የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- 1 ቆሮ. 10፡1-13፣ ማቴ. 2፡ 15፣ ኢያሱ 1፡1-3፣ ሐዋ. ሥራ 3፡22-26፣ ዕብ. 3፡7-4፡11፣ 2 ቆሮ. 10፡3-5።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም
የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ።” 1 ቆሮ. 10፡11
በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ፣ የዋና ገፀ ባህሪው(የኢያሱ) ሕይወት ከራሱ
እጅግ የላቀ ወደ ሆነ እውነት እንደሚያመለክት ፍንጭ የሚሰጥ
ነገር አለ። በሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደምናየው መርህ
ማለትም አንዱ ጋ በአካል የሚታየው በሌላ ቦታ መንፈሳዊ ትርጓሜ ያዘለ
ሲሆን ማለት ነው፤ ለምሳሌ የከነዓን ምድር የአዲሲቱ ምድር ዘላለማዊ
ተስፋን እንደሚያመላክት የኢያሱ ህይወትም እንደዚያው ነው። በዚሁ አካሄድ
የምድራዊው ቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚበልጥን እውነታ አመላክቷል፡-
“ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ በሰው
እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ ፍጥረት ወዳልሆነችው ታላቅና ፍፁም ድንኳን
ገባ።”(ዕብ. 9፡11)።
ሆኖም ጥያቄው፡- ኢያሱ ወደፊት የሚፈጸሙትን ነገሮች የጠቀሰው
በምን መንገድ ነው? እንደዚህ አይነት አተረጓጎም ትክክለኛ መሆኑን
እርግጠኛ መሆን የምንችለውስ እንዴት ነው? የኢያሱ መጽሐፍን ለአዲስ
ኪዳን እውነታዎች እና ለመጨረሻ ጊዜ ክስተቶች መተግበርን የሚቆጣጠሩት
የመጽሐፍ ቅዱስ መርሆች የትኞቹ ናቸው?
በዚህ ሳምንት፣ እንደዚህ አይነት ንፅፅርን በተመለከተ የመጽሐፍ
ቅዱስ ትርጓሜ መርሆዎችን እንመለከታለን። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የንጽጽር
ምልክቶችን እንዴት እንደያዘ እና የኢያሱ ሕይወት የመሲሑን አገልግሎት፣
የቤተክርስቲያንን አካሄድ፣ እንዲሁም የዘመን ፍጻሜ አኗኗርን በተመለከተ
አስቀድሞ የሚናገረውን እናጠናለን።
ለህዳር 27 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።
ጥላዎችን የሚያመለክቱ የሚከተሉትን ጥቅሶች በማጥናት መጽሐፍ ቅዱሳዊው የአካልና የጥላ አተረጓጎም ምን እንደሆነ ለመግለጽ ይሞክሩ፡ ሮሜ. 5:14፣ 1 ቆሮ. 10፡1-13፣ ዕብ. 8፡5 እና ዕብ. 9፡23።
እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የአዲስ ኪዳኑ ጸሐፊ በብሉይ
ኪዳን ውስጥ የሚገኝን ጥቅስ ወይም ክስተት በራሱ ጊዜ ካለ ወይም ወደፊት
ከሚሆን ክስተት ጋር አያይዞ የገለጸበትን መንገድ ለማመልከት “ዓይነት”
(በግሪኩ ታይፖስ) ወይም “መሳይ (አንቲታይፕ)” (በግሪኩ አንቲታይፖስ)
የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ።
የአካልና የጥላ አተረጓጎም ኢየሱስን ወይም በወንጌል ውስጥ
የተካተቱትን ሌሎች እውነታዎችን የሚያመለክቱ የሰዎች፣ ክስተቶች ወይም
ተቋማት አተረጓጎም ነው። ምንም እንኳን የኋለኛው አካሉ፣ የጥላውን ዓላማ
በተሟላ መልኩ የሚያሟላ ቢሆንም ጥላው አካሉን እንደ ሞዴል ወይም
የመጀመሪያውን መልክ ከሚያንፀባርቅ ቅርጽ ጋር ይዛመዳል። ስለዚህ፣
መጽሐፍ ቅዱሳዊው ጥላ የተቀረጸው በተጨባጭ፣ ወይም በጽንሰ-ሐሳብ፣
በእግዚአብሔር አእምሮ ውስጥ በነበረው መለኮታዊ ንድፍ ነው፣ እና
የወደፊቱን አካል (አንቲአይፕስ) ለመግለፅ ያገለግላል።
የአዲስ ኪዳን ጸሃፊዎች አንድን ነጥብ ለማንሳት ከአንዳንድ የብሉይ
ኪዳን ፅሁፎች ተነስተው የዘፈቀደ ትርጓሜ እንዳልሰጡ መረዳት በጣም
አስፈላጊ ነው። የብሉይ ኪዳኑ ጥላ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በአካሉ ፍጻሜ
ከማግኘቱ በፊት ሁልጊዜ በትንቢታዊ ጽሑፎች ውስጥ ይገለጻል።
ዳዊት በብሉይ ኪዳን እንዴት እንደተገለጠ፣ ከዚያም በአዲስ ኪዳን እንዴት
ዳዊት በብሉይ ኪዳን እንዴት እንደተገለጠ፣ ከዚያም በአዲስ ኪዳን እንዴት
እንደተገለጸ ይመልከቱ። ከዚህ ምሳሌ የአካልና የጥላ አተረጓጎም እንዴት
እንደሚሰራ ምን ትምህርት እናገኛለን?
ሀ. ዳዊት ( መዝ. 22:1፣ 14-18)፡
ለ. አዲሱ ዳዊት (ኤር. 23:5፣ ኢሳ. 9:5-6፤ ኢሳ. 11:1-5)
ሐ. ምሳሌያዊው ዳዊት (ዮሐንስ 19፡24)፡-
እነዚህን ጥቅሶች ስንመለከት፣ ብሉይ ኪዳን ራሱ በቅዱሳት መጻሕፍት
ውስጥ ጥላዎችን (ምሳሌዎችን) ለመለየት እና ተግባራዊ ለማድረግ ቁልፉን
እንደሚሰጠን እንገነዘባለን። ይህ ማለት ቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸው ብሉይ
ኪዳን የነበረው የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች፣ በተለየ ሁኔታ ስለ ኢየሱስና ስለ
አገልግሎቱ “የወቅቱን እውነት” ለመግለጥ የብሉይ ኪዳን ምሳሌዎችን
(ጥላዎችን) እንዲጠቀሙ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶአቸዋል/መርቶአቸዋል ማለት
ነው (2 ጴጥ. 1:12)።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥላ ምን እንደሆነ፣
ወይም አካሉ በአዲስ ኪዳን እና ከዚያም በላይ እንዴት እንደሚፈጸም በዘፈቀደ
መወሰን አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንጽጽርን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ
ራሱ አንዳንድ መቆጣጠሪያዎችን እና መርሆዎችን ይሰጣል።
በተመሳሳይ፣ አዲስ ኪዳን የአንድን ምሳሌያዊ ፍጻሜ ሦስት የተለያዩ
ደረጃዎች ያብራራል፡ (1) በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ (ክርስቶሳዊው ፍጻሜ)፣
(2) በቤተ ክርስቲያን ልምምድ ውስጥ (የቤተ ክርስቲያን ፍጻሜ) እና (3)
በፍጻሜ ዘመን (የፍጻሜ ዘመን ፍጻሜ)።
እነዚህን ዓይነቶች እና አምሳያዎች(አካል እና ጥላዎች) በመጽሐፍ ቅዱስ
ክፍሎች ውስጥ ልናገኛቸው እንችላለን፣ እና አንባቢዎች መጽሐፍ ቅዱስን እና
ስለ ኢየሱስ፣ ስለ መዳን እና ስላለን የመጨረሻው ተስፋ የእግዚአብሔር ቃል
የሚያስተምራቸውን እውነቶች እንዴት መረዳት እንዳለብን ለማሳየት በጣም
አጋዥ ናቸው።
የሚከተሉትን የብሉይ ኪዳን ዓይነቶች(ጥላዎች) ይመልከቱ፡- እስራኤል፣
ዘጸአት እና ቤተ መቅደሱ። እያንዳንዳቸው በሦስቱ የአካልነት ደረጃዎች፡
- በክርስቶሳዊው አውድ፣ በቤተ ክርስቲያናዊው እና በፍጻሜ ዘመን አውድ
የተፈጸሙት እንዴት ነው?
1. እስራኤል
ሀ. ክርስቶሳዊው አውድ (ማቴ. 2፡15)፡
ለ. ቤተክርስትያናዊው አውድ (ገላ. 6:16)፡
ሐ. የፍጻሜ ዘመን አውድ (ራዕ. 7፡4-8፣ 14)፡
2. ዘፀአት (ከግብፅ መውጣት)
ሀ. ክርስቶሳዊው አውድ (ማቴ. 2፡19–21)፡
ለ. ቤተክርስትያናዊው አውድ (2ኛ ቆሮ. 6፡17)፡
ሐ. የፍጻሜ ዘመን አውድ (ራዕ. 18፡4)፡
3. ቤተ መቅደሱ
ሀ. ክርስቶሳዊው አውድ (ዮሐ. 1:14፣ ዮሐ. 2:21፣ ማቴ. 26፡61):
ለ. ቤተክርስትያናዊው አውድ (1 ቆሮ. 3:16-17፣ 2 ቆሮ. 6:16)
ሐ. የፍጻሜ ዘመን አውድ (ራዕ. 3፡12፣ ራዕይ 11፡19፣ ራዕይ 21፡3፣ ራዕይ 21፡22)፡
“ቅዱሳት መጻሕፍት አንድ መለኮታዊ ደራሲ ስላላቸው፣ የተለያዩ
የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች እርስ በርሳቸው የሚስማሙ ናቸው። . . .
ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎች እርስ በርሳቸው ይስማማሉ፤ የአንድ
ጥቅስ ትርጓሜ ቅዱሳት መጻሕፍት በዚያ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከሚያስተምሩት
አጠቃላይ ይዘት ጋር ይስማማል።” Handbook of Seventh-day Adventist
Theology, p. 65
አንዳንድ ጊዜ የአንዳንድ ጥቅሶችን ትርጉም ለመረዳት ሲከብዳችሁ ምን
ታደርጋላችሁ?
ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ንጽጽር አንጻር፣ በሙሴ እና በኢያሱ ሕይወት መካከል ያለው ትይዩነት አስፈላጊነት ምንድነው? ዘፀ. 3:1-2፣ ኢያሱ 1:1-3፣ ዘሁ. 13:1-2፣ ኢያሱ 2:1፣ ዘፀ. 3:5፣ ኢያሱ 5፡15።
በመጀመሪያው ትምህርት እንዳየነው፣ ኢያሱ እንደ አዲስ ሙሴ
ቀርቧል፣ በሁለተኛው ትውልድ ሕይወት ውስጥ ከግብፅ የመውጣትን ጉልህ
እርምጃዎች የደገመ አዲሱ ሙሴ ሆኗል። ልክ ሙሴ እንደሆነው ተልዕኮውን
የተቀበለው ከጌታ ጋር በግል ተገናኝቶ ነው። በሁለቱም መሪዎች አመራር
የእስራኤል ዝና በሕዝቦች መካከል ፍርሃትን ቀስቅሷል። ሙሴ ቀይ ባህርን
በማቋረጥ እስራኤላውያንን ሲመራ ኢያሱ ደግሞ ዮርዳኖስን በተአምራዊ
መንገድ በመሻገር ጀመሩ። ሁለቱም መሪዎች የመገረዝ እና የፋሲካን አስፈላጊነት
እንዲያስታውሱ ተነግሯቸዋል። መና መውረድ የጀመረው በሙሴ ጊዜ ነበር፡
እና መጨረሻው በኢያሱ ዘመን ነበር። ሁለቱም ጫማቸውን እንዲያወልቁ
ታዘዋል። የሁለቱም የተዘረጋ እጅ እስራኤል ድል እየነሳች እንደሆነ ያሳያል።
ሙሴ መሬቱን ለመከፋፈል እና የመማጸኛ ከተሞች እንዲቋቋሙ መመሪያ
ሰጥቷል፡ ኢያሱ መመሪያውን ፈጽሟል። ሁለቱም ለሕዝቡ የስንብት ንግግር
ያደርጋሉ፡ በአገልግሎታቸው መጨረሻም ለህዝቡ ቃል ኪዳናቸውን ያድሳሉ።
ዘዳግም 18፡15-19፣ ዘዳግም 34፡10-12፣ ዮሐንስ 1፡21፣ የሐዋርያት ሥራ 3፡22-
26 እና የሐዋርያት ሥራ 7፡37ን ያጥኑ። ሙሴ እንደ እርሱ ያለ ነቢይ እንደሚነሳ
የተናገረውን ትንቢት የሚፈጽመው ማነው? ኢያሱ ከሥዕሉ ጋር የሚስማማው
እንዴት ነው?
የኢያሱ ሕይወት በሙሴ የተነገረው ትንቢት ከፊል ፍጻሜ ነበር (ዘዳ.
18፡15፣ 18)። ይሁን እንጂ በሙሴ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው
በዋና ፍቺው አይደለም። በዋና ፍቺው፣ ትንቢቱ የሚፈጸመው በመሲሑ
ብቻ ነበር። አብን በቅርበት ያውቀው ነበር (ዮሐንስ 1:14፣18)፣ እርሱ እውነተኛ
ነበር፣ እግዚአብሔርንም በእውነት ገልጦታል (ሉቃስ 10:22፣ ዮሐ. 14:6፣
ማቴ. 22:16)። እግዚአብሔር በእውነት ቃሉን በአፉ አድርጓል (ዮሐ. 14፡24)።
ስለዚህ፣ ሁለቱም የሙሴ እና የኢያሱ ሕይወት የመጪው መሲህ የኢየሱስ
ምሳሌ ሆነዋል።
ከእግዚአብሔር ጋር ለመራመድ ኢየሱስ ምን ያህል ዋና ነገር ነው? ኢየሱስ እና
እርሱ ያደረገልን ነገር የክርስቲያናዊ ልምምዳችን መሰረት ሊሆነን የሚገባው
ለምንድነው?
የኢያሱ ታሪክ በአካል እና በጥላ ሳጥን መታየት አለበት። ኢያሱ
ያካሄዳቸው ጦርነቶች የእስራኤል ታሪክ ወሳኝ ክፍል የሆኑ ታሪካዊ ክንውኖች
ናቸው። የእነዚህ ጦርነቶች ዓላማ እስራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር
እንዲሰፍሩ ማድረግ ሲሆን የተሰጣቸውን ርስት በሰላም እንዲያገኙና በአምላክ
ሕግ መሠረታዊ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ አዲስ ማኅበረሰብ መመሥረት
ነው።
በኋላ፣ እንደ ኢሳይያስ ያሉ የብሉይ ኪዳን ጸሐፊዎች፣ በኢያሱ መጽሐፍ
ውስጥ በተደጋጋሚ የሚገኘውን ተመሳሳይ የቃላት አገላለጽ በመጠቀም
“ባድማ የሆኑትን ርስቶች [ለሕዝቡ]” (ኢሳ. 49:8) እንደሚመልስ የመሲሑን
ሥራ አቅርበዋል። የኢያሱ ተግባር ምድሪቱን ለእስራኤላውያን ማካፈል
እንደነበረው ሁሉ፣ አዲሱ ኢያሱ የሆነው መሲህ መንፈሳዊ ውርሱን ለአዲሱ
እስራኤል ይሰጣል።
ዕብራውያን 3:7-4:11 ያንብቡ። አዲስ ኪዳን ኢያሱ (አዲሱ ሙሴ) ራሱ
የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
የአዲስ ኪዳን ፀሐፊዎች ከኢያሱ ሥራ አንፃር የኢየሱስ ክርስቶስን
አገልግሎት ብዙ ገፅታዎችን አቅርበዋል። ኢያሱ ከ40 ዓመታት በኋላ በምድረ
በዳ ወደ ከነዓን እንደገባ፣ “ምሳሌያዊው ኢያሱ” የሆነው ኢየሱስም በምድረ
በዳ ከ40 ቀናት በኋላ አገልግሎቱን ጀምሯል (ማቴ. 4፡1-11፣ ሉቃ. 4፡1-13) እና
ከትንሳኤው በኋላ የ40 ቀናት የዚህ ምድር ቆይታ በኋላ (ሐዋ. 1፡3፣ 9-11፤ ዕብ.
1:2) ሰማያዊ አገልግሎቱን ጀምሯል።
ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኋላ (የርሱ “ዮርዳኖስን መሻገር”
(ማቴ. 3፡13-17፣ ማር. 1፡9-11)) የወንጌል ጸሐፊዎች ከመዝሙር 2፡7 እና ኢሳይያስ
42፡1 ላይ ከሚገኘው ከመሲሐዊ መዝሙር እና ስለ ጎስቋላው የእግዚአብሔር
አገልጋይ ከሚናገረው (ማቴ. 3፡17፣ ማር. 1፡12) መዝሙር ጠቅሰዋል። ስለዚህ
በጥምቀቱ እስከ ሞት ድረስ በታማኝነት የመታዘዝ ህይወት ኢየሱስ እንደ
መለኮታዊ ተዋጊ ሆኖ የያህዌን ጦርነቶች ከክፉ ሀይሎች ጋር እንደሚያካሂድ
ተነግሮለታል። የእርሱ ሕይወትና የመስቀል ሞት የሰይጣን መባረርን፣
በመንፈሳዊ ጠላቶቻችን ላይ ድል መንሳትን፣ ለሕዝቡ መንፈሳዊ ዕረፍትን እና
ለተዋጁትም ርስትን አስገኝቷል (ኤፌ. 4፡8፣ ዕብ. 1፡4፣ ዕብ. 9፡15)።
ክርስቶስ ባደረገልን ነገር “ማረፍ” መቻል ማለት ምን ማለት ነው? ማለትም፣
ኢየሱስ ሰይጣንን በእኛ ፈንታ ድል እንዳደረገው ማረጋገጫ ሊኖረን የሚችለው
እንዴት ነው?
ኢያሱ፣ እንደ ምሳሌ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ባሻገር የክርስቶስ አካል የሆነችውን የቤተ ክርስቲያንን ልምምድ ያመላክታል። በኢያሱ ዘመን በእስራኤል የተካሄዱት ጦርነቶች የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ተጋድሎ የሚያሳዩት ከምን አንጻር ነው? ከዚያ የሚለዩትስ እንዴት ነው? 1 ጢሞ. 1:18፣ 2 ጢሞ. 4:7፣ ኤፌ. 6:10-12፣ 2 ቆሮ. 10:3-5፣ እና የሐዋርያት ሥራ 20:32ን ይመልከቱ።
የአዲስ ኪዳን ጸሃፊዎች የኢያሱ ህይወት በቤተክርስቲያን
(ቤተክርስትያን) ልምምድ ውስጥ ሚና እንዳለው ተገንዝበዋል። የክርስቶስ
አካል ክፍል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን፣ ከክፉ ኃይሎች ጋር መንፈሳዊ ጦርነት
ውስጥ ብትሆንም ለህዝቡ የቀረውን የእግዚአብሔርን ጸጋ (ዕብ. 4፡9-11) እና
የመንፈሳዊ ውርሳቸውን በረከቶች ይካፈላሉ።
እነዚህ ጥቅሶች ስለ ኢያሱ ምሳሌነት የመጨረሻ ፍጻሜ ምን ይላሉ? 1 ጴጥ. 1፡
4፣ ቆላ.3፡24፣ ራዕ. 20፡9፣ ራዕ. 21፡3።
የኢያሱ ተምሳሌትነት የመጨረሻ እና የተሟላ ፍጻሜ የሚሆነው
በኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ነው። የኢያሱ ሕይወት የአምላክን ባሕርያት
ከማንፀባርቁ የተነሳ በሕይወቱ ውስጥ አንዳንድ ገጽታዎች የመሲሁን ተግባርና
ማንነት የሚያመላክት ትንቢታዊ ባሕርይ አሳይቷል።
ዛሬ ለእኛ መሲሑ መጥቶ ምድራዊ አገልግሎቱን ጨርሶ ወደ ሰማይ
ሄዷል። አገልግሎቱ አስቀድሞ መገለጽ አያስፈልገውም፣ ነገር ግን አሁንም
ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመካፈል የናፈቀውን ክብር (ዮሐ. 17፡22)
እና በማሰላሰል የእኛ ሊሆን የሚችለውን የክርስቶስን ባሕርይ (2ቆሮ. 3፡18)
የማንጸባረቅ ዕድል አለን። ስለ ኢየሱስ ባሰላሰልን ቁጥር የባህሪውን ውበት
እናንጸባርቃለን:: ይህ ከክርስቶስ ጋር በየእለቱ የምናደርገው ጉዞ ለሚያመራበት
አቅጣጫ መሰረት ነው። በቃሉ ውስጥ በየቀኑ ጊዜ መውሰድ በጣም አስፈላጊ
የሆነው ለዚህ ነው። በኢየሱስ ሕይወት፣ ባህሪ እና ትምህርቶች ላይ በማሰላሰል
ጊዜያችንን ማሳለፍ ያለብን ለዚህ ነው። አተኩረን በማየት አዎ እንለወጣለን።
ምሳሌው(ጥላ) የሆነው ኢያሱ እስራኤላውያንን “የአባቶቻችሁ አምላክ
እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር ትወርሱ ዘንድ እስከ መቼ ለመግባት ቸል
ትላላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። (ኢያሱ. 18:3)። አካሉ የሆነው ኢየሱስ ዛሬ
ይህን ጥያቄ የሚያስተጋባው እንዴት ነው?
“በዘመኑ ሕዝብ ዘንድ የክርስቶስ ተልዕኮ
ምን እንደሆነ በውል አልተስተዋለም። . . . የሰው ሥርዓት፣ ወግና
ትውፊት እግዚአብሔር ለእነርሱ እንዲማሩ ያዘጋጀላቸውን ትምህርቶች
እንዳያዩ ጋረዳቸው። እነዚህ ትውፊቶችና ወጎች እውነተኛውን ሃይማኖት
እንዳያስተውሉና እንዳይለማመዱ ዕንቅፋት ሆኑባቸው። እውነት አካል ለብሶ
መሲህ ሆኖ በተገለጸ ጊዜ የእነዚያ ሁሉ ጥላዎች ፍፃሜ መሆኑን ለማስተዋል
አልቻሉም። በመሆኑም አካሉን ናቁት፡ አንቀበልህም በማለት ጥቅም አልባ
ጥላዎቻቸውን(አካሉን አመላካቾች) እና ሥርዓታቸውን አጥብቀው ያዙ።
የእግዚአብሔር ልጅ በመካከላቸው ሆኖ ሳለ ምልክት መጠየቃቸውን
ቀጠሉበት። “የእግዚአብሔር መንግስት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” ለሚለው
መልዕክት ተዓምራት እንዲደረግላቸው በመጠየቅ ምላሽ ሰጡ (ማቴ.
3:2)። . . . የክርስቶስ ወንጌል የመሰናከያ ድንጋይ ሆነባቸው። የመሲሁን
እውነተኝነት ለማረጋገጥ በምድር መንግስታት ፍርስራሽ ላይ የእርሱን
መንግስት በመመስረትና ታላላቅ ድልን በመጎናጸፍ እንዲገልጽ ጠበቁት።
ለዚህ ግምታቸውና ጥበቃቸው ክርስቶስ በዘሪው ምሳሌ መለሰላቸው።
የእግዚአብሔር መንግስት ከፍ የምትለው በጦር መሣሪያ ኃይል ወይም
በዓመጽ ተግባር ሳይሆን በሰዎች ልብ ውስጥ አዲስ መመሪያ በመትከል ነው።”
የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 14-15 (በአማርኛው)
“ቤተ ክርስቲያን ቀላል በሆነው የእግዚአብሔር መንገድ ማለትም
በመታዘዝ የዘላለምን ሕይወት ለመቀበል ዝግጁ የሆኑ ታማኝ ካሌብ እና
ኢያሱዎች ያስፈልጓታል። ቤተክርስቲያኖቻችን ሠራተኞችን ፍለጋ እየተሰቃዩ
ነው። ዓለም የእኛ እርሻ ነው። የእውነትን ብርሃን አይተው ከማያውቁ
የምሥራቅ ጣዖት አምላኪዎች በላይ በጣዖት አምልኮ በተያዙ ከተሞችና
መንደሮች ውስጥ ሚስዮናውያን ይፈለጋሉ። እውነተኛው የሚስዮናዊነት
መንፈስ እጥረት ብዙ ንስሐ ይገባባቸዋል በሚባሉት ቤተክርስትያናት ውስጥ
ከመቀዝቀዙ የተነሳ የምዕመኑ ልብ በነፍሳት ፍቅር ደብዝዞ ወደ ክርስቶስ
የመምራት ፍላጎታቸውም ጠፍቷል። Testimonies for the Church, vol.
4, p. 156
1. መጽሐፍ ቅዱሳዊው የአካልና ጥላ ትምህርት በእኛ ፈንታ ኢየሱስ ክርስቶስ
መጽሐፍ ቅዱሳዊው የአካልና ጥላ ትምህርት በእኛ ፈንታ ኢየሱስ ክርስቶስ
ያደረገውንና እያደረገ ያለውን አገልግሎት እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?
2. መንፈሳዊ ውጊያችን ከነዓንን ድል ከማድረግ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት
መንፈሳዊ ውጊያችን ከነዓንን ድል ከማድረግ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? የሚለየውስ በምን ረገድ ነው?
3. የኢያሱ ጥላነት የመጨረሻ ፍጻሜ ላይ ያሰላስሉ። ስቃይ፣ መከራና ሞት
የኢያሱ ጥላነት የመጨረሻ ፍጻሜ ላይ ያሰላስሉ። ስቃይ፣ መከራና ሞት
የሌለባት ዓለም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ለምናደርገው ትግል
እውነተኛ ተስፋ የምትሰጠን እንዴት ነው?
4. ኢያሱ የክርስቶስ አገልግሎት ጥላ እስከሚሆን ድረስ የእግዚአብሔርን
ኢያሱ የክርስቶስ አገልግሎት ጥላ እስከሚሆን ድረስ የእግዚአብሔርን
ባሕሪ አንጸባርቋል። ኢየሱስ በእርስዎ ውስጥ የእርሱን ባሕሪ ይበልጥ
እንዲያንጸባርቅ የሚፈቅዱባቸው አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች የትኞቹ
ናቸው?