መጋቢነት፡ ልብ አነሳሹ ሞተር
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከየካቲት 24 – 30

አስረኛ ትምህርት

March 3–March 9

የመጋቢነት ሚና

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ቆለ. 1:16–18፣ ዕብ. 4:14–16፣ 3ዮሐ. 3፣ ዘፍ. 6:13–18፣ ራእ. 14:6–12፣ 1ጴጥ. 1:15-16፡፡

 

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡-  “እግዚአብሔር በቅድስና እንድንመላለስ እንጂ ለርኩሰት አልጠራንምና” (1ተሰ. 4፡7)፡፡

የ መጋቢነት ጽንሰ ሃሳብ ከያዘው ስፋትና ጥልቀት አኳያ በግዙፉ ገጽታ ብቻ ተደምመን በቀላሉ ልንሰጥምና ውሉን ልንስት እንችላለን፡፡ መጋቢነት ቀላል ቢመስልም ነገር ግን ካለው ውስብስብ ይዘት አኳያ በቀላሉ በተሳሳተ አቅጣጫ ሊስተዋል ይችላል፡፡ ሆኖም ክርስቲያንም ሆነ ቤተ ክርስቲያን ከመጋቢነት ፋይዳ ውጪ ሊኖሩም፣ ሊሠሩም አይችሉም፡፡ ክርስቲያን መሆን መልካም መጋቢ መሆን ነው፡፡


“ይህ ጽንሰ-ሐሳብ ወይም ፍልስፍና ሳይሆን የሥራ መርኀ-ግብር ነው፡፡ የክርስትናን ሕግ የተከተለ የአኗኗር እውነት ነው. . . ሕይወትን በአጥጋቢ ሁኔታ ለማስተዋል ወሳኝና አስፈላጊ ነው፡፡ ለእውነተኛና በንቃት ለሚንቀሳቀስ ኃይማኖታዊ ተሞክሮ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ጉዳዩ ለአእምሮ ተስማሚ ሀሳብ የያዘ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን መላው የሕይታችንን ክፍል የሚነካ የበጎ ፈቃዳችን ውጤትና ቁርጠኝነት ወሳኝ ውል ነው፡፡” —LeRoy E. Froom, Stewardship in Its Larger Aspects (Mountain View: Calif., Pacific Press Publishing Association, 1929), p. 5.


አንዳንዶቹ የክርስቲያን መጋቢ እምቡጥ መርኅዎች ምንድን ናቸው? በዚህ ሣምንት መጋቢነት በክርስትና ሕይወት የሚጫወተውን ሚና የበለጠ እንመለከታለን፡፡

የካቲት  25
March 4
 

ክርስቶስ እንደ አስኳል

 

የሱስ የመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች አስኳል እንደመሆኑ (ዮሐ. 5፡39) ራሳችንን ከእርሱ ጋር ካለን ተዛምዶ አኳያ መመልከት ያሻናል፡፡ የሱስ የኃጢአትን ቅጣት ከፍሎ “ ‘ለብዙዎች ቤዛ’ ” ሊሆን መጣ (ማር. 10:45)፡፡ በሰማይም ሆነ በምድር ሥልጣን ሁሉ የየሱስ ነው (ማቴ. 28፡18)፡፡ ደግሞም ሁሉም ነገር በእጁ ውስጥ ነው (ዮሐ. 13፡3)፡፡ ስሙ ከሌሎች ሁሉ የላቀ ነው፡፡ እናም አንድ ቀን ጉልበት ሁሉ ለእርሱ ይንበረከክለታል (ፊልጵ. 2፡9-11)፡፡ “የሱስ የማንኛውም ነገር ሕያው አስኳል ነው” —Ellen G. White, Evangelism, p. 186.


ክርስቶስ የመጋቢነታችን የልብ ትርታና የኃይላችን ምንጭ ነው፡፡ በእርሱ ምክንያት ትርጉም ያለው ሕይወት እንኖራለን፤ እርሱ የሕይወታችን ማዕከላዊ ክፍል መሆኑንም ለወጪ ወራጁ ሁሉ እናሳያለን፡፡ ጳውሎስ በአያሌ ውጣ ውረዶች ውስጥ እንዳለፈ እንገምታለን፡፡ ሐዋርያው በማንኛውም ስፍራ ቢሆን ወይም ምንም ቢደርስበት ለመኖሩ አንድ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነበረው “ለእኔ መኖር ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ማትረፍ ነው” (ፊልጵ. 1፡21)፡፡


እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ቆለ. 1:16–18፣ ሮሜ 8:21፣ 2ቆሮ. 5:17፡፡ ለእኛ የሁሉም ነገር ማዕከል ክርስቶስ መሆኑን አስመልክቶ ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


የሕይወታችን አስኳል የሆነው ክርስቶስ የሌለበት እውነተኛ መጋቢነት የለም (ገላ. 2፡20)፡፡ “የተባረከ ተስፋችን” (ቲቶ 2፡13) ማዕከላዊ ክፍል ነው፡፡ “እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በእርሱ ነው (ቆለ. 1፡17)፡፡

በፈረሶች በሚጎተተው ሠረገላ--ሁለቱ ተሸከርካሪ አካላት የሚያያዙበት ዘንግ የጋሪውን ክብደት የሚሸከመው ማዕከላዊ ክፍል እንደመሆኑ፤ ክርስቶስ የመጋቢው ሕይወት እምብርት ነው፡፡ ሁለቱ ተሽከርካሪ አካላት የሚያያዙበት ጠጣር ዘንግ መንኰራኩሮቹ እንዲዘወሩ በማድረግ ለሠረገላው ጽናት እንደሚሰጥ--የሱስም የክርስትና ተሞክሮአችን ጽኑና አስተማማኝ አስኳል ነው (ዕብ. 13፡8)፡፡ በማንኛውም የምናስበውም ሆነ የምናደርገው ነገር ላይ የእርሱ ተጽእኖ ሊሰማን ይገባል፡፡ በዙሪያችን ያሉ የመጋቢነት ገጽታዎች እምብርት እርሱ ክርስቶስ ነው፡፡


“ ‘ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና’ ” (ዮሐ. 15:5)፡፡ የመጋቢነት ማዕከላዊ ክፍል ባዶውን የተተወ ከንቱ ነገር ሳይሆን ባህሪያችንን ለማረቅ ለአሁንና ለዘላለም በውስጣችን እየሠራ ያለ እውነት፣ ያውም ሕያው ክርስቶስ ነው፡፡


የሱስ የሕይወታችን አስኳል ነው ማለት አንድ ነገር ሲሆን ቢሆን ማለት ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ የሱስ በእርግጥ ፈቅደውለት ቃል በገባው መሰረት በውስጥዎ እየኖረ ለመሆኑ ምን ያህል እርግጠኛ መሆን ይችላሉ?

የካቲት  26
March 5
 

የቤተ መቅደሱ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ

 

ብዙውን ጊዜ አማኞች ቤተ መቅደሱን ከመጋቢነት ዐውድ አይመለከቱትም፡፡ የቤተ መቅደሱ አገልግሎት ለእምነታችን ወሳኝ ሥርዓት እንደ መሆኑ መጋቢነትም የዚህ ሥርዓት አካል ነው፡፡ “ክርስቶስ በሰማያዊው መቅደስ አገልግሎት የመስጠቱ ትክክለኛ ግንዛቤ የእምነታችን መሰረት ነው፡፡” —Ellen G. White, Evangelism, p. 221. የመጋቢነትን ሚና ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽንሰ ሃሳብ አኳያ ማስተዋላችን እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡


በ1ነገሥ. 7፡33 ስለ ሠረገላ መንኰራኩር የተጻፈ መልእክት እናገኛለን፡፡ የቤተ መቅደሱን ነገረ መለኮት የመንኰራኩሩ እምብርት አድርገን እንመለከታለን፡፡ ከሁለቱ የሠረገላው መንኰራኩሮች ወይም ተሸከርካሪ አካላት ጋር የተቆራኘው የሠረገላው እምብርት የሆነው ዘንግ በዞረ ቁጥር ለተሽከርካሪው አካል የበለጠ ጽናትና ጥንካሬ ይሰጣል፡፡ ለኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ከሞተ በኋላ በድል ያረገው (2ጢሞቴ. 1፡10) ክርስቶስ በሞቱ የቤተ መቅደስ አገልግሎት መሰረት በመሆን (ዕብ. 6፡19-20) ለእምነታችን ፅናት አስገኘ፡፡ አሁን በሰማያዊው ቤተ መቅደስ ሆኖ ስለ እኛ እያገለገለ ይገኛል (ዕብ. 8፡1-2)፡፡


“ሶላ ስክሪፕቱራ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የተሰኘውን መርኅ የምትከተለው ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ነገረ መለኮታዊ ሥርዓት የተገነባው ከቤተ መቅደሱ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ አጠቃላይ ምልከታ አኳያ ነው፡፡” —Fernando Canale, Secular Adventism? Exploring the Link Between Lifestyle and Salvation (Lima: Peru, Peruvian Union University, 2013), pp. 104, 105.


የሚከተሉት ጥቅሶች ስለ የሱስ የቤተ መቅደስ አገልግሎት ምን ይነግሩናል? 1ዮሐ. 2:1፣ ዕብ. 4:14–16፣ ራእ. 14:7፡፡


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


የቤተ መቅደሱ ነገረ መለኮት፤ የሁሉም ክርስትና ኃይማኖታዊ አስተምህሮ እምብርት የሆነውን ታላቁን የደኅንነትና የመዋጀት እውነት ገልጦ ለመመልከት ይረዳል፡፡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ--ስለ እኛ የሞተውን ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን በሰማያዊው መቅደስ እየሰጠ ያለውንም አገልግሎት እንመለከታለን፡፡ በተጨማሪም በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የእግዚአብሔርን ሕግ አስፈላጊነትና የመጨረሻውን የፍርድ እውነታ ማየት እንችላለን፡፡ በፈሰሰው የየሱስ ደም ዕውን መሆን የቻለው የቤዛነቱ ተስፋ--ዋንኛውና የዚህ ሁሉ ማዕከል ነው፡፡


በቤተ መቅደሱ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ እንደተገለጸው የመጋቢነት ሚና ከታላቁ የደኅንነት እውነት መልህቅ ጋር የተያያዘውን ሕይወት ያንጸባርቃል፡፡ ክርስቶስ ለእኛ ያደረገውንና እያደረገ ያለውን አብልጠን በጥልቀት ባስተዋልን ቁጥር ከመቼውም ይልቅ ወደ እርሱ፣ ወደ አገልግሎቱ፣ ወደ ተልዕኮውና ወደ አስተምህሮው እንቀርባለን--የመጋቢነትንም መርኅዎች በህይወታችን በተግባር እንገልጻለን፡፡

ከኃጢአት፣ ከራሳችንና ከራስ ወዳድነት ጋር እያደረግን ላለው ትግል--ዕብ. 4፡14-16 ምን ተገኝቶላችኋል ይለናል? ከጥቅሶቹ ብርታትና ተስፋ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

የካቲት  27
March 5
 

ክርስቶስን ማዕከል ያደረጉት ኃይማኖታዊ አስተምህሮዎች

 

ታላቁ የደኅንነት እውነት እና የመስቀሉ ትርጉም የተገለጸበት መቅደሱ የሁሉም ነገር ማዕከላዊ ክፍል ነው፡፡ ሁሉም ኃይማኖታዊ ትምህርቶቻችን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ከወንጌል ተስፋና ደኅንነት ጋር መቆራኘታቸው የግድ ነው፡፡ ስለ ሠረገላው ተሽከርካሪ አካል እንደተነገረው የሌሎች ኃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ምንጭ በየሱስ የሚገኘው የታላቁ የጽድቅ በእምነት እውነት ነው፡፡


“የክርስቶስ ለኃጢአት ሥርየት መሆን የሁሉም እውነቶች ስብስብ ታላቅ እውነት ነው፡፡. . . የአዳኙን አስደናቂ መሥዋዕትነት የሚያጠኑ በጸጋና በዕውቀት ያድጋሉ፡፡” —Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 5, p. 1137.


የሱስ በዮሐ. 14፡6 “ ‘እውነት’ ” ብሎ ስለ ራሱ ሲጠቅስ ምን ማለቱ ነው? ይህን ቃል ከዮሐ. 17፡17 ጋር ያስተያዩ፡፡ ከእውነት ጋር ምን እንፍጠር? (3 ዮሐ. 3)፡፡


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


የነገረ መለኮት ትምህርቶቻችን በማንነታችንና በምንመራበት አቅጣጫ ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ፡፡ ኃይማኖታዊ አስተምህሮዎች መስተዋል የማይችሉ ረቂቅ የነገረ መለኮት ጽንሰ ሀሳቦች አይደሉም፡፡ ሁሉም እውነተኛ አስተምህሮ በክርስቶስ ደኅንነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ እያንዳንዱ አስተምህሮ በተለያየ መንገድ በሕይወታችን ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይገባል፡፡ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት--የማንነታችን ሥረ መሰረት ከማንኛውም ነገር በላይ በኃይማኖታዊ አስተምህሮአችን ውስጥ በጥልቀት ይገኛል ማለት ይቻላል፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ የመነጩት አስተምህሮዎች የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ማንነት አቀዳጅተውናል፡፡

የመጋቢነት ሚና በየሱስ በተገለጠው መሰረት በመለኮት እውነት ውስጥ መኖር ሲሆን፤ በዚህ መሰረት መመላለስ በህይወታችን ላይ የአዎንታዊ የጥራት ባለቤት ያደርጋል፡፡ “በእርግጥ ስለ እርሱ ሰምታችኋል፤ በኢየሱስም እንዳለው እውነት በእርሱ ተምራችኋል፡፡ ቀድሞ ስለ ነበራችሁበት ሕይወት፣ በሚያታልል ምኞቱ የጎደፈውን አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤ ደግሞም በአእምሮአችሁ መንፈስ እንድትታደሱ፣ እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው፡፡” (ኤፌ. 4፡21-24)፡፡


እውነትን ማወቅ ብቻ ሳይሆን በእውነት መኖር ምን ማለት እንደሆነ ከጥቅሱ እንረዳለን፡፡ ኃይማኖታዊ አስምህሮዎች የቱንም ያህል ትክክል ሊሆኑ ቢችሉ መጋቢነት እነዚያን ትምህርቶች ማመን አይደለም፡፡ ይልቁንም መጋቢነት ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት እውነትን በሕይወታችን ገልጦ ማሳየት ነው፡፡

የካቲት  28
March 5
 

የሦስቱ መላእክት መልዕክት

 

በምድር ላይ የሚመጣውን ታላቅ ጥፋት አስመልክቶ እግዚአብሔር ሁለት ጊዜ ብቻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶአል፡፡ አንደኛው ለኖኅ ሲሆን (ዘፍ. 6፡13-18፣ ማቴ. 24፡37) ሁለተኛው--በሦስቱ መላእክት አማካኝነት የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ነው (ራእ. 14፡6-12)፡፡ እነዚህ መልእክቶች ወደፊት በምድር የሚከሰቱትን በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ትዕይንቶች የተሸፈኑበትን መጋረጃ ገልጠው ያሳያሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመልእክቶቹ ዙሪያ ያለን ግንዛቤ እየበሰለ ቢመጣም ነገር ግን መልእክቱና ተልዕኮው አሁንም “የሦስተኛው መልአክ መልእክት በሆነው እውነት” ይኸውም ክርስቶስን በማመን በሚገኝ ጽድቅ ላይ መተማን ያደርጋል፡፡ —Ellen G. White, Evangelism, p. 190


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡6-12፡፡ የመልእክቶቹ ፍሬ ነገር ምንድን ነው? ለዓለም ምን እያሉ ነው? ከመልእክቶቹ አኳያ ምን ዓይነት ኃላፊነት ወድቆብናል? መጋቢነት ከመልእክቶቹ ጋር ተያያዥነት የሚኖረው እንዴት ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት የእኛ ተልዕኮ ዓለም ለክርስቶስ ዳግም ምጽአት የሚዘጋጅበትን የሦስቱን መላእክት መልእክት ማቅረብ ነው፡፡ ዘላለማዊ ተጽእኖ ባለው በዚህ ጉዳይ ሕዝቦች ከውሳኔ መድረስ መቻል አለባቸው፡፡ በተልዕኮው ከእግዚአብሔር ጋር ሽርክና መፍጠር የመጋቢነት ሚና ነው (2ቆሮ. 5፡20፣ 6፡1-4)፡፡


“ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች በዚህ ዓለም በተለየ ሁኔታ ጠባቂዎችና ብርሃን ተሸካሚዎች ናቸው፡፡ ለሚጠፋው ዓለም የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ ለእነርሱ ተሰጥቶአል፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ላይ የሚነሳው አስደናቂ የብርሃን ጸዳል በእነርሱ ላይ ያንጸባርቃል፡፡ የመጀመሪያው፣ የሁለተኛውና የሦስተኛው መልአክ መልእክትን የማወጅ እጅግ የተከበረና የተቀደሰ ኃላፊነት ተሰጥቶአቸዋል፡፡ ከዚህ የላቀ ተፈላጊነት ያለው ሥራ ከቶ የለም፡፡ ምንም ዓይነት ነገር ትኩረታቸውን እንዲይዝ መፍቀድ የለባቸውም፡፡” —Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 9, p. 19.


ከመሬቱ ጋር ከሚነካካበት ነጥብ ጋር ቁርኝት ያለው የተሽከርካሪው አካል ጠርዝ የሦስቱን መላእክት ተልዕኮ ይወክላል፡፡ የእነርሱ ተልዕኮ መንፈሳዊ መዋለልን መከላከልና በመጨረሻዎቹ ክስተቶች ወቅት የእኛን ኃላፊነት መወሰን ነው፡፡ ይህን መልእክት ለዓለም የምናውጅ መጋቢዎች መሆን አለብን፡፡


ስለ መጨረሻዎቹ ክስተቶች ሲታሰብ በዚህ ጊዜ እንዲህ ይሆናል በሚሉ--የጊዜ ሠንጠረዦችን በማውጣትና በመመደብ መጠለፍ በቀላሉ ሊከሰት የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ የጊዜ ሠሌዳዎች የራሳቸው ሚና ሊኖራቸው ቢችልም ነገር ግን መልእክቱን ለዓለም ለመስበክ ካለን ብርቱ ቁርጠኝነት አኳያ የሱስን እና የእርሱን ለእኛ መሥዋዕት መሆን በቀዳሚነትና በማዕከልነት የሚያስቀምጡ ለመሆናቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

የካቲት  29
March 6

መጋቢነት

 

ክርስቶስ የተቀደሰ ህይወት እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ “ቅድስና” ን በጉልህ የሚያሳየው የእርሱ ሕይወት ፍጹም የሆነው መጋቢነት ሊኖረው የሚገባውን ገጽታ ይገልጣል (ዕብ. 9፡14)፡፡ ሕይወታችን በዐደራ የተሰጠንን ሀብት እንዴት ማስተዳደር እንዳለብን ባካተተና እግዚአብሔርን በሚያስደስት መንገድ መመራት አለበት፡፡ መጋቢነት የዚያ ቅድስና መገለጫ ነው፡፡


ጥቅሶቹን ያመሳክሩ፡ 1ጴጥ. 1፡15-16፣ ዕብ. 12፡14፡፡ “ቅዱስ መሆን” እና “ቅድስና” ምን ማለት ናቸው? ይህ ከመጋቢነታችን ጋር እንዴት ይዛመዳል?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ከመሬቱ ጋር ንክኪ የሚፈጥረው የሠረገላው ተሽከርካሪ ክፍል ዙሪያውን በብረት ሲለበጥ ረጅም ዕድሜ ሊኖረው እንደሚችል ሮማውያን ደርሰውበት ነበር፡፡ የዕደ ጥበብ ባለሙያው ብረቱን በእሳት እያጋለ ውጪያዊውን የጠርዝ ክፍል ይለብጠዋል፡፡ የጋለው ብረት የሚፈለገውን ቅርጽ ከያዘ በኋላ ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ሲነከር ይኮማተርና በተሽከርካሪው ጠርዝ ዙሪያ ልክክ ብሎ ይቀራል፡፡ ከዚያም ተሽከርካሪው ክፍል በተዘወረ ቁጥር የተለጠፈው የብረት ክፍል ብቻ ከመሬቱ ጋር ንክኪ ይፈጥራል፡፡


በሠረገላው ተሽከርካሪ ክፍል ጠርዝ ላይ የተለበጠው የብረቱ ጫፍ የመጋቢነትን ጽንሰ ሃሳብ ይወክላል፡፡ ይህ እንግዲህ መንፈሳዊ ህይወታችን በተጨባጩ ህይወታችን ላይ ሲለበጥ የሚስተዋል ገሃዳዊ እውነታ ነው፡፡ ህይወታችን ከውጣ ውረዶች ጋር ተጋፍጦ የሚያልፍባቸው የውድቀትና የስኬት ጎዳናዎች ናቸው፡፡ በአባጣ ጎርባጣው የዕለት ከዕለት ህይወታችን እምነታችን በተጨባጭ የሚፈተንበት አካሄድ ነው፡፡ መጋቢነት ውጪያዊው እኛነታችን የተለበጠበትን ማንነት እና ምን ያደረግን እንደሆን ገልጦ ያሳያል፡፡ የባህሪ እና በአግባቡ እየተመራ ያለ ህይወት ምስክር ነው፡፡ ክርስቶስን የሚገልጡት የየቀኑ ተግባሮቻችን ከመንገዱ ጋር ቀጥተኛ ንክኪ እንዳለው የሠረገላው ተሽከርካሪ ክፍል ናቸው፡፡


በተግባር የሚገለጡት ድርጊቶቻችን በብርቱ ኃይል የተሞሉ እንደመሆናቸው ለክርስቶስ በሚኖረን ቁርጠኝነት ቁጥጥር ስር ሊውሉ ይገባል፡፡ “ኅይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” (ፊልጵ. 4፡13) በሚለው የዋስትና ቃል እና ኪዳን ልንኖር የግድ ነው “በውስጣችን በሚሠራው መንፈስ ቅዱስ መቀደስ--የክርስቶስን ተፈጥሮ በሰብዓዊው ማንነት ውስጥ መትከል ነው፡፡ ሕያውና ንቁ መርኅ የሚከተለው ወንጌልን ያማከለ ኃይማኖት--ህይወቱ ክርስቶስ ነው፡፡ በታረቀ ባህሪና በመልካም ሥራ የተገለጠው የክርስቶስ ጸጋ ነው፡፡ የወንጌል መርኅዎች ከማንኛውም ተጨባጭ የዕለት ከዕለት የህይወት ክፍል መነጠል አይችሉም፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያናዊ የግንኙነት መስመርና ተግባር በክርስቶስ ያለውን የህይወት ተሞክሮ የሚወክል ሊሆን ይገባል፡፡” —Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 384.


እስቲ ወደ የቀኑ የህይወት ተሞክሮዎ መልከት ያድርጉ፡፡ እንደ አዲስ ፍጥረት--በውስጥዎ እየሠራ ያለውን ክርስቶስ በተጨባጭ ይገልጣል? የእርሱ ቅድስና በእርስዎ መገለጡን መመልከት እንዲችሉ ምን ዓይነት ብልህ ምርጫ ማድረግ ያስፈልጎታል?

የካቲት  30
March 7
 

ተጨማሪ ሀሳብ፡

 

የሠረገላ ተሸከርካሪ ውጫዊ ክፍል ከመሬቱ ጋር በሚያደርገው ፍትጊያ ከተወሰነ አገልግሎት በኋላ እየተለጠጠ ይሄዳል፡፡ ይህ ዳግም የማስተካከል ሥራ ራሱን ብረቱን አግሎ መቀጥቀጥ፣ ማረቅና የመሳሰሉትን ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ብረቱን ወደ ቀድሞው ለመመለስ የሚደረገው ይህ የማስተካከል ሥራ በቅድስና ውስጥ የሚገኘውን መጋቢነት በተጨባጭ ይወክላል፡፡ በሂደት የቱንም ዓይነት ከባድ ውጤት ሊከተል ቢችል--ለእያንዳንዱ አነስተኛም ሆነ ግዙፍ የህይወት ፈርጅ ምላሻችን በክርስቶስ አስተሳሰብ የተቃኘ ይሆናል፡፡ በዚህ መሰረት ለገንዘብ አጠቃቀማችን፣ ለቤተሰባዊው ወይም ለአሠሪና ለሠራተኛ ግንኙነት ለሁሉም የምንሰጠው ምላሽ እንደ ክርስቶስ ፈቃድ ይሆናል፡፡ ሆኖም ብዙዎቻችን በሚገባ እንደምናስተውለው አንዳንዴ እነዚህን ትምህርቶች የምንማረው “ምከረው፣ ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው” የሚለውን ብሂል እየተከተልን ነው፡፡


ቅርጹን ያጣውን ብረት ወደ ቀድሞው መመለስ ቀላል ሥራ እንደማይጠይቅ ሁሉ፤ የሰውንም ጸባይ ማረቅ ከባድ ነው፡፡ እስቲ ስለ ጴጥሮስ ተሞክሮ ያስቡ፡፡ የሱስ በነበረበት የማይጠፋው ጴጥሮስ የሱስ እንዲህ ይለኛል ብሎ አልጠበቀም “‘እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ’ ” (ሉቃስ 22፡32)፡፡ ጴጥሮስ በየሱስ ላይ ክህደት ከፈጸመ በኋላ የተለወጠ ህይወት ባለቤት ለመሆን ቢበቃም፤ ነገር ግን ይህ የሆነው በአስቸጋሪና ከባድ የመከራ ተሞክሮ ውስጥ ካለፈ በኋላ ነበር፡፡ አሁን የጴጥሮስ መጋቢነት እንደገና ትክክለኛውን ቅርጽ ያዘ፡፡ ጴጥሮስ አዲስና የተለወጠ ሰው ሆነ፡፡ ህይወቱ ወደ አዲስ አቅጣጫ ማምራት ጀመረ፡፡ ሆኖም ይህ መሆን የቻለው እውነተኛ ዋጋ ከከፈለ በኋላ ነበር፡፡

የመወያያ ጥያቄዎች:-

 

  1. ተግባራዊው የጽድቅ ሥራ የሱስ “‘ከኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየዕለቱ ይሸከም ’” (ሉቃስ 9፡23) በማለት ከሰጠው መመሪያ ጋር ያለው ተዛምዶ ምን ይመስላል? በገላ. 6፡14--መሰረት የተሰቀለው ምንድን ነው? ይህ የቅድስናን ሂደት እንዴት ያሳየናል? ተግባራዊው ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ማሰብ እንድንማር እንዴት ይረዳናል? 1ቆሮ. 2፡16፡፡
  2. ጌታን መከተልዎ እና የክርስትና ህይወት ጉዞዎ ያመጣው ፈተናና መራር ሁኔታ በሰጠዎት ብርቱ ትምህርት ዙሪያ ተሞክሮዎ ምን ይመስላል? በዚህ ዙሪያ ተሞክሯቸውን ለመናገር ምቾት ያላቸው የሰንበት ትምህርት ጥናት አባላት የተማሩትን ያካፍሉ፡፡ አንዱ ከሌላው ተሞክሮ ምን መማር ይችላል?
  3. እኛ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ከሌሎች የክርስትና ተቋማት በተለይ ስለ ያዝናቸው አስተምህሮዎች አሰብ ያድርጉ፡ ሰንበት፣ የሞቱ ሰዎች ሁኔታ፣ ፍጥረት፣ ዳግም ምጽአት. . . እነዚህ የተለያዩ የእምነታችን ክፍሎች በአጠቃላዩ አኗኗራችን ላይ ተጽእኖ የሚኖራቸው እንዴት ነው?