ. 5፡ 21)። የትዳር ጓደኞች ራሳቸውን ለማያምኑ ተጣማሪዎቻቸው አሳልፈው ሲሰጡ፤ ሁሌም ቢሆን ተቀዳሚ ታማኝነታቸው ለክርስቶስ ነው። አንድ ሰው በህይወቱ ለአምላካዊው ፈቃድ ታማኝ መሆኑ፤ በጽንፈኛ የትዳር ጓደኛ እጅ ጥቃት የመቀበሉን ዕድል ያጠበዋል። በቤተ ክርስቲያንዎ ከማያምን ወይም ከማታምን የትዳር ጓደኛ ጋር ትግል ውስጥ ያለ ሰው አለ? ካለ ወይም ካለች በምን መንገድ ሊረዱ ይችላሉ?

ሰኔ 12
Jun 19

ቤተሰባዊውን ህይወት ለሌሎች ማጋራት


“መከተል” ወይም “መምሰል” የተሰኙት ቃላት በአዲስ ኪዳን ጥቅም ላይ የዋሉበትን መንገድ ይፈትሹ። እንደ ክርስቲያን ስለ መሆን እንዲሁም ስለ ማደግ ሂደት ምን ይነግሩናል? ምሳሌ በመሆንና ምስክር በመሆን መሃል ስላለው ዝምድና ምን ዓይነት ሃሳብ የሚሰጡ ይመስሎታል? 1ቆሮ. 4:16፣ ኤፌ. 5:1፣ 1ተሰ. 1:6፣ ዕብ. 6:12፣ 13:7፣ 3ዮሐ. 11።



ምሰሉ ለተሰኘው ቃል አጽንኦት የሚሰጠው አዲስ ኪዳን፤ በመማሩ ሂደት ምሳሌ መሆን አስፈላጊ ሚና እንዳለው ያረጋግጣል። ብዙዎች የሚያዩአቸውን ሰዎች ለመሆን የመፈለግ አዝማሚያ አላቸው። ይህ መርኅ ሌላውን ለመምሰል የሚደረግ አካሄድ የተለመደ በሆነበት ለአጠቃላዩ ግንኙነት--በተለይ ደግሞ በቤታችን ሊተገበር ይችላል።

ልጆች ወላጆቻቸውንና ወንድም እህቶቻቸውን ለመምሰል ይሞክራሉ። በጋብቻ የተሳሰሩ ጥንዶችም አንዱ ሌላውን የመምሰል ነገር አላቸው። ይህ ጽንሰ ሃሳብ ጥንዶችና ቤተሰቦች ለሌሎች ባለ ትዳርና ቤተሰቦች ምስክር መሆን የሚችሉበትን እጅግ አስፈላጊ ፍንጭ ይሰጠናል።

የማኅበራዊ ተጽእኖ ጉልበት፡ ሌሎች እኛን የሚመለከቱበትን ዕድል ስንሰጥና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የቤታችንን ተሞክሮ ስናጋራ ቤታችንን ተጠቅመን እንመሰክራለን። ብዙዎች ጥሩ ምሳሌ የሚሆንና ሊከተሉት የሚገባ ዓይነት ትዳር ወይም ቤተሰባዊ ግንኙነት የላቸውም። ከዚህ አኳያ የየሱስ መንፈስ እንዴት በየቤቶቻችን ልዩነት እንደሚያመጣ የሚያዩበት ዕድል ያገኛሉ። “ማኅበራዊ ተጽእኖ አስገራሚ ጉልበት ያለው ነገር ነው። ሌሎች ስለ እኛ የሚያውቁበት መሣሪያ ካደረግነው ልንጠቀመው እንችላለን።”—The Ministry of Healing, p. 354. እንደ ባለ ትዳር ሰዎችን ለምሣ፣ ለአንድነት ጊዜ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወደ ቤታችሁ ስትጋብዟቸው እንደ ምሳሌ የሚወስዱትን ነገር ይመለከታሉ። ፈክቶ የሚመለከቱት አብሮነት፣ አዎንታዊነት፣ ተግባቦት፣ ቅራኔ መፍቻ ስልቶችና ልዩነቶች የሚታረቁበት አካሄድ--በክርስቶስ የሆነውን ቤተሰባዊ ህይወት ይመሰክራሉ። ከዚህ ዐውድ ሁሌም በጥንቃቄ ልንይዘው የሚገባ ነገር ምንድን ነው? ኤር. 17:9፣ ዮሐ. 2:25፣ ሮሜ 3:23።



ክርስቶስን የሚከተሉትን አማኞች ይከተላሉ፡ ሁሉም ሰብዓዊ ምሳሌ ኅፀፅ ወይም እንከን አለበት። የክርስቲያን ቤት ምስክርነት ፍጹም ምሳሌ መሆን አይችልም። ምሰሉ በሚል የቀረበው የአዲስ ኪዳን አስተሳሰብ ሰዎች--ክርስቶስን የሚከተሉ አማኞችን እንዲከተሉ የቀረበ ጥሪ ነው። ጽንሰ ሀሳቡ--ሰዎች የክርስትናን እምነት እንደ እነርሱ ስህተት ሊሠሩ የሚችሉ ሥጋ ለባሾች ህይወት ውስጥ ሲመለከቱ ይህን እምነት ለራሳቸው ያደርጋሉ የሚል አንደምታ አለው።

ቤትዎ ለክርስትና ምስክርነት የተሻለ ምሳሌ እንዲሆን ምን ማድረግ ይችላሉ?

ሰኔ 13
Jun 20

ከአንዱ ወደ ሌላው የሚጋቡ ወዳጃዊ ማዕከሎች


እንግዳን ስለ መቀበል--በአያሌ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ ቤተሰቦች በትክክል ከሆነው አኳያ ከዚህ በታች የቀረቡትን ማመሳከሪያዎችን ያስተያዩ፡ ኢሳ. 58:67፣ 10–12፣ ሮሜ 12:13፣ 1ጴጥ. 4:9። በጥቅሶቹ የቀረቡትን የእንግዳ አቀባበል ልዩ ባህሪያት በጥንቃቄ ይመልከቱ። አብርሃም እና ሣራ (ዘፍ. 18:1–8)፡



ርብቃ እና ቤተሰቧ (ዘፍ. 24:15–20፣ 31–33)



ዘካርያስ (ሉቃ. 19:1–9)



እንግዳ መቀበል ሌላው ሰው የሚያስፈልገውን መሰረታዊ ነገር ማለትም ማረፊያ፣ ምግብና አብሮነት ማሟላት ይጠይቃል። እንግዳ መቀበል ራስን የመስጠት ፍቅር ተጨባጭ መገለጫ ነው። የሱስ ለተራበው ስንመግብና ለተጠማው ስናጠጣ ለእርሱ እንዳደረግን እንደሚቆጠር ሲያስተምር፤ እንግዳን መቀበል ከነገረ መለኮት አስተምህሮ ጋር እንዳጣመረው እንመለከታለን (ማቴ. 25፡34-40)።

ቤታችንን ለአገልግሎት ስንፈቅድ ጎረቤቶችን ምግብ ከምንጋብዝበት መሰረታዊው የእንግዳ አቀባበል ዘይቤ-ጉዳት ለደረሰበት መጠለያ እስከ መስጠት አልፈን ልንጓዝ እንችላለን። ምናልባት ግንኙነቱ ቀለል ያለ ጓደኝነትን፣ ከአንድ ሰው ጋር ጸሎት የሚያደርጉበትን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚያካሂዱበት ሁኔታ ሊያካትት ይችላል። እውነተኛ እንግዳ ተቀባይነት ልባቸው በአምላካዊው ፍቅር ከተነካና ፍቅራቸውን በቃላትና በድርጊት ለመግለጽ ከሚፈልጉ ወገኖች ይመነጫል።

ቤተሰቦች አንዳንዴ እንግዳ ለመቀበል የሚያስችሏቸው ሁናቴዎች አለመመቻቸታቸውን፣ ጊዜ ወይም ጉልበት እንደሌላቸው እንደ ሰበብ ሲያቀርቡ ይስተዋላሉ። ሌሎች ደግሞ ራሳቸውን ከማያምኑ ጋር ማዛመድ ብዙም ምቾት የማይሰጣቸው፣ ክህሎቱ የሌላቸውና ከተለመደው አልፈው ከሌሎች ጋር ቀረቤታ ለመፍጠር እርግጠኝነት የሚጎድላቸው ናቸው። አንዳንዶች ከሌሎች ጋር ቀረቤታ በመፍጠራቸው የተነሳ በህይወታቸው ሊደርስ የሚችልን ምስቅልቅል ከወዲሁ ማስቀረት ይፈልጋሉ። ብዙዎች የዘመናችን ቤተሰቦች እንግዳን መቀበል እና ማዝናናትን ያደባልቁታል። የቤትዎ ህይወት እርስዎ በግል የሚገኙበትን መንፈሳዊ ሁኔታ የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?

ሰኔ 14
Jun 21

ተጨማሪ ሀሳብ


Ellen G. White, “A Powerful Christian Witness,” pp. 35–39; “Attitude Toward an Unbelieving Companion,” pp. 348–352, in The Adventist Home; “Ministry of the Home,” pp. 349–355, in The Ministry of Healing; “The Ambassadors From Babylon,” pp. 340–348, in Prophets and Kings. በወንጌል ሥራ ቤት የሚኖረው ጉልበት፡ “እውነተኛ ቤት በሰብዓዊው ልብ እና ህይወት የሚኖረው ተጽእኖ ሊሰበክ ከሚችል ማንኛውም ብርቱ ስብከት የላቀ ነው. .. “ሰፊ ተጽእኖ ማሳደር ባንችልም፣ ችሎታችን አነስተኛ ቢሆንም፣ ጥቂት ብቻ አመቺ ሁናቴና ጊዜ ቢኖረንም ወይም የገበየናቸው ነገሮች ውሱን ቢሆኑም--የገዛ ቤታችንን መልካም አጋጣሚዎች በታማኝነት በመጠቀም የአስደናቂ አማራጮች ባለቤት መሆን እንችላለን።”—Ellen G. White, The Ministry of Healing, pp. 352, 355.


የመወያያ ጥያቄዎች




1.ወደ አንድ ሰው መኖሪያ ቤት መሄዱ ያሳደረበት ተጽእኖ ለክርስቶስ ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲወስን መንስኤ የሆነው ሰው እንዳለ በሰንበት ትምህርት ጥናት ይጠይቁ። እንዲህ ዓይነቱ የተለየ ስሜት እንዲፈጠር የሚያደርገው ምን እንደሆነ ተወያዩ። የሰንበት ትምህርት ጥናት ክፍላችሁ ከዚህ ተሞክሮ ምን መማር ይችላል?

2.የማያምን ባል ወይም የማታምን ሚስት የሚኖሩበትን ትዳር እንደ ክፍል ይህን ቤተሰብ እንዴት ተጨባጭ በሆነ መንገድ ማገልገል ትችላላችሁ? 3.በቤት ውስጥ ከእምነት በተቃራኒ ስለሚስተዋሉ አንዳንድ ተጽእኖና ግፊቶች ተወያዩ። አንዳንዶቹን ቁልቁል በጽሑፍ ካሰፈሩ በኋላ ከፊት ለፊታቸው መፍትሔያቸውን ለመጻፍ ይሞክሩ።

4.የክርስቲያኖች ግላዊ ህይወት ለልጆቻቸው፣ ለማያምን የትዳር ጓደኛ፣ ለሌሎች ዘመዶችና እንግዶች መመስከሪያ መንገድ ነው። እምነትን በቤት ውስጥ ማካፈል አንድ ሰው እንዲሆን የሚወደውን ያህል ዘመዶችንና እንግዶችን ወደ እውነት ለማምጣትና ለመለወጥ ሁሌም ፍጹም ባይሆንም፤ ፍጽምና የሚጎድላቸው የቤተሰብ አባላት ፍጹም የሆነውን አዳኝ መንገድ ለማሳየት የዘወትር ምኞታቸው ነው። በአዳኙ ስም በተጠቀሰው በደግነት የተሞላ እንግዳ አቀባበል አማካይነት ህይወታቸውን የሚነኳቸውን ሁሉ ወደ ጸጋው ግዛት ያመጧቸዋል። በእንግድነት ወደ ቤትዎ ለሚመጡ ቤትዎ ስለሚያሳድርባቸው ተጽእኖ አያስቡ። ደጃፍዎን አልፈው ለሚገቡ ሁሉ ቤትዎ የተሻለ የምስክርነት ቦታ እንዲሆን ምን ማድረግ ይችላሉ?