የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

1ኛ እና 2ኛ ቆሮንቶስ - የክርስቲያን ሕይወት እና ምስክርነት ባሕርይ



3ኛ ሩብ ዓመት 2026


ነሐሴ 23 - 29

10ኛ ትምህርት

Aug 29 - Sep 4




እውነተኛ የክርስቲያን አገልግሎት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት እነዚህን ክፍሎች አንብቡ፦ 2ኛ ቆሮ. 3:1–9፤ 2ኛ ቆሮ. 4:7–18፤ 2ኛ ቆሮ. 5:11–15፤ ቆላ. 1:19–23፤ ኤፌ. 2:13–16፤ 2ኛ ቆሮ. 6:11–7:1፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 7።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን” (2ኛ ቆሮንቶስ 4:8–10)።

ባለፈው ሳምንት ጳውሎስ ቅንነቱንና እውነተኛነቱን በማረጋገጥ፣ በቆሮንቶስ ሰዎች ዘንድ ከቀረበበት የማይጸና ባሕርይና የፍቅር ማጣት ክስ ራሱን እንዴት እንደተከላከለ አይተናል። እርሱ ሁልጊዜ የሚሠራው ለመንፈሳዊ ልጆቹ የተሻለውን ጥቅም በማሰብ ነበር። በ2ኛ ቆሮንቶስ 2:12–17 ላይ የጀመረውንና እስከ 2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 7 የሚቀጥለውን የሐሳብ መስመር ተከትሎ፣ እውነተኛ የክርስቶስ አገልግሎት ምን እንደሚመስል ያብራራል። ከዚህ የጳውሎስ ሐሳብ ብዙ ትምህርቶችን ልንቀስም እንችላለን።

በዚህ ሳምንት ጳውሎስ ነፍሳትን ለክርስቶስ ስለ ማዳን አገልግሎቱ በሚናገርበት በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 3–7 ላይ እናተኩራለን። ኤለን ጂ ኋይት እንዲህ ትላለች፦ “የኃጢአተኞች መመለስና በእውነት መቀደስ፣ አንድ አገልጋይ እግዚአብሔር ወደ አገልግሎት እንደጠራው ሊኖረው የሚችል ታላቅ ማስረጃ ነው። የሐዋርያነቱ ማስረጃ በተመለሱት ሰዎች ልብ ውስጥ የተጻፈና በታደሰ ሕይወታቸው የሚመሰከር ነው። ክርስቶስ የክብር ተስፋ ሆኖ በውስጣቸው ተቀርጿል። አንድ አገልጋይ በእነዚህ የአገልግሎቱ ማኅተሞች እጅግ ይበረታል”። — ኤለን ጂ ኋይት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ገጽ 328።

*ለጳጉሜ 1 (September 5) ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።

ነሐሴ 24
Aug 30

የእውነተኛ አገልግሎት ፍሬዎች


2ኛ ቆሮንቶስ 3:1–9ን አንብቡ። በምን ዓይነት መንገድ የክርስቶስ ደብዳቤ ልንሆን እንችላለን?



በግሪኮ-ሮማውያን ዓለም የጥቆማ ወይም የባለ አደራነት ደብዳቤዎች (Letters of rec- ommendation) የተለመዱ ነበሩ። ሆኖም ጳውሎስ እንዲህ ያሉ ደብዳቤዎችን አልያዘም ነበር። በቆሮንቶስ ሰዎች ሕይወት ውስጥ የታየው የመንፈስ ቅዱስ ለውጥ የማምጣት ኃይል፣ የእርሱ እውነተኛ አገልግሎት ማረጋገጫ ነበር። ይሁን እንጂ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ያለችው ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በእርሱ ብልህነት ወይም ጥረት እንዳልሆነ እርግጠኛ ነበር (2ኛ ቆሮ. 3:4–6)። እርሱ ራሱን በማስተዋወቅ ወይም በማግነን ሥራ ላይ አልተሰማራም ነበር (2ኛ ቆሮ. 3:5፤ 1ኛ ቆሮ. 2:2)።

ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ሲናገር ስለ ሁለቱ ኪዳናት በአጭሩ ያብራራል፦ በሙሴ ስለተወከለው አሮጌው ኪዳን እና በእርሱና በሥራ ባልደረቦቹ ስለተወከለው አዲሱ ኪዳን። አንድ በችኮላ የሚያነብ ሰው አሮጌው ኪዳን የደኅንነት ተስፋ አልሰጠም ብሎ ሊያስብ ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ስህተት ነው። ደኅንነት በአሮጌውም ሆነ በአዲሱ ኪዳን ይገኝ ነበር። አሮጌው ኪዳን አስቀድሞ የቀረበ ወንጌል ነበር። “መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፦ “በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ” ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ” (ገላ. 3:8)።

በ2ኛ ቆሮንቶስ 3:1–4:6 ውስጥ፣ አሮጌው ኪዳን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት በራሳቸው የመታዘዝ ሥራ ላይ ይደገፉ የነበሩትን ሰዎች የሕግ አምላኪነት (legalistic) ተሞክሮ ለመግለጽ እንደ ተጠቀመበት እናያለን። አዲሱ ኪዳን ግን፣ እግዚአብሔር ለእነርሱና በውስጣቸው ሊያደርግ ቃል የገባውን ሁሉ እንዲፈጽም ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ የሚደገፉትን ሰዎች ተሞክሮ ይወክላል።

ጳውሎስ እየተናገረ ያለው አማኞችና የማያምኑት ለወንጌል ስለሚሰጡት ሁለት የተለያየ ምላሽ ነው። እርሱ በአሮጌው ኪዳን ስለነበረ አንድ ወንጌልና በአዲሱ ኪዳን ስለሚገኝ ሌላ የተለየ ወንጌል እያወራ አይደለም—ምክንያቱም እግዚአብሔር የሰጠው አንድ ወንጌል ብቻ ነውና፤ እርሱም “እንደ ገዛ ዓላማውና ጸጋው መጠን አዳነን፤ በቅዱስም አጠራር ጠራን፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ የሱስ ተሰጠን እንጂ እንደ ሥራችን አይደለም” (2ኛ ጢሞ. 1:9)።

ይህ ማለት ግን 2ኛ ቆሮንቶስ 2:14–4:6 አንዳንድ ታሪካዊ ነጥቦችን አልያዘም ማለት አይደለም። ነገር ግን ጳውሎስ ያንን ታሪክ የሚጠቀመው ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ “የሚድኑ” ሌሎቹ ደግሞ “የሚጠፉ” መሆናቸውን ለማሳየት ነው (2ኛ ቆሮ. 2:15)። ሙሴ ለአከናወነው አገልግሎት በታየው አለማመንና የእምነት ማጣት ምላሽ ምክንያት፣ አገልግሎቱ የኩነኔና የሞት አገልግሎት ተደርጎ ሊታይ ይችላል። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ስላመነች ግን፣ በጳውሎስ አማካኝነት በመካከላቸው የተከናወነው አገልግሎት የጽድቅ አገልግሎት፣ ሕይወትን የሚሰጥ የመንፈስ አገልግሎት መሆኑ ተረጋገጠ።

በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የታየው ይህ የደኅንነት ተሞክሮ፣ የጳውሎስ እውነተኛ አገልግሎት ማስረጃ ነው።

ነሐሴ 25
Aug 31

መከራና ክብር


2ኛ ቆሮንቶስ 4፡7–18ን አንብቡ። የጳውሎስን መከራዎች ዝርዝር አውጡ። መከራዎቹን እንዴት ሊቋቋም ቻለ?



የቀድሞዋ ቦሔሚያ ታላቅ የተሐድሶ ሰው የነበረው ጆን ሁስ ስለ የሱስ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እርሱ የዓለም ጌታ ነው፤ እኛ ደግሞ የተናቅን ሟቾች ነን—ሆኖም እርሱ መከራን ተቀበለ! ታዲያ እኛስ መከራን መቀበል የማይገባን ለምንድን ነው? በተለይም መከራ ለእኛ ማጥሪያ (purification) በሚሆንበት ጊዜ?” — ኤለን ጂ ኋይት፣ ታላቁ ተጋድሎ፣ ገጽ 105።

ሐዋርያው ጳውሎስ ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት ስለ ክርስቶስ መከራን ለመቀበል ተመሳሳይ ፈቃደኝነትን አሳይቷል። እርሱ ከሸክላ ከተሠራ ደካማ ዕቃ የሚበልጥ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር (2ኛ ቆሮ. 4፡7)። ሁልጊዜም እንደሚገፋ፣ እንደሚያመነታ፣ እንደሚሰደድና እንደሚወድቅ ይሰማው ነበር፤ ሆኖም አልተጨነቀም፣ ተስፋ አልቆረጠም፣ አልተጣለም ወይም አልጠፋም (2ኛ ቆሮ. 4፡8፣ 9)። “የየሱስ ሕይወት” በእርሱ ይገለጥ ዘንድ “የየሱስን መሞት በሥጋው” ለመሸከም ፈቃደኛ ነበር (2ኛ ቆሮ. 4፡10፣ 11)።

ጳውሎስ “የየሱስ መሞት” ሲል ምናልባት በቀደሙት ጥቅሶች ላይ የጠቀሳቸውን መከራዎች ማለቱ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይ መልኩ፣ “የየሱስ ሕይወት” የሚለው ሐረግ በአፋጣኝ ትርጉሙ ከሞት መዳንን ወይም ለአሁኑ ሕይወት የሚሆን መንፈሳዊ ኃይልን ሊያመለክት ይችላል። ነገር ግን፣ በመጨረሻው ደረጃ ይህ የሚያመለክተው ትንሣኤን ነው (2ኛ ቆሮ. 4፡12)።

የሚገርመው “ሞትና ሕይወት” የሚሉት ጥንድ ቃላት በ2ኛ ቆሮንቶስ 4፡10–12 ውስጥ ሦስት ጊዜ ተጠቅሰዋል። ይህም በዚህኛው ዘመን ሕይወት ከሞት ጋር የተቀላቀለች መሆኗን ማስታወሻ ነው። ሆኖም፣ በሚመጣው ክብር ውስጥ ሞት በሌለበት ሁኔታ ሕይወትን እንለማመዳለን (ራእይ 20፡14፤ ራእይ 21፡4)።

ከሁሉም በላይ፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡7–18 የሚያሳየው ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ ይሆን ዘንድ ወንጌል የሚሰበከው በደካማ የሰው ልጆች አማካኝነት መሆኑን ነው (2ኛ ቆሮ. 4፡ 15)። ሚስዮናውያን በሚያከናውኑት ሚስዮናዊ ሥራ ሂደት ውስጥ መከራ መቀበላቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም። ሆኖም፣ እዚህ ያለው መከራችን ከሚጠብቀን የዘላለም የክብር ክብደት ጋር ሲነጻጸር ቀላልና ለጥቂት ጊዜ የሚቆይ ነው (2ኛ ቆሮ. 4፡17)። አማኝ የሚኖረው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም (2ኛ ቆሮ. 4፡18፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡7)።

ይህ በሚመጣው ሕይወት ላይ ያለው ተስፋ የጳውሎስን አእምሮ እጅግ ስለማረከው በዚሁ የሐሳብ መስመር ማብራራቱን ይቀጥላል (2ኛ ቆሮ. 5፡1–10)። ለሟች አካሉ “ምድራዊ ቤት” የሚለውን ዘይቤአዊ አገላለጽ ይጠቀማል። በተቃራኒው፣ “ከእግዚአብሔር የሆነው ሕንፃ” ለትንሣኤ አካል የተሰጠ ዘይቤአዊ አገላለጽ ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡1)፤ ይህም በሁሉም ዘመናት ላሉ አማኞች ታላቅ ተስፋ ነው። አሁን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም፣ የትንሣኤውን ተስፋ—የራሳችንን ትንሣኤ (1ኛ ቆሮ. 15፡52)—ሁልጊዜ በፊታችን ማድረጋችን ለምን በጣም አስፈላጊ ይሆናል?

ነሐሴ 26
Sep 1

በክርስቶስ ላይ ያተኮረ የማስታረቅ አገልግሎት


2ኛ ቆሮንቶስ 5:11–15ን አንብቡ። ይህ ክፍል የጳውሎስ አገልግሎት በክርስቶስ ላይ ያተኮረ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?



ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ለክርስቶስ መልስ መስጠት (ሂሳብ ማቅረብ) እንዳለበት ያውቅ ነበር (2ኛ ቆሮ. 5:10)። እርሱ “የጌታን መፈራት” ያውቅ ነበር፤ ሰዎችንም ስለ ክርስቶስ ወንጌል ለማሳመን ይጋደል ነበር (2ኛ ቆሮ. 5:11)። ይህ ፍርሃት ለክርስቶስ የሚሰጥ አክብሮትና ጥልቅ ስሜት (reverence and awe) ነው፤ በመሆኑም ጳውሎስ ለክርስቶስ ካለው ፍቅርና ክርስቶስ ለእርሱ ባለው ፍቅር ላይ ካለው መታመን ጋር የተቆራኘ ነው። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔርን መፍራት ማለት በመንገዱ መሄድ፣ እርሱን መውደድ፣ እንዲሁም በፍጹም ልብና ነፍስ ማገልገል ማለት ነው (ዘዳ. 10:12)።

የጳውሎስ አገልግሎት በራሱ ላይ ሳይሆን በክርስቶስ ላይ ያተኮረ ነው። ራሱን አላገነነም (አላመሰገነም)። የትምክህቱ ምክንያት ክርስቶስ ነው (2ኛ ቆሮ. 12:9)። “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” ብሏል (ገላ. 6:14)። ስለዚህ የቆሮንቶስ ሰዎች በእርሱ እንዲመኩ የተሰጣቸው ዕድል (2ኛ ቆሮ. 5:12)፤ በራሳቸው ላይ ከሚያተኩሩት ተቃዋሚዎቹ አገልግሎት ይልቅ፣ በእርሱ በክርስቶስ ላይ ባተኮረው አገልግሎት እንዲኮሩ ማለት ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 5:16–21፣ ቆላስይስ 1:19–23 እና ኤፌሶን 2:13–16ን አንብቡ። ጳውሎስ “የማስታረቅ አገልግሎት” ሲል ምን ማለቱ ነው?



ክርስቶስ ወደር የማይገኝለት (par excellence) የማስታረቅ አገልጋይ ነው። እንደዚሁም እርሱ “የማስታረቅን አገልግሎት ሰጠን” (2ኛ ቆሮ. 5:18)። የማስታረቅ ሐሳብ በ2ኛ ቆሮንቶስ 5:16–21 ውስጥ ደጋግሞ ተጥቅሷል። ይህ ለጳውሎስ መሠረታዊ ጽንሰ-ሐሳብ ነው፤ ለእኛም እንዲሁ ሊሆን ይገባል።

እግዚአብሔር በልጁ የቤዛነት ሞት አማካኝነት የሰውን ልጅ ከራሱ ጋር አስታርቋል። ከእግዚአብሔር ጋር የታረቁት አዲስ ፍጥረት ናቸው (2ኛ ቆሮ. 5:17)። አሁን ደግሞ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ ይህንን “የማስታረቅ ቃል” ለሌሎች ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል (2ኛ ቆሮ. 5:19)። በዚህ ስሜት “እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን” (2ኛ ቆሮ. 5:20)። ክርስቶስ ለእርስዎ ስላደረገው ነገር ያስቡ። እርሱ በመስቀል ላይ ስላደረገልዎት ነገር ባይሆን ኖሮ የእርስዎ ሊሆን የሚችለውን በደል፣ ኃጢአትና ኩነኔ ያስቡ። ይህ እውነታ ከሌሎች ጋር፣ በተለይም ጌታን ከማያውቁት ጋር ባላችሁ ግንኙነት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል?

ነሐሴ 27
Sep 2

ወደ ቅድስና የሚደረግ ጥሪ


በ2ኛ ቆሮንቶስ 6፡3–10 ላይ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ማበረታታቱን ይቀጥላል። የክርስቶስ ተከታይና የእግዚአብሔር አገልጋይ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ለማሳየት ረጅም የመከራና የድል ዝርዝር ያቀርባል። በአጭሩ፦ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን (2ኛ ቆሮ. 6፡4፣ 5)፣ የባሕርይ በጎነቶችን (2ኛ ቆሮ. 6፡6)፣ ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ ትጥቆችን (2ኛ ቆሮ. 6፡7) እና የአገልግሎት ውጣ ውረዶችን (2ኛ ቆሮ. 6፡ 8–10) ዘርዝሯል። በቆሮንቶስ ያሉ አባላት ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ካስተማረ በኋላ፣ ራሳቸውን ከማያምኑት ጎጂ ተጽዕኖና ከርኩስ ነገሮች በመለየት ቅዱስ ሕይወት እንዲኖሩ ጥሪ ያቀርባል (2ኛ ቆሮ. 6፡14–17)። 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡11–7፡1ን አንብቡ። በዚህ ክፍል መሠረት ቅዱስ ሕይወት ምን ይመስላል?



ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የመዋደድና የፍቅር አስፈላጊነት ያጎላል (2ኛ ቆሮ. 6፡11–13)። ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር መታረቃቸው የሚታወቀው እርስ በርሳቸው እርቅን ሲፈልጉ ነው። በእርግጥም እነርሱ በሰዎች መካከል የእርቅ ወኪሎች ይሆናሉ።

በመቀጠልም የቅድስና ጥሪ በስድስት ማሳሰቢያዎች አማካኝነት ቀርቧል፤ እነርሱም፦ (1) “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ” (2ኛ ቆሮ. 6፡14)፤ (2) ““ከመካከላቸው ውጡ”” (2ኛ ቆሮ. 6፡17)፤ (3) ““ተለዩ”” (2ኛ ቆሮ. 6፡17)፤ (4) ““ርኩስንም አትንኩ”” (2ኛ ቆሮ. 6፡17)፤ (5) “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” (2ኛ ቆሮ. 7፡1)፤ (6) “በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እናድርግ” (2ኛ ቆሮ. 7፡1፤ አጽንኦት የተጨመረበት)። እነዚህ ምክሮች ቅዱስ የሆነው አምላክ ቅዱስ ሕይወትንና ከጣዖት አምልኮ መለየትን እንደሚፈልግ ያሳያሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ይህ ክፍል የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያንን እንደ ቅዱስ መቅደስነቷ የሚያሳዩ ሰባት ተስፋዎችን ይዟል፦ (1) ““በእነርሱ እኖራለሁ””፤ (2) ““በመካከላቸውም እመላለሳለሁ””፤ (3) ““አምላካቸውም እሆናለሁ””፤ (4) ““እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ””፤ (5) ““እቀበላችኋለሁ””፤ (6) ““ለእናንተም አባት እሆናለሁ””፤ (7) ““እናንተም ለእኔ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትሆናላችሁ”” (2ኛ ቆሮ. 6፡16፣ 17፣ 18)።

በ2ኛ ቆሮንቶስ 6፡16 ላይ ያሉት አራት ተስፋዎች በ2ኛ ቆሮንቶስ 6፡17 ላይ ላሉት ሦስት ትእዛዛት መሠረት መሆናቸውን ልብ ይበሉ (በ2ኛ ቆሮንቶስ 6፡17 መጀመሪያ ላይ “ስለዚህ” የሚለውን ቃል ይመልከቱ)። ይህም ቅድስና የአንድ ሰው ጥረት ውጤት ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ በልብ ውስጥ የመሥራቱ ውጤት መሆኑን ያሳያል። ቅድስና ከእግዚአብሔር የሚመነጭ ቢሆንም፣ አማኞች የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንዲሁም ጣዖት አምልኮንና ማንኛውንም ርኩስ ተግባር መቃወም አለባቸው። በ2ኛ ቆሮንቶስ 6፡16–18 ላይ ያሉ የእግዚአብሔር ተስፋዎች ቅድስና ምን እንደሆነ ምን ይነግሩናል?

ነሐሴ 28
Sep 3

መጽናኛና ደስታ


2ኛ ቆሮንቶስ 7ን አንብቡ። የቆሮንቶስ ሰዎች ንስሐ መግባታቸውን ሲሰማ ጳውሎስ የተሰማው ስሜት ምንድን ነው?



“በልባችን ውስጥ ናችሁ” ከሚሉት ቃላት ውስጥ ምን ያህል ፍቅር ይፈስሳል! (2ኛ ቆሮ. 7:3፤ እንዲሁም 2ኛ ቆሮ. 6:11ን ይመልከቱ)። ጳውሎስ ለእነርሱ ያለው ፍቅር በምላሹ እንዲሰጠው ካለው ጥልቅ ምኞት የተነሣ “በልባችሁ ስፍራ አድርጉልን” ይላል (2ኛ ቆሮ. 7:2)። ምንም እንኳ “በልባችሁ” የሚለው ሐረግ በግሪኩ ቅጂ ውስጥ ባይኖርም፣ አውዱ የሚደግፈው በመሆኑ አብዛኞቹ ትርጉሞች አካተውታል።

በእርግጥም የቆሮንቶስ ሰዎች ልባቸውን ለጳውሎስና ለሥራ ባልደረቦቹ ከፈቱ። ለዚህ ነው ቁጥር 4 ኃይለኛ የሆነ የደስታ መግለጫ የሆነው። የጳውሎስ ቃላት በዚህ ቅጽበት ያለውን በጎ ስሜት ይገልጻሉ፦ “ለእናንተ ያለኝ መታመን ታላቅ ነው፤ በእናንተም መመካቴ ታላቅ ነው፤ መጽናናት ሞልቶብኛል፤ በመከራችን ሁሉ ደስታዬ ከልክ በላይ ሆኖአል” (2ኛ ቆሮ. 7:4)።

ጳውሎስ በመጽናኛና በደስታ ተሞልቷል። አብያተ ክርስቲያናቶቻችን ራሳቸውን በታማኝነት ለክርስቶስ አሳልፈው በመስጠት፣ ለአገልጋዮቻቸው ልብ ምን ያህል መጽናኛና ደስታ ሊያመጡ ይችላሉ!

በ2ኛ ቆሮንቶስ 7:5–16 ላይ ጳውሎስ ለመጽናኛውና ለደስታው ያለውን ምክንያት የበለጠ ያብራራል። እነዚህ ሁለት ጽንሰ-ሐሳቦች በክፍሉ ውስጥ በጉልህ ይታያሉ። “ማጽናናት” (parakaleō) የሚለው ግስ ወይም “መጽናናት” (paraklēsis) የሚለው ስም በ2ኛ ቆሮንቶስ 7 ውስጥ በአጠቃላይ ሰባት ጊዜ ተጠቅሰዋል። ይህ የደብዳቤው ክፍል የተጀመረውም የተመሰረተውም እግዚአብሔር በሚሰጠው ታላቅ መጽናኛ ላይ ነው (2ኛ ቆሮ. 1:3–7)። በምዕራፍ 7 ላይ ያለው የጳውሎስ መጽናኛ የመጣው ያ ያስጨነቀው ደብዳቤ የፈለገውን ውጤት በማምጣቱ ከተሰማው እረፍት ነው።

ምንም እንኳ ይህ እረፍት የቲቶ በጎ ሪፖርት ውጤት ቢሆንም፣ በመጨረሻ ግን ጳውሎስ ለተለማመደው መጽናኛ ዋናው ባለቤት እግዚአብሔር ነው (2ኛ ቆሮ. 7:6)። በእርግጥም እግዚአብሔር “በመከራችን ሁሉ የሚያጽናናን... የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ነው (2ኛ ቆሮ. 1:3፣ 4)።

የሚገርመው ጳውሎስ “በመጽናናት ሲሞላ”፣ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ “ደስታው ከልክ በላይ” ነበር (2ኛ ቆሮ. 7:4፣ 7፣ 13)። ምንም እንኳ ያ ያስጨነቀው ደብዳቤ ብዙ ሐዘን ቢያመጣም፣ ያ ሐዘን ግን ንስሐን ለማምጣት የታለመ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሐዘን ነበር (2ኛ ቆሮ. 7:9–11)። የቆሮንቶስ ሰዎች “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አዝነዋል” (2ኛ ቆሮ. 7:11)፤ ይህም ሐዘን “ለደኅንነት የሚሆንና ጸጸት የሌለበትን ንስሐ” የሚያስገኝ ነው (2ኛ ቆሮ. 7:10)። ታዲያ ለእውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋይ ከዚህ የበለጠ ምን ደስታ ሊኖር ይችላል? በህይወታችሁ ውስጥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነን ሐዘን ተለማምዳችሁ ታውቃላችሁ? ያ ሐዘን ወደ ንስሐ የሚመራ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን እንዴት አወቃችሁ?

ነሐሴ 29
Sep 4


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ ኋይት፣ “የተሰማው መልእክት”፣ ገጽ 323–334፣ የሐዋርያት ሥራ።

ባለፈው ሳምንት በየሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰውን ከላይ ያለውን ክፍል አንብበናል። አሁንም በድጋሚ ማንበቡ ጠቃሚ ነው። በዚህ ጊዜ፣ ጳውሎስ ስለ ላከው አስጨናቂ ደብዳቤ፣ ደብዳቤውን በሚጽፍበት ጊዜ ስለነበረው ስሜት፣ እና የተላከላቸው ሰዎች በቅንነት ንስሐ መግባታቸውን የሚገልጽ የምስራች ሲቀበል ስለነበረው ደስታ በሚናገሩት ክፍሎች ላይ ጥቂት ረዘም ላለ ጊዜ አሰላስሉ። በመቀጠልም፣ ይህ ስለ ጳውሎስ አገልግሎት እውነተኛነት ምን እንደሚነግራችሁና ለክርስቶስ በምታከናውኑት ሥራ ውስጥ ምን ዓይነት ትምህርቶችን ልትተገብሩ እንደምትችሉ አስቡ።

“ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ እንዳለ፣ በእግዚአብሔርም ፍቅር አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር ልንታረቅ እንደምንችል ለጽንፈ ዓለሙ፣ ለወደቀው ዓለምና ላልወደቁት ዓለማት መግለጥ አለብን። ሰው ንስሐ ይገባል፣ ልቡ ይሰበራል፣ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕትነት ያምናል፣ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር እንደታረቀ ይገነዘባል።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ ልዩ የምስክርነት ቃላት በትምህርት ላይ (Special Testimonies On Education)፣ ገጽ 223።

“እንደ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ብርሃን ተቀብለናል። ይህንን ብርሃን ጌታ ለዓለም ጥቅም እንዲሆንና በረከት እንዲያመጣ አደራ ሰጥቶናል። ለእኛ የማስታረቅ አገልግሎት ተሰጥቶናል። ከላይ በሚመጣ ኃይል ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ልንማጸን ይገባል።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ ደብዳቤ 32፣ 1903።

ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር አንዴ ከታረቁ በኋላ ቅድስናን መፈለግ አለባቸው። ኤለን ጂ ኋይት በ2ኛ ቆሮንቶስ 7፡1 ላይ በሰጠችው አስተያየት፣ ጳውሎስ “በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም ማድረግ” (2ኛ ቆሮ. 7፡1) ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ጳውሎስ አዲስ የተመለሱትን አማኞች እንዲህ እንዲሆኑ ለመርዳት እንደጣረ ይናገራሉ፦ “በራሳቸው የሚተማመኑ፣ እያደጉ ያሉ ክርስቲያኖች፣ በእምነት የጠነከሩ፣ በቅንዓት የሚቃጠሉ፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔርና መንግሥቱን ለማስፋፋት በሚደረገው ሥራ ውስጥ በፍጹም ልባቸው ራሳቸውን የሰጡ እንዲሆኑ [ለመርዳት ጥሯል]።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ገጽ 201።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ጳውሎስ የወንጌልን መዝገብ የያዝን “የሸክላ ዕቃዎች” እንደሆንን አድርጎ ይገልጸናል (2ኛ ቆሮ. 4፡7)። የሰው ልጅ ሁኔታ ደካማ፣ ተሰባሪና በውስንነት የተሞላ መሆኑ፣ የወንጌልን ስብከት ከማዳከም ይልቅ እንዴት ሊያጎላው (ሊያግዘው) ይችላል?

2. “አዲስ ፍጥረት” መሆን ማለት ምን ማለት ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡17)? ይህስ በዕለት ተዕለት ሕይወታችሁ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? ክርስቶስ እናንተን አዲስ ፍጥረት ያደረጋችሁት እንዴት ነው?

3. በ2ኛ ቆሮንቶስ 6፡4፣ 5 ላይ ጳውሎስ ስለ ወንጌል ሲል የደረሱበትን ረጅም የመከራዎች ዝርዝር ያቀርባል። ለደረሰበት መከራ የሰጠው ምላሽ ምን ይመስል ነበር (2ኛ ቆሮ. 6፡6፣ 7ን ይመልከቱ)? ይህስ እናንተ ለሚገጥሟችሁ መከራዎች ምላሽ ለመስጠት እንዴት ይረዳችኋል?

4. ጳውሎስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነውን ሐዘን ከዓለም ሐዘን ጋር ያነጻጽራል (2ኛ ቆሮ. 7፡10)። ሐዘን ከንስሐ ጋር የሚገናኘው በምን ዓይነት መንገድ ነው? እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነውን ሐዘን ከዓለም ሐዘን በተለየ መልኩ እንዴት ትገልጹታላችሁ?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL