መጋቢነት፡ ልብ አነሳሹ ሞተር
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከመጋቢት 1 – 7

አስራአንደኛ ትምህርት

March 10–March 16

የእያንዳንዱን ቀን ውሳኔ የሚሻው-- ዕዳ

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ መዝ. 37:21፣ ማቴ. 4:3–10፣ ማቴ. 6:33፣ ዘዳ. 28:12፣ ምሳ. 13:11፣ ምሳ. 21:5፣ 2ቆሮ. 4:18፡፡

 

የሳምንቱ መሪ ጥናት ጥቅስ፦ “ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ከሆነ ግብርን፣ ቀረጥ ከሆነም ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባውም ክብርን ስጡ፡፡ ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ባልንጀራውን የሚወድ እርሱ ሕግን ፈጽሞአልና፡፡" (ሮሜ 13፡7-8)፡፡

ንዳንዴ ገንዘብ መበደር ፈልገው ሊያበድርዎ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ሲያገኙ ራስዎን እንደ ዕድለኛ ሊቆጥሩ ይችላሉ፡፡ ምናልባት ግለሰቡ እንዲያ ለማድረግ የወሰነው ከንጹህ መነሻ ምክንያት መንስኤነት ይኸውም ከደረሰብዎ የገንዘብ ዕጥረት እንዲወጡ ለማገዝ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው ሲታይ ሰዎች በቅን ልቦና ተነሳስተው ገንዘባቸውን አያበድሩም፡፡ ይልቁንም ተጨማሪ ገንዘብ ፍለጋ በአራጣ መልክ ይሰጣሉ፡፡

ከዕዳ ለመራቅ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን፡፡ እርግጥ ነው በአንዳንድ ሁኔታዎች ማለትም ቤት ወይም መኪና ለመግዛት፣ ቤተ ክርስቲያን ለመገንባት ወይም ትምህርት ለመማር ገንዘብ መበደር ሊያስፈልገን ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በተቻለ መጠን በአስቸኳይ ከዕዳው ለመውጣት አቅደን በብልሃት መከወን አለብን፡፡

ግን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ የሌለንን ገንዘብ ማባከን ለእግዚአብሔር ሕዝቦች “በባህሪያቸው ላይ እንዲሠለጥን ሊያደርግ ወደ ሚችለው የአጉል ምኞት እና የምድራዊው ሀብት ፍቅር መግቢያ መንገድ ነው፡፡ እነዚህ ባህሪያት እስከ ገዙን ድረስ ደኅንነትና ጽድቅ ከበስተ ኋላ ይቀራሉ፡፡” —Ellen G. White, Early Writings, p. 267.

ከዕዳ ለመራቅና በሥርዓት ለመመላለስ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ እንድንችል ክህሎቶቻችንንና ችሎታዎቻችንን ማሻሻል አለብን፡፡ በዚህ ሳምንት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዕዳ ምን እንደሚል እንመለከታለን፡፡

ጥር 2
March 11
 

መበደርና ማጥፋት

  

ነቢያቱና ኤልሳዕ እንጨት ሊቆርጡ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርደው “አንዱ ዛፍ እየቆረጠ ሳለ መጥረቢያው በሮ ከውሃው ውስጥ ወደቀ፤ እርሱም ‘አየ ጉድ ጌታዬ፤ የተውሶ መጥረቢያ እኮ ነው!’ ብሎ ጮኸ” (2ነገሥ. 6፡5)፡፡ “ተውሶ” ማለት የሌላ ሰው የሆነን ንብረት በባለ ንብረቱ ፈቃድ ወስዶ መጠቀም የሚል ፍቺ አለው፡፡ ይህ ፈቃድ አደጋ ሊያመጣ የሚችል ብርቱ ኃላፊነት ይዞአል፡፡ አንድ ሰው የተበደረውን ገንዘብ ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ማዋሉን ተከትሎ የከፋ መዘዝ ሊመጣ ይችል እንደሆነ እንጂ ገንዘብ መበደር ወይም መጥረቢያ መዋስ ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ እንዲሉ ሁለቱም ያው አንድ ናቸው፡፡

ገንዘብ የምንበደርበት ብቸኛው ምክንያት የተቸገርንበት ጉዳይ ላይ ለማዋል ነው፡፡ አደጋ ሊያስከትል የሚችለውን ብድር የመክፈል አቅም እንዳለን እና ለወደፊቱ ምንም ዓይነት የበጀት ጉድለት እንደማይኖር በማሰብ እንበደራለን፡፡ ሆኖም ግን የወደ ፊቱን አናውቅም (መክ. 8፡7)፡፡ ስለዚህ ገንዘብ መበደር ሁሌም አደጋ አለው፡፡

የሚከተሉት ጥቅሶች ስለ ዕዳ ምን ይላሉ?

መዝ. 37:21 ____________________________________________________________________________

መክ. 5:5 ___________________________________________________________________________

ዘዳ. 28:44, 45 ______________________________________________________________________

ምናልባት በጥበብ እንጠቀመዋለን በሚል እሳቤ ገንዘብ እንበደር ይሆናል፡፡ ነገር ግን በብድር እጃችን የገባውን ገንዘብ ለማጥፋት መፈተናችን ወደ ሌላ አስቸጋሪ ሁናቴ ውስጥ ይከተናል፡፡ እርግጥ ነው የተበደርነውን ገንዘበ ማጥፋት አኗኗራችን ላይ ቀውስ በመፍጠር አቅማችንን ይፈታተናል፡፡ ለመበደር እየተፈተኑ የማጥፋት ባህል ደኻውንም ሆነ ሀብታሙን እያቃወሰ ያለ የፍጆታው ገበያ የልብ ትርታ ነው፡፡ ለመበደር ስንፈተን የእግዚአብሔርን እርዳታ መማጸን የግድ ይሆናል (1ቆሮ. 10፡13) ምክንያቱም መበደር እርግማን ሊሆን ይችላልና (ዘዳ. 28፡43-45)፡፡

ገንዘብ የመበደር መጥፎ ልማድ አይጀምሩ፡፡ ከጀመሩም በተቻለ ፍጥነት ከፍለው ይጨርሱ፡፡ ገንዘብን ለአንገብጋቢ ጉዳይ ብቻ በማዋሉ ረገድ ብልህ እንሁን፡፡ እግዚአብሔር በብሩ ላይ የሾመን ጌቶች እንጂ ዓለም ለገንዘቧ የካነችን አንሁን፡፡

በእርግጥ ገንዘብ ልንበደርባቸው የሚገቡ አንዳንድ ሁናቴዎች አሉ፡፡ ሆኖም በጥንቃቄና ሁሉንም የተበደርነውን መጠን በምንችለው ፍጥነት ለመክፈል በማቀድ ልንተገብረው ይገባል፡፡

አጥብቆ በዕዳ መያዝ ምን ዓይነት መንፈሳዊ አደጋዎች ያስከትላል?

ጥር 3
March 12

መጋቢነትና ቅጽበታዊው እርካታ

  

“ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ እርሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ፡፡ ዔሳው ብኩርናውን እንዲህ አድርጎ አቃለላት፡፡” (ዘፍ. 25፡34)፡፡ ዔሳው ስሜቱን ብቻ አጥብቆ የሚከተል አስቸጋሪ የውጭ ሰው ነበር፡፡ ቤት ደርሶ ወንድሙ የሠራው ምስር ወጥ እንደሸተተው ወዲያውኑ መብላት እንዳለበት ተሰማው፡፡ ከዚህ ውጪ በረሃብ ልሞት ደርሻለሁ ማለቱ የማይመስል ነበር፡፡ በጠንካራ ውስጣዊ ስሜት ቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ዔሳው የጊዜያዊው ስሜቱ ግፊት የማመዛዘን ኃይሉ ላይ እንዲያይል በመፍቀድ፤ ብኩርናውን ለአንድ ጊዜ መብል ቅጽበታዊ እርካታ ሸጠው፡፡ ዔሳው ብኩርናው እንዲመለስ “በእንባ ተግቶ ቢፈልግም መልሶ ሊያገኘው አልቻለም” (ዕብ. 12፡17)፡፡

በተቃራኒው የየሱስ ምሳሌነት ተሰጥቶናል፡፡ የሱስ ለ40 ቀናት በመጾም ተርቦ በነበረበት ወቅት ሰይጣን ሦስት ጊዜ ፈተነው (ማቴ. 4፡3-10)፡፡ የሱስ ግን የቀረቡለትን ፈተናዎች ምንነት ከመመልከት ውጪ በዚያ በረሃብ በተዳከመና በዛለ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ስለ ሥጋው እርካታ አላሰበም፡፡ የሱስ ህይወቱን ሙሉ በኃጢአት የሚገኘውን ደስታና እርካታ ሲቃወም ኖሮአል፡፡ በዚህም እኛም በኃጢአት ላይ ኃይል ሊኖረን እንደሚችል አሳይቶናል፡፡ በብኩርናው ያልተደራደረው ወይም ብኩርናውን ያልሸጠም እርሱ--ሁላችንም አብረነው ወራሾች እንሆን ዘንድ ጥሪ ያቀርብልናል (ሮሜ 8፡17፣ ቲቶ 3፡7)፡፡ የሱስ በተፈተነ ጊዜ የሰጠንን ምሳሌ እየተከተልን ብኩርናችንን እንጠብቃለን (1ቆሮ. 10፡13)፡፡

ከምድራዊው ህይወት በኋላ ልምድ የምንቀስምበት ዕድል ስለሌለን፤ ይህ ዓለም ሊሰጠን የሚችለው ምርጥ ነገር ቢኖር ተሞክሮ ነው፡፡ ለራስ መኖር ለእግዚአብሔር ከመኖር ጋር ይቃረናል፡፡

የሚከተሉት ጥቅሶች ቅጽበታዊ እርካታ በታማኝ ወገኖች ላይ ጭምር ሊያስከትል ስለሚችለው አደጋ ምን ያስተምሩናል? 2ሳሙ. 11:2–4፣ ዘፍ. 3:6፣ ፊልጵ. 3:19፣ 1 ዮሐ. 2:16፣ ሮሜ 8:8፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ለጊዜያዊው እርካታ የሚቋምጥ አእምሮ ያልተገራና በቁጥጥር ስር ያልዋለ የመሆኑ ምልክት ነው፡፡ ይህ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ጠንቅ የሆነ ግልብ ባህሪ የትዕግሥት ጠላት እንደመሆኑ በተጠያቂነት ላይ እየተሳለቀ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ለጊዜያዊው እርካታ የመቋመጥን ስሜት ማዘግየት መቻል የዕውቀትን መርኅ መከተል ነው፡፡ ልዩ ልዩ ግፊቶችንና የምንገኝባቸውን ሁናቴዎች በአግባቡ ለመምራት የሚረዳን የሕይወት

ክህሎት ነው፡፡ በተለይ ዓለም ከሚያቀርብልን የገንዘብ ብድር ጥበብ በጎደለው አካሄድ ከመዘፈቅ የሚጠብቀን ነው፡፡ ሆኖም ይህ ጽንሰ ሃሳብ ዓለማዊ አወቃቀርን በተከተለው በፍጥነት ፍላጎትን የማርካትና በቅጽበት ሀብታም የመሆን ምድራዊ መላ ፊት ዝነኛ አይደለም፡፡ ፈጣን የሆነውን ቅጽበታዊ ደስታና እርካታ አንዴ ከተለማመድን በዚያ አናበቃም፡፡ ይልቁንም አሁንም፣ አሁንም እንፈልጋለን፡፡ ከእግዚአብሔር ስጦታዎች የተቀበልን መጋቢዎች በእንዲህ ዓይነቱ ወጥመድ መውደቅ የለብንም፡፡

ጥር 4
March 13
 

ገቢን ያገናዘበ አኗኗር

  

“በጠቢብ ቤት ምርጥ ምግብና ዘይት ተከማችቶ ይገኛል፤ ተላላ ሰው ግን ያለ የሌለውን ያሟጥጣል” (ምሳ. 21፡20)፡፡ ጥቅሱ እንደ ገቢው መጠን በኃላፊነት ቤቱን የሚያስተዳድረውን መጋቢ ከቅንጡውና አባካኙ ጋር በማነጻጸር ያቀርብልናል፡፡ ተላላ ሰዎች በገቢያቸው መጠን ለመኖር የሚያስችላቸውን ዕቅድ አያወጡም፡፡ ገንዘባቸውን በጥበብ ማስተዳደር ወይም በቁጠባ መኖር እንደ ማይፈለግ ምግብ--መከራ ሆኖ ስለሚሰማቸው ሥርዓት ወይም ረብ በጎደለው አካሄድ የተበደሩትን ሳይቀር እጃቸው ላይ ያለውን በሙሉ ያባክናሉ፡፡ ሆኖም እንደ ቤት ላለው ቋሚ ንብረት በጥንቃቄ መርምረንና በአቅማችን መኖር እንዳለብን አገናዝበን ልንበደር እንችላለን፡፡

ሀብታሞች ሀብታቸው ሳይነካ በበቂ ሁኔታ መተዳደር ይችላሉ፡፡ የእነርሱ ችግር ሁሌም ስለ ሀብታቸው መጨነቃቸውና እንዴት ሊጠብቁት እንደሚገባ ሌት ተቀን ማሰላሰላቸው ነው፡፡ ሰዎች ገቢያቸው በጣም አነስተኛ ሆኖ ደሞዝ ደረሰ አልደረሰ ብለው ግራ የሚጋቡ ከሆነ፤ ጭንቀታቸው ሀብት ማፍራት ሳይሆን ህይወትን ጠብቆ ማቆየት ነው፡፡ የቱንም ያህል መጠን ያለው ገንዘብ እጃችን ላይ ቢኖር፤ በዚያው ልክ እንዴት መኖር እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይሰጠናል፡፡ ጳውሎስ ህይወትን እጅግ ቀለል አድርጎ በማቅረብ “ነገር ግን ምግብና ልብስ ካለን፣ ያ ይበቃናል” (1ጢሞቴ. 6፡8) ሲል ምክሩን ይለግሳል፡፡ ምድራዊውን ሀብትና ንብረት እጅግ አንገብጋቢ አድርጎ የማይመለከተው ጳውሎስ፤ ለእርሱ በክርስቶስ መኖር በቂ እንደሆነ ይናገራል (ፊልጵ. 1፡21)፡፡

ከምንም ነገር በላይ የትኛው መርኅ ሊታወስ የግድ ነው? ማቴ. 6፡33፡፡ በዚህ መልኩ ህይወታችንን መምራት እንዳለብን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ገንዘባችንን እንደ ገቢ ሳይሆን ነገር ግን በዐደራ እንድናስተዳድረው እንደ ተሰጠን ሀብት ልንቆጥር ይገባል፡፡ ዕቅድ ወይም በጀት ማውጣት ይህን ተግባር ለመፈጸም የምንጠቀምበት ዓይነተኛ ዘዴ ነው፡፡ ዕቅድ በጥልቅ ሊጠና የሚገባው ዕውቀት የሚሻ ክህሎት ነው፡፡ ሚዛናዊ በሆነ የገንዘብ ዕቅድ አስተዳደር ስኬታማ ለመሆን፤ በሥርዓት የታነጸ ተግባርና ጥረት አስፈላጊ ነው (ምሳ. 14፡15)፡፡ የመጋቢነት መርኀ ግብርን ተከትለን የገንዘብ አያያዝ ስኬት ላይ ለመድረስ ቁርጥ ሃሳባችን ከሆነ፤ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑትን የገንዘብ አያያዝ ስህተቶች ማስወገድ እንችላለን፡፡

በገንዘብ አያያዝ ላይ ችግር ከገጠሞት ዕቅድ ያውጡ፡፡ ዕቅዱ የተወሳሰበ መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ የጥቂት ወራቶችን አጠቃላይ ወጪ ድምር ሠርቶ የወሩን አማካይ ወጪ ማግኘት ይቻላል፡፡ ምንም ቢመጣ ፍንክች ሳንል በወጣው ዕቅድ መሰረት መኖር ዋናው ቁልፍ ነገር ነው፡፡ ይህን በማድረግ ከዕዳ መራቅ ይቻላል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃስ 14፡ 27-30፡፡ በጥቅሱ የሱስ ደቀ መዝሙርነት ስለሚያስከፍለው ዋጋ በምሳሌ ሲናገር፤ ህንፃ የሚሠራ ሰው ግንባታው የሚፈጅበትን ወጪ አስቀድሞ አስልቶ ወደ ሥራ እንደሚገባና--ማጠናቀቅ ካልቻለ ግን ምን ሊከሰት እንደሚችል ያሳየናል፡፡ ከዚህ ምሳሌ ስለ መጋቢነት ልናገኝ የሚገባው ትምህርት ምንድን ነው?

ጥር 5
March 14
 

ባለ ዕዳ መሆንን መቃወም

  

ዘዳ. 28፡12 ብዙ ዕዳ ውስጥ ስለ መግባት ምን ያስተምረናል? በጥቅሱ በሥራ ላይ የምናየው መርኅ ምንድን ነው?

ዕዳን በተቻለ መጠን ማራቅ እንዳለብን ብዙዎቻችን ይሰማናል፡፡ ሌላው ለተበደረው ነገር ተያዥ ወይም ዋስ መሆንን መጽሐፍ ቅዱስ አይበረታታም (ምሳ. 17፡18፣ 22፡26)፡፡ ዕዳ በነገ ላይ ተጽእኖ አሳድሮ ከዚያው ከምንገኝበት ደካማ የገቢ ሁኔታ ላይ መልሰን እንድንሰጥ ያስገድደናል፡፡ አዳራሽ መጋበዝ ለመደና ሰዉ፤ ዕዳስ መብላት ሆነ የሚያስለቅሰው፤ እንዲሉ ክርስቲያኖች ከዚህ መራሩን ጣዕም የሚቀይር ከሚመስላቸው ዕዳ ለመታቀብም ሆነ እንዴት መምራት እንዳለባቸው ሲቸገሩ ይስተዋላሉ፡፡ ዕዳ ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር በሚል ባይፈረጅም፤ መንፈሳዊ ህይወታችንን ግን አያጠነክርም፡፡

“ቤታችንን ስናስተዳድር በበጀት አጠቃቀም ዙሪያ ቆምጨጭ ካላልን ከባድ ዕዳ ውስጥ ልንገባ የምንችልባቸው ሁናቴዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ያስቀመጡትን ገደብ ጥሰው አይውጡ፡፡ በሽታን እንደሚርቁ በራስዎ ላይ መከራ ሊያመጣ የሚችለውንም ዕዳ አጥብቀው ይራቁ፡፡

በብድር የተወሰደ ገንዘብ የአበዳሪ ግዞተኛ ያደርጋል--“ተበዳሪ የአበዳሪ ባሪያ ነው” (ምሳ. 22፡7)፡፡ ብድር ከዓለማችን ምጣኔ ሐብት ጋር ድርና ማግ ሆኖ በመጣመሩ እንደ ተለመደ ነገር እንወስደዋለን፡፡ ለነገሩ አገራት ሁሉ የሚንቀሳቀሱት በብድር አይደል? በተመሳሳይ ሰዎች ቢበደሩ ክፉቱ ምኑ ላይ ነው? እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ መያዝ ስህተት ነው፡፡

“በአምላካዊው በረከት ዕዳዎን ከፍለው ይጨርሳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ጎመን በጤና ብለው ከማንኛውም ብድር ለመራቅ ከእግዚአብሔር ጋር ጽኑ ኪዳን ይግቡ፡፡ በአነስተኛ ወጪ በቂና የተመጣጠነ ምግብ በቤት አብስሎ መመገብ በጣም ቀላል ነው፡፡ እርስዎ ለዝርዝሮቹ ሳንቲሞች ከተጠነቀቁ ድፍኖቹ ብሮች ራሳቸውን ይጠብቃሉ፡፡ እዚህም እዚያም የምንዘራቸው ትናንሽ የሚመስሉ ሳንቲሞች ብዙም ሳይቆይ ዋናውን ብር ይዘው ይነጉዳሉ፡፡ በዕዳ አጥር ተከብበው እያሉ ቢያንስ ሳያቅማሙ ራስዎን ይካዱ፡፡ ባለ ዕዳ ለመሆን የመረጡበትን አስተሳሰብም ሆነ እንደ ፈለጉ የመሆንን ልል ፍላጎት ይካዱ--እያንዳንዷን ሳንቲም አጠራቅመው ብድርዎን ይክፈሉ፡፡ ከዚህ በኋላ በተቻሎት ፍጥነት ከዕዳ ያምልጡ፡፡ ዳግም ነፃ ሰው ሆነው በሁለት እግሮችዎ መቆም ከቻሉ በኋላ ከማንም ምንም አይበደሩ፡፡ ይህ ሲሆን የታላቅ ድል ባለቤት ይሆናሉ፡፡” —Ellen G. White, Counsels on Stewardship, p. 257.

ዕዳ ክርስቲያኖችን ሊያቆም የማይችል ደካማ መሰረት ነው፡፡ መንፈሳዊ ተሞክሮአችንን ይጎዳል፤ የእግዚአብሔርን ሥራ በምንደግፍበት ችሎታ ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ ለሌሎች በልበ ሙሉነት ለመለገስ የሚያስችለንን ብቃት ከመዝረፉ በተጨማሪ--ከእግዚአብሔር በረከት ለመቀበል የሚያስችሉንን ዕድሎች ይሰርቃል፡፡

አላስፈላጊ ባለዕዳነትን ለማስወገድ የሚረዱዎትን ምን ዓይነት ምርጫዎች አሁን ማድረግ ይችላሉ? ከዕዳ ነፃ ሆነው ለመኖር ምን ማድረግ ይኖርቦታል?

ጥር 6
March 15

ቁጠባና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት

 

ጉንዳኖች ለክረምት የሚሆናቸውን ቀለብ በበጋ ሠርተው ይሰበስባሉ (ምሳ. 6፡6-8)፡፡ እኛም ገንዘባችንን ለአንድ የተወሰነ ዓላማ ያለማቋረጥ ስንቆጥብ የእነርሱን አሠራር ማጤናችን ብልህነት ነው፡፡ የምንቆጥብበት ምክንያት ከማባከን በተቃራኒ ለኑሮ የሚያስፈልገንን ወጪ በበቂ ሁኔታ ለመያዝ ወይም የምናገኘውን ለማከማቸት ነው፡፡ ገንዘብ ማስተዳደር ብልሃትን፣ በጀት ማውጣትንና በዲሲፕሊን መምራትን ይጠይቃል፡፡ የምንቆጥበው ለራሳችን ብቻ ከሆነ--መጋቢዎች መሆን ሲገባን የእግዚአብሔርን ሐብት እየሰረቅን ነው፡፡

“በአላስፈላጊ መንገድ የሚጠፋ ገንዘብ በእጥፍ እንደ ባከነ ይቆጠራል፡፡ ገንዘቡ መጥፋቱ ሳያንስ የመቆጠብ ክህሎትንም ያዳክማል፡፡ ታዲያ ይህን ብር ለይተን አስቀምጠን ቢሆን ኖሮ በምድር በቁጠባ በተባዛ ወይም በሰማይ በመስጠት በበለጸገ ነበር. . . ቁጠባ በገንዘብ ላይ ያለንን ሥልጣን የሚያጎለብት መልካም ምግባር ነው፡፡ ሁሉ አማረሽ ሆነን ገንዘብ እንዲቆጣጠረን በመፍቀድ ፋንታ እኛ ራሳችን እንቆጣጠረው፡፡” —Randy C. Alcorn, Money, Possessions and Eternity (Carol Stream: Illinois, Tyndale House Publishers, 2003), p. 328.

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ምሳ. 13:11፣ ምሳ. 21:5፣ ምሳ. 13:18፡፡ ከገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጋር በተሻለ እንድንሠራ ሊረዱን የሚችሉ ምን ዓይነት ተጨባጭ ቃላቶች ቀርበዋል፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

መጋቢዎች የእግዚአብሔርን ሀብት ሲያስተዳደሩ ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን መጠን ይቆጥባሉ፣ በሰማይም የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ያደርጋሉ፡፡ አንድ ሰው የቱንም ያህል ገቢ ሊኖረው ቢችል፤ ጉዳዩ ያለው የሚያገኘው የገንዘብ መጠን ላይ ሳይሆን--ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የገንዘብ አስተዳደር ዕቅድ እየተገበረ ነው? የሚለው ላይ ነው፡፡ የቤተሰባችንን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችለን ብልህ የቁጠባ ባህል መዘርጋት አለብን፡፡ የቁጠባን ዘዴ ማስፋት በዕጦት ሊገጥም ከሚችል አደጋ ለመጠበቅ ወይም መጠኑን ለመቀነስ ይረዳል (መክ. 11፡1-2)፡፡ በዚህ መልኩ ቅድሚያ ለሚሻው ቅድሚያ እየሰጡ አላስፈላጊ ወጪን መቀነስና (ምሳ. 24፡27) ከሌሎች ባለሙያዊ ምክር መፈለግ (ምሳ. 15፡22) በዚህ ሞዴል--እነዚህ ሁለቱ አርአያነት ያላቸው ውጤታማ ዘዴዎች ናቸው፡፡ የምንፈልጋቸው ነገሮች እየተሟሉ ሲመጡና ሀብት እያፈራን ስንሄድ “እንድታፈራ ችሎታ የሰጠህ እርሱ ስለሆነ አምላክህን እግዚአብሔርን አስበው” (ዘዳ. 8፡18) የሚለውን አምላካዊ ቃል ጠብቀን መራመድ ይኖርብናል፡፡

“ ‘መንግሥተ ሰማይ’ ” (ማቴ. 13፡44) የእግዚአብሔር መጋቢዎች መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱበት ደኅንነቱ የተጠበቀ አስተማማኝ ስፍራ ምሳሌ ነው፡፡ የኤኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ሥጋት ወይም ሌባ በዚያ የለም፡፡ እንደውም ፈጽሞ እንደማያረጅ የገንዘብ ቦርሳ ነው (ሉቃ. 12፡33)፡፡ አንድ ሰው ክርስቶስን የግል አዳኙ አድርጎ ሲቀበል ይህን ሒሳብ ይከፍታል፡፡ አሥራትና ስጦታው የሒሳቡ ተቀማጮች ናቸው፡፡ ለፍጆታ የምንከፍላቸውን ወጪዎችና የመሳሰሉትን አስፈላጊ ምድራዊና ዓለማዊ ነገሮች በጥንቃቄ መያዝ ቢኖርብንም ነገር ግን ትኩረታችን ሁሌም በዘላለማዊ እውነቶች ላይ ሊሆን ይገባል፡፡

ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ 2ቆሮ. 4፡18፡፡ ኃላፊነት እንደሚሰማቸው መጋቢዎች እየኖርን ይህን እውነት ሁል ጊዜ ከፊታችን ጠብቀን መጓዝ የሚኖርብን እንዴት ነው?

ጥር 7
March 16
 

ተጨማሪ ሀሳብ፡-

  

እያንዳንዱ በተፈጥሮ የሚገኝ ችሎታ፣ ስጦታ ወይም መክሊት አብሮን ሊወለድ ቢችል፣ ከትምህርት ወይም ከአካባቢያችን ወስደን ብናበለጽገው--ምንጩ ያው እግዚአብሔር ነው፡፡ የጉዳዩ አስፈላጊ ክፍል በችሎታዎቻችንና ክህሎቶቻችን ምን ልናደርግ ይገባል የሚል ነው፡፡ መጋቢዎች በትምህርትና በልምድ የችሎታዎቻቸውና የመክሊቶቻቸው ጌቶች እንዲሆኑ እግዚአብሔር ይጠብቃል (መክ. 10፡10)፡፡

ባስልኤል “በጥበብ፣ በችሎታና በዕውቀት፣ በማናቸውም ዐይነት ሙያ የእግዚአብሔር መንፈስ ሞልቶበታል” (ዘፀ. 25፡31)፡፡ እርሱና ኤልያብ (ዘፀ. 35፡34) የእነርሱን ጥበብ ለሌሎች የማስተማር ችሎታ ነበራቸው፡፡

በዚህ ቁሳዊ ዓለም ስንኖር በተለይ ዕዳን ከእኛ አርቀን መልካም መጋቢዎች ለመሆን የሚያስችለንን ትምህርት መማር እንችላለን፡፡ ሁሌም ቢሆን በንባብ፣ በዐውደ ጥናቶች፣ በመደበኛ ትምህርትና በመጨረሻም በልምድ ችሎታን ማጎልበት ከእኛ ይጠበቃል፡፡ መክሊቶቻችንን ማጎልበታችን ምርጥ የሆነውን ለእግዚአብሔር እንድናበረክትና መልካም መጋቢዎች እንድንሆን ያስችለናል፡፡

የመክሊቱ ምሳሌ እያንዳንዱ አገልጋይ “ ‘እንደ ችሎታው’ ” ተሰጥኦ መቀበሉን ያሳየናል (ማቴ. 25፡15)፡፡ ሁለቱ አገልጋዮች ተቀብለውት የነበረውን መክሊት በእጥፍ ሲያሳድጉ ሦስተኛው ግን መሬት ቆፍሮ ቀበረው፡፡ ሁሌም ቢሆን እጃችን ላይ ያለውን ነገር ለማጎልበትና ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ሌት ተቀን ልንተጋ ይገባል፡፡ በተረፈ መሬት ውስጥ ቀብሮ ማኖር የአንድን ግለሰብ ችሎታ ወይም ብቃት በምንም መልኩ አይገልጽም፡፡ ገንዘብን መቆጣጠርና ማስተዳደር፣ ከዕዳ መውጣት፣ በሥነ ስርዓት መኮትኮትና መዳበር፣ ብቃትን የሚያጎለብት ተግባራዊ ተሞክሮ ማድረግ--እነዚህ በእግዚአብሔር የተባረኩ አካሄዶች ናቸው፡፡ በሆነ ነገር ስኬታማና የተሻለ ለመሆን፤ ያንን ነገር ደግመን ደጋግመን ማድረግ ከእኛ ይጠበቃል፡፡

“የየቀኑ ህይወታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሲታነጽና ሲገነባ፤ አምላካዊው ቃል በጸባያችን ላይ ጥልቅና ዘላቂ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ ጢሞቴዎስ እነዚህን ትምህርቶች ተምሮአል፤ በተግባር ላይም አውሏል፡፡ እርሱ ልዩ ተሰጥኦ ባይኖረውም፤ በእግዚአብሔር የተሰጠውን ችሎታ ለጌታ አገልግሎት በማዋሉ ምክንያት ሥራው የከበረ መሆን ችሎአል፡፡” —Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 205.

የመወያያ ጥያቄዎች:-፡

 

  1. ራስን መቆጣጠር ምንጊዜም ለክርስቲያኖች አስፈላጊ ቢሆንም ነገር ግን ለገንዘብ ቀውስ ብሎም ውድመት ሊዳርግ ከሚችል አካሄድ ራስን መቆጣጠር በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ ሊገኙ የሚችሉ ሰዎችን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?

  2. ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ሮሜ 13፡7-8፡፡ እነዚህን ቃላት በዕለት ተዕለት ሕይወታችንና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን?

  3. አንዳንዶች የሱስ በቅርቡ ስለሚገለጥ ዕዳ ውስጥ መግባታችን እምብዛም ሊያስጨንቀን አይገባም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ እርስዎ ለዚህ አባባል መልስዎ ምንድን ነው?