የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

1ኛ እና 2ኛ ቆሮንቶስ - የክርስቲያን ሕይወት እና ምስክርነት ባሕርይ



3ኛ ሩብ ዓመት 2026


ሐምሌ 11 - 17

4ኛ ትምህርት

Jul 18 - 24




ኃጢአት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚነበቡ፦ 1ኛ ቆሮ. 5:1–13፣ 2ኛ ቆሮ 2:5–10 1ኛ ቆሮ. 6:1–13፣ 1 ተሰ. 4:1–8፣ 1ኛ ቆሮ. 6:19–7:9።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ «ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ» (1ኛ ቆሮ. 6:19፣ 20)።

አእምሯችን እንደ ስፖንጅ ነው፦ በስሜት ህዋሶቻችን አማካኝነት ወደ እርሱ የሚመጣ ማንኛውም ነገር ውስጡ ይቀራል። ወደ ውስጥ ስለሚገቡት ሰለ አብዛኛዎቹ ነገሮች አናውቅም ይሆናል (ሁሉንም ነገር ብናስታውስ ኖሮ በትክክል ማሰብ አንችልም ነበር)፣ ነገር ግን ሁሉም ነገር እዚያ ውስጥ አለ፤ እናም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የምናስበውን፣ የሚሰማንን እና የምናደርገውን ነገር ይነካል።

ለዚያም ነው እኛ ክርስቲያኖች ሆነንም እንኳ ዙሪያችን ያሉ መጥፎ ነገሮች ተፅዕኖ የሚያሳርፉብን። ቤተ ክርስቲያን ከመነሻም ጀምሮ ከዚህ ችግር ጋር ታግላለች። ለምሳሌ እሁድን መጠበቅ ከየት መጣ? ቤተ ክርስቲያን እንዲሁ ከአየር ላይ ጎትታ አመጣቸውን? በእርግጥ እንደዚያ አይደለም፤ ነገር ግን በዙሪያዋ ካለው ባህል የመጣ ነው። እናም ይህ መርህ በቆሮንቶስም ውስጥ ሲገለጥ ማየት እንችላለን። ጳውሎስ በቡድንተኝነት ላይ ተቃውሞውን ካቀረበ በኋላ (1ኛ ቆሮንቶስ 1–4) በመቀጠል ከፆታዊ እርኵሰት፣ ከመካሰስ፣ ከዝሙት አዳሪነት፣ ከጋብቻ እና ሳያገቡ ከመኖር ጋር ወደተያያዙ ጉዳዮች ይዞራል (1ኛ ቆሮንቶስ 5–7)። ዓለማዊ አስተሳሰብ በከፍተኛ ደረጃ ተፅዕኖ አድርጎባቸው ነበር። በ1ኛ ቆሮንቶስ 1–4 ላይ የተገለፀው ከፋፋይነት በሚቀጥሉት ምዕራፎች ውስጥ ለተኮነኑት የስነ ምግባር ባህሪያት በር ከፍቷል። ጳውሎስ ይህን ኃጢአት ከቤተ ክርስቲያን ለመቅረፍ የፈለገው እንዴት ነው? ከጻፈውስ ምን ትምህርት እናገኛለን? ለሐምሌ 25 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።

ሐምሌ 12
Jul 19

የእምነት እና የተግባር መለያየት


በክርስትና ታሪክ ውስጥ፣ ቤተ ክርስቲያን ምን መምሰል እንዳለባት ለማወቅ የሃይማኖት ምሁራን፣ መጋቢያንና እና ምእመናን አዲስ ኪዳንን አጥንተዋል። ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ ባለችው ቤተ ክርስቲያን እንደነቃለን። ነገር ግን ወዲያው አንድ ወሳኝ ነገርን በፍጥነት እንስታለን፡— ሰዎች ከችግር ነጻ ሊሆኑ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን መምሰል ስለሌለባት ነገር ምን እንደሚል ለማየት አዲስ ኪዳንን ማንበብ ሳያስፈልገን አይቀርም። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፋቸው ደብዳቤዎች ጥሩ መነሻ ናቸው። 1ኛ ቆሮንቶስ 5:1–13ን አንብቡ። ጳውሎስ በዚህ ምንባብ ውስጥ የትኛውን ነውረኛ ሁኔታ ገልጿል? ይህ አሳዛኝ የሆነውስ ለምንድን ነው?



“የአባቱን ሚስት” የሚለው (በ1ኛ ቆሮ. 5:1) አገላለጽ ጳውሎስ በአንድ ወንድና በእንጀራ እናቱ መካከል ስለነበረው ግንኙነት እንደተናገረ ይጠቁማል። ይህ ሁኔታ “በቀሎዔ ቤተ ሰዎች” ተዘግቦ ሳይሆን አይቀርም (1ኛ ቆሮ. 1:11)። በሥጋ የቤተሰብ አባላት በሆኑት መካከል የሚኖር ፆታዊ ግንኙነት እንደ አስከፊ ኃጢአት ይቆጠር ስለነበር “በአሕዛብም ዘንድ እንኳ” ችላ የሚባል አልነበረም (1ኛ ቆሮ. 5:1)።ነገሩ እንደዚህ ቢሆንም እንኳ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሆነው ይህ ነውን? በ1ኛ ቆሮንቶስ 5:1–2 ላይ ያሉት የጳውሎስ ቃላት አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል ይህን እያደረገ ነበር በሚለው ዘገባ በጣም እንደተደናገጠ ያሳያሉ።

ይሁን እንጂ ይህ መጥፎ ሁኔታ እየባሰ ሄዶ ነበር። የቆሮንቶስ ሰዎች ስለ ሁኔታው ከማዘን ይልቅ እንዲህ ያለውን ኃጢአት በመታገሣቸው መኩራታቸውን ሲያውቅ ጳውሎስ ይበልጥ ተደናግጧል (1ኛ ቆሮ. 5:1– 2)። ስለዚህም ኃጢአተኛውን ሰው ብቻ ሳይሆን፣ በእምነት እና በተግባር መካከል መለያየት የሚታይበትንም ቤተ ክርስቲያን ለማረም አስቧል። እንዲያውም ቤተ ክርስቲያኒቱ በዚህ ዓይነት ሥጋዊ ርኵሰት ውስጥ ለሚኖረው ሰው የነበራት ልቅ አቋም እርማት እንደሚያስፈልገው ጳውሎስ ያለማቋረጥ በግልጽ ይናገራል። ነገር ግን እንዲህ ባለው ፆታዊ ርኵሰት መኩራራት እና እንዲያውም መመካት (1ኛ ቆሮ. 5:2፣ 6)? ይህ ሊታገሰው ከሚችለው በላይ ነበር። እነዚህ ሰዎች ደህና አይደሉም እንዴ?

በቆሮንቶስ ያለችው ቤተ ክርስትያን በሥጋ የቤተሰብ አባላት መካከል ለሚፈጸም ፆታዊ ርኵሰት ለምን ትዕግስት እንደነበራት ማብራሪያ የለንም። ምናልባት ቤተ ክርስቲያን ትጠቀምበት የነበረ ሀብታም አባል ሊኖር ይችል ይሆን? ወይም፣ ምናልባት፣ “ሁሉም ነገር ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም” (1ኛ ቆሮ. 6:12) በሚል አስተሳሰብ ይሆን? ብቻ እኛ አናውቅም። እውነተኛው ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ በግልጽ ሲጣስ (ዘሌ. 18:7፣ 8) ዓይናቸውን ጨፍነው ነበር። እንዲያውም በዚህ ይኮሩ ነበር? እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን በ”ፍቅር” እና “ተቀባይነት” ስም የመቀበል አደጋ ውስጥ የምንወድቅባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተወገዙ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሐምሌ 13
Jul 20

ነውርን መጋፈጥ


ጾታዊ ጉዳዮችን መፍታት ሁል ጊዜ ከባድ ነው። ለጳውሎስ ከባድ ነበር፣ ለእኛም እንደዚያው። በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን፣ ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ መሆን እና ጉዳዩን በጸሎት እና በፍቅር መፍታት አለብን። ግባችን ተሃድሶ መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። 1ኛ ቆሮንቶስ 5:1–13ን እንደገና አንብቡ። ጳውሎስ ይህን ሁኔታ እንዲቋቋሙ የነገራቸው እንዴት ነው?



ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ጾታዊ ነውሮች የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ እንደሚያስፈልጋቸው በግልጽ ተናግሯል። በእንዲህ ዓይነት ርኵሰት የሚመላለስ ሰው ፍርድ እንዲፈረድበት (1ኛ ቆሮ. 5:2)፣ ለሰይጣን እንዲሰጥ (1ኛ ቆሮ. 5:5) እንዲሁም ከመካከላቸው እንዲያወጡት (1ኛ ቆሮ. 5:13) ተናግሯል። የቤተ ክርስቲያን አባላት “ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ” (1ኛ ቆሮ. 5:9፣ 11) ደግሞም “እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ” (1ኛ ቆሮ. 5:11) ሲል ነግሯቸዋል። ጳውሎስ ለዘመናችን ጆሮ ሊያስከፋ የሚችል ጠንካራ ቋንቋ ይጠቀማል፣ ነገር ግን ቃላቱ በእነርሱ ታሪካዊ ዐውድ ውስጥ ከግንዛቤ መግባት አለባቸው። ደግሞም፣ በማን አለብኝነት የሚፈጸምን የኃጢአት መንገድ እየተጋፈጠ እንደነበር ማስታወስ አለብን። ብዙውን ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ጠንካራ ቋንቋ አስፈላጊ ነው። ያም ሆነ ይህ፣ አንዳንድ አገላለጾችን በአጭሩ ማብራራት ጠቃሚ ነው።

“ከመካከላችሁ አውጡት” ሲል፣ (1ኛ ቆሮ. 5:2፣ በተጨማሪም 1ኛ ቆሮ. 5:13) ይህ የሚያመለክተው የቤተ ክርስቲያንን ተግሣጽና ሥርዓት ነው።

“ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው” (1ኛ ቆሮ. 5:5) ምክንያቱም ይህ ሰው እግዚአብሔርን በመታዘዝ በእርሱ ጥበቃ ስር መሆንን አልመረጠም፣ እናም ለሰይጣን የተጋለጠ ይሆናል። ስለዚህ ይህ አገላለጽ “የውሳኔውን ፍሬ ይጨድ” የሚል ዓይነት መልዕክት ብቻ ሊኖረው ይችላል።

“እንዳትተባበሩ” (1ኛ ቆሮ. 5:9፣ 11)፤ “እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ” (1ኛ ቆሮ. 5:11) ጾታዊ ርኵሰት ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር መቀራረብ አደገኛ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፤ ምክንያቱም ሌሎች ምግባራቸውን እንዲከተሉ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ስለሚችሉ። በጥንት ጊዜ መብል በጋራ መመገብ ማለት እሴቶችንም መጋራት ማለት ነበር። ሁላችንም በዙሪያችን ላሉት ተጽእኖዎች የተጋለጥን ነን፣ እናም በተለይ እንደዚህ አይነት ነገርን ለመቋቋም በተቻለ መጠን እራሳችንን መጠበቅ አለብን።

“መንፈሱ እንዲድን” (1ኛ ቆሮ. 5:5) የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ተሃድሶ ነው። ይህም ኃጢአተኞችን ወደ አእምሮአቸው ለመመለስ እና የኃጢአት አኗኗራቸውን እንዲተዉ ለማድረግ ነው። ጳውሎስ “ለሥጋው ጥፋት” ሲል የተናገረው ይህ ሳይሆን አይቀርም (1ኛ ቆሮ. 5:5)። በ1ኛ ቆሮንቶስ 5 ላይ በእንዲህ ዓይነት ኃጢአት ውስጥ የነበረው ሰው በኋላ ንስሃ እንደገባ የተጠቀሰው ሰው ሊሆን ይችላል (2ኛ ቆሮ. 2:5–10ን ተመልከቱ)። የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ዓላማውን የሚያሳካው የተሳሳተው አባል ወደ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ሲቀላቀል ነው።

ሐምሌ 14
Jul 21

የቤተ ክርስቲያንን ማንነት መጠበቅ


በ1ኛ ቆሮንቶስ 6:1–11 ጳውሎስ ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው መናገሩን ይቀጥላል። 1ኛ ቆሮንቶስ 5:3፣ 12፣ 13 እና 1ኛ ቆሮንቶስ 6:1–13ን አንብቡ። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችንም ሆነ እኛን ለማስተማር እየሞከረ ያለው ምንድን ነው?





በ1ኛ ቆሮ 6:1 የሚገኘው ፕራግማ የሚለው የግሪክኛ ቃል “ነገር /ጉዳይ” የሚል ፍቺ አለው። እዚህ ጋ ግን፣ የሕግ ጉዳይን ያመለክታል። ነገር ግን፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 6:1–11 የወንጀል ጉዳይን እንደማይመለከት ማስታወስ ጠቃሚ ነው። ዓለማዊ ፍርድ ቤቶች የወንጀል ጉዳዮች ላይ ስልጣን እንዳላቸው በሮሜ 13:1–5 ተረጋግጧል። ልክ ሙሴ በዘዳግም 22:22–24 እንዳደረገው ሁሉ፣ ጳውሎስም የዝሙት ኃጢአት ከተፈጸመ በኋላ ለነበረው የሙግት ጉዳይ መልስ ሰጥቷል። ይህ የሚያሳየው ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ችግሮችን የሚፈታበት መንገድ ምን ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ነው።

በ1ኛ ቆሮንቶስ 6:1–11 ላይ ያለው ጉዳይ ስለ ዝሙት በሚናገሩ ምንባቦች መካከል የሚገኝ መሆኑ (1ኛ ቆሮንቶስ 5 እና 1ኛ ቆሮ. 6:12–20)፥ በ1ኛ ቆሮንቶስ 6:1 ላይም ያለው “ጉዳይ” የፆታ ብልግናን እንደሚመለከት ሊያመለክት ይችላል። ጉዳዩ ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት አናውቅም፤ በንብረት አለመግባባትን የመሰለ ቀላል የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ወይም የጾታዊ ኃጢአት ጉዳይ ሊሆን ይችላል።

ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን፣ የቤተ ክርስቲያን አባላት ወደ ዓለማዊ ፍርድ ቤት ሲወስዱት በማየቱ ጳውሎስ ደስተኛ አልነበረም። እንደ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ጉዳዩን “በዓመፀኞች” ፊት ከማቅረብ ይልቅ እርስ በርሳቸው መፍታት አይችሉም ነበርን? (1ኛ ቆሮ. 6:1)

አንዳንዶች እንደሚገምቱት በ1ኛ ቆሮንቶስ 6:1 ላይ የተከራከሩት በ1ኛ ቆሮንቶስ 5:1 የተጠቀሱት አባት እና ልጅ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ፣ ጉዳዩ በትክክል ምን እንደነበረ ማወቅ መልዕክቱን ለመረዳት አስፈላጊ አይደለም። ጳውሎስን ያሳሰበው ጉዳይ በውጭ ያሉ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን እንደ ክርስቲያን ማኅበረሰብ የሚያዩበት ማንነቷ ነበር። ክርስቲያኖች ቆሻሻን ሲያስወግዱ በአደባባይ መሆን የለበትም (1ኛ ቆሮ. 6:6)። በውስጥ ጉዳዮች ላይ ለመዳኘትም ዓለማዊ መንገዶችን መጠቀም የለባቸውም። በሮማውያን ዓለም ከፍተኛ ሀብት ወይም ፖለቲካ ውስጥ የነበሩ ግለሰቦች በፍርድ ቤት ሞገስ ያገኙ ነበር። በአንጻሩ ክርስቲያኖች ክርስቶስን የሚመስል የፍትህ አሰጣጥን መፈጸምና ራሳቸውን ከአለማዊ መለኪያዎች መለየት አለባቸው። በ1ኛ ቆሮንቶስ 5: 10፣ 11 እና 1ኛ ቆሮንቶስ 6: 9፣ 10 ላይ ጳውሎስ የዘረዘራቸውን የክፋት ዓይነቶች አስቡ። ጾታዊ ኃጢአትን እንደ ጣዖት አምልኮ፣ ሌብነት፣ ስግብግብነት እና ቅሚያ ካሉ ሌሎች ኃጢአቶች ጋር አብሮ የዘረዘረው ለምንድን ነው?

ሐምሌ 15
Jul 22

ጾታዊ ኃጢአትን መከላከል


1ኛ ተሰሎንቄ 4:1–8ን አንብቡ። ይህ ክፍል በቅድስናና እና ከዝሙት በመራቅ መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ይላል?



ጳውሎስ ከላይ ባሉት ጥቅሶች ውስጥ የጻፈው ስለሌላ ሰው ቢሆንም፣ መሠረታዊ መርሁ ግን በሁሉም ክርስቲያኖች ላይ ሊሠራ ይችላል።

ይሁንና፣ “በቆሮንቶስ ምን እየተካሄደ ነበር? ለምን እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተከስቱ?” ወደሚሉት ጥያቄዎች የሚመራን ምንድን ነው?

በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ወንጌል ነፃ ስላወጣቸው ማንኛውንም ነገር እንዲያደርጉ እንደተፈቀደላቸው ያምኑ ነበር።

ሆድ ለምግብ እንደ ሆነው፣ ሥጋም ለሥጋ ተፈጥሯል ብለው ይከራከሩ ነበር (1ኛ ቆሮ. 6:13)። ጳውሎስ ይህ የክርስቲያን ነፃነትን አሳስቶ መግለጽ ነው ሲል መለሰ። በጾታዊ ጉዳዮች ላይ ታማኝነትን ማጉደል ከክርስቲያናዊ ማንነት ጋር የማይጣጣም እና በወንጌል አማካኝነት ለሰው የተሰጠውን ነፃነት አላግባብ መጠቀም ነው (ሮሜ. 8:2፣ ገላ. 5:13)። ከኃጢአት ነፃ ወጥተናል እንጂ እንድንሠራው ነጻ አልወጣንም (ሮሜ. 8:2፤ ሮሜ. 6:18፣ 22)። እንዲያውም “ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው” (1ኛ ቆሮ. 6:13)። እኛ የክርስቶስ ነን (1ኛ ቆሮ. 6:15)፣ እናም ማንነታችን በምናደርገው ነገር ላይ ተጽዕኖ ማድረግ አለበት። አንደኛው ከሌላው ጋር በማይነጣጠል ሁኔታ የተያያዘ ነው። ይህ በ1ኛ ቆሮንቶስ 6 ላይ በሦስት የተለያዩ መንገዶች ተገልጧል።

በመጀመሪያ፣ “በጌታ በየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥበናል፥ ተቀድሰናል፥ ጸድቀናል።” (1ኛ ቆሮ. 6:11)። በ1ኛ ቆሮንቶስ 6:9–10 የተዘረዘሩት ኃጢአቶች፣ እንዲሁም በ1ኛ ቆሮንቶስ 6:12–20 የተወገዙት የዝሙት ተግባራት በታጠቡ፣ በተቀደሱ እና በጸደቁ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ምንም ቦታ የላቸውም።

ሁለተኛ፣ እኛ የክርስቶስ አካል ነን (1ኛ ቆሮ. 6:15) ይህ ማለት ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን አለብን (1ኛ ቆሮ. 6:17)። ጾታዊ ኃጢአት የዚያ ኅብረት መፍረስ ምልክት ነው (1ኛ ቆሮ. 6:13፣ 15)። ከጋብቻ ውጪ ጾታዊ ግንኙነት የሚፈጽም/የምትፈጽም ሁሉ ከዚያ ሰው ወይም ከዚያች ሴት ጋር “አንድ አካል” ይሆናሉ (1ኛ ቆሮ. 6:16)። በመንፈስ ከክርስቶስ ጋር ያለን ኅብረት በጾታዊ ጉዳዮች ላይ ያለንን ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መወሰን አለበት።

ሦስተኛ፣ ሰውነታችን “የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅድስ” ነው (1ኛ ቆሮ. 6:19፣ 20)። በጾታዊ ጉዳዮች ላይ በቅንነት መንፈስ ለመኖር ብቸኛው መንገድ ከክርስቶስ ጋር በመንፈስ ቅዱስ የጠበቀ ግንኙነት ማድረግ ነው። በሌላ ቦታ፣ ጳውሎስ ሥጋን “ሕያው ቅዱስና በእግዚአብሔር ፊት ደስ የሚያሰኝ መስዋዕት አድርጎ” ከማቅረብ አንፃር የመንፈስ ቤተ መቅደስ የመሆን ልምድን ይጠቅሳል (ሮሜ 12:1)። የፆታዊ ኃጢአት በሰው ልጆች ላይ ያመጣውን ጥፋት አስቡ። ይህ ጉዳይ ለክርስቲያን ምን ያህል አሳሳቢ ሊሆን እንደሚገባው ምን ይነግረናል?

ሐምሌ 16
Jul 23

ጋብቻ እና ሳያገቡ መኖር


ሰውነታችን “የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነው” የሚለው የጳውሎስ ማረጋገጫ (1ኛ ቆሮ. 6:19) የጾታ ብልግናን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ በተሰጠበት አውድ ውስጥ የሚገኘውን የቅድስና ህይወት ለመኖር ብቸኛው መንገድ፣ የመንፈስ ቤተ መቅደስ መሆን ነው። ቤተ ክርስቲያን ራሱን ከአካባቢው የሚለይ የክርስቲያን ማኅበር ማለት ነው። ይህን እንዲቻል የሚያደርገው የመንፈስ ቅዱስ መገኘት ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 6:19–7:9ን አንብቡ። “ከዝሙት ሽሹ” የሚለውን ትእዛዝ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ይህ ክፍል ብርሃን የሚፈነጥቀው እንዴት ነው? (1ኛ ቆሮ. 6:18)



በ1ኛ ቆሮንቶስ 7 ውስጥ ስለ ጾታዊ ባሕሪ ጠቃሚ ትምህርቶች አሉ። ይህ ምዕራፍ በግርድፉ በሁለት ንዑስ ክፍሎች ሊከፈል ይችላል፡— (1) ስለ ጋብቻ የተሰጡ መመሪያዎች፤ (2) ሳያገቡ ስለ መኖር የተሰጡ መመሪያዎች። 1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 7 ስለ ጾታዊ ጉዳዮች መነጋገር ጠቃሚም አስፈላጊም መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዱናል።

ነገር ግን፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 7ን ስናነብ፣ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከነበሩ ጉዳዮች ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ማስታወስ አለብን። ይህ ካልሆነ ግን አንዳንድ ንግግሮች እርሱ ለጋብቻ ዝቅተኛ አመለካከት እንዳለው እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል፤ ነገር ግን እንደዚያ አይደለም (1 ጢሞ. 4:1–3፣ 1 ጢሞ. 5:14፤ እንዲሁም ዕብ. 13:4)።

“ከዝሙት ሽሹ” የሚለው ትእዛዝ ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆን (1ኛ ቆሮ. 6:17) እና የመንፈስ ቤተ መቅደስ በመሆን (1ኛ ቆሮ. 6:19) ውስጥ የታሰረ ነው። ከዝሙት ለመሸሽ ከዚህ የተሻለ መንገድ አለ? በእርግጥ የለም።

በተጨማሪም ፆታዊ ባህሪያትን የፈጠረው እግዚአብሔር ነው፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር በትዳር ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ መሆን አለበት። ጾታዊ ግንኙነት በወንድና በሴት ጋብቻ ውስጥ ያለ የሰዎች መብት፣ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከለላ የተደረገበት ብቸኛው ዓይነት ግንኙነት ነው።

ጳውሎስ፣ “ከዝሙት ሽሹ” ሲል የዮሴፍን ታሪክ በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል (ዘፍ. 39:6–18)። መጽሐፍ ቅዱስ የጶጢፋር ሚስት ዮሴፍን ለጾታዊ ኃጢአት ከማስገደዷ በፊት ዮሴፍ “ከቤት እንደሸሸ” ይናገራል (ዘፍ. 39:18)። ይህ በዘፍጥረት 39:6–18 ከአራት ጊዜ ያላነሰ ተጠቅሷል። መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ባይናገረውም፣ ነገር ግን ዮሴፍ ለጾታዊ ግንኙነት ጋብቻን ይጠብቅ እንደነበር ይጠቁማል (ዘፍ. 41:45)። በመንፈስ ቅዱስም የተሞላ ሰው ስለነበረ፣ (ዘፍ. 41:38) በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነውን ማድረግ ይፈልግ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ባህልን ከሚቆጣጠሩ የተዛቡ ፆታዊ አመለካከቶች እራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንችላለን?

ሐምሌ 17
Jul 24


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ ኋይት፣ በThe Acts of the Apostles “የማስጠንቀቂያ እና የልመና መልእክት፣” ገጽ 298–308።

የሚገርመው፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ 5:10–11 እና 1ኛ ቆሮንቶስ 6:9–10 ላይ ባለው የክፉ ድርጊቶች ዝርዝር ውስጥ ጣዖት አምልኮና ስካር ከዝሙት ጋር ተዘርዝረዋል። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 10:7 ላይ እንደሚያስታውሰን የጣዖት አምልኮ በዓላት ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት የሚታወቁ ነበሩ (ከዘጸ. 32:1–6 ጋር አነጻጽሩ)፤ ይህ ደግሞ ለዝሙት ኃጢአት በር ይከፍት ነበር (1ኛ ቆሮ. 10:8)። ኤለን ጂ ኋይት እንዲህ ትላለች፡— “ራስ ወዳድና ሆዳም ሰዎች በቅድስና በረከቶች ደስ ሊላቸው አይችልም … የሰው አካል የሚደርሱበትን ክፉ ነገሮች ለመቋቋም ያለው ኃይል በጣም አስደናቂ ነው፤ ነገር ግን፣ የማያቋርጥ የተዛባ የአመጋገብና የመጠጥ ሥርዓት፣ መላ የሰውነት ተግባራትን ለድካም ይዳርጋል። የረከሱ ሥጋዊ ፍላጎቶችና ስሜቶችን በማርካት ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ተፈጥሮን ሥራዋን በማስተጓጎል የአካልን፣ የአእምሮንና የሞራልን ኃይል ያደክማሉ” (ኤለን ጂ. ኋይት፣ The Sanctified Life, ገጽ 25፣26)።

“አንድ ሰው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሚሆንበት ጊዜ፣ እያንዳንዱ የሐሰት ጣዖት ከነፍስ ወጥቶ ሲጣል፣ ባዶነቱ የሚሞላው ወደ ውስጥ በሚፈሰው የክርስቶስ መንፈስ አማካኝነት ነው። እንዲህ ያለው ሰው በፍቅር የሚሠራና ነፍስን ከሥነ ምግባራዊና ከመንፈሳዊ ርኩሰት ሁሉ የሚያነጻ እምነት አለው” (ኤለን ጂ. ኋይት፣ The Home Missionary፣ ህዳር 1889)።

“እግዚአብሔር ወደ ከፍተኛ፣ ንጹሕና ሰማያዊ ደረጃ ከፍ ሊያደርገን ይፈልጋል። ለዚህ ዓላማ መንፈሱ ከእኛ ጋር ያለማቋረጥ እየታገለ ነው። ... በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ካልታረሙ በቀር የተፈጥሮ ዝንባሌዎቻችን ሥነ ምግባርን የሚገድሉ ዘሮች አሏቸው” (ኤለን ጂ. ኋይት፣ Manuscript 12፣ 1888)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በቆሮንቶስ የነበሩ ብዙ አማኞች የባህል ተቀባይነት ለማግኘት ፍላጎት አሳይተዋል። ይህ ለክርስቲያን ማንነት አደገኛ የሆነው ለምንድነው? እኛም ተመሳሳይ ስህተት እንዳንሰራ ምን ማድረግ እንችላለን?

2. “ሥጋችሁ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን?” የሚለው የጳውሎስ አጽንኦት የተሰጠው ጥያቄ (1ኛ ቆሮ. 6:19) በ1ኛ ቆሮንቶስ 5–6 ላይ “አታውቁምን?” በሚል አጠያየቅ ለቀረቡት ሰባት ተከታታይ ጥያቄዎች መዝጊያ የሚሆን ነው። (1ኛ ቆሮ. 5:6፤ 1ኛ ቆሮ. 6:2፣ 3፣ 9፣ 15፣ 16፣ 19) ሁሉም “በእርግጥ ነው” የሚል ዓይነት አዎንታዊ እና አፅንዖት ያለው መልስ የሚፈልጉ ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ስጋት እንድንገነዘብ የሚረዱን እንዴት ነው? እኛም ዛሬ እነዚህ ጉዳዮች ሊያሳሰቡን የሚገባው ለምንድን ነው?

3. ጋብቻ የተሰጠው ከእግዚአብሔር ነው (ዘፍ. 1:27፣ 28፤ ዘፍ. 2:18–24) እናም መከበር አለበት (ዕብ. 13:4)። ብዙዎች ጊዜ እንዳለፈበት ነገር አድርገው በሚቆጥሩበት በአሁኑ ጊዜ ጋብቻ በኤድን ገነት ከእግዚአብሔር ዘንድ በቀጥታ የተገኘ ስጦታ መሆኑን ለዓለም ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL