የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

1ኛ እና 2ኛ ቆሮንቶስ - የክርስቲያን ሕይወት እና ምስክርነት ባሕርይ



3ኛ ሩብ ዓመት 2026


ነሐሴ 16 - 22

9ኛ ትምህርት

Aug 22 - 28




በፍቅር የሚመራ አገልግሎት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት እነዚህን ክፍሎች አንብቡ፦ 2ኛ ቆሮ. 1፡3–14፤ 2ኛ ቆሮ. 2፡17፤ 2ኛ ቆሮ. 4፡2፤ 1ኛ ቆሮ. 16፡5–7፤ 2ኛ ቆሮ. 7፡5–13፤ 2ኛ ቆሮ. 2፡5–17።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ «በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበርና፤ ይህም እኔ ለእናንተ ያለኝ የፍቅሬ ብዛት እንዲታወቅላችሁ እንጂ እንድታዝኑ አልነበረም» (2ኛ ቆሮንቶስ 2፡4)።

ሐዋርያው ጳውሎስ ነገሮች ሁልጊዜ አልቀኑለትም ነበር። ከእስራትና ለሕይወቱ አስጊ ከሆኑ ሁኔታዎች በተጨማሪ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። ሶስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ። የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።” (2ኛ ቆሮ. 11፡24–28)።

ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፋቸው ደብዳቤዎች ውስጥ የምናየው፣ ለዚች ቤተ ክርስቲያን የነበረውን “ከባድ አሳብ” የተወሰነ ክፍል ነው። ሆኖም፣ በዚህ ሁሉ መካከል፣ ልክ የክርስቶስ ፍቅር ለእኛ እንደማይጠፋ ሁሉ ለእነርሱ የነበረው ፍቅር ፈጽሞ አልቀነሰም። እንዲያውም ጳውሎስ አብያተ ክርስቲያናትን የየሱስን ፍቅር በሚያንጸባርቅ መልኩ መውደድን የተማረው ከራሱ ከየሱስ ነበር (2ኛ ቆሮ. 5፡14፤ 1ኛ ቆሮ. 11፡1ን ይመልከቱ)።

*ለነሐሴ 23 (August 29) ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።

ነሐሴ 17
Aug 23

ምስጋና


2ኛ ቆሮንቶስ 1፡3–7ን አንብቡ። እዚህ ጋ ጳውሎስ የምስጋና መንፈስ እንዲኖረው ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው?



የጳውሎስ ምስጋና የሚያተኩረው እግዚአብሔር መከራ ለሚቀበሉ ሰዎች በሚሰጠው መጽናኛ ላይ ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ “ማጽናናት” (parakaleō) የሚለው ግስ እና “መጽናናት” (paraklēsis) የሚለው ስም በአንድ ላይ አሥር ጊዜ ተጥቅሰዋል። ይህም በ2ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ እነዚህ ቃላት ከሚገኙባቸው አጠቃላይ ቦታዎች (29 ጊዜ) ሲነጻጸር ሲሶውን (አንድ ሦስተኛውን) ይይዛል። እግዚአብሔር “የምሕረት አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ... በመከራችን ሁሉ የሚያጽናናን” ተደርጎ ተስሏል (2ኛ ቆሮ. 1፡3፣ 4)።

አንድ ሰው ከእግዚአብሔር የሚቀበለው መጽናኛ ለራሱ ብቻ እንዲያስቀረው የታሰበ አይደለም (2ኛ ቆሮ. 1፡4፣ 5)። የመከራ ልብ ሆኖ የእግዚአብሔርን መጽናኛ የተቀበለ ብቻ ነው በመከራ ውስጥ ላሉት ሌሎችም መጽናኛን ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊያካፍል የሚችለው።

ጳውሎስ ሌሎችን ሊያጽናና የቻለው፣ እርሱ ራሱ በመከራው ወቅት ከእግዚአብሔር መጽናኛን ስለ ተቀበለ ነው። “መከራም ብንቀበል፣ ስለ እናንተ መጽናናትና ደኅንነት ነው፤ ... ብንጽናናም፣ ስለ እናንተ መጽናናትና ደኅንነት ነው” (2ኛ ቆሮ. 1፡6፤ አጽንኦት የተጨመረበት)። ፍቅር ማለት ይህ ነው! በ2ኛ ቆሮንቶስ 1፡8–11 ላይ ጳውሎስ ምስጋናውን የሚገልጸው ስለ ምን ጉዳይ ነው?



ጳውሎስ እርሱና አብረውት የሚሠሩት መጨረሻቸው እንደመጣ እንዲሰማቸው ስላደረጋቸው “ከአቅም በላይ የሆነና ጽኑ” መከራ ይናገራል (2ኛ ቆሮ. 1፡8)። ለጥቂት ጊዜ ብቸኛ ተስፋቸው ትንሣኤ ብቻ እንደሆነ አስበው ነበር። ሆኖም እግዚአብሔር አዳናቸው፤ ሁኔታውም ተለወጠ (2ኛ ቆሮ. 1፡10)። ከሞት ፍርሃት (2ኛ ቆሮ. 1፡8) ተነሥተው እግዚአብሔር ደግመኛ እንደሚያድናቸው ወደሚገልጽ ጥልቅ ተስፋ ደረሱ (2ኛ ቆሮ. 1፡10)። እግዚአብሔር ባለፈው ጊዜ የተቀዳጃቸው ድሎች፣ ወደፊትም እንዲሁ እንደሚያደርግ እምነት ይሰጡናል። እግዚአብሔር በእርሱ መታመንን እንዲያስተምረን መከራዎችን ይጠቀማል። መከራዎች ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርቡን እስከፈቀድንላቸው ድረስ፣ ወደ መንፈሳዊ ብስለት ሊመሩን ይችላሉ። የጳውሎስ ምስጋና የሌሎችን የሽምግልና ጸሎት ኃይል እና በእግዚአብሔር ማዳን ምክንያት የምንለማመደውን ምስጋናም ያሳያል (2ኛ ቆሮ. 1፡11)። ሁላችንም በተለያዩ መንገዶች ለሚገጥሙን መከራዎች ምላሽ ስንሰጥ ጠቃሚ ሆኖ ያገኛችሁት ነገር ምንድን ነው?

ነሐሴ 18
Aug 24

ቅንነትና እውነተኛነት


ትላንት ጳውሎስ ከእግዚአብሔር መጽናኛን እንዳገኘ ሁሉ፣ የቆሮንቶስ ሰዎችን በመከራቸው በማጽናናት ለእነርሱ ያለውን ፍቅር እንደገለጸ ተምረናል (2ኛ ቆሮ. 1፡1–11)። ዛሬ ደግሞ ለእነርሱ ያለው ፍቅር፣ እርሱና የሥራ ባልደረቦቹ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ባሳዩት ታማኝነት (integrity) እንዴት እንደተገለጠ እናያለን። 2ኛ ቆሮንቶስ 1፡12–14ን ከ2ኛ ቆሮንቶስ 2፡17 እና 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡2 አንጻር አንብቡ። የጳውሎስ ቅንነት ለእነርሱ ያለውን ፍቅር የሚገልጸው እንዴት ነው?



2ኛ ቆሮንቶስ 1፡12–14 ጳውሎስ በደብዳቤው ቀሪ ክፍል ውስጥ የሚያብራራውን ዋና ሐሳብ ያስተዋውቃል። በቆሮንቶስ ያሉ አንዳንዶች የእርሱን ታማኝነትና ሐዋርያነት ተጠራጥረው ነበር። ጳውሎስ ለሐዋርያዊ አገልግሎት የማይመጥን፣ የሚወላውልና በውሳኔ የማይጸና ባሕርይ እንዳለው አድርገው ያስቡ ነበር። ለዚህም ምላሽ ሲሰጥ፣ እርሱና የሥራ ባልደረቦቹ ለእነርሱ ያላቸውን ከፍተኛ ታማኝነት አጥብቆ ይገልጻል።

ሁለት ቃላት የጳውሎስንና የአጋሮቹን ባሕርይ ይገልጻሉ፦ ቅንነትና እውነተኛነት (2ኛ ቆሮ. 1፡12)። “ቅንነት” የሚለው ቃል የመጣው “ሃፕሎቴስ” (haplotēs) ከሚለው የግሪክ ቃል ነው። እዚህ ጋ የተጠቀሰው በንግግርም ሆነ በባሕርይ ያለንን ግላዊ ታማኝነት ለመግለጽ ሲሆን፤ በአጭር አነጋገር የሐሳብን ንጽሕና ያሳያል (ኤፌ. 6፡5፤ ቆላ. 3፡22)። በተመሳሳይ መልኩ “እውነተኛነት” የሚለው ቃል (“ኤሊክሪኒያ” - eilikrineia ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ) ለታማኝነትና ለሐሳብ ንጽሕና ትኩረት ይሰጣል።

የቆሮንቶስ ሰዎች በጳውሎስ ዓላማ ግልጽነት ላይ ሊጠራጠሩ አይገባም ነበር። የእርሱ ቅንነትና እውነተኛነት ምንጫቸው እግዚአብሔር መሆኑን ግልጽ ያደርጋል። ይህ ሐሳብ በአዲሱ የእንግሊዝኛ ትርጉም (NET) መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ከእግዚአብሔር የሆኑ ንጹሕ ዓላማዎችና ቅንነት” ተብሎ በጥሩ ሁኔታ ተገልጿል (2ኛ ቆሮ. 1፡12፤ አጽንኦት የተጨመረበት)። በዚሁ ጥቅስ ላይ ጳውሎስ እነዚህ የአገልግሎት ባሕርያት “በእግዚአብሔር ጸጋ” የተሰጡን መሆናቸውን በድጋሚ ያረጋግጣል።

የጳውሎስ ተቃዋሚዎች ቀደም ሲል በነበሩ የጽሑፍ ግንኙነቶች ላይ የእርሱን ቃላት የተሳሳተ ትርጉም የሰጡት ይመስላል (2ኛ ቆሮ. 1፡13፣ 14)። ጳውሎስ ዓላማዎቹ ግልጽና ሊረዱ የሚችሉ መሆናቸውን ያረጋግጣል። የቃላቱ፣ የሐሳቡና የተግባሩ ቅንነት “በጌታ በየሱስ ቀን” ግልጽ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበር (2ኛ ቆሮ. 1፡14)። ምንም እንኳ ዓላማችሁ ወይም ሐሳባችሁ ለበጎና በቅንነት ቢሆንም፣ በሌሎች ዘንድ ጥርጣሬ ሲፈጠርባችሁ ወይም ተቃውሞ ሲገጥማችሁ ያላችሁ ተሞክሮ ምንድን ነው? ይህስ የሌሎችን ሰዎች ዓላማ በምትጠራጠሩበት ጊዜ ምን ያህል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባችሁ ምን ያስተምራችኋል?

ነሐሴ 19
Aug 25

በፍቅር ምክንያት የተለወጡ ዕቅዶች


በቆሮንቶስ ያሉ አንዳንዶች በጳውሎስ ዓላማና ፍቅር ላይ ጥርጣሬ አድሮባቸው እንደነበር አይተናል። ዛሬ ደግሞ ለዚህ ጥርጣሬ አንዱን የተለየ ምክንያት እንመለከታለን፤ ይኸውም የጉዞ ዕቅዱን መለወጡ ነው (2ኛ ቆሮ. 1፡15–2፡4)። 1ኛ ቆሮንቶስ 16፡5–7ን አንብቡ። የጳውሎስ የመጀመሪያ የጉዞ ዕቅድ ምን ነበር?



ጳውሎስ ቀደም ሲል ቆሮንቶስ ሄዶ ነበር። በ1ኛ ቆሮንቶስ 16፡5፣ 6 መሠረት፣ ወደ ቆሮንቶስ በሚመለስበት መንገድ በመቄዶንያ በኩል ለማለፍና ምናልባትም የክረምቱን ወራት በቆሮንቶስ ለማሳለፍ አቅዶ ነበር። ከቆሮንቶስም በመቄዶንያ ለኢየሩሳሌም ድሆች የተሰበሰበውን መባ ይዞ ወደ ይሁዳ ይሄዳል። ሆኖም ጢሞቴዎስ ከቆሮንቶስ ይዞት በመጣው መጥፎ ሪፖርት ምክንያት ዕቅዱን ለወጠ (1ኛ ቆሮ. 4፡17፤ 1ኛ ቆሮ. 16፡10፤ 2ኛ ቆሮ. 1፡1)።

ጳውሎስ ከኤፌሶን በቀጥታ ወደ ቆሮንቶስ በመሄድ ጢሞቴዎስ ያሳወቀውን ችግር ለመፍታት አስቦ ነበር። አዲሱ የጉዞ መስመር ኤፌሶን—ቆሮንቶስ—መቄዶንያ— ቆሮንቶስ—ይሁዳ የሚል ነበር (2ኛ ቆሮ. 1፡15፣ 16)። ከኤፌሶን ወደ ቆሮንቶስ ሄደ፣ ነገር ግን እንደገና ወደ ኤፌሶን ተመለሰ። ዕቅዱ ተለወጠ። የመጨረሻው ጉብኝቱ መልካም ስላልነበረ፣ ቢያንስ ወዲያውኑ ወደ ቆሮንቶስ አልተመለሰም። ስለዚህ ወደ ኤፌሶን ተመልሶ በምትኩ ደብዳቤ ጻፈላቸው። ሌላ ጉብኝት በማድረግ ነገሮችን ከማባባስ ይልቅ ደብዳቤ መላክን መረጠ (2ኛ ቆሮ. 2፡1፣ 3)።

በመጨረሻው ጉብኝቱ ላይ የነበረውን የጳውሎስን ዓላማ በተሳሳተ መንገድ ተረድተውት ነበር። በቆሮንቶስ ያሉ አንዳንዶች እርሱ የማይታመን እንደሆነና በቂ ፍቅር እንደሌለው ተናገሩ (2ኛ ቆሮ. 1፡17)። ለቀረበበት ክስ ምላሽ ሲሰጥ፣ የቆሮንቶስ ሰዎችን እይታ ወደ ክርስቶስ ወንጌል መለሰው። እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል የገባውን የተስፋ ቃል በመፈጸም የታመነ እንደሆነ ሁሉ፣ እርሱም በተሻለው አጋጣሚ ቆሮንቶስን ለመጎብኘት ባለው ዓላማ የታመነ ነበር (2ኛ ቆሮ. 1፡18–22)።

“እግዚአብሔር የሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ በእርሱ አዎን ነውና፣ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ክብር በእኛ የሚሆን አሜን በእርሱ ነው” (2ኛ ቆሮ. 1፡20)።

ስለዚህ፣ የእርሱ ምላሽ እነርሱ እንደሚሉት እንደ ሁኔታው የሚለዋወጥ የ”አዎን” እና የ”አይደለም” ድብልቅልቅ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ የሠራው ሥራ ሁልጊዜ “አዎን” እንደሆነ ሁሉ፣ የእርሱም “ሁልጊዜ አዎን” ነበር (2ኛ ቆሮ. 1፡19)።

በመሆኑም፣ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎችን ከመጎብኘት ይልቅ ደብዳቤ የጻፈበት ምክንያት ለእነርሱ ካለው እውነተኛ ፍቅር የተነሣ እንጂ ተቃራኒው አይደለም (2ኛ ቆሮ. 2፡4)። ያንን የሚያሳዝን ጉብኝት ተከትሎ ወዲያውኑ ሌላ ጉብኝት ማድረግ፣ እርሱ ሊሰጣቸው ካሰበው ደስታ ይልቅ ተጨማሪ ሐዘን ያመጣባቸው ነበር (2ኛ ቆሮ. 1፡24፤ 2ኛ ቆሮ. 2፡3)። የእርሱ መልካም ዓላማ እንዴት በቀላሉ በተሳሳተ መንገድ ተተረጎመ! ያላችሁ መልካም ዓላማ በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሞባችሁ ያውቃል? ያኔ ምን ተሰማችሁ? ከዚህስ ምን ተማራችሁ?

ነሐሴ 20
Aug 26

ይቅርታና የፍቅር ማረጋገጫ


ጳውሎስ ቆሮንቶስን ለሁለተኛ ጊዜ ከመጎብኘት ይልቅ፣ ወደ ኤፌሶን ከተመለሰ በኋላ “አስጨናቂው ደብዳቤ” ተብሎ የሚታወቀውን ላከላቸው (2ኛ ቆሮ. 2፡3፣ 4፤ 2ኛ ቆሮ. 7፡ 8፣ 12ን ይመልከቱ)። 2ኛ ቆሮንቶስ 7፡5–13ን አንብቡ። ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ ውጤቱ ምን ነበር? ጳውሎስስ በውጤቱ ላይ የነበረው ምላሽ ምን ነበር?



ጳውሎስና ቲቶ ቆይተው በመቄዶንያ ተገናኙ፤ እዚያም ጳውሎስ የጻፋቸው ጠንካራ ቃላት በጎ ውጤት ማምጣታቸውን የሚገልጽ ግሩም ዜና ከቲቶ ሰማ፤ ይህም የሐዋርያውን ልብ በታላቅ ደስታ ሞላው። ቀደም ሲል በቆሮንቶስ ያሉ አንዳንዶች በጳውሎስ ላይ ተነሥተው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከእርሱ ጎን ቆመች። መሪዎቻችንን መደገፍ ምን ያህል አስፈላጊ ነው! እኛ የቤተ ክርስቲያን አባላት የመሪዎቻችንን ሥራ ካለበት ይልቅ በጣም ቀላል ልናደርግላቸው እንችላለን። 2ኛ ቆሮንቶስ 2፡5–11ን አንብቡ። እዚህ ጋ ያለው ማዕከላዊ ሐሳብ ምንድን ነው?



ይህ ክፍል ከቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ (discipline) ጋር የተያያዘ ነው። ምሁራን ጥፋተኛው በ1ኛ ቆሮንቶስ 5፡1–5 ላይ የተጠቀሰው ዝሙት የፈጸመው ሰው ነው ወይስ ሌላ ሰው በሚለው ላይ ይከራከራሉ። ይህ ሌላ የተባለው ሰው፣ ጳውሎስ በጉዞ ውሳኔዎቹ ላይ የማይጸናና ለእነርሱ ግድ የማይለው ነው በማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትከሰው ተጽዕኖ ያደረገ ሰው ሊሆን ይችላል። አውዱ ለሁለተኛው አማራጭ የሚያደላ ይመስላል። ያም ሆነ ይህ፣ የክፍሉ ዋና ትምህርት ቤተ ክርስቲያን በኃጢአት ውስጥ ያለን ሰው እንዴት መያዝ እንዳለባት የሚመለከት ነው።

ይህ ክፍል የሚያስተምረው የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ዓላማ በይቅርታና ለኃጢአተኛው ያለን ፍቅር ዳግም በማረጋገጥ ወደ ነበረበት መመለስ (restoration) መሆኑን ነው (2ኛ ቆሮ. 2፡6–8፣ 10)።

እንዲሁም ክፍሉ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ አሳዛኝ ሊሆን ቢችልም አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማል። ይኸውም፣ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ምንም ያህል መልካም ዓላማ ቢኖራቸውና “በጸጋ” ላይ ያተኮሩ መሆን ቢፈልጉም፣ ግልጽ የሆነን ወይም በይፋ የሚታወቅን ኃጢአት ከመጋፈጥና ከመያዝ ወደኋላ ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሌሎች በጣም ጥብቅ፣ ይቅር የማይሉና ሻካራ ሊሆኑ ይችላሉ። ኃጢአት መያዝ ያለበት ቢሆንም በፍቅር መሆን አለበት። በመሆኑም፣ ጳውሎስ ራሱ ቤተ ክርስቲያኒቱን ስለሚወዳት (2ኛ ቆሮ. 2፡4)፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለበደለኛው ሰው ያላትን ፍቅር ዳግም እንድታረጋግጥ ሊመክራት ችሏል (2ኛ ቆሮ. 2፡8)! የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በደለኛውን ሊወዱ የቻሉት (2ኛ ቆሮ. 2፡8)፣ እነርሱ ራሳቸው በጳውሎስ ፍቅር አማካኝነት የእግዚአብሔር ፍቅር ተካፋዮች ስለሆኑ ነው። ይህ ስለ ፍቅር ምን ያስተምረናል?

ነሐሴ 21
Aug 27

በክርስቶስ ድል መንሣት


2ኛ ቆሮንቶስ 2፡12፣ 13ን አንብቡ። ጳውሎስ ያንን “አስጨናቂ ደብዳቤ” ከጻፈላቸው በኋላ ወዴት ሄደ? እዚያስ ምን አደረገ?



ጳውሎስ ቲቶን ይጠባበቅ በነበረበት ወቅት ልቡ እረፍት አጥቶ ነበር (2ኛ ቆሮ. 7፡5፣ 6)። ያም ጭንቀት ቢኖርበትም፣ ስለ የሱስ መናገሩን ሊያቆም አልቻለም (2ኛ ቆሮ. 2፡12)። የሱስን እጅግ ይወደው ነበር። በዚያን ወቅት የላከው ደብዳቤ ምን ውጤት እንዳመጣ ገና አያውቅም ነበር። ቲቶን ለማየትና የቆሮንቶስ ሰዎች የሰጡትን ምላሽ ለመስማት ይጓጓ ነበር።

ጳውሎስ በጢሮአዳ የነበረው ሥራ ስኬታማ ቢሆንም “እዚያ ረጅም ጊዜ ሊቆይ አልቻለም። “የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ” በተለይም የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በልቡ ላይ ክፉኛ ከብዶበት ነበር። ቲቶን በጢሮአዳ አግኝቶ ለቆሮንቶስ ወንድሞች የላከውን የምክርና የተግሣጽ ቃል እንዴት እንደተቀበሉት ከእርሱ ለመስማት ተስፋ አድርጎ ነበር፤ ነገር ግን በዚህ ተስፋው ሳይሳካ ቀረ። ስለዚህ ተሞክሮ ሲጽፍ፦ “ወንድሜን ቲቶን ስላላገኘሁት መንፈሴ ዕረፍት አልነበረውም” ይላል። በመሆኑም ጢሮአዳን ትቶ ወደ መቄዶንያ ተሻገረ፤ እዚያም በፊልጵስዩስ ጢሞቴዎስን አገኘው።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ የሐዋርያት ሥራ (The Acts of the Apostles)፣ ገጽ 323። 2ኛ ቆሮንቶስ 2፡14–17ን አንብቡ። ጳውሎስ ቲቶን በመቄዶንያ ሲያገኘውና የቆሮንቶስ ሰዎች የሰጡትን በጎ ምላሽ ሲሰማ የተሰማው ስሜት ምን ነበር?



ጳውሎስ በታላቅ ደስታ ተሞልቶ እግዚአብሔርን “ሁልጊዜ በክርስቶስ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን” በማለት ይገልጻል (2ኛ ቆሮ. 2፡14)። ምንኛ ድንቅ አባባል ነው! በክርስቶስ ሕልውና የተሞላ ልብ “የእውቀቱን መዓዛ በየስፍራው ሁሉ” ይበትናል (2ኛ ቆሮ. 2፡14)።

ጳውሎስ በክርስቶስ ደስ ይለዋል፤ ምክንያቱም ያ ያስጨነቀው ደብዳቤ እርሱ የጠበቀውን ፍሬ አፍርቷል (2ኛ ቆሮ. 7፡5–9)። ይህ ትልቅ ድል ነው። በዚያውም ቅጽበት በ2ኛ ቆሮንቶስ 2፡17 ላይ ጳውሎስ እንደ ክርስቶስ ሐዋርያነቱ ያለውን እውነተኛነት በድጋሚ ያረጋግጣል (2ኛ ቆሮ. 2፡17፤ 2ኛ ቆሮ. 1፡12)። በዚህ ክፍል መሠረት፣ የታመነ የክርስቶስ አገልጋይን ከሐሰተኛ አገልጋይ የሚለየው፤ የኋለኛው ለግል ጥቅሙ ሲል በወንጌል የሚነግድ ሲሆን፣ የቀደመው ግን የእግዚአብሔርን ቃል ለክርስቶስ ባለው ፍጹም ፍቅር የሚሰብክ መሆኑ ነው። በምታደርጉት ነገር ሁሉ፣ በተለይም በየሱስ ስም በምታከናውኑት ሥራ ውስጥ የሚያነሳሳችሁ ዓላማ (ሞቲቭ) ምንድን ነው?

ነሐሴ 22
Aug 28


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ ኋይት፣ “The Message Heeded፣” ገጽ 323–334, በ The Acts of the Apostles.

“ከፍተኛ ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች፣ ብዙ ጊዜ ለሌሎች ታላቅ መጽናኛን የሚያመጡና በሄዱበት ሁሉ ብርሃንን የሚፈነጥቁ ናቸው። እንዲህ ያሉ ሰዎች በመከራቸው ተቀጥተዋል፤ እንዲሁም ተኮትኩተዋል። ችግር ሲገጥማቸው በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት አላጡም፤ ይልቁንም ጠብቆ ወደሚይዛቸው ፍቅሩ ይበልጥ ተጠግተዋል። እንዲህ ያሉ ሰዎች ለእግዚአብሔር ርኅራኄ የተሞላበት እንክብካቤ ሕያው ምስክሮች ናቸው።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ የእግዚአብሔር ድንቅ ጸጋ (God’s Amazing Grace)፣ ገጽ 122።

“የተቀደሰ ክርስቲያናዊ ሕይወት ሁልጊዜ ብርሃንን፣ መጽናኛንና ሰላምን ይፈነጥቃል። በንጽሕና፣ በብልሃት፣ በቅንነትና በጠቃሚነት ይታወቃል። ተጽዕኖውን በሚቀድስ በዚያ ራስ ወዳድ ያልሆነ ፍቅር ቁጥጥር ሥር ነው። በክርስቶስ የተሞላ ነው፤ ባለቤቱም በሄደበት ስፍራ ሁሉ የብርሃን ፈለግ ጥሎ ያልፋል።” — የእግዚአብሔር ድንቅ ጸጋ፣ ገጽ 122።

“ሐዋርያው ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ስህተት መገሠጽ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፤ ነገር ግን ስህተትን በሚገሥጽበት ጊዜ ራሱን የመግዛት ኃይሉን አላጣም። ለወሰደው እርምጃ ምክንያቱን በጭንቀት ያብራራል። የበደሉትን ሰዎች ወዳጅ መሆኑን ለማሳየት ምንኛ በጥንቃቄ ሠራ! እነርሱን ማሳዘን ለእርሱም ሕመም እንደነበረው እንዲረዱ አደረገ። የእርሱ ፍላጎት ከእነርሱ ፍላጎት ጋር የተቆራኘ መሆኑን በአእምሮአቸው ውስጥ እንዲታተም አደረገ።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ የኤስ.ዲ.ኤ. የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ (SDA Bible Commentary)፣ ቅጽ 6፣ ገጽ 1094።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በ2ኛ ቆሮንቶስ 2፡1–14 ላይ ጳውሎስ በአገልግሎቱ ያለውን ታማኝነት (integrity) ያረጋግጣል። ይህ የአገልግሎት ባሕርይ እንዲህ ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?

2. ጳውሎስ የጉዞ ዕቅዱን መለወጡ፣ በክርስቲያናዊ አገልግሎት ውስጥ ተለዋዋጭ (flexible) መሆን አስፈላጊ ስለመሆኑ ምን ያስተምረናል? አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለለውጥ ዝግጁ መሆን ለምን ይጠቅማል?

3. ጳውሎስ በአገልግሎቱ ውስጥ ጭንቀትና መከራ ገጥሞታል። ይህም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ ማንኛውም ሰው ለጭንቀት የተጋለጡ የሰው ልጆች መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል። የቤተ ክርስቲያን አባላት የመሪዎቻቸውን ሥራ ለማቅለል ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

4. ጳውሎስ በክርስቶስ ስላለው ድል ከመጥቀሱ በፊት (2ኛ ቆሮ. 2፡14)፣ ስለ ነበረው እረፍት ማጣት ይናገራል (2ኛ ቆሮ. 2፡13)። ስለ ድክመቱና ስለ ጥንካሬው በአንድ ጊዜ መናገር የቻለው እንዴት ነው? እኛስ እንዴት እንችላለን?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL