ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዕብ. 11:8–12፣ ሮሜ. 4:13፣ 18–21፣ ማቴ. 6:24፣ ዕብ. 9:14፣ 1ዮሐ. 5:2-3፣ ሉቃ. 16:10–12፡፡
የመታሰቢያ ጥቅስ፦ “ እንግዲህ ሰው ሁሉ እኛን እንደ ክርስቶስ አገልጋዮችና እንደ እግዚአብሔር ምስጢር ባለ ዐደራዎች ሊቆጥረን ይገባል፡፡ ባለ ዐደራዎችም ታማኝ ሆነው መገኘት አለባቸው” ” (1ቆሮ. 4:1-2)፡፡
ንግዱ ማኅበረሰብ አካላት በንግድ ምልክቶችና ስያሜዎች እንደሚታወቁ
ሁሉ መጋቢዎችም በምልክቶቻቸው ወይም በልዩ መለያዎቻቸው
ይታወቃሉ፡፡ እንዲያውም ብዙዎች የገበያ ዕቃዎችን በማስተዋወቅ ዝነኞች እየሆኑ መጥተዋል፡፡
የክርስቲያን መጋቢ መለያ ምልክት ወይም አርማ የክርስቶስ ፍቅር ነጸብራቅ ነው፡፡ ይህ ነጸብራቅ መጋቢው ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ጎልቶ ይታያል፡፡ የክርስቶስን ባህሪ ስንለማመድና ስንኖርበት ህይወታችን የክርስትናን ምልክቶች ገልጦ ያሳያል፡፡
የእኛ ምልክት የእርሱ አርማ ነው፡፡ የእኛ ማንነት ከእርሱ የተዋሃደ ነው
(1ቆሮ. 6፡17)፡፡
በዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ለእግዚአብሔር መጋቢዎች ልዩ መለያ ያሰጧቸውን ባህሪያት ለይተን እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ባህሪያት ወደ የሱስ ዳግም ምጽአት እንድንመለከትና ለአምላካዊው እውነት ታማኝ ሆነን በዐደራ የተሰጠንን የመጋቢነት ሥራ እንድንሠራ ያበረታቱናል፡፡ እያንዳንዱ ባህሪ የጠፋውን ለመፈለግና ለማዳን ከመጣው ጋር ልንመሠርት ስለሚገባው ጥልቅ ግንኙነት ይገልጻል፡፡ እነዚህ ባህሪያት አብልጠው በተጠኑ ቁጥር በሕይወታችን ውስጥ ሥር እየሰደዱ ይሄዳሉ፡፡ ሁሌም ታታሪው የእግዚአብሔር የፍቅር ባህሪ የእኛ ምልክትና አርማ በመሆን ከዛሬ አንስቶ እስከ ዘላለም እያንዳንዱን የሕይወታችንን ክፍል የሚያነሳሳ ይሆናል፡፡
“ባለ ዐደራዎችም ታማኝ ሆነው መገኘት አለባው” (1ቆሮ. 4፡2)፡፡ ለታማኝ መጋቢ “መልካሙን የእምነት ገድል” (1ጢሞቴ. 6፡12) መዋጋትና ማሸነፍ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ “ታማኝ” እግዚአብሔር ሲሆን፤ በእኛ ውስጥ በሚሠራው በእርሱ የዚህ ባህሪ ባለቤት ማለትም ታማኞች እንሆናለን፡፡ ታማኝ መሆን ማለት ትክክል መሆኑን ለምናውቀው ነገር እውነተኛ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ በተለይ በልባችን ውስጥ ለሚካሄደው መንፈሳዊ ውጊያ ታማኝ መሆን ይጠበቅብናል፡፡
ትክክል በሆነውና በተሳሳተው እንዲሁም በበጎውና በክፉው መሃል መንፈሳዊ ግጭቶች መምጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡ እነዚህ ግጭቶች የእምነት ውጊያ አካል ናቸው፡፡ መጋቢዎችን በእያንዳንዱ ሁኔታ ከሌሎች የሚለያቸው ታማኝ ለመሆን መምረጣቸው ነው፡፡ እርስዎ ባለሀብት ለመሆን የሚወጥኑ፣ ሀብትንም የሚወዱ ከሆነ፤ ለእግዚአብሔር ያለዎት ታማኝነት በጽናት ለመቀጠሉና አፍቅሮተ ንዋይ ሊያስከትል ስለሚችለው አደጋ ጌታ የተናገረውን ሁሌም በልብዎ መያዝዎን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡ ዝነኛ የመሆን ብርቱ መሻት ካለዎት የእግዚአብሔር ቃል ስለ ትህትና ለሰጠው መልእክት ታማኝ ይሁኑ፡፡ የፍትዎት ሃሳብ ወደ አእምሮዎ እየመጣ እረፍት ከነሳዎት ስለ ቅድስና ለተሰጡት ተስፋዎች ታማኝ ይሁኑ፡፡ ለሥልጣን መሰላል የተለየ ፍላጎት ካለዎት እግዚአብሔር የሁሉም አገልጋይ ስለመሆን ለተናገረው ቃል ታማኝ ይሁኑ፡፡ ታማኝ ለመሆን ወይም ላለመሆን
ምርጫው ግማሽ ሰከንድ እንኳ የማይፈጅ--ውጤቱ ግን ዘላለማዊ ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡--ዕብ. 11:8–12፣ 17–19፣ ሮሜ 4:13፣ 18–21፡፡ ጥቅሶቹ ታማኝ ስለመሆን ምን ያስተምሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በዕብራውያን ቋንቋ “ታማኝነት”--እምነት የሚጣልበት የሚል ፍቺ አለው፡፡ “አሜን”--ተመሳሳይ መሰረት የሚጋራ የዕብራውያን ቃል ሲሆን “ጠንካራ” ወይም “ጥብቅ” የሚል ፍቺ አለው፡፡ ታማኝነት--ተፈትኖና ተሞክሮ ለእግዚአብሔር ዕቅድ በጽናት መቆምን ያሳያል፡፡
የተሐድሶ አራማጅ የነበረው ማርቲን ሉተር በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ለመናገር እየተዘጋጀ “ከእግዚአብሔር ቃል አንብቦ ሲያበቃ ወዳዘጋጃቸው ጽሑፎች መልከት አደረገና መልሱን በሚስማማ መልኩ ለማቅረብ ሞከረ… ሉተር ወደ ቅዱሳን መጻሕፍት ቀረበና… በስሜት ውስጥ ሆኖ ግራ እጁን በቅዱሱ መጽሐፍ ገጾች ላይ እንዳሳረፈ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ ከፍ አድርጎ--ምስክርነቱን በደሙ ለማተም እንኳ ዝግጁነቱን በመግለጽ--ለወንጌል ታማኝ ለመሆንና ያመነበትን እውነት በነፃ
ለመመስከር ማለ፡፡” —J. H. Merle d’Aubigné, History of the Reformation (New York: The American Tract Society, 1846), vol. 2, book 7, p. 260.
በራእ. 2፡10 “ ‘እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሁን’ ” የሚሉት ቃላት በየቀኑ ከጌታ ጋር ለምናደርገው ጉዞ ፍቺያቸው ምንድን ነው?
“ ‘አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል፡፡ እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም፡፡’ ” (ማቴ. 6:24)፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን እንዳለብን አስመልክቶ ጥቅሱ ምን ያስተምረናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
“ቀናተኛ” (ዘፀ. 34፡14) የእግዚአብሔር የስሙ ፍቺ መሆኑን ማወቃችን ለታማኝነት ብርቱ ጥሪ ሊያቀርብልን ይገባል፡፡ ለ “ቀናተኛው” አምላክ ታማኝ መሆን ለፍቅር ታማኝ መሆን ነው፡፡ ታማኝነት--በእምነት ተጋድሎአችን ማንነታችንን እንድንገልጽና ውጊያውን በጽናት እንድንቀጥል ያበረታታናል፡፡
ታማኝ መሆናችን ለእግዚአብሔር አስፈላጊ ነው (1ነገሥ. 8፡61)፡፡ ታማኝነት የደንቦች ዝርዝር ሳይሆን የግል እምነታችን፣ እውነታችንና መሰጠታችን ነው፡፡
ይህን ጥቅስ ያንብቡ 1ዜና 28፡9፡፡ ጥቅሱ ስለ ታማኝነት አስፈላጊነት ምን ያስተምረናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ታማኝነት ባለበት ክህደት ሊኖር የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩ መዘንጋት የለበትም፡፡ ታማኝነት እንደ ፍቅር ሁሉ ያለ አንዳች ተጽእኖ በነፃነት መበርከት ካልቻለ እውነተኛ መባል አይችልም፡፡ ወታደሮች በጦር ግንባር ከፊተኛው ረድፍ ተሰልፈው ከባላንጣዎቻቸው ጋር በሚፋለሙበት ወቅት እስከ መጨረሻው በጽናት ከመዋጋት ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡ ወደ ኋላ አፈገፍጋለሁ ቢሉ ከጀርባቸው በአዛዦቻቸው ጥይት ሊመቱ ይችላሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ወታደሮች ግዳጃቸውን እየተወጡ ቢሆንም ከታማኝነት የተነሳ ነው ሊባል ግን አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ይህ ዓይነቱን ታማኝነት አይደለም፡፡
የኢዮብን ታሪክ ለመቃኘት ብንሞክር--ኢዮብ ቤተሰቡን፣ ንብረቱንና ጤንነቱን ሊያወድም ያለውን አስፈሪ ክስተት አስቀድሞ አልተመለከተም፡፡ ምንም እንኳ የደረሰበት ነገር በእግዚአብሔር ላይ የነበረውን መታመን፣ ፍቅርና ቁርጠኝነት እርግፍ አድርጎ እንዲተው የማድረግ ኃይል ቢኖረውም--ኢዮብ ግን በእግዚአብሔር ላይ የማይናወጥ ግብረገባዊ ምርጫ ነበረው፡፡ ታማኙና እግዚአብሔርን በይፋ ለማመስገን ፍርሃት ያልነበረው ኢዮብ “ቢገድለኝም እንኳ በእርሱ ተስፋ አደርጋለሁ” (ኢዮ. 13፡15) ሲል ዝነኞቹን ቃላት ተናገረ፡፡ ኢዮብ ብርቱ አደጋ እየተጋፈጠ በነበረበት በዚያ ወቅት ያሳየው ታማኝነት እጅግ የረቀቀውንና ውበት የተላበሰውን ታማኝ መጋቢ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ሆነ፡፡
እስቲ ራስዎን እንዲህ ብለው ይጠይቁ፡ ህይወቱን ለእኔ ለሰጠው ጌታ ምን ያህል ታማኝ ነኝ? ያን ታማኝነት በተሻለ መግለጽ የምችለውስ እንዴት ነው?
አንጡራ ሀብታችን ልናደርጋቸው የምንችላቸው አያሌ የከበሩ ነገሮች አሉ፡፡ ጤና፣ ፍቅር፣ ጓደኛ፣ ቤተሰብ--እነዚህ ሁሉ በረከቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ከእነዚህም በላቀ ከሚያስፈልገው አንዱ ንጹህ ኅሊና ነው፡፡
እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዕብ. 10፡19-22፣ 1ጢሞቴ. 4፡1-2፡፡ ሐዋርያው “ክፉ ኅሊና” እና “ኅሊናቸው በጋለ ብረት የተጠበሰ” ሲል ምን ማለቱ ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ኅሊናችን ውጪያዊውን የሕይወታችንን ክፍል የሚቆጣጠር ውስጣዊ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ኅሊና ራሱን ከፍ ካለውና ፍጹም ከሆነው ከፍታ--ይኸውም ከአምላካዊው ሕግ ጋር ራሱን ማስተሳሰር ይኖርበታል፡፡ እግዚአብሔር ሕጉን በአዳም ልብ ውስጥ ጽፎ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኃጢአት እርሱን ብቻ ሳይሆን የእርሱን ትውልዶች ጭምር ጋርዶ ነበር፡፡ ስለዚህ ጥቂት የተሸራረፉ ሕጎች ብቻ ቀርተው ነበር፡፡ አሕዛብ “ኅሊናቸው ስለሚመሰክር፣ ሐሳባቸው ስለሚከሳቸው፣ ደግሞም ስለሚከላከልላቸው የሕግ ትእዛዝ በልባቸው የተጻፈ መሆኑን ያሳያሉ፡፡” (ሮሜ. 2፡15)፡፡ የእግዚአብሔር ሕግ በየሱስ ልብ ውስጥ በመኖሩ (መዝ.
40፡8) አዳም ሲወድቅ የሱስ ግን የስኬት ባለቤት ሆነ፡፡
ለመጥፎው ኅሊና ብቸኛው መፍትሔ ምን እንደሆነ አስመልክቶ ጳውሎስ ምን ይላል? ዕብ. 9:14፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
“ድር ያደራበት የህሊና ጓዳ አገልግሎት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ብሩህዎቹ የጽድቅ ጨረሮች ያለ አንዳች መከልከል መፈንጠቅ ይችሉ ዘንድ ወደ ምድር አቅጣጫ የሚከፈቱት የነፍስ መስኮቶች ሊዘጉ--ወደ ሰማይ አቅጣጫ ያሉት ደግሞ ወለል ብለው ሊከፈቱ የግድ ነው፡፡ አእምሮ በመልካምና በክፉ መሃል ያለውን ልዩነት በሚገባ መገንዘብ እንዲችል ንጹህና የጠራ ሊሆን የተገባ ነው፡፡” —Ellen G. White, Mind, Charac-
ter, and Personality, vol. 1, pp. 327, 328. የእግዚአብሔር ሕግ በአማኙ ልብ
ሲጻፍና (ዕብ. 8፡10) በእምነት የዳነው አማኝ ሕጉን የመከተል መሻት ሲያድርበት-በውጤቱ ንጹህ ኅሊና ይወለዳል፡፡
በጥፋተኝነት ስሜት ግብግብ ውስጥ ካለፉ ጉዳዩ ምን ያህል አሰቃቂ እንደሆነና ኅሊናን ያለማቋረጥ ሰላም እንደሚነሳ ያውቃሉ፡፡ ትኩረትዎን በየሱስና ስለ እርስዎ ኃጢአት በሞተበት መስቀሉ ላይ ማድረግዎ ከጥፋተኝነት ርግማን ነፃ ሊያደርግዎ የሚችለው እንዴት ነው?
አቤል በመታዘዝ መንፈስ እግዚአብሔር ያዘዘውን የበግ ጠቦት ይዞ በመሠዊያው ፊት ተንበረከከ፡፡ በሌላ በኩል ቃየን በቁጣ፣ ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ይዞ በሠራው መሠዊያው ፊት ተንበረከከ፡፡ ምንም እንኳ ሁለቱም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ቢያቀርቡም--ከወንድማማቾቹ መሃል የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የተከተለው አንደኛው ብቻ ነበር፡፡ የታረደው ጠቦት ተቀባይነት ሲያገኝ ከምድር ፍሬ የቀረበው መሥዋዕት ግን ተቃውሞ ገጠመው፡፡ ምንም እንኳ ሁለቱም ወንድማማቾች ስለሚቀርበው መሥዋዕት ትርጉምና መመሪያ ጠንቅቀው ያውቁ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን እንደ ጌታ ፈቃድ የታዘዘው አንደኛው ብቻ ነበር
(ዘፍ. 4፡1-5)፡፡
“ቃየን በየሱስ ክርስቶስ ደም የሚድንበትንና ወደ ክርስቶስ ያመላክት የነበረውን የመሥዋዕት ምሳሌ በመታዘዝ አምላካዊውን ዕቅድ ለመቀበል የመቃወሙ ውጤት የአቤልን ሞት አስከተለ፡፡ ቃየን ለዓለም የሚፈሰው የየሱስ ደም ምሳሌ እንዳይፈስ
ተቃወመ፡፡” —Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1109.
ታዛዥነት በአእምሮ ውስጥ ይጀምራል፡፡ መታዘዝ ከፍ ካለው የሥልጣን እርከን የሚወርደውን ትእዛዝ ለመፈጸም ኃላፊነትን በአእምሮ የመቀበል ሂደት ያካትታል፡፡ ታዛዥነት ከአንድ ከፍ ያለ አካል ጋር ዝምድና መኖሩን ተከትሎ የሚመጣና ያን አካል ለመታዘዝ በሚኖር ፈቃደኝነት ላይ የተገነባ ነው፡፡ እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ዝምድና አኳያ በፈቃደኝነትና በፍቅር ላይ የተመሰረተው መታዘዛችን ግብረገባዊ ባህሪያችንን ይቀርጻል፡፡ እግዚአብሔርን የምንታዘዘው እኛ እንደምናስበውና እንደምንመኘው ብቻ ሳይሆን ልክ እርሱ በሚያዘው መሰረት ሊሆን ይገባል፡፡ የቃየን ሁኔታ እግዚአብሔር የሚጠይቀውን ከመፈጸም ይልቅ
የራሱን ነገር እያደረገ ላለው ፍጹም ምሳሌ ነው፡፡
የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ዮሐ 5:2-3፣ ሮሜ 1:5፣ 10:16-17፡፡ መታዘዝ በሥራ ሳይሆን በእምነት ለዳነው ክርስቲያን ምን ማለት እንደሆነ ጥቅሶቹ ምን ያስተምሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
እግዚአብሔርን የምንታዘዘው ለመዳን አይደለም፡፡ ይልቁንም ስለዳን እንታዘዘዋለን፡፡ መታዘዝ ማመናችንን በተግባር የምንገልጥበት ግብረገባዊ መንገድ ነው፡፡ ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ ብሎት ነበር “ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣ በሚቃጠል ቁርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል” (1ሳሙ.
15፡22)፡፡
መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል ሲል ሳሙኤል ምን ማለቱ ነው? እንደ ክርስቲያን በተሳሳተው ርካሽ የጸጋ አስተምህሮ እንዳንወድቅ ይህ ምን ሊነግረን ይችላል?
በሉቃ. 16፡10-12 የቀረበው መልእክት ስለ ታማኝነት ምን ያስተምረናል? ይህ ባህሪ ለአንድ ታማኝ መጋቢ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ይህ የታማኝነት መርኅ በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ታሪክ--አራቱ ሌዋውያን የበር ጠባቂ አለቆች የብሉይ ኪዳኑን መቅደስ ክፍሎችና ግምጃ ቤቶች በሌሊት የመጠበቅ ዐደራ ተቀብለው ነበር፡፡ የጥበቃውን ሥራ የሚያከናውኑት እነርሱ በመሆናቸው የሚያድሩትም በዚያው በቤተ መቅደሱ አካባቢ ነበረ፡፡ ቁልፉ በእጃቸው በመሆኑ ጠኋት ላይ ደጆቹን የሚከፍቱት እነርሱ ነበሩ (1ነገሥ. 9፡26-27)፡፡ እነዚህ ሰዎች ኃላፊነት የሚጣልባቸው ሆነው በመገኘታቸው ዐደራው ተሰጥቶአቸው ነበር፡፡
እምነት የሚጣልበት ሰው መሆን የመልካም መጋቢ ጸባይ ነው፡፡ ይህ ማለት ታማኝ መጋቢዎች የእነርሱ ሚና ጥልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠንቅቀው ይገነዘባሉ፡፡ እግዚአብሔር የሚታመን አምላክ መሆኑን የሚያስተውሉት እነዚህ ወገኖች
እነርሱም እርሱን ለመምሰል ያልማሉ፡፡ (ዘዳ. 32፡4፣ ነገሥ፣ 8፡56)፡፡
እምነት የሚጣልበት ሰው መሆን የበሳል ባህሪ ባለቤትነትን ያመላክታል፡፡ ስለዚህ አንድ ግለሰብ ይህን ባህሪ ሲቀዳጅ በተመልካቾች ዐይን ከፍተኛ የጠባይ ብቃት ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል፡፡ በማናቸውም ዓይነት አስቸጋሪ ሁናቴ ላይ ሊገኙ ቢችሉ እንኳ ለተናገሩት ቃል ታማኝ መሆን የእግዚአብሔርን ጸባይ ማንጸባረቅ
ማለት ነው--(2ነገሥ. 12:15)፡፡
ዳንኤል በሁለቱ የዓለም ልዕለ ኃያላን አገሮች ነገሥታት ፊት እምነት የሚጣልበት ሰው መሆኑ ተመስክሮለት ነበር፡፡ ዳንኤል ያለ አንዳች ፍርሀት ጥበብ እና እውነትን በቀጥታ ለነገሥታት በማቅረብ--በታማኝ የአማካሪነት ህይወቱ ያተረፈው ዝና፤ በሟርተኞችና ጠንቋዮች ጉባዔ ቀጥተኛ ተቃውሞ ይገጥመው ነበር፡፡ ታማኝነት የሥነ ምግባር ዘውድ እንደመሆኑ የአንድን ሰው ግብረገባዊ መርኅዎች ከነንጽህናቸው ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ የመጋቢነት ብቃት በአንድ ሌሊት የሚቀዳጁት ሳይሆን--ለትናንሾቹ ነገሮች ታማኝ በመሆን የሚመጣ ነው፡፡
ሰዎች ምን ያህል ታማኝ እንደሆንን ይመለከታሉ፡፡ በቀላሉ በሌሎች ተጽእኖ ስር ወድቀን የማናረግድ፣ ወረት የማያጠቃን ወይም ሽንገላ የማይቃጣን ሆነን ስንገኝ ሰዎች ያከብሩናል፣ ይተማመኑብናል፡፡ እምነት የሚጣልበት ሰው መሆን-በእያንዳንዱ ምድራዊ ህይወት ለተሸከምነው ኃላፊነት የጸባይ ብቃታችንን ገልጦ ማሳየት እና ሰማይን በተጨባጭ መመስከር ነው፡፡ “ዓለማዊ ጥበብ ያላቸው ሰዎች-የእውነተኛ ባለጠግነት፣ የመልካምነት፣ የምኅረት፣ የርኅራኄና የመልካም ምግባር ባለቤት ሆነው የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች ይሆኑ ዘንድ፤ ታማኝና እምነት የሚጣልባቸው የክርስቶስ መንግሥት ሕዝቦች ሆነን ተጠርተናል፡፡” —Ellen G.
White, Testimonies for the Church, vol. 6, p. 190.
በግል ስለሚያውቁት እምነት ሊጣልበት የሚችል ሰው አሰብ ያድርጉ፡፡ እርስዎ ይበልጥ እምነት የሚጣልበት ሰው መሆን ይችሉ ዘንድ ከዚያ ሰው ምን መማር ይችላሉ?
ሌላው የመልካም መጋቢነት ምልክት ግለሰባዊ ተጠያቂነት ነው፡፡ “በየሱስ ላይ ሊሆን የተገባውን የሕዝቡን አስተሳሰብ ወደ ሰው በማዞር ግለሰባዊ ተጠያቂነትን ማጥፋት የቀደመው የሰይጣን አሠራር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ልጅ በፈተነው ጊዜ ይህ ዓላማው ቢከሽፍበትም፤ ነገር ግን በኃጢአት ወደ ወደቀው ሰብዓዊ ፍጡር ሲመጣ በተሻለ ስኬት ማግኘት ቻለ፡፡ ይህን ተከትሎ ክርስትና በብልሹ አሠራር ተዋጠ፡፡” —Ellen
G. White, Early Writings, p. 213.
ክርስቶስ የስብዕናችን ማዕከል መሆን ከቻለ ለአምላካዊው ምሪት ክፍት እንሆናለን፡፡ በውጤቱም በእኛ ውስጥ ያለው እምነት፣ ታማኝነት፣ የንጹህ ኅሊና ባለቤትነት፣ እምነት የሚጣልበት ሰው መሆናችንና የግል ተጠያቂነታችን በህይወታችን ይገለጣል፡፡ በመሆኑም እኛ እንደ መጋቢዎች ፍጹም ሆነን
በእግዚአብሔር እጆች ተሠርተናል (መዝ. 139፡ 23-24)፡፡
ግለሰባዊ ተጠያቂነት በእጅጉ አስፈላጊ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርኅ ነው፡፡ የሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ግለሰባዊ ተጠያቂነቱ ለአብ ነበር (ዮሐ. 8፡28)፡፡ ከአንደበታችን ለሚወጣው ለእያንዳንዱ ከንቱ ቃል ተጠያቂዎች ነን (ማቴ. 12፡48)፡፡ “ብዙ ዐደራ ከተቀበለም ብዙ ይጠበቅበታል” (ሉቃ. 12፡48)፡፡ የግለሰባዊ ተጠያቂነት ትልቁ ሥጋት የግል ኃላፊነቶቻችንን ወደ ሌላው የማስተላለፍ ዝንባሌአችን ነው፡፡ “በእጃችን ያለው መዋዕለ ንዋይ የግላችን ሳይሆን በአደራ የተሰጠን መሆኑን ልብ እንበል፡፡ እንዲያማ ባይሆን በራሳችን ውሳኔ የመስጠት ኃይል እንዳለን በማወጅ--ኃላፊነታችንን ወደ ሌሎች ገሸሽ እያደረግን መጋቢነታችንን ለእነርሱ በተውነው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም ጌታ እያንዳንዳችንን በግል መጋቢዎቹ አድርጎ ፈጥሮናል፡፡” —Ellen G.
White, Testimonies for the Church, vol. 7, p. 177.