የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከኢያሱ መጽሐፍ የሚገኙ የእምነት ትምህርቶች



4ኛ ሩብ ዓመት 2025


ጥቅምት 15 - 21

5ኛ ትምህርት

Oct 25 - 31




እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፦ ዘፍ. 15:16፣ ዘሌ. 18:24- 30፣ 2 ጢሞ. 4:1፣8፣ ዘፀ. 23:28-30፣ ዘዳ. 20:10፣ 15-18፣ ኢሳ. 9፡6።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ ‘የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ለእስራኤል ስለ ተዋጋላቸው ኢያሱ እነዚህን ነገሥታት ሁሉ ምድራቸውንም በአንድ ጊዜ ያዘ።” ኢያሱ 10፡42

የኢያሱ መጽሐፍ አንዳንድ የሚረብሹ ክስተቶችን ይዟል። ከባድ ጥያቄዎች የሚነሱት ሌላ ቡድንን ማጥፋትን ከእግዚአብሔር እንደተሰጠ ሃላፊነት አድርገው በሚቆጥሩ ቡድኖች በኩል ስለ ቅዱስ ጦርነት በሚናገረው ጽንሰ-ሀሳብ ዙሪያ ነው። በብሉይ ኪዳን የነበረው ሃይማኖታዊ ጦርነት ጉዳይ ፈታኝ ነው።

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የዓለማት ሉዓላዊ ጌታ ሆኖ ስለተገለፀ የሚሆነው ነገር ሁሉ በሆነ መንገድ ከሱ ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ ፈቃድ ጋር የተያያዘ መሆን አለበት። ስለዚህ “እግዚአብሔር እንዲህ ያሉትን ነገሮች እንዴት ሊፈቅድ ይችላል?” የሚለው ጥያቄ የማይቀር ይሆናል። ባለፈው ሳምንት፣ እግዚአብሔር ራሱ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተካሄዱት ከማንኛቸውም ጦርነቶች ወይም ውጊያዎች እጅግ የላቀ በሆነና ሁሉንም የሕይወት ገጽታችንን በሚነካው ጦርነት ውስጥ እንዳለ አይተናል። በመጽሐፍ ቅዱሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ታሪክ ውስጥ የተከሰቱትን ክስተቶች በሙላት ልናስተውል የምንችለው ከዚህ ግጭት አንጻር ብቻ እንደሆነም አይተናል።

በዚህ ሳምንት፣ በመለኮት የተነሳሱ ጦርነቶችን ውስብስብነት፣ የመለኮታዊ ጦርነት ገደቦችን፣ በብሉይ ኪዳን ነቢያት የተነገሩትን የመጨረሻው የሰላም ራዕይ፣ እና የእንደዚህ አይነት ጦርነቶች መንፈሳዊ አንድምታዎችን መመርመራችንን እንቀጥላለን። ለጥቅምት 22 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ጥቅምት 16
Oct 26

የከነዓናውያን በደል


ዘፍጥረት 15:16፣ ዘሌዋውያን 18:24-30፣ ዘዳግም 18:9-14፣ እና ዕዝራ 9:11ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር የከነዓንን ምድር ለእስራኤላውያን ለመስጠት ስላለው ትልቅ እቅድ ምን እየነገሩን ነው?



በከነዓን የሚኖሩ ሕዝቦች ኃጢአት ምን ማለት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ከኢያሱ መጽሐፍ ባሻገር መመልከት አለብን። የነዚህ ሕዝቦች አስጸያፊ ልጅን የመስዋት ልማድ፣ ሟርት፣ አስማት፣ ጥንቆላ፣ መተት እና መናፍስት ጠሪነት ፍንጭ ይሰጡናል (ዘዳ. 18፡9-12)።

የጥንት የኡጋሪት ጽሑፎች (ከራስ ሻምራ) መገኘት ስለ ከነዓናውያን ሃይማኖትና ማኅበረሰብ የበለጠ ግንዛቤን ይሰጣል፣ እናም ይህን ባህል ማውገዝ የሚስተዋል ብቻ ሳይሆን እንደ ብሉይ ኪዳን የሥነ ምግባር መስፈርቶችም የተገባ ነው።

የከነዓናውያን ሃይማኖት የመራባትን ዕድል የሚያረጋግጡ የተፈጥሮ ክስተቶች በወንድ አማልክት እና በሴት አማልክት መካከል ባለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ቁጥጥር ስር ናቸው በሚለው እምነት ላይ የተመሠረተ ነው።

ስለዚህም የወንድ አማልክት እና የሴት አማልክት የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲያደርጉ ለማነሳሳት ከራሳቸው ፆታዊ ፍላጎት አንፃር የአማልክትን ፆታዊ ተግባር በማሰብ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ተግባራት ተጠምደዋል። ይህ ጽንሰ- ሐሳብ በሥርዓተ አምልኮ ውስጥ የሚሳተፉ ወንድ እና ሴት ዝሙት አዳሪዎችን በመፍጠር “የተቀደሰ” የዝሙት አዳሪነት የሚባል ነገርን አስከትሏል።

አንድ ሕዝብ ሕዝቡ ከሚያመልኩት አማልክት ከፍ ያለ የሞራል ደረጃ ላይ መድረስ አይችልም። አማልክቶቻቸውን በተመለከተ እንዲህ ያለ ግንዛቤ በማግኘታቸው የከነዓናውያን ሃይማኖታዊ ልማዶች መጽሐፍ ቅዱስ የተፀየፈውን ልጆችን መሥዋዕት ማድረግን ማጠቃለላችው አይገርምም።

የከነዓን ነዋሪዎች የበኩር ልጆቻቸውን ለሚያመልኳቸው አጋንንት አዘውትረው ይሠዉ እንደነበር አርኪኦሎጂያዊ መረጃዎች አረጋግጠዋል።

በትልልቅ ማሰሮዎች ውስጥ ተጨፍልቀው የተገኙት ትናንሽ አፅሞች፣ ደመቅ ብለው ከተፃፉት ፅሁፎች ጋር ስለ ሃይማኖታቸው ወራዳነት እና ለብዙ ልጆቻቸው ምን ትርጉም እንዳለው ይመሰክራሉ።

የከነዓናውያን መጥፋት እግዚአብሔር የከነዓንን ምድር ለእስራኤላውያን ለመስጠት ባደረገው ውሳኔ ምክንያት በኋላ የታሰበ ነገር አልነበረም። የከነዓን ነዋሪዎች በመካከላቸው በሚኖሩ አባቶች ምስክርነት እግዚአብሔርን እና ባህሪውን የማወቅ እድል ያገኙበት ተጨማሪ የምሕረት ጊዜ ተሰጥቷቸው ነበር። ዕድሉ ነበራቸው፣ ግን በግልጽ አባከኑት፣ እና ጌታ በመጨረሻ እስኪያስቆማቸው ድረስ በአሰቃቂ ተግባሮቻቸው ቀጠሉ።

ጥቅምት 17
Oct 27

ታላቁ ዳኛ


ዘፍጥረት 18:25፣ መዝሙረ ዳዊት 7:11፣ መዝሙረ ዳዊት 50:6፣ መዝሙረ ዳዊት 82:1፣ መዝሙረ ዳዊት 96:10፣ እና 2 ጢሞቴዎስ 4:1፣ 8ን ያንብቡ።

እነዚህ ጥቅሶች ስለ እግዚአብሔር ባሕሪ ምን ይላሉ? የእግዚአብሔር የዓለም ፈራጅነት በእርሱ የሚነሳሱ ጦርነቶችን ጥያቄ እንድንረዳ የሚያግዘን እንዴት ነው?



የእግዚአብሔር ባሕርይ ቅድስና ማለት ኃጢአትን መታገስ አይችልም ማለት ነው። ታጋሽ ነው። ነገር ግን፣ ኃጢአት የመጨረሻ ውጤቱን ማጨድ አለበት፣ እርሱም ሞት ነው (ሮሜ. 6፡23)። ኃጢአት በእስራኤልም ሆነ በከነዓናውያን መካከል ቢገኝ እግዚአብሔር ጦርነት አውጆበታል።

እስራኤላውያን ከሌሎች ሕዝቦች በተለየ ሁኔታ በቅዱስ ጦርነቶች በመካፈላቸው አልተቀደሱም (ዘዳ. 9:4-5፤ ዘዳ. 12:29-30)። እስራኤላውያን ከሌሎቹ የጥንት ቅርብ ምስራቅ ሕዝቦች በተለየ፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ ሳይሆን በእነርሱ ተቃራኒ ሆኖ ጠላቶቻቸው እንዲጨቁኗቸው ሲፈቅድ (ከኢያሱ 7 ጋር ያነፃፅሩ) ተመልክተዋል።

የቅዱስ ጦርነትን አጠቃላይ ጽንሰ-ሐሳብ ልንረዳ የምንችለው እግዚአብሔር እንደ ዳኛ ሲሰራ ካየነው ብቻ ነው። በዚህ መንገድ ሲታይ፣ የእስራኤል ምድሪቱን የመውረስ ጦርነቶች ፍጹም የተለየ ባህሪ ይኖራቸዋል።

በጥንቱ ዓለም (ዛሬም ቢሆን) ከተስፋፉት የንጉሳዊ አገዛዝ ጦርነቶች በተቃራኒ የእስራኤል ጦርነቶች ለራሳቸው ክብርን ለማስገኘት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፍትህና ሰላም በምድር ላይ ለማስፈን የተደረጉ ነበሩ። ስለዚህ፣ የቅዱስ ጦርነት ጽንሰ-ሀሳብን ማእከል በመረዳት ውስጥ ያሉት የእግዚአብሔር ገዥነት እና ሉዓላዊነት ጽንሰ-ሀሳቦች ጦረኛነቱ፣ ንጉስነቱ ወይም ዳኝነቱ አደጋ ውስጥ እንደወደቁ ሁሉ አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ።

እግዚአብሔር እንደ ተዋጊ ልክ እንደ ዳኛ የባህሪው መገለጫ የሆነውን ህግ የበላይነት ለማስፈን፣ ለማረጋጋት እና ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነው። እንደ ዳኛ እና ንጉስ የሚመስለው የእግዚአብሔር ተዋጊነት፣ ይሖዋ በተመሰረተው ስርአቱ ላይ ማመፅን ለዘላለም እንደማይታገሥ ያረጋግጣል። ስለዚህ፣ አንድ ሰው የያህዌ እንቅስቃሴ መዳረሻ በጭራሽ ጦርነት ወይም ድል ሳይሆን የፍትህ እና የሰላም እንደገና መስፈን መሆኑን ማረጋገጥ ይችላል። በዋናነት መፍረድ፣ ጦርነት መግጠም ወይም ፍትህ መስጠት፣ የድርጊቱ ፈፃሚ እግዚአብሔር ሲሆን አንድ አይነት ናችው። መማለጃ የማይቀበል ወይም አድልዎ የማያውቅ ጻድቅ ዳኛ ስለሆነው አምላካችን ተወያዩ። ኃጢአትን፣ ግፍን፣ የንጹሃንን ስቃይ፣ እና ጭቆናን እስከመጨረሻው የማይታገሰው አምላክ የወንጌል ማእከል የሆነው እንዴት ነው?

ጥቅምት 18
Oct 28

መውረስ ወይስ መጥፋት?


ከዘፀአት 23:28-30፣ ዘጸአት 33:2፣ ዘጸአት 34:11፣ ዘኍልቍ 33:52፣ እና ዘዳግም 7:20 በዘፀአት 34:13፣ ዘዳግም 7:5፣ ዘዳግም 9:3፣ ዘዳግም 12:2-3፣ እና ዘዳግም 31:3-4 እነዚህ ጥቅሶች ስለ ድል ዓላማና ስለ ጥፋቱ መጠን ምን ያሳያሉ?



እግዚአብሔር ለከነዓናውያን የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ማጥፋት ሳይሆን፣ ምድራቸውን መውረስ ነበር። እስራኤል ምድሪቱን በመውረስ ጦርነት ውስጥ የተካፈለችበትን መንገድ የሚገልጹትን ምንባቦች ስንመረምር በተስፋይቱ ምድር ነዋሪዎች ላይ ስለተፈጸመው መባረር እና መበታተን የሚናገሩ ቃላት ተጠቅሟል። ሁለተኛው የቃላት ቡድን ጥፋትን የሚገልጽ እና በእስራኤል መፈፀሙን አስምሮ በአብዛኛው የሚያመለክተው እንደ አረማዊ አምልኮ ጽሑፎች እና መዋጊያ መሳሪያዎች አይነት ግዑዝ ነገሮችን ነው።

የአረማውያን አምልኮ ቦታዎችና መሠዊያዎች የከነዓን ሃይማኖት ዋና ማዕከላት እንደሆኑ ግልጽ ነው።

ቅዱስ ጦርነት በዋናነት የከነዓንን ብልሹ ባህል እና ማህበረሰብ ማስወገድ ላይ ያተኮረ ነው። እስራኤል ከመንፈሳዊው አንፃር የሚያበላሹትን ሁሉንም አካላት ማጥፋት ነበረበት። ነገር ግን ከወረራው በፊት ወይም በጦርነቱ መሃል በግለሰብ ደረጃ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት የተገነዘቡት የከነዓን ነዋሪዎች በስደት ማምለጥ ችለዋል (ኢያሱ 2፡9-14፤ ከመሳ. 1፡24-26 ጋር ያነፃፅሩ)። ጥፋት የተፈረደባቸው ከነዓናውያን ወደ ተመሸጉ ከተሞች የሸሹት፣ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ባለው ዕቅድ ላይ በማመፅ የቀጠሉት እና ልባቸውን ያደነደኑት (ኢያሱ 11:19-20) ብቻ ነበሩ። ይሁን እንጂ ይህ ጥያቄ ያስነሳል:- ከነዓንን የመውረር የመጀመሪያ ዓላማ የምድሪቱን ነዋሪዎች ለማጥፋት ሳይሆን ለመውረስ ብቻ ከሆነ እስራኤላውያን ለምን ብዙ ሰዎችን መግደል አስፈለጋቸው?





ከከነዓን ወረራ ጋር የተያያዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ትንተና እንደሚያሳየው የወረራው የመጀመሪያ ሐሳብ ከነዓናውያንን መበታተን እንደነበረ ያመለክታል። ነገር ግን አብዛኞቹ ከነዓናውያን ልክ እንደ ግብፁ ፈርዖን ልባቸውን አደነደኑ እና ከባህላቸው ጋር እጅግ የሙጥኝ ስላሉ አብረው መጥፋት ነበረባቸው። ከራሳችን ባህሪ እና ልማዶች ውስጥ መነቀል እና መጥፋት ያለባቸው የትኞቹ ናቸው?

ጥቅምት 19
Oct 29

ነፃ ምርጫ


ዘዳግም 20:10፣15-18፣ ዘዳግም 13:12-18፣ እና ኢያሱ 10፡40ን ያንብቡ።

በዘዳግም መጽሐፍ ላይ የተገለጸው የጦርነት ሕግና ጣዖት አምላኪ በሆነች በእስራኤል ከተማ ላይ የተደረገው ሥርዓት እስራኤላውያን ባካሄዱት ጦርነት ውስጥ ፈፅሞ ማጥፋት የሚለው ፅንሰ-ኃሳብ ያለውን ውስንነት እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?



የዕብራይስጡ ጽሑፍ የሰዎችን በጦርነት ውስጥ የሚደርሰውን ጥፋት ለመግለጽ ልዩ ቃል ይጠቀማል፡- ቼረም። ይህ ቃል የሚያመለክተው “የታገደውን፣” “የተረገመውን” ወይም “ለጥፋት የተወሰነውን” ነው።

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች፣ እንስሳት ወይም ግዑዝ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሔር ልዩ ግዛት ውስጥ እንዲወጡ ማለትም ከጦርነት አውድ አንፃር እንዲጠፉ የሚያዝ ነው። በጦርነት ውስጥ ያለን ህዝብ በአጠቃላይ ማጥፋትን የሚገልፀውን የቼረምን ጽንሰ-ሀሳብ እና ልምምድ፣ እግዚአብሔር ባህሪውና ተአማኒነቱ በአደጋ ውስጥ ከወደቀበት ከክፉ ኃይሎች ጋር ካለው ግጭት አንጻር ልንረዳው ይገባናል።

እንደገና፣ በዓለም ላይ ኃጢአት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገለልተኝነት የሚባል ነገር የለም፤ ወይ በእግዚአብሔር ጎራ ወይም በተቃራኒው ብቻ ነው የምንሆነው። አንደኛው ወገን ወደ ዘላለማዊ ሕይወት፣ ሌላኛው ደግሞ ወደ ዘላለማዊ ሞት ይመራል።

ፈፅሞ የማጥፋት ልምምድ እግዚአብሔር በኃጢአት እና በክፋት ላይ ያለውን የጽድቅ ፍርድ ይገልጻል። አምላክ የፍርዱን የተወሰነ ክፍል ለተመረጠው ሕዝቡ ለጥንቷ እስራኤል ልዩ በሆነ መንገድ አሳልፎ ሰጥቷል።

ለጥፋት መሰጠቱ በእሱ ጥብቅ አመራር ስር፣ በተወሰነ የታሪክ ጊዜ እና በደንብ በተገለጸችው ምድር በጥንታዊቷ ከነዓን ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር። በትናንቱ ጥናት ላይ እንደተመለከትነው፣ እንዲጠፉ የተወሰነባቸው ሰዎች ሁልጊዜ በአምላክ ዓላማ ላይ ያመፁትና ንስሐ ያልገቡት ብቻ ነበሩ። ስለዚህ፣ አምላክ እነሱን ለማጥፋት የወሰነው ውሳኔ የዘፈቀደ ወይም ብሔር ተኮር አልነበረም።

ከዚህም በላይ፣ እስራኤል እንደ ከነዓናውያን ተመሳሳይ የአኗኗር ዘይቤን ለመከተል ቢወስኑ ተመሳሳይ ጥፋት ይጠብቃቸው ነበር (ከዘዳግም 13 ጋር ያነፃፅሩ)። በመለኮት በተነሳሱት በነዚህ ጦርነቶች በሁለቱም በኩል ያሉት ቡድኖች አስቀድሞ የተገለጹ ቢመስሉም (እስራኤላውያን ምድሪቱን ይወርሳሉ፣ ከነዓናውያንም ይጠፋሉ)፣ በረዓብ፣ በአካን እና በገባዖናውያኑ ታሪክ ላይ እንደምናየው ከአንዱ ወገን ወደ ሌላው የመሸጋገር ዕድል አለ።

ሰዎች ጥበቃ የተደረገላቸው ወይም እንዲጠፉ የተወሰኑት በዘፈቀደ አልነበረም። ከያህዌ ጋር በመጠለል ሲጠቀሙ የነበሩ ሰዎች በአመፃ የነበራቸውን መብት ሊያጡ ይችላሉ፤ እና ለመጥፋት ከታሰቡት ስር ያሉት ደግሞ ለእግዚአብሔር ሥልጣን ራሳቸውን ቢያስገዙ በሕይወት ሊኖሩ ይችላሉ። የከነዓናውያን አምላክን መቃወም ዛሬ በእኛ አውድ ያለው መንፈሳዊ አንድምታ ምንድን ነው? ማለትም፣ በግል ምርጫችን የምናመጣቸው ውጤቶች ምንድናቸው?

ጥቅምት 20
Oct 30

የሰላም ልዑል


የሚከተሉት ጥቅሶች እግዚአብሔር ለህዝቡ ወደፊት ያሰበውን መልካም ጊዜ የሚገልጹት እንዴት ነው? ኢሳ. 9፡6፣ ኢሳ. 11፡1-5፣ ኢሳ. 60፡17፣ ሆሴ. 2፡18፣ ሚክ. 4፡3።



ምንም እንኳን የዚህ ሳምንት ትምህርት ዋና ትኩረት በመለኮት አነሳሽነት እና ደጋፊነት በብሉይ ኪዳን የተካሄዱ ጦርነቶች ቢሆኑም፣ በብሉይ ኪዳን ትንቢታዊ ጽሑፎች ውስጥ ሌላ ጉልህ ጭብጥ መኖሩን መጥቀስ ያስፈልገናል፡- ያም ሰላማዊው የመሲሐዊ ዘመን የወደፊት ራእይ ነው።

መሲሑ “የሰላም አለቃ” ተብሎ ተገልጿል (ኢሳ. 9፡6)። አንበሳና በጉ አብረው በሚሰማሩበት(ኢሳ. 11፡1-8)፣ ጥፋትና ጉዳት በማይደርስበት (ኢሳ. 11፡9)፣ ሰላም በሚነግስበት (ኢሳ. 60፡17) እንደ ወንዝም በሚፈስበት (ኢሳ. 66፡12) መንግሥት ውስጥ ይመራል። 2 ነገሥት 6:16-23ን ያንብቡ። ይህ ታሪክ እግዚአብሔር ለህዝቡ እና ለመላው ሰብዓዊ ዘር ስላለው ጥልቅ አላማ ምን ግንዛቤዎችን ይሰጣል?



በኤልሳዕ አነሳሽነት የሶርያን ሠራዊት የመገቡበትን ታሪክ እንመልከት።

እነሱን ከመጨፍጨፍ ይልቅ (2 ነገሥት 6:22) አምላክ ምንጊዜም ለሕዝቡ ያለውንና ከሁሉ የላቀውን ሐሳብ ማለትም ሰላምን አሳያቸው። ኤልሳዕ በጠላት ዙሪያ ያለው የማይታየው ሠራዊት የበለጠ ኃያል መሆኑን ጠንቅቆ ማወቁ ያስገርማል (2ኛ ነገ. 6፡17)። እግዚአብሔር በምድራችን ላይ ተጽዕኖ ባደረገው ዓለም ዓቀፋዊ ግጭት ውስጥ እየተሳተፈ ቢሆንም፣ የመጨረሻው የመቤዠት ታሪክ ግብ ዘላለማዊ ግጭት ወይም በባርነት ውስጥ ጠላትን ለዘላለም መግዛት ሳይሆን ዘላለማዊ ሰላም ነው። ዓመፅ ዓመፅን እንደሚያመጣ (ማቴ. 26፡52)፣ ሰላም ሰላምን ያመጣል። ታሪኩ የሚያጠቃልለው “ከዚያም በኋላ የሶርያ አደጋ ጣዮች ወደ እስራኤል አገር አልመጡም።” (2 ነገሥት 6፡23) በማለት ነው። ኢየሱስን ለመምሰል በመፈለግ የሰላም ወኪሎች ለመሆን የምንችልባቸውን ሁሉንም መንገዶች ያሰላስሉ። አሁን በኛ ሕይወት በሚያጋጥሙን የትኞቹም አይነት ግጭቶች ከልዩነት ይልቅ የሰላም ወኪል መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

ጥቅምት 21
Oct 31


ተጨማሪ ሀሳብ


የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት ከሚለው መጽሐፍ ውስጥ “የኢያሪኮ ውድቀት” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ ያንብቡ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳሉት ጥቅሶች ሁሉ፣ ዐውዱንና ታሪኩን ማወቅ ወሳኝ ነው። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፣ በከነዓናውያን ላይ የሚደረጉ ጦርነቶችን ለመረዳት፣ የዓለምዓቀፋዊው ግጭት እና የእግዚአብሔር ፈራጅነት መነሻ ኃሳብ መረዳት ወሳኝ ናቸው።

“እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ ነው፥ ኃጥኣተኛ የሆኑ አሕዛብም ከእርሱና ከባሕርያቱ ጋር እንዲተዋወቁ የሙከራ ጊዜን ሰጣቸው። በተሰጣቸው ብርሃን መሠረት ብርሃንን ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆናቸው እና ከእግዚአብሔር መንገድ ይልቅ የራሳቸውን መንገድ በመምረጣቸው ጥፋታቸው ተከሰተ።

እግዚአብሔር ከነዓናውያንን በአንድ ጊዜ ያላሳደደበትን ምክንያት ተናገሯል። የአሞራውያን የበደል ፅዋ አልሞላም ነበር። በአመፃቸው ቀስ በቀስ እየጨመሩ የእግዚአብሔር ትዕግስት እስኪያልቅ ድረስ በመቀጠላቸው እስከመጥፋት ደረሱ። ጽዋቸው እስኪሞላ እና አመፃቸው እስኪበዛ ድረስ የእግዚአብሔር የበቀል እርምጃ ይዘገያል። ሁሉም ሀገራት የምህረት ጊዜ ተሰጥቷቸው ነበር።

የእግዚአብሔርን ህግ የጣሱና ያቃለሉ ሁሉ ከአንዱ ክፋት ወደ አንዱ ክፋት እየቀጠሉ ይሄዳሉ። ልጆች የወላጆቻቸውን አመፀኛ መንፈስ ይወርሱና የእግዚአብሔር ቁጣ በነርሱ ላይ እስኪወርድ ድረስ ከአባቶቻቸው የከፋ ኃጢአት ያደርጋሉ። ቅጣቱ ስለዘገየ ግን ቀንሷል ማለት አይደለም። Ellen G. White Comments, The Sda Bible Commentary, Vol. 2, P. 1005


የመወያያ ጥያቄዎች




1. እግዚአብሔር የእኛ ዳኛ እና የዓለማት ሁሉ የበላይ ዳኛ በመሆኑ አንድምታ እግዚአብሔር የእኛ ዳኛ እና የዓለማት ሁሉ የበላይ ዳኛ በመሆኑ አንድምታ ዙሪያ ተወያዩ። እግዚአብሔር ፈራጅ የመሆኑ እውነታ ለወንጌልና ለደህንነታችን መሠረት የሆነው ለምንድነው?

2. የከነዓናውያን ጉዳይ የአምላክን ትዕግሥትና ፍትሕ እንድናውቅ የሚረዳን የከነዓናውያን ጉዳይ የአምላክን ትዕግሥትና ፍትሕ እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው? ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት የአምላክን ባሕርይ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

3. ስለነጻ ምርጫ ተፈጥሮ ያሰላስሉ። እግዚአብሔር የመምረጥ ነፃነታችንን ስለነጻ ምርጫ ተፈጥሮ ያሰላስሉ። እግዚአብሔር የመምረጥ ነፃነታችንን የሚያከብረው ለምን ይመስላችኋል? ፍቅር እና የመምረጥ ነፃነት እርስ በርስ የተያያዙት እንዴት ነው?

4. ብሉይ ኪዳን ብዙ የጦርነት እና የግጭት ታሪኮችን ቢይዝም የሰላም ብሉይ ኪዳን ብዙ የጦርነት እና የግጭት ታሪኮችን ቢይዝም የሰላም ጊዜን ወደፊት በራዕይ ያያል። እኛ ክርስቲያኖች በአካባቢያችን ሰላምን ከመፍጠር ረገድ ያለብን ኃላፊነት ምንድነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL