የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት እንዚህን ክፍሎች አንብቡ፦ 1ኛ ቆሮንቶስ 13፤ ማቴዎስ 24፡12፤ ገላትያ 5፡22፣ 23፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡14፤ 1ኛ ዮሐንስ 4፡8።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ «እንዲሁም እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው
ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው» (1ኛ ቆሮንቶስ 13፡13)።
ፍቅር ሁሉንም ነገር ማሸነፍ ይችላል። ጳውሎስ ስለ ፍቅር ብዙ የተናገረው ለዚህ ነው።
በአዲስ ኪዳን ውስጥ የፍቅርን ጽንሰ-ሐሳብ ለመግለጽ በብዛት ጥቅም ላይ የዋለው
“አጋፓኦ” (agapaō) የተሰኘው የግሪክ ቃል በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ ከ135 ጊዜ
በላይ ተጠቅሷል። ይህም በአጠቃላይ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከተጠቀሰው ግማሽ ያህሉን
ይወክላል። ይህ ሁኔታ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ ስላለው
ማዕከላዊ ጭብጥ አንድ ነገር ሊነግረን ይገባል።
በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ ፍቅር የሚናገሩ ብዙ አስደናቂ ክፍሎች አሉ—ለምሳሌ
ሮሜ 8፡35–39፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡9፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡3፣ ገላትያ 2፡20፣ ቆላስይስ 1፡13፣ 1ኛ
ተሰሎንቄ 3፡12 እና ሌሎችም። ሆኖም ከ1ኛ ቆሮንቶስ 13 ጋር የሚወዳደር ምንም ነገር የለም።
ባለፈው ሳምንት፣ ያለ ፍቅር ሁሉም ነገር፣ መንፈሳዊ ስጦታዎች እንኳ ሳይቀሩ ዋጋ ቢስ
መሆናቸውን አይተናል። በዚህ ሳምንት ደግሞ፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 13ን እና በውስጡ ያለውን
አስደናቂ የፍቅር ስዕል በጥልቀት እንመለከታለን።
በምናየው መሠረት፣ ፍቅር ከስሜት ይልቅ አመለካከት ነው፤ ይህም አመለካከት
በሕይወት፣ በተግባር እና በቃል መገለጥ አለበት፤ አለበለዚያ ትርጉም አይኖረውም።
ፍቅር በእውነት ምን እንደሆነና ምን እንደሚያደርግ በየሱስ ሕይወት ውስጥ ሙሉ
በሙሉ ተገልጧል።
*ለነሐሴ 9 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።
ባለፈው ሳምንት በ1ኛ ቆሮንቶስ 13 ላይ እንደሚታየው ስለ ፍቅር ጭብጥ ጥቂት ዳስሰናል። አሁን የጳውሎስን ቃላት እዚህ ጋ ይበልጥ በጥልቀት መመርመር ያስፈልገናል። 1ኛ ቆሮንቶስ 13ን አንብቡ። ስለ ፍቅር እየነገረን ያለውን ሐሳብ በአጭሩ አጠቃልሉ።
ጳውሎስ በአዲስ ቋንቋ መናገር (1ኛ ቆሮ. 13፡1)፣ ትንቢት፣ ማስተዋል፣ እውቀት፣ እምነት
(1ኛ ቆሮ. 13፡2) እና ምጽዋት (1ኛ ቆሮ. 13፡3) ዋጋ የሌላቸው ናቸው ማለቱ አይደለም።
እነዚህ ነገሮች ዋጋ ቢስ የሚሆኑት በፍቅር ካልተመሩ ብቻ ነው።
ጳውሎስ እየተናገረ ያለው የፍቅር ዓይነት እንደ “እንጆሪ እወዳለሁ” ወይም “ጓደኞቼን
እወዳለሁ” ወይም ደግሞ “ባለቤቴንና ልጆቼን እወዳለሁ” እንደሚባለው ዓይነት አገላለጽ
አይደለም። እንዲሁም በፊልሞች ላይ እንደሚታየው ዓይነት ፍቅር አይደለም። ምንም
እንኳ ይህ ክፍል በሰርግ ስብከቶች ላይ በብዛት ጥቅም ላይ ቢውልም፣ ስለ ወሲባዊ ፍቅር
እየተናገረ አይደለም።
ይህ ፍቅር በስሜታዊነት፣ በቸርነት፣ በበጎነት ወይም በምጽዋት ብቻ ሊገደብ አይችልም።
ሆኖም እነዚህ ሁሉ በተለያየ ደረጃ ይወክሉታል። ይህ ፍቅር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት
ለእኛ የተሰጠ ልዩ ጸጋ ነው። በእርግጥም በ1ኛ ቆሮንቶስ 13 ላይ ያለው ፍቅር በስሜት፣
በቸርነት፣ በበጎነት እና በምጽዋት እንድንሠራ የሚገፋፋን በመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ መነሻ
ኃይል ነው። ይህም ለክርስቶስ እና ለባልንጀሮቻችን የምናሳየው የተግባራችን፣ የስሜታችን
እና የአስተሳሰባችን ሙሉ ቁርጠኝነት ነው።
ማቴዎስ 24፡12ን አንብቡ። የሱስ እዚህ ጋ ምን ዓይነት ማስጠንቀቂያ
ይሰጠናል?
“አጋፔ” (agapē) እንዲህ አስፈላጊና መሠረታዊ የሆነው ለዚህ ነው። በክርስቶስ ኃይል፣
በቤቶቻችን፣ በቤተ ክርስቲያኖቻችን እና በአካባቢያችን ፍቅር እንዲቀዘቅዝ መፍቀድ
የለብንም። ለእኛ ሲል በመስቀል ላይ የሞተልን የክርስቶስ ምሳሌ አለን። ከዚህ የላቀና ይበልጥ
ኃይለኛ የሆነ የዚህ ዓይነት ፍቅር መግለጫ ምን ሊኖር ይችላል? እርግጥ ነው፣ ያንን ዓይነት
ፍቅር እኩል መግለጽ ባንችልም፣ በእግዚአብሔር ጸጋ በምንችለው መጠን በገዛ ሕይወታችን
ለመግለጥ መጋደል አለብን።
ይህንን ፍቅር ከምንም በላይ ለሚፈልግ ሰው፣ እንዲህ ዓይነቱን የፍቅር መግለጫ
ማሳየት እጅግ ጠቃሚና አዎንታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችልባቸው አንዳንድ
አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?
1ኛ ቆሮንቶስ 13፡4–7 የዚህ ምዕራፍ እምብርት ነው። ጳውሎስ ትኩረት የሚያደርገው
በፍቅር ባሕርያት ላይ ነው፤ ፍቅር ምን እንደሆነና ምን እንዳልሆነ፣ ወይም ፍቅር ምን
እንደሚያደርግና ምን እንደማያደርግ ያሳያል። በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ፍቅር ያለው
ሰው እንዴት እንደሚመላለስ ፍንጭ ይሰጠን ዘንድ ፍቅርን እንደ ሰው አድርጎ ይስለዋል።
ጳውሎስ ፍቅርን በሚገልጽበት ጊዜ ተከታታይ ግሶችን ይጠቀማል። ለእርሱ ፍቅር ከስሜት
ይልቅ ከተግባር ጋር የተያያዘ ነው።
ታዲያ ፍቅር ምን ያደርጋል?
1.
ይታገሣል (makrothymeō)፦ “ማክሮቲሜኦ” ማለት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም
እንኳ ትዕግሥትን ማሳየት ማለት ነው። ትዕግሥት ደግሞ እርስ በርስ የመቻቻልን
ችሎታ ያጎላል (ኤፌ. 4፡2)።
2. ቸርነት ያደርጋል (chrēsteuomai)፦ “ክሬስቴዎማይ” የሚለው ቃል በአዲስ
ኪዳን ውስጥ እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው የሚገኘው፤ ነገር ግን ከዚሁ ሥርወ ቃል
የወጡ ሌሎች ቃላት በሌሎች ቦታዎች በስፋት ይገኛሉ። በብሉይ ኪዳን የግሪክ
ትርጉም (Septuagint)፣ ከዚህ ሥር የተገኙ ቃላት በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ
ከእግዚአብሔር ምሕረት ጋር የተያያዘውን የእግዚአብሔርን ቸርነት ለመግለጽ
በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ውለዋል (መዝ. 145፡9)። ጳውሎስ ፍቅር ቸርነት ያደርጋል
ሲል፣ አንድ ሰው ለሌሎች ያለው ፍቅር እግዚአብሔር ለእኛ ያሳየውን ርኅራኄና
ምሕረት መምሰል አለበት ማለቱ ነው።
3. ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል (synchairō)፦ “ሲንካይሮ” ከአንድ ሰው ጋር አብሮ ደስ
የመሰኘትን ችሎታ ያመለክታል (ሉቃስ 1፡58፤ ሉቃስ 15፡6፣ 9፤ 1ኛ ቆሮ. 12፡26፤
ፊልጵ. 2፡17፣ 18)።
4. ሁሉን ይታገሣል/ይሸፍናል (stegō)፦ “ስቴጎ” ማለት “መሸፈን” ይኸውም አንድን
ነገር በሚስጥር መያዝ (ይህም ጥበቃ የማድረግ ስሜት አለው) ማለት ነው ወይስ
“መጽናት” በሚል የጥንካሬ ስሜት በሚለው ላይ ምሁራን ይከራከራሉ። የመጽናት
ጽንሰ-ሐሳብ በ1ኛ ቆሮንቶስ 9፡12 ላይ በግልጽ ስለሚታይ፣ አብዛኞቹ ተርጓሚዎችና
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ሁለተኛውን አማራጭ ይበልጥ ተመራጭ ያደርጉታል።
5. ሁሉን ያምናል (pisteuō)፦ “ፒስቴዎ” የሚለው ቃል “እምነት” (pistis) ከሚለው
የግሪክ ቃል ጋር አንድ ዓይነት ሥርወ ቃል አለው። በ1ኛ ቆሮንቶስ 13 አውድ ውስጥ፣
ሁሉን ማመን ማለት ለሌሎች በጎ ግምት መስጠት ማለት ነው።
6. ሁሉን ተስፋ ያደርጋል (elpizō)፦ በአዲስ ኪዳን “ኤልፒዞ” የሚለው ግስ ሁልጊዜም
አንድ መልካም ነገር እንደሚከሰት ማመንን ወይም መጠበቅን ያመለክታል።
7.
በሁሉ ይጸናል (hypomenō)፦ በ1ኛ ቆሮንቶስ 13፡7 ላይ “ስቴጎ” እና “ሂፖሜኖ”
በሚሉት ግሶች መካከል ልዩነት የለም ሊባል ይችላል። ሁለቱም ተመሳሳይ ትርጉም
ያላቸው ሲሆን፣ እዚህ ጋ በመከራ ውስጥ መጽናትን ያመለክታሉ። ጳውሎስ “ስቴጎ”
የሚለውን ቃል ላለመድገም በቁጥሩ መጨረሻ ላይ “ሂፖሜኖ”ን ተጠቅሟል።
ተመሳሳይ ሐሳብን በተለየ ቃል በመድገም፣ ማመንንና ተስፋ ማድረግን እንደ
ማዕከላዊ ነጥብ ትኩረት እንዲሰጣቸው ያደርጋል። በሌላ አነጋገር፣ ፍቅር
በመታመንና በተስፋ ይጸናል።
1ኛ ቆሮንቶስ 13፡4–7ን ከገላትያ 5፡22፣ 23 ጋር አነጻጽሩ። በሁለቱ ክፍሎች
መካከል ምን ዓይነት የሚያመሳስሉ ሐሳቦችን ያያሉ? ይህንን የፍቅር ዓይነት
በራሳችን ሕይወት እንዴት ልንገልጠው እንችላለን?
1ኛ ቆሮንቶስ 13፡4–7ን እንደገና አንብቡ። ጳውሎስ ስለ ፍቅር በጎ ባሕርያት ብቻ ከመጥቀስ ይልቅ፣ ፍቅር የሌለባቸውን አሉታዊ ባሕርያት ጭምር የጠቀሰው ለምንድን ነው?
ትላንት ፍቅር በሚያደርጋቸው ሰባት ነገሮች ላይ ትኩረት አድርገን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ
የማያደርጋቸውን ስምንት ነገሮች እንመለከታለን። ፍቅር፦
1. አይቀናም (zeloō)፦ “ዜሉኦ” የሚለው ቃል እንደ “የሚበልጠውን ስጦታ በጽኑ
ፈልጉ [zeloō]” (1ኛ ቆሮ. 12፡31)፣ “መንፈሳዊ ስጦታን በጽኑ ፈልጉ [zeloō]” (1ኛ
ቆሮ. 14፡1) እና “ትንቢት ለመናገር በጽኑ ፈልጉ [zeloō]” (1ኛ ቆሮ. 14፡39) ባሉት
ክፍሎች ውስጥ በአዎንታዊ መልኩ ሊሠራበት ይችላል። እዚህ ጋ ግን፣ በሐዋርያት
ሥራ 7፡9 ላይ እንዳለው ሁሉ አሉታዊ ነው። መንፈሳዊ ስጦታዎችን መፈለግ
መልካም ቢሆንም፣ ስጦታ ባላቸው ሰዎች ላይ መቅናት ግን ተገቢ አይደለም። ይህ
መከፋፈልን ያመጣል (1ኛ ቆሮ. 3፡3)።
2. አይመካም (perpereuomai)፦ “ፔርፔሬውኦማይ” የሚለው ግስ የትዕቢትንና
ከሌሎች ምስጋና የመፈለግን ሐሳብ ያስተላልፋል። ፍቅር ግን እንደዚያ በራስ ላይ
ያተኮረ አይደለም። ይህ ደግሞ በሚቀጥሉት ነጥቦች ላይ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል።
3. በትዕቢት አይነፋም (physioō)፦ “ፊሲኦ” የሚለው ግስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 8፡1 ላይ
ጳውሎስ፦ “እውቀት” በትዕቢት ይነፋል፣ ፍቅር ግን ያንጻል” በሚለው አስደናቂ
አገላለጹ ውስጥ ይገኛል። ይህ በገዛ ራሱ አስፈላጊነት የተወጠረን ሰው ያመለክታል።
4. የማይገባውን አያደርግም/ጨዋነት የጎደለው ባሕርይ አያሳይም (aschēmo-
neo)፦ “አስኬሞኔኦ” የሚለው ግስ ሰፊ የትርጉም ክልል ሊኖረው ይችላል።
በአጠቃላይ ግን፣ ከማኅበራዊና ከሥነ-ምግባር ደንቦች ውጭ በሆነ፣ ክብር
በሌለው፣ አሳፋሪ፣ ነውረኛ ወይም ተገቢ ባልሆነ መንገድ መንቀሳቀስ ማለት ነው።
ምናልባትም ጳውሎስ እያመለከተ ያለው በቆሮንቶስ የነበሩት “ጠንካራ” ወገኖች
በ”ደካማ” አባላት ላይ ያሳዩት የነበረውን ትዕቢትና ሻካራ ባሕርይ ሊሆን ይችላል
(1ኛ ቆሮ. 4፡10፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 8)።
5. የራሱን [መብት] አይፈልግም (zēteo)፦ ይህ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፡24 ላይ፦
“እያንዳንዱ ለባልንጀራው የሚጠቅመውን እንጂ ማንም የራሱን አይፈልግ” ካለው
ጋር ተመሳሳይ ነው። ፍቅር ስለ ሌሎች ሲል የገዛ መብቱን ይተዋል (5ኛ ትምህርትን
ይመልከቱ)። እያንዳንዱ ሰው የሌላውን መብት በሚያስከብርበት ሁኔታ ውስጥ
ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናሉ።
6. አይበሳጭም (paroxynō)፦ “ፓሮክሲኖ” የሚለው ግስ ለአንድ ሰው ለቁጣ
መቸኮልን የሚያመለክት የውስጥ መነሳሳትን ያሳያል። ይህ ማለት ፍቅር ግልፍተኛ
ወይም ቶሎ የሚቀየም አይደለም ማለት ነው።
7.
ክፉን አይቆጥርም (logizomai)፦ “ሎጊዞማይ” የሚለው ግስ እዚህ ጋ የሂሳብ
አያያዝ ስሜት አለው፤ ይህም ማለት ፍቅር የሰውን በደል በዝርዝር መዝግቦ
አይይዝም ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ፍቅር ማለት ይቅር ማለትም ጭምር ነው።
8. በዓመፅ ደስ አይለውም (chairō)፦ ፍቅር የሌላውን ሰው በደል መዝግቦ የማይይዝ
ብቻ ሳይሆን፣ በበደሉም ደስ አይሰኝም። ሌሎችን በእውነት ስንወድ በስህተታቸው
አንደሰትም፤ ይልቁንም እነርሱን ለመርዳት እንጥራለን።
ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት አሉታዊ ባሕርያት መካከል እናንተን ይበልጥ
የሚፈታተኗችሁ የትኞቹ ናቸው? በክርስቶስ ኃይል እነዚህን እንዴት ማሸነፍ
ትችላላችሁ?
በ1ኛ ቆሮንቶስ 13፡4–7 ላይ የተዘረዘሩትን ስንመለከት፣ እነዚህን ሁሉ የፍቅር ባሕርያት በተሟላ ሁኔታ ባለመግለጣችን በተወሰነ ደረጃ የተሸነፍን ሊመስለንና ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። ጳውሎስ 1ኛ ቆሮንቶስ 13ን ሲጽፍ ምናልባትም በአእምሮው የነበረው የየሱስ ማንነት ሳይሆን አይቀርም። በእርግጥም እነዚህን ሁሉ የፍቅር ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ የገለጠው ክርስቶስ ብቻ ነው። ስለዚህ፣ በመጨረሻው ትንታኔ፣ የጳውሎስ የፍቅር መግለጫ የየሱስ ሥዕል ነው። ዮሐንስ 13፡1፣ 34፤ ዮሐንስ 15፡9፣ 12፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡14፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡7፣ 13፤ 1ኛ ዮሐንስ 3፡16፤ እና 1ኛ ዮሐንስ 4፡7–12፣ 19–21ን አንብቡ። ከእነዚህ ክፍሎች ስለ ፍቅር ምን እንማራለን?
እግዚአብሔር ፍቅር ነው (1ኛ ዮሐ. 4፡8)። እርሱ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ እጅግ
ወደደን (ዮሐንስ 3፡16)። የሱስ የዚህ ፍቅር ሙሉ መግለጫ ነው (ዕብ. 1፡3)። ፍቅር ራሱን
እንዴት እንደሚገልጥ ማወቅ ከፈለግን፣ ወደ የሱስ ረዘም ያለ እይታ ማድረግ አለብን። በአዲስ
ኪዳን ውስጥ ለተሳለው የየሱስ ሥዕል ትኩረት ከሰጠን፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ 13 ላይ የተጠቀሱት
ሁሉም በጎ የፍቅር ባሕርያት በእርሱ ውስጥ የታዩ መሆናቸውን እንረዳለን።
•
የሱስ ይታገሣል፦ “ነገር ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ለሚያምኑ ምሳሌ
እንድሆን፣ ከሁሉ ይልቅ ኃጢአተኛ በምሆን በእኔ ላይ የሱስ ክርስቶስ የነበረውን
ትዕግሥቱን [makrothymia] ሁሉ ያሳይ ዘንድ ስለዚህ ምሕረትን አገኘሁ” (1ኛ
ጢሞ. 1፡16)።
•
የሱስ ቸር ነው፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ጌታ ቸር [kind] መሆኑን” ይናገራል (1ኛ ጴጥ. 2፡
3)። በዚህ ክፍል ውስጥ “ጌታ” የሚለው ቃል የሱስን ያመለክታል። “ቸር” የሚለው
ቃል በ1ኛ ቆሮንቶስ 13፡4 ላይ “ቸርነት ያደርጋል” (chrēsteuomai) ከሚለው ግስ
ጋር አንድ ዓይነት ሥርወ ቃል ካለው “ክሬስቶስ” (chrēstos) ከሚለው የግሪክ ቃል
የተገኘ ነው።
•
የሱስ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል፦ የሱስ የአባቱን ፈቃድ ሲከተል እና የአባቱን ፍቅር
ሲለማመድ ደስታን አግኝቷል (ዮሐንስ 15፡9–11፣ ዮሐንስ 17፡12–14)።
•
የሱስ ሁሉን ይታገሣል/ይጸናል፦ ዕብራውያን 12፡2፣ 3 የሱስ “መስቀሉን የታገሠ...
በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፣ ከኃጢአተኞች በደረሰበት በእንዲህ ያለ
ተቃውሞ የጸናውን አስቡ” ይላል። እንደ የሱስ ብዙ የታገሠ ማንም የለም (ፊልጵ.
2፡8)። ይህንንም ያደረገው በፊቱ ስላለው ደስታ ነው!
•
የሱስ ሁሉን ያምናል፦ ሐናንያ የጳውሎስን መለወጥ እውነተኛነት በተጠራጠረ ጊዜ
(ሐዋ. 9፡13፣ 14)፣ የሱስ፦ “ይህ... ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና” ብሎ መለሰለት (ሐዋ.
9፡15)። የሱስ ሰዎችን የሚያያቸው ባሉበት ሁኔታ ሳይሆን፣ በእርሱ ኃይል ወደፊት
በሚሆኑት ማንነት ነው።
የሱስ እውነተኛ ፍቅር ምን እንደሆነ ለእኛ የሚገልጥባቸው ሌሎች መንገዶች
የትኞቹ ናቸው?
እስካሁን ድረስ የሱስ እነዚህን ሁሉ በመሆኑ ፍቅር ታጋሽ፣ ቸር፣ ደስተኛ፣ ጽኑ፣ አማኝ፣
ተስፋ የሚያደርግ እና የሚጸና (ወይም የማይለወጥ) መሆኑን ተምረናል። እነዚህን ባሕርያት
በየሱስ ውስጥ ካየን በኋላ፣ የሚቀጥለው እርምጃ እርሱን መምሰል ነው። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ
ሰዎች የነበረው ምኞትም ይህ ነበር። ሆኖም፣ በስምንቱ አሉታዊ የፍቅር ባሕርያት ውስጥ
ያለውን “አይ” የሚለውን ቃል ብናስወግድ፣ “በቤተ ክርስቲያን ክበባቸው ውስጥ የነበረውን
የቆሮንቶስ ሰዎችን ባሕርይ የሚያሳይ ጥሩ መግለጫ እናገኛለን፦ ቀናተኞች፣ ተመካሪዎች፣
ትዕቢተኞች፣ ባለጌዎች፣ የራሳቸውን ጥቅም ፈላጊዎች፣ ቶሎ የሚቆጡ እና ሌሎች ምን
ስህተት እንደሠሩ የሚከታተሉ ነበሩ። ጳውሎስ እዚህ ጋ የተጠቀመባቸውን ግሶች ለቆሮንቶስ
ሰዎች ሁኔታ እንዲመጥኑ አድርጎ ነው የቀረጸው።” — ቨርሊን ዲ. ቨርብሩግ፣ “1ኛ ቆሮንቶስ፣”
“1 Corinthians,” in The Expositor’s Bible Commentary: Romans–Galatians, re-
vised edition (Grand Rapids, MI: Zondervan, 2008)፣ ገጽ 372።
የቆሮንቶስ ሰዎች ብዙ የሚማሩት ነገር ነበረ። እኛም እንዲሁ። ጳውሎስ ፍቅር ምን
እንደሚያደርግና ምን እንደማያደርግ ከገለጸ በኋላ፣ እውነተኛ ፍቅርን በተግባር ለማዋል
እንዲያነሳሳ የፍቅርን ዘላለማዊ ባሕርይ በማጉላት ክፍሉን ያጠቃልላል።
አንድ ቀን ትንቢቶች አስፈላጊ መሆናቸው ያቆማል፤ የምንናገረውም አንድ ቋንቋ ብቻ ይሆናል፤
ጉድለት ያለበት የሰው ልጅ እውቀትም ቦታውን ለአዲስና ፍጹም ለሆነው ለእግዚአብሔር
እውቀት ይለቃል (1ኛ ቆሮ. 13፡12)። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች የሚቀሩት የተሰጡበት ዓላማ
ግቡን ሲመታ ብቻ ነው (1ኛ ቆሮ. 13፡10)። “ፍቅር ግን ለዘላለም ይኖራል!” (1ኛ ቆሮ. 13፡8)።
በተመሳሳይ መልኩ፣ ክርስቶስ ሲመለስ እምነት ቦታውን ለማየት (sight) ይለቃል (2ኛ
ቆሮ. 5፡7)፤ ለረጅም ጊዜ ተስፋ ያደረግነውም ነገር እውን ይሆናል (ሮሜ 8፡24)። ከሁሉ
በላይ ደግሞ፣ ፍቅር የአምላካችን የአብ፣ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ መለያ ሆኖ
ለዘላለም ይጸናል። ይሁን እንጂ እምነትና ተስፋም ለዘላለም የሚኖሩበት ሁኔታ አለ። እምነት
እንደ ደኅንነት ተሞክሮ (ሮሜ 4፡3)፣ ተስፋ ደግሞ በአዲሲቱ ምድር ስለሚኖሩ አዳዲስ
ደስታዎችና እውቀቶች እንዳለን ናፍቆትና ጥበቃ ሆኖ የዳኑትን ሰዎች ተሞክሮ ለዘላለም
ያጅባል። ሆኖም ፍቅር፣ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ ለዘላለም ነግሦ ይኖራል።
በጣም በቅርቡ ጌታችንን ፊት ለፊት እናየዋለን (1ኛ ቆሮ. 13፡12)። ያ ቀን እስኪመጣ ድረስ፣
ሕይወታችንን በእነዚህ ሦስት በጎ ባሕርያት ልንገልጽ ይገባል፦ እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር። ይህ
ሦስትነት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚገኘውን የክርስቲያናዊ ሕይወት ሙላትን ይወክላል።
በክርስቲያኖች መካከልም በተደጋጋሚ ይጠቀስ የነበረው ለዚህ ነው (ሮሜ 5፡1–5፤ ገላትያ 5፡
5፣ 6፤ ኤፌሶን 1፡15፣ 18፤ 4፡1–5)። ሆኖም ፍቅር ከሁሉ ይበልጣል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን
ማንነት ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለ ብቸኛው በጎ ባሕርይ እርሱ ነው (1ኛ ዮሐ. 4፡8)።
“እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በሚለው አገላለጽ ላይ አሰላስሉ። የዚህን ቃል
ትክክለኛ ትርጉም እንዴት ልንረዳው ይገባናል? ሐሳቡን በከፊል ብቻ መረዳት
ብንችልም እንኳ፣ ይህ ሐረግ ለእኛ እንዲህ ያለ የምሥራች የሆነው ለምንድን ነው?
ኤለን ጂ ኋይት፣ “The Need of Love፣” ገጽ 545፣ 546፣ Re-
view and Herald፣ ነሐሴ 28፣ 1888።
“የሰውዬው ምስክርነት ምንም ያህል ከፍ ያለ ቢሆንም፣ ልቡ ለእግዚአብሔርና
ለባልንጀራው በፍቅር ካልተሞላ እርሱ እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር አይደለም።
ምንም እንኳ ታላቅ እምነት ቢኖረውና ተአምራትን የመሥራት ኃይል ቢኖረውም፣ ያለ ፍቅር
ግን እምነቱ ከንቱ ነው። ታላቅ ለጋስነት ሊያሳይ ይችላል፤ ነገር ግን ከእውነተኛ ፍቅር ውጭ
በሌላ ምክንያት ያለውን ሀብት ሁሉ ለድሆች ቢሰጥ፣ ያ ድርጊቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን
አያስገኝለትም። በቅንዓቱ ምክንያት እስከ ሰማዕትነት ሞት ድረስ ሊደርስ ይችላል፤ ሆኖም
በፍቅር ካልተገፋፋ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ተታለለ ቀናተኛ ወይም እንደ ትዕቢተኛ
ግብዝ ይቆጠራል።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ገጽ 318፣ 319።
“የስብከት ብዛት አለን። ከሁሉ በላይ የሚፈለገው ግን... ለሚጠፉ ነፍሳት የሚሆን ፍቅር
ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር ዙፋን በተትረፈረፈ ፈሳሽ የሚመጣው ፍቅር ነው። እውነተኛ
ክርስቲያንነት ፍቅርን በመላው ማንነት ውስጥ ያስርጻል። እያንዳንዱን ወሳኝ ክፍል—
አንጎልን፣ ልብን፣ ረዳት እጆችንና እግሮችን ይነካል፤ ይህም ሰዎች እግዚአብሔር እንዲቆሙ
በሚፈልግበት ቦታ በጽናት እንዲቆሙ ያስችላቸዋል፤ በዚህም እግራቸው እንዳይሰናከልና
አንካሳው ከመንገድ እንዳይወጣ ቀጥተኛ መንገድ ያደርጋሉ። ለሚጠፉ ነፍሳት የሚሆን
የሚነድና የሚበላ የክርስቶስ ፍቅር፣ የመላው ክርስቲያንነት ሥርዓት ሕይወት ነው” (ኤለን
ጂ ኋይት፣ Lift Him Up፣ ገጽ 134)።
“መፈወስ የሚችለው ከክርስቶስ ልብ የሚፈሰው ፍቅር ብቻ ነው። የቆሰለችን ነፍስ ወደ
ቀድሞ ሁኔታዋ ሊመልስ የሚችለው ያ ፍቅር ልክ በዛፍ ውስጥ እንደሚፈስ ፈሳሽ ወይም
በሰውነት ውስጥ እንደሚዘዋወር ደም በእርሱ ውስጥ የሚፈስለት ሰው ብቻ ነው፡፡” (ኤለን
ጂ ኋይት፣ ስነ ትምህርት፣ ገጽ 114)።
1.
ጳውሎስ የዘረዘራቸው በጎ የፍቅር ባሕርያት ሁሉንም ያካተቱ ይመስላችኋል?
ካልሆነ፣ በዝርዝሩ ላይ ምን ሌሎች ነገሮችን ትጨምራላችሁ?
2. ጳውሎስ “ፍቅርን ተከታተሉ” (1ኛ ቆሮ. 14፡1) ሲል ምን ማለቱ
ይመስላችኋል? ይህ በ1ኛ ቆሮንቶስ 13፡4–7 ላይ ከገለጸው ሐሳብ ጋር
ምን ግንኙነት አለው?
3. በዕለት ተዕለት ሕይወታችሁ ውስጥ ይበልጥ በተግባር ላይ ማዋል
የሚገባችሁ የፍቅር ባሕርይ የትኛው ነው? በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችሁ
ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትስ የትኞቹ ናቸው? ለመሆኑ ጳውሎስ
ፍቅርን እንደ ትንቢት፣ ልሳን እና እውቀት ካሉ ስጦታዎች ጋር ለምን
ያነጻጽረዋል (1ኛ ቆሮ. 13፡8)?
4. ጳውሎስ በቆሮንቶስ አባላት መካከል ላለው የአንድነት ማጣት ዋነኛው
መፍትሔ ፍቅር እንደሆነ ይጠቁማል። ለምን? ይህ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያናችን
እንዴት ይሠራል?