የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ
ደብዳቤ መጻፍ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረ ነገር ግን ያልቀረ ተግባር ነው። እኛ ፊደሎች
የሚጻፉበትን መንገድ ብቻ ቀይረናል። አዎ፣ ወረቀት በማህበራዊ ሚዲያ ተተካ። ነገር
ግን፣ በይዘታቸው፣ ኢሜይሎች እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክ ፊደሎች መሠረታዊ በሆነ
መንገድ አንድ አይነት ተግባር ያከናውናሉ፤ ይህም መረጃን፣ ስሜትን እና ሀሳቦችን በማለዋወጥ
ሰዎችን ማገናኘት ነው።
ሰዎች ለምን ደብዳቤ ይጽፋሉ? መልሱ የሚናገሩት ነገር ስላላቸው ነው የሚል ሊሆን
ይችላል። ለሐዋርያው ጳውሎስም እንዲሁ ነበር። ብዙ የሚናገረው ቢኖረውም ሊያናግራቸው
ከሚፈልጋቸው ጋር ፊት ለፊት የመገናኘት ዕድል አልነበረውም።
ከዚያ ይልቅ አንደ ቆሮንቶስ ሰዎች ላሉት፣ አንዳንድ የቅዱሳት መጻሕፍት ጥልቅ እውነቶችን
የያዙ ደብዳቤዎችን ጻፈ። ከእነዚህም መካከል፦ “ከየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደ
ተሰቀለ በቀር ምንም እንዳላውቅ ቆርጬ ነበር” (1ኛ ቆሮ. 2፡2) እንዲሁም “የጌታችንን
የየሱስ ክርስቶስን ጸጋ አውቃችኋልና እርሱ ባለ ጠጋ ሳለ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች
ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ” የሚሉት ይገኙበታል (2ቆሮ. 8:9)። በ1ኛ ቆሮንቶስ 13
ላይ የሚገኘው አስደናቂ የፍቅር መዝሙርስ?
በሌላ በኩል፣ የጳውሎስን መልእክት ለቆሮንቶስ ሰዎች ያነበበ ማንኛውም ሰው ግራ
መጋባቱ የማይቀር ነው፤ ይህም ግራ መጋባት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉ እንደ ዝሙት
ባሉ አንዳንድ ጉልህ ችግሮች ብቻ ሳይሆን፣ በአባላቶቹ መካከል በነበረው ከንቱ መከፋፈል
አማካኝነት በተከሰተው መርዝ ምክንያት ጭምር ሊሆን ይችላል። ቤተ ክርስቲያናችሁ ፈታኝ
ጉዳዮች እንዳሉባት የምታስቡ ከሆነ፣ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ያጋጠመውን አለመግባባት ለማየት
ተዘጋጁ። ምናልባት የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችሁ ችግሮች እናንተ እንደምትገምቱት ጉልህ
ላይሆኑ ይችላሉ። ይልቁንም በቆሮንቶስ የነበሩት ነገሮች በጣም የከፉ እንደነበሩ ትገነዘባላችሁ።
በቆሮንቶስ የነበሩት ችግሮች አሳሳቢ እንደሆኑ ሁሉ፣ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጻፋቸው
ደብዳቤዎች ትኩረታችንን የሚስቡት ወደ ችግሮቹ ሳይሆን ነገር ግን ጳውሎስ ችግሮቹን በተጋፈጠበት
አስደናቂ መንገድ ላይ ነው። ምእመናን ከየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አንጻር ራሳቸውን፣ ባህሪያቸውንና
የአካባቢያቸውን ባህል እንዲገመግሙ በማሳሰብ የመስቀሉን መልእክት ከፍ ከፍ ያደርጋል።
በሌላ ስፍራ የሚገኘውን የጳውሎስን አነጋገር እዚህ ጋ እንጠቀምና፦ ከወንጌል መልእክት ያነሰ
ማንኛውም መመዘኛ “የተረገመ” እንደሆነ መታየት አለበት (ገላ. 1:8፣ 9)።
በጳውሎስ ዘመን፣ ቆሮንቶስ በሀብቷ እና በጠንካራ ንግዷ ዝነኛ ነበረች፤ ይህም ሁሉ
ደግሞ በወደቧ፣ በሥነ-ሕንጻዎቿ፣ በመርከብ ግንባታዎቿ እና በሸክላ ሥራዎቿ ምክንያት
ነበር። ከተማዋ ጠቃሚ የፋይናንስ ማዕከል ነበረች። ቢሆንም፣ በጾታ ብልግና፣ በሃይማኖታዊ
መደበላለቋ እና ለተለያዩ አማልክት በተሰየሙ መቅደሶችዋም ትታወቅ ነበር። በእርግጥም፣
በቆሮንቶስ የነበረው የዕለት ተዕለት ኑሮ መናፍቅ ከሆነው ከጣዖት አምልኮ ተለይቶ የሚታወቅ
አይደለም። ይህ ታሪካዊና ባሕላዊ ዳራ ጳውሎስ በዚያች ከተማ ስላሉት ክርስቲያኖች ዋና ዋና
ጉዳዮች እና በዚህም የተነሳ ለእነርሱ የሰጣቸውን ማሳሰቢያዎች እንድንገነዘብ ይረዳናል።
በዚህ ሩብ ዓመት፣ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የላከውን መልእክት እንቃኛለን። በእነዚህ
ሁለት አስደናቂ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ፣ ሐዋርያው የወንጌል መልእክትን ለክርስቲያን
ሕይወትና ምስክርነት አስፈላጊ፣ እንዲሁም ሌላው ነገር ሁሉ የሚዳኝበት መነጽር አድርጎ
አቅርቧል። ወደ መንግሥተ ሰማይ በምናደርገው ጉዞ እያንዳንዳችን በግለሰብ ሆነ በአጠቃላይ
በቤተ ክርስቲያን ደረጃ የሚያጋጥሙን ፈተናዎች ምንም ቢሆኑ፣ ለክርስቶስ በምናደርገው
ሥራ ውስጥ ላሉ በጣም ግራ የሚያጋቡ ጉዳዮች መልሱ ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈው “የሱስ
ክርስቶስ… እርሱም እንደ ተሰቀለ” የሚል ነው። (1ኛ ቆሮ. 2:2)
የሱስ በቅርቡ ይመጣል። ይህ ጊዜ በክርስቶስ ሆነን በላቀ አንድነት ውስጥ የምንኖርበት፣
ለመንፈስ ቅዱስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ክፍት የምንሆንበት፣ መንፈሳዊ ስጦታዎችን በትጋት
የምንጠቀምበት እና ከሞት ከተነሳው ጌታችን ጋር የበለጠ ጥልቅ ልምምድ የምናገኝበት ጊዜ
ነው። ጊዜው የእውነተኛ ክርስቲያናዊ አገልግሎት፣ በመጋቢነት እና በተልዕኮ ውስጥ የመሳተፍ፣
ከሐሰት ትምህርቶች ጋር መንፈሳዊ ውጊያ የማድረግና እንዲሁም በጸጋ፣ በፍቅር እና በኅብረት
የማደግ ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ እምነታችንን አጥብቀን የምንይዝበት እና ለመስቀሉ መልእክት
ታማኝ የምንሆንበትም ጊዜ ነው፤ እናም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈው መልእክት ይህን
እንድናደርግ የሚስተምረን ነው።
አዴኒልተን ታቫሬስ ደ አጉዋየር (ዶ/ር) በካቾይራ፣ ባሂያ፣ ብራዚል ውስጥ በሚገኘው፣ በሰሜን ምስራቅ
የአድቬንቲስት ኮሌጅ ውስጥ የአዲስ ኪዳን ትርጓሜ ፕሮፌሰር ናቸው፤ በዚያም ከ 2010 ጀምሮ
ሲያገለግሉ ቆይተዋል።