መጋቢነት፡ ልብ አነሳሹ ሞተር
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከየካቲት 17 - 23

ዘጠነኛ ትምህርት

February 24–March 2

የምስጋና ስጦታዎች 

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ. 6:19–21፣ ኤፌ. 2:8፣ 1ጴጥ. 4:10፣ ሉቃ. 7:37–47፣ 2ቆሮ. 8:8–15፣ 2ቆሮ 9:6-7፡፡

 

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፦ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ. 3፡16)፡፡

አ ምላካችን ለጋስ አምላክ ነው፡፡ ይህ ታላቅ እውነት እጅግ ብርቱ ሆኖ በየሱስ መሥዋዕትነት ታይቷል፡፡ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ. 3፡16)፡፡ “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!” (ሉቃ. 11፡13)፡፡
የእግዚአብሔር ጸባይ መስጠት፣ መስጠት ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ጸባይ ማንጸባረቅ የምንፈልግ ሁሉ መስጠት ይጠበቅብናል፡፡ “ራስ ወዳድ ክርስቲያን” ከሚለው ሀረግ የበለጠ ከተጨባጩ እውነታ ጋር የሚጋጭ ነገር የለም፡፡


ለተደረገልን በጎነት ምላሻችንን ከምናቀርብባቸው መንገዶች አንዱ ስጦታ ነው፡፡ ስጦታዎቻችን--ምስጋናችንንና ፍቅራችንን የምንገልጽበትን ዕድል ይሰጡናል፡፡ የሱስ የተዋጁትን ቅዱሳን እንኳን በደህና መጣችሁ ብሎ በሚቀበልበት በዚያ ቀን ጸጋውን ተቀብለው የዳኑ ወገኖችን ስንመለከት እነዚህ ነፍሳት የመንግሥተ ሰማይ ወራሾች የሆኑት በእኛ ስጦታ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡


በዚህ ሣምንት አንዳንድ ጠቃሚ የስጦታ ክፍሎችን እንመለከታለን፡፡ ከገንዘባችን፣ ከጊዜያችንም ሆነ ከመክሊታችን ላይ በለጋስነት መቸር ማለት--ባመንነው መሰረት መመላለስና የምናገለግለውን የእግዚአብሔር ባህሪ በጠንካራ መንገድ መግለጽ ነው፡፡

የካቲት 18
February 25
 

“ሀብትህ ባለበት”

 

ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ማቴ. 6፡19-21፡፡ ምንም እንኳ ለጥቅሶቹ ዕንግዳ ባንሆንም፤ ምድራዊው ሀብትና ንብረት በእኛ ላይ ሊኖረው ከሚችለው ብርቱ ተጽእኖ ነፃ የምንሆነው እንዴት ነው? ቆለ. 3፡1-2፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


“ ‘ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናልና’ ” (ማቴ. 6፡21) ሲል ክርስቶስ ይነግረናል፡፡ የዚህ መግለጫ ሙሉ ዐውደ ሃሳብ ቀደም ባሉት ሁለት ቁጥሮች ማለትም--ሀብትን በምድርና በሰማይ በማከማቸት መሃል ያለው ልዩነት በንጽጽር ቀርቦአል፡፡ በምድር የሚከማቸው ሀብት በሶስት ቃላት ይኸውም፡ ብል፣ ዝገት እና ሌባ (ማቴ፣ 6፡19) በሚል ተገልጾአል፡፡ እነዚህ ሁሉም ምድራዊ ሀብታችን ምን ያህል ጊዜያዊና መንገደኛ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ምድራዊ ነገሮች ምን ያህል በፍጥነት ሊጠፉ እንደሚችሉ የማያውቅ ከቶ ማን አለ? “በዚህ ምድር ማንኛውም ነገር ሊበሰብስ፣ ሊጠፋ፣ ሊሰረቅና ሊታጣ የሚችል እንደመሆኑ--ተለዋዋጭ፣ የማያስተማምንና ደኅንነቱ የማይጸና ነው፡፡ ሰማይ ግን የምድር ተቃራኒ እንደመሆኑ በዚያ ማንኛውም ነገር ዘላለማዊ፣ ጸንቶ የሚኖር፣ አስተማማኝ ደኅንነት ያለውና የማይጠፋ ነው፡፡ —C. Adelina Alexe, “Where Your Heart Belongs,” in Beyond Blessings, edited by Nikolaus Satelmajer, (Nampa, Idaho: Pacific Press Publishing Association, 2013), p. 22.

ወደ ንብረትዎ መልከት ያድርጉ፡፡ ያፈሩት ሀብት የቱንም ያህል አነስተኛ ሊሆን ቢችል የኋላ ኋላ መወገዱ አይቀርም፡፡ ይሁን እንጂ ብልህ መጋቢ ሀብቱን ሰላማዊ ስፍራ ከሆነው ሰማይ ውጪ ማኖሩ ሊያሳስበው ይገባል፡፡ በዚያ የተከማቸ ሀብት--የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ ሌብነት ወይም ዝርፊያ አያሰጋውም፡፡
ማቴ. 6፡19-21 የመጋቢነትን እጅግ አስፈላጊ ጽንሰ ሃሳብ ይዟል፡፡ ያፈሩት ሀብት ልቦን ከመሳብ፣ ከመጥለፍ፣ ከመነዝነዝና ከማጥመድ አይቦዝንም፡፡ በቁሳዊው ዓለም ልብ የሚከተለው ሀብትን በመሆኑ፤ ሀብት የሚገኝበት ስፍራ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡ በምድራዊው አስፈላጊ ነገርና ጥቅም ላይ አብልጠን ትኩረት ካደረግን ስለ ሰማያዊ ነገሮች ማሰብ አዳጋች ይሆንብናል፡፡


በእግዚአብሔር እናምናለን እየተባለ ልብ ግን ያለው በምድራዊው መዝገብ ላይ ከሆነ ይህ--መመጻደቅ ነው፡፡ ተግባራችን ከአንደበታችን ከሚወጣው ቃል ጋር መስማማት አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር በምድር ያለውን ሀብታችንን በዐይነ ሥጋ ብንመለከተውም፤ ነገር ግን መባችንና ስጦታችን በሰማይ መከማቸቱን በእምነት ልናይ ይገባል (2ቆሮ. 5፡7)፡፡ ምንም እንኳ የሚያስፈልጉን ነገሮች በተጨባጭ መሟላት የሚገባቸው ቢሆንም ነገር ግን ዘላለማዊ ባህሪ ያለውን ትልቁን ሥዕል ሁሌም በአእምሮአችን ልናኖር የተገባ ነው፡፡


ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ዕብ. 10፡34፡፡ ጳውሎስ ምድራዊውንና ሰማያዊውን ሃብት በንጽጽር በማቅረብ ምን ዓይነት አስፈላጊ ነጥብ ያነሳል?

የካቲት 12
February 26
 

የአምላካዊው ጸጋ መጋቢዎች


በኤፌ. 2፡8 መሰረት ሌላው በእግዚአብሔር የተሰጠን ነገር ምንድን ነው?


ጸጋ “የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፡፡” ጸጋ ለእኛ የማይገባ አምላካዊ ስጦታ ነው፡፡ እግዚአብሔር በዚህች ምድር ላይ ጸጋውን አፍስሶአል፡፡እኛ የማንቃወመው ከሆነ ይህ ጸጋ ቁልቁል ወደ ህይወታችን ወርዶ ለአሁንና ለዘላለም ይለውጠናል፡፡ ሰማያዊው ባለጠግነትና ብርታት በሙሉ በእግዚአብሔር ጸጋ ውስጥ ተካትቶአል (2ቆሮ. 8፡9)፡፡ መላእክት ሳይቀሩ በዚህ ወደር የለሽ ስጦታ ይደነቃሉ (1ጴጥ. 1፡12)፡፡


እግዚአብሔር ከሰጠን ስጦታዎች ሁሉ እጅግ የከበረው በየሱስ ክርስቶስ የተሰጠን ጸጋ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ጸጋው ባይሰጠን ያለ ተስፋ በቀረን ነበር፡፡ ኃጢአት በሰው ልጆች ላይ ያለው ተጽእኖ እጅግ ግዙፍ በመሆኑ ሰብዓዊው ፍጡር ከዚህ አሳዛኝ ክስተት ራሱን ነፃ ማድረግ አይቻለውም፡፡ ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ እንኳ በራሱ ህይወት ሊሰጠን አይችልም፡፡ “ታዲያ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? ከቶ አይደለም፤ ሕግ የተሰጠው ሕይወትን ለማስገኘት ቢሆን ኖሮ፣ በርግጥም ጽድቅ በሕግ በኩል በተገኘ ነበር፡፡” (ገላ. 3፡21)፡፡ ደግሞም እኛን ሊያድን የሚችል ሕግ ቢሆን፤ የእግዚአብሔር ሕግ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ሕግ ያን ማድረግ እንደማይችል ጳውሎስ ተናግሯል፡፡ ከዳንን--የምንድነው በጸጋው ብቻ ይሆናል፡፡


ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 4፡10፡፡ መጋቢነት ከጸጋ ጋር እንዴት ይዛመዳል? ለእግዚአብሔርና ለሌሎች መስጠት አምላካዊውን ጸጋ እንዴት ሊያሳይ እንደሚችል ያስረዱ፡፡


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


አምላካዊውን የጸጋ ስጦታ ስንቀበል በምላሹ “የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ” (1ጴጥ. 4፡10) እንሆናለን ሲል ጴጥሮስ ተናግሯል፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሔር ስጦታዎችን ሰጥቶናል፡፡ እኛ ደግሞ ከዚያ ከተሰጠን ላይ መልሰን መስጠት ያስፈልገናል፡፡ በጸጋው የተሰጠን ስጦታ ራሳችንን ደስ ለማሰኘትና ለግል ጥቅማችን ብቻ ሳይሆን የወንጌልን ሥራ ለማፋጠን ጭምር ነው፡፡ በነፃ ስለተሰጠን (ጸጋ ማለት ይኸው ነው) አቅማችን በፈቀደ መጠን በነፃ መስጠት ይጠበቅብናል፡፡


በእግዚአብሔር ስለተሰጦት ሁሉም ነገሮች ያስቡ፡፡ በነፃ ለተሰጦት ጸጋ መጋቢ መሆን የሚችሉባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

የካቲት 20
February 27
 

ምርጡ ስጦታችን


ጥቅሱቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 7፡37-47፡፡ ታሪኩ ስጦታ ለማቅረብ ትክክለኛው መነሻ ምክንያትን ምን መሆን እንዳለበት ያስተምረናል?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


ማርያም ወደ ክፍሉ ስትገባ የሱስ በጠረጴዛው ፊት ማዕድ ተቀምጦ ተመለከተችው፡፡ ከዚያም ውድ ዋጋ ያለውን የአልባስጥሮስ ሽቶ ብልቃጥ ሰብራ አፈሰሰችበት፡፡ አንዳንዶች አጉል ህይወት የኖረች ሴት መሆኗን ከግምት በማስገባት ይህ ድርጊቷ ተገቢ እንዳልሆነ አሰቡ፡፡


ነገር ግን ማርያም ከእርኩሳን መናፍስት ነፃ ሆና የተፈወሰች ሴት ነበረች (ሉቃ. 8፡2)፡፡ ከዚያም ለዓልአዛር ትንሳኤ ምስክር ከሆነች በኋላ በከፍተኛ ምስጋና የተሞላች ሴት ሆነች፡፡ በጣም ውድ ንብረቷ የነበረውን ሽቶ፤ ለየሱስ አመስጋኝነቷን የምታሳይበት መንገድ አድርጋ ተጠቀመችበት፡፡


ይህ ታሪክ ስጦታ ስንሰጥ እውነተኛው መነሻ ምክንያታችን ምስጋና ሊሆን እንደሚገባ ይነግረናል፡፡ ደግሞስ በዋጋ ሊተመን ለማይችለው የጸጋ ስጦታው ምን ሌላ ምላሽ ሊኖረን ይችላል? አምላካዊው ቸርነት እንድንሰጥ ያበረታታናል፡፡ ቸርነቱ ከምናቀርበው ምስጋና ጋር ውህደት ሲፈጥር ጊዜያችንን፣ መክሊታችንን፣ ሀብታችንንና አካላችንን ያካተተ ትርጉም ያለው ስጦታ ይሆናል፡፡


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 34:26፣ ዘሌዋ. 22:19–24፣ ዘኁ. 18:29፡፡ ምንም እንኳ ዐውደ ጽሑፉ ከዛሬው ዓለም ፍጹም የተለየ ቢሆንም ነገር ግን ከምናቀርበው ስጦታ አኳያ ከጥቅሶቹ ልንወስድ የሚገቡን መርኅዎች ምንድን ናቸው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ምንም እንኳ ምርጥ ያልናቸው ስጦታዎች የልባችንን የማያደርሱ ቢመስሉንም በእግዚአብሔር ፊት ግን ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ ምርጥ የሆነውን ለእግዚአብሔር መስጠታችን በህይወታችን ውስጥ እርሱን ማስቀደማችንን ያሳያል፡፡ መቼም የሆነ ውለታ ፍለጋ ስጦታ አንሰጥም፡፡ ይልቁንም በክርስቶስ የሱስ ለተሰጠን ነገር ከማመስገንና ከማድነቅ የተነሳ የስጦታ እጆቻችንን እንዘረጋለን፡፡


“በምስጋና የተሞላ ፍቅር፣ አምልኮና ቸርነት ትንሽዋን ስጦታ የመስጠት ተነሳሽነትን ይፈጥራል፡፡ መለኮታዊ መዐዛ የተላበሰው በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመሥዋዕት ስጦታ እጅግ የከበረ ዋጋ አለው፡፡ ነገር ግን መስጠት የምንችለውን ያህል ቤዛ ለሆነልን አዳኝ ለመስጠት ፈቃደኞች ከሆንን በኋላ በእርግጥ ምን ያህል የምስጋና ዕዳ ለእግዚአብሔር እንዳለብን ከተመለከትን፤ ለእኛ የከበረ ብለን ያቀረብነው ማንኛውም ስጦታ በጣም አነስተኛና በቂ እንዳልሆነ ይሰማናል፡፡ ሆኖም ይህን ለእኛ ምስኪን ሆኖ የታየንን ስጦታ መላእክት እንደ መልካም መአዛ ገጸ በረከት በዙፋኑ ፊት ያቀርቡና ተቀባይነት ያገኛል፡፡” —Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 3, p. 397.

የካቲት 21
February 28
 

የልብ መነሻ ምክንያቶች


ቀደም ባለው ትምህርት የምስኪኗን መበለት ልግስና ታሪክ ተመልክተን ነበር፡፡ የእርሷ መባ ከሌሎቹ ስጦታዎች ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ቢመስልም ነገር ግን እውነተኛውን የባህሪዋንና የልቧን ተፈጥሮ ያሳየ ስለ ነበር “እርሷ ግን የሰጠችው በደኻ ዐቅሟ ያላትን መተዳደሪያ በሙሉ ነው” (ሉቃስ 21፡3) ብሎ የሱስ እንዲናገር መንስኤ ሆናው ነበር፡፡


እግዚአብሔር ብቻ (ያዕ. 4፡12) እውነተኛውን የእኛን መነሻ ምክንያት ያውቃል (ምሳ. 16፡2፣ 1ቆሮ. 4፡5)፡፡ አትረፍርፎ መስጠት እምብዛም የእምነታችንን ጥልቀት ስለማይጠይቅ፤ ከተሳሳተ መነሻ ምክንያት ተነስተን ትክክለኛ ነገር ልናደርግ የምንችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ስለ ሌሎች በጎ ሲባል መሥዋዕት የሚያስከፍል ስጦታ ስንሰጥ፤ በእርግጥ ይህ ልግስናችን ስለ ልባችን የሚለው ብርቱ ነገር አለው፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ቆሮ. 8፡8-15፡፡ ጳውሎስ ስለ መስጠትና ስለ መስጠት መነሻ ምክንያቶች ምን እያለ ነው? መጋቢነትን አስመልክቶ ከጥቅሶቹ ምን ዓይነት መርኅዎችን መውሰድ እንችላለን?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


ለመስጠት የቱንም ዓይነት መነሻ ምክንያት ሊኖር ቢችልም ነገር ግን ሂደቱ ከእኔነት ራስን ለሌሎች መሥዋዕት ወደ ማድረግ ያሸጋግራል፡፡ ይህ በራስ ወዳድነትና በመስጠት መካከል የሚደረግ የማያቋርጥ ጦርነት ከማንኛውም መንፈሳዊ ውጊያ በላይ በብርቱ ተጋድሎ የተሞላ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት በአንድ ወቅት የጋመ ፍም የነበረን ልብ እንደ በረዶ ያቀዘቅዛል፡፡ ችግሩ የሚከሰተው ራስ ወዳድነት የክርስትና ተሞክሮአችን አካል እንዲሆን ስንፈቅድና ለዚሁ ራስ ወዳድነታችን ማመካኛ እየፈለግን በክርስቶስ ስም ማድረግ ስንጀምር ነው፡፡


የሁሉም ነገር ሥረ መሰረት አንድ ቃል ሲሆን ይኸውም ፍቅር ነው፡፡ ለሌሎች በጎ ሲባል ራስን መሥዋዕት አድርጎ እስከ መስጠት ፈቃደኛ የመሆን ፍቅር እኔነት ካልተካደ በቀር ተገልጦ መታየት አይችልም፡፡


የእግዚአብሔር ፍቅር በሕይወታችን መንጸባረቅ ካልቻለ በቀር መስጠታችን የእግዚአብሔርን ፍቅር አያንጸባርቅም፡፡ የራስ ወዳድ ልብ ዝንባሌ ወደ ራሱ ብቻ በመሆኑ ራሱን ብቻ ይወዳል፡፡ እኛ እንደ ተወደድን ሁሉ ሌሎችን መውደድ መማር እንችል ዘንድ ጌታ የልባችንን “ሸለፈት” እንዲገርዝ እንጠይቀው (ዘዳ. 10:16)፡፡


የሁሉም እውነተኛ ልግስና መሰረት የሆነው ፍቅር የአጠቃላዩ የክርስትና ለጋስነት ድምር ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር እኛም ለሌሎች የፍቅር አጸፋ እንድንሰጥ መንፈሳችንን ይቀሰቅሳል፡፡ ይህ ደግሞ ለመስጠት ዋና መነሻ ምክንያት ነው፡፡
ከፍቅር ስሜት ይልቅ ከግዴታ አኳያ በፈቃደኝነት መስጠት ምን ችግር አለው?

የካቲት 22
March 1

የመስጠት ተሞክሮ


ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው ትክክለኛውን የእግዚአብሔር ጸባይ ሊገልጥ ነው ካልን አሁን አንድ ነገር ግልጽ ሊሆን ይገባል፡ እግዚአብሔር ይወደናል፣ ለእኛ እንዲሆን የሚሻውም ምርጥ የሆነውን ብቻ ነው፡፡ እርሱ ፈጽሞ ጉዳት የማያደርስብንን፣ ለገዛ ጥቅማችን የሚበጀውን ብቻ እንድናደርግ ይጠይቀናል፡፡ ይህ ደግሞ ለተሰጠን ነገር ደግ፣ ለጋስ፣ ፍልቅልቅና ደስተኛ ለጋሾች እንድንሆን እርሱ ያደረገልንን ጥሪን ያካትታል፡፡ በሙሉ ፈቃደኝነታችን ላይ የተመሰረተው የልግስና ስጦታችን እንደ ተቀባዮቹ ሁሉ ለገዛ ራሳችን--ለሰጪዎቹ ጥቅም የሚያስገኝ ነው፡፡ ከመቀበል ይልቅ መስጠት ምን ያህል የተባረከ እንደሆነ በዚህ መልኩ የሚሰጡ ራሳቸው ብቻ ያውቃሉ፡፡


ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ 2ቆሮ. 9፡6-7፡፡ እንዴት መስጠት እንዳለብን ጥቅሱ ጠቅለል አድርጎ የሚያቀርበው ሃሳብ ምን ይመስላል?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


በልግስና መስጠት እጅግ ግላዊና መንፈሳዊ ድርጊት ሊሆን ይገባል፡፡ በክርስቶስ ለተሰጠን ነገር ምስጋናችንን የምንገልጽበት የእምነት ሥራ ነው፡፡
“እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ” (ያዕ. 2፡20 /1962 ትርጉም/) እንደሆነ ሁሉ መስጠት እምነት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ እምነታችን እንዲጨምር ከተፈለገ በተግባር ከመግለጽ ውጪ ሌላ ምንም የተሻለ ነገር የለም፡፡ ይኸውም እምነታችን ፈልቆ እንዲወጣ የሚያደርጉ ነገሮችን መተግበር ነው፡፡ በነጻና በልግስና ስንሰጥ የክርስቶስን ጸባይ የምናንጸባርቅበት ጎዳና ላይ ነን፡፡ በገዛ ድርጊታችን እርሱን እየተለማመድን እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል አብልጠን እየተማርን ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ መልኩ የሚፈጸም የልግስና ተግባር በጌታ ፊት ተአማኒነትን በመገንባት “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ፤ እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ቡሩክ ነው!” ለማለት ዕድል ይሰጠናል (መዝ. 34፡8)፡፡


“በየሱስ ፊት ላይ የሚያበራው ክብር የመሥዋዕትነት ፍቅር ሆኖ ይታያል፡፡ ከቀራንዮ የሚፈነጥቀው ብርሃን ራስን ለሌላ አሳልፎ የመስጠት ፍቅር ሲሆን ይህም ፍቅር ለምድራዊና ለሰማያዊ ሕይወት መመሪያ ሕግ ነው፡፡ ‘የራስዋን የማትሻ ፍቅር’ የምትመነጨው ከእግዚአብሔር ልብ ነው፡፡ ትሑቱና ራሱን ያዋረደው የሱስ ሰው ሊደርስበት በማይችለው ብርሃን የሚኖረውን እግዚአብሔር ባሕሪ ገለጸ፡፡” የዘመናት ምኞት ገጽ 9-10 (አማርኛው ትርጉም)፡፡
ከተሰጠዎት በላይ በነፃ እና በልግስና በመስጠት እምነት በተጨባጭ እያደገ የሚሄድበትን እውነታ የተለማመዱበት መንገድ ምን ይመስላል?

የካቲት 23
March  2
 

ተጨማሪ ሃሳብ፡፡-

 

“የነፃነት መንፈስ የሰማይ መንፈስ ሲሆን፤ የራስ ወዳድነት መንፈስ ደግሞ የሰይጣን መንፈስ ነው፡፡ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው የክርስቶስ ፍቅር እነሆ በመስቀል ላይ ተገለጠ፡፡ ሰብዓዊው ፍጡር ይድን ዘንድ ያለውን ሁሉ ከሰጠ በኋላ ከዚያም ራሱን መሥዋዕት አደረገ፡፡ እያንዳንዱ የዚያ የተባረከ አዳኝ ተከታይ ቅን ይሆን ዘንድ የክርስቶስ መስቀል ተማጽኖውን ያቀርባል፡፡ በዚያ በጉልህ የተቀመጠው መርኅ መስጠት፣ መስጠት የሚል ነው፡፡ ይህ በቅን ልብ ገቢራዊ የሚሆን የልግስና ተግባር የእውነተኛ ክርስቲያን ህይወት ፍሬ ነው፡፡ ምድራዊው መርኅ መያዝ፣ መሰብሰብ፣ ማጋበስ ሲሆን፤ በዚህም ደስታ ይገኛል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ሆኖም ፍሬው ሁሉ ሥቃይ፣ መከራና ሞት ነው፡፡”—Ellen G. White, in Advent Review and Sabbath Herald, Oct. 17, 1882.

የመወያያ ጥያቄዎች:-፡

 

  1. ስስትን ከክርስቶስ መንፈስ ጋር በእጅጉ ተቃራኒ የሚያደርገው ምንድን ነው? በኃጢአት የወደቀው ሰብዓዊ ፍጡር ከሚያዘነብልበት ተፈጥሮው በተቃራኒ ህሊናችን የሚፈቅደውን በማድረግ ራሳችንን መጠበቅ የምንችልባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?
  2. “እያንዳንዱ ሰው በቅሬታ ወይም በግዴታ ሳይሆን፣ በልቡ ያሰበውን ያህል ይስጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል” (2ቆሮ. 9፡7)፡፡ “በደስታ” በሚል የተተረጎመው ይህ የግሪክ ቃል በአዲስ ኪዳን የምናገኘው አንድ ስፍራ ላይ ብቻ ሲሆን በእንግሊዝኛው “በመፍነክነክ” የሚል ፍቺ አለው፡፡ አባባሉ ስለ አኳኋናችን ምን ይነግረናል?
  3. በክርስቶስ የተቀበሏቸውን ነገሮች በሙሉ በዝርዝር ይጻፉ፡፡ ስለሚጽፏቸው ነገሮች ይጸልዩባቸው፡፡ ለተቀበልናቸው ነገሮች ምላሽ መስጠት ለምን እንዳስፈለገ እነዚህ ያሰፈሯቸው ዝርዝሮች ምን ሊያስተምሩን ይገባል?
  4. ራስ ወዳድነት--ራስን ከንቱ ለማድረግ አስተማማኝ ጎዳና የሆነው ለምንድን ነው?
  5.  በአሁኗ ደቂቃ በእርስዎ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በእጦት የምትገኝን እህት ወይም ወንድም አሰብ ያድርጉ፡፡ ዛሬ ነገ ሳይሉ አሁኑኑ ወደ ግለሰቡ ደርሰው ለማገልገል ምን ማድረግ ይችላሉ? ጉዳዩ ብርቱ መሥዋዕትነት የሚያስከፍሎ ቢሆን እንኳ ምን ማድረግ ይችላሉ?