የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

1ኛ እና 2ኛ ቆሮንቶስ - የክርስቲያን ሕይወት እና ምስክርነት ባሕርይ



3ኛ ሩብ ዓመት 2026


መስከረም 2 - 8

12ኛ ትምህርት

Sep 12 - 18




ከሐሰተኞች አስተማሪዎች ጋር መጋፈጥ



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት እነዚህን ክፍሎች አንብቡ፦ 2ኛ ቆሮ. 10:1–17፤ ኤር. 9:24፤ 2ኛ ቆሮ. 11:1–15፣ 22–28፤ 2ኛ ቆሮ. 12:20፣ 21፤ 2ኛ ቆሮ. 13:5።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ «የጦር መሣሪያችን የሥጋ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው» (2ኛ ቆሮንቶስ 10:4)።

ጳውሎስ ያሉበት ችግሮች ሳይበቁት፣ ሊጋፈጠው የሚገባ ሌላ አዲስ ፈተና ተከሰተ፦ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተነሱ ሐሰተኞች መምህራን። እነዚህ ሰዎች እርሱን፣ ሥራውንና አገልግሎቱን ይቃወሙ ነበር። ይባስ ብሎ ደግሞ፣ እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን የቆሮንቶስን አባላት ጭምር አሳስተው ነበር። ጳውሎስ ከዚህ ችግር ጋር የሚያደርገውን ትግል እንደ መንፈሳዊ ጦርነት ይቆጥረዋል።

ይህ አገላለጽ ማጋነን ይሆን? በፍጹም። ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች በመጨረሻ እየተቃወሙ ያሉት እርሱን ሳይሆን ክርስቶስን ራሱን መሆኑን ያውቅ ነበር። እርሱ በበታቾቹ ላይ ያለውን ሥልጣንና የበላይነት ለማረጋገጥ ሲል ዝናውን ለመጠበቅ የሚጨነቅ ዓይነት ለራሱ ብቻ የሚኖር (narcissistic) መሪ አልነበረም። እንዲሰብክ የተላከው መልእክት የዘላለም ውጤት ያለው፣ የሞትና የሕይወት ጉዳይ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ይህንንም እንዲያደርግ በራሱ በእግዚአብሔር እንደተላከ ያውቃል፦ “በእግዚአብሔር ፈቃድ የየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ ጳውሎስ” (1ኛ ቆሮ. 1:1)።

ከሐሰት ትምህርቶች ጋር በተያያዘ፣ ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ላይ ተመስርታ በፍቅር ግን ደግሞ በጽናት እርምጃ መውሰድ ይኖርባታል። ለነፍሳት የዘላለምን ተስፋ ለመስጠት ሲባል የወንጌል መልእክት ሳይበረዝ፣ ሳይበላሽና በንጽሕናው ተጠብቆ ሊቆይ ይገባል። *ለመስከረም 9 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።

መስከረም 3
Sep 13

መንፈሳዊ ጦርነት


2ኛ ቆሮንቶስ 10፡1–11ን አንብቡ። ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ያሳየው የነበረው የዋህነት አንዳንድ ጊዜ ከደካማነት ጋር ይደባለቅ ነበር። በዚህ ክፍል ውስጥ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ያሉትን የሐሰተኛ መምህራን ችግር ለመጋፈጥ ያለውን ድፍረት የሚገልጡት ቃላት ወይም ሐረጎች የትኞቹ ናቸው?



ጳውሎስ 2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 10ን በግል አነጋገር ይጀምራል፦ “እኔ ጳውሎስ... እመክራችኋለሁ” (2ኛ ቆሮ. 10:1)። ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰርገው ስለገቡት የሐሰት ትምህርቶች ጳውሎስ ምን ያህል ተጨንቆ እንደነበር ያሳያል። በ2ኛ ቆሮንቶስ 10:1 ላይ ያሉት ቃላቱ፣ ተቃዋሚዎቹ “በደብዳቤው ከሩቅ ሲሆን የሚያስፈራራ ጉልበተኛ ነው፤ ፊት ለፊት ሲሆን ግን ምስኪን ፈሪ ነው” በማለት ለሚያቀርቡበት ክስ በቅኔ (ironically) የሰጡት ምላሽ ናቸው (2ኛ ቆሮ. 10:10, 11)። እርሱም ደካማነት መስሎ የታየው ነገር እንደ ብርቱ የዋህነትና እንደ ክርስቶስ ያለ ገርነት ሊታይ እንደሚገባው ይመልሳል።

ሐሰተኞች መምህራን በድፍረትና በመተማመን ሊገጥሟቸው ይገባል (2ኛ ቆሮ. 10:2)፤ ነገር ግን ይህ ከክርስቶስ ገርነት ጋር የተቀላቀለ መሆን አለበት (2ኛ ቆሮ. 10:1)። የሱስ በአንድ ወቅት “እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝ” ብሎ ነበር (ማቴ. 11:29)። ሆኖም የሱስ በመቅደስ የነበሩትን ለዋጮች ጠረጴዛ በመገልበጥና “ወንበዴዎች” ብሎ በመጥራት በድፍረት ተጋፍጧቸዋል (ማቴ. 21:12, 13)። ፈሪሳውያንንም ፊት ለፊት “ግብዞች” እና “በኖራ የተመረጉ መቃብሮች” ብሏቸዋል (ማቴ. 23:23–27)። እንደ የሱስ ሁሉ ጳውሎስም ሙሉውን የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ መጠቀምን የሚጠይቅ መንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ እንዳለን ያውቃል (ኤፌ. 6:12–17)።

የሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ በመሆኑ ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 10 ላይ የተጠቀመው ቋንቋ ወታደራዊ ነው (2ኛ ቆሮ. 10:3–6)። ይህ ተራ የሰው ግጭት ሳይሆን ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለመማረክ የሚደረግ መለኮታዊ ውጊያ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ማንኛውም የሐሰት ክርክርና ከፍ ያለ ሐሳብ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመስርቶ ሊመረመርና ሊፈርስ ይገባል፤ ይህም “አእምሮን ሁሉ ለክርስቶስ እንዲታዘዝ” ለመማረክ ነው (2ኛ ቆሮ. 10:5)።

በዚህ መንፈሳዊ ተጋድሎ ውስጥ ጳውሎስ በክርስቶስ ሥልጣን ይንቀሳቀሳል። ሆኖም ይህ ሥልጣን ዓላማው ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለም (2ኛ ቆሮ. 10:8)። መንፈሳዊ መሪዎች በእግዚአብሔር ሥልጣን እየሠራን ነው ብለው ማረጋገጥ ቀላል ሊሆንላቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ሥልጣናቸው በክርስቶስ የተሰጠ መሆኑን ማስታወስ አለባቸው፤ እንደ እርሱም በልባቸው የዋህና ትሑት መሆን ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ በክርስቶስ የተሰጠውን ሥልጣን አጥብቆ የገለጸው፣ የቆሮንቶስ ሰዎች የተሳሳቱ ሰዎችን እየሰሙ ለክርስቶስ ያላቸውን ታማኝነት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ካለው ስጋት የተነሣ ነው። ከሐሰተኞች መምህራን ጋር በምንጋፈጥበት ጊዜ እንዴት በተመሳሳይ ጊዜ ገሮችና ደፋሮች መሆን እንችላለን? ሁለቱንም መሆን ለምን አስፈለገን?

መስከረም 4
Sep 14

በጌታ መመካት


ትላንት ጳውሎስና የሥራ ባልደረቦቹ አገልግሎታቸውን እንደ መንፈሳዊ ውጊያ እንዲሁም የእግዚአብሔርን የጦር መሣሪያ በመጠቀም እንዴት እንዳከናወኑ አይተናል። ዛሬ ደግሞ ሐሰተኞች መምህራን በሰዋዊ መመዘኛዎች እንደሚንቀሳቀሱ እናያለን። እነርሱ አግባብ ባልሆነ መንገድ ይመካሉ። በአንጻሩ ጳውሎስ የሚመካው በጌታ ብቻ ነው። እርሱም፦ “የሚመካ ግን በጌታ ይመካ” በማለት ጽፏል (2ኛ ቆሮ. 10፡17)። 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡13–17ን አንብቡ። የፉክክር መንፈስ የወንጌልን ስብከት እንዴት ሊጎዳ ይችላል?



ጳውሎስ የመመካት ቋንቋን መጠቀሙ ለዘመናት ተርጓሚዎችን ሲያስገርም ቆይቷል። ሆኖም በጥንቱ ዓለም ራስን ማሞገስ ወይም መመካት የተለመደ ተግባር ሲሆን፣ ሰሚውን እንዳያስቀይም ግን በማኅበራዊ ሥርዓቶች የተገደበ ነበር። ጳውሎስ እነዚህን ሥርዓቶች ያውቅና ይከተል ነበር። በተጨማሪም፣ የእርሱ የመመኪያ መንገድ ከሐሰተኞች መምህራን የተለየ መሆኑን ግልጽ ያደርጋል። እርሱ የሚመካው በጌታ ነው (2ኛ ቆሮ. 10፡17)። ይህም ከብሉይ ኪዳን የተወሰደ ጥቅስ ነው፦ “ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ” (ኤር. 9፡24)። ጳውሎስ ይህንን የኤርምያስን ክፍል በመጥቀስ፣ ትኩረቱ በክርስቶስ ላይ— በክርስቶስ ፍቅር፣ ፍርድና ጽድቅ ላይ መሆኑን ያሳያል።

በሌላ አነጋገር፣ የጳውሎስ ትምክህት በክርስቶስ በኩል በተከናወኑት የእግዚአብሔር ሥራዎች ላይ ያተኮረ ነው። ስለዚህ የእርሱ መመካት መጽሐፍ ቅዱሳዊ በመሆኑ ቅር የሚያሰኝ አይደለም። በአንጻሩ ተቃዋሚዎቹ ራሳቸውን እርስ በርስ በማነጻጸር በፉክክር መንፈስ ውስጥ ገብተው ነበር። ይህ ደግሞ ስንፍና ነው! (2ኛ ቆሮ. 10፡12)።

በ2ኛ ቆሮንቶስ 10፡14–16 ላይ ጳውሎስ በቆሮንቶስም ሆነ ከቆሮንቶስ ወዲያ ባሉ አካባቢዎች የአገልግሎቱ ቀዳሚ ትኩረት ወንጌልን መስበክ እንደሆነ ይጠቁማል። ጳውሎስ ለየሱስ ያለው ፍቅር፣ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ስለሚገኘው የምስራች ዘወትር እንዲናገር አድርጎታል።

ራሳቸውን እንደሚያመሰግኑት በቆሮንቶስ እንዳሉ ሐሰተኞች መምህራን ሳይሆን፣ ጳውሎስ በእግዚአብሔር የተመሰገነና የተፈተነ (የተመረጠ) ነበር (2ኛ ቆሮ. 10፡12፣ 18)። እርሱ “በእግዚአብሔር ፈቃድ የየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ” ነበር (1ኛ ቆሮ. 1:1)። እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ለዚህ ጥሪ ታማኝ ሆኖ ቆይቷል (2ኛ ጢሞ. 4፡7)። 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡12–18ን ደግማችሁ አንብቡ። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወይም አባላት የፉክክር መንፈስን እንዴት ሊያስወግዱ ይችላሉ? በእርግጥም ዋጋ በሌላቸው (በማይረቡ) ነገሮች ውስጥ መዘፈቅ ለምን እንዲህ ቀላል ይሆናል?

መስከረም 5
Sep 15

የሐሰተኞች መምህራን ማንነት መጋለጥ


አዲስ ኪዳን በክርስቲያን ማኅበረሰቦች ውስጥ ስለሚነሱ ሐሰተኞች መምህራን በርካታ ማስጠንቀቂያዎችን ይዟል። የሱስ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ አስጠንቅቋል (ማቴ. 7፡15–20)። ሐዋርያትም ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል (ገላ. 1፡6–9፤ 1ኛ ጢሞ. 6፡3–5፤ 2ኛ ጴጥ. 2፡1–3)። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡1–15ን አንብቡ። ጳውሎስ ከእነዚህ ሐሰተኞች መምህራን ጋር እያጋጠሙት ያሉትን ፈተናዎች እንዴት ይገልጻቸዋል?



ጳውሎስ የሐሰተኞች መምህራንን ሥራ ያጋልጣል። በተመሳሳይ ጊዜ፣ የእርሱ አገልግሎት በክርስቶስ ላይ ያተኮረ መሆኑን ይጠቁማል። በቆሮንቶስ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ከሙሽራ ጋር ያነጻጽራታል፤ ራሱንም ለክርስቶስ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለበት እንደ አባት አድርጎ ይቆጥራል (2ኛ ቆሮ. 11፡2)። ይህን የሚያደርገው ቤተ ክርስቲያንን ስለሚወድ ነው (2ኛ ቆሮ. 11፡11)። ስለዚህ፣ በቤተ ክርስቲያን የመርዳት መብት ቢኖረውም፣ ለእነርሱ የገንዘብ ሸክም ላለመሆን ጭምር ፈቃደኛ ነበር (2ኛ ቆሮ. 11፡7–12)።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ከሁሉ የሚበልጡ ሐዋርያት” (ይህ ምናልባት በቅኔ ሐሰተኞቹን መምህራን ማመልከቱ ሊሆን ይችላል) ሔዋንን ካታለላት እባብ ጋር ተነጻጽረዋል (2ኛ ቆሮ. 11፡3)። በኤደን ገነት እንደነበረው ሰይጣን ሁሉ፣ በቆሮንቶስ ያሉት ሐሰተኞች መምህራንም በተንኮልና በብልሽት ይታወቃሉ (2ኛ ቆሮ. 11፡3፣ 4)። የጳውሎስ ዋና ስጋት የቆሮንቶስ ሰዎችን ከቅንነታቸውና ለክርስቶስ ካላቸው ታማኝነት ሊያርቋቸው ይችላሉ የሚል ነበር።

እነዚህ ሰርገው የገቡ ሰዎች ጳውሎስ ከሰበከው የተለየ መልእክት—የተለየ የሱስንና የተለየ ወንጌልን ይሰብኩ ነበር (2ኛ ቆሮ. 11፡4)። ይህም ስለ የሱስ የሚሰብክ ሁሉ በእግዚአብሔር የተላከ መሣሪያ አለመሆኑን ያሳያል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሱስ ራሱ፦ ““በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም”” ብሏል (ማቴ. 7፡21)። በገላትያ 1፡6–9 ላይ ጳውሎስ ሌላ ወንጌል የሚሰብክ ሁሉ በራሱ ላይ እርግማን ያመጣል ይላል፤ ነገር ግን በቆሮንቶስ ያሉ አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱን ስሕተት ይታገሱ ነበር።

ጳውሎስ ሐሰተኞቹን ሐዋርያት “የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን የሚለውጡ፥ ተንኰለኞች ሠራተኞች ናቸው” በማለት ያጋልጣቸዋል (2ኛ ቆሮ. 11፡13)። “ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና”፣ እንዲሁም “የእርሱ [የሰይጣን] አገልጋዮች ደግሞ የጽድቅ አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ” እንግዳ ነገር አይደለም ይላል (2ኛ ቆሮ. 11፡14፣ 15)። ምንኛ የሚያሳዝን ሁኔታ ነው፦ የክርስቶስ አገልጋዮች ነን የሚሉ ሰዎች የሰይጣን ወኪሎች ሆነው ሲሠሩ። ጳውሎስ ሐሳቡን ሲያጠቃልል “ፍጻሜአቸው እንደ ሥራቸው ይሆናል” ይላል (2ኛ ቆሮ. 11፡15)። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላለው ስሕተት ምን ያህል በጽኑ ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ ተመልከቱ! ይህ ለእኛስ ምን ሊነግረን ይገባል?

መስከረም 6
Sep 16

ስለ ወንጌል መከራ መቀበል


ሐሰተኞች መምህራን የሰይጣን ወኪሎች መሆናቸውን ካጋለጠ በኋላ (2ኛ ቆሮ. 11:1– 15)፤ ጳውሎስ አሁን የቆሮንቶስ ሰዎች የሐሰተኞች መምህራንን ንግግር መስማት ምን ያህል ትርጉም የለሽ እንደሆነ ይረዱ ዘንድ፣ እንደ ሰነፍ በመሆን ጥቂት በመመካት የእነርሱን “ጨዋታ ይጫወታል” (2ኛ ቆሮ. 11:16–21)። የቆሮንቶስ ሰዎች ለእነዚያ ከፍተኛ ክብር የሚሰጡ ከሆነ፣ ጳውሎስ ደግሞ የበለጠ ሊከበር ይገባው ነበር። ስለ ወንጌል የተቀበለው መከራ እርሱ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ መሆኑን ያሳያል (2ኛ ቆሮ. 11:22, 23)። 2ኛ ቆሮንቶስ 11:22–28ን አንብቡ። ጳውሎስ እዚህ ጋ ምን ነጥብ ለማንሳት እየሞከረ ነው?



ምንም እንኳ የጳውሎስ አይሁዳዊ ማንነት (credentials) ከሐሰተኞች መምህራን ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም (2ኛ ቆሮ. 11:22)፤ ለክርስቶስ የሚያቀርበው አገልግሎት ግን ከእነርሱ በእጅጉ ይበልጣል (2ኛ ቆሮ. 11:23)። “የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን?” ሲል ይጠይቃል። መልሱም “እኔ እበልጣለሁ” የሚል ነው። ድካሙ የበለጠ የበዛ፣ እስራቱ የበዛ፣ ግርፋቱም እጅግ የበረታ ነበር።

ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም። የመከራዎቹ ዝርዝር አምስት ጊዜ የደረሰበትን የሠላሳ ዘጠኝ ግርፋት (2ኛ ቆሮ. 11:24)፣ በበትር መመታትን፣ በድንጋይ መወገርን፣ የመርከብ መሰበርን፣ በጥልቅ ባሕር ውስጥ የገጠመውን አደጋ ያካትታል (2ኛ ቆሮ. 11:25)። እንዲሁም በመንገድ ላይ የነበረ አደጋ፣ የወንዝ አደጋ፣ የወንበዴዎች አደጋ፣ ከወገኖቹ (ከአይሁድ) የደረሰበት አደጋ፣ ከአሕዛብ የደረሰበት አደጋ፣ በከተማ የነበረ አደጋ፣ በምድረ በዳ የነበረ አደጋ፣ በባሕር ላይ የነበረ አደጋ፣ በሐሰተኞች ወንድሞች መካከል የነበረ አደጋ (2ኛ ቆሮ. 11:26)፣ የድካምና የጥረት ብዛት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ረሃብ፣ ጥማት፣ እጦት፣ ቅዝቃዜና እራቁትነት ይገኙበታል (2ኛ ቆሮ. 11:27)። ይህ ሁሉ ሳይበቃ ደግሞ፣ ስለ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከሚሰማው ጥልቅ ጭንቀት የተነሣ በአእምሮው የሚሰማው ሥቃይ ነበረ (2ኛ ቆሮ. 11:28)።

እውነተኛ የክርስቶስ አገልጋይ ብቻ ነው ስለ ወንጌል ሲል እንዲህ ያለውን መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ የሚሆነው። ጳውሎስ በእርግጥ ስለ መከራው መመካት ቢፈልግ ኖሮ የሚናገረው ብዙ ነገር ነበረው። ሆኖም፣ የሚቀጥለው የደብዳቤው ክፍል እንደሚያሳየው የመመካቱ ምክንያት እርሱ ለክርስቶስ ባደረገው ላይ ሳይሆን፣ ክርስቶስ ለእርሱ ባደረገለት ነገር ላይ የተመሰረተ ነው። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ኃይል በሰው ድካም ውስጥ ይበልጥ በግልጽ እንደሚታይ ያውቅ ነበር (2ኛ ቆሮ. 12:9, 10)። እግዚአብሔር በሥጋው ውስጥ የሚወጋውን “እሾህ” በመስጠት (2ኛ ቆሮ. 12:7) ጳውሎስ በራሱ ስኬቶች እንዳይመካ ጠብቆታል። ይህም ትሑት እንዲሆን፣ ድካሙን እንዲረዳ፣ በመለኮታዊ ኃይል ላይ እንዲደገፍ፣ እና የእግዚአብሔርን ጸጋና ምሕረት አብዝቶ በሚቀበልበት ሁኔታ ውስጥ እንዲቆይ አድርጎታል። እናንተስ ስለ ወንጌል መከራ ተቀብላችሁ ታውቃላችሁ? ከዚህ ልምምድስ ምን ተማራችሁ? ጳውሎስ መከራዎቹን የገጠመበት መንገድ የእናንተን መከራዎች ለመጋፈጥ እንዴት ሊረዳችሁ ይችላል?

መስከረም 7
Sep 17

ንስሐ ላልገቡት የቀረበ ጥሪ


በ2ኛ ቆሮንቶስ 12፡14–13፡10 ውስጥ ጳውሎስ ስለ ሦስተኛው ጉብኝቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያሳውቃል (2ኛ ቆሮ. 12፡14፤ 2ኛ ቆሮ. 13፡1)። እርሱ ከማንኛውም ሐሰተኛ ሐዋርያ እንደማያንስ አሳይቷል፤ አሁንም በድጋሚ ወደ ቆሮንቶስ መጥቶ ንስሐ ያልገቡ አባላትን ለመመለስ (ለመጠገን) በራስ መተማመን አለው። እንዲያውም የዚህ ጉብኝቱ አንዱና ዋና ዓላማው ይህ ነበር። ጳውሎስ ያደረገውና የተናገረው ነገር ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ የታለመ ነበር (2ኛ ቆሮ. 12፡19)። 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡20፣ 21ን አንብቡ። የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሁኔታ አደጋ ላይ ጥለው የነበሩት ኃጢአቶች የትኞቹ ነበሩ?



በ2ኛ ቆሮንቶስ 12፡20፣ 21 ላይ የተዘረዘሩት ኃጢአቶች በሌሎች የጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ ከሚገኙት ጋር ተመሳሳይ ናቸው (ሮሜ 1፡29–31፤ ገላ. 5፡19–21)። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ነጥቦች በ1ኛ ቆሮንቶስ 3፡3 ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በዚያም ጳውሎስ በቆሮንቶስ አባላት መካከል ስላለው ቅናትና ክርክር ይጠቅሳል። ጳውሎስ በሦስተኛው ጉብኝቱ ወቅት ነገሮች ብዙም ሳይለወጡ እንዳይጠብቁት ይሰጋል። “ስመጣ እንደምወደው ባላገኛችሁ... ብዬ እፈራለሁና” ይላል። በተቃራኒው ደግሞ “እኔም እንደማትወዱት ሆኜ እንዳታገኙኝ [እፈራለሁ]” ይላል (2ኛ ቆሮ. 12፡20)። ይህ ማለት በእነርሱ ላይ “በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት” ከመንቀሳቀስ ይልቅ (2ኛ ቆሮ. 10፡1)፣ አሁን “አለመታዘዝን ሁሉ ለመቅጣት የተዘጋጀሁ” እሆናለሁ ማለቱ ነው (2ኛ ቆሮ. 10፡6)።

ዋናው ስጋቱ “በርኩሰትና በዝሙት በሴሰኝነትም” ውስጥ የነበሩት እነዚያ አባላት ንስሐ ሳይገቡ ቀርተው ይሆናል የሚል ነው (2ኛ ቆሮ. 12፡21)። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈልን የሚፈጥሩት ደግሞ እንዲህ ያሉ ኃጢአቶች ናቸው።

በመቀጠልም ጳውሎስ በኃጢአት ያሉትን ለመመለስ በቤተ ክርስቲያን ሥነ-ሥርዓት (discipline) ሚና ላይ ያተኩራል (2ኛ ቆሮ. 13፡1–4)። ድካም ለኃጢአተኛ የሕይወት መንገድ ሰበብ ሊሆን አይችልም። ድል የነሣ ሕይወት ለሚፈልጉ የሚሆን ኃይል አለ (2ኛ ቆሮ. 13፡4)። በቆሮንቶስ ያሉ አንዳንዶች የፆታ ብልግናን መለማመዳቸው የእግዚአብሔር ኃይል በሕይወታቸው ውስጥ እውን አለመሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

ጳውሎስ ንስሐ እንዲገቡና ወደ ታዛዥነት የሚመራውን ኃይል እንዲለማመዱ ይፈልግ ነበር። እነርሱን መቅጣት (ዲሲፕሊን ማድረግ) የመጨረሻው አማራጩ እንጂ የሚፈልገው ነገር አልነበረም። “ክፉ ነገር ከቶ እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን... እናንተ ግን መልካሙን ታደርጉ ዘንድ ነው... ለመታነጻችሁ ደግሞ እንጸልያለን” ይላል (2ኛ ቆሮ. 13፡7–9)። ምንኛ የሚያምር ጸሎት ነው! በእምነት መሆናቸውን ያውቁ ዘንድ ራሳቸውን እንዲመረምሩ ይጠይቃቸዋል። 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡5ን አንብቡ። በእምነት መሆን ማለት ምን ማለት ነው? እናንተ በእምነት ውስጥ መሆናችሁን እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ?

መስከረም 8
Sep 18


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ ኋይት፣ The Laodicean Church፣ ገጽ 125፣ The Advent Review and Sabbath Herald፣ መስከረም 30፣ 1873።

“ጌታ ሕዝቡ ያለፈውን ስህተትና ዝንጉነት እንዳይደግሙ እየጠበቃቸው ነው። የተሳሳቱ ትምህርቶችንና ቅዱስ ያልሆኑ ልምምዶችን የሚያራምዱ፣ እንዲሁም በተሳሳቱ መርሆዎች ላይ ተመስርተው በሚያባብል፣ በተሰወረና አታላይ በሆነ መንገድ የሚሠሩ ሐሰተኞች መምህራን ሁልጊዜም በዙሪያችን ሞልተዋል። እነዚህም ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ለማሳት ይጥራሉ።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ The Advent Review and Sabbath Herald,፣ ጥር 7፣ 1904።

“ጌታ እኛ በእምነት መሆናችንንና አለመሆናችንን ለማወቅ ሕያው የሆኑትን የእግዚአብሔር ቃላት በጥንቃቄ መመርመር አስፈላጊ መሆኑን እንድንረዳ፣ የእኛ አመለካከቶች እንዲፈተኑ ይፈቅዳል። እውነትን እናምናለን የሚሉ ብዙዎች፦ “ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም” እያሉ በምቾት ተቀምጠዋል።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ Coun- sels to Writers and Editors፣ ገጽ 36።

“እውነቱ በግልጽ ተቀምጦ ሳለ ሰዎች ስህተትን ያስተናግዳሉ። ትምህርቶቻቸውን ወደ እግዚአብሔር ቃል ቢያመጡ ኖሮ፣ እንዲሁም ሐሳባቸውን ትክክል ለማስመስል የእግዚአብሔርን ቃል በትምህርቶቻቸው ብርሃን ባያነቡት ኖሮ፣ በጨለማና በዕውርነት ባልተጓዙ ወይም ስህተትን ባላቀፉ ነበር። ብዙዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት የገዛ አመለካከታቸውን የሚደግፍ ትርጉም ይሰጣሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በተሳሳተ መንገድ በመተርጎምም ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ያስታሉ። የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት ስንጀምር በትሕትና ሊሆን ይገባል። ራስ ወዳድነትና የራስን ሐሳብ የማድነቅ ፍላጎት ሁሉ ወደ ጎን ሊባል ይገባል። ለረጅም ጊዜ የቆዩ አመለካከቶች ስህተት የማይገኝባቸው ተደርገው ሊወሰዱ አይገባም” (ኤለን ጂ ኋይት፣ Counsels to Writers and Editors፣ ገጽ 36፣ 37)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. 2ኛ ቆሮንቶስ 10:1–6ን ደግማችሁ አንብቡ። ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር እውነት የሚደረጉ መንፈሳዊ “ጦርነቶችን” ለመጋፈጥ የተጠቀመው ስልት ምንድን ነው? ይህንንስ በእኛ የግል መንፈሳዊ ተጋድሎዎች ውስጥ እንዴት ልንተገብረው እንችላለን?

2. መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜው ከመምጣቱ በፊት ብዙ ሐሰተኞች መምህራን ሰዎችን ከእውነት ለማራቅ እንደሚሞክሩ ይናገራል። የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችሁ አባላት በዚያው በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ እንኳ ሊኖሩ በሚችሉ ሐሰተኞች መምህራን እንዳይሳቡ ምን ማድረግ ትችላለች? ይህስ የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ ለመፈጸም እንዲህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3. ጳውሎስ ረጅም የመከራ ዝርዝሩን መጥቀስና መመካት (2ኛ ቆሮ. 11:16– 33) ለምን አስፈለገው? ደግሞስ “በጌታ መመካት” ማለት ምን ማለት ነው?

4. የቤተ ክርስቲያን አባላት በእምነት መሆናቸውንና አለመሆናቸውን ለማወቅ ራሳቸውን መመርመራቸው ለምን አስፈላጊ ነው (2ኛ ቆሮ. 13:5)? ይህስ ምን ለውጥ ያመጣል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL