የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ
መጽሐፈ ኢያሱ ከሙሴ አመራር ወደ ኢያሱ የተሸጋገረበት
ጊዜ ላይ ይጀምራል፡፡ የሚጀምረው እስራኤል ወደ ተስፋይቱ
ምድር በመግባታቸው ታሪክ ሲሆን መጨረሻው በዚያች
ምድር መስፈራቸው ነው።
ኢያሱ በእርግጥም ከባድ የሆነ መንገድን መከተል ነበረበት። ማለትም
ሙሴ (ያውም ሙሴ!) ካቆመበት መቀጠል ነበር። ያ ግን የትግሉ ጅምር ብቻ
ነበር። ኢያሱ ሙሴ ያላደረገውን ማድረግ ነበረበት፡- እግዚአብሔር ከዓመታት
በፊት ለአባቶች በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ
የተንከራተተውን ሕዝብ ዮርዳኖስን አሻግሮ ወደ ከነዓንም ማስገባት።
“ባሪያዬ ሙሴ ሞቶአል፤ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል
ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስ ተሻገሩ።” (ኢያሱ. 1:2)።
የታሪኩ ሁሉ ቁልፍ የሚገኘው እግዚአብሔር ለኢያሱ በተናገራቸው
ቃላት ውስጥ ነው፡ “እኔ ወደምሰጣቸው ምድር” ሊገቡ ነው፡፡
አዎን፣ ኢያሱ ብቻውን የሚያደርገው ነገር አልነበረም፤ ነገር ግን
ህዝቡ ቃል ኪዳኑን ጠብቀው ቢሆን ኖሮ ከአንድ ትውልድ በፊት ወደ ምድሪቱ
ሊያስገባቸው ይችል በነበረው ጌታ ኃይል እና ምሪት ብቻ ይሳካ ነበር፡፡ አሳዛኙ ነገር
ህዝቡ አልታዘዙም፤ ስለዚህ ድርጊታቸው የሚያስከትለውን ውጤት ተቀበሉ፡፡
እውነታው ቀደም ባሉት አርባ ዓመታት እስራኤል የቃል ኪዳኑን ጣጣ
ተሸከሙ፡፡ ከግብፅ በድንቅ እና በተዓምራት መውጣትን የተለማመደው ሙሉ
ትውልድ በእግዚአብሔር ላይ በማመፁ ምክንያት ከኢያሱ እና ከካሌብ በስተቀር
በበረሀ ጠፋ፡፡ ከአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት አራቱ በዚያ ሁሉ ጊዜ ውስጥ በበረሀ
ሲንከራተቱ ምን እንዳጋጠማቸው ይተርካሉ፡፡ አሁን በኢያሱ አመራር ስር የሆነው
ሁለተኛው ትውልድ ምድሪቱን የመውረስን ትግል ለመታገል ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
“ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት፦ አንተ ከዚህ ሕዝብ
ጋር እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው እንዲሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ትገባለህና፥
እርስዋንም ለእነርሱ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። በፊትህም የሚሄድ እርሱ
እግዚአብሔር ነው ከአንተ ጋር ይሆናል፥ አይጥልህም፥ አይተውህም አትፍራ፥
አትደንግጥ አለው።” (ዘዳ. 31፡7-8)
ለአባቶች እና ለሙሴ የተገቡት የተስፋ ቃላት ሊፈጸሙ ነበር፡፡ ለረዥም
ጊዜ ቤት አልባ እና የተገፋ በነበረው ህዝብ መካከል ለአዲሱ ጅማሮ የጉጉት እና
የደስታ ነፋስ ነፈሰ፡፡ እግዚአብሔር እነርሱን ከባርነት በማውጣት ታማኝ ነበር፤
እናም ምድሪቱን በተመለከተ የገባላቸውን የተስፋ ቃላት ከመፈፀም አንፃር
በእርግጥም ሊታመኑበት ይችላሉ፡፡
“የኢያሱ መጽሐፍ የመጀመሪያ አላማ እስራኤል ወደ ተስፋይቱ
ምድር መግባታቸውን፣ በምድሪቱ ያሉ ሕዝቦችን ማሸነፋቸውንና ምድሪቱን
መከፋፈላቸውን ለመግለፅ ነው፡፡ ይህ አላማ የመጽሐፉን መልዕክት ማለትም
እግዚአብሔር ለአብርሃም ቃል የገባውን ምድር በማውረሱ ታማኝ ነው
የሚለው ላይ ትኩረት ይሰጣል፡፡ መጽሐፉ እግዚአብሔር ለገባው ቃል ኪዳን
ታማኝ መሆኑን አጠንክሮ ይናገራል፡፡ (ኢያሱ 21:43-45)” Andrews
Bible Commentary (Andrews University Press,
2020), p. 365
ምንም እንኳን የኢያሱ መጽሐፍ የተፃፈው ከሶስት ሺህ ዓመታት በፊት
ቢሆንም ያለንበት ዘመን ከመንፈሳዊ ግድድሮሹ አንፃር ከኢያሱ ዘመን ብዙም
ልዩነት ያለው እንዳልሆነ አብረን እንመለከታለን፡፡ የተለየ አይነት ግድድሮሽ
ይገጥመን ይሆናል፤ ሆኖም ሰላማችንን የሚነሱ፣ እምነታችንን የሚያናውጡ
እና እግዚአብሔር ለህዝቡ የሰጠው ተልዕኮ አፈፃፀም ላይ ጥርጣሬ የሚያሳድሩ
መንፈሳዊ ተግዳሮቶች ዛሬም አሉ፡፡
ባርና ማግያሮሲ የኢንተር-ኢሮፕያን ዲቪዥን ፀሐፊ እና የዲቪዥኑ
የቢብሊካል ሪሰርች ኢንስቲትዩት ሊቀመንበር ናቸው፡፡ አገልግሎታቸውን እንደ
ፓስተር እና የደቡብ ትራንሲልቫንያ ኮንፍረንስ የዲፓርትመንት ኃላፊ በመሆን
የጀመሩ ሲሆን በሮማንያ በአድቬንቲስት ዩኒቨርሲቲ የስነመለኮት መምህር እና
ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግሎታቸውን ቀጥለዋል፡፡