የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ዘጸአት



3ኛ ሩብ ዓመት 2025


ሐምሌ 26 - ነሐሴ 2

6ኛ ትምህርት

Aug 2 - 8




በቀይ ባህር መካከል



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ዘጸ. 12:31–36፣ ያዕቆብ 2:17–20፣ ዘጸ. 13:1–14:31፣ ዕብ. 11:22፣ ዘጸ. 15:1–21፣ ራዕይ. 15:2–4።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ሙሴም ለሕዝቡ፦ አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው” (ዘጸ. 14:13፣ 14)።

ዘጸአት በብሉይ ኪዳን ውስጥ እጅግ ትዕይንታዊና በግርማ የተሞላ የእግዚአብሔር ሕዝብ ልምምድ ነው። ይህ ክስተት እግዚአብሔር የዕብራውያንን ጠላቶች እንዴት እንዳሸነፈ እና እሥራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዴት በድል እንዳመጣ የሚያሳይ መለኮታዊ ሞዴል ነው።

በክርስቶስ የመዳንና የመቤዠት ምልክትም ነው።

ከሰብአዊ አኳያ ሲታይ የእሥራኤል ልጆች ተስፋ በሌለው፣ እንዲያውም በማይቻል እና በራሳቸው ራሳቸውን ማዳን በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ነበሩ፤ ነጻ መውጣት ካለባቸው መሆን ያለበት በመለኮታዊ ተግባር ብቻ ነው። የእኛና የኃጢአት ጉዳይም ተመሳሳይ ነው፡- በራሳችን ተስፋ ቢስ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። ከዘጸአት የበለጠ ትዕይንታዊ የሆነ ነገር ያስፈልገናል። ያንንም አግኝተናል።

እርሱም የክርስቶስ መስቀል እና እዚያ ለሁላችንም ክርስቶስ ያደረገልን ነገር ነው።

በዘጸአት 12 ላይ ከተጠቀሱት የእሥራኤላውያን ከጎሼን ምድር መውጣት አንስቶ በዘጸአት 15 ላይ በደስታ እስከተዘመረው የሙሴ መዝሙር ድረስ ያሉ ክስተቶች በጣም የሚያስገርሙና ለማመን የሚያስቸግሩ ናቸው። የእግዚአብሔር ምልክቶች፣ ድንቆችና አስደናቂ የማዳን ሥራዎች ጫፍ (ቁንጮ) ላይ ደርሰው ነበር። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

ነገር ግን እነዚህ እንኳን፣ ነጻ የመውጣቱ ትዕይንት ጥላ ከሆነለት፣ ክርስቶስ ለእኛ በመስቀል ላይ ካደረገው ነገር ጋር አይወዳደሩም። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለነሐሴ 3 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

ሐምሌ 27
Aug 3

ሂዱና ለእግዚአብሔር ስገዱ


በፋሲካው ሌሊት በደም ባልተሸፈነት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ ወረደ (ዘጸ. 12:1–12)። ማንም ሰው በሥልጣኑ፣ በትምህርቱ፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ ባለው ማህበራዊ ደረጃ ወይም በጾታው ምክንያት አላመለጠም።

ቅጣቱ ከፈርዖን ጀምሮ እስከ ባሪያዎች፣ እንዲያውም እስከ እንሰሳት ድረስ ሁሉንም ቤተሰቦች መታ። የግብጽ ኩራት በአቧራ ውስጥ ወደቀ። ዘጸ. 12:31–36ን ያንብቡ። ፈርዖን ሁሉም እንዲሄዱ እየፈቀደላቸው ሳለ እንኳን ምን ዓይነት እንግዳ ጥያቄ ነበር ያቀረበው? ለምን?



ዕብራውያን ሄደው ለአምላካቸው እንዲሰግዱ እየነገራቸው ሳለ “እኔንም ደግሞ ባርኩኝ” የሚለውን ጥያቄ ማከሉ እንዴት የሚያስገርም ነው! እኔንም ደግሞ ባርኩኝ?

የግብጽ ንጉሥ፣ በሕዝቡ መካከል በምድር ላይ “አምላክ፣” ለምን ይህንን ጥያቄ ይጠይቃል? በመጨረሻ የዕብራውያንን አምላክ ኃይል ያስተዋለ እና ከእርሱም ጥቅም ማግኘት የፈለገ ይመስላል። ነገር ግን በአመጽ፣ በትዕቢት፣ በኃጢአትና በኩራት ተሞልቶ ሳለ እንዴት እግዚአብሔር ሊባርከው ይችላል? በመጨረሻ መስመማቱን መግለጹ እርግጥ ነው፣ ነገር ግን ለያህዌህ ፈቃድ ራሱን ከማስገዛት የመነጨ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ከሽንፈት የመነጨ ጥያቄ ነበር። ኋላ በፈጸማቸው ተግባሮቹ እንደተገለጠው ለኃጢአቱ ንስሃ አልገባም። እርሱ የፈለገው መንግሥቱን እያጠፋ ያለው ውድመት እንዲቆምለት ብቻ ነበር።

ፈርዖን ተዋርዷል። ከሁሉም መቅሰፍቶች እጅግ የከፋው መቅሰፍት መውረዱ ካስከተላቸው አሳዛኝ ሁኔታዎች የተነሣ እሥራኤላውያን ከግብጽ እንዲወጡ ፈቃድ ሰጠ። አስቀድመው በነበሩ ጊዜያቶች እርሱ የወሰዳቸው እርምጃዎች በሕዝቡ ላይ መከራ ቢያመጡም ለመፍቀድ እምቢ ያላቸውን ነገሮች ሁሉ አሁን ፈቀደ።

ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው የግብጽ ሕዝብም ዕብራውያን እንዲሄዱላቸው ጉጉት ነበራቸው። “ሁላችንም እንዳንሞት” እባካችሁ ሂዱልን አሉ።

ይህ እየሆነ ሳለ እሥራኤላውያን ባዶ እጃቸውን እንዳይወጡ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን አመቻቸ፣ ነገር ግን የሚፈልጉአቸው ነገሮች ጉዞአቸውን ከተጠበቀው በላይ የሚያዘገዩ ሆኑ። ሕዝቡ ከአገራቸው ቶሎ እንዲወጡላቸው ለማስቸኮል ግብጻውያን ለአይሁዶች ውድ የሆኑ ዕቃዎችን ሰጡአቸው፣ ነገር ግን እነዚህ ዕቃዎች እሥራኤላውያን ለብዙ መቶ አመታት በባርነት ሲሰሩ ያልተከፈላቸው የልፋታቸው ዋጋ ነበሩ። በርግጥ እሥራኤላውያን ከአገራቸው እንዲወጡላቸው ግብጻውያን የከፈሉት ዋጋ ርካሽ ነበር። የፈጸምናቸው ተግባሮቻችን ስህተት መሆናቸውን ስላመንን ሳይሆን የሚያስከትሉአቸውን መዘዞች በመፍራት “የተናዘዝነው” ምን ያህል ጊዜ ነው? ይህ እውነተኛ ንስሃ የማይሆነው ለምንድር ነው? ቢያንስ ለአጭር ጊዜ እንኳን ቢሆን፣ ኃጢአታችን ከሚያስከትለው “ቅጣት ለማምለጥ፣” ለኃጢአታችን ማዘንን መማር የምንችለው እንዴት ነው?

ሐምሌ 28
Aug 4

የበኩር ልጅ መቀደስ/መለየት


ቃል የተገባው የመቤዠትና ነጻ የመውጣት ጊዜ ሊደርስ ነበር። ሕዝቡ መዘጋጀት ነበረበት። ማመን ብቻ ሳይሆን እምነታቸውን ወደ ተግባር መቀየር ነበረባቸው። ምን ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው እግዚአብሔር ነግሮአቸው ነበር፤ አሁን በእምነት መፈጸም ነበረባቸው። ያዕቆብ ይጽፍ ከነበረው አውድ ሙሉ በሙሉ ልዩ በሆነ አውድ ቢሆንም መርሁ ግን በደንብ ገጣሚ ነው። “አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን?” (ያዕቆብ 2:17–20)። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት ዘጸ. 13:1–16ን ያንብቡ። የመጨረሻው መቅሰፍት ሲወርድ የእሥራኤላውያን በኩሮች በእግዚአብሔር ጸጋ ከመቅሰፍቱ ድነው ነበር። ይህ ቀጣይነት ያለው ትዕዛዝ የሆነበት ምክንያት ምን ነበር? ይህ ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም ይሰጣል?



እሥራኤላውያን ቤተሰቦች በእምነት የበር መቃኞቻቸውን ደም ስለቀቡ እግዚአብሔር በምህረቱ ጠበቃቸው። እነዚህ አዳዲስ መመሪያዎች በሙሴ አማካይነት ከእግዚአብሔር መጡ፡- “ ማሕፀንን የሚከፈት በኵር ወንድ ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ” (ዘጸ. 13:2)። ይህ ድንጋጌ ለሰውም ለእንስሳትም የሚሰራ ድንጋጌ ነበር።

ከዚህ ትዕዛዝ በስተጀርባ ያለው መርህ እርሱ ፈጣሪና የሁሉም ነገር ባለቤት ስለሆነ ሁሉም የእርሱ ነው የሚል ነው፡- “ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ” (መዝ. 24:1)። “ብሩ የእኔ ነው፥ ወርቁም የእኔ ነው፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” (ሐጌ 2:8)። የእሥራኤላውያን የበኩር ልጆች ከእርሱ የተሰጡ የእግዚአብሔር በረከቶች የመጀመሪያ ፍሬዎች ሲሆኑ ለእርሱ ሙሉ በሙሉ የመቀደሳቸውና ያላቸው ነገር ሁሉ ከእርሱ ብቻ መምጣቱን የመረዳታቸው ምልክትም ነበሩ።

በዚህ ቦታ የመቤዠትና የድነት ሀሳብንም እንመለከታለን። የበኩር ልጆች ከሞት የተረፉት በደሙ ስለተሸፈኑ ነበር። በኢየሱስ ደም ሥር የሆኑት ሁሉ እንደሚዋጁ እነርሱም ከሞት ተዋጅተዋል። ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ “ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ባገኘንበት በእርሱ” (ቆላ. 1:14) በማለት ጽፏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ይህ የመቀደስ ተግባርና ከግብጽ ባርነት ነጻ የመውጣት በዓል እንዴት እንደሚፈጸም መመሪያዎች ተሰጥተው ነበር።

እንስሳቱን መሰዋት ነበረባቸው፣ ነገር ግን ወንዶች ልጆቻቸው መዋጀት ነበረባቸው(ዘጸ. 13:12፣ 13፣ 15)። ዘጸ. 13:16 በእጆቻቸውና በዓይኖቻቸው መካከል ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይነግራል። ምንም ያህል እምነት ቢኖረንም እምነታችንን በሥራ ማሳየት እንዳለብን የሚገልጸውን ወሳኝ መንፈሳዊ እውነት ይህ የሚያመለክተው እንዴት ነው?

ሐምሌ 29
Aug 5

ቀይ ባህርን መሻገር


ዘጸ. 13:17–14:12ን ያንብቡ። እሥራኤላውያን ግብጽን ለቀው በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር እንዴት ነበር የመራቸው? ቀጥሎስ ምን ሆነ?



እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጣቸውን መመሪያዎች በመከተል እሥራኤላውያን ከግብጽ የወጡት በደንብ እንደተደራጀ የጦር ሰራዊት ነበር።

ትሳባ እና ማክሃኔህ የሚሉ የዕብራይስጥ ቃላት “የጦር ሰራዊት” “ክፍለ ጦር” “ሰልፍ” እና “ሰራዊቶች” የሚሉ ትርጉሞች ያሉአቸው ሲሆን እነርሱም ይህ መግለጫ እውነት መሆኑን ይመሰክራሉ (ዘጸ. 6:26፤ ዘጸ. 7:4፤ ዘጸ. 12:17፣ 41፣ 51፤ ዘጸ. 14:19፣ 20ን ከ ዘጸ. 13:18 ጋር ያነጻጽሩ)። በትናንሽ ቡድኖች ተከፍለው እንደ ጦር ሰራዊት በሰልፍ ተጓዙ። ኋላ በለዓም ከሞአብ ተራሮች ላይ ሆኖ እሥራኤልን “በየነገዱ ተቀምጦ (ሰፍሮ) አየ” (ዘሁ. 24:2)።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ “ሙሴ የዮሴፍን አጥንቶች ከእርሱ ጋር ወሰደ” (ዘጸ. 13:19)። ይህ በጥቅሱ ውስጥ ያለ ወሳኝ ዝርዝር ሲሆን ዮሴፍ በእግዚአብሔር ተስፋ ላይ የነበረው እምነት ተፈጻሚነት ማግኘቱን ያሳያል።

ምንም እንኳን ዮሴፍ በግብጽ ውበትና መልካም ዕድሎች ውስጥ ቢኖርም የተስፋይቱ ምድር ከዕይታው ጠፍታ አታውቅም ነበር። አጥንቶቹ ወደ ከነዓን ምድር እንዲወሰዱ ጠየቀ(ዘፍ. 50:24፣ 25)። እግዚአብሔር እንደማለው በእርግጥ እሥራኤልን በግብጽ ምድር እንደሚጎበኝና ወደ ከነዓን ምድር እንደሚያመጣቸው አመነ (ዕብ. 11:22)። እሥራኤላውያን ወደ ከነዓን እንደደረሱ የዮሴፍን አጥንት “በሴኬም ቀበሩ” (ኢያሱ 24:32)።

የደመና እና የእሳት አምዶች እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ስለመሆኑ የሚታዩ ምልክቶች ነበሩ። እግዚአብሔር በዚያ በመኖር ከደመናው ተናገረ (ዘጸ. 14:24፤ ዘሁ 12:5፣ 6). የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፈርዖን የልቡን እውነተኛ ማነሳሻ ምክንያቶች ገለጠ። እርሱ አልተለወጠም፣ ከእውነተኛ ልቡ በፍጹም ተናዝዞ አያውቅም።

እግዚአብሔር እንዲባርከው መጠየቁ ቀልድ እና ምናልባትም የራሱ ልብ መታለል ሊሆን ይችላል። ሰራዊቱን ሰብስቦ ያመለጡትን ባሪያዎች ለመመለስ ሄደ። በርግጥ ይህ ሰው ምንኛ በኃጢአት ታውሯል።

ሕዝቡ የፈርዖን ሰራዊት ሲመጣባቸው በተመለከቱ ጊዜ ከአንድ ጊዜ በላይ የተስተጋቡ አመለካከቶችን በመግለጽ የሚከተሉትን ቃላት ተናገሩ፡- “ በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው?” (ዘጸ. 14:11)።

ሕዝቡ የበኩር ልጆቻቸውን መዳን ጨምሮ ትዕይንታዊ የሆነ የእግዚአብሔርን ኃይል መገለጥ ተመልክተው ሳሉ አሁንም አስገራሚ የሆነ አለማመንን አሳዩ።

አስከፊ የሆነ ሁኔታ የገጠመዎትን ጊዜ ያስቡ። የመጀመሪያ ምላሽዎ ምን ነበር? በእግዚአብሔር ማመን ወይስ እምነት ማጣት? ከዚያ ሁኔታ በቀጣይ ጊዜ ሌላ አስከፊ ሁኔታ ሲገጥምዎት ሊረዱዎ የሚችሉ ምን ትምህርቶችን ተማሩ?

ሐምሌ 30
Aug 6

በእምነት ወደ ፊት መጓዝ


ዘጸ. 14:13–31ን ያንብቡ። ምንም እንኳን የእሥራኤል ልጆች እምነት ባይኖራቸውም እግዚአብሔር ምን አደረገላቸው?



ሙሴ ከሙሉ ልቡ በእግዚአብሔርና በቃሉ ስለታመነ ሕዝቡን አደፋፈረ።

አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንዴት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አራት ወሳኝ ነጥቦችን አቀረበ፡-
1. “ አትፍሩ ” (ዘጸ. 14:13)። የመጀመሪያው ተማጽኖ በእግዚአብሔር የመታመን ነበረ፤ ለዚህ ምክንያቱ ፍርሃትን ማሸነፍ የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ ስለሆነ ነው። ኢሳይያስ አማኞች በእግዚአብሔር እጆች እንደሆኑ እና እርሱን እንደ አምላካቸውና እንደ ጌታቸው አድርገው ሲቀበሉ ለእነርሱ እንደሚሰራ በመናገር ይህን እውነት ያስታውሰናል፡- “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።…አትፍራ፥ እረዳሃለሁ ብዬ ቀኝ እጅህን የምይዝ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ” (ኢሳ 41:10፣ 13)።
2. “ ጸንታችሁ ቁሙ ” (ዘጸ. 14:13፣ )። “ዝም ብሎ መቆም” ማለት ማጉረምረምን ማቆምና ታላላቅ ነገሮችን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር መታመንና እርሱ ስለሚሰራ ኃይለኛ የሆነ የእርሱን ጣልቃ መግባት በትዕግሥት መጠበቅ ነው።
3. “ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን ታያላችሁ” (ዘጸ. 14:13)። እምነታችን እንዲያድግ የእግዚአብሔርን አመራርና እርዳታ መገንዘብ እና ሊረዳን ስለሰጠን ተስፋ አመስጋኝ መሆን አስፈላጊ ነው። “ማየት” ማለት አለማመን እውርነት ስለሆነ ዓይንን መግለጥ ማለት ነው። ድልን፣ ደህንነትን እና ድነትን የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ ነው። እግዚአብሔር እየተጠነቀቀልን እና በተገቢ ጊዜ የሚያስፈልገንን በመስጠት ሁልጊዜ ለእኛ ይቆምልናል።
4. “እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል” (ዘጸ. 14:14)። ይህ እግዚአብሔር ምን እንደሚያደርግ ያመለክታል፡-ለሕዝቡ በግል ይዋጋላቸዋል። ክርስቶስ የዘላለም ሕይወት ሊሰጠን ሰይጣንን በመስቀል ላይ ድል ስለነሳው፣ ቀራኒዮ የዚህ እውነታ የመጨረሻው ማረጋገጫ ነው (ዮሐንስ 5:24፤ ዕብ. 2:14፤ ራዕይ. 12:10፣ 11)። ኋላ ግብጻውያን እንኳን እግዚአብሔር ለእሥራአላውያን እየተዋጋ እንደሆነ ተገንዝበዋል (ዘጸ. 14:25)። እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ትዕዛዝ ግልጽ ነበር፡- “ውጡ።” እግዚአብሔር የትግበራ ዕቅዱን እንደሚከተለው ደረጃ በደረጃ ገለጸ፡- (1) የእግዚአብሔር መልአክና የደመና አምድ ከእሥራኤል ካምፕ ፊት ተንቀሳቅሶ ከኋላቸው በመቆም እሥራኤላውያንን ከግብጽ ሰራዊት ተከላከለ፤ (2) ሙሴ በእምነት በባህሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ (3) እግዚአብሔር ብርቱ ንፋስን በማምጣት ውኃውን በመክፈል አደረቀው፤ እና (4) የዚህ ውጤት እሥራኤላውያን በባህር ውስጥ በደረቅ መሬት በሰላም መሻገር ነበር። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ከተለመደው ውጭ የሆነ ነገር እያደረገ መሆኑን ስላላዩ ግብጻውያን በጭፍን ተከተሉአቸው፤ ይህ ማለት በዘጸአት 14፡25 ላይ ያለው ኑዛዜአቸው እንደሚያመለክተው ጊዜው እስኪያልፍባቸው ድረስ ማየት አልቻሉም ነበር። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

ነሐሴ 1
Aug 7

የሙሴና የሚሪያም መዝሙር


ጠቅላላው የግብጽ ሰራዊት ተገርስሷል፣ ፈርዖንን ጨምሮ አንድም አልተረፈም (መዝ. 136:15ን ይመልከቱ)። ለግብጻውያን አስደንጋጭ ሽንፈት ሲሆን ለእግዚአብሔር ሕዝብ ደግሞ ፍጹም ድል ነበር። አይሁዶች በታሪካቸው ሁሉ፣ ዛሬ እንኳን፣ ይህንን ታሪክ መዘገባቸው አያስገርምም። ዘጸ. 15:1–21ን ያንብቡ። የሙሴ መዝሙር ይዘት ምንድር ነው?



እግዚአብሔር ሕዝቡን የተቃወሙትን ያሸነፈ ኃያል ተዋጊ ስለሆነ ይህ መዝሙር ያወድሰዋል። ሙሴ አምላኩ የሆነው እግዚአብሔር ብርታቱ፣ ዝማሬውና ድነቱ እንደሆነ አጽንዖት በመስጠት በዚህ ዋና ሀሳብ ላይ በግሉ ማብራሪያ ይሰጣል።

ማንም እንደ እርሱ ያለ የለም፣ “በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንዳንተ ያለ ማን ነው?” (ዘጸ. 15:11)።

የሙሴ መዝሙር ሙሉ በሙሉ ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ እርሱ ማንነትና እርሱ እያደረገ ስላለው ነገር ነው። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላደረገው ድንቅ ነገር ከፍ ከፍ ብሏል፣ ተወድሷል፣ ተደንቋልም። ምስጋናና አምልኮ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውን መልካምነት የሚገልጹ ተፈጥሮአዊ ውጤቶች ናቸው። የእርሱን ፍቅር ማድነቅ ንቁ (ሕያው) ለሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ቅድመ ሁኔታ ነው። እግዚአብሔር የዋጀውን ሕዝብ ስለሚመራና ወደ ቅዱስ መኖሪያ ስለሚወስዳቸው የእርሱ ጽኑ ፍቅር በተለየ ሁኔታ አጽንዖትና ክብር ተሰጥቶታል። እግዚአብሔር በርስቱ ተራራ ላይ ቤተ መቅደስን እንደሚመሰርት ሙሴ ተነበየ (ዘጸ. 15:17)፣ ይህ ሁሉ ወደ ጽዮንና በኢየሩሳሌም ወደሚመሰረተው ቤተ መቅደስ ያመለክት ነበር።

ራዕይ 15:2–4 ውስጥ የዳኑት የሙሴንና የበጉን መዝሙር ይዘምራሉ። ይህ እግዚአብሔር ላደረጋቸው ታላላቅና አስደናቂ ተግባራት የሚቀርብ ምሥጋና፣ ፍርዱ ጽድቅና እውነት ለሆነው አምላክ የሚቀርብ ምሥጋና፣ እንዲሁም ጻድቅ ለሆኑ ተግባራቱና ስለ ቅድስናው የሚቀርብ ምሥጋና በሰማይ ምን እንደሚመስል ማሰብ ይችላሉ?

የመዝሙሩን የመጨረሻውን መስመር ልብ ይበሉ፡- “ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ” (ቁ. 4)።

ይህ ማለት፣ የእግዚአብሔር ፍርዶች ሁሉ--በተለይም ለብዙ ሺህ አመታት በክፋትና በጭቆና ላይ ሳይተላለፉ የቆዩ ፍርዶች--ስለተገለጡ ከሕዝቦች ሁሉ የዳኑት ለእነዚህ ፍርዶች እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። እማኑኤል ካንት የተባለ ሰው እግዚአብሔር ጻድቅ (ፍትሃዊ) ከሆነ፣ ከዚህ ሕይወት በኋላ ሌላ ሕይወት መኖር አለበት ብሏል። ይህ አባባል ትክክል የሆነው ለምንድር ነው? ከዚህች ምድር ለረዥም ጊዜ ጠፍቶ የነበረው ፍትህ አንድ ቀን እንደሚመጣ መታመንን መማር የምንችለው እንዴት ነው? ከዚህ ተስፋ መጽናኛ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

ነሐሴ 2
Aug 8


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ ኋይት አባቶችና ነቢያት በሚለው መጽሐፏ ገጽ 281–290 ላይ “ዘጸአት” በሚል ርዕስ ሥር የጻፈችውን ያንብቡ።

እሥራኤላውያን እምነታቸው ትንሽ ቢሆንም እግዚአብሔር ይቆምላቸው ነበር። እንደ እርሱ ምርጥ ሕዝብ እንዴት ማሰብና መሆን እንዳለባቸው ሊያስተምራቸውና ሊመራቸው ተመኘ። እግዚአብሔር በትዕግስት እየመራቸው አነስተኛ ተግዳሮቶች ወደሚገጥሟቸው ቦታ መራቸው። ኤለን ጂ. ኋይት እንዲህ በማለት ታብራራለች፡- “እሥራኤላውያን ስለ እግዚአብሔር የነበራቸው እውቀትና በእርሱ የነበራቸው እምነት ትንሽ ስለነበር ፈርተውና ልባቸው ዝሎ ነበር።…የጦር መሣሪያ ያልታጠቁና የጦርነት ልምድም ያልነበራቸው ነበሩ።

ከረዥም ዘመን ባርነት የተነሣ መንፈሳቸው ዝሎ ነበር፣ በልጆች፣ በሴቶች፣ በከብቶችና በመንጎችም ተጨናንቀው ነበር። እግዚአብሔር በቀይ ባህር መንገድ በመምራቱ ራሱን የርኅራኄና የፍርድ አምላክ እንደሆነ ገለጠ።”—Ellen G. White፣ Patriarchs and Prophets፣ p. 282.

የአንድሪውስ የመጽሐፍ ቅዱስ ሀተታ ስለ ሙሴ መዝሙር ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “በታሪክ ውስጥ የታየው ይህ የእግዚአብሔር የማዳን ተግባር እርግጠኝነት የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት ለወደፊቱ የሚያስፈራን ምንም ነገር እንደሌለ ያረጋግጥልናል። የመጨረሻው ስንኝ ከነዓንን የማሸነፍ ሂደት ውስጥ በሚገጥሙ የወደፊት ጠላቶች ላይ ትኩረት ያደርጋል። ብርቱ ከሆነው የእግዚአብሔር ክንድ የተነሣ እንደ አለት የጸኑ ይሆናሉ (ቁ. 16). አንዳንድ የማይቻሉ ነገሮች ሲገጥሙን፣ ጥግ እንዳስያዙን ሲሰማንና የትኛውን መንገድ መያዝ እንዳለብን ሳናውቅ ስንቀር ‘በሙሴ መዝሙር’ ውስጥ መተማመኛ እናገኛለን። ይህ የሚሆነው በእግዚአብሔር ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ያለውን ታላቅ ክስተት ስለሚያስታውስ ነው።”—Andrews Bible Commentary፣ “Exodus” (Berrien Springs፣ MI: Andrews University Press፣ 2020)፣ p. 214.


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ዕብራውያን አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ከግብጽ ወጥተው የቀይ ባህር ዕብራውያን አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ከግብጽ ወጥተው የቀይ ባህር ግድድሮሽን ከመጋፈጣቸው በፊት በነበራቸው አቋም ብዙ ጊዜ ራሳችንን የምናገኘው ለምንድር ነው? ይህ ማለት እግዚአብሔር ለእኛ ስላለው መልካምነትና ስለ ኃይሉ እጅግ ብዙ ማስረጃ እያለ እምነት ማጣትን ለማሳየት እና ለመግለጽ እጅግ የሚቀልለን ለምንድር ነው?

2. የበኩር ልጅን ማጣትን ጨምሮ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ እንኳን የበኩር ልጅን ማጣትን ጨምሮ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ እንኳን ፈርዖን እሥራኤልን ለምን አሳደደ? ለማናችንም ቢሆን በኃጢአት መጽናት ወይም ኃጢአትን ለመፈጸም ልበ ደንዳና መሆን እንዴት አደገኛ እንደሆነ ይህ ምን ሊነግረን ይገባል?

3. አንዳንድ ጊዜ ሁላችንም አሰቃቂ የሆኑ ፈተናዎች ቢገጥሙንም አንዳንድ ጊዜ ሁላችንም አሰቃቂ የሆኑ ፈተናዎች ቢገጥሙንም ብዙዎቻችን በራሳችንም ሆነ በምንወዳቸው ሰዎች ላይ ምንም ክፉ ነገር ስላልደረሰ ጥቂት በጣም ጥሩ የሆኑ ቀናትና ጊዜያት ነበሩን። በጠላት ክልል እንደምንኖር ስለምንረዳ እነዚህን ጊዜያቶች እንደ እግዚአብሔር ፀጋና ጥበቃ ማስረጃ አድርገን ማየት ያለብን ለምንድር ነው? ይህ ማለት ከምን መቅሰፍቶች እንደዳንን በፍጹም ስለማናውቅ በመልካም ጊዜያቶች እግዚአብሔርን ማመስገንን ሁልጊዜ ማስታወስ ያለብን ለምንድር ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL