የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከኢያሱ መጽሐፍ የሚገኙ የእምነት ትምህርቶች



4ኛ ሩብ ዓመት 2025


ጥቅምት 1 - 7

3ኛ ትምህርት

Oct 11 - 17




የፀጋ ማስታወሻዎች



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢያሱ 3፣ ዘኍ. 14፡44፣ ሉቃ 18፡18-27፣ ኢያሱ 4፣ ዮሐ. 14፡26፣ ዕብ. 4፡8-11።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ የኤርትራን ባሕር ከፊታችን እንዳደረቀ እንዲሁ እስክትሻገሩ ድረስ አምላካችሁ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ውኃ ከፊታችሁ አደረቀ። ይኸውም የእግዚአብሔር እጅ ጠንካራ እንደ ሆነች የምድር አሕዛብ ሁሉ እንዲያውቁ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ለዘላለሙ እንድትፈሩ ነው።” (ኢያሱ 4፡23-24)።

ትራፊኩ ምልክት ሰጠ። ጆን መኪናውን ማቆም ነበረበት። ትራፊኩ የመንጃ ፈቃዱን እንዲያሳይ ጠየቀ፤ እና በዚያን ጊዜ፣ ጆን ቦርሳውን ከመንጃ ፈቃዱ ጋር በቢሮ ውስጥ እንደረሳው አወቀ። ጆን ምን እንደተፈጠረ ገለጸ፣ እና መኮንኑ ስለ ሥራው ጠየቀው፤ ጆን ፕሮፌሰር ነኝ ብሎ መለሰ። መኮንኑ ለጆን የቅጣት ወረቀት እየሰጠው፣ እንደ ቅጣት እንዳይቆጥረው ነገረው።

“የትምህርት ክፍያ ነው” አለ። “ሰዎች አንድ ነገር መማር ሲፈልጉ ክፍያ ይከፍላሉ፤ ይህ እርስዎ በሚያሽከረክሩበት ጊዜ መንጃ ፈቃድዎን እንዳይረሱ የሚያስተምር ክፍያ ነው መልካም ቀን፣ ፕሮፌሰር!” አለው።

ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ከፊት ለፊታችን የሌሉ ነገሮችን ለመርሳት የተጋለጥን ነን። ያላነሳናቸውን የስልክ ጥሪዎች መመለስ፣ ለኢሜይሎች ምላሽ መስጠት፣ አበቦችን ውሃ ማጠጣት፣ የመልካም ልደት ምኞቶችን መላክ እና የመሳሰሉትን እንረሳለን። ይሁን እንጂ ስለ መንፈሳዊ ፍላጎታችን መርሳት ቅጣት ከመቀበል የበለጠ ከባድ መዘዝ ሊያስከትልብን ይችላል፣ ለዚህ ምክንያቱ የዘላለም እጣ ፈንታችንን ስለሚወስን ነው።

የዕብራውያንን የዮርዳኖስን መሻገር ስናጠና ከተሞክሯቸው ምን እንደምንማር እንመልከት። ለጥቅምት 8 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ጥቅምት 2
Oct 12

ዮርዳኖስን መሻገር


ኢያሱ 3፡1-5 እና ዘኁልቁ 14፡41-44ን ያንብቡ። እግዚአብሔር እስራኤላውያን ሊሆን ላለው ነገር ልዩ ዝግጅት እንዲያደርጉ የጠየቃቸው ለምንድን ነበር?



በመጽሐፈ ኢያሱ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ሲነገር ይህ የመጀመሪያው ነው። እስከዚህ ነጥብ ድረስ በብሉይ ኪዳን ታቦቱ በመቅደሱ አውድ ውስጥ (ዘፀ. 40፡21)፣ እስራኤል ከሲና ባደረጉት ጉዞ (ዘሁ. 10፡33-36)፣ እና የከነዓንን ወረራ ለመጀመር በተደረገው ያልተሳካ ሙከራ (ዘሁ. 14፡44) ውስጥ ተገልጧል።

በእስራኤላውያን መቅደስ ውስጥ እጅግ የተቀደሰ ነገር ሲሆን እያንዳንዳቸው እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ልዩ ዝምድና የሚገልጹ ሦስት ዕቃዎችን ይዟል: እነርሱም (1) አሥርቱን ትእዛዛት የያዙ ጽላቶች፣ (2) የሊቀ ካህኑ የአሮን በትር፣ እና (3) መና ያለባት የወርቅ መሶብ (ዘጸ. 16፡33፤ ዕብ. 9፡ 4) ናቸው።

ታቦቱ እና ዮርዳኖስን ለመሻገር የተደረገው ዝግጅት እስራኤላውያን ወደ ከነዓን የሚገቡት በራሳቸው መንገድና ጊዜ እንዳልሆነ አሳሰባቸው። ድሉ የሚሳካው የእግዚአብሔርን መንገድ እና ጊዜ ከተከተሉ ብቻ ነው። የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሸፈኑት ኪሩቤል በላይ በዙፋን ላይ እንደተቀመጠ የተገለፀው አምላክ (ዘፀ. 25:22፣ ዘኍ. 7:89) እና በታቦቱ መገኘቱን የሚገልጠው አምላክ ድል መንሳቱን እየመራ በእስራኤላውያን ፊት ወደ ከነዓን ገባ።

“መቀደስ” (ኢያሱ 3፡5) ወይም “ራስን ቀድሶ መስጠት” የሚለው ቃል ካህናቱ በቤተ መቅደስ አገልግሎታቸውን ከመጀመራቸው በፊት ከሚከተሉት (ዘፀ. 28:41፣ ዘጸ. 29:1) እና የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር በሲና ከመገለጡ በፊት ካከናወኗቸው ነገሮች (ዘጸ. 19፡14) ጋር ተመሳሳይ የሆነ የመንጻት ሂደትን የሚያመለክት ነው። ይህ ቅድስና ኃጢአትን ወደ ጎን መተው እና ሁሉንም ርኩስ የአምልኮ ሥርዓቶች ማስወገድን ያካትታል። ይኸው ትእዛዝ ሊገለጥ ከነበረው የእግዚአብሔር ተአምር ጋር በተያያዘ በዘኍልቍ 11፡18 ላይም ተጠቅሷል።

ጦርነቶች ከመደረጋቸው በፊትም እንዲህ ዓይነት ዝግጅት እንደሚያስፈልግ የተነገረበት ሁኔታ አለ (ዘዳ. 23፡14)። እግዚአብሔር ለእስራኤል በጦርነት ከመዋጋቱ በፊት ህዝቡ ታማኝነታቸውን ለእርሱ እንዲያረጋግጡ እና በአዛዣቸው እንደሚተማመኑ ማሳየት አለባቸው።

ዮርዳኖስን የማቋረጡ ተአምር ለእስራኤላውያን ያረጋገጠላቸው ጌታ ከነዓናውያንን ከምድሪቱ ለማባረር ለገባው ቃል ታማኝ እንደሚሆን ነው።

ዮርዳኖስን ከፍሎ በደረቅ ያሻገረው አምላክ የምድሪቱን ስጦታ ሊሰጣቸው ይችላል። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ዮርዳኖስን አይከፍልም። የእሱ በሁኔታዎች መሀል መገኘት ሁልጊዜ ግልጽ አይደለም። በእኛ ምትክ የእግዚአብሔርን መገኘት ለመለማመድ እና ለመለየት መንፈሳዊ ዝግጁነትን ማዳበር የምንችለው እንዴት ይመስላችኋል?

ጥቅምት 3
Oct 13

ተዓምረኛው ህያው አምላክ


ኢያሱ 3:6-17ን ያንብቡ። የዮርዳኖስ ተአምራዊ መከፈል ስለምናገለግለው አምላክ ምን ይነግረናል?



ዮርዳኖስን መሻገር በኢያሱ 3፡5 ላይ “ኒፍላኦት” በሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገለጠ ሲሆን ትርጉሙም “ተአምራት፣ ድንቅ” ማለት ነው፤ ይህም በአብዛኛው ኃይለኛ፣ ከተፈጥሮ በላይ የሆኑትን የእግዚአብሔርን ተግባራት እና የእርሱን ልዩ መሆን ያሳያል (መዝ. 72፡18፣ መዝ. 86፡10)። በኋላም እስራኤላውያን በእነዚህ ድርጊቶች ላይ አሰላሰሉ፤ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔርን አመሰገኑ (መዝ. 9፡1)፤ በአሕዛብም መካከል ስሙን አወጁ (መዝ. 96፡3)። በግብፅ የነበሩት መቅሰፍቶች (ዘፀ. 3፡20፣ ሚክ. 7፡15)፣ ቀይ ባህርን መሻገር፣ እንዲሁም በምድረ በዳ የታየው የእግዚአብሔር ምሪት (መዝ. 78፡12-16) ከእነዚህ ድንቅ ነገሮች ተርታ ተሰልፈዋል።

ዓለምን የፈጠረው አምላክ በፍጥረቱ ያልተገደበ መሆኑን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ተረድተው መስክረዋል። ለእርሱ የሚሳነው ለመፈጸምም የሚከብደው (ኤር. 32፡17) ነገር የለም። ስሙና ተፈጥሮው ድንቅ ናቸው (መሳ. 13፡18)፤ ከአእምሮአችንም በላይ ነው።

ማዳን ከማይችሉት ከሌሎቹ አማልክት በተለየ (መዝ. 96፡5፣ ኢሳ. 44፡ 8) የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር “ሕያው አምላክ” ነው፤ ተከታዮቹ በእነርሱ ፈንታ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት በመጠባበቅ ሊታመኑበት የሚችሉት የሚሠራ እና ሕያው አምላክ ነው።

ነቢዩ ዘካርያስ ከባቢሎን ግዞት በኋላ ስለ እስራኤል ስለወደፊቱ ጊዜ ሲመለከት (ኒፍላኦት ከሚለው ሥርወ ቃል የተወሰደውን) ተመሳሳይ ቃል ተጠቅሟል። በከተማይቱ ጎዳናዎች ላይ ሽማግሌዎች ተቀምጠው፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ሲጫወቱ ኢየሩሳሌምም ሙሉ በሙሉ እንደምትገነባ ተመለከተ።

በዋና ከተማይቱ ውስጥ አሁንም የመውደሟን ምልክቶች እያዩ የማያምኑ ለሆኑት ዘካርያስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህ ወራት በዚህ ሕዝብ ቅሬታ ዓይን ዘንድ ድንቅ ቢሆን፥ በውኑ በእኔ ዓይን ዘንድ ደግሞ ድንቅ ይሆናልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሕዝቤን ከምሥራቅ ምድርና ከምዕራብ ምድር አድነዋለሁ፤ አመጣቸዋለሁም፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ይኖራሉ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፥ እኔም በእውነትና በጽድቅ አምላክ እሆናቸዋለሁ።” (ዘካ. 8፡6-8)። ሉቃስ 18፡18-27 ያንብቡ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠው መልስ የማይቻል በሚመስለው ሁኔታ በእግዚአብሔር እንድንታመን የሚያበረታታን እንዴት ነው?

ጥቅምት 4
Oct 14

አስታውሱ


ኢያሱ 4ን ያንብቡ። እግዚአብሔር እስራኤላውያን የመታሰቢያ ሐውልት እንዲያቆሙ የጠየቃቸው ለምንድን ነበር?



የእነዚህ ድንጋዮች ዓላማ “ምልክት” መሆን ነበር። የዕብራይስጡ ‘ኦት’ የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ “ድንቅ” ማለት ሲሆን በግብፅ ላይ እንደወረዱት መቅሰፍቶች (ዘፀ. 7፡3፣ ዘዳ. 4፡34) በእግዚአብሔር የተደረጉ ተአምራዊ ድርጊቶችን ሊያመለክት ይችላል (የትናንቱን ጥናት ይመልከቱ)። እንዲሁም ጥልቅ የሆነን እውነታ ውጫዊ “ምልክት” ለመግለፅ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። ለምሳሌ ቀስተ ደመና የቃል ኪዳኑ “ምልክት” ነው (ዘፍ. 9:12-13)፤ በእስራኤላውያን ቤት መቃኖች ላይ የተቀባው ደም “ምልክት” ተብሎ ይጠራል (ዘጸ. 12:13)፤ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰንበት የፍጥረት እና የእግዚአብሔር መቀደስ “ምልክት” ነው (ዘፀ. 31:13፣17፤ ሕዝ. 20:12)።

በዚህ ቦታ ምልክቱ እያንዳንዱ ቀጣይ ትውልድ ዮርዳኖስን ስለ መሻገር ተአምር የሚያስታውስበት መታሰቢያ ሆኖ ያገለግላል። መታሰቢያ (ዚክካሮን) የሚለው ቃል ዛካር ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን አንድን ነገር ከማስታወስ ያለፈ ተግባርን ያመለክታል። ቃሉ የሚያመለክተው ማስታወስን ተከትሎ የሚመጣ ድርጊትን ነው (ዘዳ. 5:15፣ ዘዳ. 8:2)። በብሉይ ኪዳን የድንጋይ መታሰቢያዎችን ማቆም (ዘፍ. 28፡18–22) እና ጥያቄዎችን የሚቀሰቅሱ ሥርዓቶችን (ዘጸ. 12፡ 26-27፣ ዘዳ. 6፡20-25) ማካሄድ የተለመደ ነበር። እግዚአብሔር ተአምራቱን ደጋግሞ ከመፈፀም ይልቅ የድንቅ ተግባራቱን ትውስታ የሚያነሳሱ እና ትርጉም ያላቸው መልሶችን የሚያፋጥኑ ሀውልቶች እንዲቆሙ አድርጓል።

ስለዚህ፣ ምልክቱ “ለዘላለም” መሆኑ ይህን የጌታን ተአምር ለዘላለም በህዝቡ ትውስታ ውስጥ ማቆየት አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል።

በቀጣዩ ትውልድ ሊነሳ የሚችለውና በግል ልንመልሰው የሚገባን ዋና ጥያቄ “እነዚህ ድንጋዮች ለአንተ/ቺ ምንድናቸው?” የሚለው ነው። እያንዳንዱ አዲስ ትውልድ የእነዚህን ድንጋዮች ትርጉም ከሕይወቱ ጋር አዋህዶ ሊረዳው ይገባል። ተአምረኛ በሆነው አምላክ ላይ ያለን እምነት በሕይወት ሊቆይ የሚችለው እያንዳንዱ ትውልድ የያህዌን ኃያላን ሥራዎች ከራሱ ጋር አዋህዶ ከተረዳ ብቻ ነው። እንዲህ ዓይነቱ እምነት በታማኝነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ወጎችን በመከተል እና ሙት በሆነ ግለት አልባ ወግ አጥባቂነት መካከል ትልቅ ልዩነት ያመጣል። በመጨረሻም፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን እምነት የራሳችን ማድረግ አለብን። ማንም ሰው በተለይም ቅድመ አያቶቻችን በእኛ ፈንታ ሊያምኑልን አይችሉም። እርስዎ ከጌታ ጋር ባደረጉት የእስከዛሬ ጉዞ እርሱ ያደረገልዎትን እንዲያስታውሱ የሚረዳዎት አንዳንድ የግል መታሰቢያዎች ምንድን ናቸው?

ጥቅምት 5
Oct 15

መርሳት


ኢያሱ 4፡20-24ን ከሚከተሉት ጥቅሶች ጋር በማነፃፀር ያንብቡ፡ መሳ. 3:7፣ መሳ. 8:34፣ መዝ. 78:11፣ ዘዳ. 8:2፣ 18፣ መዝ. 45፡17። የጌታን ተአምራት ማስታወስ የሚያስፈልገው ለምንድነው?



በኢያሱ 4፡23 ላይ በተውላጠ ስም የተደረገውን ለውጥ ልብ ይበሉ።

የዮርዳኖስ ውኃ “በአንተ” ማለትም ዮርዳኖስን በተሻገሩት እስራኤላውያን ፊት ደረቀ ተብሏል። በአንጻሩ ከግብጽ ምድር ከወጣው የመጀመሪያ ትውልድ ጀምሮ እስከዚያ ጊዜ የተገኙትን በመግለጽ የቀይ ባህር “ከእኛ” ፊት እንደደረቀ ይናገራል። በሁለት የተለያዩ ትውልዶች የተከሰቱት ሁለቱ ክንውኖች በትርጉም ተመሳሳይ ነበሩ፣ ይህም ሁለተኛው ትውልድ፣ በወላጆቻቸው ምስክርነት፣ ዮርዳኖስን የመሻገርን ተመሳሳይ ትርጉም እንደገና እንዲያገኝ አስችሎታል።

በአጠቃላይ፣ መርሳትን የምንገነዘበው እንደ ሰው ልጆች ሁሉ መደበኛ ባህሪ ነው። ይሁን እንጂ በመንፈሳዊ ሁኔታ መርሳት ወደ አስከፊ መዘዞች ሊመራ ይችላል።

ዛሬም ቢሆን፣ ልዩ ጥሪና ተልዕኮ ያለው ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን ማንነታችንን ጠብቀን ለመቆየት ከፈለግን ከየት እንደመጣን፣ ማን እንደ ሆንን እና የመኖራችን ምክንያት ላይ ለማተኮር የግልም ሆነ የድርጅት መንፈሳዊ ትውስታችንን የምናድስበት አጋጣሚዎች መፍጠር አለብን። 1 ቆሮንቶስ 11:24-25 እና ዮሐንስ 14:26 ያንብቡ። ክርስቶስ ለእኛ ያደረገውን ሁልጊዜ ማስታወስ ያለብን ለምንድን ነው? ከመስቀሉ የበለጠ ሌላ ምን አስፈላጊ ነገር አለ?



ኤለን ጂ ኋይት እራሳችንን ያለማቋረጥ በእግዚአብሔር ሥራ እና መገለጥ ብርሃን ካልመራን ተልእኳችንን ለመወጣት ያለንን ተነሳሽነት በእርግጠኝነት እንደምናጣ አስተውላለች፡- “ጌታ ትናንት እኛን የመራበትን መንገድ እና ትምህርቱን ካልረሳን በስተቀር ለወደፊቱ ምንም የሚያስፈራን ነገር የለም።”—Ellen G. White, Life Sketches, p. 196. ያለፈውን እና ጌታ በህይወታችን የሠራውን ማስታወስ ጠቃሚ ቢሆንም፣ በየዕለቱ የእሱን ፍቅር እና ህልውና መለማመድ የሚገባን ለምንድነው? በየዕለቱ የእሱን ፍቅር እና ህልውና መለማመድ የሚገባን ለምንድነው?

ጥቅምት 6
Oct 16

ከዮርዳኖስ ማዶ


“ባሕርን የብስ አደረጋት፥ ወንዙንም በእግር ተሻገሩ፤ በዚያ በእርሱ ደስ ይለናል።” (መዝ. 66፡6)። ሁለቱም የቀይ ባህር እና የዮርዳኖስ መሻገር ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ውስጥ የአዲስ ዘመን ምልክቶች ናቸው፣ እና ሁለቱም ምሳሌያዊ ጠቀሜታ አላቸው (መዝ. 66፡6፣ መዝ. 114፡1-7 እና 2 ነገ. 2:6-15ን ይመልከቱ)

ቀድሞውኑ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሁለቱን የመሻገር ሁነቶች የሚያገናኙ እና ከመጀመሪያው መቼት የተሻገረ ትርጉም ያዘሉ ጽሑፎች አሉ። በመዝሙር 66፡6 መዝሙረኛው የቀይ ባህርን እና የዮርዳኖስን መሻገር ታሪካዊ ምሳሌዎችን በመጥቀስ የእግዚአብሔርን የማዳን ስራ በህይወቱ ስላየ (መዝ. 66፡16-19) ያመሰግናል።

መዝሙረ ዳዊት 114 ሁለቱን ክንውኖች የሚያያይዘው ደራሲው በመካከላቸው ያለውን የጊዜ ልዩነት ስላላየ ሳይሆን ሁለቱ መሻገሮች የሚጋሩት ሥነ-መለኮታዊ ጠቀሜታ ስላለ ነው። ስለዚህም ሁለቱም ክስተቶች ለእስራኤል ህልውና አስተዋፅዖ ያደረጉ ናቸው፣ አንድ ጊዜ ከባርነት ወደ ነፃነት በመምጣት ውስጥ፣ ከዚያም ከመሬት አልባነት ወደ ሀገርነት ለመቀየራቸው አስተዋፅዖ አድርገዋል። በእነዚህ መዝሙሮች ውስጥ፣ የሁለቱ መሻገሮች ምሳሌዎች የጸሐፊውን ደረጃ ከጭቆና፣ ከድህነት፣ ረዳት ከማጣት፣ እና ከውርደት ወደ ደህንነት፣ መዳን እና ክብር መቀየሩን ያሳያሉ።

በኢያሱ ውስጥ ከተመዘገበው ጋር ተመሳሳይ በሆነ ተአምር ውስጥ የኤልያስ መነጠቅ የተከናወነው በዮርዳኖስ አጠገብ ነው። ለኤልያስ፣ ወንዙን መሻገሩ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ለውጥ አምጥቷል፡ ያም ወደ ሰማይ መወሰዱ ነው። ለውጡም ለኤልሳዕም አስፈላጊ ነበር፡ የነቢዩ ረዳት የነበረው ሰው(1ኛ ነገሥት 19፡21) የሕዝቡ ነቢይ ሆነ (2 ነገሥት 2፡22)። ማቴዎስ 3:16-17ን እና ማርቆስ 1:9ን ያንብቡ። የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የዮርዳኖስን ወንዝ ምሳሌያዊ፣ መንፈሳዊ ትርጉም እንዴት ያመለክታሉ?



የኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት፣ እንደ እስራኤል ተወካይነቱ ፣ የጥንቷ እስራኤልን ታሪክ ምሳሌነት ይከተላል። ኢየሱስ “በቀይ ባህር” እና በ“ዮርዳኖስ” ልምምዶች ውስጥ አልፏል። ከሞት አዋጅ በኋላ ከግብፅ እንዲወጣ ተጠርቷል (ማቴ. 2፡14-16)፣ ከጥንቷ እስራኤል 40 ዓመታት ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ 40 ቀናት በምድረ በዳ ኖረ (ማቴ. 4፡2) ፣ እና ከግል ህይወቱ ወደ ህዝባዊ አገልግሎቱ ሲሸጋገር፣ በዮርዳኖስ ተጠመቀ (ማቴ. 3፡16-17፤ ማር. 1፡9)።

በኋላ ላይ ዕብራውያን 3-4 እንደሚገልፀው ዮርዳኖስን የመሻገር ምሳሌያዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ ከነዓን መግባት ክርስትያኖች በማመን በኩል የሚገቡበትን“የጸጋ ዕረፍት” ምሳሌ ሆኖ ያሳያል።

ጥቅምት 7
Oct 17


ተጨማሪ ሀሳብ


የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት ከሚለው መጽሐፍ “ዮርዳኖስን መሻገር” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ ያንብቡ።

“እስራኤላውያን ወደ ከነዓን በሚያደርጉት ጉዞ ያጋጠሟቸውን ነገሮች በጥንቃቄ አጥኑ። ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ተስፋይቱ ምድር ያደረጉትን ዝግጅት በመመዝገብ የመጽሐፈ ኢያሱን ሦስተኛ እና አራተኛ ምዕራፎች አጥኑ።

ጌታ ለጥንት ሕዝቦቹ ያስተማራቸውን ትምህርቶች በማስታወስ ልባችንንንና አእምሮአችንን ማሠልጠን አለብን። ከዚያም ለእነሱ እንዲሆን እንደነደፈው፣ ለእኛም የቃሉ ትምህርቶች አስደሳች እና አስደሳች ይሆኑልናል።” Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 2, p. 994

“የዘመናችን እስራኤል ከጥንት ሕዝቦቹ በበለጠ እግዚአብሔርን ለመርሳት ወደ ጣዖት አምልኮ ለመመራት የተጋለጠ ነው። ሰንበት ጠባቂ ነን የሚሉት እንኳ ብዙ ጣዖታትን እያመለኩ ነው። እግዚአብሔር በተለይ የጥንት ሕዝቦቹን ከጣዖት አምልኮ እንዲጠበቁ አዝዟቸዋል፣ ምክንያቱም ሕያው እግዚአብሔርን ከማገልገል ቢያፈገፍጉ እርግማኑ በእነርሱ ላይ ይሆናል፤ እርሱን በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸው፣ በፍጹም ኃሳባቸው፣ በፍጹም ኃይላቸው ቢወዱት፣ ማድጋቸውን እና ቡሃቃቸውን አትረፍርፎ ይባርካል፤ ከመካከላቸውም በሽታን ያስወግዳል።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ የቤተክርስትያን ምክሮች፣ ገጽ. 609።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ተአምራዊውን የዮርዳኖስን መሻገር በክፍላችሁ ውስጥ ተወያዩበት። ተአምራዊውን የዮርዳኖስን መሻገር በክፍላችሁ ውስጥ ተወያዩበት። ተአምራትን እንዴት ትተረጉሟቸዋላችሁ? በዛሬው ጊዜ አምላክ ተመሳሳይ ተአምራትን እያደረገ እንዳልሆነ የሚመስለው ለምንድን ነው?

2. በክፍላችሁ ውስጥ በግልም ሆነ በቤተክርስቲያን ደረጃ መንፈሳዊ በክፍላችሁ ውስጥ በግልም ሆነ በቤተክርስቲያን ደረጃ መንፈሳዊ መርሳትን ለመከላከል ምን ተግባራዊ መንገዶችን ልንጠቀም እንደምንችል ተነጋገሩ። ሙሉ ክርስቲያናዊ ልምምዳችንን በኃይለኛ የቀድሞ ልምምዶች ላይ ብቻ እንዳንገነባ ከእግዚአብሔር ጋር ቀጣይነት ያለው እያደገ የሚሄድ ግንኙነት ቢኖረን መልካም ቢሆንም፣ ያለፉ ልምምዶቻችንን እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንዴት እንደሠራ ለማስታወስ ልንጠቀምባቸው የምንችለው እንዴት ነው?

3. ሰንበት በአንድ በኩል፣ የእግዚአብሔርን በሕይወታችን ውስጥ ሰንበት በአንድ በኩል፣ የእግዚአብሔርን በሕይወታችን ውስጥ ጣልቃ ገብነት እንድናስታውስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ በዘላለማዊ መንግሥቱ ውስጥ ስለሚኖረን ዕረፍት ቅድመ ቅምሻ የሚሰጠን እንዴት ይመስላችኋል? ሰንበት ማስታወስ የሚገባንን ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ተስፋ የምናደርገውን የሚጠቁመን እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL