የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፦ ዘዳ. 18፡15-22፣ ኢያሱ 1፣ ዕብ. 6፡17-18፣ ኤፌ. 6፡10-18፣ መዝ. 1፡1-3፣ ሮሜ 3፡31።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን
ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ
ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። (ኢያሱ 1፡7)
የቦስተን ፊልሐርሞኒክ ኦርኬስትራ የሙዚቀ ዳይሬክተር የሆነው ቤንጃሚን
ዛንደር የሙዚቃ ትርጉም ክፍለ ጊዜን ያስተምራል። ብቃታቸው
በሚፈተሽበት ጊዜ የተማሪዎቹን ጭንቀት ይመለከት ስለነበር ተማሪዎቹ
እንዳይጨናነቁ እና ሙሉ አቅማቸውን መጠቀም እንዲችሉ በመጀመሪያው
ክፍለ ጊዜ ሁሉም ሰው ኤ እንደሚያገኝ ነገራቸው። ይህ ኤ ግን ዝም ብለው
የሚጠብቁት ሳይሆን ለማግኘት በመስራት ውስጥ የሚሳካ ነበር። ብቸኛው
ቅድመ ሁኔታ ተማሪዎቹ በሴሚስተሩ የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት ውስጥ
የደብዳቤውን ቀን የትምህርቱ መጨረሻ ቀን አድርገው ደብዳቤ መፃፍ ነበር።
ደብዳቤው ለምን ያ ከፍ ያለ ውጤት እንደሚገባቸው መግለፅ ነበረበት።
የኢያሱ መጽሐፍ የሚናገረው ስለ አዲስ ጅማሮዎች እና አዲስ
ውጤቶች ነው። የእስራኤልን ታሪክ 40 ዓመታት የመራው ሙሴ አሁን ያለፈ
ታሪክ ነበር። በሚያሳዝን ሁኔታ በአመፅ እና በአንገተ ደንዳናነት የሚታወቀው
ከግብጽ የመውጣትና በበረሃ የመንከራተት ዘመን አብቅቷል። እግዚአብሔርን
ለመታዘዝ ፈቃደኛ የሆነው አዲሱ ትውልድ፣ እንዲሆን በተስፋ እንደሚጠብቅ
ሳይሆን በውስጡ እንደሚኖር ሕዝብ፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት
ተዘጋጅቶ ነበር።፡
በእስራኤል ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔር እንዴት አዲስ ምዕራፍን
እንደከፈተ እና በእኛም ሕይወት ውስጥ ተመሳሳዩን ማድረግ እንደሚችል
የሚናገረውን ታሪክ አብረን እናጥና።
ለመስከረም 24 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።
ዘዳግም 18፡15-22ን እና ኢያሱ 1፡1-9ን ያንብቡ። መጽሐፈ ኢያሱ ሙሴ ከሞተ በኋላ ሊሆን ስለሚችለው ነገር የተነገረውን የተስፋ ቃል በማስተጋባት መጀመሩ ፋይዳው ምንድን ነው?
ምንም እንኳን ሙሴ ሞቶ አዲሱ መሪ ኢያሱ በእግዚአብሔር ቢቀባም
ሁለቱንም የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። ሁለቱም ህዝቡን ለአባቶቻቸው
ቃል ወደተገባችው ምድር እንደሚመሩ በእግዚአብሔር ተነግሯቸዋል።
እግዚአብሔር ለኢያሱ እንዳለው “ለሙሴ እንደ ነገርሁት የእግራችሁ ጫማ
የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቼአለሁ።” (ኢያሱ 1፡3)። ኢያሱ
መጀመሪያ ለሙሴ የተሰጠውን ሥራ ሊጨርስ ነው። እውነትም አዲስ ሙሴ።
ዘፀ. 33፡11፣ ዘሁ. 14፡6፣ 30፣ 38፣ ዘሁ. 27፡18፣ ዘሁ. 32፡12፣ ዘዳ. 1፡38፣ ዘዳ.
31፡23 እና ዘዳ. 34፡9ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለኢያሱ ምን ይነግሩናል?
እዚህ ጋ እግዚአብሔር እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ እንደሚያስነሳላቸው
የተነገረው የተስፋ ቃል የተፈፀመ ሳይሆን ገና ሊሆን የሚችል ብቻ ነበር።
መጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ ያሉ የመጀመሪያ ቃላት አንባቢዎቹ ይህን የተስፋ ቃል
በማስታወስ ሊፈፀም ይችላል ብለው እንዲጠብቁ ያነሳሳል።
ሙሴ ቢሞትም የመጀመሪያውን ምዕራፍ ሞልቶት ነበር። የሙሴ
ስም አስር ጊዜ ሲጠቀስ የኢያሱ ግን አራት ጊዜ ብቻ ተጠቅሷል። ሙሴ
“የእግዚአብሔር አገልጋይ” ተብሎ የተጠራ ሲሆን ኢያሱ “የሙሴ
አገልጋይ” ተብሎ ተጠርቷል(ኢያሱ 1፡1)። ኢያሱ “የእግዚአብሔር አገልጋይ”
ተብሎ እንዲጠራ ህይወቱን ሙሉ በታማኝነት እና በታዛዥነት ማገልገል
ነበረበት(ኢያሱ 24፡29)።
ምንም እንኳን የመጽሐፈ ኢያሱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በእስራኤል
ሁለቱ ታላላቅ መሪዎች የመሪነት ሽግግር ላይ ቢያተኩርም ዋናው ገፀ ባህሪ
ቃሉ የመጽሐፉ መክፈቻ የሆነው እና ምሪቱ በሙላት የተገለጠው ራሱ
እግዚአብሔር ነው።
በዘመናት ሁሉ እግዚአብሔር ወንዶችን እና ሴቶችን የራሱን ሕዝብ
እንዲመሩለት ሲጠራ ነበር። የማይታየው የቤተክርስትያን መሪ ማን እንደሆነ
ማወቅ ወሳኝ የሆነው ለምንድነው?
ኢያሱ ምዕራፍ 1ን ያንብቡ። ከዚህ መክፈቻ ከሆነ ምዕራፍ ስለ መጽሐፉ ቅርጽ ምን መማር እንችላለን?
የኢያሱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ለመላው መጽሐፍ መግቢያ ሆኖ
ያገለግላል። ከመጽሐፉ አራት ዋና ዋና ክፍሎች ጋር የሚዛመዱ አራት ንግግሮችን
ያካትታል፡ መሻገር (ኢያሱ 1፡2-9)፣ መውረስ (ኢያሱ 1:10-11)፣ ምድሪቱን
መከፋፈል (ኢያሱ 1፡12-15)፣ እና ለሕግ በመታዘዝ ማገልገል (ኢያሱ 1፡16-18)።
የኢያሱ መጽሐፍ በመለኮት አነሳሽነት የተደረጉ ተከታታይ ነገሮችን
እንደያዘ ሊታይ ይችላል። እያንዳንዱን እግዚአብሔር ሲያነሳሳ ለኢያሱ
ከከነዓን ድል ጋር የተያያዘ የተለየ ሥራ ሰጥቶታል፤ እያንዳንዱም በተሳካ ሁኔታ
ከተጠናቀቀ በኋላ በመጽሐፉ ውስጥ ተገልጧል።
በመጨረሻ፣ ስለ ምድሪቱ ወረራ እግዚአብሔር የገባቸው የተስፋ ቃላት
ይፈጸማሉ። ከዚያን በኋላ ምድሪቱን የማቆየት ኃላፊነት በእስራኤላውያን እጅ
ላይ ስለሚወድቅ ሊሳካ የሚችለው በእውነተኛ እምነትና ከእውነተኛ እምነት
ሁሌም በሚመነጨው መታዘዝ ብቻ ነበር።
በሦስቱ ግሦች የተገለጹት የእግዚአብሔር ኃሳቦች፡- “መሻገር”፣
“መውረስ” እና “መከፋፈል” ከአራተኛው ኃሳቡ ማለትም ከ“ማገልገል”
በሚመነጨው ታዛዥነት ውስጥ ተገቢውን መልስ ያገኛሉ።
የኢያሱ መጽሐፍም አራት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፣ እያንዳንዱም
በዕብራይስጥ ቃል ጠበቅ ብለው በተገለጹት ልዩ ጽንሰ-ሐሳቦች ይገለጻል።
(1) መሻገር (ኢያሱ 1:1-5:12)
(2) መውረስ (ኢያሱ 5:13-12:24)
(3) መካፈል (ኢያሱ 13:1-21:45)
(4) ማገልገል (ኢያሱ 22፡1-24፡33)።
ስለዚህ የመጽሐፉ አወቃቀር ራሱ ዋና መልእክቱን ያስተላልፋል፤
የእግዚአብሔር ኃሳቦች ወዲያውኑ አይፈጸሙም። ይልቁንም፣ የህዝቡን
ታማኝ ምላሽ ይፈልጋሉ። ማለትም ለራሳችን ማድረግ የማንችለውን ሁሉ
እግዚአብሔር እንዳደረገልን ስናውቅ እኛም ከእኛ የሚጠበቀውን እንድናደርግ
ተጠርተናል፡- ይህም እግዚአብሔር እንድናደርገው ያዘዘንን መፈፀም ነው።
በሁሉም የተቀደሰ ታሪክ ውስጥ እንደዚህ ነበር፤ ዛሬም እንደዛው ነው። ለምሳሌ
በራእይ 14፡12 ላይ ያለው የእግዚአብሔር የመጨረሻ ዘመን ሰዎች መግለጫ
ተመሳሳይ ሐሳብ ያስተላልፋል፡ እግዚአብሔር ባደረገልን ነገር ላይ ማመን እና
ከእምነት የሆነ መታዘዝ።
ለእርስዎ በጣም ውድ የሆኑትን አንዳንድ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃላት ያስቡ።
ቃላቱ እውን እንዲሆኑ በእርስዎ በኩል ምን ዓይነት ምላሽ ይፈልጋሉ?
በኢያሱ 1፡2-3 ላይ እግዚአብሔር ምድሪቱን እንደሚሰጣቸው ለኢያሱ ነገረው።
በሌላ በኩል ቀድሞውንም ሰጥቻለሁ ብሏል። ያ ማለት ምን ማለት ነው?
ምድሪቱ እውነተኛው ባለቤት ከሆነው ጌታ ስጦታ ነበረች። በኢያሱ
1፡2-3 ላይ “መስጠትን” የሚገልፁ ሁለት የተለያዩ ዓይነት ግሶች ጥቅም ላይ
ውለዋል፤ እነዚህም መሬትን የመውረስን ሁለት ጉልህ ገጽታዎች የሚያንጸባርቁ
ናቸው። የመጀመሪያው መሬቱን የመስጠት ሂደትን ይገልፃል። በእስራኤል
የተያዙት የዮርዳኖስ ማዶ ግዛቶች ብቻ ነበሩ። አብዛኛው የተስፋይቱ ምድር
ገና መወሰድ ነበረበት።
በኢያሱ 1፡3 ላይ ግሱ ፍፁም በሆነና ምድሪቱ አስቀድሞ
እንደተሰጠቻቸው በሚጠቁም መልኩ ጥቅም ላይ ውሏል። የእነዚህ ድርጊቶች
ባለቤት እግዚአብሔር ከሆነ ቅርጹ “ትንቢታዊ ፍጹም” ይባላል። ምክንያቱም
እግዚአብሔር የገባውን የተስፋ ቃል ልክ አሁን እንደተፈፀመ አድርገን መቀበል
የምንችለው እውነታ ስለሆነ ነው።
በቁጥር 3 ላይ ያሉት “አንተ” እና “የአንተ” የሚሉት ተውላጠ ስሞች
በብዙ ቁጥር ናቸው። ስለዚህ የተስፋው ቃል የተሰጠው ለኢያሱ ብቻ ሳይሆን
ለመላው የእስራኤል ህዝብ ነው። ለሙሴ የተሰጠው የተስፋ ቃል መጠቀሱ
የእግዚአብሔር ሥራ እንደቀጠለ የሚያሳይ ነው።
በተጨማሪም “ሁሉ”፣ “ሁሉም” (ኮል) የሚለው ቃል በመጀመሪያው
ምዕራፍ ላይ ብዙ ጊዜ ተደጋግሟል። ይህ ድግግሞሽ በኢያሱ ፊት
የተቀመጠውን ዓላማ ሁሉን አቀፍነት እና እውነተኝነት ያሳያል። የተስፋይቱን
ምድር መውረስን ስኬት ለማረጋገጥ በእግዚአብሔር፣ በኢያሱ እና በእስራኤል
ሕዝብ መካከል ፍጹም የሆነ አንድነት ሊኖር ግድ ነበር።
ኢያሱ 1:4-6ን እና ዕብራውያን 6:17-18ን ያንብቡ። በዚያን ጊዜ የተስፋይቱ
ምድር ቃል ኪዳን(የተስፋ ቃል) ብቻ ነበር። እግዚአብሔር ግን ርስት ብሎ
ይጠራዋል። የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ወራሽ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?
በእግዚአብሔር የተስፋ ቃላት ውስጥ ምንም አስማታዊ ነገር የለም።
የተስፋ ቃሉን በእጃቸው ለመጨበጥ በራሳቸው ብቻ ኃይል የላቸውም።
የተስፋ ቃላቱ እውን እንደሚሆኑ ማረጋገጫቸው “ከአንተ ጋር እሆናለሁ” ያለው
አምላክ መገኘት ብቻ ነው። በእርግጥም የጌታ መገኘት ለእስራኤል ህልውና
ወሳኝ ነበር። ያለርሱ መገኘት ልክ እንደሌሎቹ ሕዝቦች ልዩ ጥሪ፣ ማንነት፣
ወይም ተልእኮ የሌላቸው ይሆኑ ነበር (ዘጸ. 33፡12-16)። የጌታ መገኘት ኢያሱ
እንዲሳካለት የሚያስፈልገው ብቸኛ ነገር ነበር።
ዛሬም ምንም የተለወጠ ነገር የለም፤ ለዚህም ነው በማቴዎስ 28፡20 ላይ
የሚገኘው የኢየሱስ የተስፋ ቃል የተሰጠን።
ኢያሱ 1:7-9ን ያንብቡ። ጌታ ጠንካራ እና ደፋር መሆን እንዳለበት ለኢያሱ ሁለት ጊዜ አጽንዖት በመስጠት መናገር ያስፈለገው ለምንድነው?
ለኢያሱ የተሰጠው ሥራ ከባድ ፈተናዎችን የሚያካትት ነበረ።
የከነዓናውያን ከተሞች ግንቦች የማይታለፉ የሚመስሉ ሲሆኑ የምድሪቱ
ሕዝብም ለጦርነት የሰለጠነ ነበር። በአንፃሩ እስራኤላውያን፣ ተራ ዘላኖች የነበሩ
ሲሆኑ የተመሸጉትን ግንቦች ለመያዝ በጣም ጥንታዊ የሆኑ የጦር መሣሪያዎች
እንኳን ያልያዙ ነበሩ። የዚያን ጊዜ ልዕለ ኃያል የነበረችው ግብፅ እንኳን ከነዓን
መግባት እንዳልቻለች ታሪክ ይነግረናል።
ሆኖም በዚህ ቦታ ኢያሱን ጠንካራ እና ብርቱ እንዲሆን የሚመክሩት
ማበረታቻዎች ከጦርነት ዝግጁነት ወይም ከጦርነት ስልቶች ጋር የተገናኙ
አልነበሩም። እስራኤል ከያህዌ ጋር የገባችውን ቃል ኪዳን ለሚገልጹት ለሙሴ
መጻሕፍት እና ለተለዩት መጠይቆች ታማኝ ለመሆን ድፍረት እና ጥንካሬ
ያስፈልጋል።
ኤፌሶን 6:10-18ን ያንብቡ። በዛሬው ጊዜ በወታደራዊ ውጊያ እንድንካፈል
ባይጠበቅብንም ለኢያሱ የተሰጡትን የማበረታቻ ቃላት በየዕለቱ በምናደርገው
መንፈሳዊ ትግል ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
ዛሬም ክርስቲያኖች ክርስቶስ የሰጣቸውን አደራ በመፈጸም ረገድ
ከኢያሱ ጋር ተመሳሳይ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። ማለትም ከራሳቸው
የኃጢአተኝነት ዝንባሌዎች፣ ከክፋት ገዢዎች፣ ከስልጣኖች፣ እና ከጨለማው
ዓለም ገዥዎች እና ከክፋት ጭፍሮች ጋር በጦርነት ውስጥ ናቸው። ልክ እንደ
ኢያሱ፣ የክርስቶስን መገኘት የሚያረጋግጥ የተስፋ ቃል አላቸው፡- “እኔ እስከ
ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. 28፡20)። የኢያሱን
ፍርሃት ለማስወገድ የጌታ ድጋፍ በቂ እንደሆነ ሁሉ ዛሬም ጥርጣሬያችንን እና
ጭንቀታችንን ለማስወገድ መገኘቱ በቂ ሊሆንልን ይገባል።
የኛ ግድድሮሽ በእርሱ እና በሰጠን ተስፋዎች ለመታመን ጌታን በሚገባ
ማወቅ ነው። ከምንም በላይ ከእርሱ ጋር ግላዊ ግንኙነቱ የሚያስፈልገን ለዚያ
ነው ።
ዛሬ እኛን የገጠመን ወሳኙ ጥያቄ ኢያሱ ከገጠመው የተለየ አይደለም። ብዙም
በማይወደድበት ወይም ለመታዘዝ በማይመችበት ጊዜ እንኳን የእግዚአብሔር
ቃል ለሚናገረው ነገር ታማኝ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
ኢያሱ 1፡7–9ን ከዘፍጥረት 24፡40፣ ኢሳያስ 53፡10 እና መዝሙር 1፡1-3 ጋር ያንብቡ። በእነዚህ ጽሑፎች ላይ በመመስረት ባለፀጋ እና ስኬታማ መሆን ምን ማለት ነው?
ጻላክ፣ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል (ኢያሱ 1:8) የታቀደው ነገር አጥጋቢ
በሆነ መንገድ መከናወኑን ወይም ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ያመለክታል።
ሳካል የሚለው የዕብራይስጥ ቃል (ኢያሱ 1፡8) “መበልፀግ” ወይም
“ስኬታማ መሆን” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ነገር ግን “ብልህ መሆን” ወይም
“በጥበብ መሥራት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ስኬት እግዚአብሔርን
ከመፍራት እና ቃሉን በመታዘዝ በጥበብ ከመመላለስ ጋር ተያይዞ
በተገለፀባቸው በኢዮብ፣ በምሳሌ እና በመዝሙረ ዳዊት መጻሕፍት ውስጥ
ይህ በተደጋጋሚ ተገልጧል።
በዚህ መረዳት መሰረት፣ ስኬት ውስጥ ብልፅግና ሊኖር ቢችልም በቁሳዊ
ብልፅግና ብቻ ግን አይገለፅም። ስኬት በእግዚአብሔር በተፈጠረው ዓለም
መሠረት ላይ ከሚገኙት እና በሕጉ ውስጥ ከተገለጹት መንፈሳዊ እሴቶች እና
መርሆዎች ጋር እንደ መስማማት ሊታይ ይገባዋል።
በእርግጥ፣ በእግዚአብሔር ተስፋዎች መታመን፣ በተለይም በእምነት
ብቻ መዳን እና ህጉን መታዘዝ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አይደሉም። የአንድ
ሳንቲም ሁለት ገጽታዎችን ይወክላሉ።
ሮሜ 3:31ን ያንብቡ። ይህ ጽሑፍ በሕግ እና በእምነት መካከል ስላለው
ግንኙነት ምን ይላል?
ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝን በመቃወም በኢየሱስ የኃጢያት ክፍያ
እና መሥዋዕታዊ ሞት ላይ እምነት ማሳደር ሐሰተኛ እና አደገኛ አስተሳሰብ
መፍጠር ነው። ህግ እና ፀጋ ሁልጊዜ አብረው የሚሄዱ ናቸው። የሕግን
ሚና ላይ ላዩን መረዳት “ሕግን” እና “ጸጋን” እንደ ተቃራኒዎች እንድንገነዘብ
ሊያደርገን ይችላል።
የብሉይ ኪዳን ጸሐፊዎች ለህጉ ከፍ ያለ ግምት ስለነበራቸው የደስታ
ምንጭ አድርገው ይመለከቱት ነበር (መዝ. 1:2፣ መዝ. 119:70፣77፣174)።
በትክክለኛው ጥቅም ላይ ሲውል ሕጉ ስለ ራሳችን ኃጢአተኝነት (ሮሜ. 7:7)
እና የክርስቶስ ጽድቅ ምን ያክል እንደሚያስፈልገን በጥልቅ ወደ መገንዘብ
ይመራል (ገላ. 3: 24)።
ምንም ያህል በእግዚአብሔር ጸጋ ሕጉን ለመጠበቅ ቢፈልጉ፣ ገመና ሸፋኙ
የክርስቶስ ጽድቅ እንደሚያስፈልግዎት የራስዎት ህይወት ያሳየዎት እንዴት ነው?
የኃይማኖት አባቶች እና ነብያት ከሚለው
መጽሐፍ ውስጥ “ዮርዳኖስን መሻገር” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ እና The
Story of Redemption ከሚለው መጽሐፍ ውስጥ Entering the Promised
Land የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ ያንብቡ።
“በተስፋ ቃሉ እና ማስጠንቀቂያዎቹ ውስጥ፣ ኢየሱስ እየተናገረ ያለው
ስለ እኔ ነው። እኔ በእርሱ አምኜ እንዳልጠፋ፣ ነገር ግን የዘላለም ህይወት ይኖረኝ
ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ አለምን እንዲሁ ወዶአል።
በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተነገሩት ልምምዶች የእኔ ልምምዶች ሊሆኑ
ይገባል። ጸሎቶቹ፣ የተስፋ ቃላቱ፣ ትዕዛዛቱ እና ማስጠንቀቂያዎቹ የእኔ(ለእኔ)
ናቸው…። እምነት የእውነትን መርሆዎች አምኖ እንደሚቀበል እነዚህም
የህይወት አካል እና አነሳሽ የህይወት ኃይሎች ይሆናሉ። የእግዚአብሔር ቃል
የተቀበለውን ሰው ሐሳብን ይቀርፃል የባሕርይ እድገትንም ያመጣል።”—
ኤለን ጂ. ኋይት፣ የዘመናት ምኞት ገፅ 390-391
“የወደቀው ሰብዓዊ ዘር በራሱ መልካም ስራ ምንም ነገር ሊያገኝ
እንደማይችል በሁሉም አእምሮ ውስጥ በትጋት፣ በተደጋጋሚ በጥልቅ መታሰብ
አለበት። መዳን የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው።”—Ellen
G. White, Faith and Works, p. 19.
1. ኢያሱ የነበረበት ሁኔታና ልምምዱ ከኛ የተለየ ቢሆንም ከእርሱ ህይወት
ዛሬ ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባን ምን መንፈሳዊ ትምህርት አለ? ሆኖም
መመሳሰሎችን ስናይ አውዱንም አብረን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን
ለምንድነው?
2. የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃላት እና ለእርሱ መታዘዝ ያላቸው ግንኙነት ላይ
ይወያዩ። አብረው የሚሄዱት እንዴት ነው? አንዱን ከአንዱ እጅግ ከሚገባው
በላይ ከፍ ማድረግ ምን አደጋ አለው? ማለትም ፀጋን ከፍ አድርጎ ህጉን ወደጎን
መግፋት ምን አደጋ ይዞ ይመጣል? ወይም ህጉን እጅግ ከፍ አድርጎ ፀጋውን
ማኮሰስስ ምን አደጋ አለው?
3. በዚህ ሳምንት ጥናት መሰረት ከመጽሐፍ ቅዱስ እይታ አንፃር ስኬት
ምንድነው? ብልፅግና በክርስትያን የስኬት ትርጓሜ ላይ ያለው ቦታ ምንድነው?
4. ኢያሱ የሙሴን ቦታ ሲይዝ ምን እንደተሰማው በምናብዎ ይሳሉ። በተሰጡት
ታላላቅ ኃላፊነቶች ውስጥ እግዚአብሔር ኢያሱን ለማበርታት ምን አይነት
የተስፋ ቃል ሰጠው?