የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከኢያሱ መጽሐፍ የሚገኙ የእምነት ትምህርቶች



4ኛ ሩብ ዓመት 2025


ጥቅምት 29 - ህዳር 5

7ኛ ትምህርት

Nov 8 - 14




የመጨረሻ ታማኝነት፣ በጦርነት ቀጠና ውስጥ አምልኮ



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ኢያሱ 5:1-7፣ ዘጸ. 12:6፣ 1 ቆሮ. 5:7፣ ኢያሱ 8:30-35፣ ዘዳ. 8:11፣ 14፣ ዕብ. 9:11-12።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (ማቴዎስ 6፡33)

በዚህ ሳምንት እስራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር በገቡበት ወቅት፣ እራሳቸውን እንደገና ለጌታ ያስረከቡበትንና በአደጋ ውስጥ ሆነው እንኳን ይህንን ያደረጉባቸውን አንዳንድ ቁልፍ ጊዜያት እንመለከታለን።

ኢያሱ እስራኤላውያን በጠላት ቀጠና ውስጥ እንዲገረዙ በማድረግ(ኢያሱ 5፡ 1-9)፣ ሊመጣ በሚችለው አደጋ ውስጥ እንኳን ፋሲካ እንዲከበር በማድረግ (ኢያሱ 5፡10-12)፣ ድል በመንሣት ላይ ሳሉ መሠዊያ በመሥራት እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ በማድረግ (ኢያሱ 8፡30-35)፣ በእስራኤልም የነበሩት ሰባት ነገዶች ርስታቸውን ገና ሳይቀበሉ የእግዚአብሔርን ድንኳን በመትከል (ኢያሱ 18፡1-2) ምክንያታዊ ያልሆኑ የሚመስሉ ውሳኔዎችን ወሰነ።

በተጨናነቀ ህይወታችን ውስጥ፣ ህይወት በእኛ ላይ ለምታመጣቸው አጣዳፊ ነገሮች ትኩረት እንሰጣለን። ብዙ ጊዜ ለእግዚአብሔር ያለንን ቁርጠኝነት ለማደስ እና እሱ ላደረገልን እና በየቀኑ ስለሚያደርግልን ነገሮች ቆም ብለን ምስጋናችንን ለመግለጽ ጥራት ያለው ጊዜ ለመስጠት ስንቸገር እንታያለን። የጠዋት እና የማታ አምልኮ፣ እንዲሁም የቤተሰብ መሠዊያ፣ በእኛ ከልክ በላይ በተጨናነቀ፣ በምቾት ላይ በተመሰረተ፣እና ስኬትን መሰረት ባደረገው ህይወታችን ውስጥ ከአውድ ውጪ የሆኑ ይመስላሉ። ሆኖም ሁላችንም በልባችን ውስጥ፣ ከእግዚአብሔር እና ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር አብረን የምናሳልፋቸው ጊዜያት በውስን ጊዜያችን ውስጥ የምናሳልፋቸው ምርጥ ጊዜያት እንደሆኑ እናውቃለን። ለህዳር 5 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ጥቅምት 30
Nov 9

ቅድሚያ ለቃል ኪዳን


ኢያሱ 5:1-7ን ያንብቡ። በዚህ ልዩ የመውረስ ጊዜ እግዚአብሔር ኢያሱን የእስራኤልን ሁለተኛ ትውልድ እንዲገርዝ ያዘዘው ለምንድነው?



አገሪቱን ሰልለው የሰላዮቹ አበረታች ዘገባ ከተሰማ በኋላ እና ዮርዳኖስን በተአምር ከተሻገሩ በኋላ ከጠላት ጋር በአስቸኳይ ወደ ጦርነት እንደሚገቡ እንጠብቃለን። ሆኖም፣ ከወታደራዊ ወረራ የበለጠ ጠቃሚ ነገር ነበር፤ እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር የገቡት ቃል ኪዳን።

አዲሱ ትውልድ መሬቱን ለመውሰድ ከመውጣቱ በፊት፣ ከምድሪቱ ዋና ባለቤት ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ መረዳት ነበረበት።

የቃል ኪዳኑ መታደስ እስራኤልን በጸጋው እና በተአምሩ ዮርዳኖስን ላሻገረው ለእግዚአብሔር የተሰጠ ምላሽ ነበር።

ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ቃል ኪዳን ሁልጊዜ እሱ ላከናወነልን ነገር የምስጋና ምላሽ መሆን አለበት እንጂ፣ ከህጋዊ መስፈርቶች ጋር በመስማማት የተወሰነ ጥቅም ለማግኘት የመሞከር ድርጊት ሊሆን አይገባውም። (ይህ ተመሳሳይ ጽንሰ-ሐሳብ፣ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ በግልጽ እንደሚታየው ከአሕዛብ የተመለሱ ወንድሞች እንዲገረዙ አጥብቀው ከሚጠይቁት ጋር ላደረገው ትግል ወሳኝ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።) እስራኤል በታሪኳ ታላቁ ወታደራዊ ዘመቻ አፋፍ ላይ ነበረች፣ እና መላው ካምፑ በጦርነት ዝግጅት ይጠመዳል ብለን እንጠብቃለን። ነገር ግን በተለመደው መልኩ አልሆነም። ፈረሶችን ከማዘጋጀትና ሰይፍን ከመሳል ይልቅ አብዛኛውን ተዋጊ ሃይል ቢያንስ ለሶስት ቀናት ለጥቃት ያጋለጠ ሥርዓት ፈጸሙ።

ይህን ያደረጉት ከግብፅ ነፃ ካወጣቸው አምላካቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማክበር ነው። ለምን? ምክንያቱም ጦርነቱ የጌታ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። ድል እና ስኬትን የሚሰጣቸው እርሱ ነው። ኢየሱስ ተመሳሳዩን መሠረታዊ ሥርዓት በመጠኑም ቢሆን በተለየ ቃላት ተናግሯል፡ - “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (ማቴ. 6፡33)። ብዙ ጊዜ፣ የእለት ተእለት ኑሮአችን በብዙ አስፈላጊ ነገሮች አጣዳፊነት ጫና እየፈጠረብን በህይወታችን ውስጥ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ማለትም ለክርስቶስ ያለንን ቁርጠኝነት በየቀኑ ለማደስ ቅድሚያ መስጠትን እስከመርሳት እንደርሳለን። በይበልጥ “አስፈላጊ” በምንላቸው ጉዳዮች ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ጊዜ ችላ ያልንበትን ጊዜ እናስታውስ። ይህን ማድረግ ቀላል የሆነው ለምንድን ነው? እሱንስ ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

ህዳር 1
Nov 10

ፋሲካ


ኢያሱ የተስፋይቱን ምድር የመውረስ ከባድና ትልቅ ሥራ ቢኖርበትም ፋሲካን ለማክበር መምረጡ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ኢያሱ 5:10፣ ዘጸ. 12:6፣ ዘሌ. 23:5፣ ዘሁ. 28:16፣ ዘዳ. 16:4፣6ን ያንብቡ።



ከድሉ በፊት ያለው ሁለተኛው አስፈላጊ ተግባር ፋሲካን ማክበር ነበር።

ይህ የሚከናወነው በወሩ በአሥራ አራተኛው ቀን ምሽት በእግዚአብሔር የተሰጠውን መመሪያ በጥንቃቄ በማክበር ነበር። የፋሲካ በዓል ምሳሌያዊ ጠቀሜታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡ በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ የተከናወኑት ነገሮች ከግብጽ የወጡበትን ሁኔታ ያንጸባርቃሉ። ፋሲካ አሥረኛው መቅሠፍት በወረደበት ሌሊት (ዘጸአት 12) የእግዚአብሔር መልአክ በግብፅ ያሉትን በኵር ልጆች ሁሉ የገደለበትንና እስራኤላውያንን ያዳነበትን ጊዜ ትዝታ ይቀስቅሳል።

ይህን ተከትሎ ከግብፅ መውጣት፣ ቀይ ባህርን መሻገር እና በምድረ በዳ የተደረገው ጉዞ ተራ በተራ ቀጠሉ።

በተቃራኒው የሁለተኛው ትውልድ ታሪክ በምድረ በዳ ተጀምሮ፣ ዮርዳኖስን በመሻገር ቀጥሎ፣ ግርዛትን እና የፋሲካን አከባበርን በማካተት፣ የእስራኤል ጠላቶች በሆኑት የከነዓን ነዋሪዎች ላይ ሌላ ተአምራዊ የጌታ ጣልቃ ገብነት ወደ ሚጠበቅበት ወሳኝ ወቅት ያመራል። ከዚህ ቀደም ከተፈጸሙት ድርጊቶች ሁሉ ጋር የፋሲካ በዓል አከባበር በእስራኤል ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ መጀመሩን ይጠቁማል።

ደግሞም በመስዋዕቱ በግ ምሳሌነት የፋሲካ በዓል እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ መውጣታቸውን ያመለክታል። ነገር ግን ከኃጢአት ባርነት ነፃ ባወጣን በእግዚአብሔር በግ (ዮሐንስ 1:29፣ 36፤ 1 ቆሮ. 5:7፤ 1 ጴጥ. 1:18- 19) ፍጻሜውን እንደሚያገኝም አመልክቷል። ራሱን እንደ ዋናው መስዋዕት ከማቅረቡ በፊት፣ በጌታ ራት፣ ኢየሱስ ፋሲካን ወደ ሞቱ መታሰቢያነት ለወጠው (ማቴ. 26፡26-29፣ 1 ቆሮ. 11፡23-26)።

ነገር ግን፣ ፋሲካ እና የጌታ እራት የተዋጁት ሰዎች ወደ ሰማያዊት ከነዓን የሚያልፉበትን በማመላከት የበለጠ ክብር ያለውን እውነታ ያመለክታሉ።

ባለ ራእዩ ዮሐንስ ይህን ምሳሌያዊ የ“መሻገር” ክስተት 144,000ዎቹ በእግዚአብሔር ዙፋን(ዮሐ. ራዕይ 4:6 ፣ 7:9-10) ፊት የቀይ ባሕርና የዮርዳኖስ ወንዝ ምሳሌ በሆነው የብርጭቆ ባህር ላይ ሲመላለሱ እና የፋሲካ እና የጌታ እራት ምሳሌ የሆነውን፣ የበጉን ራት ሲያከብሩ ተመልክቷል (ማቴ. 26:29 ዮሐ.19፡9)። የጌታን እራት ላናከብር ብንችልም የመስቀሉን እውነታ ሁልጊዜ በፊታችን ልናቆይ የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ህዳር 2
Nov 11

የመታደስ መሠዊያዎች


ኢያሱን ለእግዚአብሔር መሠዊያ ለመሥራት ያነሳሳው ምን ነበር? ኢያሱ 8:30-31ን፣ ከዘዳ. 11:26-30፣ ዘዳ. 27፡2-10 ጋር ያነፃፅሩ።



በአባቶች ዘመን፣ መሠዊያዎች የጉዞአቸው ምልክት ሆነው ጥቅም ላይ ይውሉ ስለነበረ በእግዚአብሔር ቃል የተገባላቸውን ምድር የይገባኛል ጥያቄዎች የሚያሳዩ ተጨባጭ ምስሎች ሆነዋል። አሁን፣ እስራኤላውያን መሠዊያን በመሥራት ለአባቶች የተሰጣቸው ተስፋዎች ፍጻሜ መሆናቸውን መስክረዋል። በዚህ ሁኔታ፣ የመሠዊያው መተከል በሙሴ የተሰጠው መመሪያ ፍፃሜ ነው (ዘዳ. 11፡26-30፣ ዘዳ. 27፡2-10)።

ኢያሱ 8፡30-35 የመጽሐፉን አጠቃላይ ሥነ-መለኮታዊ መልእክት በመቅረጽ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል። እጅግ አሰቃቂ ከሆኑት የዓመፅ ታሪኮች አንዱን (ጦርነት) ፍጹም ከተለየ ነገር ጋር ማለትም ከቃል ኪዳን ማረጋገጫ ትዕይንት (አምልኮ) ጋር በማገናኘት ኢያሱ በመግቢያው ላይ በመጽሐፉ ውስጥ ከተጀመሩት በጣም አስፈላጊ ሥነ-መለኮታዊ ጭብጦች ወደ አንዱ ይወስደናል፤ ያም ኢያሱ እስራኤልን ወደ ቃል ኪዳናዊ ታዛዥነት ሕይወት የመምራት ግዴታ አለበት (ኢያሱ 1፡7)። ይህ ደግሞ በመጽሐፉ መጨረሻ ላይም ያለው የኢያሱ ምስል ነው (ኢያሱ 24)።

የጦርነትና የድል አድራጊነት አስፈላጊነት እንዳለ ሆኖ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ፦ ይህም ለአምላክ ሕግ መሥፈርቶች ታማኝ መሆን። ምድሪቱን መውረስ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያለው እቅድ አፈጻጸም እና የሰው ልጆች ሁሉ ወደ ነበረበት የመመለስ ግብ አንድ እርምጃ ብቻ ነው። ለኦሪት ትእዛዛት ታማኝ መሆን የሰውን ልጅ እጣ ፈንታ ከሚወስኑት ነገሮች አንዱ ነው። ኢያሱ የሕጉን ግልባጭ የጻፈው ከመሠዊያው ድንጋዮች በተለዩ በኖራ በተለጠፉ ትላልቅ ድንጋዮች ላይ ነው (ከዘዳ. 27፡2-8 ጋር ያነፃፅሩ)። ስለዚህ አሥርቱን ትእዛዛት የያዙት ድንጋዮች በመሰዊያው ላይ ካሉት ቦታዎች ለየት ብለው የተቀመጡት እስራኤላውያን በቃል ኪዳኑ ውስጥ ያሏቸውን መብቶችና ግዴታዎች ዘወትር ለማሳሰብ ነው።

ተልእኮው ከሌሎች ተልዕኮዎች ጋር የሰውን ልጅ ወደ እግዚአብሔር መታዘዝ የመመለስን ተልዕኮ ያነገበው የአዲስ ኪዳኑ ኢያሱ (ኢየሱስ) ጥላ ነው። ይህንን ግብ ለማሳካት ከክፉ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባት ነበረበት። ዋና ግቡ በእኛ ፈንታ ሆኖ የቃል ኪዳኑን መጠይቆችን ማሟላት ነበር፡- “በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በእርሱ ነውና፤ እኛም በእርሱ አማካኝነት ለእግዚአብሔር ክብር “አሜን” የምንለው በዚህ ምክንያት ነው።” (2ቆሮ. 1፡20)። በጥንቱ ጊዜ መሠዊያ ከመገንባት ጋር ተመሳሳይ የሆኑ አሁን ልንሰራቸው የምንችላቸው አንዳንድ መንፈሳዊ ልምምዶች የትኞቹ ናቸው?

ህዳር 3
Nov 12

በድንጋይ ላይ የተፃፈ


ኢያሱ 8:32-35ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የተገለጸው ድርጊት ትርጉም ምንድን ነው? በዛሬው ጊዜስ ምን ይነግረናል?



የጌባል ተራራ በዘዳግም 11፡29፣ ዘዳ. 27፡4፣ 13 እና በኢያሱ መጽሐፍ (ኢያሱ 8፡30፣ 33) ብቻ ተጠቅሷል። ልክ እንደ ገሪዚም የቃል ኪዳኑ በረከትና እርግማን የሚነበብበት ቦታ ነበር። በተለይ በዘዳግም 11:29 እና በዘዳግም 27:4፣ 13 መሠረት እርግማኑ የሚነገርባት ቦታ ነበረች። በዚህ ስፍራ እስራኤላውያን በካህናቱ ፊት በታቦቱ በሁለቱም በኩል ይቆሙ ነበር (ኢያ. 8፡ 33)። አንደኛው ቡድን በጌባል ተራራ ፊት ለፊት፣ ሌላው በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት ይቆም ነበር። እዚህ ላይ ከቃል ኪዳኑ ጋር ሊገናኙ የሚችሉ ሁለቱን መንገዶች በምሳሌያዊ ሁኔታ አጽድቀዋል። በዚያ የሚቀርቡት መስዋዕቶች የሚያመለክቱት በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ በረከቱን ይቀበሉ ዘንድ የቃል ኪዳኑን እርግማኖች ሁሉ ወደ ወሰደው ወደ ኢየሱስ ነበር (ገላ. 3፡13፣ 2 ቆሮ. 5፡21)። የቃል ኪዳኑን ግልባጭ በመታሰቢያ ሐውልት ላይ መጻፍ ለምን አስፈለገ? (ዘዳ. 4:31፣ ዘዳ. 6:12፣ ዘዳ. 8:11፣ 14፣ 2 ነገስት 17:38፣ መዝ. 78:7 ያንብቡ።)



እኛ ሰዎች የምንረሳ ነን። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውን ግራ የሚያጋቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ፍላጎቶችን ወደ አጭር የጊዜ ክፍሎች ጨምረናቸው እንወጠራለን። ቶሎ ቶሎ የማይደጋገሙ ነገሮችን መርሳታችን አይቀሬ ሆኗል። በእያንዳንዱ የጌታ ራት አገልግሎት ራሳችንን ለጌታ የምንቀድስበት እና ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት ልዩ አጋጣሚ አለን። እነዚህን እድሎች እንደ ግለሰብ ዳግም የመቀደስ እድል ብቻ ሳይሆን እንደ ህብረት የምናድስበት አጋጣሚዎችም እንደሆኑ ብናስተውላቸው መልካም ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ግለሰባዊነትን እየጨመረ በመጣው ማህበረሰብ ውስጥ፣ ተመሳሳይ የአለም እይታ፣ ተመሳሳይ እሴቶች እምነቶች፣ እና ተመሳሳይ ተልዕኮ ያለው ማህበረሰብ አባል የመሆንን ሃይል እንደገና ማግኘት አለብን። በህይወት ጥድፊያ እና እምብርት ውስጥ፣ ጌታን መርሳት እና ነገሮችን በራሳችን ሀይል እና አቅም ለመስራት መፈለግ ምን ያህል ቀልሎን ይሆን? በተለይ ነገሮች በመልካም በሚሄዱበት ወቅት ይህን ማድረግ ቀላል የሚሆንልን ለምንድነው?

ህዳር 4
Nov 13

የእርሱን መገኘት መናፈቅ


ኢያሱ 18:1-2ን ያንብቡ። ኢያሱ ምድሪቱን የመከፋፈል ሂደቱ እንዲቋረጥ አድርጎ እንዲከናወን ያደረገው ተግባር ምን ነበር?



ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ላሉት ለሁለቱ ታላላቅ ነገዶች እና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ከተሰጡት ግዛቶች መግለጫ በኋላ ይህ ክፍል በሴሎ የሚገኘውን ጉባኤ የሚያሳይ ሲሆን ምድሪቱ ለቀሩት ሰባት ትናንሽ ነገዶች የተከፋፈለችበትን ታሪክ ይናገራል።

“መቅደሴ” የተሰኘው መቅደሱ መቋቋም፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ለመኖር የገባውን ቃል መፈጸምን የሚወክል ሲሆን (ዘፀ. 25:8፣ ዘሌ. 26:11-12) የመጽሐፉን ዋና ጭብጥ ማለትም፡ የእግዚአብሔር በእስራኤል መካከል መገኘት ምድሪቱን ርስት ለማድረግ አስችሎታል እናም ለእስራኤልና በእነርሱ በኩል ለምድር ሁሉ የበረከት ምንጭ ይሆናል (ዘፍ. 12:3) የሚለውን ይገልፃል። ምድርን ከመውረርና ከመከፋፈልም በላይ የእግዚአብሔር አምልኮ ዋና ደረጃ እና የላቀ ቦታ ይይዛል! ቤተ መቅደሱ ሰዎች በመካከላቸው የእግዚአብሔርን መገኘት እና ቃል ኪዳኑን የመከተል ግዴታቸውን እንዲገነዘቡ መርዳት ነበረበት። ዕብራውያን 6:19-20፣ ዕብራውያን 9:11-12፣ እና ዕብራውያን 10፡19-23ን ያንብቡ። በመካከላችን የእግዚአብሔርን አካላዊ መገኘት የሚገልጽ ምድራዊ መቅደስ የሌለን ክርስቲያኖች ከኢያሱ ምን እንማራለን?



የመቅደሱ መምጣት ድንገተኛ ሊሆንብን አይገባም፣ ምክንያቱም የመቅደሱ ጭብጥ በኢያሱ ትረካ ውስጥ በቃል ኪዳኑ ታቦት በኩል ስለሚገኝ ነው። ይህ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ያለው ማዕከላዊ ዕቃ ነበር፣ እናም የመጽሐፉን የመጀመሪያዎቹን ሁለት ክፍሎች ማለትም መሻገሩን እና ምድሪቱን መውረስን ያሳያል። ኢያሱ የማደሪያውን ድንኳን በምድሪቱ ዋና ቦታ ላይ መትከሉ የእስራኤል ሕይወት በሙሉ የይሖዋ ምድራዊ ዋና መሥሪያ ቤት በሆነው በመቅደሱ ዙሪያ እንደሚያጠነጥን ያሳያል።

በስርየት ቀን የምንኖር ክርስቲያኖች፣ እምነታችንን፣ ተስፋችንን እና መንፈሳዊ ውርሳችንን ከሚፈታተኑት ከዘመናችን (ወይም ከድህረ ዘመናዊ) ግዙፎች ጋር ትግላችንን ስንቀጥል ዓይኖቻችንን በሰማያዊው መቅደስ ላይ ማተኮር ለእኛ የበለጠ አስፈላጊ ነው። በመስቀሉ እና በሰማያዊው መቅደስ ውስጥ በተከናወነው የክርስቶስ ስራ ላይ ዘወትር ስንታመን፣ እግዚአብሔር በህዝቡ መካከል ያውም ለዘላለም የሚኖርበትን ጊዜ በእምነት እንጠባበቃለን።

(ከራእይ 21:3 ጋር ያነፃፅሩ።)

ህዳር 5
Nov 14


ተጨማሪ ሀሳብ


የኃይማኖት አባቶች እና ነብያት ከሚለው መጽሐፍ “በረከቶች እና እርግማኖች” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ ያንብቡ።

“ሙሴ በሰጠው መመሪያ መሠረት በጌባል ተራራ ላይ የታላላቅ ድንጋዮች ሐውልት ተተከለ። በእነዚህ ድንጋዮች ላይ ቀደም ሲል በጄሶ መሸፈኛ ተዘጋጅቶ ሕጉ ተጽፏል - በሲና የተነገሩትና በድንጋይ ጽላቶች ላይ የተቀረጹት አሥሩ ትእዛዛት ብቻ ሳይሆኑ ለሙሴ የተነገሩት ሕጎችም ተካተው ነበር። ከዚህ ሀውልት አጠገብ ለጌታ መስዋዕት የሚቀርብበት ከድንጋይ የተሰራ መሰውያ ነበር። መሠዊያው የእርግማን ተራራ በሆነው በኤባል ተራራ ላይ መቆሙ ትልቅ ትርጉም ነበረው፤ ይህም የአምላክን ሕግ በመተላለፍ ምክንያት እስራኤል ቁጣውን እንደተቀበለና ወዲያውኑም ክርስቶስ ሊያስተሰርይ እንደገና እንደሚጎበኘው ያሳያል፡ ይህም በመሥዋዕቱ መሠዊያ ተመስሏል።” የኃይማኖት አባቶችና ነብያት፣ ገጽ 500

“ቅዱስ ቁርባን የሐዘን መግለጫ ጊዜ አይደለም። የጌታ ደቀመዛሙርት ለጌታ ራት በተሰበሰቡ ጊዜ ድክመታቸውን ማስታወስና መተከዝ የለባቸውም። ደግሞ ባለፈው መጥፎ ሃይማኖታዊ ኑሮአቸው ላይ ማተኮር አይገባቸውም። በእነርሱና በወንድሞቻቸው መካከል ያለውን ልዩነት ማስታወስ አይኖርባቸውም። ይህ ሁሉ በቅድመ ዝግጅቱ ማለትም በእግር እጥበት አገልግሎት ጊዜ መጠናቀቅ ያለበት ነው። ራስን መመርመር ኃጢአትን መናዘዝና በመካከል ያለን አለመግባባት ማስወገድ ቀደም ብሎ በቅድመ ዝግጅቱ ጊዜ መፈፀም አለበት። ምዕመናን ለቅዱስ ቁርባን የሚመጡት ከክርስቶስ ጋር ለመገናኘት ነው። ምዕመናኑ የሚሰበሰቡት የመስቀሉ ጥላ እንዲወድቅባቸው ሳይሆን የመስቀሉን የማዳን ኃይል ለመቀበል ነው።

ከጽድቅ ፀሐይ የሚፈነጥቀውን ብርሃን ለማስገባት የነፍሳቸውን በር መክፈት አለባቸው።” የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 694 (በአማርኛው)


የመወያያ ጥያቄዎች




1. አስቀድሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት መፈለግ ለእርስዎ ምን ማለት አስቀድሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት መፈለግ ለእርስዎ ምን ማለት ነው? ይህ መሠረታዊ መርህ የዕለት ተዕለት ሕይወትዎን የሚቀርፀው እንዴት ነው?

2. በእለት ተዕለት የኑሮ ጥድፊያ ውስጥ ጌታን መርሳት ምን ያህል ቀላል በእለት ተዕለት የኑሮ ጥድፊያ ውስጥ ጌታን መርሳት ምን ያህል ቀላል እንደሆነ ለረቡዕ ክፍል የመጨረሻ ጥያቄ የሰጡትን መልስ ይመልከቱ። በክፍልዎ ውስጥ ይህን ማድረግ ለምን ቀላል እንደሆነ ይወያዩ። መፍትሄዎቹስ ምንድን ናቸው?

3. እንደ አድቬንቲስትነታችን፣ ኢየሱስ በእኛ ምትክ በሰማያዊው መቅደስ እንደ አድቬንቲስትነታችን፣ ኢየሱስ በእኛ ምትክ በሰማያዊው መቅደስ እያገለገለ እንደሆነ እናምናለን። ይህ እምነት የማያቋርጥ የተስፋና የብርታት ምንጭ ሊሆነን የሚችለው እንዴት ነው? በተለይ በአሁኑ ጊዜ በሥርየት ቀን ውስጥ ‘የሚማልደው’ (ዕብ. 7:25) ኢየሱስ መሆኑን ማወቃችን በሰማያዊው መቅደስ ውስጥ የሚሠራው ሥራ ምን ዓይነት የምሥራች እንደሆነ እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL