የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚነበቡ፦ 1ኛ ቆሮንቶስ 8፤ የሐዋርያት ሥራ 15:20፤ 1ኛ ቆሮ. 9:1–6፤ 1ኛ ቆሮ. 10:5–22፤ ዘዳ. 6:4፣ 5፤ ማርቆስ 12:28–31።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ስለዚህ ስትበሉ ወይም ስትጠጡ ወይም ማናቸውን ነገር
ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” (1ኛ ቆሮንቶስ 10:31)።
አንደኛ ቆሮንቶስ 8–10 (በምዕራፍ 5–6) ስለ ጾታዊ ጉዳዮች የተደረገውን ውይይት
ወደ መደምደሚያ ያመጣል፤ በዚያውም ስለ አንድ የተለየ ጉዳይ ከቆሮንቶስ ሰዎች
በደብዳቤ ለተጠየቀ ጥያቄ የጳውሎስን መልሶች ያስተዋውቃል (1ኛ ቆሮ. 7:1)። እነዚህ
መልሶች የቀሩትን የ1ኛ ቆሮንቶስ ክፍሎች በአብዛኛው ይይዛሉ።
1ኛ ቆሮንቶስ ወደ ምዕራፍ 7 የሚሸጋገርበት ሁኔታ፣ የፆታ ብልግና (ከምዕራፍ 5–7) እና
ጣዖት አምልኮ (ከምዕራፍ 8–10) ተዛማጅ ርዕሶች መሆናቸውን ያመለክታል። በእርግጥ እነዚህ
ኃጢአቶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ ጊዜ አብረው ተጠቅሰዋል (የሐዋርያት ሥራ 15:20፣ 29፤
የሐዋርያት ሥራ 21:25፤ 1ኛ ቆሮ. 6:9፤ ኤፌ. 5:5፤ ቆላ. 3:5፤ ራዕ. 21:8፤ ራዕ. 22:15)።
በአጠቃላይ፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ 5–7 ጳውሎስ ስለ ዝሙት ችግር ሲናገር፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ
8–10 ደግሞ ዋና ትኩረቱ የጣዖት አምልኮ ጉዳይ ነው። ክርስቲያኖች ከሁለቱም መሸሽ
እንዳለባቸው ይናገራል (1ኛ ቆሮ. 6:18፣ 1ኛ ቆሮ. 10:14)።
ባለፈው ሳምንት፣ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ በመሆን (1ኛ ቆሮ. 6:19፣ 20) ከዝሙት
መሸሽ እንደሚቻል አይተናል። በዚህ ሳምንት፣ አንድ ሰው “ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር”
በማድረግ ከጣዖት አምልኮ መሸሽ እንደሚችል እንመለከታለን (1ኛ ቆሮ. 10:31)።
ለነሐሴ 1 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።
1ኛ ቆሮንቶስ 8:1–13ን አንብቡ። ጳውሎስ እውቀትን ከፍቅር ጋር ያነጻጸረው ለምንድን ነው? እዚህ ላይ ያለው አውድ ምንድን ነው? ምን ቁም ነገር እያስተላለፈ ነው?
ጳውሎስ ለጣዖት ከሚቀርብ ምግብ ጋር የተያያዘን ጭብጥ በማንሳት ጠለቅ ላለ ጉዳይ
ምላሽ ለመስጠት ይጠቀምበታል፤ ይህም ለሌሎች ፍቅር የማጣትን ጉዳይ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ
8)። ለጣዖት የተሠዋው ምግብ ጉዳይ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ከፍሎ ነበር።
አንዳንዶች ሌሎች አማልክት አለመኖራቸውን ማወቃቸው ማንኛውንም ነገር የመብላት መብት
እንደሰጣቸው ያምኑ ነበር (1ኛ ቆሮ. 8: 4)። እነዚህም “ጠንካሮች” ተብለው ተጠርተዋል (1ኛ
ቆሮ. 4:10)። ይህንን ባህሪ የተቃወሙት “ደካሞች” ይባላሉ (1ኛ ቆሮ. 8:9–12)። ጳውሎስ ቀደም
ሲል የነበሩአቸውን የአረማዊ ህይወታቸው መገለጫ የሆኑ አንዳንድ አጉል እምነቶችን ስላላሸነፉ
እንዲህ ያለውን መለያ ተጠቅሟል። ደካማዎቹ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ “ጠንካሮቹ” ሲመገቡ
ሲያዩ ክርስትናና ጣዖት አምልኮ አብረው የሚሄዱ ናቸው ብለው ይደመድሙ ይሆናል። ስለዚህ
ጳውሎስ “ጠንካሮቹ” ለደካሞቹ ማሰናከያ እንዲሆኑባቸው አልፈለገም።
መጽሐፍ ቅዱስ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ የመብላትን ድርጊት በጣም አሉታዊ በሆነ
መልኩ ይመለከታል (ሐዋ 15:20፣ 29፤ ሐዋ 21:25፤ ከራእይ 2:14፣ 20 ጋር አነጻጽሩ)።
ነገር ግን፣ ጳውሎስ በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ እንደምናየው ዓይነት ከረር ያሉ ንግግሮችን
አልተጠቀመም። ምክንያቱም ቀዳሚ ትኩረቱ እውቀትን አላግባብ መጠቀም ሊያስከትል
በሚችለው አንድነት ማጣት ላይ ነበር። ጳውሎስ እውቀትን በራሱ እንደ ክፉ ነገር እየነቀፈ
አይደለም፤ ይልቁንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወደ ትዕቢትና መለያየት የሚመራውን
የዕውቀት ዓይነት ይቃወማል። ፍቅር የሌለበት እውቀት በፍፁም እውነተኛ እውቀት
አይደለም (1ኛ ቆሮ. 8:2)። እውነተኛ እውቀት የሚመነጨው አንድ ሰው እግዚአብሔርን
ሲወድና በእርሱ ሲታወቅ ብቻ ነው (1ኛ ቆሮ. 8:3)።
“ጳውሎስ ዘዳግም 6፡4ን በመጥቀስ፤ አማኞች አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ማወቅ
እንዳለባቸው ያሳያል (1ኛ ቆሮ. 8፡4-6)። የሚገርመው ነገር፣ ጳውሎስ በዘዳግም 6፡4፣ 5 ላይ
የሚታየውን ተመሳሳይ ሐሳብ ይከተላል፤ በዚያም ሥፍራ እርሱ አምላካችን አንድ መሆኑ
ከተገለጸ በኋላ “አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ” የሚል ትእዛዝ ይከተላል። ለጳውሎስም
ሆነ ለሙሴ፣ ያለ ፍቅር የሚሆን እውቀት ከንቱ ነው።
“ጠንካሮች” በእውቀታቸው በመተማመን ለጣዖት የተሠዋውን መብላት ምንም ጉዳት
እንደሌለው ያምኑ ነበር። ረቡዕ እና ሐሙስ እንደምንመለከተው፣ ጳውሎስ በተወሰኑ
ሁኔታዎች ውስጥ ያንን መብት እንደሚፈቅድላቸው ገልጿል። ይሁን እንጂ፣ ያ ድርጊት
ለ”ደካሞች” ዕንቅፋት የሚሆን ከሆነ (1ኛ ቆሮ. 8፡9)፣ ሊያስወገዱት ይገባል። ክርስቲያኖች
ለክርስቶስ እና ለሌሎች ካላቸው ፍቅር የተነሳ ራስን የመካድ ተግባር ሊለማመዱ ይገባል።”
“ጳውሎስ ያለ ፍቅር የሚሆን እውቀት መጥፎ ነገር ሊሆን እንደሚችል
ይከራከራል (1ኛ ቆሮንቶስ 8)። ያለ ፍቅር የሚሆን እውቀት በእርግጥ መጥፎ
ሊሆን የሚችልባቸው ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?”
1ኛ ቆሮንቶስ 9፡1–6ን አንብቡ። ይህ ክፍል ከፍቅር የተነሳ ራስን መካድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተግባራዊ ምሳሌ የሚሰጠው እንዴት ነው?”
በመጀመሪያ ሲታይ፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ 9 ላይ የሚገኘው የጳውሎስ የሐዋርያነት መከራከሪያ፣
ከእውቀት እና ከፍቅር ጋር በተያያዘ ቀደም ብሎ ከቀረበው ውይይት ጋር ምንም ግንኙነት
የሌለው ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ ሲጻፍ በምዕራፎች
ያልተከፋፈለ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 9 የሚያስተምረው
ትምህርት ከቀደመው ክፍል የተነጠለ አይደለም። እንዲያውም 1ኛ ቆሮንቶስ 9 ለክርስቶስ
እና ለወንድሞች ያለንን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የሚያሳይ ተግባራዊ ምሳሌ ያቀርባል።
ጳውሎስ ስለ ፍቅር ሲል ጥቂት መብቶቹን ትቷል።
“መብላትና መጠጣት” (1ኛ ቆሮ. 9፡4)። እዚህ ላይ መብልና መጠጥ በአጠቃላይ
ራስን በገንዘብ መደገፍን ይወክላሉ። ጳውሎስ እንደ ሐዋርያ ከሚያገለግላቸው ሰዎች ቁሳዊ
ድጋፍ የመቀበል መብት ነበረው። በዘመኑ የነበሩ ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ያደርጉት
የነበረውም ይኸው ነበር። እርሱ ግን ይህን አላደረገም፤ ይልቁንም ድንኳን በመስፋት ራሱን
ይረዳ ነበር (ሐዋ. 18፡3)።
“ከአማኝ ሚስት ጋር አብሮ መጓዝ” (1ኛ ቆሮ. 9፡5)። ያገባ ሐዋርያ በሚያደርገው
የሚስዮናዊነት ጉዞ ከባለቤቱ ጋር በቤተ ክርስቲያን ወጪ የመጓዝ መብት ነበረው።
ለሚስዮናውያን ባልና ሚስት ምሳሌ የሚሆኑት ጵርስቅላና አቂላ (ሮሜ 16፡3) እንዲሁም
አንደሮኒቆስና ዩልያ (ሮሜ 16፡7) ይገኙበታል። ጳውሎስ ግን ያላገባ ነበር (1ኛ ቆሮ. 7፡8)።
ማግባት እና ለሁለቱም በሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ ከባለቤቱ ጋር የመታጀብ መብት ተጠቃሚ
መሆን ይችል ነበር።
ለመኖር “ሥራ ከመሥራት መቆጠብ” (1ኛ ቆሮ. 9፡6)። ጳውሎስና በርናባስ
ለሚስዮናዊነት ሥራቸው ደመወዝ የማግኘት መብት ነበራቸው (1ኛ ቆሮ. 9፡4-6)።
ጳውሎስ ለኑሮው ድንኳን ሰፊ ነበር (ሐዋ. 18፡3)፤ የበርናባስ የሥራ መስክ ምን እንደነበረ
ግን አናውቅም። ነገር ግን በጣም ለጋስ እንደነበረ እናውቃለን (ሐዋ. 4፡36፣ 37)፤ ስለሆነም
ራሱን ለማስተዳደር ፈቃደኛ እንደነበር እርግጥ ነው።
በ1ኛ ቆሮንቶስ 9፡7-11 ላይ፣ ጳውሎስ እርሱ እና በርናባስ ከቤተ ክርስቲያን ድጋፍ
አግኝተው መኖር ተገቢ መሆኑን ለማሳየት የ1ኛ ቆሮንቶስ 9፡6ን ሐሳብ ያብራራል (1ኛ ቆሮ.
9፡11፣ 12)። ጌታ ራሱ፦ “ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ ይውጣላቸው” ብሎ አዟል
(1ኛ ቆሮ. 9፡14፤ ከ1ኛ ጢሞ. 5፡18 ጋር ያነጻጽሩ)። ቢሆንም ጳውሎስ፦ “እኛ ግን በዚህ
መብት አልተጠቀምንም” ይላል (1ኛ ቆሮ. 9፡12)። በዚህም ጳውሎስ ራሱን የራስን መካድ
ምሳሌ አድርጎ ያቀርባል (1ኛ ቆሮ. 9፡1-18)፤ ይህም በቆሮንቶስ ለሚደረገው የወንጌል ስብከት
ጠቃሚ ስለመሆኑ ይከራከራል (1ኛ ቆሮ. 9፡19-23)።”
ምናልባት የሚገባችሁ መብት ቢሆን እንኳ፣ ለጌታ ይበልጥ ውጤታማ ምስክር
ለመሆን ስትሉ ብትተዋቸው የሚሻላችሁ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
ጳውሎስ ከራሱ ተሞክሮ ራስን የመካድ ምሳሌ ካቀረበ በኋላ፣ ይበልጥ ትኩረቱን ወደ ጣዖት አምልኮ ጉዳይ ያዞራል። በሌላ አገላለጽ፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 10 ጳውሎስ የተጣለ እንዳይሆን ራሱን እንደሚገሥጽ የገለጸበትን የ1ኛ ቆሮንቶስ 9፡27ን ሐሳብ ያብራራል። የቆሮንቶስ ሰዎች የእርሱን ምሳሌ እንዲከተሉ ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከሁሉ የሚበልጠው አርአያ የሱስ ነው (1ኛ ቆሮ. 11፡1)። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡7–11ን አንብቡ። እስራኤላውያን በምድረ በዳ ምን ዓይነት ኃጢአቶችን ፈጸሙ? የተሰጧቸው መብቶችስ ኃጢአታቸውን ይበልጥ የከፋ የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፡1–5 ላይ፣ ጳውሎስ በምድረ በዳ የነበረውን የእግዚአብሔርን ሕዝብ
ታሪክ ይጠቅሳል። ደመናው እና ባሕሩ የእግዚአብሔርን መሪነት፣ መገኘት እና ጥበቃ
ያስታውሳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ መብሉ እና መጠጡ የእግዚአብሔርን መጋቢነት
ይወክላሉ። ጳውሎስ የእስራኤልን በደመና እና በባሕር ውስጥ ማለፍ ከክርስቲያናዊ ጥምቀት
ጋር በሚመሳሰል መልኩ እንደ ጥምቀት ይቆጥረዋል። በተመሳሳይ መልኩ፣ ስለ መብል እና
መጠጥ በመጥቀስ፣ ጳውሎስ የጌታን እራት ያመለክታል።
በሌላ አነጋገር፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 10 የሚያስተምረው፣ በአንድ በኩል ክርስቲያኖች እንደ
እስራኤላውያን ተመሳሳይ ተሞክሮዎችን እየኖሩ መሆናቸውን ነው። ይሁን እንጂ ጳውሎስ
የእስራኤልን ታሪክ ያስታወሰው ያ ታሪክ እንዳይደገም ስለሚፈልግ ነው። እስራኤላውያን ያን
ሁሉ መብት ቢያገኙም፣ ብዙዎቹ ግን እንደ ጣዖት አምልኮ (1ኛ ቆሮ. 10፡7) እና እንደ ዝሙት
(1ኛ ቆሮ. 10፡8) ያሉ ክፉ ነገሮችን ተመኝተዋል (1ኛ ቆሮ. 10፡6)። በመሆኑም “እግዚአብሔር
ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም” ቢባል አያስገርምም (1ኛ ቆሮ. 10፡5)።
በጥንታዊ እስራኤላውያን ላይ ጣት በመቀሰር ታላላቅ ኃጢአቶችን ፈጽመዋል ማለት
ቀላል ነው። ነገር ግን፣ ጳውሎስ የሚከራከረው፣ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ታሪክ የማወቅ
ትልቅ መብት ቢኖራቸውም፣ ተመሳሳይ ኃጢአቶችን የመሥራት ዕድል እንዳላቸው ነው።
ይህ በታላቁ ማስጠንቀቂያ ግልጽ ሆኗል፦ “ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ
ይጠንቀቅ” (1ኛ ቆሮ. 10፡12)። “የሚመስለው” የሚለው ሐረግ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ
ያሉ አንዳንድ ሰዎች በእነዚያ ኃጢአቶች ውስጥ የመውደቅ አደጋ እንደተጋረጠባቸው
አለመገንዘባቸውን ያሳያል። እኛስ ዛሬ ተመሳሳይ አደጋ ተጋርጦብናልን?
“እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።” ከእኛ መካከል የዚህን ማስጠንቀቂያ
እውነታ ያልተለማመደ ማን አለ?
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ከምንችለው በላይ እንድንፈተን እንደማይፈቅድ፣
ነገር ግን “ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርጋል” ይላል (1ኛ ቆሮ.
10፡13)።ታዲያ፣ አሁንም በኃጢአት መውደቅ እንዲህ ቀላል የሚሆንብን
ለምንድን ነው?
1ኛ ቆሮንቶስ 10፡5–22ን አንብቡ። ከጣዖት አምልኮ መሸሽ ያለብን ለምንድን ነው?
በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፡14–22 ላይ፣ ጳውሎስ ለጣዖት የተሠዋ መሥዋዕትን ጉዳይ እንደገና
ያነሳል። ለጣዖት መሥዋዕት ማቅረብ ዛሬ በብዙ ባሕሎች እንግዳ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የተለመደ ነበር። በአረማውያን ቤተ መቅደሶች ውስጥ ለአማልክት
እንስሳት በሚሠዉበት ጊዜ፣ የእንስሳቱ የተወሰነ ክፍል ለሚያገለግሉ ካህናት ይሰጥ ነበር፤
እነርሱም ሥጋውን ይሸጡት ነበር። ከዚህ ሥጋ መካከል የተወሰነው ክፍል በሕዝብ ገበያ ላይ
ይቀርብ ነበር። ይህ ሥጋ በገበያ ላይ ለሽያጭ ከሚቀርበው ሌላ ሥጋ ተለይቶ የማይቀመጥ
በመሆኑ፣ አንድ ክርስቲያን ሳያውቅ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ሊገዛ ይችላል። የሐዋርያው ምክር
ግን፦ እንዲህ ዓይነቱን ሥጋ ክርስቲያኖች በነፃነት ሊገዙት ይችላሉ የሚል ነው።
ይሁን እንጂ፣ ቀደም ሲል በመቅደስ ውስጥ የታረደ ሥጋ በቤት ውስጥ በክርስቲያኖች ሊበላ
ቢችልም (1ኛ ቆሮ. 8፡1–13)፣ ወደ አረማውያን ቤተ መቅደሶች መሄድና በበዓላቶቻቸው ላይ
መሳተፍ ለክርስቲያኖች በግልጽ የተከለከለ ነበር። መመዘኛው ግልጽ ነው፦ ጣዖታት ከንቱ
በመሆናቸው (1ኛ ቆሮ. 8፡4) ክርስቲያኖች ያንን ሥጋ በቤታቸው እንዲበሉ ተፈቅዶላቸዋል፤
ሆኖም ክርስቲያኖች በአረማውያን ሥነ ሥርዓቶች ላይ መሳተፍ የለባቸውም፤ ምክንያቱም
ይህ ከአጋንንት አምልኮ ጋር ስለሚቆጠር ነው (1ኛ ቆሮ. 10፡20፣ 21)። በአረማውያን ሥነ
ሥርዓቶች ላይ መሳተፍ ከአጋንንት ጋር ኅብረት እንደ ማድረግ ይቆጠራል (1ኛ ቆሮ. 10፡
20)፤ ይህም በጌታ እራት ላይ መሳተፍ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት እንደ ማድረግ ከመሆኑ ጋር
ይመሳሰላል (1ኛ ቆሮ. 10፡16)።
ስለዚህ ጳውሎስ፦ “የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና
ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም” ይላል (1ኛ ቆሮ. 10፡21)። የሱስ እንዳለው፦ “ለሁለት
ጌቶች መገዛት የሚችል ማንም የለም” (ማቴ. 6፡24)።
እግዚአብሔር ሙሉ ልብ ያለው ታማኝነትን እንደሚፈልግ ጳውሎስ ያስተምራል።
የጣዖት አምልኮ “ጌታን ለቅናት” እንደሚያነሳሳውም ይጠቅሳል (1ኛ ቆሮ. 10፡22)። ያ
እንዳይሆን ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 8፡4-6 ላይ ዘዳግም 6፡4፣ 5ን በመጥቀስ ከጣዖት
አምልኮ ለመጠበቅ የማይሳሳት/ጠንካራ መመሪያ ይሰጣል፦ “እስራኤል ሆይ ስማ፤
አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን
በፍጹም ልብህ፣ በፍጹምም ነፍስህ፣ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ” (ዘዳግም 6፡4፣ 5፤
አፅንዖት ተጨምሮበታል)። የሱስ በዘዳግም 6፡5 ላይ ካለው እግዚአብሔርን ከሁሉ በላይ
የመውደድ ሐሳብ ላይ “ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን ጨምሯል (ማርቆስ
12፡31፤ ዘሌዋውያን 19፡18ን ይመልከቱ)።
ጣዖት የግድ የድንጋይ ሐውልት መሆን የለበትም። ከማንኛውም ነገር ጣዖት
ልንሠራ እንችላለን። እናንተ በራሳችሁ ሕይወት ልትሸሹዋቸው የሚገባችሁ
ጣዖታት ካሉ ምንድን ናቸው?
በ1ኛ ቆሮንቶስ 8፡1–3 ላይ ጳውሎስ ፍቅር አንድን ሰው ከጣዖት አምልኮ እንደሚጠብቀው ይከራከራል። ይህ መከራከሪያ በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፡23–11፡1 ላይ እንደገና ተነስቶ በስፋት ተብራርቷል። በ1ኛ ቆሮንቶስ 8፡3 ላይ ለእግዚአብሔር ስላለን ፍቅር ይናገራል። “እያንዳንዱ ለባልንጀራው የሚጠቅመውን እንጂ ማንም የራሱን አይፈልግ” ይላል (1ኛ ቆሮ. 10፡24)። ይህ ለሌሎች ያለ ፍቅር ነው። ማርቆስ 10፡17–22 እና ማርቆስ 12፡28–31ን አንብቡ። እነዚህ ሁለት ክፍሎች ምን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ? በ1ኛ ቆሮንቶስ 10 ላይ ካለው ሁኔታ ጋርስ እንዴት ይዛመዳሉ?
ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 10 ላይ እያደረገ ያለው ነገር በትክክል የሱስ በማርቆስ 12፡
28–31 ያደረገውን ነው፤ ይኸውም ሁለቱን ታላላቅ የሕግ ትእዛዛት ማለትም፦ ከሁሉ በላይ
እግዚአብሔርን መውደድ እና ሌሎችን መውደድ የሚሉትን በአንድ ላይ ማያያዝ ነው።
በሀብታሙ ወጣት አለቃ ታሪክ ውስጥ (ማርቆስ 10፡17–22) የሱስ እነዚህን ሁለት ዓይነት
ፍቅሮች ያጣምራል፤ ይህንንም ያደረገው በቅደም ተከተል ዘዳግም 6፡4ን (ማርቆስ 10፡
18ን ይመልከቱ) እና የዐሥርቱ ትእዛዛትን ሁለተኛውን ጽላት (ማርቆስ 10፡19ን ይመልከቱ)
በመጥቀስ ነው። የዚያ ሀብታም ወጣት ችግር ከእግዚአብሔርና ከባልንጀሮቹ ይልቅ ንብረቱን
አብልጦ መውደዱ ነበር (ማርቆስ 10፡22)። በሰማይ ካለው መዝገብ ይልቅ በምድር ያለውን
መዝገብ አበለጠ። ከድሆች ይልቅ ለገንዘቡ ቅድሚያ ሰጠ (ማርቆስ 10፡21)። እርሱ ጣዖት
አምላኪ ነበር።
የየሱስን ትምህርቶች በመከተል፣ ጳውሎስ እግዚአብሔርን ከሁሉ በላይ የመውደድ
እና ባልንጀራን እንደ ራስ የመውደድ መመሪያ በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፡27፣ 28 ላይ ለጠቀሳቸው
ግምታዊ ሁኔታዎች መዋል እንዳለበት ይጠቁማል። ይህ ማለት ሕጋዊ የሆኑ ነገሮች እንኳ
የሌላውን ሰው ሕሊና የሚጎዱ ከሆነ ጠቃሚ ወይም የሚያንጹ ላይሆኑ ይችላሉ (1ኛ ቆሮ. 10፡
23)። ይህ መመሪያ “ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” በሚሉት ቃላት በሚያስደንቅ
ሁኔታ ተጠቃሏል (1ኛ ቆሮ. 10፡31)። ጳውሎስ ሁሉም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር መደረግ
አለበት በማለቱ፣ ጣዖት አምልኮ በተለያዩ መንገዶች ሊገለጥ እንደሚችል ያሳያል፤ ምክንያቱም
ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባውን ክብር የሚቀማ ማንኛውም ነገር የጣዖት አምልኮ ዓይነት
ነውና (ኢሳ. 42፡8)።
በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፡31–11፡1 ላይ ያሉት የጳውሎስ ቃላት ከምዕራፍ 8 እስከ 10 ላሉት
ክፍሎች እንደ ማጠቃለያ ያገለግላሉ። የራሱን ጥቅም ሳይሆን “ብዙዎች እንዲድኑ የብዙዎቹን
ጥቅም” እንደሚፈልግ በግልጽ ተናግሯል (1ኛ ቆሮ. 10፡33)። ክርስቶስን የገለጠው በዚህ
መንገድ ነበር (1ኛ ቆሮ. 11፡1)።
ባልንጀራችሁን እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁ በተሻለ ሁኔታ መውደድን እንዴት
መማር ትችላላችሁ?
ኤለን ጂ ኋይት፣ “ጣዖት አምልኮ በሲና”፣ ገጽ 315–330፣
በኃይማኖት አባቶችና ነቢያት።
“እርስ በርሳችን ካለን ግንኙነት ትክክለኛ አጠቃቀም ብናደርግ ምንኛ ብዙ መልካም
ነገር በተሠራ ነበር! ሰማያዊ በረከቶችን የተቀበለ እያንዳንዱ ሰው በሌሎች ጎዳና ላይ ብርሃን
የመፈንጠቅ ግዴታ አለበት.... ያን ጊዜ እግዚአብሔርን በእውነት የሚወዱ ሁሉ ለራስ
ያላቸውን ጣዖታዊ የሆነን አምልኮ ያቆማሉ።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ በ Advent Review and
Sabbath Herald፣ ኅዳር 18፣ 1884፣ ገጽ 730።
“ጳውሎስ ወንድሞቹ ንግግራቸውና ተግባራቸው በሌሎች ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ
ሊኖረው እንደሚችል ራሳቸውን እንዲጠይቁ አሳስቧል። በራሱ ምንም ጉዳት የሌለው
ቢሆንም እንኳ፣ ጣዖት አምልኮን የሚደግፍ የሚመስል ወይም በእምነት ደካማ የሆኑትን
ሕሊና የሚጎዳ ማንኛውንም ነገር እንዳያደርጉ መክሯል። “እንግዲህ ብትበሉ ወይም
ብትጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት....”
“ሐዋርያው ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የሰጠው የማስጠንቀቂያ ቃል ለሁሉም ዘመናት
የሚሠራ ሲሆን፣ በተለይም ለእኛ ዘመን የሚስማማ ነው። ጣዖት አምልኮ ሲል የጣዖታትን
አምልኮ ብቻ ሳይሆን፣ ራስን ማገልገልን፣ ምቾትን መውደድን፣ የምግብ ፍላጎትንና ሥጋዊ
ስሜትን ማርካትንም ጭምር ማለቱ ነው።” — ኤለን ጂ ኋይት፣ The Acts of the Apos-
tles፣ ገጽ 316፣ 317።
“አንዳንድ በትክክል የማድረግ መብት ያላችሁን ነገሮች በማድረጋችሁ የእግዚአብሔር
ሥራ እንዲሰናከል የምታዩ ከሆነ፣ እነዚያን ነገሮች ከማድረግ ተቆጠቡ። የሌሎችን አእምሮ
ለእውነት የሚዘጋ ምንም ነገር አታድርጉ.... ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን አይጠቅምም።”
— ኤለን ጂ ኋይት፣ Testimonies for the Church፣ ቅጽ 9፣ ገጽ 215።
1.
ጳውሎስ እንደሚለው፣ የበሰለ ክርስቲያን ባሕርይ አንዳንድ ጊዜ
ገና ያልበሰለ ክርስቲያንን ዕድገት ሊያደናቅፍ ይችላል። ይህ ሊከሰት
የሚችልባቸውን ሁኔታዎች አስቡ። ይህንን ፈተና ለመወጣት ብቸኛው
መንገድ ከሁሉ በላይ እግዚአብሔርን መውደድ እና ሌላውን እንደ ራስ
መውደድ የሚለው መመሪያ የሆነው ለምንድን ነው?
2. ክርስቲያኖች እንኳ ጥንቃቄ ካላደረጉ ሊያመልኳቸው የሚችሏቸው አንዳንድ
ጣዖታት የትኞቹ ናቸው? ወደ ጣዖት ልንቀይራቸው የምንችላቸው አንዳንድ
መልካም ነገሮችስ የትኞቹ ናቸው? እንዲሁም፣ በጣም የሚንከባከቡት
ነገር ወደ ጣዖትነት መለወጡን እንዴት ማወቅ ይችላሉ?
3. ጳውሎስ ወንጌልን በሚሰብክበት ጊዜ ውድቅ እንዳይሆን ሥጋውን
እየጎሰመ እንደሚያስገዛው ተናግሯል (1ኛ ቆሮ. 9፡27)። በዚህ ሳምንት
ጥናት ላይ በመመስረት፣ አንድን ሰው በወንጌል ሰባኪነት ብቁ እንዳይሆን
ሊያደርጉት የሚችሉ ነገሮች ምን እንደሆኑ አስቡ።
4. በ1ኛ ቆሮንቶስ 10 ላይ ጳውሎስ የጣዖት አምልኮን አደገኛነት በማንሳት
“ከጣዖት አምልኮ ሽሹ” ይላል (1ኛ ቆሮ. 10፡14)። የጣዖት አምልኮ
እንዲህ የከፋ የሆነው ለምንድን ነው?