የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከኢያሱ መጽሐፍ የሚገኙ የእምነት ትምህርቶች



4ኛ ሩብ ዓመት 2025


ጥቅምት 22 - 28

6ኛ ትምህርት

Nov 1 - 7




በውስጥ ያለው ጠላት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1 ጴጥ. 1:4፣ ኢያሱ 7፣ መዝ. 139፡1-16፣ ዕዝራ 10፡11፣ ሉቃ 12፡15፣ ኢያሱ. 8፡1-29።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ።” (ኤርምያስ 17፡10)

የእስራኤል ህዝብ የቃል ኪዳኑን ረዥም ርቀት የሚጓዝ መዘዝ እና ጥልቅ ትርጉሙን የተማሩበት የመጀመሪያው ምሳሌ የሚገኘው ኢያሱ 7 ላይ ነው። የቃል ኪዳኑን መመሪያዎች መታዘዝ ድልን ቢያረጋግጥም፣ አለመታዘዝ ደግሞ ሽንፈትን አስከትሏል። የእስራኤል ወታደራዊ ስኬት የተመሠረተው በቁጥራቸው፣ በውጊያ ስልታቸው ወይም በብልሃታቸው ሳይሆን መለኮታዊው ተዋጊ ከእነርሱ ጋር በመኖሩ ነበር።

የተስፋይቱ ምድር በተያዘችበት ወቅት የእስራኤል በጣም አደገኛ ጠላት ከጦር ሰፈራቸው ውጭ ሳይሆን በራሳቸው ውስጥ እንዳለ በከባድ መንገድ መማር ነበረባቸው። ከፊታቸው ተደቅኖ የነበረው ትልቁ ፈተና የከነዓናውያን ከተሞች የተመሸጉ ግንቦች ወይም የላቁ የውትድርና ቴክኖሎጅዎች ሳይሆኑ በራሳቸው ካምፕ ውስጥ የጌታ መመሪያዎች ችላ እንዲባሉ ግትር አቋም የነበራቸው ግለሰቦች ነበሩ።

እኛም ሰማያዊውን ውርሳችንን ስንጠባበቅ (1 ጴጥ. 1:4፣ ቆላ. 3:24) ተመሳሳይ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። በተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ሆነን ታማኝነታችን ሲፈተን፣ ድል መንሳት የምንችለው ለኢየሱስ ክርስቶስ በመገዛት ብቻ ነው። ለጥቅምት 30 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ጥቅምት 23
Nov 2

የቃል ኪዳኑ መጣስ


ኢያሱ 7ን ያንብቡ። እስራኤላውያን በጋይ ነዋሪዎች የተሸነፉባቸው ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ምን ምን ነበሩ?



አንባቢው ከመጀመሪያው ጀምሮ የያህዌ ቁጣ የወረደበትን ምክንያት እንዲሁም የጥፋተኛውን ስም ማወቁ አስገራሚ ነው። ስለዚህ፣ የአካንን በደል የማጋለጡ ታሪክ ልብ አንጠልጣይ የሚሆነው በአንባቢው፣ በኢያሱ እና በእስራኤላውያን እይታ መካከል ባለው ውጥረት ነው። ልክ እንደ ሌሎች የብሉይ ኪዳን ምዕራፎች፣ ኢያሱ 7 የካያስቲክ መዋቅር አለው። በውስጡ ያለው ማዕከላዊ እና ከፍተኛ የጡዘት ክፍል እስራኤላውያን በመጀመሪያ ሙከራቸው ጋይን ለምን ማሸነፍ አልቻሉም? ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

እስራኤላውያን በጋይ የተሸነፉባቸው ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነበሩ፦ እነርሱም አንደኛው የአካን ኃጢአት እና እስራኤላውያን በራሳቸው ጥንካሬ ከሚገባው በላይ መተማመናቸው ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በጋይ ላይ ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት የጌታን ፈቃድ መጠየቅን ቸል ማለት እና የጠላትን ኃይል ማቃለል ነበር።

በኢያሱ 7:1፣ 11–13 ላይ በመመስረት፣ አካን መመሪያውን በመጣስ ክህደት ተጠያቂ ቢሆንም ሕዝቡ ሁሉ ተጠያቂ እንደሆነና መከራ ሲደርስበት እንመለከታለን። እግዚአብሔር የአካን ኃጢአትን ክብደት ቀስ በቀስ በማሳየት በቁጥር 11 ላይ “እንኳ” ወይም “እንዲሁም” በማለት ገልጿል። በመጀመሪያ፣ በጣም የተለመደው የኃጢአት ቃል ጥቅም ላይ ይውላል፡- “ካታ”። ከዚያም የበደል ድርጊት በጋም ተውላጠ ተውሳክ በተካተቱት አምስት ተጨማሪ ኃጢአቶች ይገለጻል፡- (1) ‘አባር፣ እንዲሁም “መሻገር፣ መተላለፍ፣” (2) እንዲጠፉ የተባሉትን ነገሮች (ኬረም)እንኳ መውሰድ (ላቃክ) (3) እንዲሁም መስረቅ (ጋናብ)፣ (4) እንዲሁም ማታለል (ካካሽ)፣ እና (5) የተሰረቀውን ዕቃ (ሲም) ከራስ እቃ ጋር ማስቀመጥ ናቸው።

በያህዌ እና በእስራኤል መካከል የተገባው ቃል ኪዳን ህዝቡን በግለሰብ እና በድርጅት ደረጃ ያሳተፈ ነበር። በቃል ኪዳኑ ብርሃን፣ እስራኤል እንደ እግዚአብሔር የተመረጠ ሕዝብ የማይከፋፈል አንድነት ያለው ነው። ስለዚህ፣ የአንዱ፣ ወይም እንዲያውም የአንዳንዶቹ፣ አባላቶቹ ኃጢአት በመላው የቃል ኪዳኑ ማህበረሰብ ላይ ጥፋተኝነትን ያመጣል። እግዚአብሔር እንደተናገረው፦ እስራኤል በድሎአል፤ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፤” (ኢያሱ. 7፡11) በማህበረሰቡ ውስጥ ባሉ ግለሰቦች መጥፎ ድርጊቶች መላው ማህበረሰብ የሚሰቃዩበት እና የሚሰቃዩባቸው መንገዶች ምንድናቸው? የትኞቹን እንደዚህ አይነት ምሳሌዎች ሊያስቡ ይችላሉ እና ማህበረሰቡ ተጽዕኖ የደረሰበት እንዴት ነበር?

ጥቅምት 24
Nov 3

የአካን ኃጢአት


ኢያሱ 7:16-19ን ያንብቡ። አጠቃላይ ሂደቱ ስለ እግዚአብሔርም ሆነ ስለ አካን ምን ይነግረናል?



እግዚአብሔር የበደለኛውን ማንነት ከመግለጥ ይልቅ ፍትሃዊውን እና ፀጋውን የሚገልጥ አሰራርን ዘረጋ። እስራኤላውያን የተሸነፉበትን ምክንያት ከገለጸ እና ሕዝቡ እንዲቀደስ ጥሪ ካቀረበ በኋላ (ኢያሱ 7:13) አካን እንዲያስብ፣ እንዲጸጸት እና ኃጢአቱን ለመናዘዝ ጊዜ እንዲያገኝ ሂደቱን በመናገር እና በአተገባበሩ መካከል ያለውን ጊዜ ፈቀደ። በተመሳሳይ መልኩ ቤተሰቦቹ (የሆነውን የሚያውቁ ከሆነ) ከአባታቸው ጋር ለመወገን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከጥፋት እንደተረፉት እንደ ቆሬ ልጆች ኃጢአትን በመሽፈን ውስጥ የመተባበር ወይም ተባባሪ ያለመሆን እድል ነበራቸው (ዘሁ. 16:23-33 ፣ ዘሁ. 26:11)። የችግሩ መፍትሄ እርግማኑ ወደ እስራኤል የገባበትን እና ያስስጨነቀበትን መንገድ ተቃራኒ አቅጣጫ ተከትሏል፤ የህዝቡ ጥፋተኝነት ተወግዶ ከእስራኤል ሕዝብ ወደ አንድ ነገድ እየጠበበ መጣ፤ ከነገድ ወደ ቤተሰብ፣ ከቤተሰብ ወደ ቤት እና ከቤት ወደ ግለሰብ ደረሰ። ወንጀለኛውን ከማጋለጥ በተጨማሪ የምርመራ ሂደቱ ንፁሃንንም ንጽህናቸውን አረጋግጧል። ይህም (ንፁሃንን መለየቱ) እግዚአብሔር ራሱ ለአካን ድብቅ ድርጊቶች ምስክር ሆኖ በሰራበት ጥንቃቄ የተሞላበት የፍርድ ሂደት በእኩል ደረጃ አስፈላጊ ነበር።

እግዚአብሔር ወደ አካን ሲደርስ አንባቢው ውጥረቱ ሊሰማው ይችላል። ሰውዬው አይታወቅብኝም ብሎ በማሰብ በግትርነት በመፅናቱ ያልተገረመ ማን አለ? ወደ ውስጥ ጠልቀው ከሚገቡ የእግዚአብሔር ዓይኖች የተሰወረ ምንም ነገር የለም (መዝ. 139፡1-16፣ 2ኛ ዜና. 16፡9)፤ በሰው ልብ ውስጥ የተደበቀውንም ያውቃል (1 ሳሙ. 16፡7፣ ኤር. 17፡10፣ ምሳ. 5፡21)።

ኢያሱ አካንን “ልጄ” ብሎ የተናገረበትን መንገድ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይህ አገላለጽ የኢያሱን ዕድሜ እና የመሪነት ሚና ብቻ ሳይሆን ይህ ታላቅ ተዋጊ ፍትህን ሊያደርግ የተዘጋጀበትን መንፈስም ያሳያል። በደለኛው ላይ ፍርድ እንዲፈጽም ቢታዘዝም ልቡ ለአካን በጣም አዘነ። ኢያሱ በአመለካከቱ “ክብረ ነክ ያልሆነ፣ ክፉ ቃልን በከንቱ የማይናገር፣ የተሸበረች ነፍስን አላስፈላጊ ሥቃይ ውስጥ የማይከት… ሆኖ ሳለ ያለ ፍርሃት ግብዝነትን፣አለማመንን፣ እና አመፅን የሚገስፅ ነበር። ነገር ግን በድምፁ ውስጥ ሀዘንን የቀላቀለ ተግሳፅ ይነበባል።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ. 353. እግዚአብሔር የምናደርገውን ሁሉ የተደበቁ ነገሮቻችንን እንኳ እንደሚያውቅ ማወቁ፣ አኗኗራችን ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ያለው እንዴት ነው? ይህ በአኗኗራችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚገባውስ እንዴት ነው?

ጥቅምት 25
Nov 4

እጣ ፈንታን የሚወስኑ ምርጫዎች


ኢያሱ 7:19-21ን አንብብ። ኢያሱ አካንን ምን እንዲያደርግ እየጠየቀው ነው? የዚህ ዓይነቱ ጥያቄ ጠቀሜታ ምንድነው? የእርሱን ኑዛዜ እንዴት እንረዳዋለን?





ኢያሱ አካንን ሁለት ነገሮችን እንዲያደርግ ጠየቀው፡- በመጀመሪያ፡ ለእግዚአብሔር ክብር እንዲሰጥ እና እንዲያከብረው፤ ሁለተኛ፡ የሰራውን ሳይደብቅ እንዲናዘዝ። አካን ያደረገውን በማመን ለእግዚአብሔር ክብር መስጠት ነበረበት። እዚህ (ቶዳህ) የሚለው ቃል ምስጋናን ሊያመለክት ይችላል (መዝ. 26፡7፣ ኢሳ. 51፡3፣ ኤር. 17፡26)፣ ነገር ግን የኃጢአት ኑዛዜንም ሊገልፅ ይችላል (ዕዝራ 10፡11)።

እንደ አለመታደል ሆኖ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አካን የእውነተኛ ንስሐ ምልክት እንዳሳየ አልተፃፈም። እስከ መጨረሻው ድረስ ተደብቆ እንደሚቆይ ተስፋ አድርጓል። የእሱ የክህደት ዝንባሌ እንደ ሙሴ ህግ ስርየት እንደሌለው ከፍተኛ ወንጀለኛ ለመቆጠር ብቁ አድርጎታል (ከዘኁ. 15፡27-31 ጋር ያነፃፅሩ)።

በኢያሱ 7፡21 ላይ ያለው የአካን ቃል የአዳምንና የሔዋንን ውድቀት የሚያስታውስ ነው። ሔዋን (ራአ) ዛፉ ያማረ(ካማድ) እንደሆነ አየች በመጨረሻም ከፍሬው ወሰደች(ላቃክ)። አካን በኑዛዜው ላይ በብዝበዛው ወቅት የሚያምር የሰናዖር ካባ፣ 200 ሰቅል ብር እና አንድ አሞሌ ወርቅ እንዳየ(ራዓ) ተናግሯል። ከዚያም ተመኘ (ካማድ) እና ወሰዳቸው(ላቃህ)።

ልክ እንደ አዳምና ሔዋን፣ የአካን ምርጫ የመጎምጀትና የአለማመን ኃጢአት መሆኑን ያሳያል። ይህ የአካን ምርጫ እግዚአብሔር ለፍጥረታቱ መልካሙን እንደማይፈልግ እና የመለኮት ብቻ የሆኑትን አንዳንድ አስደሳች ነገሮች እንደሚደብቅብን እንድንጠራጠር ያደርጋል።

የመጀመሪያው የሰው ልጅ ውድቀት እንዳለ ሆኖ ጥቅሱ በረዓብ (ከኢያሱ 2፡1-13 ጋር ያነፃፀሩ) እና በአካን አመለካከት መካከል ያለውን ልዩነት ያሳያል። አንዷ ሰላዮቹን ወደ ጣሪያዋ ወስዳ በመደበቅ ከወታደሮቹ አስመለጠቻቸው፤ ሌላው የተከለከሉትን ነገሮች ወስዶ ከኢያሱ ደበቀው።

አንዷ ለእስራኤላውያን ሰላዮች ደግነት አሳይታ ድል እንዲቀዳጁ ረዳች፤ ሌላው በስግብግብነቱ በእስራኤል ላይ ችግር በማምጣት እንዲሸነፉ አደረጋቸው።

አንዷ ከእስራኤላውያን ጋር ቃል ኪዳን አደረገች፤ ሌላው ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ቃል ኪዳን አፈረሰ። ረዓብ ራሷንም ቤተሰቧንም አዳነች፤ በእስራኤልም የተከበሩ ዜጎች ሆኑ፤ አካን እራሱን እና ቤተሰቡን ለሞት በመዳረግ የውርደት ምሳሌ ሆነ። ስለ መጎምጀት ኃጢአት ያስቡ። ምንም ያህል ቢኖረን ወይም ባይኖረን በዚህ ኃጢአት ከመሸነፍ ማምለጥ የምንችለው እንዴት ነው? (ከሉቃስ 12፡15 ጋር ያነፃፅሩ)

ጥቅምት 26
Nov 5

የተስፋ በር


ኢያሱ 8:1-29ን ያንብቡ። እግዚአብሔር እጅግ በጣም አስነዋሪ ውድቀቶቻችንን ወደ እድሎች እንዴት እንደሚለውጥ ይህ ታሪክ ምን ይነግረናል?



የያህዌ ስልት የእስራኤልን የመጀመሪያ ሽንፈት ወደ ትርፍ በመቀየር የአኮርን ሸለቆ (በዕብራይስጥ ቃል “ችግር” የሚለው ቃል) ወደ ተስፋ በር (ከሆሴዕ 2፡15 ጋር ያነፃፅሩ) ይለውጣል። ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤላውያን ላይ በተቀዳጁት ድል በራስ የመተማመን መንፈስ በማዳበራቸው፣ የጋይ ሰዎች ወደኋላ በማፈግፈግ እና በሽንፈት የሚያውቋቸውን እስራኤላውያንን ለማጥቃት ስልታቸውን ደገሙ። የጋይ ሰዎች ከምሽጉ ተታልለው ከወጡ በኋላ ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙት 30,000ዎቹ እስራኤላውያን (ኢያሱ 8:4) ባዶዋን ከተማ በእሳት በማቃጠል ይያዛሉ። ኢያሱ 8፡7 በግልፅ እንደሚያስቀምጠው ድል የሚያመጣው ስልቱ ሳይሆን የጋይን ከተማ ለእስራኤላውያን አሳልፎ የሚሰጠው ጌታ ራሱ ነው። ከየትኛውም የመጽሐፍ ምእራፍ በበለጠ የውትድርና ገድል ገፅታዎች በሚገኑበት ምዕራፍ ውስጥ እንኳን፣ ጥቅሱ ድል የያህዌ ስጦታ የመሆኑን እውነታ አጉልቶ ያሳያል።

የጦርነቱ ወሳኝ ቅፅበት የጋይ ሰዎች ከተማዋን ለቀው እስራኤላውያንን ማሳደድ ሲጀምሩ ነው። ኢያሱ 8፡2 ላይ እግዚአብሔር ስልቱን ካስቀመጠ በኋላ ጦርነቱን እንደሚቆጣጠር በመግለጽ በአጠቃላይ ምዕራፍ ውስጥ ሲናገር ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። እስከዚህ ቅጽበት ድረስ የውጊያውን ውጤት አናውቅም። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የእስራኤላውያን ሠራዊት ድል ማድረጋቸው ግልጽ ይሆናል።

በኢያሱ እጅ የነበረው መሳሪያ ከሰይፍ ወይም ከጦር ይልቅ ማጭድ ያለበት ሰይፍ ነበር። በዘመነ ኢያሱ፣ ይህ እንደ ጦር መሣሪያ ባይታይም የሉዓላዊነት ምልክት ሆኖ ማገለግል ቻለ። እና የጥቃት ምልክት ከመስጠት በተጨማሪ፣ በጋይ ሽንፈት የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት ይገልጻል። ኢያሱ ሙሉ ድል እስኪገኝ ድረስ የማጭድ ሰይፉን በመዘርጋት ሙሴ ቀይ ባህርን ሲያቋርጡ እንዳደረገው (ዘፀ. 14፡16) እና ከአማሌቃውያን ጋር ባደረጉት ጦርነት (ዘጸ. 17፡ 11-13) ላይ እንደሆነው፣ የመሪነቱን ሚና ሙሉ በሙሉ መወጣቱን ያሳያል።

በዚህ ጊዜ ምንም የሚታይ፣ ተአምራዊ የሆነ የእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ባይኖርም ከመለኮታዊ እርዳታ አንፃር በጋይ ላይ የተቀዳጁት ድል የመጀመሪያው ትውልድ በግብፃውያን ላይ ወይም የቅርቡ በኢያሪኮ ላይ ከተቀዳጁት ድል ያነሰ አይደለም። ለስኬት ቁልፉ ኢያሱ በጌታ ቃል ላይ የነበረው እምነት እና ለእሱ ያለው የማያወላውል ታዛዥነት ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥ የሚታየው መርህ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች በየትኛውም ቦታ ቢኖሩና ምንም አይነት ችግር ቢያጋጥሟቸው የሚሠራ ነው።

ጥቅምት 27
Nov 6

የእግዚአብሔር ኃይል ምስክር


ከዚህ ቀደም እንደተማርነው (ትምህርት አምስትን ይመልከቱ)፣ እግዚአብሔር ለአረማውያን መንግስታት ስለ እርሱ እንዲያውቁ እና ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ እድል ሰጥቷቸው ነበር። እነርሱ ግን እምቢ ብለው የእግዚአብሔርን ፍርድ ተቀበሉ። ባጋጠማቸው ጥፋት የኢያሱ የመጀመሪያ ምላሽን የሚዳስሰውን ኢያሱ 7:6- 9ን ያንብቡ። በተለይ በኢያሱ 7፡9 ላይ ያተኩሩ። በቃሉ ውስጥ ምን ጠቃሚ ሥነ-መለኮታዊ መመሪያ ይገኛል?



መጀመሪያ ላይ ኢያሱ የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመከራቸው መካከል ያደረጉትን እያደረገ ይመስላል፡- “ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ እኛን ወደዚች ምድረ በዳ አውጥታችኋል፤ በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እንጀራ ስንበላ ስንጠግብ ሳለን በግብፅ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን! አሉአቸው።” (ዘጸ. 16፡3)።

ኢያሱም እነሆ፡- “ዋይ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን ታጠፋንም ዘንድ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ!” (ኢያሱ. 7:7) እያለ ነው።

ብዙም ሳይቆይ ግን በዚህ ሽንፈት የእግዚአብሔር ስምና ዝና ለሚያመጣው ጉዳት ያለውን ታላቅ አሳቢነት ያሳያል። “ ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ፤ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው?” (ኢያሱ. 7:7)።

ይህ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ስለነበረው ዓላማ ዋና ጭብጥ እና መርሆ ያሳያል። በዙሪያቸው ያሉት አረማዊ ሕዝቦች እግዚአብሔር ለሚታዘዙት ሕዝቦቹ ምን ታላቅ ነገር እንደሚያደርግ እንዲያዩ ቢፈልግም ረዓብ እንዳደረገችው በሕዝቡ ድል ኃይል አማካኝነት ስለ እስራኤል አምላክ መማር ይችላሉ። በሌላ በኩል፣ ነገሮች መጥፎ ከሆኑ፣ እዚህ እንዳደረጉት፣ ሕዝቦች የእስራኤል አምላክ ደካማ እና ውጤታማ እንዳልሆነ አድርገው ይቆጥሩታል (ዘኁ. 14:16፣ ዘዳ. 9:28 ይመልከቱ)፣ ይህም የከነዓናውያንን ተቃውሞ ሊያበረታታ ይችላል።

በሌላ አነጋገር፣ ዕብራውያን ምድሪቱን በወሰዱበት አውድ ውስጥ እንኳን፣ ለአረማውያንና ለእስራኤልም ብቸኛው ተስፋ ለሆነው ለእግዚአብሔር ክብርን እና ሞገስን ማምጣትን ጨምሮ ታላላቅ ጉዳዮች እና መርሆዎች ተነግረዋል። ዘዳግም 4:5-9ን ያንብቡ። በእስራኤል እና ዛሬ እኛ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ለዓለም በምንሰጠው ምስክርነት መካከል ያለውን ተመሳሳይነት በምን መንገዶች ማየት እንችላለን?

ጥቅምት 28
Nov 7


ተጨማሪ ሀሳብ


የኃይማኖት አባቶች እና ነብያት ከሚለው መጽሐፍ ‘’የኢያሪኮ መውደቅ’’ የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ ያንብቡ።

‘ወደ አካን ጥፋት የመራው ገዳይና ቀለል ተደርጎ የሚታየው ኃጢአት በመጎምጀት ላይ ያተኮረ ነው። . . . አካን ጥፋተኛ መሆኑን ቢያምንም ይህን ያመነው ኑዛዜው ለርሱ ጥቅም በማያስገኝበት እና ከረፈደ ነበር። የእስራአኤል ሠራዊት ከጋይ ተሸንፈውና ልባቸው ተሰብሮ ሲመጡ ቢያይም ወደፊት ወጥቶ ኃጢአቱን አልተናዘዘም።

ኢያሱ እና የእስራኤል ሽማግሌዎች ሊገለጥ በማይችል ኃዘን ወደ መሬት ሲንበረከኩ ተመልክቷል። በዚያ ሰዓት ተናዝዞ ቢሆን ኖሮ የእውነተኛ ንስሐ ምሳሌ ይሆን ነበር፡ ሆኖም ዝም አለ። ከባድ ወንጀል እንደተፈፀመና የወንጀሉ አይነት ሲነገር ሰምቷል። ነገር ግን ከንፈሮቹ ተለጉመው ነበር። ከዚያ ጥልቅ የሆነው ምርመራ ጀመረ። የርሱ ነገድ፣ የርሱ ቤተሰብ እና የርሱ ቤት እየተጠቆመ ሲመጣ ምን ያክል ነፍሱ ተጨንቃ ይሆን! እንደዚህም ሆኖ የእግዚአብሔር ጣት በእርሱ ላይ እስኪያርፍ ድረስ አልተናዘዘም። ከዚያ ኃጢአቱ ከዚያ በላይ ተደብቃ ልትቆይ እንደማትችል ሲያውቅ እውነቱን አመነ። እንደዚህ አይነት ኑዛዜዎች ምን ያክል ብዙ ይሆኑ! እኛና እግዚአብሔር ብቻ የምናውቀውን ኃጢአት በመናዘዝ እና ከታወቀብን በኋላ በመናዘዝ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። አካን ባለመናዘዝ የጥፋቱን ቅጣት አስቀራለሁ ብሎ ስላሰበ ሳይናዘዝ ቆየ። ነገር ግን ኑዛዜው የቅጣቱን ፍትሃዊነት ለማሳየት ብቻ ጠቀመ። ስለ ኃጥያቱ የተደረገ እውነተኛ ንስሐ፣ ራስን ማስጨነቅ፣ የአላማ ለውጥና ኃጥያትን መጥላት አልታየበትም። ኤለን ጂ. ኋይት፣ የኃይማኖት አባቶች እና ነብያት፣ ገጽ 496-498


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በማስታወቂያዎችና ብዙ በማካበት በተሞላው በዚህ ዓለም የአስረኛው በማስታወቂያዎችና ብዙ በማካበት በተሞላው በዚህ ዓለም የአስረኛው ትዕዛዝ (ዘፀ. 20፡17) መልዕክት ምንድነው? በፍላጎታችንና የግድ በሚያስፈልገን መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ልዩነቱን ማወቅ የሚጠቅመን ለምንድነው?

2. ዳን. 9:4-10 ላይ ያለውን የዳንኤል ጸሎት ያንብቡ። ዳንኤል እነዚያን ዳን. 9:4-10 ላይ ያለውን የዳንኤል ጸሎት ያንብቡ። ዳንኤል እነዚያን ኃጢአቶች ስለማድረጉ ምንም የተፃፈ ነገር ባይኖርም የእስራኤልን ኃጢአት ሲናዘዝ እኛ ብሎ መደጋገሙ ምን ፋይዳ አለው?

3. በሐሙሱ ክፍል መጨረሻ ላይ በተጠየቀው ጥያቄ ላይ ያሰላስሉ። በሐሙሱ ክፍል መጨረሻ ላይ በተጠየቀው ጥያቄ ላይ ያሰላስሉ። የእስራኤላውያን ለእጝዚአብሔር መመሪያዎች መታዘዝ ለምስክርነታቸው ጠቃሚ የሆነው ለምንድነው? ዛሬም ቢሆን ለቤተክርስትያናችን ተመሳሳዩ መርህ የሚሠራው እንዴት ነው? ማለትም በእግዚአብሔር የተስጡንን መመሪያዎች ሁሉ ተከትለን ቢሆን ኖሮ ምስክርነታችን ምን ያክል ውጤታማ ይሆን ነበር?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL