የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

1ኛ እና 2ኛ ቆሮንቶስ - የክርስቲያን ሕይወት እና ምስክርነት ባሕርይ



3ኛ ሩብ ዓመት 2026


ነሐሴ 30 - መስከረም 1

11ኛ ትምህርት

Sep 5 - 11




መጋቢነትና ተልዕኮ



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት እነዚህን ክፍሎች አንብቡ፦ 2ኛ ቆሮንቶስ 8–9፤ ዮሐንስ 3:16፤ ዮሐንስ 17:5፤ ሉቃስ 9:58፤ ራእይ 13:8፤ ሮሜ 12:8፤ ሮሜ 15:26, 27።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ «የጌታችንን የየሱስ ክርስቶስን ጸጋ አውቃችኋልና፤ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ፣ እርሱ ባለ ጠጋ ሲሆን ስለ እናንተ ድሃ ሆነ» (2ኛ ቆሮንቶስ 8:9)።

ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 8 እና 9 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በይሁዳ ያሉ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን እንዲያገለግሉ ዕድል እንደሰጣቸው ያሳያሉ። ይህ ክፍል መስጠት እግዚአብሔር የክርስቶስን ራስን የመስጠት ባሕርይ እንድንመስል የሰጠን ልዩ መብት መሆኑን ያስገነዝባል። የሰማይ ቋንቋ የመስጠት ቋንቋ ነው። እነዚህን አስደናቂ ቃላት ልብ ይበሉ፦ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐንስ 3:16፤ አጽንኦት የተጨመረበት)።

ከዚህም በላይ፣ ዮሐንስ 3:16 እግዚአብሔር የሱስን የሰጠበትን ዓላማ በግልጽ ያስቀምጣል፤ ይኸውም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ... የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው” ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ መጋቢነትና ተልዕኮ አብረው ይሄዳሉ። እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች የማይነጣጠሉ ናቸው። ጳውሎስ ራሱንና የሥራ ባልደረቦቹን “የእግዚአብሔር ምስጢር መጋቢዎች” (1ኛ ቆሮ. 4:1) ብሎ መጥራቱ አያስደንቅም። እኛም በተመሳሳይ መልኩ መጋቢዎች ነን።

በዚህ ሳምንት የመጋቢነትና የተልዕኮ ጽንሰ-ሐሳቦች በየሱስ አርአያነት ውስጥ እንዴት በጥልቀት ሥር እንደሰደዱ እናያለን። በእርግጥም መጋቢነትና ተልዕኮ የማይነጣጠሉ ናቸው። መጋቢነት ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ተልዕኮ እንድትፈጽም የሚያስፈልጋትን የገንዘብና የሰው ኃይል ግብዓቶችን ያቀርባል።

*ለጳጉሜ 7 (September 12) ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።

ጳጉሜ 1
Sep 6

የየሱስ ምሳሌነት


የ2ኛ ቆሮ 8 እኛ 9 ዐውድ የቆሮንቶስ ቤተክርስትያን አባላት ለተቸገሩት የይሁዳ ክርስትያኖች የሚያደርጉትን የገንዘብ ማሰባሰቢያ እንዲያጠናቅቁ ከማበረታታት ጋር የተያያዘ ነው።

በርግጥም ያን በማድረግ እየተጉ ነበር (2ኛ ቆሮ 8:10– 11፤ 2ኛ ቆሮ 9:5፤ በተጨማሪም 1ኛ ቆሮ 16:1-4)፤ ነገር ግን በእነርሱና በጳውሎስ መካከል የነበሩ የግንኙነት ችግሮች ነገሮችን እያወሳሰቡ ነበር። እነዚህ ችግሮች ከተፈቱ በኋላ (2ኛ ቆሮ 1-7) ጳውሎስ ያን ተግባር ወደ ማጠናቀቅ ጉዳይ ይመለሳል (2 ኛ ቆሮ 8-9)።

በመጀመሪያ ድህነታቸው በልግስና አትረፍርፈው ከመስጠት (2ኛ ቆሮ 8:2) ያልከለከላቸውን መቄዶንያውያንን ምሳሌ አድርጎ ያቀርባል (2ኛ ቆሮ 8:1-7)። አዎ፣ ድህነትና ለጋስነት አብረው ሊሄዱ ይችላሉ። ነገር ግን፣ ይህ የሚደነቅ የመቄዶንያውያን ልግስና ክርስቶስ ስለ እኛ ራሱን የመስጠቱ ምሳሌ እንጂ ሌላ አይደለም (2ኛ ቆሮ 8:8-15)። 2ኛ ቆሮ 8:9ን አንብቡ። ይህ ክፍል ስለ የሱስ ምሳሌነት ምን ይነግረናል?



በ2ኛ ቆሮ 8:9 ውስጥ ያለው የጳውሎስ ንግግር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት ከሁሉ ይልቅ አስደናቂ፣ ኃይለኛ እና መሠረታዊ የሆኑ ክፍሎች አንዱ ነው። ጳውሎስ ስለ የሱስ ተልዕኮ በአስደናቂ የቃላት አጠቃቀም ይናገራል። እዚህ ጋ ብዙ ሥነ መለኮታዊ ሀሳብ አለ። ይህ በአንድ ጥቅስ ውስጥ ብቻ ያለ የመዳን ታሪክ ነው።

ይበልጥ አስደናቂ የሚሆነው ደግሞ ይህ ታሪክ በገንዘብ ቋንቋ መነገሩ ነው። አዎ፣ የሱስ ባለጠጋ ነበር። ባለጠጋነቱ የሚያመለክተው ከፍጥረት በፊት በሰማይ የነበረውን የጥንት ህልውናውን ነው (ዮሐንስ 17:5)። እርሱ ግን ሰማያዊ ክብሩን በመተውና ወደዚህ በሀዘን የተሞላ ዓለም በመምጣት ድሃ ለመሆን ወሰነ። በተግባርም ድሃ ሆነ (ሉቃስ 9:58)። ምንም እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ቢሆንም፣ “የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ” (ፊልጵስዩስ 2:7)። “በሰውም አምሳል ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም ለመስቀል ሞት የታዘዘ ሆነ” (ፊልጵስዩስ 2:8)።

ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንኖር ዘንድ የሱስ የራሱን ህይወት አሳልፎ ሰጠ። ይህ መስዋዕትነት ዓላማ አለው፡– ያም መዳናችን ነው። መጋቢነትና ተልዕኮ አብረው የሚሄዱ ናቸው። 2ኛ ቆሮንቶስ 8–9 የአንድ የተለየ የገንዘብ ስጦታ ታሪክ ይናገራል፣ ነገር ግን ታሪኩ ክርስቶስን መሠረት ያደረገ ነው። በዚህ ሳምንት የክርስቶስን ራስን መስጠት መሠረት ካደረጉ ሥጦታዎች ጋር የተያያዙ ሥነ መለኮታዊ መርሆችን እናያለን። በየሱስ መወለድ፣ ህይወት፣ ሞትና ትንሳኤ ላይ ጊዜ ውሰዱ። ይህ ሁሉ የተደረገው ከዚህ የጉስቁልና ኑሮ ባሻገር ያለ ተስፋ ይኖራችሁ ዘንድ እንደሆነ ስታረጋግጡ ምላሻችሁ ምን ይሆናል?

ጳጉሜ 2
Sep 7

መነሳሳት


2ኛ ቆሮንቶስ 8፡1፣ 5 እና 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡7፣ 9፣ 13፣ 15ን አንብቡ። የእነዚህ ክፍሎች ማዕከላዊ መልእክት ምንድን ነው?



የመስጠት ቋንቋ በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 8 እና 9 ውስጥ ተንሰራፍቶ ይገኛል፦ “የእግዚአብሔር ጸጋ... ተሰጥቶአል” (2ኛ ቆሮ. 8፡1)፤ “ራሳቸውን ሰጡ” (2ኛ ቆሮ. 8፡5)፤ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና... እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ” (2ኛ ቆሮ. 9፡7)፤ “ለድሆች ሰጠ” (2ኛ ቆሮ. 9፡9)፤ “ስለ ስጦታችሁ ልግስና... እግዚአብሔርን ያከብራሉ” (2ኛ ቆሮ. 9፡13)፤ “ስለማይነገር ስጦታው ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” (2ኛ ቆሮ. 9፡15)። ሁለቱ ምዕራፎች የሚጀምሩትም የሚጨርሱትም በመስጠት ቋንቋ ነው (2ኛ ቆሮ. 8፡1 እና 2ኛ ቆሮ. 9፡15)። እነዚህን ሁለት ምዕራፎች ስናነብ የመስጠትን ሐሳብ በአእምሮአችን መያዝ አለብን። ክፍሎቹ መባ ለመስጠት ቢያንስ አራት ዋና ዋና ምክንያቶችን ያቀርባሉ፦

ለእግዚአብሔር ጸጋ ያለን ምስጋና (2ኛ ቆሮ. 8፡1፤ 2ኛ ቆሮ. 9፡14፣ 15)፦ 2ኛ ቆሮንቶስ 8–9 የሚጀምረው “ስለ እግዚአብሔር ጸጋ” በመጥቀስ ነው (2ኛ ቆሮ. 8፡1)። በመቀጠልም ጳውሎስ “የጌታችንን የየሱስ ክርስቶስን ጸጋ አውቃችኋልና” ይላል (2ኛ ቆሮ. 8፡9)። እዚህ ጋ የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ጸጋ መባ ለመስጠት እንደ ቀዳሚ ምክንያት ቀርቧል። እግዚአብሔር ክርስቶስን በመስጠት ለእኛ ብዙ አድርጎልናል። እኛም በምላሹ ስጦታዎቻችንን ስናቀርብ፣ በሕይወታችን ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ዕውቅና እንሰጣለን። ልክ እንደ መስጠት ሐሳብ ሁሉ “ጸጋ” (charis) የሚለው ቃልም

በምዕራፍ 8–9 ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። ጳውሎስ በሕይወታችን ውስጥ ያለው የክርስቶስ ጸጋ ለሌሎች ወደሚተርፍ ጸጋና ወደ ምስጋና እንደሚመራ ለማሳየት ይህን ቃል በተለያዩ ትርጉሞች ይጠቀምበታል።

የየሱስን አርአያነት የመከተል ፍላጎት (2ኛ ቆሮ. 8፡9)፦ የሱስ ባለጠጋ ነበረ ነገር ግን ደሃ ሆነ (እነዚህ ቃላት እርሱ ከዘላለም የነበረውን አምላክነቱንና ከዚያም ወደ ሰውነቱ መምጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች መሆናቸውን ያስታውሱ)። ይህ ሊሆን የቻለበት አንድ መንገድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሁሉንም ነገር መስጠቱ ነው። እኛም እንዲሁ መባችንን በማካፈል ሌሎች ክርስቶስን እንዲያውቁ መንገድ እንከፍታለን።

የእግዚአብሔርን በረከቶች የማካፈል ፍላጎት (2ኛ ቆሮ. 9፡10፣ 11)፦ ለሌሎች የምንሰጠው በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ስለተቀበልን ብቻ ነው። ለጋሶች እንድንሆን እርሱ ባለጠጋ ያደርገናል።

እውነተኛ ፍቅር (2ኛ ቆሮ. 8፡8፣ 24)፦ መስጠት የእውነተኛና የቅን ፍቅር መፈተኛ ነው። ፍቅር በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ለመኖሩ ትልቁ ማስረጃ ነው። በአጭር አነጋገር፣ ፍቅራችሁን በተግባር (በገንዘባችሁ) ግለጡ ማለት ነው። ለጋስነታችሁ ምን ያህል ነው? ከመስቀሉ ብርሃን አንጻር፣ ልትሰጡ ከምትችሉት አንጻር የምትሰጡት ምን ያህል ነው?

ጳጉሜ 3
Sep 8

ማቀድ


2ኛ ቆሮንቶስ 9፡7ን አንብቡ። ይህ ክፍል መባ ስለ መስጠት ተግባር ምን ይላል?



እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን የወሰነው ዓለም በኃጢአት ከመውደቋ በፊት ነበር። ክርስቶስ ለእኛ ለመሞት መምጣቱ የጥንታዊ እቅድ አካል ነበር (ራእይ 13፡8)። እግዚአብሔር ነገሩ ድንገት አልሆነበትም፤ በየሱስ በኩል ራሱን ለመስጠት አስቀድሞ አቅዶ ነበር። በ2ኛ ቆሮንቶስ 8 እና 9 ውስጥ፣ እቅድ ማውጣት ከመስጠት ተግባር ጋር የተያያዘ መሠረታዊ ሥነ- መለኮታዊ መርህ ነው። ይህንንም ቢያንስ በሁለት መንገዶች ማየት ይቻላል፦

በመጀመሪያ፣ እቅድ ማውጣት አስቀድሞ መወሰንን ይጠይቃል። ጳውሎስ “እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ” ይላል (2ኛ ቆሮ. 9፡7)። “አሰበ” (ወሰነ) ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል proaireō የሚለው ግስ ነው። ይህ ውህድ ቃል ሲሆን፤ pro ማለት “አስቀድሞ” ማለት ሲሆን aireō ደግሞ በዚህ አውድ “መወሰን” ማለት ነው። ስለዚህ proaireō የሚያመለክተው አስቀድሞ የተደረገን ውሳኔ ነው። በተጨማሪም፣ ንግግሩን “እያንዳንዱ” ብሎ በመጀመር፣ ጳውሎስ የሚሰጠው መጠን ለሁሉም እኩል እንደማይሆን ይጠቁማል። የእርሱ ነጥብ ሰዎች ለመስጠት የሚወስኑት ምንም ይሁን ምን፣ በጥንቃቄ በማሰብ ሊያደርጉት ይገባል የሚል ነበር። ለእነርሱ ትክክለኛ ነው ብለው ያመኑትን መጠን መስጠት አለባቸው።

በሁለተኛ ደረጃ፣ እቅድ ማውጣት የምጥጥን (proportionality) መርህን ያካትታል። ጳውሎስ የመቄዶንያ ሰዎች “እንደ አቅማቸው” እንደሰጡ ይናገራል (2ኛ ቆሮ. 8፡ 3)። በመቀጠልም ይህንኑ የምጥጥን መርህ በቆሮንቶስ ሰዎች ላይ ይተገብረዋል። ቀደም ሲል የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ ሲያበረታታቸው፣ በእጃቸው ያለውን ሀብት ተጠቅመው ፕሮጀክቱን እንዲያጠናቅቁ ያሳስባቸዋል (2ኛ ቆሮ. 8፡11)። ይህንንም ሐሳብ ሲያጠቃልል “ሰው እንዳለው መጠን ቢሰጥ ተቀባይነት አለው እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም” ይላል (2ኛ ቆሮ. 8፡12)። መጽሐፍ ቅዱስ የአሥራት መጠንን (አሥር በመቶ) ቢገልጽም፣ ለመባ ግን ተመሳሳይ ነገር አይሠራም። “እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ” (2ኛ ቆሮ. 9፡7) የሚለው ቃል የምጥጥን መርህን በመተግበር የሚከናወን ነው። በሌላ አነጋገር፣ እያንዳንዱ ሰው ከገቢው ውስጥ ምን ያህሉን (ምን ያህል ፐርሰንት) መባ አድርጎ እንደሚሰጥ ራሱ ይወስናል። እያንዳንዱ ካለው አንጻር በመመጠን መስጠት ይጠበቅበታል። ይህ ደግሞ ያለ እቅድ ሊደረግ አይችልም። ባለጠጋም ሆናችሁ ድሃ፣ በአሥራትና በመባ ረገድ ምን ያህል የታመናችሁ ናችሁ? የበለጠ ማድረግ እንደምትችሉ እያወቃችሁ ከመስጠት ለመቆጠብ ምን ዓይነት ሰበቦችን ትጠቀማላችሁ?

ጳጉሜ 4
Sep 9

አመለካከት


2ኛ ቆሮንቶስ 8፡1–5ን አንብቡ። የመቄዶንያ ሰዎች መባቸውን እንዲህ ባለ ልግስና ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑት በምን ምክንያት ሊሆን ይችላል?



የመቄዶንያ ሰዎች የነበራቸው በጎ አመለካከት በበርካታ መንገዶች ሊታይ ይችላል፦

በመጀመሪያ፣ በታላቅ ደስታ ሰጥተዋል (2ኛ ቆሮ. 8፡2)። ጳውሎስ የመቄዶንያ ሰዎች “የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸው ባለጠግነት ሆኖ ተረፈ” ይላል (2ኛ ቆሮ. 8፡2)። ቆየት ብሎም “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል” በማለት ይጠቅሳል (2ኛ ቆሮ. 9፡7)። “ደስታ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው የሚገኘው። ከዚሁ የቃል ቤተሰብ የተገኘ ሌላ ቃል ደግሞ፦ “የሚምር በደስታ ይማር” በሚለው ክፍል ውስጥ ይገኛል (ሮሜ 12፡8)። እነዚህ ቃላት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ባሉ ጽሑፎች ውስጥም “ሐሴትና ደስታ” በሚል ትርጉም ይታያሉ። በ2ኛ ቆሮንቶስ 9፡7 መሠረት ደስተኛ ሰጪ መሆን ማለት ያለ ምንም ማቅማማት መስጠት ማለት ነው።

ሁለተኛ፣ በልግስና ሰጥተዋል (2ኛ ቆሮ. 8፡2)። ጳውሎስ ስለ መቄዶንያ ሰዎች ልግስና ከመጥቀሱ በፊት፣ መጀመሪያ ስለ “ጥልቅ ድህነታቸው” ተናግሮ ነበር (2ኛ ቆሮ. 8፡ 2)። “ልግስና” (haplotētos) የሚለው ቃል በ2ኛ ቆሮንቶስ 8 እና 9 ውስጥ ሁለት ጊዜ በተጨማሪ ተጠቅሷል። ጳውሎስ “ለልግስና ሁሉ በሁሉ ባለጠጎች ትሆናላችሁ” ይላል (2ኛ ቆሮ. 9፡11፤ አጽንኦት የተጨመረበት)፤ ይህም ማለት የምንቀበለው እኛም መልሰን እንድንሰጥ ነው ማለት ነው። ጥቂት ዝቅ ብሎም “ስለ ስጦታችሁ ልግስና” በማለት ይጠቅሳል (2ኛ ቆሮ. 9፡13፤ አጽንኦት የተጨመረበት)። በዚህ ክፍል መሠረት በመስጠት ረገድ ለጋስ መሆን የክርስቶስን ወንጌል የመመስከሪያ (የመናገሪያ) መንገድ ነው።

ሦስተኛ፣ “በገዛ ፈቃዳቸው” ሰጥተዋል (2ኛ ቆሮ. 8፡3)። ይህ ማለት በፈቃደኝነት ሰጥተዋል ማለት ነው። ያላቸው ሀብት እጅግ ውስን ሆኖ ሳለ፣ ካላቸው ትርፍ ሳይሆን ካላቸው ጥቂት ነገር መስጠታቸው ነገሩን ይበልጥ የሚያስደንቅ ያደርገዋል። ጳውሎስ ቲቶ የቆሮንቶስን ሰዎች ለመጎብኘት ያለውን ፈቃደኝነት ለመግለጽም ይህንኑ ሐሳብ ተጠቅሟል፤ እርሱ ወደ ቆሮንቶስ የሄደው በገዛ ፈቃዱ ነበር (2ኛ ቆሮ. 8፡17)።

አራተኛ፣ መስጠትን እንደ ልዩ መብት በመቁጠር ሰጥተዋል (2ኛ ቆሮ. 8፡4)። ይህ አመለካከት የመቄዶንያ ሰዎች መባውን በማሰባሰቡ ሥራ ለመካፈል ባቀረቡት ልመና ውስጥ ይታያል። “ይህንም ቸርነት ቅዱሳንንም በማገልገል መካፈልን በብዙ ልመና አጥብቀው ለመኑን” (2ኛ ቆሮ. 8፡4)።

በመጨረሻም፣ በመባው የተሳተፉት ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ በመቀደስ (በመስጠት)

ተግባር ነበር (2ኛ ቆሮ. 8፡5)። ጳውሎስ “አስቀድመው ራሳቸውን ለጌታ በኋላም በእግዚአብሔር ፈቃድ ለእኛ ሰጡ” ይላል (2ኛ ቆሮ. 8፡5)። ራስን ለጌታ መስጠት ራስን ለሌሎች ወደ መስጠት ይመራል። የመቄዶንያ ሰዎች በተልዕኮ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከገንዘብ እርዳታ ባለፈ ሰፍቶ ነበር። ይህም ማለት መስጠትና ለጋስ መሆን በገንዘብ ብቻ የተገደበ አይደለም።

ጳጉሜ 5
Sep 10

አንድነት


ጳውሎስ በቆሮንቶስ ያሉ አባላት በይሁዳ ለሚገኙ ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት የሚሆን መባ በማሰባሰቡ ሥራ እንዲሳተፉ ሲያበረታታቸው እናያለን። ከዓላማዎቹ አንዱ የአንድነት ስሜትን መቀስቀስ ነበር። እነርሱም በዚህ ተልዕኮ ውስጥ ተሳታፊና አካል እንዲሆኑ ይፈልጋል። አሕዛብ የሆኑት አብያተ ክርስቲያናት በኢየሩሳሌም ካሉት አይሁዳውያን አማኞች ጋር የአንድ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል መሆናቸውን ለማሳየት ይሻል። ይህም ማለት ቀደም ሲል ተቃዋሚዎቻቸው የነበሩት እነዚህ ሰዎች፣ አሁን በእግዚአብሔር አዲስ ኪዳን ቅሬታዎች ውስጥ አብረዋቸው አባላት መሆናቸውን ነው የሚያሳየው። ጳውሎስ መላው የክርስቲያን ቤተሰብ—አይሁድም አሕዛብም—ለሚመጡት ትውልዶች ምስክር ሊሆን በሚችል በኃይለኛ መንገድ ተባብሮ ማየት ይፈልጋል።

ቲቶና ሌሎች ሁለት የተመሰከረላቸው ወንድሞች የገንዘቡ ኃላፊዎች ነበሩ። እግዚአብሔር ይህንን ለቤተ ክርስቲያን የማሰብ ሐሳብ በቲቶ ልብ ውስጥ አኖረው (2ኛ ቆሮ. 8:16)። በአብያተ ክርስቲያናት በኩልም እግዚአብሔር ሌሎቹን ሁለት ወንድሞች መረጠ (2ኛ ቆሮ. 8:18–23)። እነርሱም “የአብያተ ክርስቲያናት መልክተኞችና የክርስቶስ ክብር” ተብለው ተጠርተዋል (2ኛ ቆሮ. 8:23)። “የክርስቶስ ክብር” የሚለው አገላለጽ የሚገልጸው እነዚህን ሁለት ታማኝ ወንድሞች ይሁን ወይም አብያተ ክርስቲያናቱን ራሳቸውን፣ ያን ያህል ልዩነት የለውም። መባ መስጠት በመጨረሻ የቤተ ክርስቲያን ራስ ለሆነው ለክርስቶስ ያለንን ታማኝነት ማሳያ ነው (ኤፌ. 4:15)።

2ኛ ቆሮንቶስ 8–9 መባ መሰጠት ያለበት በእግዚአብሔር በኩል በቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ለተሾሙ ሰዎች መሆኑን ይጠቁማል። “አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ” (2ኛ ቆሮ. 8:18)፣ “በአብያተ ክርስቲያናት የተመረጠ” (2ኛ ቆሮ. 8:19)፣ እና “የአብያተ ክርስቲያናት መልክተኞች” (2ኛ ቆሮ. 8:23) የሚሉት ሐረጎች በትክክል ይህንኑ ያመለክታሉ። ስለዚህ፦ “የፍቅራችሁን ማስረጃ... በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ግለጡላቸው” የሚለው ማሳሰቢያ የሚጠበቅ ነው (2ኛ ቆሮ. 8:24)።

መባን ወደ ቤተ ክርስቲያን—በምድር ላይ ወደ ተሾመው የእግዚአብሔር አገልጋይ— ማምጣት አንድነትን ያበረታታል፤ በተመሳሳይ ጊዜም የአንድነት ስሜት ውጤት ነው (2ኛ ቆሮ. 8:13, 14)። ገንዘብ ታላቅ አንድነት ፈጣሪ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሰዎች ዓይን ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ ካልሆነ (single eye)፣ ገንዘብ መከፋፈልን ሊፈጥር ይችላል። ሮሜ 15:26, 27 ጳውሎስ እዚህ ጋ ያለውን የአንድነት ፍላጎት እንዴት ይገልጻል?



በመጨረሻም ጳውሎስ መባ ማሰባሰቡን እንደ አገልግሎት፣ እንደ ጸጋ ተግባር፣ እንደ በረከት፣ እንደ አምልኮ እና እንደ ኅብረት ይገልጸዋል። ይህ ሁሉ ከአንድ መባ? እስቲ አስቡበት። ለአብያተ ክርስቲያናት ወንድሞቻችሁና በባሕር ማዶ (ብዙውን ጊዜ በጣም ርቀው በሚገኙ ስፍራዎች) ላሉ ሚሲዮኖች የምትሰጡት ስጦታ፣ ለዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያናችሁ አንድነትን ለማምጣት የሚረዳው እንዴት ነው?

መስከረም 1
Sep 11

, 2019

ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ ኋይት፣ A Liberal Church፣ ገጽ 335–345፣ በ The Acts of the Apostles።

“ልባቸው በክርስቶስ ፍቅር የተሞላ ሰዎች፣ እኛ በእርሱ ድህነት ባለጠጎች እንሆን ዘንድ ስለ እኛ ድሃ የሆነውን የእርሱን አርአያ ይከተላሉ። ገንዘብን፣ ጊዜን፣ ተፅዕኖን— ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበሏቸውን ስጦታዎች ሁሉ—ዋጋ የሚሰጧቸው የወንጌልን ሥራ ለማስፋፋት እንደ መሣሪያ እስከተጠቀሙባቸው ድረስ ብቻ ነው። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የነበረው ሁኔታ እንዲህ ነበር፤ በዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያንም አባላት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ፍቅራቸውን ከዚህ ዓለም ነገር ሲያርቁ፣ እንዲሁም ባልንጀሮቻቸው ወንጌልን ይሰሙ ዘንድ መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ሲሆኑ ሲታይ፣ የሚሰበኩት እውነቶች በሰሚዎቹ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ገጽ 71።

“ጌታ የእኛ መባ አያስፈልገውም። በስጦታዎቻችን እርሱን ባለጠጋ ልናደርገው አንችልም። መዝሙረኛው እንዲህ ይላል፦ “ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፣ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃል”። ሆኖም እግዚአብሔር ለእኛ ያሳየውን ምሕረት ለሌሎች ለማዳረስ በምናደርገው መሥዋዕትነት በሚጠይቅ ጥረት፣ ለእርሱ ያለንን አድናቆት እንድንገልጽ ይፈቅድልናል። ለእግዚአብሔር ያለንን ምስጋናና ፍቅር ልንገልጽበት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ይህ ነው። እርሱ ከዚህ ውጭ ሌላ መንገድ አላዘጋጀም።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ በመጋቢነት ላይ የሚሰጡ ምክሮች (Counsels on Stewardship)፣ ገጽ 18፣ 19።

“እግዚአብሔር ለሰው የሰጠው ስጦታ ምንኛ ታላቅ ነው! እንዲህ ያለውን ስጦታ መስጠትም ለአምላካችን ምንኛ የሚስማማው ነው! ዓመፀኛ የሆኑ የሰው ልጆችን ለማዳን፣ ዓላማውን እንዲያዩና ፍቅሩን እንዲረዱ ለማድረግ፣ ሊታለፍ በማይችል ልግስና ሰጠ። ታዲያ እናንተስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ አንድያ ልጁን ለሰጠው” ለእርሱ፣ ምንም ነገር እንደማይበዛበት በስጦታችሁና በመባችሁ ታሳያላችሁን?” — ኤለን ጂ ኋይት፣ አድቬንት ሪቪው ኤንድ ሰንበት ሄራልድ (Advent Review and Sabbath Herald)፣ ግንቦት 7፣ 1892 (May 15, 1900)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በ2ኛ ቆሮንቶስ 8፡9 ላይ በጥልቀት አሰላስሉ። ከመጋቢነት (steward- ship) አንጻር የየሱስ አርአያነት እንዲህ ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?

2. ዮሐንስ 3:16 የሰማይ ቋንቋ የመስጠት ቋንቋ መሆኑን ይጠቁማል። ዮሐንስ 15:13፤ ኤፌሶን 5:2፣ 25፤ ገላትያ 2:19፣ 20 እና 1ኛ ዮሐንስ 3:16ን አንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ከዮሐንስ 3:16 ጋር ምን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ? ከእነርሱስ ምን መልእክት ልንወስድ እንችላለን?

3. በ2ኛ ቆሮንቶስ 8–9 ላይ ባነበባችሁት መሠረት፣ መስጠት ለግለሰብ የሚያስገኘው ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

4. ሥርዓታዊ (መደበኛ) መባ ከመስጠት በተጨማሪ፣ የየሱስን ራስን የመስጠት አርአያነት ለመከተል ሌላ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL