የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የትንቢት ስጦታ



4ኛ ሩብ ዓመት 2026


ታኅሣሥ 10 - 16

13ኛ ትምህርት

Dec 19 - 25




ከትንቢታዊ ቃል የሚገኙ በረከቶች



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ። 1ኛ ቆሮ 2፡2፤ ዮሐ 1፡1-5፤ 2ኛ ጢሞ 3፡117፤ 2ኛ ጢሞ 4፡ 1-5፤ ኢሳ 40፡1-5፤ ዮሐ 17፡20-23፤ 1ኛ ቆሮ 1፡10-13።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡”ማልደውም ተነሡ፥ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና፦ ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሰላላችኋል አለ” (2ኛ ዜና 20፡20)።

እግዚአብሔር ዝም ብለን በጭፍን እንድናምን አይጠይቀንም። በተቃራኒው ስለ እርሱ መኖር ኃይለኛ መረጃ አለ። ከስድስት ሺህ የኃጢአት ዘመናት በኋላ አንኳን ተፈጥሮ ብቻዋን የእግዚአብሔርን የሚያስገርም የፈጣሪነት ኃይል ብቻ ሳይሆን የፍቅር አምላክ መሆኑንም ጭምር ትመሰክራለች።

ይህ ብቻ አይደለም። ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፦”እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን። ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፥ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ” (2ኛ ጴጥ 1፡18ና 19)። እንደ ጴጥሮስ የእግዚአብሔርን ድምጽ ላንሰማ እንችላለን። ነገር ግን እኛም “የትንቢቱ እርግጠኛ ቃል” አለን።

እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ቃላቸው በተዘገበ እና ባልተዘገበ ነቢያት አማካኝነት ተናግሮናል። የተሰጠን መረጃ ከበቂ በላይ ነው። ጥያቄው እኛ ለመቀበል ዝግጁ ነን ወይ? የሚለው ነው።

ቅዱስ ታሪክ የሚያሳየው ብዙዎች ለመቀበል እንዳልተዘጋጁ ነው። የእነርሱን ስህተት ከመድገም የእግዚአብሔር ጸጋ ይጠብቀን። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለታኅሳስ 17 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

ታህሣሥ 11
Dec 20

ትንቢት ክርስቶስን ከፍ ከፍ ያደርጋል


ትንቢት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የሚነጋገርበት እና ከእርሱ ጋር የሚያቆራኝ መሣሪያ ነው። ታዲያ ሰይጣን (ዘንዶው) በሴቲቱ (ቤተ ክርስቲያን) ላይ ቢቆጠና በዘርዋ ላይ ጦርነት ቢያውጅ አያስገረምም (ራዕይ 12፡17ን ይመልከቱ)።

የዚህች ሴት ቅሬታ ዘሮች ዋና የመለያ ምልክቶቻቸው ምንድን ናቸው? ትእዛዙን ይጠብቃሉ፣ የክርስቶስ ምስክርነትም አላቸው። ራዕይ 19፡10 እንደሚነግረን ምስክሩ “የትንቢት መንፈስ” ነው። 1ኛ ቆሮ 2፡2 እና ገላ 6፡14ን ያንብቡ። ጳውሎስ የአገልግሎቱንና የመኖሩን ዓላማ--የኖረለትን ትልቁን ማነሳሻ-- እንዴት ይመለከተዋል?



ሐዋርያቱ ከራሳቸው የኑሮ ልምምድ ተጨማሪ በብዙ ምዕተ አመታት የተዘረጉትን የቅዱሳን ነቢያትን ቃላት መሠረት በማድረግ ኢየሱስን መቀበል ቻሉ። የክርስትናው ዓለም ብሉይ ኪዳንን እና አዲስ ኪዳንን የሚያካተት የመረጃ ሰንሰለት ቀርቦለታል። ብሉይ ኪዳን የኢየሱስን መምጣት ሲተነቢይ አዲስ ኪዳን ደግሞ ስለ አዳኙ የተነገሩ ሁኔታዎች በኢየሱስ መፈጸማቸውን አሳይቷል። ይህ ሁሉ ለማመን ለሚፈልጉ ሁሉ በቂ መረጃ ነው። “የእግዚአብሔር ዕቅድ ለሰው ዘር በእግዚአብሔር አብና በእግዚአብሔር ወልድ ኃይል ለማመንና የመንፈስ ቅዱስን ስራ ለመቀበል በቂ መረጃ መስጠት ነው።” (The spirit of prophecy vol 3, page 182)

በብዙ መንገዶች የሚያድን እምነት ጉዳይ የእውቀት ጉዳይ ሳይሆን የሞራል ጉዳይ ነው። የጭንቅላት ሳይሆን የልብ ጉዳይ ነው። የሚያሳዝነው ነገር ሰዎች ልባቸውን ሲዘጉ ጭንቅላታቸውም ይዘጋል። ዮሐ 1፡1-5ን ያንብቡ። እነዚህ ቁጥሮች ስለ ኢየሱስ ማንነት ምን ይነግሩናል?



እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል የሆነውና ቀድሞ የነበረው ኢየሱስ ስጋ ለብሶ በመካክላችን ካደረ፣ እግዚአብሔር ለነቢያቱ በሰጣቸው ቃላት ወይም መልዕክቶች ተባባሪ ነበር ማለት ነው። ክርስቶስን በስም ያልጠቀሱ ነቢያትም ሳይቀሩ በመንፈስ ቅዱስ ተነስተዋል። የአለማችንን ስፋት ይገመቱና ይህን የፈጠራው ኢየሱስ፣ የሞተልንም እርሱ መሆኑን ያስቡ። ይህን ማወቅዎ ምን ያህል ታላቅ ተስፋ ይሰጥዎታል?

ታህሣሥ 12
Dec 21

ትንቢት መጽሐፍ ቅዱስን ያረጋግጣል


መጽሐፍ ቅዱስ በትንቢት ስጦታ የተሰጠ የመንፈስ ቅዱስ ውጤት ነው። እግዚአብሔር የተጠቀመበትን ሂደት 2ኛ ጴጥሮስ 1፡21 እንዲህ ሲል ይገልጠዋል፦”ትንቢት ከቶ ከሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።” 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16ና 17ን ያንብቡ። ይህ ምንባብ በመጽሐፍ ቅዱስ (በቃሉ) ስልጣንና በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ስለመጻፉ አጽንዖት የሚሰጠው እንዴት ነው?



መጽሐፍ ቅዱስ ባይኖር የሰው ዘር የዚህን በኃጢአት የተሞላ ዓለም መሰናክሎች ሁሉ ማለፍ አይችሉም። እንዲያ ቢሆን ኖሮ የከባድ ጥፋት ምንጭ ይሆን ነበር። በአሁኑ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ በሁሉም ቦታና በተለያዩ ሁኔታዎች ይገኛል፣ ነገር ግን ድሮ እንደሱ አልነበረም። ለምሳሌ ኢየሱስ በዚህ ምድር በነበረበት ጊዜ ብሉይ ኪዳን በብራና መልክ ብቻ ይገኝ ነበር። የሚያነቡትም መምህራንና ካህናት ብቻ ነበሩ። ተራው ህዝብ መጽሐፍ ቅዱስ አልነበረውም። በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ውድ ነበር። ሉቃ 24፡27ን ያንብቡ። ከትንሳኤው በኋላ ሁለት ያዘኑ ደቀመዝሙርት የእርሱን የተለየ ዓላማ እንዲረዱ ለመርዳት ኢየሱስ ምንን ተጠቀመ?



ኢየሱስ፣ እርሱ ብቻ ቃል የሆነውና ከነቢያት ሁሉ የላቀው ነቢይ፣ ቃሉን/መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ ከፍ አደረገ (ዮሐ 1፡1-3, ዮሐ 7፡38)። ከትንቢት መንፈስ ውድ በረከቶቹ መካከል አንዱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጽናት (ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ) ነው።

“መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ድምጽ መሆኑን የሚያምኑና ትምህርቶቹን መከተል የሚፈልጉ ሁሉ ለእውነተኛ አማኝ በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የተሰጠውን ቃሉን በየቀኑ ማጥናትና በየቀኑ መንፈሳዊ ግለትና ሀይል መቀበል አለባቸው” (ኤለን ጂ ዋይት signs of the time, march 8,1910)። ሀቀኛው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሁልጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ ከፍ ያደርጋል። የእግዚአብሔር ቃል የእምነትና የተግባር መሪ መሆኑን ሁልጊዜ ለሰዎች ያመለክታል። ኢየሱስ በኢማሁስ መንገድ ላይ ለሁለቱ ደቀ መዛሙርት ራሱን ከመግለጡ በፊት ወደ ቃሉ ያመለከታቸው ለምንድን ነው? ቃሉ ለእኛ መሰረታዊ መሆን እንዳለበት ይህ እንዴት ያሳየናል?

ታህሣሥ 13
Dec 22

ትንቢት የእግዚአብሔርን እውነት ይመረምራል


ትንቢት የእግዚአብሔርን እውነት ይመረምራል/ለይቶ ያሳያል ለይቶ ያሳያል

አንዳንድ ምሁራን በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ አርባ አምስት ሺህ የክርስቲያን ድርጅቶች ይገኛሉ ብለው ይገምታሉ። በክርስቶስ የተጀመረ አንድ እምነት እንዴት እንደ እንጉዳይ ሊራባ ቻለ? መልሱ በዘመናት ሁሉ በተደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ አተረጓጎሞች ይሆናል። ሁሉም ትክክል አለመሆናቸው ግልጽ ነው። ምክንያቱም አንዱ ድርጅት የሚያስተምረውን ሌላው ያፈርሰዋል (ይቃወመዋል)።

ሲጀመር ጀምሮ (ዘፍ 2፡16፣17ን ና ዘፍ 3፡1-5ን ይመልከቱ)፣ ሰውን ከእግዚአብሔር እውነት ለማራቅ የሰይጣን ዋና መሳሪያው ማደናገር ነው። በአዳምና ሄዋን ላይ እንዳደረገው ከውሸት ጋር ትንሽ እውነት ያቀላቅላል። ይህን የሚያደርገው ሰውን ከቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ነው። ሰይጣን በዘመናት ሁሉ የእግዚአብሔርን ህዝብ ሲያሳስት ኖሯል (2ኛ ዜና 36፡14-16)። ኢየሱስን ሳይቀር ሊያሳስት ሞክሯል (ማቴ 4፡ 1-11)። ኢየሱስ ግን በማያጠራጥር “ተጽፏል” በሚል መልስ ተቋቋመው (ማቴ 4፡4)። 2ኛ ጢሞ 4፡1-5ን ያንብቡ። የእግዚአብሔርን ቃል በተመለከተ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ምን አይነት ወሳኝ ምክር ሰጠው? ለሚያጋጥሙ ነገሮች ሁሉ መንፈሳዊ ዝግጅት እንዲያደርግ አጥብቆ የመከረው ለምንድን ነው?



ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል የሚጥሉበትና የማይታዘዙት ቀን እንደሚመጣ ጳውሎስ በትንቢታዊ ዓይኑ አስቀድሞ ታየው። በዚያ ፋንታ በተንኮል የተሞሉ ተረታ- ተረቶችን እየነገሩ ደስ የሚያሰኙአቸውን መንፈሳዊ አስተማሪዎች ይፈልጋሉ። እንደ እነዚህ ላሉት የፈለጉትን ውሸት እንዲያምኑ ጠንካራ የሆነ ማታለያ ይልክባቸዋል። “ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል” (2ኛ ተሰሎንቄ 2፡11-12)።

ፈቃደኛ ለሆኑ ግን ኢየሱስ “እውነትን ታውቃላችሁ” በማለት ተስፋ ሰጣቸው (ዮሐ 8፡32)። ትንቢታዊ ስጦታ እውነትን ከስህተት፣ ብርሃንን ከጨለማ ለይተን የምናውቅበት መንገድ ነው።

በአንድ በኩል ከእነዚህ የተለያዩ ድርጅቶች መካከል እውነተኛ የሆነው የቱ እንደሆነ በቀላሉ ለይተን ማወቅ እንችላለን። ሰባተኛውን ቀን ሰንበትን ካልከዱ (መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሰረተ) 99.5% ምርጫዎችዎን አስወገዱ ማለት ነው። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ድርጅቶች አራተኛውን ትዕዛዝ አያከብሩም (አይጠብቁም)።

ሙታን ከኢየሱስ ጋር ለመሆን ቀጥታ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ወይም ለዘላለም በገሃነም ይቃጠላሉ ብለው ካላመኑም የቀሩትን 0.5% አጠቃለሉ ማለት ነው። ታዲያ ምን ቀረ? እንዲህ ከሆነ ወደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ከመሄድ በቀር ሌላ የት ይሄዳሉ?

ታህሣሥ 14
Dec 23

ትንቢት የእግዚአብሔርን ህዝብ ያጽናናል


ማቴ 11፡28ና 29ን ያንብቡ። ኢየሱስ ምን እንድናደርግ ይነግረናል? ወደ እርሱ ለሚመጡት ሁሉ ምን አይነት ተስፋ ይሰጣቸዋል?



የሰዎች ደህንነት ምንጊዜም እግዚአብሔርን ያሳስበዋል። አዳምንና ሄዋንን ከመፍጠሩ በፊት የሚያስደስት እና የሚያጓጓ ፍፁም የሆነ መኖርያ ቤት አዘጋጅላቸው (ዘፍ 1)። ለምቾታቸው የሚበጀውን ነገር ሁሉ ሰጣቸው። ቅዱሳኑ ባልና ሚስት ሲወድቁ ሊፈልጋቸው መጣ (ዘፍ 3፡9)። መድህን እንደሚመጣላቸው ተነበየ (ዘፍ 3፡15)። ራቁትነታቸውን ለመሸፈን ልብስ አዘጋጀላቸው (ዘፍ 3፡21)። የፍጡራን ሁሉ ደህንነት እግዚአብሔርን ግድ ይለዋል።

ምናልባት ከትንቢት ስጦታ በረከት ሁሉ፣ ይህ ስጦታ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በዘመናት ሁሉ የመጽናናትና የመታደስ ምንጭ መሆኑን ችላ የማለትን ያህል ችላ የተባለ ሌላ ነገር የለም። ኢሳ 40፡1-5ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ለተጎዱት ህዝቡ እንዲያስተላልፍ ለነብዩ ምን መልዕክት ሰጠው? እኛስ ዛሬ ያንኑ መልዕክት በራሳችን ህይወት እንዴት በስራ ላይ ልናውለው እንችላለን?



እግዚአብሔር ቢቀጣቸውም ፈጽሞ እንደማይተዋቸው ይሁዳ እንዲያውቅ ፈለገ። ለወደቁት ህዝቡ እንዲነግር ለኢሳይያስ የማደፋፈሪያ መልዕክት ብቻ አልሰጠውም። መልዕክቱን እንዴት እንደሚያስተላልፍም በትክክል ነገረው። መልእክቱ በርህራሄ፣ በፍቅርና በጥንቃቄ መቅረብ ነበረበት። ይህ የማጽናኛ መልዕክት የህዝቡን ልብ እንዲነካ እግዚአብሔር አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ አደረገ። እነዚህ የመጽናኛ መልዕክቶች በኢሳይያስ መጽሐፍ በሙሉ ተደጋግመው ተነግረዋል (ኢሳ 12፡1፣ ኢሳ 49፡13፣ ኢሳ 51፡3,... ወዘተ)።

የክርስቶስ ተከታዮች ከባድ መሰደድ እንደሚደርስባቸው ሐዋርያው ጳውሎስ ያስጠነቀቃል (2ኛ ጢሞ 3፡12)። ለወደፊት ለሚጠብቀን አስቸጋሪ ጊዜ የማጽናናትና የተስፋ ቃላት ያስፈልጉናል። በሚመጣው ችግር ህዝቡን ለማጽናናትና ለማበረታታት እግዚአብሔር የሚጠቀመው የትንቢትን ስጦታ ነው። ኢየሱስ ዳግመኛ መጥቶ ወደ ሰማይ ቤታቸው እንደሚወስዳቸው ማወቁ ከተስፋዎች ሁሉ የበለጠ አበራታች ተስፋ ነው። የተስፋና የመጽናናት ቃላትን መስማት የሚያስፈልግዎ ለየትኛው የህይወት (የኑሮ) ክፍል ነው? እግዚአብሔር ካጽናናን በኋላ ምን እንድናደርግ ነው ሃይል የሚሰጠን?

ታህሣሥ 15
Dec 24

ትንቢት የክርስቶስን አካል አንድ ያደርጋል


ዮሐንስ 17፡20-23ንና 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡10-13ን ያንብቡ። እነዚህ ሁለት የቃሉ ምንባቦች ዋና መልዕክታቸው ምንድን ነው?



ኢየሱስ ስቅለቱ ሲቀረብ ልቡ በአንድ ወሳኝ ምኞት ተይዞ ነበር። አብና እርሱ በፍቅርና በስራ አንድ እንደሆኑ ሁሉ፣ ተከታዮቹም አንድ እንዲሆኑ ፈለገ። ኢየሱስ የጸለየበት አንድነት ተራ የሆነ ጭፍን አንድ ወጥነት አልነበረም። ኢየሱስ ከመመለሱ በፊት የሚፈጸምን ሀይለኛ ትንቢታዊ ጸሎት ጸለየ። ጸሎቱ የተለያየ ዳራ፣ ብሔር፣ አስተሳሰብና ዘር ያላቸውን ሰዎች ከእርሱና ከአብ ጋር በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሚያስተባብር ጠንካራ ሃይል ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስን አማኞች አንድ ሀሳብ እንዲኖራቸው፣ አንድ እውነት እንዲናገሩና መከፋፈል እንዳይኖርባቸው የመከራቸው በዚሁ መንፈስ ተነሳስቶ ነበር (1ኛ ቆሮ 1፡10)።

ታዲያ ይህ ትንቢታዊ አንድነት ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጸለየ፦”ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ” (ዮሐንስ 17፡20-21)።

እግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ ይፈልጋል። ነገር ግን ለመዳን ከፈለጉ በኢየሱስ ማመን እና አብ ዓለምን ለማዳን እንደላከው ማመን አለባቸው። የተለያዩ ሰዎች ኢየሱስን የግል ጌታቸው እና ዳኛቸው አድርገው ሲቀበሉ፣ በፍቅር እና ራስን በመካድ አንዱ ሌላውን ሲያገለግል፣ ያን ጊዜ እውነትም ክርስቶስ ስለ ማንነቱ የተናገረው እውነት ነው ብሎ ዓለም ሁሉ ያምናል። ክርስቶስ የጸለየበት አንድነት አላማ ያለውና ኃይለኛ ነበር። የሚያሳዝነው ነገር ገና ከመጀመሪያው ያንን አንድነት ለማፍረስ ብርቱ የሆኑ ኃይላት ተሰልፈው ነበር። ለምሳሌ የሐዋ 6፡1ን ይመልከቱ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ክርስትና በብርቱ ተከፋፍሎ ይኖራል!

ይህ አንድነት መንፈስ ቅዱስ በሚለግሰው ኃይል የተደገፈ አንድነት ነው። ኤፌሶን 4፡1-5 የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አማኞችን ለማበረታታትና የክርስቶስን አካል አንድ ለማድረግ እንደተሰጡ ይነግረናል። “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ” (ኤፌሶን 4፡12-13)። ከመንፈስ ስጦታዎች መካከል ዋነኛ የሆነው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ አማኞችን አንድ ለማድረግ አስፈላጊ ነው። የኢየሱስ ዳግም ምጽዓት ስለተቃረበ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው እንዲድኑ የመንፈስ ቅዱስ መሪነት ያስፈልጋቸዋል። የ7ኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ምናልባት ከሁሉም የፕሮቴስታንት ተቋማት ሁሉ የተለያዩ ህዝብ ጥርቅም በሆነበት በዚህ ጊዜ ሰዎች በኢየሱስ እንዲያምኑ ሊረዳ የሚችል አንድነት ልናሳይ የምንችለው በምን መንገድ ነው? ይህ አይነት አንድነት እንዳይኖር የሚያስፈራሩ ኃይላት ምንድን ናቸው?

ታህሣሥ 16
Dec 25

እንደገና ይሞክሩ


እንደገና ይሞክሩ (ሞክሩ ሞክሩ)

ከጥቂት አመታት በፊት ለቁርስ የሚሆኑ አዝርእቶችን በማስተዋወቅ የድሮ ደንበኞችን ለመመለስ በመጣር የኬሎግ ድርጅት “ለመጀመሪያ ጊዜ እንደገና ቅመሱት (ሞክሩት)” የሚል ማስታወቂያ መፈክር አውጥቶ ነበር። ምናልባት ይህ አባባል ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ ኤለን ጂ ዋይት ጽሑፎች ለመማር ብዙ ጊዜ ስላባከኑና ጽሑፎቿን “ለመቅመስ” አነስተኛ ጊዜ ለሰጡት የ7ኛ ቀን አድቬንቲስቶች ይሰራ ይሆን? ስለ ኤለን ጂ ዋይት መማርና ማንበብ ስለ አገልግሎቷና ስለ ህይወቷ ዕውቀት ሊያስገኝልዎ ይችላል። ነገር ግን ራስዎ “የመቅመስን” ያህል አይጠቅምዎትም። የመንፈሳዊ ጥቅሙን በትክክል ሊረዱት አይችሉም። በአውድ በተመሠረተ ጥናት ጽሑፎቿን የሚያነቡ ብቻ መንፈሳዊ በረከት ሊያገኙባቸውና እግዚአብሔር የሰጠንን ነገር በሙላት ሊያደንቁ ይችላሉ።

በዚህ ሩብ ዓመት ውስጥ ደጋግመን እንደተመለከትነው ኤለን ጂ ዋይት በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ እንድንመሠረትና ከእግዚአብሔር ጋር እንድንገናኝ ታደርገናለች። ትንቢታዊ መልዕክቶቿን በማንበብ የሚገኙ ብዙ በረከቶች አሉ።

ሮጀር ደድሊ እና ዴስ ከሚንግስ በተባሉ ሰዎች የተካሄደ አንድ ምርምር አንዳንድ አስገራሚ እውነታዎችን አሳይቷል። የኤለን ጂ ዋይትን መጻሕፍት የሚያነቡ ሰዎች ከማያነቡት ይልቅ ከኢየሱስ ጋር በበለጠ የጠለቀና የቀረበ ግንኙነት እንዳላቸው ያሳያል። ስለ መዳናቸው ጠንካራ ማረጋገጫ፣ የበለጠ መደበኛ የሆነ የቤተሰብ አምልኮ እና ለሌሎች የመመስከር ፍላጎት አላቸው። ሁለቱ መርማሪዎች እንዲህ ይላሉ፦”ምርምር የዚህ ዓይነት ግልጽ ውጤት ሲያሳይ ማየት የተለመደ አይደለም። የቤተ ክርስቲያን እድገትንና የግል አስተያየትን እድገት በተመለከተ፣ የኤለን ጂ ዋይትን ጽሑፎች አዘውትሮ የሚያነብ አባል አልፎ አልፎ ከሚያነበው ወይም ጨርሶ ከማያነበው አባል ይልቅ ግልጽ የሆነ ብልጫ ያሳያል።” (Dudly and commings, “who reads Ellen white” in ministry october 1982, page 12)

በዚህ ሩብ ዓመት እግዚአብሔር በነቢያቶቹ አማካኝነት እንደሚናገር ተምረናል። መልዕክቶቻቸው እኛን ከእግዚአብሔር ጋር በማገናኘት በሰብአዊ ሕይወት ሁሉም ገጽታዎች፣ በተላይም “እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱ፣ እዩም” (መዝ 34፡8) ከሚለው በኢየሱስ ካለው የድነት ተስፋ ጋር በተገናኘ፣ ቅዱስና የሚቀድስ ተጽእኖ ያመጡልናል።። ወደ ቅዱስ ተግባር፣ ወደ ህይወት መለወጥ፣ ወደ የግል ወንጌል ስራና ሌሎችን ወደ ማገልገል ሕይወት ይጠሩናል። የኢየሱስን ዳግም ምጽአት ስንጠባበቅ ሳለ የመጨረሻውን አዋጅ በማወጅ የበኩላችንን እንድንወጣ ይህ አስፈላጊ ዝግጅት ነው።



የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ለሚፈልጉ የተደራጁ ቤተከርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎትድርጅቶች የተሠጠ

ማሳሰቢያ


የትንቢት መንፈስ(Spirit of Prophecy - SOP)መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡

እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ የተደራጀ ቤተከርስቲያንም ሆነ በዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ ያለው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን በበላይነት በሚያስተዳድራቸው ሰበካዎችና ኮንፍራንስ የጽሁፍ ከፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ አንዲያስተረጉም ፈቃድ ይሰጠዋል ትርጉሙም ሲጠናቀቅ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጽ በታተመ ወረቀትና ሙሉውን መጽሐፍ በሲዲ ካስረከበ በኋላ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ ሥራውን መፈፀም ይቻላል።

በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገለግሎት ድርጅቶች በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡

ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ ከርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ ማስራጨት፤ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡

ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕከት መልዕከት ለማዳረስ እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡

ድርጅቱ




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL