የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚነበቡ፦ 1ኛ ቆሮ. 1:17–31፣ ቆላ. 1:20፣ 1ኛ ጴጥ. 2:24፣ የሐዋርያት ሥራ 13:16–47 ፣ 1ኛ ቆሮ. 2:1–5
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን
የእግዚአብሔር ኃይል ነውና”(1ኛ ቆሮንቶስ 1:18)።
ሲሴሮ የተባለው አረማዊውና ሮማዊ ጸሐፊ እና ተናጋሪ፣ ለሮማውያን መስቀልን
እንደ መቅጫ መንገድ የመጠቀምን ሀሳብ ከአእምሮአቸው እንዲያርቁ ነግሯቸዋል።
ሲሴሮ የሞተው የሱስ ከመወለዱ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ቢሆንም፣ ንግግሩ ሮማውያን
ለመስቀል የነበራቸውን ንቀት ያሳያል። በጣም መጥፎ ከመሆኑ የተነሳ ሊያስቡበት እንኳ
አይገባቸውም ነበር።
በአንጻሩ ጳውሎስ “የመስቀሉ መልእክት... የእግዚአብሔር ኃይል ነው” በማለት ጽፏል
(1ኛ ቆሮ. 1:18)። ለጳውሎስ፣ መስቀል በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የመታረቂያ መሣሪያ
ነው (ኤፌ. 2:16፣ ቆላ. 1:20)፣ የየሱስ የትሕትና ምልክት (ፊልጵ. 2:8)፣ እና ታላቅ ዕዳችን
የተከፈለበትም ጭምር ነው (ቆላ. 2:14)።
በቆሮንቶስ ላሉት ችግሮች የጳውሎስ መልስ መስቀሉ ነው። አንድ ትልቅ ጉዳይ በጣም
ያሳስበው እንደነበር ለመረዳት በ1ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ብዙ ርቀት መሄድ አያስፈልግም፦
ይኸውም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረው መከፋፈል ነው። ጳውሎስ በነበረው ነገር በጣም
ግራ ከመጋባቱ የተነሳ ከሠላምታውና ከምስጋናው ክፍል (1ኛ ቆሮ. 1:1–9) በኋላ መጀመሪያ
የሚያነሳው ይህን ርዕስ ነው (1ኛ ቆሮ. 1:10–17)። በዚህ ሳምንት፣ ለዚህ ችግር እና ለሌሎች
የቆሮንቶስ ጉዳዮች መልስ ወደሆነው የመስቀል ኃያል መልእክት እንሸጋገራለን።
ለሐምሌ 11 ለሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።
ጳውሎስ የመስቀል መልእክት ለእኛ የእግዚአብሔር ኃይል ነው ብሏል። ስለዚህም “የሱስ ክርስቶስ ብቻ፣ እርሱም እንደተሰቀለ” የሚለው የስብከቱ ማዕከል መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም (1ኛ ቆሮ. 2:2)። 1ኛ ቆሮንቶስ 1:17–31ን አንብቡ። ጳውሎስ እዚህ ላይ ምን አስፈላጊ ነጥብ እየተናገረ ነው?
በ1ኛ ቆሮንቶስ 1:18–31፣ ጳውሎስ በሰዎች ሞኝነት እና በመለኮታዊ ጥበብ መካከል ያለውን
ልዩነት ገልጿል። መስቀል የሰውን እጅግ በጣም መጥፎውን፣ የእግዚአብሔርን ግን ከሁሉ
ይልቅ መልካምነቱን የማሳየት ኃይል አለው። ይህ የ1ኛ ቆሮንቶስ ክፍል በ1ኛ ቆሮንቶስ 1:17
ባለው መግለጫ ይጀምራል። የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን፣ (1ኛ ቆሮ. 1:17)፣ የመስቀሉ
መልእክት የስብከታችንን ዋና ቦታ መያዝ አለበት (በተጨማሪ 1ኛ ቆሮ. 2:2 ይመልከቱ)።
ጳውሎስ የተላከው ለማጥመቅ ሳይሆን የመስቀሉን ወንጌል ለመስበክ እንደሆነ
ተናግሯል። ይህ መግለጫ ሁለት አስፈላጊ ምልከታዎችን ይፈልጋል። በመጀመሪያ፣ “መላክ”
ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ አፖስቴሎ ነው፣ እርሱም ሐዋርያ ከሚለው ቃል የመነጨ
ነው። ስለዚህም የጳውሎስ መሠረታዊ ሐዋርያዊ ተግባር የወንጌል ስብከት ነበር። ሁለተኛ፣
ጳውሎስ ስለ ጥምቀት የተናገረው ሐሳብ ጥምቀት አስፈላጊ አይደለም ወይም ቢያንስ
የስብከትን ያህል አስፈላጊ አይደለም ማለት አይደለም። ይልቁንም በየሱስ ከመጠመቅ ይልቅ
ያጠምቋቸው የነበሩትን ከፍ ከፍ የሚያደርጉትን እየገሰጻቸው ነበር።
ጳውሎስ ‘የቃላት ጥበብ’ ሲል፣ (1ኛ ቆሮ. 1:17) አንደበተ ርቱዕ የሆኑ ንግግሮች በራሳቸው
መጥፎ ናቸው ማለቱ አልነበረም። ነጥቡ የሰው ጥበብ የመስቀሉን መልእክት ሊያደበዝዝ
አይገባም የሚል ነው። ይህ ሐረግ የግሪክ–ሮማን አነጋገርን የሚያመላክት ነው። በአቴንስ፣
ጳውሎስ አመክንዮን፣ ሳይንስን እና ፍልስፍናን ይጠቀም ነበር፣ ነገር ግን ይህ ብዙ ፍሬያማ
አልሆነም። ስለዚህ “በቆሮንቶስ ውስጥ የቸልተኞችን እና የግዴለሾችን ትኩረት ለመያዝ
ባደረገው ጥረት ሌላ የሥራ ዕቅድ ለመከተል ወሰነ። የተብራሩ ክርክሮችንና ውይይቶችን
ለማስወገድ እንዲሁም በቆሮንቶስ ሰዎች መካከል ‘ከየሱስ ክርስቶስ በቀር፣ እርሱም እንደተሰቀለ
ሌላ እንዳያውቅ ቆርጦ ነበር” (ኤለን ጂ. ኋይት፣ The Acts of the Apostles፣ ገጽ. 244)።
የተተነተኑ ንግግሮች በምን መንገዶች የመስቀሉን መልእክት ሊያደበዝዙ
ይችላሉ? ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እርሱም እንደተሰቀለ ማወጅ በአቴንስ
ከነበሩት አመክንዮ፣ ሳይንስ እና ፍልስፍና ይልቅ በቆሮንቶስ የበለጠ ፍሬ
ለምን አፈራ? ሆኖም ግን፣ አመክንዮ፣ ፍልስፍና እና ሳይንስ ወንጌልን
ለማወጅ ሊረዱ የሚችሉባቸው ጊዜዎች ሊኖሩ ይችላሉን?
ጳውሎስ የሰውን ሞኝነት ከመለኮታዊ ጥበብ ጋር በማነፃፀር “የመስቀሉ መልእክት ለሚጠፉት ሞኝነት ነው” (1ኛ ቆሮ. 1:18) ብሏል። ይህ በ1ኛ ቆሮንቶስ 1:18–31 ውስጥ ስለ ስንፍና ወይም ሞኝነት ከተሰጡት ከስድስቱ ማጣቀሻዎች ውስጥ የመጀመሪያው ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 1:20፣ 21፣ 23፣ 25 እና 27ን እንብቡ። እነዚህ ሞኝነትን የሚገልጹ ጥቅሶች ጳውሎስ የመስቀል መልእክት ለሚጠፉ ሰዎች ሞኝነት እንደሆነ ሲናገር ምን ማለቱ እንደሆነ እንድንገነዘብ የሚረዱን እንዴት ነው?
በ1ኛ ቆሮንቶስ 1:18 ላይ ያለው ሞኝነት የሚለው የግሪክ ቃል ‘ሞሪያ’ (‘mōria’) የሚል
ነው። ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን አምስት ጊዜ ብቻ የተገለጸ ሲሆን ሁሉም በ1ኛ ቆሮ. 1:18፣21፣23፤
1ኛ ቆሮ. 2:14፤ 1ኛ ቆሮ. 3:19) የተጠቀሱ ናቸው። ይህ እና ሌሎች ከአንድ ቤተሰብ የመጡ
ቃላት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚከሰቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ግማሾቹ በጳውሎስ
መልእክቶች ውስጥ ይገኛሉ። በአዲስ ኪዳን ከሚገኙት የዚህ ቃል ዝርያዎች ብዙዎቹ በ1ኛ
ቆሮንቶስ ውስጥ ይገኛሉ።
ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 1:18፣ 23 ላይ የተናገረው ሞኝነት ከብልግና ጠባይና አስተሳሰብ፣
ከማስተዋል ማነስ አልፎ ተርፎም በእግዚአብሔር ላይ ከማመፅ ጋር የተያያዘ የመሆኑን ያህል፣
ከአእምሮ ልቀት ማነስ ጋር የተያያዘ አይደለም። ይህም በ1ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ከመጀመሪያ
እስከ መጨረሻ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ የተናገረበትን ምክንያት ያብራራል።
ጳውሎስ በዚህች ከተማ ስለነበረበት ሁኔታ አስቡ። በራሳቸው እውቀት እና ጥበብ
እንዲሁም የባህል ውስብስብነት ወደሚኩራሩበት ቦታ ነበር የመጣው። እናም በዚህ
ዐውደ–ጽሑፍ የናዝሬቱ የሱስ ስለተባለ የገሊላ አይሁዳዊ፣ ስለ እነርሱ ብቻ ሳይሆን ስለ
ዓለም ሁሉ ኃጢአት ዋጋ ለመክፍል በሮማውያን እንደተሰቀለ፣ ከዚያም ከሞት እንደተነሳ
ይናገራል። ይህ ሰው የምሩን ሊሆን ይችላል? በማን ላይ እየቀለደ ነበር? ይህ በፍልስፍናዊ
ዘዴዎች ሊፈታና እና ሊተነተን የሚችል ጥልቅና አዲስ የፍልስፍና ፅንሰ–ሀሳብ አልነበረም።
ማንኛውም ብልህ እና የተማረ የቆሮንቶስ ሰው በቁም ነገር ሊመለከተው የማይችል ትርጉም
የለሽ የእብደት ነገር ይመስል ነበር።
የጳውሎስ መልእክት ለአረማውያን ሞኝነት የመሆኑን ያህል፥ የመስቀሉ መልእክት
ለብዙ አይሁዶች ደግሞ ከዚያም የከፋ ነበር። ምን ዓይነት አይሁዳዊ ሰው ነው መሲሕ
በሮም ይገደላል ብሎ ሊጠብቅ የሚችለው? መሲሑ ሮማውያንን እንዲገለብጣቸው እንጂ
በእነርሱ እንዲሰቀል ሊጠበቅ አይችልም ነበር።
ስለዚህም፣ ከመጀመሪያ ጀምሮ፣ በቆሮንቶስ በጳውሎስ ላይ ብዙ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር።
ነገር ግን፣ ይህ ሁሉ ቢሆንም እንኳ፣ ከአይሁድም ሆነ ከአሕዛብ ዘንድ ነፍሳት በወንጌል
አምነው ተማርከው ነበር።
እዚህ ጋ ያለው መልእክት ምንድን ነው?
ምንም ዓይነት ተቃውሞ ቢያጋጥመን፣ እግዚአብሔር እውነትን ለመስማት ልባቸው ክፍት
የሆኑ ሰዎች አሉት። እነዚህ ሰዎች የትም ቢሆኑ፣ ዛሬም እንደ ቆሮንቶስ መጥፎ የሆኑ ወይም
ከዚያም የከፉ ቦታዎችን እንኳ ለመድረስ እርሱ እንዲጠቀምብን ዝግጁ መሆን አለብን።
የ1ኛ ቆሮንቶስ 1:18 መልእክት እጅግ በጣም ግልጽ ከመሆኑ የተነሳ ማንም ሰው ነጥቡን ሊስተው አይችልም። የመስቀሉ ትርጉም በሰዎች ዕይታ ላይ ይወሰናል። በእግዚአብሔር ላይ ለሚያምፁ ሞኝነት ነው፥ ማዳኑን ለሚናፍቁ ግን ኃይል ነው። ቆላስይስ 1:20 እና 1ኛ ጴጥሮስ 2:24ን አንብቡ። የሱስ በመስቀል ላይ ምን አከናወነልን?
አስቀድመን እንዳየነው ወንጌል ሲሰበክ “የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን” የጥበብ
ቃልን ማስወገድ ይገባል (1ኛ ቆሮ. 1:17)። 1ኛ ቆሮንቶስ 1:17 ግልጽ ሲሆንልን፣ የሞኝነት ተቃራኒው
የሰው ጥበብ ሳይሆን የእግዚአብሔር ኃይል እንደሆነ መረዳት ቀላል ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 1:18)።
ከሰው ጥበብ ተቃራኒ የሆነው መስቀል፣ የሰው ጥበብ ምን ያህል ሞኝነት እንደሆነ ያሳያል።
በ1ኛ ቆሮንቶስ 1:18 ላይ የሚገኘው የግሪክኛ ጥቅስ ‘የሚጠፉት’ የስራቸውን ፍሬ እያገኙ
እንደሆነ ይጠቁማል። ጽሑፉ እንዲህ ሊነበብ ይችላል፦ “የመስቀሉ መልእክት ራሳቸውን
ለሚያጠፉት ሞኝነት ነውና”። ‘አፖሉሚ’ (apollymi) የሚለው የግሪክ ግስ “መጥፋት” ብቻ
ሳይሆን፣ “ማጥፋት” ማለትም ሊሆን ይችላል (ዮሐንስ 10:10)። እንዲያውም ‘አፖሉሚ’ በ1ኛ
ቆሮንቶስ 1:19 ላይ “ማጥፋት” ተብሎ ተተርጉሟል።
እዚህ ጋ ምን እየሆነ ነው? ጳውሎስ ስለነዚህ ስለሚጠፉት ሰዎች በቁጥር 18 ለተጠቀሰው
ለዚህ አባባል፣ በቁጥር 19 ላይ የእግዚአብሔርን ቃል ከኢሳይያስ 29:14 በማጣቀስ መጽሐፍ
ቅዱሳዊ መሠረት ይሰጣል። በቁጥር 19 ላይ ለተጠቀሰው “ማጥፋት” ባለቤቱ እግዚአብሔር
ነው፣ ይህም ልክ ከዚያ በፊት ከተጠቀሰው ራስን ከሚያጠፋው ትዕቢት ጋር የሚቃረን
ይመስላል። ሆኖም ግን፣ ምንም ተቃርኖ የለም። ሀሳቡ በመጀመሪያውኑ እራሱን እያጠፋ
ያለውን እግዚአብሔር ያጠፋዋል የሚል ነው።
ከሚጠፉት በተቃራኒ “ለእኛ ለምንድን” የሚለው ሐረግ (1ኛ ቆሮ. 1:18) መዳን የሚገኘው
ከእግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ያመለክታል። ጳውሎስ ድነናል እያለ ነው፤ እራሳችንን እያዳንን
አይደለም ማለት ነው። እኛ በእርግጥ ይህን ማድረግ አንችልም። መዳናችን የውጭ ምንጭ
አለው። ጥፋት በራሱ ምክንያት ቢሆንም፣ መዳን ግን ለኃጢአተኞች ሊሰጥ የሚችል የጸጋ
ስጦታ ብቻ ነው። በ1ኛ ቆሮንቶስ 1:21 በግልፅ እንደተቀመጠው የሚያምኑትን የሚያድናቸው
እግዚአብሔር ነው። ሞኝነት፣ በዚህ አገላለጽ፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በክርስቶስ
መስቀል ያቀረበውን አለመቀበል (1ኛ ቆሮ. 1:30)፣ እናም በራስ ላይ ጥፋትን ማምጣት ነው።
“የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ
የሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው” (ሮሜ. 6:23)። ይህ ጥቅስ ጳውሎስ
በ1ኛ ቆሮንቶስ 1: 18፣ 19 ላይ የተናገረውን በድጋሚ የሚገልጸው በምን
መንገዶች ነው?
ጳውሎስ “አይሁድ ምልክትን ይፈልጋሉ ግሪኮችም ጥበብን ይሻሉ” ሲል ጽፏል (1ኛ ቆሮ.
1:22)። የእግዚአብሔር ሐሳብ የሆነው መስቀሉ፣የተሰቀለው መሲሕ፣ አይሁዶች የጠበቁት
ምልክት አልነበረም። ግሪኮችም የሚፈልጉት ጥበብም አልነበረም። ሁሉም ሰው ከጠበቀው
በተቃራኒ ነበር የሆነው።
በርግጥም ይህ ሀሳብ በተለይ ለአይሁድ ምን ያህል እንግዳ እና ደስ የማያሰኝ እንደሆነ
ለማየት አንድ ሰው ማድረግ የሚጠበቅበት ነገር ቢኖር፣ ደቀ መዛሙርቱ ስለ የሱስ መሰቀል
(በማርቆስ 8:31፣ 32፤ ማርቆስ 9:30–32፣ እና ማርቆስ 10:32–34) ምን ዓይነት ምላሽ
እንደሰጡ ማንበብ ብቻ በቂ ነው። ቀደም ሲል እንደተባለው አይሁዶች መሲሑ ሮማውያንን
ድል እንደሚያደርግ ጠብቀው ነበር፤ ነገር ግን ቢያንስ በዓለማዊው ወታደራዊ አስተሳሰብ
የሆነው እንደዚያ አልነበረም።
ለዘመናት መስቀል ለክርስቲያኖች የእምነት ምልክት ሆኖ ቆይቷል። ለመጀመሪያው ክፍለ
ዘመን አዕምሮ የተሰቀለው አምላክ ሃሳብ ምን ያህል የእብድ አስተሳሰብ ይመስል እንደነበር
መረዳት ለዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ከባድ ነው።
ሆኖም፣ ይህን በጣም በጥልቀት እንድናስብበት የሚገባ የሚያደርገው፣ በእርግጥም ያን
ያህል ለማመን የሚከብድ መልእክት ስለነበረ ነው። የተሰቀለው መሲህ ምስል እግዚአብሔር
የመቤዠትን እቅድ ለማጠናቀቅ ምን ያህል ርቀት ለመሄድ ፈቃደኛ እንደሆነ ለመላው አጽናፈ
ዓለማት ግልጽ ያደርገዋል። የመስቀሉ እና የጌታ በመስቀል ላይ መሞት ሃሳብ ለእኛ በምድር ላይ
ላለን ኃጢአተኞች የሚያስደንቅ ነው። (ነገር ግን በሰማያት ያለውን ጌታ የሱስን ለሚያውቁት
እና ለሚሰግዱለት፣ ኃጢአት ለሌላቸው ፍጡራን ምን ማለት እንደሆነ ደግሞ አስቡት!)
የሐዋርያት ሥራ 13:16–47ን (በተለይ ቁጥር 26፣ 38 እና 47ን) አንብቡ።
ይህ ክፍል ስለ መስቀሉ ትርጉም ምን ያስተምረናል?
ጳውሎስ ወንጌልን እንዲሰብክ ክርስቶስ እንደ ላከው ተናግሯል። ስለዚህም ጳውሎስ
የተሰቀለውን መሲህ መልእክት ሰበከ (1ኛ ቆሮ. 1:23)። እነዚህኑ ሃሳቦች በ1ኛ ቆሮንቶስ
2:1–5ም ይቀጥላል። ሐዋርያው ለክርስቶስ ተልእኮ ታማኝ ነበር። ወንጌልን በማወጅ “ከፍ
ያለ ንግግር ወይም ጥበብ” አልተጠቀመም (1ኛ ቆሮ. 2:1)፤ ይልቁንም ትኩረቱን ያደረገው
ስለ”የሱስ ክርስቶስና እና እርሱም እንደተሰቀለ” (1ኛ ቆሮ. 2:2) ብቻ ነው። ንግግሩና
መልእክቱ “መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነው እንጂ፣ በጥበብ ቃል አልነበረም” (1ኛ ቆሮ.
2:4)፤ ምክንያቱም “የሰው ጥበብ” እንዲያውም ከ”እግዚአብሔር ኃይል” በተጻራሪ የቆመ
በመሆኑ ነው (2ኛ ቆሮ. 2:5)።
የተሰቀለው መሲህ በአይሁዶች እና በግሪኮች ፈጽሞ ያልተጠበቀ ነገር ነበር።
እግዚአብሔር ሁልጊዜ እኛ በምንጠብቀው መንገድ እንደማይሰራ ይህ ምን
ይነግረናል? በተለይ ነገሮች እንደጠበቅነው በማይሄዱበት ጊዜ ይህ ልንረዳው
የሚገባ ጠቃሚ ፅንሰ–ሀሳብ የሆነው ለምንድን ነው?
በ1ኛ ቆሮንቶስ 1:19፣ 20፣ 30 እና 31፣ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ጥበብ እና የሰው ጥበብ
በማይታመን ሁኔታ እንዴት እንደሚለያዩ እና አንደኛው በሌላኛው ውስጥ ፈፅሞ ሊኖር
እንደማይችል ተናግሯል። ጳውሎስ ጥበብን ከነጭራሹ እንደማይቃወም፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር
ጋር ለመወዳደር የሚሞክረውን ዓይነት ሰብዓዊ ጥበብ እንደማይቀበል ልብ እንበል። የሰው
ጥበብ ሰዎችን ከኃጢአት ነፃ የማውጣት ብቃት የለውም። ይህንን ሥራ መሥራት የሚችለው
የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ብቻ ነው። ከታች ያለውን ሰንጠረዥ ተመልከቱ።
ለእኛ ግን ለምንድን
[የመስቀሉ ቃል] የእግዚአብሔር ኃይል ነው።
1ኛ ቆሮ. 1:18
ለተጠሩት ሁሉ ግን፣
ክርስቶስ የእግዚአብሔር [ኃይል] ነው።
1ኛ ቆሮ. 1:24
1ኛ ቆሮንቶስ 1:18 እና 1ኛ ቆሮንቶስ 1:24 ሁለቱም ክርስቶስ ሰዎችን ከኃጢአታቸው
የማዳን ኃይል ስላለው የእግዚአብሔር ኃይል መሆኑን ያሳያሉ። በእርግጥም “በስብከት
ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና” (1ኛ ቆሮ. 1:21)። “ለእኛ
ለምንድን” (1ኛ ቆሮ. 1:18)፣ “የሚያምኑትን” (1ኛ ቆሮ. 1:21) እና “ለተጠሩት” (1ኛ ቆሮ. 1:24)
የሚሉት ሐረጎች/ቃላት አንድን ሕዝብ፣ ማለትም በእምነት መዳንን በመለማመድ የሚኖሩ
ሰዎችን ያመለክታሉ። “በወንጌል አላፍርምና … ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል
ለማዳን ነውና” (ሮሜ. 1:16)።
ክርስቶስ ኃይል ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ጥበብም ነው። ይህም ማለት እግዚአብሔር
በእርሱ በኩል የኃጢአትን ችግር ፈትቶታል፤ ይህም የሰው ጥበብ ሊፈታው ያልቻለውን
ችግር ነው። የዚህ ዓለም ጥበብ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያውቁ ማድረግ አይችልም (1ኛ
ቆሮ. 1:21)። በአንጻሩ በክርስቶስ በኩል ለመዳን ጥበበኞች እንሆናለን (2ኛ ጢሞ. 3:15)።
1ኛ ቆሮንቶስ 1:24–29ን አንብቡ። እዚያ ውስጥ ያሉትን ቃላት ልብ በሉ፦
“ሞኝነት”፣ “ድካም”፣ “ኃይል” እና “ጥበበኞች”። ጳውሎስ ምን መልዕክት
እያስተላለፈ ነው?
1ኛ ቆሮንቶስ 1:24–29ን የሚያነብ ሰው “ሞኝ” (ወይም “ሞኝነት”) እና “ደካማ” (ወይም
“ድካም) የሚሉትን ቃላት ልብ ማለት አለበት። ቁም ነገሩ የሰው ጥበብ የመስቀሉን መልእክት
እንደ ሞኝነትና ድክመት ሊቆጥረው ይችላል። ነገር ግን፣ “ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር
ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና” (1ኛ ቆሮ. 1:25)።
ይህ ማለት እግዚአብሔር ደካማ ወይም ሞኝ ነው ማለት አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር
ኃይልና ጥበብ ከሰው ሁሉ እንዴት እንደሚበልጥ የሚያሳይ መግለጫ ብቻ ነው።
“እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፣ ኃያላን የሆኑ ብዙዎች፣ ባላባቶች
የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም” በሚለው ቃል ላይ ጊዜ እንውሰድ (1ኛ ቆሮ.
1:26)። ለእኛ ምን መልእክት አለው?
ኤለን ጂ. ኋይት፣ “የዘመናት ምኞት” “ቀራኒዮ” ገጽ 741–757።
“በአሁኑ ጊዜ ለሚኖሩ ብዙ ሰዎች አእምሮ፣ የቀራንዮ መስቀል በቅዱሳት ትዝታዎች
የተከበበ ነው። የተቀደሱ ማኅበራት ከስቅለቱ ትዕይንቶች ጋር የተቆራኙ ናቸው። ነገር ግን
በጳውሎስ ዘመን መስቀል ማለት በመጸየፍና በፍርሃት የሚመለከቱት ነገር ነበር። በመስቀል
ላይ ሞትን የተቀበለውን የሰው ልጅ አዳኝ አድርጎ መያዝ ማላገጫነትን እና ተቃውሞን በራስ
ላይ መጋበዝ ነበር።
“ጳውሎስ መልእክቱ በአይሁዶችም ሆነ በቆሮንቶስ ግሪኮች ዘንድ እንዴት እንደሚታይ
ጠንቅቆ ያውቃል። ... ከሚሰሙት አይሁድ መካከል እርሱ ሊሰብከው ባለው መልእክት
የሚናደዱ ብዙዎች ነበሩ፣ በግሪኮች ግምት ደግሞ፣ ቃሉ የእብድ የሚመስል ከንቱ ሞኝነት
ነበር። መስቀሉ ከሰው ዘር ከፍ መደረግ ወይም ከሰው ልጆች መዳን ጋር ግንኙነት እንዳለው
ለማሳየት ሲሞክር እንደ ደካማ አእምሮ ይቆጠር ነበር።
“ለጳውሎስ ግን መስቀሉ ከሁሉ የላቀ ትኩረት የሚሰጠው ነገር ነበር። የተሰቀለው የናዝሬቱ
የሱስ ተከታዮችን በማሳደድ ስራ ላይ ሳለ፣ በክርስቶስ ቁጥጥር ሥር ከዋለበት ጊዜ አንስቶ
የመስቀሉን ቃል ከፍ ከፍ ማድረግን አላቋረጠም። በዚያን ጊዜ በክርስቶስ ሞት እንደተገለጠው
ያለ የእግዚአብሔር ፍቅር መገለጥ ተሰጠው፤ ዕቅዶቹን ሁሉ ከሰማይ ጋር እስኪያስማማ
ድረስ በሕይወቱ አስደናቂ ለውጥ ሆነለት። ልጁን መሥዋዕት ያደረገበትን የአብን ፍቅር አንድ
ኃጢአተኛ አንድ ጊዜ ካየ እና ለመለኮት ተፅዕኖ እራሱን አሳልፎ ከሰጠ፣ ከዚያ በኋላ የልብ
መለወጥ እንሚሆንለት በግል ልምምዱ ያውቅ ነበር፤ እናም ከዚያ በኋላ ክርስቶስ ሁሉና
በሁሉ ነው” (ኤለን ጂ ኋይት፣ The Acts of the Apostles፣ ገጽ 245፣ 246)።
1.
በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ፣ የሱስ፣ “አባቴ ሆይ፣ ቢቻልስ ይህች ጽዋ
ከእኔ ትለፍ” (ማቴ. 26:39) አለ። ይህ ጸሎት የሱስ በመስቀል ላይ
ስለከፈለው እጅግ ታላቅ ዋጋ ምን ይነግረናል?
2. ጳውሎስ “ከሰዎች ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ጠቢብ ነው” (1ኛ
ቆሮ. 1:25) ይላል። የእግዚአብሔር ጥበብ ከሰው ጥበብ የሚለየው በምን
መንገዶች ነው?
3. የተሰቀለው የክርስቶስ መልእክት ለአይሁድ ማሰናከያ ለግሪኮችም ሞኝነት
ነበር። በዛሬው ጊዜ የምንሰብካቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጭብጦች በዘመናችን
ባሉ አድማጮች ዘንድ ተመሳሳይ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል? ለምን?
4. ጳውሎስ “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና
አይቀበለውም” ይላል (1ኛ ቆሮ. 2:14)። ታዲያ ስለ የሱስ ለእነዚህ ሰዎች
ልባቸውን በሚነካ መንገድ መናገር የምንችለው እንዴት ነው? ወይንስ
ተግባራችን ብቻውን ሊደርሳቸው ይችላል?