መጋቢነት፡ ልብ አነሳሹ ሞተር
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከየካቲት 10 – 16

ስምንተኛ ትምህርት

February 17–February 23

የአሥራት   ተጽእኖ 

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡  ማር.16:15፣ 1ጴጥ. 3:8-9፣ 1ቆሮ. 9:14፣ ሮሜ 3:19–24፡፡ 

 

የሳምንቱ መሪ ጥቅስ፦ ““በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙ፣ በመሠዊያውም የሚያገለግሉ ከመሥዋዕቱ እንደሚካፈሉ አታውቁምን? እንደዚሁም ወንጌልን የሚሰብኩ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ከወንጌል እንዲቀበሉ ጌታ አዞአል” (1ቆሮ. 9፡13-14)

አ ሥራት እጅጉ አስፈላጊ የእምነታችን መገለጫ መንገድ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ጥናታችን ተመልክተናል፡፡ አሥራት እምነታችንን በተጨባጭ የምንገልጥበት ወይም የምንፈትንበት አንዱ መንገድ ነው፡ “በእምነት መሆናችሁን ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፡፡ ከፈር የወጣችሁ ካልሆነ በስተቀር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በውስጣችሁ እንዳለ አታውቁምን? (2ቆሮ. 13፡5)፡፡

ስለ አሥራት የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ማጣቀሻ አብርሃም ለመልከጼዴቅ የሰጠው ነው (ዘፍ. 14፡18-21፣ ዕብ፣ 7፡4)፡፡ በተጨማሪ ሌዋውያን በቤተ መቅደስ ለሚሰጡት አገልግሎት አሥራት ያወጡ ነበር (2ዜና 31፡4-10)፡፡ ዛሬ አሥራት የወንጌል ሥራን ለመደገፍ ይውላል፡፡ አሥራት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን መንፈሳዊ ግንኙነት የምንለካበት መሣሪያ በመሆን ያገለግላል፡፡


የአሥራት አወጣጥ፣ አጠቃቀም፣ አስፈላጊነትና የአሰረጫጨት ሥልት የእግዚአብሔርን ሥራ ለመደገፍ፣ መንፈሳዊ ህይወታችንን ለማጎልበትና ወንጌል የሚሰበክበትን አስተማማኝ የገንዘብ አቅም ለመፍጠር ታልሞ የተነደፈ ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ዕቅድ ሲሆን አንድ ታማኝ መጋቢ የሚወስደው የመጀመሪያ እርምጃ ተብሎ ይጠራል፡፡


በዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በአሥራት ዙሪያ በጀመርነው ምልከታ ቆይታ በማድረግ፡ የአሥራት ስርጭት በሌሎች ላይ ያለውን አንደምታና በህይወታችን ያለውን ተጽእኖ እንፈትሻለን፡፡

የካቲት 11
February 18
 

ኅብረት ፈጥሮ ተልዕኮውን በገንዘብ መደገፍ

 

የሱስ “ ‘ወንጌልን ስበኩ’ ” (ማር. 16፡5) “ ‘ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ ” “ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” (ማቴ. 28፡19-20) ሲል ያዘናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በዓለም እጅግ አስፈላጊ በሆነው ሥራ ላይ እንድንሰማራ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ከሰጠን ሀብት ይህን ተልዕኮ መደገፍ የመጋቢነት ኃላፊነት ነው፡፡ የመጋቢነት ተሳትፎ ክርስቶስን ለሌሎች በማቅረቡ ረገድ የግል ቁርጠኝነት ጥልቀት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ እያንዳንዱ ደቀ መዝሙር፣ መጋቢና ሠራተኛ ከአሥራቱ ምንም ሳያስቀር ለዚህ የተቀደሰ ሥራ ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ተልዕኮ በታማኝነት በገንዘባችን እየደገፍን ኅብረት እንዲኖረን ጌታን በጸሎት እንጠይቅ፡፡


ይህንን ተልዕኮ ለመፈጸም እግዚአብሔር ያጸደቀው የገንዘብ ዕቅድ ምንድን ነው? “‘አሥራቱን ሁሉ’ ” ማለት ምን ማለት ነው? (ሚልክ. 3፡10)፡፡ “ ‘በቤቴ መብል እንዲኖር’ ” የሚለው ሐረግ ፍቺስ ምን ይመስላል?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ሰዎች ከአብርሃምና ያዕቆብ ዘመን አንስቶ--ምናልባት ከዚያም በፊት አሥራታቸውን እየመለሱ ይገኛሉ (ዘፍ. 14፡20፣ 28፡22)፡፡ አሥራት ከፍ ባለ የገንዘብ ምንጭነት የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ለመደገፍ የተዘረጋ በእጅጉ ተገቢና ትክክለኛ አሠራር አካል ነው፡፡


የዚህ ዘመን አብላጫ ሕዝበ ክርስቲያን ለአምላካዊው ተልዕኮ እየሰጠ የሚገኘው ድጋፍ በአንፃራዊነት ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ክርስቲያን አሥራቱን በታማኝነት ሰጥቶ ቢሆን ውጤቱ “የማይገመት፣ አስደናቂና ከአእምሮ በላይ በሆነ ነበር” —Christian Smith and Michael O. Emerson, Passing the Plate (New York: Oxford University Press, 2008), p. 27.


በእያንዳንዱ ዘመን እግዚአብሔር አምላካዊውን ተልዕኮ በገንዘባቸው የሚደግፉ ሕዝቦች ነበሩት፡፡ እኛ ሁላችን ይህን ዓለማቀፋዊ ኃላፊነት በገንዘባችን እየደገፍን በማስተዋልና በኅብረት የመሥራት ዐደራ ተጥሎብናል፡፡ ተልዕኮውን በገንዘባችን የምንደግፈው ባልተቀናጀ፣ በቸልተኝነት ወይም በድንገትና ያለ ዕቅድ መሆን የለበትም፡፡ የእኛ ተግዳሮት የእስራኤል ሕዝብና ሌዋውያኑ “እኛም የአምላካችንን ቤት ቸል አንልም” (ነህ. 10፡39) በማለት ከተናገሩት በላይ ነው፡፡ በ 1800ዎቹ ዘመናት አማኞች ከተጋፈጧቸው ሁናቴም ይበልጥ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ ዛሬ የቤተ ክርስቲያን አባላትና ፓስተሩ ዓለም አቀፍ ዓላማዎችን በሚያሟላና ለተልእኮው የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርግ መልኩ በመንፈሳዊ ነገር አንድ ሆነው የጠበቀ ኅብረት ሊመሰርቱ ይገባል፡፡


አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ ያለው ስፋትና መጠን ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ አስቡ (ራእ. 14፡6-7)፡፡ እያንዳንዳችን ይህን ሥራ በገንዘባችን ለመደገፍ ስላለብን ኃላፊነት ምን ያህል አስተውለናል?

የካቲት 12
February 19
 

የእግዚአብሔር በረከቶች

 

በሚልክ. 3፡10 እንደተመለከትነው በአሥራታቸው ታማኝ ለሆኑ እግዚአብሔር ታላቅ በረከት እንደሚያፈስላቸው ቃል ገብቷል፡፡ ሆኖም የእግዚአብሔር በረከትባለ አንድ ገጽ ብቻ አይደለም፡፡ ነገሩን ጎላ አድርጎ ለመመልከት ያህል ለምሳሌ ሌሎች ነገሮችን ወደ ጎን ብለን የቁሳዊውን ሀብት ክምችት ብቻ እንደ በረከት የምንመለከት ከሆነ ከትክክለኛው የእግዚአብሔር በረከት አኳያ እንዲህ ያለው ዕይታ እጅግ ጠባብ ነው፡፡


በሚልክያስ የቀረበው በረከት መንፈሳዊ እንዲሁም ጊዜያዊ ነው፡፡ የእግዚአብሔር በረከት--በመዳን፣ በደስታ፣ በአእምሮ ሰላምና እግዚአብሔር ሁሌም ለእኛ በሚያደርግልን ምርጥ ነገሮች በተጨባጭ የተደገፈ ነው፡፡ ደግሞም በእግዚአብሔር ስንባረክ በረከቶቻችንን በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች የማካፈል ግዴታ አለብን፡፡ እኛ የተባረክነው ሌሎችን እንድንባርክ ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛን ተጠቅሞ በረከቱን ወደ ሌሎች ማስተላለፉ እርግጥ ነው፡፡


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 3፡8-9፡፡ ጴጥሮስ በመባረክና መባረክን ወደ ሌሎች በማስተላለፍ መሃል ስላለው ዝምድና ምን እያለን ነው?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


አሥራትን በመመለስ የሚገኘው በረከት ሁሌም እጥፍ ነው፡፡ እኛ በመባረካችን ሌሎችን እንባርካለን፡፡ ከተሰጠን ላይ ለሌሎች መለገስ እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር በእኛ ላይ የሚያፈሳቸው በረከቶች በውስጣችን አልፈው ወደ ውጭ ይኸውም ወደ ሌሎች ይፈሳሉ፡፡ “ስጡ፣ ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩት መስፈሪያ… ተሰፍሮ በዕቅፋችሁ ይሰጣችኋል” (ሉቃስ 6፡38)፡፡


በተጨማሪ በሐዋ. 20፡35 የቀረበው መልእክት ከአሥራት ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ የምናውለው እንዴት ነው?


አሥራት መመለስ የሚያስተምረን ታላቁ በረከት በእግዚአብሔር መታመን ነው (ኤር. 17፡7)፡፡ “በዓይነቱ ልዩ የሆነው የአሥራት ሥርዓት የተመሰረተው ልክ እንደ እግዚአብሔር ሕግ ጽኑ በሆነው መርኅ ላይ ነው፡፡ ይህ የአሥራት ሥርዓትለአይሁዶች በረከት ባያመጣ ኖሮ እግዚአብሔር ባልሰጣቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ይህን ሥርዓት እስከ ጊዜው ፍጻሜ ለሚከተሉ ሁሉ በረከት ይሆንላቸዋል፡፡ ሰማያዊ አባታችን ይህን ሥርዓት የተከተለ ቸርነት ያቋቋመው ለራሱ ሳይሆን ለሰዎች ታላቅ ብልጽግና ለማምጣት ሲል ነው፡፡ ይህ የበጎነት ሥርዓት ለሰዎች እንደሚያስፈልግ እግዚአብሔር ተመልክቶ ነበር፡፡” —Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 3, pp. 404, 405.


ሌላው ሰው ለእርስዎ የሰጠውን አገልግሎት ተከትሎ በጌታ ስለተባረኩባቸው ጊዜያት ያስቡ፡፡ እርስዎም በተመሳሳይ ወደ ሌላው ወገን መውጣት የሚችሉት እንዴት ነው?

የካቲት 13
February 20
 

የአሥራት ዓላማ

 

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍ “እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሠር፤ ‘ደግሞም፣ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል’ ” ይላል፡፡ (1ጢሞቴ5፡18)፡፡ ሙሴ በዘዳግም 25፡4 ስለ በሬ፣ የሱስ ደግሞ በሉቃ. 10፡7 ስለ ሠራተኛ የተናገረውን ጳውሎስ ይጠቅሳል፡፡ ስለ በሬ የተነገረው ሀረግ ምሳሌያዊ የአነጋገር ስልትን የተከተለ እንደመሆኑ እየሠራ ያለን በሬ የሚበላውን አትንፈገው የሚል አንደምታ አለው፡፡ በተመሳሳይ ሁለተኛው ምሳሌያዊ አነጋገር ደግሞ፤ ወንጌል ለመስበክ ቀናኢ የሆኑ ወገኖች ደሞዝ ሊከፈላቸው እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡


እግዚአብሔር የሚፈጥረውም ሆነ የሚሠራው ሥርዓትን ተከትሎ ነው፡፡ ሥርዓተ ፀሐይን፣ ሥርዓተ ምህዳርን፣ ቅንባሮተ ልመትን (በሰውነታችን የሚካሄድ የምግብ መፈጨት ሥርዓት)፣ የነርቭ ሥርዓትንና የሌሎች አያሌ ነገሮች ንድፍ አውጪ እርሱ ራሱ ነው፡፡ የአሥራት ሥርዓት ጥቅም ላይ የዋለው ለሌዋውያን ሲሆን (ዘኁ. 18፡26) በዚህም አሥራት በመገናኛው ድንኳን አገልጋዮቹን ለመደገፍ ይውል ነበር፡፡ ዛሬ በእኛ ዘመን ህይወታቸውን ለወንጌል ሥራ አሳልፈው የሰጡ ሰባኪዎችንከሌዋውያኑ ጋር አመጣጥነን ልንመለከታቸው እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር የዘረጋውና በመላው የደኅንነት ታሪክ ጥቅም ላይ የዋለው ሥርዓተ አሥራት--አገልግሎቱ እንዲደገፍ እርሱ የመረጠው ዘዴ ነው፡፡


ጳውሎስ “ወንጌልን የሚሰብኩ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ከወንጌል እንዲቀበሉ ጌታ አዞአል” (1ቆሮ. 9፡14) ሲል ምን ማለቱ ነው? የሃረጉ ሥነ ምግባራዊ አንደምታስ ምንድን ነው? ወንጌል የሚያሰራጩ ወገኖችን ስለ መደገፍ አስፈላጊነት 2ቆሮ. 11፡7-10 ምን ያስተምራል?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


“እናንተን ለማገልገል ስል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ርዳታ በመቀበሌ እነርሱን ዘርፌአቸዋለሁ” (2ቆሮ. 11፡8) በማለት ጳውሎስ ይናገራል፡፡ ጳውሎስ ሀብታም የነበረችውን የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እያገለገለ ከደኻዋ የመቄዶኒያ ቤተ ክርስቲያን ምንዳ መቀበሉን በምጸት እየተናገረ ነበር፡፡ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ወንጌልን የሚሰብኩ ሊከፈላቸው ይገባል የሚል ነው፡፡


አሥራት ለአንድ የተወሰነ ዓላማ ጥቅም ላይ ሊውልና በዚያው እንደጸና ሊቆይ ይገባል፡፡ “አንድ የተለየ ጥቅም ላይ እንዲውል የተመደበው አሥራት ለድኾች መደጎሚያ የገንዘብ ምንጭ አይደለም፡፡ ይልቁንም በተለይ ወንጌልን ለዓለም ለማዳረስ የሚሠሩ ታማኞችን ለመደገፍ ሊውል የተገባ ነው፡፡ ከዚህ ዓላማ ውጪ ወደ ሌላ መሄድ የለበትም፡፡” —Ellen G. White, Counsels on Stewardship, p. 103.


ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ዘሌዋ. 27፡30፡፡ በዚህ ስፍራ የምንመለከተው መርኅ ከዛሬው ጋር ገጣሚ የሚሆነው በምን መልኩ ነው?

የካቲት 14
February 21
 

ጎተራ

 

ለነፋስ ግምጃ ቤት (ኤር. 10፡13)፣ ለውሃ ማከማቻ (መዝ. 33፡7)፣ ለበረዶና ለዐመዳይ መጋዘን (ኢዮ. 38፡22) ያለው እግዚአብሔር ሁሉንም ሙሉ ለሙሉ ይቆጣጠራል፡፡ አሥራት ግን እጅግ የከበረው የእርሱ ጎተራ ነው፡፡ “ ‘በመገናኛው ድንኳን በሚያገለግሉበት ጊዜ ለሚሠሩት ሥራ ደመወዝ እንዲሆናቸው ከእስራኤል የሚወጣውን አሥራት ሁሉ ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ’ ” (ዘኁ. 18፡21)፡፡ ይህ አሥራት ስለ ሚውልበት ስፍራ በመጀመሪያ የተጠቀሰው ጥቅስ ዛሬም “የግምጃ ቤቱ መርኅ” በመባል ይታወቃል፡፡ እስራኤላውያን አሥራታቸውን እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ይዘው የሚመጡበት ተጨማሪ መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር (ዘዳ. 12፡5-6)፡፡ በሰለሞን ዘመን አሥራት የሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ይመለስ ነበር፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ “ ‘አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አስገቡ’ ” (ሚልክ. 3፡10) በማለት ለእስራኤላውያን የነገራቸውን ተከትሎ የዚህን “ጎተራ” ምንነትና የሚገኝበትን ስፍራ ጠንቅቀው ተረድተው ነበር፡፡ አምላካዊው ግምጃ ቤት ኃይማኖታዊ አገልግሎቶች የሚከናወኑበትንና ሌዋውያን የሚደገፉበትን ስፍራ ይወክል ነበር፡፡


የእግዚአብሔርን ጎተራ ለማሳየት ሌሎች ምን ዓይነት ስያሜዎች ጥቅም ላይ ውለዋል? 1ዜና. 26፡20፣ 2ዜና. 31፡11-13፣ ነህ. 10፡38)፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ቅዱስ የሆነውን አሥራት ወደ እግዚአብሔር ጎተራ ማምጣት ብቸኛው ልንከተለው የሚገባ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ ነው፡፡ እግዚአብሔር በእያንዳንዱ አግባብ አሥራትን የሚያስተዳድርበት ማዕከላዊ ግምጃ ቤት ነበረው፡፡ ዓለም አቀፍ ሰባተኛቀን አድቬንቲስትን አስመልክቶ ቤተ ክርስቲያን የምትከተለው የግምጃ ቤት መርኅ ተቀባይነት ያለውና በተግባርም የዋለ ነው፡፡ አባላት--የቤተ ክርስቲያን አባል በሆኑበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት አሥራታቸውን ለሰበካው (ፊልድ) እንዲመልሱ ይበረታታሉ፡፡ ፓስተሮች ደሞዛቸውን ከሰበካው ግምጃ ቤት ይቀበላሉ ነው፡፡


“የእግዚአብሔር ሥራ እየተስፋፋ በሄደ መጠን ለእርዳታ የሚቀርቡ ጥሪዎች ያለማሰለስ ይበራከታሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ጥሪዎች ምላሽ ያገኙ ዘንድ ክርስቲያኖች ‘በቤቴ መብል እንዲኖር አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አስገቡ’ (ሚልክ. 3፡10) የሚለውን አምላካዊ ትእዛዝ ሊሰሙ የተገባ ነው፡፡ ራሳቸውን በክርስቲያንነት የገለጹ ወገኖች አሥራታቸውንና መባቸውን በታማኝነት ለእግዚአብሔር የሚያመጡ ከሆነ ጎተራው ሙሉ ይሆናል፡፡ እንዲህ ከሆነ ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ሥራን ለመደገፍ ልዩ ልዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች መጠቀም አያስፈልጋትም፡፡” —Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 338.


ሰዎች አሥራታቸው ወደ ፈለጉት አቅጣጫ ቢልኩ ሊከሰት ስለሚችለው ነገር አሰብ ያድርጉ፡፡ ሁሉም ሰው እንደዚያ አድርጎ ቢሆን በእግዚአብሔር ሥራ ላይ ምን ሊከሰት ይችል ነበር? ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ አሥራታችንን ወደ ትክክለኛው ክፍል መላካችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

የካቲት 15
February 22

አሥራት እና ጽድቅ በእምነት

 

በሮሜ 3፡19-24 የምናገኘው የእምነታችን ማዕከልና ወሳኝ እውነት ምንድን ነው? ይህን አስተምህሮ ሁልጊዜ የእምነታችን መሰረት አድርገን መጠበቃችን የግድ የሆነው ለምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ሁላችንም ኃጢአት የሠራንና የእግዚአብሔር ክብር የጎደለን ፍጡራን እንደመሆናችን የደኅንነት ባለቤቶች መሆን እንደማይገባን ከእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጽ ፍሬ ሃሳብ መረዳት እንችላለን (ሮሜ 3፡23)፡፡ በችሎታችን ወይም በመልካም ሥራችን የጽድቅ ባለቤት ከሆንን ደግሞ፤ እንዲህ ያለው ጽንሰ ሃሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሊጣረስ ነው፡፡


ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ሮሜ 4፡1-5፡፡ ጥቅሶቹ ከመልካም ሥራ በተቃራኒ ስለ ጸጋ ምን ያስተምሩናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


ስለዚህ ደኅንነት ለማይገባቸው የተሰጠ ስጦታ ነው (ኤፌ. 2፡8-9)፡፡ የደኅንነት ባለቤት መሆን የቻልነው የክርስቶስ ፍጹም መሥዋዕትነት ለእኛ በመቆጠሩ ነው፡፡ አሥራትን በተመለከተ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር በመመለሳችን ይህ አምላክ የእኛ ዕዳ የለበትም፡፡ አሥራት የእግዚአብሔር በመሆኑ ከተስማማን የራሱን ለራሱ መልሰን በጎ ምላሽ መጠበቅ ይኖርብናል?


እንደ ክርስቲያን መልካም ተግባሮችን እንድናደርግ የተፈጠርን ብንሆንም አሥራታችንን መመለሳችን ከሌሎች በጎ ተግባራት በላቀ የደኅንነት ባለቤት አያደርገንም፡፡ “ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀልንን መልካም ሥራ እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን” (ኤፌ. 2፡10)፡፡


አሥራት መመለስ እግዚአብሔር እንድናደርግ ከጠየቀን አኳያ ግለሰቡ የሚገኝበትን ሁናቴ ይኸውም ትሁትና ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ወይም ሀሳበ ግትር እና እምቢተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆነ እንታዘዘዋለን፡፡ አሥራት እኛ በእርግጥ በዚህ ምድር መጋቢዎች መሆናችንንና ሁሉም ነገር የእግዚአብሔር መሆኑን ማስተዋላችንን ውጫዊ በሆነ አኳኋን የምንገልጽበት መንገድ ነው፡፡ ሰንበትየእግዚአብሔርን ፈጣሪነትና አዳኝነት በየሳምንቱ የምናስታውስበት ዕለት እንደመሆኑ፤ አሥራት መመለስም ተመሳሳይ ተዛምዶ ሊኖረው ይችላል፡፡ በመሆኑም እኛ የራሳችን አለመሆናችንን ይልቁንም ህይወታችንና መዳናችን ከእግዚአብሔር የተሰጡ ስጦታዎች መሆናቸውን ያስታውሰናል፡፡ በውጤቱም አሥራት መመለስ የዚያ እምነት ተጨባጭ መገለጫ መሆኑን በመቀበል እውነታውን ልንገነዘብና የእምነት ህይወት መኖር እንችላለን፡፡


ሉቃ. 21፡1-4 በእምነት ስለ መኖር የሚሰጠን ፍቺ ምን ይመስላል?

የካቲት 16
February  23
 

ተጨማሪ ሃሳብ፡፡-

 

እያንዳንዱ እስትንፋስ፣ እያንዳንዱ የልብ ምት እና እያንዳንዱ የህልውናችን መንስኤ የሚመጣው ከጌታ ብቻ መሆኑን በቀላሉ ስንረሳ እንስተዋላለን፡፡ በሐዋ. ምዕ. 17 (“ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ” [ሐዋ. 17:24] ) እርሱ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነገር ደግፎ የያዘ (“የምንኖረውና የምንንቀሳቀሰው፤ ያለነውም በእርሱ ነው [ሐዋ. 17:28]) እውነተኛ አምላክ መሆኑን ጳውሎስ ለአቴናውያን ሲመሰክር ይደመጣል፡፡ የአቴና ሰዎች ስለ እውነተኛው አምላክ አያውቁም ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ለምናውቅ ለእኛ ይህ ዕውቀታችን የዕለት ከዕለት አኗኗራችን አስኳል ሊሆን ይገባል፡፡ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ባለቤትነት ስፍር ቁጥር የሌለው እንደመሆኑ፤ እኛም እንደ ባለቤትነቱ አግባብ መመላለስ ይጠበቅብናል፡፡


“እግዚአብሔር በእኛ ላይ የባለቤትነት መብት አለው፡፡ ሀብት ንብረቱን በሰው ልጆች እጅ ያኖረው ይህ አምላክ ከሰጠው አንድ አሥረኛ ለሥራው በታማኝነት እንዲመለስ ይጠይቃል፡፡ ይኸው መጠን በአምላካዊው ጎተራ እንዲገባ ያዛል፡፡ ይህ ለተቀደሰ ዓላማ መዋል የሚኖርበት፣ ባለቤቱ እንደ ራሱ ንብረት የሚመለከተው አሥራት ቅዱስ እንደ መሆኑ፤ የደኅንነትን መልእክት ለሁሉም የዓለም ክፍሎች ለሚያስራጩ ወገኖች መዋል ይኖርበታል፡፡ ወደ አምላካዊው ግምጃ ቤት የሚፈሰው የገንዘብ መጠን የእውነት ብርሃን በቅርብም ሆነ በሩቅ ወዳሉ ወገኖች የሚደርስበት ነው፡፡ የጌታን ድንጋጌ በታማኝነት በመታዘዝ ሁሉም ነገር የእርሱ መሆኑን አምነን መቀበላችንን እናሳያለን፡፡”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 6, p. 386.

የመወያያ ጥያቄዎች:-፡

 

  1. ጊዜው በፍጥነት ወደ ዘላለማዊነት እየተሻገረ ይገኛል፡፡ የእግዚአብሔር የሆነውን ለራሳችን አናስቀር፡፡ በውስጣችን ምንም መልካም ነገር ሳይኖር መስጠት እንደማንችል ሁሉ ያለ አንዳች ጥፋት መከልከልም አንችልም፡፡ በፍጥረትም ሆነ በቤዛነት የእርሱ የሆነውን ልባችንን ምንም ሳናስቀር እንድንሰጠው ይጠይቀናል፡፡ ዕውቀትዎን እንዲያካፍሉ ሲጠይቆት ከማካፈል ወደ ኋላ አይበሉ፤ ገንዘብዎን ሲጠይቆትም እንዲሁ--ይስጡ ምክንያቱም የእርሱ ነውና፡፡”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 566. ኤለን ኋይት በዚህ መልእክቷ “የእግዚአብሔር የሆነውን ለራሳችን አናስቀር… በውስጣችን ምንም መልካም ነገር ሳይኖር መስጠት እንደማንችል ሁሉ ያለ አንዳች ጥፋት መከልከልም አንችልም” ስትል ምን ማለቷ ነው? አሥራት ሳንመልስ ስንቀር ከራሳችን ምን እንሰርቃለን?
  2. ሁሉም የቤተ ክርስቲያን አባላት አሥራታቸውን ከአምላካዊው “ጎተራ” በተቃራኒ ለፈለጉት ፕሮጀክት ቢያውሉ ሊከሰት በሚችለው አንደምታ ዙሪያ ተወያዩ፡፡ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ መጥፎ የሆነው ለምንድን ነው? በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ምን ሊከሰት ይችላል? እንዲህ ያለው ድርጊት በመሃላችን አስከፊ መሰነጣጠቅ የሚያስከትለው ለምንድን ነው?
  3. በሉቃ. 21 እንደምናነበው ምንም እንኳ የሱስ በወቅቱ በቤተ መቅደስ ይካሄድ የነበረውን ንቅዘት ያውቅ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ድኻዋ መበለት ይዛ ስለቀረበችው ስጦታ አመስግኗል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን በሚመለስ አሥራት አጠቃቀም ዙሪያ ጥያቄ አለኝ በሚል አሥራቱን ወደ ሌላ ፕሮጀክት ለማዞር ለሚያስብ ሰው ይህ ምን ሊያስተምር ይገባል?