የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢያሱ 22፣ ኤፌ. 6:7፣
ዮሐንስ 7:24፣ ዘኍልቍ 25፣ ምሳ. 15:1፣ 1 ጴጥ. 3፡8፣9።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “የለዘበች መልስ ቍጣን ትመልሳለች፤ ሸካራ
ቃል ግን ቍጣን ታስነሣለች።” (ምሳሌ 15፡1)
በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ መኖር አንዳንድ ጊዜ ወደ አለመግባባቶች
እና ውጥረት ሊመራ ይችላል። ይህ በተለይ እንደ ቤተ ክርስቲያን
ባሉ ማኅበረሰቦች ውስጥ እውነት ነው፤ ምክንያቱም በቤተክርስትያን
ውስጥ ከተለያዩ አስተዳደግ፣ ማኅበራዊ ደረጃዎች የተውጣጡ እና አንዳንዴም
ፍጹም በተለያየ ባህል ያደጉ፣ ለጋራ ዓላማ አብረው የሚኖሩ እና የሚሰሩ ሰዎች
ስለሚገኙ ነው።
በዚህ ሳምንት ኢያሱ 22ን እና በሰዎች መካከል በተፈጠረ ታላቅ
አለመግባባት የተነሳውን ፈተና እናጠናለን። በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ፣ ኢያሱ
አንዳንድ ነገዶች ዮርዳኖስን እንዲሻገሩ እና በዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ካሉ
ነገዶች ጋር በድል አድራጊነት እንዲሳተፉ አዘዛቸው (ኢያሱ 1፡12-18)። አሁን
ሥራው ስለተጠናቀቀ፣ ለመመለስ ነፃ ናቸው። ይሁን እንጂ ከዮርዳኖስ በስተ
ምዕራብ ባሉ የዮርዳኖስ ጎሣዎች መካከል አሳሳቢ የሆነ መሠዊያ ሠሩ።
ስለ ሌሎች ባህሪ በችኮላ መደምደሚያ ላይ መድረስ አደገኛ የሆነው
ለምንድነው? በቤተክርስቲያን ውስጥ አንድነትን ማጎልበት የምንችለው እንዴት ነው? የጥሪያችንን ሰፊ መጠን ግምት ውስጥ ማስገባት እና ትኩረትን
በሚከፋፍሉ ነገሮች ውስጥ እንዳንገባ ማሰብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?
በዚህ ሳምንት የምንመለከታቸው አንዳንድ ጥያቄዎች እነዚህ ናቸው።
ለታህሳስ 3 ለሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።
ኢያሱ 22:1-8ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ ሮቤላውያን፣ ስለ ጋዳውያን እና ስለ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ቁርጠኝነት ምን ይነግሩናል?
ኢያሱ በዮርዳኖስ ማዶ ያሉት ነገዶች ለእስራኤል የጋራ ጥቅም ራስን
በመወሰን እና መስዋዕት በማድረግ ሙሴ እና እራሱ ያወጧቸውን ግዴታዎች
ሙሉ በሙሉ እንዳሟሉ አረጋግጧል። ከወንድሞቻቸው ጎን ሆነው ለ“በርካታ
ቀናት” ተዋግተዋል፣ እሱም ከስድስት እስከ ሰባት ዓመታት ገደማ ማለት ነው
(ከኢያሱ 11፡18፣ ኢያሱ 14፡10፣ ዘዳ. 2፡14 ጋር ያነፃፅሩ)። ሚስቶቻቸውና
ልጆቻቸው ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ቤታቸው ቀርተው
ነበር፤ ሆኖም በጦርነት ውስጥ የመቁሰልና የመሞት ዛቻ ተጋርጦባቸው
ከወንድሞቻቸው ጎን በመሆን በታማኝነት ለመታገል ወሰኑ።
እነዚህ ጥቅሶች የሀገርንና የምድሪቱን አንድነት አስፈላጊነት በተዘዋዋሪ
ያጎላሉ። ለቀጣዩ ታሪክም መንገዱን ያዘጋጃሉ፤ ይህም በዋናነት ስለ አንድነት
ነው። በመካከላቸው ጠንካራ የተፈጥሮ ድንበር የሆነው ዮርዳኖስ ቢኖርም
የእስራኤል ነገዶች አንድ ሆነው ይቆያሉ? መልክዓ ምድር በብሔራዊ
ማንነታቸው ላይ የራሱን ምልክት እንዲያደርግ ይፈቅዳሉ ወይስ አንዱን
አምላክ ማምለካቸው እንደተመረጠ ሕዝብ፣ ህብረታቸው በእርሱ አመራር ስር
ጠንካራ ሆኖ እንዲቆይ ያደርጋሉ?
ኢያሱ እንዲህ ዓይነት ታማኝነት ሊኖር የቻለበትን ብቸኛ
መንገድ ገልጿል፡- ተልእኳቸውን እንዲፈጽሙ የሰጣቸውን ያህዌን እንጂ
እስራኤላውያንን አላገለገሉም።
ይህንኑ መርሕ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እናገኘዋለን። ሐዋርያው ጳውሎስ
ክርስቲያኖች ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር እንደሚሠሩ
አገልግሎታቸውን እንዲያቀርቡ መክሯቸዋል (ኤፌ. 6:7፣ ቆላ. 3:23፣ 1 ተሰ.
2:4 ይመልከቱ)። ለዓለማት ፈጣሪ ከመሥራት የበለጠ ምን ጥሪ አለ?
በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ብዙውን ጊዜ በቀላሉ ተስፋ
የሚያስቆርጡን እና ትግሉን እንድንተው የሚያደርጉን ፈተናዎች እና ችግሮች
ያጋጥሙናል። አንዳንድ ጊዜ ማድረግ ቀላል ነው። ሆኖም ከእኛ ጋር እንደሚሆን
ቃል የገባልንን እና መልካሙን እንድንፈጽም የሚያስችለንን የጌታን ኃይል
መጥራት እንችላለን። ከፍ ያለውን ጥሪያችንን በፊታችን ካስቀመጥን፣ የወደቀው
ህልውናችን አካል የሆኑት የማይቀሩ ተግዳሮቶች እና ተስፋ አስቆራጭ
ሁኔታዎች ቢኖሩም ወደፊት ለመግፋት መነሳሳት እንችላለን።
ኢያሱ 22:5-6 እንደዘገበው ኢያሱ ከወንዙ ማዶ የቀሩትን ነገዶች ለይሖዋ
ታማኝ ሆነው እንዲቀጥሉ በማሳሰብ ባረካቸው። ከእኛ በላይ ስለ እርስ በርሳችን
ብንጸልይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለን ግንኙነት እንዴት ይለወጥ ይሆን?
የተመለሱትን ነገዶች ታሪክ በኢያሱ 22፡9-20 ያንብቡ። የምዕራብ ዮርዳኖስ ነገዶች በምስራቅ ዮርዳኖስ ጎሳዎች ላይ ምን ክስ አቀረቡ? እነዚህ ክሶች ምን ያክል መሠረት ነበራቸው?
ከቁጥር 1 በተቃራኒ፣ በምስራቅ በኩል ያሉት ነገዶች በተለመደው
መልክ (ሮቤላውያን፣ ጋዳውያን፣ ወዘተ.) ከሚጠሩበት የተለየ አገላለጽ ጥቅም
ውሏል፡- “የሮቤል ልጆች፣ “የጋድ ልጆች” እና “የምናሴ ነገድ እኩሌታ”
ማለትም “የእስራኤል ልጆች” (ኢያሱ 22፡11) ከሚለው አንፃር የተለየ አካልን
የሚያመለክት ይመስላል።
በትረካው ላይ “የእስራኤል ማኅበር ሁሉ” የሚለው አገላለጽ
የሚያመለክተው በምዕራብ ዮርዳኖስ የሚገኙትን ዘጠኝ ተኩል ነገዶችን ብቻ
ሲሆን ይህም በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት አጉልቶ
ያሳያል። በእርግጥም የሚቀጥለው ታሪክ ዋነኛ ጥያቄ ከወንዙ በስተ ምሥራቅ
ያሉት ነገዶች እንደ እስራኤላውያን ሊታዩ ይችላሉ ወይ የሚለው ነው።
ለታሪኩ ለስላሳ መደምደሚያ እንጠብቅ ይሆናል፤ ነገር ግን በስተምስራቅ
ያሉት ነገዶች በዮርዳኖስ ላይ መሠዊያ እንዳቆሙ ሲነገር ውጥረት ተፈጥሯል።
እዚህ ያለው ጥቅስ ለድርጊቱ ምንም ምክንያት አይሰጥም፤ የመሠዊያውን ተግባር
ወይም ከእሱ ጋር የተያያዘ የተለየ እንቅስቃሴንም አይገልጽም። እስራኤል ሁሉ
ወደ ከነዓን ለመሻገር በዮርዳኖስ ዳርቻ የመጡበትን የዮርዳኖስን የመጀመሪያ
መሻገር በምዕራፍ 3 እና 4 ላይ የተጠቀሱትን ብልጭታዎች ከተመለከትን
የመሠዊያ ትርጉምን በተመለከተ ያለው አሻሚነት የበለጠ ይጨምራል። እዚህ
አንድ የእስራኤል ክፍል ወደ ዮርዳኖስ ይቀርባል፤ አሁን ግን ወንዙን በተቃራኒ
አቅጣጫ ለመሻገር ነው።
በሁለቱም ሁኔታዎች የድንጋይ መዋቅር ቆሟል። የመጀመሪያው እንደ
መታሰቢያ ሆኖ ያገለግል ነበር፤ ሁለተኛው ደግሞ አስደናቂ መሠዊያ እንደሆነ
ይታሰባል። ወደ አእምሯችን የሚመጣው ጥያቄ “እነዚህ ድንጋዮች ምን ማለት
ናቸው?” የሚለው ነው። (ከኢያሱ 4:6፣ 22 ጋር ያነፃፅሩ)። ይህ መሰዊያ
የተሰራው ለመሥዋዕት ነው ወይስ መታሰቢያ ብቻ ነው? እነዚህ ሌሎች ነገዶች
በክህደት ውስጥ መውደቅ እየጀመሩ ይሆን?
ከኢያሱ፣ ከአልዓዛር ወይም ከነገዱ መሪዎች ጋር አለመመካከር ወደ
አስከፊ ግጭት ሊመራ ለሚችል አለመግባባት ክፍተት ይፈጥራል።
ኢየሱስና ጳውሎስ በሌሎች ላይ ከመፍረድ እንድንቆጠብ ሲመክሩን
ምን እያሉ ነው? ሉቃስ 6:37፣ ዮሐንስ 7:24፣ 1 ቆሮ. 4፡5ን ያንብቡ። የሌሎችን
ፍላጎት በተመለከተ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ በጣም ቀላል
የሆነው ለምንድን ነው?
ኢያሱ 22:13-15ን እንደገና በዘኁልቁ 25 ብርሃን ያንብቡ። እስራኤላውያን ፊንሐስን የሁለት ነገድ ተኩል የልዑካን መሪ አድርገው የመረጡት ለምንድን ነበር?
“የእስራኤል ልጆች” ተብለው ሁለት ጊዜ የተጠሩት ዘጠኝ ተኩል
ነገዶች የነጻነት መግለጫ ተብሎ ስለሚነገረው ወሬ ሙሉ እውቅና ከመስጠቱ
በፊት የመሠዊያውን ዓላማና ትርጉም ግልጽ ለማድረግ ልዑካን ላኩ።
የልዑካን ቡድኑ አልዓዛር ከሞተ በኋላ የሚተካውን የሊቀ ካህኑ የአልዓዛር ልጅ
ፊንሐስን ያካተተ ነበረ (ኢያሱ 24፡33)። ፊንሐስ በበኣል ፌጎር (ዘኍልቍ 25)
የእስራኤልን መቅሰፍት ያስቆመ ካህን መሆኑ ይታወሳል።
“የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ
መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ፤ ያንንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ
ድንኳኑ ገባ። እስራኤላዊውንም ሰውና ሴቲቱን ሁለቱን ሆዳቸውን ወጋቸው።
ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተከለከለ።” (ዘኍ. 25፡7)።
ፊንሃስ የተወሰነ ተጽዕኖ እንደነበረው ምንም ጥርጥር የለውም። ሌሎቹ
መልእክተኞች ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያሉት ዘጠኝ ተኩል ነገዶች ተወካዮች
ነበሩ፣ እያንዳንዳቸውም በእስራኤል ነገዶች ውስጥ የጎሳ ቤተሰብ መሪዎች
(“የአባታቸው ቤት አለቃ”) ነበሩ።
የልዑካን ቡድኑ “. . .እንዲህ ይላል” በማለት የርኩሰት እና የአመፅ
ክስን ይከፍታል። እዚህ ላይ ልዩነቱ የሚናገረው ጌታ ሳይሆን “የእግዚአብሔር
ማኅበር ሁሉ” (ኢያሱ 22፡16) መሆናቸው ነው። እስራኤላውያን በደልን፣
ክህደትንና ዓመፅን ፈጽመዋል የሚለውን ክስ ጀመሩ። “በደል” የሚለው ቃል
የአካንን ኃጢአት ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለው ተመሳሳይ የዕብራይስጥ ቃል
ነው (ኢያሱ 7፡1)፤ እናም በሙሴ የመጀመሪያዎቹ አምስት መጻሕፍት ውስጥ
ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል (ለምሳሌ ዘሌ. 5፡15፤ ዘሌ. 6፡2፤ ዘኍ. 5፡6፣ 12)። የአካን
እና የብዔልፌጎር ምሳሌዎች አንዱ ለተንኮል ሌላኛው ደግሞ ለአመፅ እንደ
ምሳሌ ሆነው ያገለግላሉ። እንዲሁም ያልተፈቀደ መሠዊያ የመሥራት ተግባር
ወደ ክህደት፣ ጣዖት አምልኮ እና ብልግና እንደሚያመራ፣ ይህም በመላው
የእስራኤል ሕዝብ ላይ የጌታን ቁጣ እንደሚያመጣ የዘጠኙን ተኩል ነገዶች
ፍራቻ ይገልጻሉ።
ሁላችንም ወደፊት ተመሳሳይ ሁኔታዎችን የምንቋቋምበትን መንገድ የሚቀርጹ
የትላንት መጥፎ ተሞክሮዎች አሉን። ያለፈው አሳዛኝ ሁኔታ አሁን ባለንበት
ዘመን ጎረቤቶቻችንን የምንይዝበትን መንገድ እንዳይወስን የእግዚአብሔር ጸጋ
ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
ኢያሱ 22፡21-29ን በምሳሌ 15፡1 ብርሃን ያንብቡ። ከምስራቃውያን ነገዶች መልስ ምን እንማራለን?
እንደ ክሱ ቀጥተኛ እና ኃይለኛ የሆነው የተከሳሾቹ መልስ፣ በመልዕክት
እና በመዋቅር የምዕራፉ ልብ ሆኗል። እስካሁን ድረስ ነገዶቹ ለተነሱት
ውንጀላዎች ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጡ በጸጥታ የተከሰሱባቸውን
ውንጀላዎች አዳመጡ። የክሱን ከባድነት ስንመለከት፣ “የለዘበች መልስ ቍጣን
ትመልሳለች፤ ሸካራ ቃል ግን ቍጣን ታስነሣለች።” (ምሳ. 15፡1) የሚለውን
የምሳሌውን ትክክለኛ ትርጉም በተግባር በመግለጽ ትዕግሥታቸው አርአያ
የሚሆን ነው።
የመከላከያ ንግግሩ የመክፈቻ ዓረፍተ ነገር ለእስራኤል አምላክ፡ ኤል፣
ኤሎሂም፣ ያህዌ (ኢያሱ 22፡22) የተሰጣቸው መለኮታዊ ስሞች ሕብረት
ነው። በእስራኤል ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆኑ
የሚችሉ ጥርጣሬዎች እና የሐሰት ውንጀላዎችን ለማስወገድ ከባድ መሃላ
እንደመሆኑ መጠን በኃይል ሁለት ጊዜ ተደግሟል። አምላክ ሁኔታውን በሚገባ
እንደሚያውቅና እንደሚረዳው አጥብቀው እርግጠኞች ናቸው፤ እና የመጡት
ልዑካንም ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ እንደሚደርሱ ተስፋ አድርገዋል።
ሁለት ተኩሉ ነገዶችም በእርግጥ ጥፋተኞች ከሆኑ የበቀል እርምጃ እንዲወስድ
በመጠየቅ በጌታ ፊት ተጠያቂነታቸውን ተገንዝበዋል (ከዘዳ. 18፡19፣ 1 ሳሙ.
20፡16 ጋር ያነፃፀሩ)።
በመቀጠልም በአንድ በኩል የክሱን ባዶነት (መሠዊያ እንደ መስዋዕት
ቦታ ብቻ ሊያገለግል አይችልም) እና በሌላ በኩል እውነተኛ ምክንያታቸውን
በመግለፅ አስገራሚ ነገርን ይገልጣሉ። ለድርጊታቸው ትክክለኛ ምክንያት
ከክህደት ይልቅ ከእስራኤል የመገንጠል ፍራቻ ነበር። ስለዚህ የመሠዊያው
መገንባት እንደታሰበው የክህደት ማስረጃ አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣
ተቃራኒው እውነት ነው፣ ልክ እንደ ምዕራብ ዮርዳኖስ ነገዶች እግዚአብሔርን
ከመፍራት የተነሳ እርምጃ ወስደዋል። የእስራኤል እውነተኛ አንድነት መሰረት
የሆነው መልክዓ ምድር ወይም የርስቱ መጠን ሳይሆን ለጌታ መስፈርቶች
ያላቸው መንፈሳዊ ታማኝነት ነው።
በወንዙ በስተ ምዕራብ ያሉት ነገዶች እውነተኛ አሳቢነታቸውና
በምስራቅ ያሉ ነገዶች ደግሞ ንፁህ መሆናቸው በመረጋገጡ እውነተኛ
ደስታቸው ተገልጧል። በወንድሞቻቸው ክርክር እንደተሸነፉ ከማሰብ ይልቅ
ጥርጣሬያቸው የተሳሳተ በመሆኑ እውነተኛ ደስታን አሳዩ። በእስራኤልም
የእርስ በርስ ጦርነት ተወግዶ የሕዝቡ አንድነት ተጠብቆ ቀጠለ።
የሐሰት ውንጀላዎች ሲደርሱብዎ እንዴት ያስተናግዱዋቸዋል? አመለካከትዎን
የሚመሩ አንዳንድ መርሆዎችን ያካፍሉ። በተመስጥዖ መዝሙር 37:3-6፣ 34፣
37 ይመልከቱ።
ኢያሱ 22:30-34ን ያንብቡ። ይህ ክስተት ስለ ግጭት አፈታት እና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የማረጋገጥ መንገዶችን በተመለከተ አንዳንድ ግንዛቤዎችን የሚሰጠን እንዴት ነው? (ከመዝሙር 133፣ ዮሐንስ 17:20-23፣ 1 ጴጥ. 3:8-9 ጋር ያነፃፅሩ።)
የኢያሱ 22 ታሪክ በቤተሰብ፣ በቤተክርስቲያን እና በማህበረሰቡ ውስጥ
ባሉ የዕለት ተዕለት የሰዎች ግንኙነት ላይ ተግባራዊ የሚሆኑ በርካታ የግንኙነት
መርሆዎች አሉት።
1. ነገሮች ሲበላሹ ወይም የተሳሳቱ በሚመስሉበት ጊዜ የሚበጀው
ነገር እስኪፈነዳ ድረስ የእኛን ምልከታ ከማፈን ይልቅ መነጋገር
ነው። የአምላክ ሕዝቦች ችግሮች የሚነሱ በሚመስሉበት ጊዜ
በግዴለሽነት ባይቆዩ መልካም ነው። እርግጥ ነው፣ ከዮርዳኖስ ማዶ የነበሩት ጎሳዎች መሠዊያ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎትና
ምክንያቱን ቢገልጹ፣ ችግሩን በሙሉ ማስወገድ ይቻል ነበር።
2. አንድ ሰው ስለተፈጠረው ሁኔታ ፍርድ ለመስጠት በቂ ሁኔታ
ላይ እገኛለሁ ብሎ ቢታመንም፣ ቸኩላችሁ ወደ መደምደሚያ
አትሂዱ። የምዕራብ ዮርዳኖስ ነገዶች ጆሮአቸው ላይ የደረሰውን
ወሬ በፍጥነት አምነው የምስራቅ ዮርዳኖስ ነገዶች ክደዋል የሚል
የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደረሱ።
3. በመደምደሚያችሁ ላይ ወደ እርምጃ ከመሄዳችሁ በፊት ስለ
እውነተኛው ወይም ስለተገመቱት ችግሮች ተነጋገሩ።
4. አንድነትን ለማምጣት መስዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ሁኑ።
የምዕራብ ዮርዳኖስ ነገዶች ከዮርዳኖስ ማዶ መሆናቸው
የክህደታቸው ምክንያት ከሆነ ለሌሎቹ ነገዶች ማስተናገጃ
የሚሆን ድርሻቸውን በከፊል ለመተው ፈቃደኛ ነበሩ።
5. በውሸትም ሆነ በትክክለኛ መንገድ ሲከሰሱ ቁጣን የሚመልስ
ረጋ ያለ መልስ ይስጡ። ክስን በክስ መመለስ መቼም ወደ ሰላም
አያመጣም። ሌሎች እርስዎን እንዲረዱዎ ከመጠበቅዎ በፊት
ለመረዳት ይሞክሩ።
6. ሰላም ዳግመኛ ሲመሰረት ደስ ይበላችሁ እና እግዚአብሔርን
ባርኩ። ዋናው የእስራኤል ጉባኤ የሁለት ተኩል ነገዶቹ እውነተኛ
መነሻ ኃሳብን ሲያውቁ እውነተኛ ደስታን ማግኘታቸው በጣም ደስ
የሚል ነው። ፍረጃቸው ስህተት እንደነበረ እስከማይቀበሉ ድረስ
በግምታቸው ያን ያህል እርግጠኛና ልበ ግትሮች አልነበሩም።
የምሥራቅ ዮርዳኖስ ነገዶች እግዚአብሔርን ቢክዱ ኖሮ የእስራኤል
ሕዝብ የቃል ኪዳኑን መሥፈርቶች(ቅጣቱን) ተግባራዊ ባደረጉ ነበር። አንድነት
እውነትን ለመጣል ወይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆችን ለመተው ምክንያት
ሊሆን በፍጹም አይችልም። ሆኖም የቤተ ክርስቲያን የቅጣት እርምጃ
ምንጊዜም በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረተ የእርቅ እና የመንፈሳዊ እርዳታ
ሙከራ ከከሸፈ በኋላ የመጨረሻው (የመጀመሪያው ሳይሆን) አማራጭ መሆን
አለበት። እነዚህ ቀላል መርሆች በቋሚነት ቢተገበሩ ቤተ ክርስቲያናችን ምንኛ
የተለየች ትሆን ነበር!
የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት ከሚለው መጽሐፍ
“የከነዓን ክፍፍል” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ ያንብቡ።
“በአንድ በኩል ከኃጢአት ጋር በተያያዘ ቸልተኝነትን ማስወገድ አስፈላጊ
ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጨካኝ ፍርድንና መሠረተ ቢስ ጥርጣሬን መራቅ
አስፈላጊ ነው። . . .
ሮቤላውያን እና ባልደረቦቻቸው ያሳዩትን ጥበብ ልንከተለው የተገባ ነው። የእውነተኛውን ሃይማኖት መንገድ ለመከተል በሐቀኝነት ቢፈልጉም
ተበድለዋል ክፉኛም ተወቅሰዋል፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ቅሬታ አላሳዩም።
መከላከያ ለማቅረብ ከመሞከራቸው በፊት የወንድሞቻቸውን ክስ በአክብሮት
እና በትዕግስት ያዳምጡ ነበር፡ ከዚያም መንስኤያቸውን ሙሉ በሙሉ አስረዱ
እናም ከባድ መዘዝ ሊያስከትል የነበረው ነገር በአሳማኝ መልኩ ተረጋጋ።
“በሐሰት ውንጀላ እንኳን ትክክለኛ አቋም የያዙ ሰዎች መረጋጋት እና
አሳቢ መሆን ይችላሉ። እግዚአብሔር በሰዎች በተሳሳተ መንገድ የተስተዋሉትን
ሁሉ ያውቃል፡ እናም ጉዳያችንን በእጁ መተው እንችላለን። የአካንን ጥፋተኝነት
እንደመረመረ በእርሱ የታመኑትን ፍርድ ያስተካክላል። በክርስቶስ መንፈስ
የተነሳሱት ትሁቱንና ታጋሽ የሆነውን መልካምነት ይለብሳሉ።
“የእግዚአብሔር ፈቃድ በሕዝቡ መካከል አንድነትና የወንድማማች
ፍቅር እንዲኖር ነው። ክርስቶስ ከመስቀሉ በፊት የጸለየው ጸሎት እርሱ
ከአብ ጋር አንድ እንደሆነ ደቀ መዛሙርቱ አንድ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር
እንደ ላከውም ዓለም ያምን ዘንድ ነበር። ይህ እጅግ ልብ የሚነካ እና አስደናቂ
ጸሎት እስከ ዘመናችን ድረስ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው፤ ምክንያቱም ቃሉ
“የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ ብቻ
አልጸልይም” (ዮሐ. 17:20) የሚል ነበር። አንድን የእውነት መርህ ለመሠዋት
አለመፈለጋችን እንዳለ ሆኖ ወደዚህ የአንድነት ሁኔታ ለመድረስ የማያቋርጥ
ግባችን ሊሆን ይገባል።” የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፣ ገጽ 519-520።
1. ጳውሎስ “ሌሎችን ከእናንተ እንደሚሻሉ በትህትና ቍጠሩ” (ፊልጵ.
ጳውሎስ “ሌሎችን ከእናንተ እንደሚሻሉ በትህትና ቍጠሩ” (ፊልጵ.
2:3) ብሎ የሰጠው ምክር በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ ክፉ ነገር
እንዳናስብ የሚረዳን እንዴት ነው?
2. ቀደም ሲል በፈጸምናቸው ስሕተቶች ምክንያት ብዙውን ጊዜ በአንድ
ቀደም ሲል በፈጸምናቸው ስሕተቶች ምክንያት ብዙውን ጊዜ በአንድ
ሁኔታ ከልክ ያለፈ ስሜታዊ የምንሆነው ለምንድን ነው? ይህን ዝንባሌ
ማስወገድ የምንችለውስ እንዴት ነው?
3. የሌሎችን አመለካከት የማዳመጥን አስፈላጊነት ተወያዩበት። በቤተ
የሌሎችን አመለካከት የማዳመጥን አስፈላጊነት ተወያዩበት። በቤተ
ክርስቲያናችን የመደማመጥ ባህልን እንዴት ማዳበር እንችላለን? (ከያዕቆብ
1:19 ጋር ያነፃፅሩ።)
4. የምንኖረው የሥራ ሕይወታችን ኃላፊነቶች፣ የቤተሰብ ኃላፊነቶች፣
የምንኖረው የሥራ ሕይወታችን ኃላፊነቶች፣ የቤተሰብ ኃላፊነቶች፣
ከቤተክርስቲያን ጋር የተያያዙ ኃላፊነቶች እና ሌሎች ተግባራት በጣም
በሚያስጨንቁበት ማህበረሰብ ውስጥ ነው። ሁሉን ነገር ለጌታ የማድረግ
መርህ የበለጠ ኃላፊነት እንዲሰማን ብቻ ሳይሆን የአእምሮ ሰላምም
ሊያመጣልን የሚችለው እንዴት ነው?