መጋቢነት፡ ልብ አነሳሹ ሞተር
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከየካቲት 3 - 9

ሰባተኛ ትምህርት

February 10–February 16
 
ከእግዚአብሔር ጋር በታማኝነት መመላለስ

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሉቃ. 16:10፣ ሌዋ. 27:30፣ ዘፍ. 22:1–12፣ ዕብ. 12:2፣ ሉቃ. 11:42፣ ዕብ. 7:2–10፣ ነኸ. 13፡፡

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፦ “ ‘በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው፡፡ ’ ” (ሉቃ. 8፡15)፡፡

ለመሆኑ ቅንና በጎ ልብ ስንል ምን ማለታችን ነው? እንዴትስ ይገለጣል?

ዘመናዊው ባህል ብዙውን ጊዜ ሐቀኝነትን እንደው በደምሳሳው በአንጻራዊ የግበረገብ ሕግነት ብቻ ይመለከተዋል፡፡ አብዛኛው ሰው አልፎ አልፎ ታማኝነት ቢጎድለውም ነገር ግን ጥሰቱ የበዛ እስካልሆነ ድረስ ተቀባይነት እንዳለው ተደርጎ ይታመናል፡፡ በተጨማሪ የታማኝነትን መጓደል ያሳያሉ ተብለው የተቀመጡ ልዩ ልዩ ሁናቴዎች አሉ፡፡

እውነትና ታማኝነት ሁሌም አይነጣጠሉም፡፡ በእርግጥ እኛ ታማኞች እንድንሆን በሚያስችለን ዝንባሌ አልተወለድንም፡፡ ሐቀኝነት እያደር የምናስተውለው ግብረገባዊ ምግባርና የአንድ መጋቢ ሥነ ምግባር እምቡጥ ባህሪ ነው፡፡

ታማኝነትን ስንለማመድ መልካም ነገሮች ከውስጣችን መውጣት ይጀምራሉ፡፡ ለምሳሌ ሐሰት ስንናገር ቢነቃብንስ? በሚል ወይም ያንን ለመሸፋፈን በሚደረግ ሥጋት ውስጣችን አይጨናነቅም፡፡ በዚህና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች የተነሳ ሐቀኝነት የከበረ ዋጋ የተላበሰ ግላዊ ባህሪ ነው--በተለይ በአስቸጋሪ ሁናቴዎች ውስጥ ወድቀን ፈተና በቀላሉ ወደ ታማኝነታችን የሚያመራ ሲመስል፡፡

በዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን አሥራትን መመለስ በመለማመድ የታማኝነትን መንፈሳዊ ጽንሰ-ሃሳብ እንመለከታለን፡፡ በተጨማሪ አሥራት ለመጋቢው ብሎም ለመጋቢነት ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ እንመለከታለን፡፡
 
የካቲት 4
February 11
 
በትንሽ ነገር ታማኝ የመሆን ጉዳይ

ታማኝነትን ማጉደል--አብዛኞቻችን በጋራ የማንወደው ነገር ነው፡፡ በተለይ በሌሎች ተገልጦ መመልከቱን አንወደውም፡፡ በእርግጥ በራሳችን ደርሶ መመልከቱ ቀላል ባይሆንም--ከሆነ ግን--ምክንያት ደርድረን የተሠራውን ስህተት ማቃለልና ነገሩ የሚያስከትለውን ጉዳት ዝቅ አድርጎ ማቅረብ ይቀናናል፡፡ ይሄ እንኳ ያን ያህል የከፋ አይደለም . . . ምን አለው በጣም ትንሽ ነገር አይደል እንዴ?… ምንም እንኳ ብዙ ጊዜ ራሳችንን ብናታልልም እግዚአብሔርን ግን ፈጽሞ ማሞኝት አንችልም፡፡

“ታማኝ አለመሆን በሁሉም ደረጃ እየተስተዋለ ያለ ልምድ መሆኑ እውነትን አምኜ ተቀብያለሁ ያለው ወገን በለብታ ውስጥ ለመመላለሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከክርስቶስ ጋር ትስስር ሳይፈጥሩ የገዛ ነፍሳቸውን በከንቱ ይሸነግላሉ፡፡” —Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 4, p. 310.

“በትንሽ ነገር” እንኳ ታማኝ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስመልክቶ የሱስ በሉቃ. 16፡10 የሚገልጸው መርኅ ምን ያህል ወሳኝ ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ይሁን እንጂ በተለይ ባፈራነው ሀብት ዙሪያ እንዴት በቀላሉ ታማኝነታችንን ማጉደል እንደምንችል እግዚአብሔር ያውቃል፡፡ በዚህ ምክንያት ቢያንስ ከሐብት ንብረታችን ጋር በተያያዘ ለምናጎድለው ታማኝነትና ለራስ ወዳድነት ብርቱ ማርከሻ ሰጥቶናል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘሌዋ. 27፡30፣ ሚልክ. 3፡8፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ምን ሊያስተምሩን ይችላሉ? ይህ የሚናገሩለት ነገር ታማኝ እንድንሆን ምን ያህል ሊረዳን ይችላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“ለምስጋና ወይም ለለጋስነት ምንም ዓይነት ተማጽኖ ሊቀርብ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ሌላ ሳይሆን ከታማኝነት ጋር ብቻ የተቆራኘ ነው፡፡ አሥራት የጌታ እንደመሆኑ የራሱ የሆነውን እንድንመልስ ይናገረናል. . . ታማኝነት የንግዱ ዓለም ወሳኝ መርኅ ነው ከተባለ ለእግዚአብሔር ላለብን ግዴታ ዕውቅና መቸር የለብንምን?

አሥራት መመለስዎ እርስዎ ያለዎት ሁሉ የማን መሆኑን እንዲያስታውሱ እንዴት ይረዳዎታል? አለን የምንለው ነገር የማን መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት የሌለብን ለምንድን ነው?
 
የካቲት 5
February 12
 
የእምነት ሕይወት

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 22፡1-12፡፡ ታሪኩ ስለ አብርሃም እምነት ተጨባጭ እውነታ ምን ይነግረናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የእምነት ሕይወት የአንድ ጊዜ ክስተት አይደለም፡፡ እምነት በእርግጠኝነት በጸጋው የምንኖርና በክርስቶስ ደም የተሸፈን ታማኝ ክርስቲያን መሆናችንን በአንድ ወቅት ብቻ በብርቱ ገልጸን የምናልፈው ጉዳይ አይደለም፡፡

ለአብነት ያህል የእምነቱ ዓለም ከሺዎች ዓመታት አስቀድሞ አብርሃም ይስሐቅን ይዞ በሞሪያ ተራራ ካሳየው እምነት ጋር ዛሬም እንደተደመመ ይገኛል (ዘፍ. 22)፡፡ ሆኖም እንደዚያ ዓይነቱ እምነት አብርሃም በምትሃት የሚያገኘው ክስተት አልነበረም፡፡ አብርሃም ያን ለማድረግ ያስቻለው ቁልፍ ነገር በእርሱ ዘንድ አስቀድሞ የነበረው የታማኝነትና የመታዘዝ ህይወት ነበር፡፡ አብርሃም ቀደም ባለው ሕይወቱ ታማኝነት የጎደለው ሰው ቢሆን ኖሮ ያን የቀረበለትን ፈተና ማለፍ በተሳነው ነበር፡፡ በእንደዚያ ዓይነት እምነት ያለፈ ሰው ይህ ዓይነቱን አጋጣሚ ተከትሎ እምነቱን መግለጽ መቻሉ እምብዛም አያጠያይቅም፡፡

ዋናው ነጥብ ያለው የመጋቢው ህይወት በአንድ ጊዜ ተግባር ቦግ ብሎ የሚጠፋ አለመሆኑ ላይ ነው፡፡ አማኙ እምነቱን የሚለማመድበትን አካሄድ ተከትሎ--በጊዜ ሂደት እያደገ፣ ሥር እየሰደደና እየተጠናከረ ይሄዳል ወይም ጥልቀት የጎደለውና ልፍስፍስ ይሆናል፡፡

ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ዕብ. 12፡2፡፡ መልእክቱ ስለ እምነታችን ምንጭ እና እምነታችን እንዴት ሊጎለብት እንደሚገባ ምን ይነግረናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

እንደ ታማኝ መጋቢነታችን ብቸኛው ረዳታችን “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል” (ዕብ. 12፡2)፡፡ በጥቅሱ “ፍጹም አድራጊ” (አዲሱ መደበኛ ትርጉም) በሚል ጥቅም ላይ የዋለው ቃል “ፈጻሚ” (1962 ትርጉም) ተብሎም ተተርጉሟል፡፡ ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን ይህን ፍቺ ይዞ የቀረበው እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ሲሆን፤ በተጨማሪ “ፍጹም አድራጊ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ አባባሉ የሱስ እምነታችንን ወደ ብስለትና ሙላት የማምጣት ፍላጎት አለው የሚል አንደምታ አለው (ዕብ. 6፡1-2)፡፡ በመሆኑም የእምነት ሕይወት ሁሌም የሚያድግ፣ የሚበስልና እየተስፋፋ የሚሄድ በኃይል የተሞላ ተሞክሮ ነው፡፡

እምነትዎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየበሰለ መሄዱን ያዩባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?
 
የካቲት 6
February 13
 
የእምነት መገለጫ መንገድ

በትናንቱ ጥናታችን እንደተመለከትነው እምነት የማያቋርጥ ሂደት ሲሆን ዘወትር እያደገና በሳል እየሆነ የሚሄድ ተሞክሮ ነው፡፡ እግዚአብሔር እምነታችንን ወደ ፍጹምነት ወይም ወደ ሙላት ከሚያመጣባቸው መንገዶች አንዱ አሥራት ነው፡፡ አሥራትን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ሕግን ጠብቆ ለመዳን የሚደረግ አካሄድ አለመሆኑ በትክክል ሊስተዋል ይገባል፡፡ አሥራት ስንመልስ በራሳችን መንገድ ወደ ሰማይ ለመሄድ እየተመኘን ወይም እየሠራን አይደለም፡፡ ይልቁንም አሥራት የእምነታችን መገለጫ መንገድ ነው፡፡ ግላዊውን እምነታችንን በተጨባጭና በሚታይ ውጪያዊ አኳኋን የምንገልጽበት መንገድ ነው፡፡

ደግሞም ማንም ሰው እምነት እንዳለው፣ በእግዚአብሔር እንደሚያምንና የሱስንም እንደሚቀበል ሊናገር ይችላል፡፡ እንደምናውቀው “አጋንንትም ይህንኑ ያምናሉ” (ያዕ. 2፡19)፡፡ ነገር ግን ከገቢዎ ላይ 10 በመቶውን አንስተው ወደ እግዚአብሔር መመለስ? ይህ የእምነት ተግባር ነው፡፡

ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ሉቃ. 11፡42፡፡ አሥራታችንን ሳንመልስ መቅረት እንደሌለብን አስመልክቶ የየሱስ ንግግር አንደምታ ምን ይመስላል? አሥራት ክብደት ካላቸው የሕጉ ጉዳዮች ጋር እንዴት ይዛመዳል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አሥራት በእግዚአብሔር የምንመካ መሆናችንን እና በየሱስ ቤዛችን መታመናችንን በትህትና የምንገልጽበት መንገድ ነው፡፡ እግዚአብሔር “በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን” (ኤፌ. 1፡3) እና የላቀ ተስፋ የሰጠን ለመሆኑ እውቅና የምንቸርበት መንገድ ነው፡፡ በዘፍ. 28፡14-22 እንደምናነበው እግዚአብሔር ለያዕቆብ ለሰጠው የተስፋ ቃል ምላሹ ምን ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“ያልተወሳሰበውና በእኩልነት ላይ የተመሰረተው እግዚአብሔር በአሥራት ዙሪያ የዘረጋው እቅድ እጅግ ውብ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ይህን ቀደም ብሎ በመለኮት የተጠነሰሰ ዕቅድ በእምነትና በጀግንነት አጥብቆ እንዲይዝ ይጠየቃል፡፡ በአሥራት ዕቅድ ውስጥ ቀናነትና ጠቃሚነት በአንድ በመጣመራቸው ኃሳቡን አስተውሎ ወደ ትግበራው ለማምራት ጥልቀት ያለው አስተምህሮ አይጠይቅም፡፡ ወንዶች፣ ሴቶችም ሆኑ ወጣቶች የጌታ ግምጃ ቤት ኃላፊዎችና የግምጃ ቤቱን ጥያቄ የሚያሟሉ ወኪሎች መሆን ይችላሉ፡፡” —Ellen G. White, Counsels on Stewardship, p. 73.

አሥራት በመመለስ የሚመጡ እውነተኛ መንፈሳዊ በረከቶችን በግልዎ ያስተዋሉት እንዴት ነው? አሥራት መመለስዎ እምነትዎ እንዲያድግ ያደረገው አስተዋጽኦ ምን ይመስላል?
 
የካቲት 7
February 14
 
በአሥራት መታመን--ለጌታ መቀደስ

ዘወትር አሥራት ስለ መስጠት እናወራለን፡፡ ነገር ግን አስቀድሞውኑ የእርሱ የሆነውን ነገር ለእግዚአብሔር የምንሰጠው እንዴት ነው?

ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ዘሌዋ. 27፡30፡፡ ከአሥራት ጋር በተያያዘ በመልእክቱ የምናገኛቸው ሁለት ዋና ዋና ነጥቦች ምንድን ናቸው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“አሥራት የጌታ በመሆኑ ቅዱስ ነው፡፡ ቅድስናው በስለት ወይም በመለየቱ ሳይሆን በራሱ ልዩ ባህሪ ይኸውም የጌታ በመሆኑ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ሰው በአሥራት ላይ ሥልጣን የለውም፡፡ ማንም ቢሆን አሥራትን ለጌታ መቀደስ አይችልም፤ ምክንያቱም አሥራት የየትኛውም ሰው ንብረት አካል አይደለም፡፡” —Ángel Manuel Rodríguez, Stewardship Roots (Silver Spring, Md.: Stewardship Ministries Department, 1994), p. 52.

አሥራትን የተቀደሰ ማድረግ አንችልም፡፡ እግዚአብሔር ግን በሥልጣኑ ያደርገዋል፡፡ እርሱ ያን የማድረግ መብት አለው፡፡ እኛ እንደ መጋቢነታችን የእርሱ የሆነውን ለእርሱ እንመልሳለን፡፡ አሥራት የተለየ ተግባር ላለው የእግዚአብሔር ሥራ የሚውል ነው፡፡ አሥራትን ከዚህ ውጪ በሌላ ማንኛውም ነገር ለማዋል መያዝ ታማኝነትን ማጉደል ይሆናል፡፡ ቅዱስ የሆነውን አሥራት የመመለስ ኪዳን ፈጽሞ ሊበጠስ አይገባም፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 7፡2-10፡፡ አብርሃም ለመልከጼዴቅ አሥራት ማውጣቱን አስመልክቶ ጳውሎስ ያነሳቸው ነጥቦች በአሥራት ዙሪያ ያለውን ጥልቅ አንደምታ እንዴት ይገልጻሉ? አብርሃም በእርግጥ አሥራት ያወጣው ለማን ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ስለዚህ ሰንበት ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ አሥራትም ቅዱስ ነው፡፡ “ቅዱስ” የሚለው ቃል “ለመንፈሳዊ አገልግሎት የተለየ” የሚል ፍቺ አለው፡፡ ሰንበትና አሥራት በዚህ መልኩ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ሰባተኛውን ቀን ሰንበት ከሌሎቹ የሳምንቱ ቀናት የተቀደሰ አድርገን እንደምንለየው ሁሉ፤ ቅዱስ የሆነውን አሥራትንም እንደ ተቀደሰ የእግዚአብሔር ንብረት እንለየዋለን፡፡

“እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ቀደሰው፡፡ ያ ኃይማኖታዊ አምልኮ ይደረግበት ዘንድ በራሱ በእግዚአብሔር የተለየው፤ የተወሰነ የጊዜ ክፍል መጀመሪያ በፈጣሪያችን ያገኘው ቅድስና እነሆ ዛሬ ድረስ ጸንቶአል፡፡

“በተመሳሳይ የገቢያችን አንድ አሥረኛው አሥራት ‘ለጌታ ቅዱስ ነው፡፡’ አዲስ ኪዳን እንደ ሰንበት ሁሉ በአሥራት ዙሪያ ያጸደቀው ሌላ ሕግ የለም፡፡ የሁለቱም ተገቢነት ጥቅም ላይ ውሏል--የያዙት ጥልቅ መንፈሳዊ ይዘትም ተብራርቷል. . . እኛ እንደ ሕዝብ እግዚአብሔር ለራሱ የመደበውን ጊዜ በታማኝነት ለእርሱ ለማዋል እንደምንተጋ ሁሉ፤ ለእኔ የተገባ ነው የሚለንን መጠን አንመልስለትምን?” —Ellen G. White, Counsels on Stewardship, p. 66.

አሥራትዎ በእርግጥ “ቅዱስ” የመሆኑን ግንዛቤ በልብዎና በአእምሮዎ ህያው አድርገው እንደጠበቁ ለመጓዝ ይረዳዎ ዘንድ ምን ማድረግ ይችላሉ?

የካቲት 8
February 15

መነቃቃት፣ ተሐድሶ እና አሥራት

ረጅም ዓመታት ያስቆጠረው የሕዝቅያስ የንግሥና ዘመን የይሁዳ ነገድ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ከንጉሥ ዳዊት እና ሰሎሞን አንስቶ እስከዚያ ዘመን ድረስ እስራኤላውያን በከፍተኛ መጠን የእግዚአብሔርን በረከት አላገኙም ነበር፡፡ በ2ኛ ዜና 29-31 የሕዝቅያስ መነቃቃትና ተሐድሶ እንዲህ ሰፍሮአል፡ “እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ” (2ዜና 29፡2)፡፡ “የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት እንደገና ተደራጀ” (2ዜና 29፡2)፡፡ ፋሲካም መጠበቅ ጀመረ (2ዜና 30፡5)፡፡ “በኢየሩሳሌም እንዲህ ያለ በዓል ተደርጎ” አያውቅም (2ኛ ዜና 30፡26)፡፡ የአረማውያን ምስሎች፣ መሠዊያዎችና ኮረብታማ መስገጃዎች እንዲወድሙ ተደረገ (2ኛ ዜና 31፡1)፡፡ በህዝቡ ልብ ድንገተኛ መነቃቃትና ተሐድሶ መፈጠሩ የተትረፈረፈ አሥራትና ስጦታ ይዘው እንዲቀርቡ መንስዔ ሆነ (2ኛ ዜና 31፡4-5፣ 12)፡፡

መጽሐፈ ነህምያ ስለ መነቃቃት፣ ተሐድሶና አሥራት ሌላ ምሳሌ ይሰጠናል፡፡ ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ነህ. 9፡2-3፡፡ በወቅቱ የተስተዋለው የልብ መነቃቃት ትርጉም ምን ነበር?--ነህ. 13፡፡ ነህምያ “በእግዚአብሔር ቤት” ተሐድሶ ካመጣ በኋላ (ነህ. 13፡14) የይሁዳ ሕዝቦች ምን ይዘው ቀረቡ? (ነህ. 13፡12)፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“መነቃቃትና ተሐድሶ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ለመንፈሳዊው ህይወት መታደስ አጽንኦት የሚሰጠው መነቃቃት በአእምሮና ልብ ውስጥ ታምቆ የተቀመጠውን ኃይል በመቀስቀስ ለመንፈሳዊው ሞት ትንሳዔ ያመጣል፡፡ ተሐድሶ-እንደገና ማደራጀት፣ የጽንሰ ሃሳብ፣ የንድፈ ሃሳብ፣ የልማድና የተግባር ለውጥ ማድረግን ያመላክታል፡፡” —Ellen G. White, Christian Service, p. 42.

በመነቃቃት፣ በተሐድሶ እና በአሥራት መካከል ያለው ግንኙነት እርስ በርሱ የተሳሰረ ነው፡፡ አሥራት መመለስን ያላካተተ መነቃቃትና ተሐድሶ--መነቃቃት ከተባለ፤ በለብታ ከመመላለስ ውጪ ሌላ ፍቺ የለውም፡፡ ብዙውን ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች የጌታን ሥራ በንቃት መካፈል ሲገባን እንዲያው በከንቱ ጥግ ጥጉን ይዘን ስንቆዝም እንስተዋላለን፡፡ መነቃቃትና ተሐድሶ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ሁሉ አሥራትም የዚህ ተመሳሳይ ቁርጠኝነት አካል ነው፡፡ እግዚአብሔር እንድንመልስ የሚጠይቀንን ለራሳችን እያስቀረን ይህን አድርግልኝ ብለን መለመናችን--ወርቅ ላበደረ ጠጠር፣ እህል ላበደረ ዐፈር--አይሆንብንም?

ልዩነት የሚያመጣው ድርጊት ሳይሆን ተነሳሽነትንና ቁርጠኝነትን ገላጩ የአእምሮና የውስጣዊ ስሜት ውሳኔ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ የሚመጡት ውጤቶች፡ የእምነት መጨመር፣ የሰላ መንፈሳዊ ዕይታና መታደሰ ያገኘ ታማኝነት ይሆናሉ፡፡
 
የካቲት 9
February 6
 
ተጨማሪ ሃሳብ፡-

በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱትን ኪዳኖች ሁሉ የወጠነው እግዚአብሔር ሕዝቦቹን ወደነዚህ ኪዳኖች በመምራቱ ረገድ ቀዳሚነቱን ወስዷል (ዕብ. 8፡10)፡፡ የኪዳኑ ተስፋዎች የእርሱን ጸጋ፣ ፍቅር እና እኛን ለማዳን ያለውን ምኞት ያንጸባርቃሉ፡፡

ብዙ ነገሮችን የሚያካትተው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገባው ኪዳን እንደሚከተለው ቀርቧል፡ ራሱን እግዚአብሔርን፣ ኪዳን ተቀባዩን፣ የኪዳኑን ሁኔታዎች፣ ሁለቱም አካሎች ለሁኔታዎች ያሏቸው ቁርጠኝነት፣ ኪዳኑን ያፈረሰ አካል የሚጣልበት የቅጣት ዓይነት እንዲሁም ኪዳኑ ያስገኛል ተብለው የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው፡፡ በሚልክ. 3፡9-10 የቀረበው የአሥራት ጽንሰ ሃሳብ እነዚህን ከፍሎች ያንጸባርቃል፡፡ ጥቅሱ በእግዚአብሔርና በመጋቢዎቹ መሃል ያለውን በዓይነቱ የተለየ የአሥራት ኪዳን ያጠናክራል፡፡ የእንዲህ ዓይነቱ ኪዳን አካል ስንሆን ብልጭልጩን የፍጆታ ወጪ መርኅ እንቃወማለን፡፡ በተለወጠው ኃጢአተኛ ልብ አንዳች በጎ ነገር ሊመጣ ይችላል ብለን ማመናችንንም እንመሰክራለን፡፡

“ለራስ ወዳድነት ቅርብ የሆነው መንፈስ ሰዎች የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር እንዳይመልሱ የማገድ ባህሪ አለው፡፡ ሕዝቦቹ ለክርስቶስ መንግሥት መፋጠን ቁልፍ ሚና የሚጫወተውንና በእርሱ የተወሰነውን አሥራት በቋሚነት ወደ ቤቱ የሚመልሱ ከሆነ ማስቀመጫ ቦታ እስኪያጡ ጌታ እንደሚባርካቸው በመንገር ከእነርሱ ጋር የተለየ ኪዳን ገብቷል፡፡ ነገር ግን ሰዎች የእግዚአብሔር የሆነውን ለራሳቸው የሚያስቀሩ ከሆነ ጌታ ‘የተረገማችሁ ናችሁ’ ሲል በግልጽ ይናገራል’ ” —Ellen G. White, Counsels on Stewardship, p. 77.

ከእግዚአብሔር ጋር በኪዳን ተሳስሮ መኖር የራሱ ኃላፊነቶች አሉት፡፡ ከእርሱ ጋር በገባነው ውል ደስተኞች ብንሆንም ነገር ግን ትእዛዞቹንና ኃላፊነቶቹን እምብዛም ስንወዳቸው አንስተዋልም፡፡ በዐውደ ጽሑፉ መሰረት ኪዳን የሁለት ወገን ስምምነት ሲሆን፤ አሥራት ደግሞ ለቃል ኪዳኑ ከምንገዛባቸው ደንቦች መሃል አንደኛው ክፍል ነው፡፡
 
የመወያያ ጥያቄዎች:-፡

  1. የእኛ ድርሻ የሆነው አሥራት የመመለስ ኃላፊነት ወሳኝ የእምነታችን መገለጫ የሆነው ለምንድን ነው?

  2. “አሥራት የመመለስ አቅሙ የለኝም” ለሚል ሰው ምን ዓይነት ቃል ያጋራሉ? ራሱን በዚያ ሁኔታ ውስጥ የሚያየውን ሰው ሊረዱ የሚችሉት እንዴት ነው? ደግሞም ከቃላት ባለፈ እንደዚያ ዓይነቱን ሰው ለመርዳት ምን ተጨማሪ ነገር ሊደረግ ይገባል?

  3. በረቡዕ ትምህርት የመጨረሻ ጥያቄ ላይ--አሥራትዎ በእርግጥ “ቅዱስ” የመሆኑን ግንዛቤ በልብዎና በአእምሮዎ ህያው አድርገው እንደጠበቁ ለመጓዝ ይረዳዎ ዘንድ ምን ማድረግ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ከቀረቡት ምላሾች መሃል አንዳንዶቹ ምን ነበሩ? አሥራት ቅዱስ የመሆኑ ሐቅ ወደ እግዚአብሔር ቤት ለመመለስ ያለው ዝምድና ምንድን ነው?