ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ. 7:5፣ ኤፌ. 1:7፣ ፊልጵ. 2:4–8፣ ኤፌ. 4:26-27፣ ያዕ. 1:19-20፣ ቆለ. 3:19፣ ማቴ. 7:12።
መታሰቢያ ጥቅስ:- “ተቆጡ፤ ነገር ግን ኃጢአት አትሥሩ፤’ በቁጣችሁ ላይ ጸሐይ አይግባ” (ኤፌ. 4:26)
ም
ርጥ የሚባል ቤተሰብ ሳይቀር የትግል፣ የውዝግብ ጊዜ ይገጥመዋል። ይህ
ደግሞ የወደቀው ዓለም ህይወት እውነታ ነው። የቆሻሻውን ማጠራቀሚያ
ዕቃ ደጅ የማውጣት ተራው የማን ነው? ወይም በዐሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ
ሴት ልጅዎ የቤት ሥራዋን ካልጨረሰች ወይም ደግሞ ወንዱ ልጅዎ እንደ ተነገረው
የቤት ውስጥ ሥራውን ካላከናወነ--እነዚህ ነገሮች ሊረብሹ ቢችሉም ግን ደግሞ
በቀላሉ መፍትሔ የሚያገኙ እጅግ አነስተኛ ጉዳዮች ናቸው።
በእርግጥ የቤተሰብን
ህይወት ሊያናውጡ የሚችሉ ሌሎች ጉዳዮችም አሉ። አማትና ምራት ሳይተያዩ
መሬት እንዲሉ በሁለቱ መሀል የሚከሰት አለመግባባት በእማወራዋ ትዳርና ጤና
ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጽኑ ችግር፣ በልጆቹ ላይ ጉዳት የሚያደርስ የአእምሮ
ችግር ያለው አባት፣ ከታች የወጣበትን ኃይማኖታዊ አስተዳደግ ግብረገብ በጎደለው
ሴሰኝነት ርግፍ አድርጎ የሚተው/ የምትተው ልጅ--ከብዙ በጥቂቱ መጠቀስ ይችላሉ።
እርስ በርሳችን እንድንዋደድ፣ (ዮሐ. 13:34፣ ሮሜ. 12:10) ከሰዎች ጋር በሰላምና
በስምምነት እንድንኖር (ሮሜ. 15:5፣ ዕብ. 12:14)፣ ትዕግሥተኞች፣ ደጎችና ርኅሩሆች
እንድንሆን (1ቆሮ. 13፡4)፣ ሌሎችን እንደ ራሳችን እንድናይ (ፊልጵ. 2፡3)፣ አንዳችን
የሌላውን ሸክም እንድንሸከም (ኤፌ. 4፡2) በተደጋጋሚ በአዲስ ኪዳን ተነግሮናል።
በእርግጥ እነዚህ ነገሮች በተግባር ሳይሆን በአፍ ሲነገሩ ይቀላሉ--ለገዛ ቤተሰቦቻችን
ጭምር። በዚህ ሣምንት ትምህርታችን በተለይ በቤተሰብ መሃል ሊነሱ የሚችሉ አነስ
ያሉ አስቸጋሪ ጊዚያቶችን ለማለዘብ የሚረዱ ነጥቦችን እንመለከታለን።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 7:5 እና ምሳ. 19:11። ከሌሎች ጋር ሊገጥሙን የሚችሉ ግጭቶችን ለማስወገድ የሚረዱን ሁለት አስፈላጊ መርኅዎች ምንድን ናቸው?
የመጽሐፈ ምሳሌ ጸሐፊ ብልህ ምልከታ አለው፡ “ጠብ መጫር ግድብን እንደ
መሸንቆር ነው፤ ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ” (ምሳ. 17፡14)። ጠብ ወይም
ግጭት አንዴ ከተጀመረ በቀላሉ ለማቆም አስቸጋሪ ነው። ሁለት ነገሮችን በመከተል
ግጭትን መከላከል እንደምንችል ሮሜ 14፡19 ይነግረናል--ሰላም በመፍጠርና አንዱ
ሌላውን በማነጽ። በቤተሰብ መሃል ለዛ ያለው ስምምነት ለመፍጠር እነዚህ ሁለት
መርኅዎች ምን ያህል መሰረታዊ ናቸው?
አንዳንዴ ግጭት ተከስቶ እርስዎ ኃላፊነት ሲወስዱ ሌላው አካል የሚለሳለስበት
ሁናቴ ይፈጠራል። ወደ ኋላ መለስ ብለው ጠቡ ሊፈጠር ይገባ እንደነበር ለማጤን
ይሞክሩ። “ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች፤ በደልን ንቆ መተውም መከበሪያው
ነው” (ምሳ. 19፡11)። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁኔታው በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት ውስጥ
የሚያመጣውን ልዩነት ያመዛዝኑ። ወይም ከዚያ ባለፈ በአምስት ወይም በዐሥር
ዓመታት ውስጥ ምን ዓይነት ልዩነት ያመጣል? ለምሳሌ ዛሬ ላይ ሲታይ ዋጋ ቢስ
ለሆኑ ነገሮች ስንት ትዳሮች አስቸጋሪ ሁናቴ ገጥሟቸዋል?
ከሌላው ሰው ማለትም ከባለቤትዎ፣ ከልጅዎ፣ ከጓደኛዎ፣ ከሥራ ባልደረባዎ ጋር
በሚኖሮት ንግግር ወይም አነጋጋሪ ጉዳይ ግጭት ነክ የሆነው ነገር ረዘም ላሉ ጊዜያቶች
ሰቅዞ እንዲይዞ ላለመፍቀድ ችግሩን በግልጽ አስቀምጠው ወደ ቀጣዩ ርዕሰ ነጥብ
ለማለፍ ይሞክሩ ይሆናል። ለእሰጣገባው መንስዔ የሆነው ጉዳይ በቁጣ መታጀብ
ከጀመረ ግን አቅጣጫውን መሳት ይጀምርና ግጭቱ ፈር እየለቀቀና እየተበላሸ
ይሄዳል። ይባስ ብሎ ቀደም ያሉ አነታራኪ ትውስታዎች መመዘዝም ይጀምራሉ
(በተለይ በባልና ሚስት መሃል ከሆነ)።
እሰጣገባውን ማለዘብ ከሚቻልባቸው
መንገዶች አንዱ ከግለሰቡ ጋር ላሎት ግንኙነት አዎንታዊ አጽንኦት መስጠት ነው።
ለግለሰቡና ለግንኙነታቸሁ አጥብቀው የሚጨነቁና የሚጠበቡ መሆንዎን ሌላው
ሰው እንዲረዳ ይፍቀዱ። አዎንታዊውን ስሜትዎን አንዴ ከገለጹ ወደ ተያዘው
ጉዳይ መመለስ ይችላሉ። አሁንም ቢሆን ነገር ግን የተሰኘውን ቃል ላለመጠቀም
ጥንቃቄ ያድርጉ። አዎንታዊውን አስተሳሰብ ተከትለው መናገር ጀምረው “ነገር ግን”
የሚሉትን ቃላት ጣልቃ ካስገቡ የቀደመውን በአሉታዊ ያፈርሱቦታል። የእርስዎን
ሀሳብ ካካፈሉ በኋላ ለሌላው ሀሳብ ጆሮዎን ይስጡ። የግለሰቡን አነጋገር እያንጸባረቁ
የሁላችሁንም ፍላጎት ምርጥ በሆነ መንገድ የሚያንጸባርቅ የመፍትሔ ሀሳብ ያቅርቡ
(ፊልጵ. 2፡4-5)።
አሁን አልፎ ሲያዩት ማስተዋል የጎደለው የቂል ጠብ እና ንትርክ ሆኖ
ስላገኙት ጉዳይ አሰብ ያድርጉ። ቢያንስ እንዲህ ያለው ነገር ዳግም
እንዳይከሰት ለመከላከል ካለፈው ተሞክሮ ምን መማር ይችላሉ?
እንደ ሰንበት ሁሉ ጋብቻም ከኤደን የአትክልት ስፍራ የሚመዘዝ እግዚአብሔር
ለሰብዓዊው ፍጡር ያበረከተው ስጦታ ነው። እኛ እንደ ሰባተኛው ቀን አክባሪ
የምጽአቱ ተጠባባቂ ሕዝብ፤ የነፍሳት ጠላት በሰንበትና በጋብቻ ላይ ያደረገውንና
እያደረገ ያለውን ነገር በሚገባ እናስተውላለን። ምርጥ የተባሉ ጋብቻዎች ሳይቀሩ
አልፎ አልፎ በጠብና ንትርክ ውስጥ ሲያልፉ መስተዋላቸው ያደባባይ ምስጢር
ነው።
የትዳር ተጣማሪዎች ለንትርኮች እንደ መፍትሔ ሊከተሏቸው የሚገቡ ጥቂት
መርኅዎች አሉ።
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኤፌ. 1፡7። የማንኛውም ትዳር አካል ሊሆን የሚገባ ምን ዓይነት
ወሳኝ መርኅ በጥቅሱ ቀርቦአል?
በተለይ ባለቤትዎ ይቅርታ የማይገባቸው ሆነው በተገኙበት ወቅት ይቅርታ ማድረግ መማርዎ የግድ ይሆናል። ይቅርታ ለሚገባው ሰው ማንም ቢሆን ይቅርታ ያደርጋል-እምብዛም ይቅርታ ባይባልም። እውነተኛ ይቅርታ ጌታ በክርስቶስ በኩል እኛን ይቅር እንዳለ፤ ይቅርታ የማይገባቸውን ይቅር ማለት ነው። የይቅርታ አካሄዳችን ይህን ታሳቢ ማድረጉ የግድ ይሆናል። ያለበለዚያ ትዳራችን ባይፈርስም እንኳ የሥቃይ ስፍራ መሆኑ አይቀሬ ነው። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ሮሜ 3፡23። በጥቅሱ የቀረበው መሰረታዊ መርኅ ምን ይመስላል?
እርስዎ ትዳር የመሰረቱት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ስሜታዊ፣ አካላዊና መንፈሳዊ
ጉዳት ከደረሰበት ኃጢአተኛ ጋር መሆኑን መቀበልዎ የግድ ይሆናል። ራስዎን ከዚህ
ሁኔታ ጋር ያስተካክሉ። የባለቤትዎን ስህተቶች ይቀበሉ፣ ይጸልዩ። ከእነዚህ ስህተቶች
ጋር መኖር ሊያስፈልጎ ቢችልም በስህተቶቹ አይብሰልሰሉ። ቅዱስና ፍጹም የሆነው
አምላክ ባለንበት ሁናቴ በክርስቶስ እንደሚቀበለን ሁሉ፤ እምብዛም ቅዱስና ፍጹም
ያልሆኑት እርስዎም ተመሳሳዩን ለባለቤትዎ ያድርጉ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ፊልጵ. 2፡4-8። በትዳር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም
ችግር ባላቸው ግንኙነቶች ይህን መርኅ ጥቅም ላይ ማዋል የምንችለው
እንዴት ነው?
ለመሆኑ ቁጣን የማያውቅ ማን አለ? ሆኖም ቁጣ በቤተሰብ አባል ላይ ሲያነጣጥር
ጠጠር ያለ ገጽታ ሊይዝ ይችላል። ይቅርታ ለማድረግ አሻፈረኝ የሚባልበት ዓይነት
ሁናቴ ሲከሰት፤ ቁጣ በአጠቃላይ በቤትና በቤተሰብ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና
ሥቃይ ሊያስከትል ወደሚችል መርዛማነት መለወጥ ይችላል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 4፡26-27፣ መክ. 7፡9። ከኃጢአት ተጠብቀን በቁጣ ዙሪያ
ያለንን ግንዛቤ ሚዛናዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በሁለቱ ጥቅሶች መካከል
ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
ያዕቆብ በተለይ አንዳንድ ድርጊታቸው፣ አመለካከታቸውና የሚናገሯቸው ቃላት ሊያስቆጣን ከሚችል የቤተሰብ አባሎቻችን ጋር ባለን ግንኙነት በተቻለን ሁሌም ልንተገብረው ስለሚገባ ነገር ምን ይለናል ያዕ. 1፡19-20?
የተበሳጩበት ነገር ካለ እንደ ጥቁር ደመና በህይወትዎ እንዲያንዣብብ በመፍቀድ
ፋንታ ወደ አንድ አዎንታዊ ሁኔታ ይለውጡት። በእርስዎ ላይ ጉዳት ለሚያደርሱ
ይጸልዩ፣ እነርሱን ይቅር በማለት በረከት ይሁኗቸው። በእርግጥ መጀመሪያ ላይ
ቀላል ላይሆን ቢችልም ነገር ግን ውሳኔ ላይ ሲደርሱና ወሳኔዎን አጥብቀው ሲይዙ፤
ለተቀረው እግዚአብሔር ይጠነቀቃል፣ ኃላፊነቱንም ይወስዳል።
አንዳንዴ የቁጣችን ሥር ከተወለድንበትና ካደግንበት ቤት ሊመዘዝ ይችላል።
ብዙውን ጊዜ የብስጩ ሰዎች ምንጭ ብስጩ ቤተሰብ እንደሆነ ይታመናል። ልጆች
ይህን ባህሪ ከቤተሰባቸው በመማር እንደ አርአያ ከቀዱ በኋላ ወደፊት ወደ ራሳቸው
ቤተሰብ ማለትም ወደ ልጆቻቸው ያጋቡታል። አንዳንዴ የቁጣ ምንጭ ቃየን
ወንድሙን እንዲገድል የገፋፋው ዓይነት መሟላት ያልቻለ ፍላጎት ወይም ምቀኝነት
ሊሆን ይችላል።
አንዳንዴ ለቁጣዎ በቂ ምክንያት ሊኖርዎ ቢችልም፤ ሆኖም ይህን እንደ ምክንያት
ተጠቅመው በቁጠኝነት መዝለቅ አይኖርቦትም። ቁጠኛ ከሆኑ ችግሩን አምነው
ይቀበሉ እንጂ ምክንያት ለመደርደር አይሞክሩ። ይልቁንም ጉዳዩን በአዎንታዊ
መንገድ መያዝ የሚችሉበትን መንገድ እግዚአብሔርን ይጠይቁ። ሐዋርያው ጳውሎስ
በዚህ ዙሪያ መልካም ምክረ ሃሳብ አለው፡ “ክፉን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ
አትሸነፍ” (ሮሜ 12፡21)።
ሁላችንም ብንሆን ህመምን ጨምሮ ሊያስቆጡን የሚችሉ ነገሮች
አያጡንም። ጥያቄው፡ እግዚአብሔር በሚሰጠን ኃይል፤ ራሳችንንና
በዙሪያችን ያሉትን ከቁጣ ዳፋ መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው
የሚል ይሆናል።
አንዳንዴ ያልተቋጨ ውዝግብና ቁጣ አሉታዊ ጥፋት ወደ ማድረስ ደረጃ ሊሸጋገር ብሎም በግንኙነት ላይ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል። ጥቃት ብዙ ዓይነት ገጽታዎች ሊኖሩት ይችላል--አካላዊ፣ ንግግራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ወሲባዊ ወዘተ። ማንኛውም ዓይነት ጥቃት የእግዚአብሔር መንግሥት ማዕከላዊ መርኅ ከሆነው ራስ ወዳድ ያልሆነ ፍቅር በተቃራኒ ይገኛል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ዮሐ. 4፡7-8፣ ቆለ. 3፡19። ግንኙነትን አስመልክቶ በጥቅሶቹ የምናገኛቸው ወሳኝ አስተምህሮዎች ምንድን ናቸው?
“ባሎች ሆይ፤ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው” (ቆለ. 3፡19)። መራራ
በሚል የቀረበው ቃል የቀደመ የግሪክ ፍቺው--የትዳር ተጣማሪዎች በባለቤታቸው
ላይ የሚያሳዩትን የማያባራ ቁጠኝነት ወይም መራራነት ተከትሎ የሚከሰተውን ብርቱ
የጥላቻ ስሜት ያመለክታል።
ባል በሚስቱ ላይ ወይም ሚስት በባሏ ላይ ጥለኛ ወይም
ሞገደኛ አይሁኑ ሲል ጳውሎስ በግልጽ ይናገራል። ግልፍተኝነት፣ ወሲባዊና አካላዊ
ጥቃት በክርስቲያን ባለ ትዳሮች ወይም ተጣማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት የሌለው
ባህሪ ነው። ይልቁንም የትዳር ጓደኛን መውደድ ተስማሚውና ደስ የሚያሰኘው ነገር
ነው።
ጳውሎስ ስለ ፍቅር መናገሩን ሲቀጥል ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው ይለናል።
ፍቅር አይመቀኝም፣ አይመካም፣ አይታበይም፣ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፣ ራስ
ወዳድ አይደለም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋር እንጂ
በዐመጽ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁል ጊዜ ይታገሳል፣ ሁልጊዜ ያምናል፣ ሁል ጊዜ ተስፋ
ያደርጋል፣ ሁል ጊዜ ጸንቶ ይቆማል።
ሁለቱም ተጣማሪዎች ከክፉ የተጠበቀና ሰላማዊ ግንኙነት ሲኖራቸው ጤናማ
የሚባለውን ግንኙነት ይመራሉ። ቁጣ ጤናማ በሆነ መንገድ ሲመራና ሲስተናገድ
አንዱ ሌላውን ማገልገሉ የተለመደ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ የጥቃት ሰለባዎች
ጥቃት ፈጻሚዎቻቸውን ለክፉ ያነሳሱ ወይም የተቀበሉት በደል የሚገባቸው
ይመስል የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል።
ጥቃት ፈጻሚዎች በሌላው ላይ ተጽእኖ
የሚያሳድሩና በተንኮል የተካኑ ሊሆኑ ከመቻላቸው አኳያ፤ የጥቃት ሰለባዎቻቸው
ለተቀበሉት በደል ኃላፊነቱን ራሳቸው መውሰድ እንዳለባቸው እንዲሰማቸው
ማድረግ ይችላሉ። ነገር ግን ማንም ቢሆን፣ በማንም ሰው ጥቃት ሊፈጸምበት
አይገባም። ጥቃት ፈጻሚዎችም ለገዛ ምርጫቸውና ድርጊታቸው ኃላፊነቱን
ራሳቸው ይወስዳሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ለጥቃት ሰለባዎች መጽናናት ያመጣል እንጂ
የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው አያደርግም። ይህ ደግሞ መልካም የምሥራች
ነው። አንዳንዴ ችግሮች ከቁጥጥር ውጪ ሲሆኑ ሰዎች ወደ ውጭ ወጥተው እርዳታ
ለመጠየቅ ሊፈሩ አይገባም።
አንዳንድ ባህሎች በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መፍቀዳቸው
ወይም እንዳላየ ማለፋቸው እጅግ አሳዛኝ ልምድ ነው። ባህሉ እንኳ
ቢፈቅድ ማንኛውም ክርስቲያን የእንዲህ ያለው አጉል ልምድ አካል
መሆን የሌለበት ለምንድን ነው?
“ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው፤ ኦሪትም፣ ነቢያትም በዚህ ይጠቃለላሉና” (ማቴ. 7፡12)። ይህንን መርኅ በቤተሰብዎ ብሎም ከቤተሰብዎ ውጪ መተግበር ስለሚችሉባቸው ሁሉም አግባቦች አሰብ ያድርጉ። እንዴት ሊያደርጓቸው እንደሚችሉና በእምነት ሊያደርጉ በሚችሉባቸው ጊዜያቶች ዙሪያ ያሎትን ቁርጥ ሀሳብ ከታች በቀረቡት መስመሮች ያስፍሩ።
የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊው ጳውሎስ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር
የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ለመቀደስም ፈልጉ፤ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት
አይችልምና” (ዕብ. 12፡14) ሲል ምክሩን ይለግሳል። እኛ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ
ብንወስድም አንዳንድ ጉዳት ያደረሱብን ሰዎች ግን አይሰሙንም፣ አይለወጡምም።
ምናልባት አንዳንዶች ይቅርታ ቢጠይቁንም ሌሎች ግን ላያደርጉት ይችላሉ። በተለይ
ቀደም ብለን የተነጋገርነው የይቅርታ ጉዞ ከቤተሰብ አባል ጋር የተያያዘ ከሆነ በዚህም
ሆነ በዚያ ጥቅሙ ለእኛው ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ ይቅርታ በተለይ በቤተሰብ መሃል መሰረታዊ ቅራኔ መፍቻ መንገድ
ነው። አንድ ሰው በእኛ ላይ ኃጢአት ሲሠራ ክርስቶስ እኛን እንደ ወደደ ይህን ሰው
የምንወድበትን መንገድ የእግዚአብሔር ጠላት ጥርቅም አድርጎ ለመዝጋትና በእኛና
በግለሰቡ መሃል ግድግዳ ለማቆም ደስታውን አይችለውም። ይቅርታ ማድረግ ለዚያ
መንገድ መፍትሔ ለማበጀት የምናደርገው ምርጫ ነው።
“ይቅርታ የተደረገልን ይቅርታ በማድረጋችን ሳይሆን እኛም ደግሞ ይቅር እንደምንል
ነው። የይቅርታ ሁሉ መሰረት ለእኛ የማይገባው የእግዚአብሔር ፍቅር ቢሆንም፤
ያንን ፍቅር የግላችን ማድረግ አለማድረጋችን ለሌሎች በሚኖረን አመለካከት
ይንጸባረቃል። ስለዚህ ክርስቶስ እንዲህ ይላል፡ ‘በምትፈርዱበትም ዐይነት
ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩትም መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል’ Matt. 7:2.”—Ellen
G. White, Christ’s Object Lessons, p. 251.
በተመሳሳይ በዳዮቹ ራሳችን ከሆንን ከበደልነው ሰው ጋር የነበረንን ግነኙነት
ወደ ቀድሞው ለመመለስ መሞከር ይኖርብናል። ይህም ባደረግነው ነገር የተጸጸትን
መሆናችንን ወደ ግለሰቡ ቀርበን በመንገርና ይቅርታ በመጠየቅ ይሆናል።
የሱስ በዚህ
ዙሪያ ሲናገር እንዲህ ይላል፡ “ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር
በምታቀርብበት ጊዜ ወንድምህ የተቀየመህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣ መባህን በዚያው
በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም
ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ” (ማቴ. 5፡23-24)። የጎዳን ሰው በደሉን
ተገንዝቦ ይቅርታ መጠየቁ መልካም እንደሆነ ሁሉ እኛም ተመሳሳይ ጥንቃቄ
የተሞላው አጸፋ መመለሳችን ጥሩ ነው።
ይቅር ሊባሉ እንደሚገባ ማሰብዎ ሌሎችን ይቅር ለማለት ሊረዳዎ
የሚችለው እንዴት ነው?
“ብዙውን ጊዜ ወላጆች ቤተሰብ በማስተዳደሩ ኃላፊነት
አንድ ግንባር አይፈጥሩም። አዘውትሮ እንደሚስተዋለው ከልጆቹ ጋር አነስተኛ ጊዜ
የሚያጠፋ አባት ለልዩ ልዩ ባህሪዎቻቸው እንግዳ ነው። ጥብቅና ጽኑም ነው። ንዴቱን
ስለማይቆጣጠር በስሜት ሊያርማቸው ይሞክራል። ይህን ለሚገነዘበው ልጅ ቅጣቱ
ራሱን እንዲያስገዛ በማድረግ ፋንታ የሚያስቆጣው ይሆናል።
ልጇ ጥፋት ሲሠራ
አንዴ የተመለከተች እናት በሁለተኛው በጽኑ ትቀጣዋለች። ልጆች ምን ሊከተል
እንደሚችል ስለማያውቁ ለጥፋታቸው ሳይቀጡ የሚቀሩባቸውን ሁናቴዎች ግዝፈት
ለማየት ይፈተናሉ። በዚህም የክፉው ዘር ተዘርቶ በማደግ ፍሬ ያፈራል”—Ellen G.
White, The Adventist Home, pp. 314, 315.
“ቤት የንጹህና ጥልቅ ፍቅር ማዕከል ሊሆን ይገባል።
የከበሩት ነገሮች ማለትም፡
ሰላም፣ ስምምነት፣ ፍቅርና ደስታ የቤተሰብ አባላት ልብ አካል እስኪሆኑ በየቀኑ በጽኑ
መንከባከብ ይገባል። የፍቅር ተክል ጥንቃቄ የተሞላው እንክብካቤ ካልተደረገለት
በቀር ይሞታል። እያንዳንዱን መልካም መርኅ የምንንከባከብ ከሆነ በነፍሳችን ውስጥ
ሊዳብር፣ ሊፋፋና ሊያብብ ይችላል። ሰይጣን በሰብዓዊው ልብ የሚተክላቸው-ምቀኝነት፣ በክፉ መጠርጠር፣ ክፉ ንግግር፣ ግልፍተኝነት፣ ጠባብነት፣ ራስ ወዳድነት፣
ክፉ ምኞትና እብሪተኝነት ሊነቀሉ የግድ ነው። እነዚህ ክፉ ነገሮች በነፍሳችን ውስጥ
እንዲኖሩ የምንፈቅድ ከሆነ ብዙዎችን ሊያረክሱ የሚችሉ ፍሬዎችን ያፈራሉ።
የከበሩ የፍቅር ፍሬዎችን ያጠወለጉና ነፍስን ያረከሱ መርዛማ ተክሎችን ስንቶች
የሙጥኝ ብለው ተንከባከቡ!”—Pages 195, 196.
፡
1.በጋብቻ ዐውድ ከተጻፈ መልእክት የተወሰደውን ይህን ጥቅስ
ያንብቡ፡ “በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን
እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ
ምንም ኃጢአት አልሠራም” (ዕብ. 4፡15)። ክርስቶስ ምርጥ በሆነ
መንገድ ከእኛ ጋር ለመዛመድ ራሱን በእኛ ቦታ እንደሚያስቀምጥ
ሁሉ እኛም ለትዳር ተጣማሪያችን ተመሳሳይ ማድረግ ይጠበቅብናል።
ክስተቶችን ከራስዎ ሳይሆን ከባለቤትዎ ዕይታ አኳያ ለመመልከት
ይሞክሩ። ባለቤትዎ ለአንድ ጉዳይ የሚኖራቸውን አተያይ፣ ጉዳዩ
በእርሳቸው ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ወይም ለጉዳዩ እንደዚያ ዓይነት
ስሜት ሊሰማቸው የቻለበትን ምክንያት ለመመልከት ይሞክሩ። ይህ
መርኅ ከባድ ሁናቴዎችን በማቅለል ረጅም መንገድ ሊጓዝ ይችላል።
በተመሳሳይ ከሌሎች ጋር ውዝግብ ውስጥ ሊከቱን በሚችሉ ሁናቴዎች
ይህን መርኅ መተግበር የምንችለው እንዴት ነው?
2.ቁጣ ሁሌም ኃጢአት መሆን ይችላል? በዚህ ዙሪያ ክፍል ውስጥ
ተወያዩ።