የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

1ኛ እና 2ኛ ቆሮንቶስ - የክርስቲያን ሕይወት እና ምስክርነት ባሕርይ



3ኛ ሩብ ዓመት 2026


ሰኔ 20 - 26

1ኛ ትምህርት

Jun 27 - Jul 3




የጳውሎስ አገልግሎት በቆሮንቶስ



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚነበቡ፦ 1ኛ ቆሮ. 1:1 ገላ. 1:1 የሐዋርያት ሥራ 17:16-34 1ኛ ቆሮ. 5:9–11፣ የሐዋርያት ሥራ 18:4–10፣ 2ኛ ቆሮ. 2:4።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ «ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን፡- እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው» (ሐዋ. 18:9፣ 10)።

ታላቁ እንግሊዛዊ ሚስዮናዊ ዊልያም ኬሪ ኑሮውን ለማሸነፍ ጫማ ይጠግን እንደነበር ይናገር ነበር፤ ነገር ግን እውነተኛው ስራው ነፍሳትን መማረክ ነበር።

በተመሳሳይ፣ ጳውሎስ ለኑሮው ድንኳን ሰፊ ሆኖ ሠርቷል (ሐዋ. 18:1-3)፣ ነገር ግን እውነተኛ ሥራው ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ማምጣት ነበር።

በዚህ ሳምንት፣ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከተማ በምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ስለነበረው አገልግሎት ፍንጭ እናገኛለን። እንደምናየው ቤተ ክርስቲያኒቱ በብዙ ችግሮች የተሞላች ነበረች፤ ቢሆንም ብዙዎቹ ችግሮች ከሁለት ሺህ ዓመታት በኋላ ዛሬ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ከሚገጥሟቸው ነገሮች የተለየ መልክ አልነበራቸውም። በእርግጥም በክርስትና ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየ ወይም በቤተ ክርስቲያን ሥራ ውስጥ የተካፈለ ማንኛውም ሰው የሚከተለውን ጥያቄ ሊጠይቅ ይችላል፦ ምንም ዓይነት ችግር የሌለበት የክርስቲያን ህብረት አግኝታችሁ ታውቃላችሁ? መልሱ በእርግጥ ግልጽ ነው።

ጳውሎስ በቆሮንቶስ ፈተናዎችን ይጋፈጥ ነበር፤ ነገር ግን ይህን የሚያደርገው በመስቀሉ መልእክት ነበር (1ኛ ቆሮ. 2:2)። ለዚህ መልእክት ታማኝ መሆን በዛሬው ጊዜ ያሉብንን ተግዳሮቶች የምንቋቋምበት መንገድም ነው። በዚህ ሳምንት እና በዚህ ሩብ ዓመት ውስጥ እንደምንመለከተው፣ የ1ኛ እና የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት በእኛም ሕይወት ላይ ይሠራል። ለሰኔ 28 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።

ሰኔ 21
Jun 28

የየሱስ ሐዋርያ ተብሎ የሚጠራው ጳውሎስ


ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጻፈውን መልእክት የጀመረው ‹በእግዚአብሔር ፈቃድ› የየሱስ ሐዋርያ መሆኑን በመግለጽ ነው (1ኛ ቆሮ. 1:1፤ ከ2ኛ ቆሮ. 1:1 ጋር አወዳድሩ)። ከየሱስ ጋር ባለው ማንነቱ ላይ ያለው እምነት በጣም ጽኑ ስለሆነ፣ ከጥቂቶች ሥፍራዎች በስተቀር ደብዳቤዎቹን የሚጀምረው በዚህ ዓይነት መንገድ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 1:1 እና ሮሜ 1:1ን አንብቡ። በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ ሁለት አጽንዖት የተሰጣቸው የጳውሎስ አገልግሎት ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? (ገላ. 1:1ን ተመልከቱ።)



ጳውሎስ ጥሪውና ሐዋርያነቱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም እንደሆነ ተናግሯል። ጥሪው ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው እንዳልሆነ እርግጠኛ ሆኗል (ገላ. 1:1)። እንደ ኤርምያስ ሁሉ (ኤር. 1: 5) ጳውሎስም እንደ እግዚአብሔር የጸጋ ሥራ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ በእግዚአብሔር ለጥሪው ተለይቷል (ገላ. 1: 15)፤ ስለዚህም የክርስቶስን ወንጌል በአሕዛብ መካከል እንዲሰብክ ሆነ።

በ1ኛ ቆሮንቶስ 15:8 ላይ፣ ጳውሎስ ራሱን ከትንሣኤ በኋላ ክርስቶስ ከተገለጠላቸው መካከል አንዱ እንደሆነ ይናገራል (1ኛ ቆሮ. 15:5-7)። ከጥቂት ጥቅሶች በኋላ፣ የሐዋርያነት ጥሪው የመጣው በዚያን ጊዜ ክርስቶስ ከተገለጠለት በኋላ መሆኑን ገልጿል (1ኛ ቆሮ. 15:9–11)።

“የየሱስ ሐዋርያ” የሚለው ማዕረግ ተከታታይ ጽንሰ-ሐሳቦችን ያካትታል። በዋነኛነት የሱስ የላከውን ሰው የመሆንን ሐሳብ ያስተላልፋል። ደግሞም፣ ጳውሎስ ራሱን የክርስቶስ አገልጋይ (ሮሜ 1:1፣ ቲቶ 1:1፣ ገላ. 1:10) ፣ እንዲሁም ሰባኪና አስተማሪ (1ጢሞ. 2:7፣ 2ጢሞ. 1:11) መሆኑን ለመግለጽ ይህን ሐረግ ይጠቀማል። ቢሰብክም ቢያስተምርም ክርስቶስ ምንጊዜም ማስረጃ ነው። በአጭሩ፣ ጳውሎስ የየሱስ ሐዋርያ ነው።

የሱስ የጳውሎስ ሐዋርያነት ማዕከል ብቻ አይደለም። እርሱ የጳውሎስ የሕይወቱ ማዕከልም ነው። የጳውሎስ ሀሳቦች እና ስሜቶች በየሱስ መገኘት ተሞልተዋል። ለዚህም ማስረጃው የሱስን በ1ኛ ቆሮንቶስ የመክፈቻ እና የምስጋና ክፍል (በዘጠኝ ቁጥሮች ዘጠኝ ጊዜ ማለት ነው) ደጋግሞ መናገሩ ነው። ጳውሎስ የሱስን በጣም ይወደው ስለነበር ስለ እርሱ ማሰብና መናገር ማቆም አልቻለም። በእርሱ እንክብካቤ ሥር ላሉትም፣ ሕይወታቸው ክርስቶስን ያማከለ ይሆን ዘንድ የሱስን ለማካፈል ይፈልግ ነበር። እርሱ ለሐዋርያነት ሲጠራ፣ እነርሱም ደግሞ ጌታ በጠራቸው በማናቸውም አገልግሎቶች ታማኝ የየሱስ ተከታዮች እንዲሆኑ ተጠርተዋል። ጳውሎስ ሐዋርያ እንዲሆን ተጠርቷል። እኛስ ጥሪያችን ምንድን ነው? ጥሪያችን መሆኑንስ እንዴት እናውቃለን? ጥሪ የሌለን ከመሰለን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ጉዞ ውስጥ ያለብን ችግር ምንድን ነው?

ሰኔ 22
Jun 29

ከአቴንስ እስከ ቆሮንቶስ


የሐዋርያት ሥራ 17:16–34ን አንብቡ። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ከመሄዱ በፊት የት ነበር? እዚያስ ምን አደረገ?



የሐዋርያት ሥራ 17:16–34 ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ከመሄዱ በፊት ለአቴናውያን የሰበከውን ስብከት ይገልጻል። በግልጽ፣ በዚያን ጊዜ አቴንስን ለመጎብኘት አላሰበም፣ ነገር ግን በቤርያ ባጋጠመው ተቃውሞ ምክንያት በአንዳንድ ጓደኞቹ እርዳታ ወደዚያ ሄደ (ሐዋ. 17:13–15)።

ከጳውሎስ ጋር ወደ አቴና የሄዱት ሰዎች፣ ጢሞቴዎስና ሲላስ በተቻለ ፍጥነት ወደ እርሱ በመሄድ አብረውት ይሆኑ ዘንድ ትእዛዝ ይዘውላቸው ወደ ቤርያ ተመለሱ (ሐዋ. 17:15)። የሐዋርያት ሥራ 17:16-34 ጳውሎስ ሲጠብቃቸው ሳለ ያደርግ ስለነበረው ነገር ይናገራል። ስለ የሱስ በምኩራብ፣ በገበያ ቦታና በአርዮስፋጎስ ተናግሯል። ስለ የሱስ መናገሩን ማቆም አልቻለም እናም ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞበታል። የሐዋርያት ሥራ 18:1-11ን አንብቡ። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሲደርስና በዚያች ከተማ በነበረው የቆይታ ጊዜ ሁሉ ምን አደረገ?



ጳውሎስ በሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወደ ቆሮንቶስ ሄደ። ጳውሎስ እዚያ አንድ ዓመት ተኩል እንደቆየ ሉቃስ ገልጾልናል።

እንደተለመደው፣ ጳውሎስ የሚስዮናዊነት ስራውን በምኩራብ ጀመረ (ሐዋ. 18:4-6)። የሐዋርያት ሥራ 17:1፣2 ይህ ልማዱ እንደሆነ ይጠቅሳል። የሱስ ለሐዋርያቱ እንዳዘዛቸው (የሐዋርያት ሥራ 1:8 ይመልከቱ) “በመጀመሪያ ለአይሁድ” የሚለውን ስልት (ሮሜ 1:16፣ የሐዋርያት ሥራ 13:46) ተከተለ።

በመጨረሻ ሲላስና ጢሞቴዎስ በቆሮንቶስ ከጳውሎስ ጋር ሲገናኙ፣ “የሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ለቃሉ ይተጋ ነበር።” (ሐዋ. 18:5)። በቆሮንቶስ በነበረው ቆይታ፣ “የእግዚአብሔርን ቃል በማስተማር” ተጠምዶ ነበር (ሐዋ. 18:11)። በዚህ አውድ ውስጥ ነበር በቆሮንቶስ ሰዎች መካከል ሳለ እነዚያን “ከየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደ ተሰቀለ” የሚሉ ዝነኛ የሆኑ ቃላቶችን በመጠቀም (1ኛ ቆሮ. 2:2) “ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና” ሲል የገለጸው። ጳውሎስ በአቴናና በቆሮንቶስ ካደረገው ሚስዮናዊ እንቅስቃሴ የሱስን ለማካፈል ሁሉንም ዕድሎችና ምቹ አጋጣሚዎች ስለ መጠቀም ምን እንማራለን? የሱስን ለሌሎች ለማካፈል ስላሏችሁ ዕድሎችና እንዴት ልትጠቀሙባቸው እንደምትችሉ አስቡ።

ሰኔ 23
Jun 30

የቆሮንቶስ ከተማ


የሐዋርያት ሥራ 18:1–3፣ 1 ቆሮንቶስ 5:9–11 እና 1 ቆሮንቶስ 8:4ን አንብቡ። ስለ ቆሮንቶስ ኢኮኖሚ፣ ሥነ ምግባር እና ሃይማኖታዊ ሕይወት ምን ማለት እንችላለን?



ቆሮንቶስ የጥንቱ ዓለም አስፈላጊ ማዕከል እንዲሁም በበለጸገ ንግድዋ የታወቀች ነበረች። ከተማዋ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ146 ዓመተ ዓለም በሮም ተደምስሳ የነበር ሲሆን፣ የሮማውያን ቅኝ ግዛት በመሆን እንደገና በጁሊየስ ቄሳር በ44 ዓመተ ዓለም ተገንብታለች። በአዲስ ኪዳን ውስጥ የምናገኛት ይህች ከተማ የሮም ቆሮንቶስ ናት ማለት ነው። በጳውሎስ ዘመን ቆሮንቶስ ከአቴንስ ተቀናቃኞች መካከል አንዷ የነበረች ሲሆን፤ እንዲያውም በተለያዩ ገጽታዎቿ ከሌሎች ትበልጥ ነበር። ቆሮንቶስ የንግድ ልውውጥን እና እንቅስቃሴን ቀላል የሚያደርጉ ሁለት ጠቃሚ ወደቦች ነበሯት።

በእርግጥም፣ ጳውሎስ ቆሮንቶስን የመረጠው በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥዋ ጠቃሚ እና አመቺ በመሆኗ ነው። “ስለዚህ ወንጌልን ለማዳረስ የሚያስችል አጋጣሚ ተፈጠረ። [ወንጌል] በቆሮንቶስ ከተቋቋመ በኋላ ለሁሉም የዓለም ክፍሎች በቀላሉ ለማዳረስ ይቻል ነበር” (ኤለን ጂ. ኋይት፣ Sketches From the Life of Paul, ገጽ. 99)።

እያበበ የነበረው የቆሮንቶስ ንግድ፣ ጳውሎስ በዚያ ከተማ ወንጌልን እየሰበከ ድንኳን በመስፋትና በመሸጥ ራሱን መደገፍ ቀላል እንዲሆንለት አድርጎታል። በአንድ ትልቅና የበለጸገ ከተማ ውስጥ የሚስዮናዊነት ሥራ ከችግር የጸዳ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ቆሮንቶስ በሃይማኖታዊ ብዝሃነቷ ተለይታ ትታወቅ ነበር (1ኛ ቆሮ. 8:5)፤ ይህም እንደ አፖሎ፣ አቴና፣ እና አፍሮዳይት ያሉ አማልክቶችን፣ እንዲሁም እንደ ሳራፒስ እና አይሲስ ያሉ ሌሎች የግብፅ አማልክትን ለማምለክ በተገነቡት በርካታ መቅደሶች በግልጽ ይታያል።

ከዚህ ሃይማኖታዊ ግራ መጋባት በተጨማሪ ቆሮንቶስ በጾታዊ ልቅነትዋ ትታወቅ ነበር። ግሪካዊው የጂኦግራፊ እና የታሪክ ምሁር ስትራቦ በቆሮንቶስ በሚገኘው ቤተ መቅደሷ ውስጥ ለአፍሮዳይት አምልኮ ያደሩ 1,000 ዝሙት አዳሪዎች እንደነበሩ ተናግሯል። ምንም እንኳን ብዙ ሊቃውንት ይህንን በጥርጣሬ ቢመለከቱትም እና አባባሉንም አቴናውያን በቆሮንቶስ ላይ ከሚያሰራጩት ፕሮፓጋንዳ ጋር ቢያገናኙም፣ በጥንቱ ዓለም ዝሙት አዳሪነት የተለመደ ነበር። ፆታዊ እርኩሰት እንደ ሌሎች ቦታዎች ሁሉ በቆሮንቶስም ችግር ነበር። ጣዖት አምልኮ እና ርኩሰት የዕለት ተዕለት ሕይወት አካል ነበሩ፣ እና ይህ አሳዛኝ እውነታ አብዛኛውን የአንደኛ እና ሁለተኛ ቆሮንቶስ መልእክት ይዘት ይገልጻል። ጳውሎስ በቆሮንቶስ በሚስዮናዊነት ባደረገው እንቅስቃሴ ከጣዖት አምላኪና ሴሰኛ ማኅበረሰብ ፈተና ገጥሞት ነበር። በዛሬው ጊዜ ባለው ባሕል ወንጌል መስበክን አስቸጋሪ የሚያደርጉት ተፈታታኝ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው? እንዴትስ ልናሸንፋቸው እንችላለን? ዛሬ በቆሮንቶስ እና በእኛ ከተሞች መካከል ምን ያህል ልዩነት አለ?

ሰኔ 24
Jul 1

"ብዙዎች በዚህች ከተማ ውስጥ"


የሐዋርያት ሥራ 18:4–8ን አንብቡ። የጳውሎስ ስብከት ውጤቶች ምን ነበሩ?





ጳውሎስ በቆሮንቶስ በነበሩት አይሁዶች መካከል ያከናወነው ሥራ የፈለገውን ያህል ፍሬያማ አልነበረም። አንዳንድ ጠላትነትን እና ጥላቻን መጋፈጥ ነበረበት። መጽሐፍ ቅዱስ “በተቃወሙትና በተሳደቡ ጊዜ” ይላል (የሐዋርያት ሥራ 18:6)። ‹ስድብ› (blasphēmeō) የሚለው የግሪክ ግስ የሚፈጸመው በሰው ላይ ሲሆን “በሚያዋርዱ ቃላት ማጥቃት” ወይም “ስም ማጥፋት” ማለት ነው። በሌላ አነጋገር የጳውሎስን ስም ለማጉደፍና የሚስዮናዊነት ሥራው እንዳይሳካ ለማድረግ አስበው ነበር ማለት ነው።

እንደ እድል ሆኖ፣ በቆሮንቶስ ምኩራብ ውስጥ የጳውሎስ ሥራ ከንቱ አልነበረም። ምንም ሆነ ምን፣ የተልእኮው ኃላፊ እግዚአብሔር ነበር። “[ቃሌ] የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም” (ኢሳ. 55:11) ሲል ቃል ገባ። አንዳንድ አይሁዶች የምኩራቡ አለቃ ቀርስጶስ እና ቤተሰቡ የሱስን መሲህ አድርገው እንደሚቀበሉና እንደሚጠመቁ አልጠበቁም ነበር (የሐዋርያት ሥራ 18:8)። እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ “ከቆሮንቶስ ሰዎች ብዙዎች ሰምተው አምነው ተጠመቁ” (የሐዋርያት ሥራ 18:8)፤ ይህ የሆነው ደግሞ ምናልባት በቀርስጶስ ተጽዕኖ ምክንያት ሊሆን ይችላል። የሐዋርያ ሥራ 18:9፣ 10ን አንብቡ። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ያጋጠሙትን ፈታኝ ሁኔታዎች በመጋፈጡ ስለተሰማው ስሜት ምን ማለት እንችላለን? እግዚአብሔር አገልጋዩን ያበረታው እንዴት ነበር?



ጳውሎስ ከምኵራብ ከወጣ በኋላ ወዲያውኑ የሚያበረታታ ተሞክሮ አግኝቶ ነበር። ክርስቶስ ራሱ ኢሳይያስ 41:10ን በመድገም፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ” ሲል በሌሊት ራእይ ተገለጠለት። በእርግጥም ጳውሎስ በቆሮንቶስ “በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥ” እንደነበረ ተናግሯል (1ኛ ቆሮ. 2:3)። ከባድ ተቃውሞ ስለገጠመው ከቤርያ ወደ አቴንስ መሄድ ነበረበት። በተመሳሳይ በከባድ ተቃውሞ ምክንያት ቆሮንቶስን ለቅቆ መውጣት እንዳለበት ያሰበ ይመስላል። ያን ጊዜ የሆነው ግን እንደዚያ አልነበረም። የሱስም እንዲህ አለው፦ “በዚህች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝ” (የሐዋርያት ሥራ 18:10)። ጳውሎስ የመዳንን ዜና ወደ እነርሱ ይዞ የሚሄድ የየሱስ መሳሪያ ነበር። ኢሳይያስ 41:10ን አንብቡ። በዚህ አጭር ክፍል ውስጥ ምን አስደናቂ ተስፋዎች ተሰጡን? በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?

ሰኔ 25
Jul 2

የጳውሎስ መልእክቶች ለቆሮንቶስ ሰዎች


1ኛ ቆሮንቶስ 1:11–13፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 4:14፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 5:11፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 7:1፤ እና 1ኛ ቆሮንቶስ 14:37፣ 40 እንዲሁም 2ኛ ቆሮንቶስ 1:12፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 2:9፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 11:3 እና 2ኛ ቆሮንቶስ 13:10ን አንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ደብዳቤ የጻፈው ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ የሚረዱን እንዴት ነው?



ጳውሎስ 1ኛ ቆሮንቶስን ሲጽፍ በኤፌሶን ነበር (1ኛ ቆሮ. 16:5–9)። እነርሱ በነበሩበት በቆሮንቶስ ነገሮች በጣም ጥሩ እንዳልነበሩ የቀሎዔ ቤተሰብ ወደ እርሱ መረጃውን ይዘው ሄዱ (1ኛ ቆሮ. 1:11)። በ1ኛ ቆሮንቶስ 1–6 ላይ፣ ጳውሎስ ቀሎዔ ይዛ ስለመጣችው ጉዳዮች ተናግሯል። ከችግሮቹ መካከል የቡድንተኝነት፣ የፆታ ብልግና፣ መካሰስ እና ዝሙት አዳሪነት ይገኙበታል። ጳውሎስ የተወሰኑ ጥያቄዎችን የያዘ ደብዳቤም ደርሶታል (1ኛ ቆሮ. 7:1)። የእርሱ ምላሽ ከምዕራፍ 7 ጀምሮ ያለውን ቦታ ይይዛል። ጥያቄዎቹ ከጋብቻ፣ ከፍቺ፣ ሳያገቡ ከመኖር፣ ለጣዖት ከተሠዋ ምግብ፣ ከአምልኮ ሥነ ምግባር፣ ከመንፈሳዊ ስጦታዎች አጠቃቀምና አንዲሁም ስለ ትንሣኤ ከነበረ የተሳሳተ ግንዛቤ ጋር የተያያዙ ነበሩ። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በጣም ችግር ያለባት እና ያልበሰለች ነበረች። አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችሁም ምናልባት ብዙ ችግሮች ሊኖሩባት ትችላላች። ሆኖም የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ግን ከዚህም የከፋች ነበረች።

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈው የመጀመሪያ መልእክት ለዘመናችንም ጠቃሚ ነው። ደግሞስ ዛሬም በተወሰነ ደረጃ በብዙ አብያተ ክርስትያኖቻችን ውስጥ አንዳንድ ተመሳሳይ ጉዳዮች አያጋጥሙንምን? ይህ ደብዳቤ ብዙ የሚነግረን አለው። እርሱ “ከጻፋቸው ደብዳቤዎች ሁሉ በመረጃ የዳበሩ፣ አስተማሪና በጣም ኃይለኛ ከሆኑት አንዱ ነው” (ኤለን ጂ. ኋይት፣ The Acts of the Apostles, ገጽ. 301)።

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሦስት ወይም አራት መልእክቶችን ጽፎ ሊሆን ይችላል (ከ2ቆሮ. 10:9 ጋር አወዳድሩ)። 1ኛ ቆሮንቶስን ከመጻፉ በፊት አንድ የመነሻ ደብዳቤ ጽፎ ነበር፣ ነገር ግን ጠፍቷል። ከ2ኛ ቆሮንቶስ በፊት ምሁራን “ከባድ ደብዳቤ” በማለት የገለጹትን ደብዳቤ ጽፏል (2ኛ ቆሮ. 2:3፣ 4፣ 9፤ 2ኛ ቆሮ. 7:8)፤ ይህም ደግሞ ጠፍቷል። አንዳንዶች እርሱ የሚናገረው ስለ 1ኛ ቆሮንቶስ ነው ወይም ይህ መልእክት በከፊል በ2ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ይገኛል ብለው ያስባሉ።

ከ2ኛ ቆሮንቶስ እንደምንረዳው፣ የቆሮንቶስ [ቤተ ክርስቲያን] አባላት በዙሪያው ባለው ባህል ተጽዕኖ ውስጥ እንደነበሩ እንገነዘባለን። ዛሬም ቤተ ክርስቲያናችንን ሊፈታተኑ ለሚችሉ እንደ ፉክክር፣ ሥልጣንና ሀብት የመሳሰሉ ነገሮች ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጡ ነበር። በተቃራኒው፣ ጳውሎስ በክርስቶስ ላይ ያተኮረ ባህል፣ ዓለም በወንጌል መነጽር የሚታይበትን መንገድ ለመፍጠር ይፈልግ ነበር። እኛም አሁን ያለንበትን ዓለም በወንጌል መነጽር መመልከታችን ምንኛ ወሳኝ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 2:4ን እንደገና አንብቡ። ጳውሎስ ለእነዚህ ሰዎች ምን ያህል ያስብላቸው እንደነበር ይህ ምን ይነግረናል? ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ የኛ ልብ ለሌሎች ምን ያህል ቀዝቃዛ ሊሆን ይችላል?

ሰኔ 26
Jul 3


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ. ኋይት፣ The Acts of the Apostles ውስት ከሚገኘው “ቆሮንቶስ” የሚለው ምዕራፍ ገጽ 243–254።

“ሐዋርያው በቆሮንቶስ ወንጌልን በሚሰብክበት ጊዜ፣ በአቴና ውስጥ ካሳየው ልፋት የተለየ አካሄድ ተከተለ።... ሰፊ ክርክርና ውይይት ላለማድረግ እንዲሁም በቆሮንቶስ ሰዎች መካከል ሳለ፣ ‘ከየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳያውቅ ቆርጦ’ ነበር” (ኤለን ጂ. ኋይት፣ The Acts of the Apostles ገጽ. 244)።

“ጳውሎስ የተወሰነ ስኬት ነበረው” ነገር ግን እዚያ ባገኛቸው ነገሮች ላይ ቤተ ክርስቲያን የመመስረትን ጥበብ አልወደደውም።

ቆሮንቶስ ላይ መድከም አጠራጣሪ ሆኖበት ከዚያ ወደሚሻል መስክ ሊወጣ ሲያስብ፥ ...እግዚአብሔርም በሌሊት ራእይ ተገለጠለትና፦ “አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር፥ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው።” ጳውሎስ ይህ በቆሮንቶስ ለመቆየት የተሰጠ ትእዛዝ እንደሆነና ጌታ በተዘራው ዘር ላይ እንደሚጨምር የሰጠው ዋስትና እንደሆነ ተረድቶታል።... ትልቅ ቤተ ክርስቲያን በየሱስ ክርስቶስ ባንዲራ ሥር ተተክሏል” (ኤለን ጂ. ኋይት፣ Sketches from the Life of Paul፣ ገጽ 106፣ 107)።

“ጳውሎስ በቆሮንቶስ አንድ ዓመት ከስድስት ወር እንደሠራ ተመዝግቧል። ጥረቱም በዚያ ከተማ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ...ቆሮንቶስን እንደ ዋና መሥሪያ ቤት አደረገው... በዚህ መንገድ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተነሥተዋል (ኤለን ጂ. ኋይት፣ Sketches from the Life of Paul፣ ገጽ 109)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ጳውሎስ የየሱስ ሐዋርያ እና ይህ ጥሪ ደግሞ ከእግዚአብሔር እንደሆነ እርግጠኛ ነበር። ማን እንደሆንን እና ጥሪያችን ምን እንደሆነ ማወቅ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?

2. ለአፍታ ያህል፣ ጳውሎስ በቆሮንቶስ የነበረውን የተልዕኮ ሥራ ትቶ ከተማዋን ለቆ መውጣት እንደሚሻል ተሰማው። ሃሳቡን እንዲቀይር ያደረገው ምንድን ነው? የወንጌል ተልዕኮን ፕሮጀክት መተው ስናስብ ይህ እንዴት ሊረዳን ይችላል?

3. ይህ ሁሉ ሆኖ ግን፣ መተው ያለብን ጊዜስ ይኖር ይሆን?

4. በቆሮንቶስ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አባላት በዙሪያው ባለው ባህል ተጽዕኖ ውስጥ እንደነበሩ ግልፅ ነው። ይህ ደግሞ ዛሬም በመካከላችን የሚታይ እውነታ ነው። “በዓለም ባለው ነገር ማለትም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮት፣ ስለ ገንዘብም መመካት” ተጽዕኖ ሳያድርብን (1ኛ ዮሐ 2: 16) በዓለም ውስጥ መሆን የምንችለው እንዴት ነው (ዮሐንስ 17: 11፣ 15)? ቤተ ክርስቲያናችን በዙሪያዋ ባለው ባህል አሉታዊ ተጽዕኖ ሥር የምትሆንባቸው ሌሎች መንገዶችስ ምን ምን ናቸው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL