የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከኢያሱ መጽሐፍ የሚገኙ የእምነት ትምህርቶች



4ኛ ሩብ ዓመት 2025


መስከረም 24 - 30

2ኛ ትምህርት

Oct 4 - 10




የፀጋ ጉብኝት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፦ ኢያሱ 2:1-21 ፣ ዘሁ. 14:1-12 ፣ ዕብ. 11:31 ፣ ዘፀ. 12:13 ፣ ኢያሱ 9 ፣ ነህ. 7:25።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙ ጋር በእምነት አልጠፋችም። ዕብ. 11:31

የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ሁለተኛ እድል ተሰጠው እና ኢያሱም ይህን ኃላፊነት በትኩረት ወስዶታል። የመጀመሪያው እርምጃ ከፊታቸው ሊገጥማቸው ስላለው ነገር ትክክለኛ ማስተዋልን መያዝ ነው። ሁለት ሰላዮችን ስለ ምድሪቱ ስለ መከላከያው፣ ስለ ጦርነት ዝግጁነታቸው፣ ስለ ውሃ አቅርቦታቸው እና ወራሪ ሲመጣ ህዝቡ ስላላቸው አመለካከት መረጃን እንዲያመጡ ላከ።

አንድ ሰው ምድሪቱን ለመውረስ ለእስራኤላውያን እግዚአብሔር የሰጣቸው የተስፋ ቃል በህዝቡ በኩል ጥረት የሚጠይቅ ላይመስለው ይችላል። ሆኖም የመለኮታዊው እርዳታ መኖር እርግጠኝነት የሰውን ኃላፊነት አያስቀርም። እስራኤል በከነዓን ድንበር ለሁለተኛ ጊዜ ቆሟል። ብዙ ጉጉት የነበረ ቢሆንም እስራኤል ለመጨረሻ ጊዜ በድንበሩ ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ በነበሩበት ወቅት ከባድ ውድቀት አጋጥሟቸው ነበር።

በዚህ ሳምንት በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ የሚገኙ ሁለት አስደናቂ ታሪኮችን እንመረምራለን። ዛሬ ላለን እምነትም ያለውን ፋይዳ እንመለከታለን።

የእግዚአብሔር ፀጋ እኛን የሚያስደንቁ መንገዶች አሉት። ለጥቅምት 1 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

መስከረም 25
Oct 5

ሁለተኛ ዕድል


ኢያሱ 2:1ን ከዘኍ. 13:1- 2፣ 25–28፣ 33፣ እና ዘኍ. 14፡1-12 ጋር ያንብቡ።

ኢያሱ የተስፋይቱን ምድር የመውረስ ተልእኮውን ሰላዮችን በመላክ የጀመረው ለምንድን ነው?



ሁለቱ ሰላዮች የተላኩበት ቦታ አካሽያ ግሮቭ (አኪጄቪ) በዕብራይስጥ “ሺቲም” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሁለት የእስራኤልን ታሪክ አሉታዊ ገጽታዎች ያስታውሰናል።

የመጀመሪያው ተመሳሳይ አስፈላጊ ነገሮችን ማለትም የሰላዮቹን ተልዕኮ፣ በጠላት ግዛት ውስጥ የሰላዮቹን ሚስጥራዊ አገባብ፣ የሰላዮቹን መመለስ፣ በግኝታቸው ላይ የሰላዮቹ ሪፖርት፣ እና በሪፖርቱ መሰረት እርምጃ ለመውሰድ የተደረገ ውሳኔን የያዘ ሌላ የስለላ ታሪክ ነው (ዘኍልቍ 13)።

በሺቲም ላይ የተከሰተው ሌላው ክስተት እስራኤላውያን በበለዓም አነሳሽነት ከሞዓባውያን ሴቶች ጋር ዝሙት መፈፀማቸው እና አማልክቶቻቸውን ማምለካቸው (ዘኁ. 25፡1-3፣ ዘኁ. 31፡16) የታየበት እና ሕዝቡ በምንዝር ቃል ኪዳኑን የጣሱበት ሁኔታ ነው። ከዚህ ዐውድ አንፃር፣ የሺቲም ስም የታሪኩን አጠቃላይ የወደፊት አቅጣጫ በተመለከተ ከባድ ውጥረት ይፈጥራል።

በተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ሌላ ውድቀት ይመጣ ይሆን? ወይስ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው እድሜ ጠገቡ ተስፋ ፍጻሜውን ያገኝ ይሆን? ዮሐንስ 18:16-18፣ 25-27 እና ዮሐንስ 21:15-19 ያንብቡ። ለእስራኤል እንደ ሕዝብ እና ለጴጥሮስ እንደ ግለሰብ በተሰጠው ሁለተኛ ዕድል መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?





እግዚአብሔር የሁለተኛ እድሎች አምላክ ነው (ከሁለትም በላይ)።

መጽሐፍ ቅዱስ ሁለተኛውን ዕድል (ከሁለትም በላይ የሆነውን) “ጸጋ” ብሎ ይጠራዋል። ጸጋ በቀላሉ የማይገባንን መቀበል ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በጸጋ ጽንሰ ሐሳብ የተሞላ ነው (ከሮሜ 5፡2፣ ኤፌ. 2፡8፣ ሮሜ. 11፡ 6 ጋር ያነፃፅሩ)። እግዚአብሔር በጸጋ ለሁሉም የአዲስ ጅምር እድል ይሰጣል (ቲቶ 2፡11–14)። ጴጥሮስ ራሱ ይህንን ጸጋ ተቀብሎ ቤተክርስቲያን በጸጋ እንድታድግ አሳስቧል (2ጴጥ. 3፡18)። እናም ዜናው የበለጠ ተሻሽሎ ከሁለተኛ እድል በላይ እናገኛለን፣ አይደል? (ባይሆን የት እንሆን ነበር?) ስለ እስራኤላውያን ተሞክሮ፣ ወደ ከነዓን ለመግባት ሁለተኛ እድል ስለማግኘታቸው እና ጴጥሮስ ጌታውን ከካደ በኋላ ስለተቀበለው ጸጋ ያስቡ።

እኛም ጸጋን ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዴት መስጠት እንዳለብን እነዚህ ክስተቶች ምን ያስተምሩናል?

መስከረም 26
Oct 6

ባልተጠበቀ ቦታ የተገኘች


ኢያሱ 2፡2-11፣ ዕብራውያን 11፡31 እና ያዕቆብ 2፡25 ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ ረዓብ ምን ይነግሩናል?



በረዓብ ታሪክ ውስጥ ማዕከል የሆነው ጉዳይ ሰላዮቹን ለመጠበቅ የተነገረው ውሸት ነው። ውሸቷን ስንመለከት፣ በመጨረሻ እግዚአብሔር በዚያ ማህበረሰብ ላይ ጥፋትን ለማምጣት እስኪወስን ድረስ (ዘፍ. 15፡16፣ ዘዳ. 9፡5፣ ዘሌ. 18፡25-28) እጅግ በጣም ኃጢአተኛ በሆነው ማህበረሰብ ውስጥ እንደነበረች ልንገነዘብ ይገባናል። አዲስ ኪዳን እምነቷን እንደ አብነት የሚጠቅስ መሆኑ እውነት ቢሆንም፣ የረዓብን ድርጊት በተመለከተ የአዲስ ኪዳንን ማጣቀሻዎች በጥንቃቄ ስንመረምር ማንም ስለ እሷ ሁሉንም ነገር እንደማይደግፍ እና ውሸቷን የሚያበረታታ እንደሌለ እንመለከታለን።

ዕብራውያን 11፡31 በዙሪያዋ የነበረውን ብልሹ ባሕል የሙጥኝ ከማለት ይልቅ ከሰላዮቹ ጋር መሆንን መምረጧ የእምነቷ ማረጋገጫ መሆኑን ይናገራል። ያዕቆብ 2:25 ደግሞ ሁለቱ እስራኤላውያን ሰላዮችን በቤቷ በማሳደሯ እና በሰላም መንገድ እንዴት እንደሚመለሱ አቅጣጫ በማሳየቷ ያመሰግናታል።

በከፋ፣ ብልሹ በሆነ ባህል እና በኃጢአተኛ የረዓብ የአኗኗር ዘይቤ መሀል፣ እግዚአብሔር በጸጋው፣ ሊያድናት የሚችልበትን የእምነት ብልጭታ አየ።

እግዚአብሔር በረዓብ መልካም የሆነውን ማለትም በእርሱ ላይ ያላትን በሥራ የተገለጠ እምነት እና ከእግዚአብሔር ህዝብ ጋር ለመሆን የመረጠችውን ምርጫ አክብሮታል፤ ነገር ግን ያደረገችውን ሁሉ ትክክል ብሎ አልተናገረም።

እግዚአብሔር የረዓብን ልዩ የሆነ ድፍረት፣ ቆራጥ እምነት፣ የመዳን ወኪል መሆን እና የእስራኤል አምላክን መምረጥ ከፍ አድርጎ ተመለከተው።

የሆነውን ነገር ካየች በኋላ “አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነው” ብላ አወጀች (ኢያሱ 2:11)። አንዲት ከነዓናዊት በተለይ ደግሞ በአረማዊ ሃይማኖቷ የሰማይ አማልክት ናቸው ተብለው ለሚታመኑት ጸሎቶች ይቀርቡ የነበረበት ሰገነት ከነበራት ሴት ይህን መስማት አስገራሚ ነው።

የረዓብ አገላለጽ እግዚአብሔር ከዚህ ቀደም አምልኮ ለእሱ ብቻ መሆኑን በተናገረበት አውድ ውስጥ ብቻ ይገኛል (ዘፀ. 20:4፣ ዘዳ. 4:39፣ ዘዳ. 5:8)። ቃላቷ አስባበት እና በማስተዋል መርጣ የእስራኤል አምላክ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን አምና መቀበሏን ይመሰክራሉ። ንግግሯ በአምላክ ሉዓላዊነት እና በኢያሪኮ ላይ ሊመጣ ባለው ፍርድ መካከል ያለውን የጠበቀ ዝምድና መረዳቷን ያሳያል።

ከያህዌ ፍርድ አንፃር፣ ሁለት አማራጮች ብቻ እንደነበሩ ተረድታለች፡ ማለትም በእርሱ ላይ ማመፅን መቀጠል እና መደምሰስ፣ ወይም በእምነት እጅ ለመስጠት መምረጥ። የእስራኤላውያንን አምላክ በመምረጥ የኢያሪኮ ነዋሪዎች በሙሉ ወደ እስራኤል አምላክ ቢመለሱ ኖሮ ምን ዓይነት ዕጣ ፈንታ ሊኖራቸው እንደሚችል ረዓብ አሳየች። ይህ ታሪክ ለእግዚአብሔር እስከ መጨረሻው ታማኝ መሆን እንዳለብን የሚያስተምረን እንዴት ነው?

መስከረም 27
Oct 7

አዲስ መሐላ


ኢያሱ 2፡12-21ን እና ዘፀአት 12:13፣22፣23ን ያንብቡ። በዘፀአት ላይ የሚገኙት ጥቅሶች በሰላዮቹና በረዓብ መካከል ያለውን ስምምነት እንድንረዳ የሚረዱን እንዴት ነው?



የረዓብ ስምምነት በጣም ግልጽ ነው፡ ሕይወት ለሕይወት እና ደግነት ለደግነት። ቼሰድ (ኢያሱ 2:12) የሚለው ቃል፣ “ከፍቅር የሆነ ደግነት” የሚለው ቃል በሌሎች ቋንቋዎች በአንድ ቃል መግለጽ የሚከብድ ብዙ ትርጉም አለው። ቃሉ በዋነኛነት የሚያመለክተው ቃል ኪዳናዊ ታማኝነትን ነው፤ ነገር ግን ታማኝነትን፣ ምህረትን፣ በጎነትን እና ደግነትን ጭምር የሚገልፅ ነው።

የረዓብ ቃል እግዚአብሔር ራሱ ለእስራኤል ቸርነቱን ለመጠበቅ ሲል የማለበትን ዘዳግም 7፡12ን ያስታውሳል። “እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለአንተ ይጠብቅልሃል፤” (ዘዳ. 7፡12)።

የሚገርመው፣ ይኸው ምዕራፍ (ዘዳግም 7) በከነዓናውያን ላይ እርግማንን (ቼረም) ያዝዛል። በእርግማን ሥር የነበረችው ከነዓናዊቷ ረዓብ ግን በማደግ ላይ ባለው እምነቷ ለእስራኤላውያን የተገባውን ተስፋ አረጋገጠች።

በዚህም ምክንያት ዳነች።

ሰላዮቹ ከረዓብ ጋር ካደረጉት ውይይት ጋር ተያይዞ ወደ አእምሮ የሚመጣው የመጀመሪያው ምስል በዘፀአት ላይ ያለው ፋሲካ ነው። እዚያም እስራኤላውያን ጥበቃ እንዲደረግላቸው በቤታቸው ውስጥ ተቀምጠው የቤቶቻቸውን መቃኖች በተሠዋው በግ ደም መቀባት ነበረባቸው።

“ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም።” (ዘፀ. 12፡13፣ 22-23)

“ህዝቡ በመታዘዝ ለማመናቸው ማረጋገጫ መስጠት ነበረባቸው።

በክርስቶስ ደም ሥራ በማመን ሊድኑ ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ መዳናቸውን ለማረጋገጥ በሥራ ሊገልጡት ይገባል። ከኃጢአት ቅጣት የሚዋጀን ክርስቶስ ብቻ ቢሆንም ከኃጢአት ወደ መታዘዝ መመለስ ይኖርብናል። ሰው በሥራ ሳይሆን በእምነት ነው የሚፀድቀው፤ ነገር ግን ማመኑ በተግባር ሊገለጥ ይገባዋል።” ኤለን ጂ. ኋይት ፣ የኃይማኖት አባቶች እና ነብያት፣ ገፅ 279

ከዚህ አንፃር ደሙ ከአጥፊው መልዓክ ለመዳናቸው ማረጋገጫ ነበር።

እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በግብፅ ከነበረው የመጨረሻ መቅሰፍት እንዳዳናቸው እስራኤላውያኑ ረዓብን እና ቤተሰቧን በኢያሪኮ ሊመጣ ከነበረው ጥፋት ማዳን ነበረባቸው።

በነዚህ ሁለት ታሪኮች ውስጥ ምን አይነት ኃይለኛ የወንጌል መልዕክቶችን እናገኛለን? ምን ዓይነት ትምህርቶችንስ እናገኝባቸዋለን?

መስከረም 28
Oct 8

የሚጋጩ እሴቶች


ኢያሱ 9፡1-20ን ያንብቡ። በገባዖናውያኑ እና በረዓብ ታሪክ መካከል ያለው መመሳሰል እና ልዩነት ምንድነው? ታሪኮቹ ትርጉም ያላቸው የሆኑት ለምንድነው?



የመጽሐፈ ኢያሱ ይህ ምዕራፍ በትናንሽ ከተሞች ላይ የነገሱ አምስት ከነዓናውያን ነገስታት ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት ጥምረት እንደፈጠሩ ይነግረናል። በተቃራኒው የገባዖን ሰዎች ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት ወስነዋል።

እስራኤላውያኑን ለማታለልና ቃል ኪዳን ለመግባት ገባዖናውያን ከሩቅ አገር የመጡ ተወካዮች ነን በማለት አሴሩ። በዘዳግም 20፡10-18 መሠረት እግዚአብሔር በከነዓናውያን እና ከተስፋይቱ ምድር ውጪ በሚገኙት መካከል ልዩነትን ፈጥሯል።

ተንኮል ተብሎ የተተረጎመው ቃል በአዎንታዊ ሲወሰድ ብልሃትን እና ጥበብን(ምሳሌ 1፡4፣ ምሳሌ 8፡5፣12) ለመግለፅ ልንጠቀመው የምንችል ሲሆን በአሉታዊ ደግሞ ለማጥፋት ወይም ወንጀልን ለመሥራት ማሴርን ሊገልፅ ይችላል(ዘፀ. 21፡14፣ 1 ሳሙ. 23፡22፣ መዝ. 83፡3)። ከገባዖናውያን አንፃር ሲታይ ከድብቁ ተግባራቸው ጀርባ ራስን የማቆየት እና አነስተኛ ጉዳት የሚያመጣ ሆኖ እናየዋለን።

የገባዖናውያኑ ቃላት ከረዓብ ቃላት ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።

ሁለቱም የእስራኤልን አምላክ ኃይል ገልፀዋል፣ የእስራኤል ስኬትም ከሰው እንዳልሆነ ተረድተዋል። ከሌሎቹ ከነዓናውያን በተቃራኒ ምድሪቱን ለእስራኤል ለመስጠት እግዚአብሔር ያቀደውን እቅድ አይቃወሙም፤ እነዚህንም ሕዝቦች ከእስራኤል ፊት እንዲሸሹ የሚያደርጋቸው ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ አምነዋል። ከግብፅ የመውጣታቸው ዜና እና በኦግ እና በሲሆን ላይ የተቀዳጇቸው ድሎች ከእስራኤላውን ጋር እንዲወዳጁ ምክንያት ሆኗቸዋል።

ሆኖም ልክ ረዓብ እንዳደረገችው ለእስራኤል አምላክ ራሳቸውን ለማስገዛት ፈቃደኛ ከመሆን ይልቅ ገባዖናውያኑ ግባቸውን ለማሳካት ማታለልን መረጡ።

እንደዚህ ባሉት ጉዳዮች የሙሴ ሕግ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመማር መደረግ ያለበትን አስቀምጧል (ዘሁ. 27፡16-21)። ኢያሱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቆ ከገባዖን ሰዎች ማታለል መራቅ ይችል ነበር።

የማንኛውም ክርስቲያን መሪ መሰረታዊ ግዴታ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈለግ ነው (1ዜና. 28፡9፣ 2ዜና. 15፡2፣ 2 ዜና 18፡4፣ 2 ዜና. 20፡4)።

ይህንን ችላ በማለታቸው እስራኤላውያኑ መሬቱን ለመውረስ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ሁኔታዎች ለመጣስ ወይም በጌታ ስም የገቡትን መሐላ ለማፍረስ የሚያስገድድ አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ። ራሳችንን በሁለት የሚጋጩ በሚመስሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እሴቶች መካከል ስንታገል ያገኘነው ምን ያህል ጊዜ ይሆን?

መስከረም 29
Oct 9

አስደናቂ ጸጋ


ኢያሱ 9:21-27ን ያንብቡ። የኢያሱ መፍትሔ ፍትህን ከጸጋ ጋር ያጣመረው እንዴት ነው?



እስራኤላውያን ገባዖናውያንን ለማጥቃት ቢፈልጉም እንኳ መሐላ (ውል) በመግባታቸው ምክንያት አይፈቀድላቸውም ነበር። የእስራኤላውያን መሪዎች አንድ መሐላ ኃጢአትን ወይም የወንጀል ድርጊትን እስካልፈቀደ ድረስ (መሳ. 11:29-40) አንድ ሰው ላይ በግል ጉዳት ቢደርስም እንኳ አስገዳጅነት እንዳለው በሚገልጸው መሠረታዊ ሥርዓት መሠረት ይተዳደራሉ።

በብሉይ ኪዳን ከመሐላ በፊት ማስተዋል እና መሐላውን ማክበር ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዳለው ሰው ምግባሮች ይታያሉ (መዝ. 15:4፣ መዝ. 24:4፣ መክ. 5:2፣6)። መሐላው በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ስለተፈጸመ መሪዎቹ ሊለውጡት አልቻሉም።

በእስራኤላውያን መሪዎች በተካሄደው ታላቅ መሐላ፣ የእስራኤል እጣ ፈንታ ከገባዖናውያን ጋር ፈጽሞ የተያያዘ ሆነ። እንደውም ገባዖናውያን ለአምላክ ቤት እንጨት ጠራቢዎችና ውኃ አቀባዮች በመባላቸው (ኢያሱ 9:23) ምክንያት የእስራኤል አምላኪ ማኅበረሰብ አካል ሆኑ። የእስራኤል ገዥዎች ከሰጡት ፍርድ በተለየ የኢያሱ መልስ፣ “ለጉባኤው ሁሉ” አገልጋይ እንዲሆኑ በማወጅ (ኢያሱ 9፡21) እርግማኑን ለገባዖናውያን በረከት ሊሆን ወደሚችል ሁኔታ ለውጦታል (ከ 2ሳሙ. 6፡11 ጋር ያነፃፅሩ)።

ተከታዩ የገባዖን ታሪክ ከተማዋ ያገኘቻቸውን ከፍተኛ ሃይማኖታዊ መብቶች እንዲሁም ለአምላክ ሕዝቦች ያላቸውን ታማኝነት ይመሰክራል።

እስራኤላውያን የገቡት ቃል ኪዳን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ቆይቶ እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ሲመለሱ ገባዖናውያን ኢየሩሳሌምን ለመገንባት ከረዱት መካከል ሆኑ(ነህ. 7፡25)። ተግባራቸው ዘላለማዊና አዎንታዊ ውጤት ይኖረዋል ነገር ግን ይህ የሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ብቻ ነው።

ገባዖናውያን ማንነታቸውን ቢገልጹና ረዓብ እንዳደረገችው ምሕረትን ጠይቀው ቢሆን ምን ሊሆን ይችል ነበር? አናውቅም፣ ነገር ግን የእስራኤላውያን የአምላክን ፈቃድ መጠየቅ ገባዖናውያንን ከመጥፋት ሊያድናቸው እንደሚችል እንኳን አፋችንን ሞልተን መናገር አንችልም። የእግዚአብሔር የመጨረሻ ዓላማ ኃጢአተኞችን መቅጣት ሳይሆን ንስሐ ሲገቡ ማየት እና ምህረቱን መስጠት ነው (ከሕዝ. 18፡23 እና ሕዝ. 33፡11 ጋር ያነፃፅሩ)። የገባዖናውያን የማታለል ሥራ የእግዚአብሔርን ምሕረት፣ ደግነቱን እና ፍትሐዊ ባህሪውን እንደመጠየቅ ሊታይ ይገባዋል። ከነዓናውያን እንዲጠፉ ያደረጋቸው ንስሐ ለመግባት እምቢ ማለታቸው እና የእግዚአብሔርን ዓላማ መቃወማቸው ነው (ዘፍ. 15፡16)።

እግዚአብሔር ገባዖናውያን ለእርሱ ታላቅነት እውቅና መስጠታቸውን፣ ከአመፅ ይልቅ ሰላም እንዲሰፍን ያላቸውን ፍላጎት እንዲሁም ጣዖት አምልኮን ለመተው እና እውነተኛውን አምላክ ብቻ ለማምለክ ያላቸውን ፈቃደኝነት አከበረ።

መስከረም 30
Oct 10


ተጨማሪ ሀሳብ


የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት ከሚለው መጽሐፍ ላይ ዮርዳኖስን መሻገር የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ ያንብቡ።

ከዚህ የረዓብና የሰላዮች ታሪክ በኋላ፣ በኢየሱስ የትውልድ ሐረግ እንደገና ስሟ እስኪጠቀስ ድረስ የቀረው የብሉይ ኪዳን ስለ እርሷ ምንም አይናገርም። ከይሁዳ ነገድ የሆነው የሳልሞን ሚስት፣ የቦዔዝ አያት፣ እና በተመሳሳይ የትውልድ ሐረግ ውስጥ የተጠቀሰችው የሌላዋ አስደናቂ ሴት የሩት አማች እንደሆነች ተገልጿል (ማቴ. 1:5፣ 4:13፣ 21 ጋር ያነፃፅሩ)። ሙሉ በሙሉ እንድትጠፋ ተፈርዶባት የነበረችው የኢያሪኮ ጋለሞታ በእግዚአብሔር ላይ ባላት እምነት የተነሳ በዳዊት ንጉሣዊ የዘር ሐረግ ውስጥ የገባች ስትሆን የመሲሑ ዘር ግንድ ውስጥም ትገኛለች። እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት እምነታችን ትንሽ እንኳን ብትሆን እግዚአብሔር እርሱን በማመናችን ምክንያት ይህንን ሊፈጽመው ይችላል (ማቴ. 17፡20፣ ሉቃ. 17፡6)።

“የረዓብ መለወጥ እግዚአብሔር አምላካዊ ሥልጣኑን ለተቀበሉ ጣዖት አምላኪዎች ያለው ምሕረት ብቸኛ ታሪክ አልነበረም። በምድሪቱ መካከል ብዙ ሕዝብ ማለትም ገባዖናውያን አረማዊነታቸውን ትተው ከእስራኤል ጋር በቃል ኪዳኑ በረከቶች ተካፍለዋል።

“የብሔር፣ የጎሳ ወይም የዘር ልዩነት በእግዚአብሔር ዘንድ አይታወቅም።

እርሱ የሰው ልጆች ሁሉ ፈጣሪ ነው። ሰዎች ሁሉ በፍጥረት አንድ ቤተሰብ ናቸው፤ ሁሉም ደግሞ በክርስቶስ መቤዠት ምክንያት አንድ ናቸው። ክርስቶስ የመጣው የልዩነት አጥሮችን ለማፍረስ የቤተመቅደስ ክፍሎችን ከፍቶ ነፍስ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ ዕድልን እንዲያገኝ ለማድረግ ነው። ፍቅሩ ሁሉንም ገደብ አልፎ መግባት የሚችል ሰፊና ጥልቅ ነው። በሰይጣን ማታለል የወደቁትን ከወጥመድ አላቆ በተስፋ ቃል ቀስተ ደመና ወደተከበበው ወደ አምላክ ዙፋን ያቀርባቸዋል። በክርስቶስ አይሁድ ወይም ግሪክ፣ ባሪ ወይም ነፃ ሰው የለም።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ ነቢያትና ነገስታት ገፅ 369-370


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ስለ “ሁለተኛ ዕድሎች” (ወይም ከዚያ በላይ ስላገኘናቸው ዕድሎች) ስለ “ሁለተኛ ዕድሎች” (ወይም ከዚያ በላይ ስላገኘናቸው ዕድሎች) አጠቃላይ ጥያቄን እና እንዴት ለሌሎች ያንን ፍቅር ማሳየት እንዳለብን ተወያዩ። በተመሳሳዩ ይህን ጽንሰ ሐሳብ አላግባብ ከመጠቀም መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ያህል፣ በግንኙነት ውስጥ በደል የተፈጸመባትን ሴት፣ አንዳንድ ጊዜ በደሉ(ጥቃቱ) ሊቀጥል ቢችል እንኳን በፍቅር ግንኙነቱ ውስጥ እንድትቀጥል መምከር ልክ ይሆናል? በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ትክክለኛውን ሚዛን ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

2. ረዓብን እንደ እምነት ምሳሌ አድርጋችሁ ተወያዩባት። አኗኗራቸው ረዓብን እንደ እምነት ምሳሌ አድርጋችሁ ተወያዩባት። አኗኗራቸው ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ የራቀ ቢሆንም እንኳ ሰዎች ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፈቃደኝነት ማድነቅ የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንድ ተግባሮቻቸውን ችላ ብሎ እምነታቸውን ማድነቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

3. ኢያሱ በገባዖናውያን ሽንገላ ምክንያት እና ጌታን ባለማማከሩ በራሱ ኢያሱ በገባዖናውያን ሽንገላ ምክንያት እና ጌታን ባለማማከሩ በራሱ ቸልተኝነት የመጣበትን ችግር ለመፍታት ፍትህንና ጸጋን በተግባራዊ መንገድ አገናኝቷል። በሕይወታችሁ ውስጥ ፍትህ እና ጸጋን የሚፈልግ ሁኔታን አስቡ። ሁለቱን ማዋሃድ የምንችልባቸው ተግባራዊ መንገዶች ምንድናቸው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL