የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

1ኛ እና 2ኛ ቆሮንቶስ - የክርስቲያን ሕይወት እና ምስክርነት ባሕርይ



3ኛ ሩብ ዓመት 2026


ሐምሌ 4 - 10

3ኛ ትምህርት

Jul 11 - 17




በክርስቶስ አንድነት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚነበቡ፦ 1ኛ ቆሮ. 1:12–17፣ ሮሜ. 1:29፣ 1ኛ ቆሮ. 1:10፣ 1ኛ ቆሮ. 3:1–4፣ ፊል. 2:5–8፣ 2ኛ ቆሮ. 11:23–28፣ ቆላ. 1:24


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ «ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ» (1ኛ ቆሮንቶስ 1:10)።



ዱር እንስሳትን የሚያጠኑ ሰዎች አንዳንድ ፍጥረታት መጠናቸው ቢለያይም በህብረት፣በመንጋ፣ በቡድን እንደሚኖሩ ያውቃሉ። ከተኩላዎች እስከ ዶልፊኖች፣ እንዲሁም እስከ ገብረጉንዳኖች ድረስ እነዚህ ፍጥረታት በአንድ ላይ ይኖራሉ። በተለይ ቺምፓንዚዎች ጥብቅ ትሥሥር ያላቸው ከ15 እስከ 150 የሚደርሱ አባላት ያሉት ቡድን መሥርተው በማህበር በመኖር ይታወቃሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ግንኙነቶች ሁልጊዜ ስምምነት ያላቸው አይደሉም፤ አንዳንድ ጊዜ ቺምፓንዚዎች እርስ በእርሳቸው ይጣላሉ።

ሰዎችም በተወሰነ መልኩ እንዲሁ ናቸው፤ በቡድን መኖር ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንድ ጊዜ በቡድናቸው ውስጥ እርስ በርስ ይጣላሉ። በእኛም አብያተ ክርስትያናት ውስጥ ያለው ሁኔታ ይኸው ነው! ብዙ ጊዜ አንደበተ ርቱዕ በሆኑ ተናጋሪ መሪዎች ዙሪያ ቡድንተኝነቶች ይመሰረታሉ። እንዲያውም ይባስ ብሎ፣ አንዱ ቡድን ከሌሎች ጋር አይጣጣምም። በቤተ ክርስቲያናችሁ ውስጥ ይህን ተመልክታችሁ ታውቃላችሁ?

እንደዚያ ከሆነ፣ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ምን እንዳጋጠመው ትገነዘባላችሁ። በዚህ ሳምንት ሐዋርያው ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላለው አለመግባባት እና እንዴት በክርስቶስ አንድነት ማሸነፍ እንደሚቻል የሚናገርበትን 1ኛ ቆሮንቶስ 1–4ን እናያለን። *ለሐምሌ 18 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።

ሐምሌ 5
Jul 12

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው የመለያየት ችግር


“ነገር ግን፥ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ” (1ኛ ቆሮንቶስ 1:10) የሚለው የጳውሎስ ልመና የ1ኛ ቆሮንቶስ የመጀመሪያዎቹ 4 ምዕራፎች ዋና መልዕክት ነው። በመሠረቱ አንድነት ሁሉንም የደብዳቤውን ክፍሎች አንድ ላይ የሚያገናኝ፣ ሁሉን አቀፍ ጭብጥ እንደሆነ አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይስማማሉ። 1ኛ ቆሮንቶስ 1:12–17ን አንብቡ። ይህ ክፍል በአጥቢያ መሪዎች ዙሪያ መለያየቶችን መፍጠር ምን ያህል ሞኝነት እንደሆነ እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው? የጳውሎስ መፍትሔስ ምንድን ነው?



ጳውሎስ በቆሮንቶስ ባሉ የቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል የነበረውን አንድነት ማጣት ለማሳየት ጠንከር ያሉ ቃላትን ተጠቅሟል። ‘ስኪዝማ’ (‘schisma’) (“መለያየት” 1ኛ ቆሮ. 1:10) እና ‘ኤሪስ’ (‘eris’) (“ክርክር” 1ኛ ቆሮ. 1:11) የሚሉትን የግሪክ ቃላት ይጠቀማል። ‘ስኪዝማ’ የሚለው ስም (እንዲሁም ‘ስኪዞ’ “መገንጠል” የሚለው ግስ) በአዲስ ኪዳን ውስጥ የአንጃዎች ልዩነትን ለመግለጽ በሌላ ቦታ ጥቅም ላይ ውሏል። ‘ኤሪስ’ (“ክርክር”) የሚለውም ስም እንዲሁ በክርስቲያኖች ሊተገበሩ የማይገባቸው የክፋት ዝርዝሮች ውስጥ በተደጋጋሚ ይታያል። ሮሜ 1:29፣ ሮሜ 13:13፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 3:3፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 12:20 እና ገላ. 5:20ን አንብቡ። ከኤሪስ (“ክርክር” ወይም “ጠብ”) ጋር የተዘረዘሩ ሌሎች ኃጢአቶች ምን ምን ናቸው? ይህ ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ ምን ይነግረናል?



አንዳቸው በሌላቸው ላይ ከሚያነሱት ክስ የተነሳ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩት አለመግባባቶች ገሃድ ወጡ (1ኛ ቆሮ. 6:1–3)። ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመካከላቸው ስለነበረው መካሰስ ሲናገራቸው “አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ” አለ (1ኛ ቆሮ. 6:5)። እንዲያውም፣ የጌታን እራት በሚካፈሉበት ጊዜ እንኳ ልዩነታቸውን ወደ ጎን አልተዉም (1ኛ ቆሮ. 11:17–22)።

በቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል የነበረው የአንድነት እጦት ችግር በጣም አስፈሪ ነበር፤ እናም ጳውሎስ ስለ ጉዳዩ በጣም ተጨንቆ ነበር። በዚህ የቆሮንቶስ ሰዎች መልእክት ውስጥ የተናገረው የመጀመሪያው ጉዳይም ይህንኑ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 1:12–27ን እንደገና አንብቡ። እንግዲያውስ ይህ ክፍል ቡድንተኝነቶች ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ለምን አደገኛ እንደሆኑ እንድንገነዘብ እንዴት እንደሚረዳን እናስብ። ይህን ችግር ለማስወገድ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችሁ ምን ማድረግ ትችላለች?

ሐምሌ 6
Jul 13

የሱስን ማዕከል ማድረግ


1ኛ ቆሮንቶስ 1:10ን አንብቡ። ጳውሎስ “በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ” ሁኑ ሲል ምን ማለቱ ይመስላችኋል?



የቡድንተኝነት መፈጠር ማለት አንድ ሰው ለክርስቶስ ያለውን ታማኝነት መካድ ማለት ነው (1ኛ ቆሮ. 1:10)። እግዚአብሔር “ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ የሱስ ክርስቶስ ኅብረት” ጠርቶናል (1ኛ ቆሮ. 1:9)። ጌታችን ክርስቶስ ነውና ማዕከላችን እርሱ ሊሆን ይገባል። ስለዚህም “ክርስቶስ ተከፍሏልን? ጳውሎስ ስለ እናንተ ተሰቅሎአልን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን?” (1ኛ ቆሮ. 1:13) ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ፣ “አይደለም!” የሚለው ቃል ነው። ክርስቶስ አልተከፋፈለም። ስለ እኛ የተሰቀለው ክርስቶስ ነው። የተጠመቅነው “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” ነው (ማቴ. 28:19)።

“እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ” በማለት ተናግሯል (1ኛ ቆሮ. 12:27)። አካሉ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ተግባራት ያላቸው ብዙ ክፍሎች ቢኖሩትም፣ ሰውነቱ ግን ያው አንድ ነው። ሰውነት በትክክል እንዲሠራ እያንዳንዱ ክፍል እንደ አቅሙ ሥራውን መሥራት አለበት። ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር የሚያመለክተው ጳውሎስ እየፈለገ ያለው አንድነትን እንጂ አንድ ዓይነትነትን አለመሆኑን ነው። በልዩነት ውስጥ አንድነትን እየፈለገ ነው። እንዲያውም፣ ልዩነት ቢኖርም እንኳ አንድነትን እየፈለገ ነው ማለት ነው።

ነገር ግን፣ ሁሉም ሃሳቦች እና አስተያየቶች ለጌታችን ለክርስቶስ መገዛት አለባቸው። ክርስቶስ ጌታችን የመሆኑ እውነታ ለጳውሎስ ጠቃሚ ጽንሰ–ሀሳብ ከመሆኑ የተነሳ በ1ኛ ቆሮንቶስ መክፈቻ ላይ ደጋግሞ ያነሳዋል (1ኛ ቆሮ. 1:2፣ 7፣ 8፣ 9፣ 10)። ስለዚህም ጳውሎስ ስለ ተገንጣይ ቡድኖችና መሪ ነን ስለሚሉ ሰዎች ጉዳይ ከመናገሩ በፊት፣ በመጀመሪያ የሱስ የሁላችንም ጌታ እንደሆነ አበክሮ ተናግሯል። የቤተ ክርስቲያን ማዕከል ሥጋ ለባሽ መሪዎች አይደሉም። የክርስቲያኖች ማዕከል የሱስ ነው።

በ1ኛ ቆሮንቶስ የመክፈቻ ጥቅሶች ውስጥ ስለ የሱስ ጌትነት የተሰጠው አጽንዖት (በ1ኛ ቆሮ 1:10) ጳውሎስ “በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። “የተባበራችሁ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል ‘ካታርቲዞ’ (‘katartizō’) ከሚለው ግስ የመጣ ሲሆን፣ ይህም አንድ ነገር ወደ ትክክለኛው ሁኔታው ሊመለስ እንደሚገባው የሚጠቁም ነው። ሰው በሆኑ መሪዎች ዙሪያ መለያየቶች ሲፈጠሩ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ግንኙነቶች ወደ ትክክለኛው ሁኔታቸው መመለስ አለባቸው፣ ይህም የሚሆነው በክርስቶስ በሚሆን አንድነት እና እኔነት ደግሞ ሲሞት ነው። ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት፣ የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን አንዳንድ ክፍሎች በትንንሽ ቡድኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ላይ አጽንዖት ሰጥተዋል። በትናንሽ ቡድኖች እና በተገንጣይ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ትንንሽ ቡድኖች ወደ ተገንጣይ ቡድኖች እንዳይቀየሩ እንዴት መጠንቀቅ እንችላለን?

ሐምሌ 7
Jul 14

ጥበብ እና ብስለት


በአብዛኛው፣ ተገንጣይ ቡድኖች የሚመነጩት ሰው በሆኑ መሪዎች ላይ ከልክ ያለፈ ዕይታ ከመኖሩ የተነሳ ነው። ይህ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ያለው የተዛባ አመለካከት ቤተ ክርስቲያን ለተወሰኑ መሪዎች ከመጠን ያለፈ ቦታ እንድትሰጥ በማድረግ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እና የአባላቱን መንፈሳዊ ጤንነት ሁሉ አደጋ ላይ ይጥላል። የዚህ ዓይነቱ ባህሪ መዘዝ ቤተ ክርስቲያንን ሊከፋፍል የሚችል የፉክክር ድባብ ማስከተሉ ነው። ከዚህም በላይ፣ የሰው መሪዎችን የክርስቲያናዊ ማንነታችን ዋና አካል አድርገን የምንይዝ ከሆነ፣ ክርስቶስን በሕይወታችን ውስጥ ከትክክለኛው ቦታ የማንሳት አደጋ ውስጥ እንገባለን። 1ኛ ቆሮንቶስ 3:1–4ን አንብቡ። ጳውሎስ እዚህ ላይ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን መንፈሳዊ ብስለት የገለጸው እንዴት ነው?





መንፈሳዊ ብስለት አማኞችን የእግዚአብሔርን ጥበብ ወደ ማድነቅ እንደሚመራቸው፤ ይህንንም መንፈስ ቅዱስ እንደሚናገረን፣ እንዲሁም የዚህ ዘመን ከሆነው ከሰው ጥበብ ጋር እንደሚቃረን ጳውሎስ ይገልጻል (1ኛ ቆሮ. 2:6፣7፣ 2:6፣ 13)። የእግዚአብሔር ጥበብ በክርስቶስ መስቀል ውስጥ ተገልጧል (1ኛ ቆሮ. 2:1–4)። በርግጥም፣ የእግዚአብሔር ጥበብ በክርስቶስ መከራ፣ ሞት እና ትንሣኤ ውስጥ ተገልጧል። ስለዚህ፣ የአንድነት ልመናውን ወደ ማቅረብ ከመመለሱ በፊት (1ኛ ቆሮ. 3:1–17) ጳውሎስ አንባቢዎቹ በክርስቶስ ውስጥ ያለውን እውነተኛ ጥበብ እና ብስለት አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ይፈልጋል።

ጥበበኛ እና የበሰሉ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሰዎች እንጂ ሥጋዊ አይደሉም፣ እንደ ሕፃናትም አይደሉም (1ኛ ቆሮ. 3:1)። መንፈሳዊ ነገሮችን ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር ያወዳድራሉ፣ ምክንያቱም “የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ... በመንፈስ የሚመረመር ስለሆነ” ነው (1ኛ ቆሮ. 2:13፣ 14)። ጥበበኛና የበሰሉ ክርስቲያኖች የሚመገቡት ጠንካራ ምግብ እንጂ ወተት አይደለም (1ኛ ቆሮ. 3:2፤ ከዕብ. 5:12 ጋር አወዳድሩ)። “ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው” (ዕብ. 5:13፣ 14)። ጥበበኛ እና የጎለመሱ ክርስቲያኖች የተለያዩ ሰዎችን በመጥቀስ “እኔ የጳውሎስ ነኝ” ወይም “እኔ የአጵሎስ ነኝ” አይሉም።

ደግሞም እነዚህ ሰዎች እንደ እነርሱ “ከእግዚአብሔር ጋር አብረው የሚሠሩ” ናቸው (1ኛ ቆሮ. 3:9)። እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር መስክ፣ ሕንፃ እና ቤተ መቅደስ ነን (1ኛ ቆሮ. 3:9፣ 16፣ 17)። እኛ ሁላችን በክርስቶስ የእግዚአብሔር ነን (1ኛ ቆሮ. 3:11)። በጣም ስታደንቋቸው በነበሩ ሰዎች በጣም ያዘናችሁበት ምን ተሞክሮ አላችሁ? ይህ ዓይነት ተሞክሮ ካላችሁ ምን ትምህርት አግኝታችኋል?

ሐምሌ 8
Jul 15

ክርስቶስን የመሰለ አገልጋይነት


1ኛ ቆሮንቶስ 4:1፣ 2ን አንብቡ። ይህ ክፍል ለሰብዓዊ መሪዎች ሊኖር ስለሚገባው ትክክለኛ አመለካከት ምን ያስተምራል?





በ1ኛ ቆሮንቶስ 3:1–4፣ ጳውሎስ ተገንጣይ ቡድኖች በመንፈሳዊ ብስለት እጦት እንደሚመጡ ፍንጭ ሰጥቷል። ነገር ግን፣ ስለዚህ ርዕስ ከመናገሩ በፊት፣ “የክርስቶስ ልብ አለን” ሲል አረጋግጧል (1ኛ ቆሮ. 2:16)። ይህ ሐረግ የክርስቶስን አስተሳሰብና ተግባር የሚያመለክት ነው ሊሆን የሚችለው። በሌላ አነጋገር፣ አማኙ እንደ ክርስቶስ ሲያስብ እና ሲያደርግ “የክርስቶስ ልብ” አለው። ይህን ዓይነት አስተሳሰብ በሁሉም የሕይወት ጉዳዮች ላይ ተግባራዊ ማድረግ ያን ያህል ቀላል አይደለም፤ አይደል? በግሪኮ–ሮማን ዓለም በፖለቲካ መሪዎች፣ ፈላስፎች፣ አሳቢዎች እና የሃይማኖት መሪዎች መካከል ብዙ ፉክክር ነበር። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ለባህል ተቀባይነት ያላት ጉጉት ዓለማዊ መንገዶችን እንድትከተል አድርጓታል። ይህ ዛሬም ለቤተ ክርስቲያን አደጋ ሊሆን ይችላል። ፊልጵስዩስ 2:5–8ን አንብቡ። ይህ ጥቅስ “የክርስቶስን ልብ” (1ኛ ቆሮ. 2:16) የሚለውን ሐረግ እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?



ልክ በቆሮንቶስ እንደነበረው፣ በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያንም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መከፋፈል ይከስት ነበር (ፊልጵስዩስ 2:1–4)። ፊልጵስዩስ 2:1–8 ክርስቶስን የመሰለ አገልጋይነት ለራስ እና ለራስ ወዳድ ምኞት መሞትን እንደሚጠይቅ እና ይልቁንም የሱስ እንዳደረገው ሌሎችን ከራሳችን በላይ ለመባረክ መፈለግን እንደሚጠይቅ ያስተምረናል።

ጳውሎስ (በ1ኛ ቆሮ. 4:1) “የክርስቶስ ሎሌዎች” ሲል እንደ ክርስቶስ ያለ አገልጋይነትን ማለቱ ነው። ይህ ሐረግ ክርስቶስን ረዳት ወይም የበታች ሆኖ ማገልገል የሚለውን ሃሳብ ሊያስተላልፍ ይችላል። ለሰብዓዊ መሪዎች ሊኖር የሚገባው ትክክለኛ አመለካከት በክርስቶስ የአመራር ምሳሌ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ግልጽ ነው። አገልጋዮቹም “መጋቢዎች” ተደርገው ተገልጸዋል (1ኛ ቆሮ. 4:1፣ 2)። መጋቢ የሌላ ሰውን ንብረት እንዲያስተዳድር አደራ የተሰጠው ሰው ነው። ያለን ምንም ይሁን ምን ሁሉም የክርስቶስ ነው። በፊልጵስዩስ 2:5–8 ውስጥ ባለው መልእክት ላይ በጸሎት ቆዩ። እግዚአብሔር ለእኛ ስላለው እራስን የሚያስክድ ፍቅር ይህ የሚነግረንን እንዴት እንረዳለን? እኛም ደግሞ በራሳችን ሕይወት ይህንን ፍቅር መከተልን እንድንችል ለራሳችን መሞትን እንዴት መማር እንችላለን?

ሐምሌ 9
Jul 16

መስቀልን የሚያንፀባርቅ የአኗኗር ዘይቤ


በተለይ በሰው መሪዎች ዙሪያ ተገንጣይ ቡድኖችን መመስረት የለብንም ሲባል፣ መሪዎቻችንን መደገፍ የለብንም ማለት ግን አይደለም። በቤተ ክርስቲያን ሥራ የሚመሩትን ልናደንቃቸው እና ልንረዳቸው ይገባል። እግዚአብሔር ሰዎችን በምድር ላይ አገልግሎቱን እንዲያከናውኑ አዟል። በመስቀል የተወከለውን መገዛት የሚያንፀባርቅ የአኗኗር ዘይቤን የሚያሳዩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊደመጡና ሊከተሏቸው የሚገባቸው ናቸው።

ይህም የሚሆነው በተንኮል የተተበተበን ማንኛውንም ዓይነት የመቆጣጠር ፍላጎት ለእግዚአብሔር ቃል በመገዛት ሊቀለብስ የሚችል ኃይል ያለው መስቀሉ ብቻ ስለሆነ ነው። እንደ ክርስቶስ ያሉ መሪዎች የአገልግሎታቸው ስኬት በእግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። የሱስ ሰው ሆኖ በምድራዊ አገልግሎቱ ለእግዚአብሔር ክብር ሰጥቷል (ዮሐንስ 17:4)።

ጳውሎስ እንዳለው፣ ታማኝ የሆነ የክርስቲያን አገልግሎት፣ የመስቀል ሥነ–መለኮት ነው ብለን ልንጠራው በምንችለው ሥነ–መለኮት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። መስቀል የእግዚአብሔር ጥበብ እና የማዳን ኃይሉ መገለጥ ነው።

በተመሳሳይም የሰውን ጥበብ ሞኝነት እንደሆነ ያሳያል። በ1ኛ ቆሮንቶስ 4:1–13 ጳውሎስ እንዲህ ያለ የመስቀል ሥነ–መለኮት ምን እንደሚመስል ግልጽ አድርጓል። በመጀመሪያ፣ ለክርስቲያናዊ አመራር መለኪያ መሥፈርት የሚያወጣው እግዚአብሔር መሆኑን አመልክቷል (1ኛ ቆሮ. 4:1–5)። ሁለተኛ፣ መከራ የእውነተኛ ክርስቲያናዊ አገልግሎት መለያ ምልክት መሆኑን አመልክቷል (1ኛ ቆሮ. 4:9፣ 11–13)። ይህ ሁለተኛው ነጥብ የበለጠ ሊዳብር ይገባዋል። 2ኛ ቆሮንቶስ 11:23–28 እና ቆላስይስ 1:24ን አንብቡ። ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበል ምን ማለት እንደሆነ ይህ ምን ያስተምረናል?



ክርስቲያን መሪዎች ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆን እና ለአገልግሎታቸው ሲሉ እስከ ሞትም እንኳ የየሱስን ፈለግ ይከተላሉ። ጳውሎስ ራሱን እና አጵሎስን “ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች” ሲል ይገልጻል (1ኛ ቆሮ. 4:9)። የምግብ እና የውሃ እጦት እንደተጋፈጡ፣ እንዲሁም እንደተራቆቱ፣ እንደተደበደቡና እንደተንከራተቱ ተገልጿል (1ኛ ቆሮ. 4:11)። በተጨማሪም ተሰድበዋል፣ ተሰደዋል፣ ስማቸው ጠፍቷል እንዲሁም “እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ” ሆነዋል (1ኛ ቆሮ. 4:12፣ 13)። በተጨማሪም ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ሀብታሞች፣ ነገሥታት፣ ጥበበኞች እና ታዋቂዎች እንደሆኑ በምፀት በመጥቀስ (1ኛ ቆሮ. 4:8፣ 10) ትዕቢት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመከፋፈል ምክንያት ስለሆነ፣ በእውነተኛ ክርስቲያናዊ አመራር ውስጥ ምንም ቦታ እንደሌለው አሳይቷል (1ኛ ቆሮ. 4:6)። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላችሁ ድርሻ ምንም ይሁን ምን ስለ ክርስቶስ ስትሉ ምን ያህል መከራ ተቀብላችኋል? በመልሶቻችሁ ውስጥ ምን ትምህርቶች ሊገኙ ይችላሉ?

ሐምሌ 10
Jul 17


ተጨማሪ ሀሳብ


“የአሥራ ሁለቱ ሥልጠና” (ኤለን ጂ.ኋይት፣ The Acts of the Apostles፣ ገጽ 17–24)።

“በእግዚአብሔር እውነት የሚያምኑ ቅሬታዎች አንድነትና ህብረታቸው፣ እውነት ያላቸውና ልዩ የሆኑ የተመረጡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ስለመሆናቸው ለዓለም ጠንካራ ምስክርነት ይሰጣል። ይህ ህብረትና አንድነት ጠላትን ምቾት ስለሚነሳው እንዳይኖር ይተጋል። የጊዜው እውነት ከልብ ሲያምኑበትና በህይወታቸው ምሳሌ ሲሆኑበት የእግዚአብሔርን ሕዝቦች አንድ ያደርጋል፤ ጠንካራ ተፅዕኖም እንዲኖራቸው ያደርጋል (ኤለን ጂ. ኋይት፣ Testimonies for the Church፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ. 327)።

“እግዚአብሔር ሰዎችን በዘላለም እውነት መድረክ ላይ ፍጹም በሆነ አንድነት እንዲቆሙ እየመራቸው ነው። ክርስቶስ ‹ለበጎ ሥራ የሚቀኑ ልዩ ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ› ራሱን ለዓለም ሰጠ። ይህ የማጥራት ሂደት ቤተ ክርስቲያንን ከዓመፃ ሁሉ እና ከክርክር መንፈስ ለማንጻት የታቀደ ነው፤ ይህም በማፍረስ ፈንታ እንዲገነቡ እና በሙሉ ኃይላቸው በፊታቸው ባለው ታላቅ ሥራ ላይ እንዲያተኩሩ ነው። የእግዚአብሔር ዕቅድ የእርሱ የሆኑ ሕዝቦች ሁሉ ወደ እምነት አንድነት ይመጡ ዘንድ ነው። ከመሰቀሉ በፊት የክርስቶስ ፀሎት ልክ እርሱ ከአባቱ ጋር እንደነበረ ሁሉ፣ አብ እንደላከው ዓለም ያውቅ ዘንድ፣ ደቀመዛሙርቱም አንድ ይሆኑ ዘንድ ነበር። ይህ ልብ የሚነካ እና አስደናቂ ጸሎት ከዘመናት አልፎ እስከ ዘመናችን ድረስ ይደርሳል፤ ምክንያቱም ቃሉ ‘ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም’ የሚሉ ነበሩ (ኤለን ጂ. ኋይት፣ Testimonies for the Church፣ ጥራዝ. 4፣ ገጽ. 17)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በምድራዊ አገልግሎቱ መጨረሻ፣ የሱስ ስለ አንድነት ጸለየ፡— “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ... ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ ያውቅ ዘንድ” (ዮሐንስ 17:21–23)። ዓለምን ያድን ዘንድ እግዚአብሔር ልጁን ስለላከበት እውነት በክርስቶስ ውስጥ ያለው አንድነት ጠንካራ ማስረጃ የሆነው ለምንድን ነው? ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድነት ማጣት ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ እንቅፋት የሆነው ለምንድነው?

2. 1ኛ ቆሮንቶስ 4:9–13ን አንብቡ። በዚህ ክፍል ሐዋርያት እንዴት እንደተገለጹ በትኩረት ተከታተሉ። ይህ ስለ ሐዋርያቱ የሚቀርበው መግለጫ በዓለማችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው የአመራር ገጽታዎች ጋር የሚጻረረው እንዴት ነው? የእግዚአብሔር መመዘኛዎች እና የዚህ ዓለም ደረጃዎች ምን ያህል የተለያዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይህ ክፍል ምን ያስተምረናል?

3. በ1ኛ ቆሮንቶስ 4:16 ላይ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች እርሱን እንዲመስሉ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። ሰብዓዊ መሪዎችን ለመምሰል ፈቃደኛ እንሆናለን? መሪን መከተል ያንን መሪ ያለ አግባብ ከፍ ከፍ ከማድረግ የሚለየው እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL