የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ዘጸአት



3ኛ ሩብ ዓመት 2025


ሐምሌ 12 - 18

4ኛ ትምህርት

Jul 19 - 25




መቅሰፍቶቹ



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ: ዘጸ. 7:8–10:29፤ ዘሁ. 33:4፤ ሮሜ 1:24–32፤ መዝ. 104:27፣ 28፤ ኢሳ. 28:2፣ 12–17፤ ኢሳ. 44:9፣ 10፣ 12–17።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “የፈርዖንም ልብ ጸና፤ እግዚአብሔርም በሙሴ አፍ እንደ ተናገረ የእስራኤልን ልጆች አልለቀቀም” (ዘጸ. 9:35)።

አንድ ገበሬ አህያው እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ እየሞከረ ነበር፤ እንስሳው ግን አይንቀሳቀስም። ስለዚህ ገበሬው ወፍራም ቅርንጫፍ ወሰደና መታው። በድጋሚ ለአህያው ተናገረና መንቀሳቀስ ጀመረ። የሆነ ሰው ይህ ዘዴ ለምን እንደሰራ ገበሬውን ጠየቀው። ገበሬው እንዲህ በማለት መለሰ፡- “ደህና፣ መጀመሪያ ትኩረቱን ማግኘት አለብህ።”

ሰው ስለ እንስሳት ጭካኔ ሊያነሳ የሚችላቸውን ነገሮች በሙሉ ወደ ጎን በመተው፣ በተለይ ከዕብራውያን ከግብጽ መውጣት አውድ፣ በዚህ ቦታ ሊባል የሚችል ነገር አለ። ሙሴ ወደ ፊት እንዲጓዝ ትዕዛዝ የተሰጠው ሲሆን ወደ ፈርዖን ዝነኛ የሆኑ ሻላች ኢት አሚ (shalach et ami) የሚሉ ቃላትን በመናገር ሄደ። ትርጉሙም “ሕዝቤን ልቀቅ!” የሚል ነው።

ነገር ግን ፈርዖን የእግዚአብሔርን ሕዝብ መልቀቅ አልፈለገም። ዕብራውያን ወታደራዊ ሥጋት እንደሆኑ በመቁጠር ግብጻውያን ቢፈሩአቸውም (ዘጸ. 1:10ን ይመልከቱ) ፈርዖን ለምን ይህን ያህል ዳተኛ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ በፍጹም ግልጽ አድርጎ አያብራራም። ብዙ ጊዜ ባርነትን በተመለከተ እንደሚታወቀው ምክንያቱ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር ሊሆን ይችላል። የዕብራውያን ጉልበት ርካሽ ስለነበር እነዚህ ባሪያዎች የሚሰጡትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማጣት አልፈለገም። ከዚህ የተነሣ ትኩረቱን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን አእምሮውን ለመለወጥም የሆነ ማሳመኛ ዘዴ ያስፈልግ ነበር። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለሐምሌ 19 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

ሐምሌ 13
Jul 20

እግዚአብሔርና አማልክት


ዘጸአት 7:8–15ን ያንብቡ። የዕብራውያን አምላክና የግብጻውያን አማልክት ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት በገጠሙበት በዚህ ቦታ ምን ትምህርቶች ይገኛሉ?



እየመጡ ያሉ ጦርነቶች በሕያው እግዚአብሔርና በግብጻውያን “አማልክት” መካከል ሊሆኑ ነው። ሁኔታውን የከፋ ያደረገው ፈርዖን ራሱን ከእነዚህ አማልክት አንዱ አድርጎ መቁጠሩ ነው። እግዚአብሔር የተዋጋው ግብጻውያንን ወይም ግብጽን ሳይሆን አማልክቶቻቸውን ነበር (ግብጻውያን ከ1500 በላይ ወንድና ሴት አማልክትን ያመልኩ ነበር)።በዚህ ጉዳይ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ግልጽ ነው፡-“በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” (ዘጸ. 12:12)። በኋላ እሥራኤላውያን ከግብጽ ያደረጉት ጉዞ በዝርዝር ሲቀርብ አንድ ጊዜ በድጋሚ አጽንዖት ተሰጥቶበታል፡ - “በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው” (ዘሁ 33:4)።

በአማልክቶቻቸው ላይ የወረደው የዚህ ፍርድ ምሳሌ በትሩ ወደ እባብ በተለወጠበት ተዓምራት ታይቷል (ዘጸ. 7:9–12)። በግብጽ ዋጄት የተባለች የዩራኡስ አማልክት ኮብራ በሚባል መርዘኛ እባብ ተመስላ በታችኛው ግብጽ ላይ ሉአላዊ ኃይል እንደሆነች ተደርጋ ተወክላለች። የኮብራ እባብ ምልክት በፈርዖን ዘውድ ላይ ያለ ሲሆን ይህም የኃይሉ፣ የአምላክነቱ፣ የንጉሥነቱ እና የመለኮታዊ ሥልጣኑ ምልክት ነው። ለዚህም ምክንያቱ ይህቺ አማልክት በጠላቶቹ ላይ መርዟን ስለምትተፋ ነው። ግብጻውያን ቅዱሱ እባብ ፈርዖንን ወደ ኋለኛው ሕይወቱ ይመራል ብለው ያምናሉ።

የአሮን በትር በንጉሡ ፊት እባብ ሆና ሌሎቹን እባቦች ሁሉ በበላች ጊዜ ሕያው አምላክ ከግብጻውያን አስማትና ጥንቆላ በላይ እንደሆነ ተገለጠ። የፈርዖን ኃይል ምልክት የሆነው እባብ የተሸነፈ ብቻ ሳይሆን አሮንና ሙሴም በእጃቸው ይዘውታል (ዘጸ. 7:12፣ 15)። የመጀመሪያው ፊት ለፊት ግንኙነት የእግዚአብሔርን ኃይልና ጌትነት አሳይቷል። ሙሴ፣ እንደ እግዚአብሔር ወኪል፣ እንደ “አምላክ” ይቆጠር የነበረው ፈርዖን ካለው ሥልጣንና ኃይል የሚበልጥ ሥልጣንና ኃይል ነበረው።

የጥንቶቹ ግብጻውያን ኔሄብካኡ (“መናፍስትን አንድ ላይ የሚያስተሳስር”) የሚባል እባብ አምላክን ቅዱስ፣ እንደ አምላክ የሚከበርና የሚመለክ እድርገው ይመለከቱ ነበር። እንደ አፈ-ታሪካቸው (ሚቶሎጂ) ከሆነ ይህ እባብ አምላክ ትልቅ ሥልጣን እንዲኖረው ያደረገው ሰባት ኮብራዎችን ስለዋጠ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ለግብጻውያን እባብ አምላክ ሳይሆን እርሱ ሉአላዊ ኃይልና ሥልጣን እንዳለው ነገራቸው። ይህን ከመሰለ ኃይለኛ የፊት ለፊት ግንኙነት በኋላ ይህን መልእክት ወዲያውኑ በግልጽ መረዳት ችለው ነበር። በሕይወታችን የበላይነትን ለመያዝ በሚሹ “አማልክት” ላይ ጌታ ሉአላዊነት እንዲኖረው መፍቀድ የምንችለው እንዴት ነው?

ሐምሌ 14
Jul 21

የፈርዖንን ልብ ያደነደነው ማን ነው?


ዘጸ. 7:3፣ 13፣ 14፣ 22ን ያንብቡ። እነዚህን ጥቅሶች እንዴት እንረዳቸዋለን?



በዘጸአት መጽሐፍ ውስጥ የፈርዖንን ልብ ያደነደነው (ያጸናው) እግዚአብሔር እንደሆነ ዘጠኝ ጊዜ ተነግሯል (ዘጸ. 4:21፤ ዘጸ. 7:3፤ ዘጸ. 9:12፤ ዘጸ. 10:1፣ 20፣ 27፤ ዘጸ. 11:10፤ ዘጸ. 14:4፣ 8፤ ደግሞ ሮሜ 9:17፣ 18ን ይመልከቱ)።

ሌላ ዘጠኝ ጊዜ ደግሞ ፈርዖን ራሱ ልቡን እንዳደነደነ ተነግሯል (ዘጸ. 7:13፣ 14፣ 22፤ ዘጸ. 8:15፣ 19፣ 32፤ ዘጸ. 9:7፣ 34፣ 35)። የንጉሡን ልብ ያደነደነው ማን ነው? እግዚአብሔር ወይስ ፈርዖን ራሱ?

በኦሪት ዘጸአት በተነገረው የአሥሩ መቅሰፍቶች ታሪክ፣ ከመጀመሪያዎቹ አምስት መቅሰፍቶች በእያንዳንዱ ታሪክ ውስጥ ልቡን ያደነደነው ፈርዖን ብቻውን ነበር። ስለዚህ ልቡን የማደንደን ተነሳሽነቱን የወሰደው እርሱ ራሱ ነበር። ነገር ግን ከስድስተኛው መቅሰፍት ጀምሮ የፈርዖንን ልብ ያደነደነው እግዚአብሔር እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይገልጻል(ዘጸ. 9:12)። ይህ ሁሉ እየነገረን ያለው እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሙሴ አደርጋለሁ ብሎ እንደነገረው የፈርዖንን የራሱን ምርጫ እና ፈቅዶ ያደረገውን ድርጊቱን እንዳጠናከረው ወይም ጥልቀት እንዲኖረው እንዳደረገው ነው (ዘጸ. 4:21)። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

በሌላ አገላለጽ፣ እግዚአብሔር መቅሰፍቶቹን የላከው ፈርዖን ንስሃ እንዲገባና ከአእምሮው ጨለማና ስህተት ነጻ እንዲወጣ ለመርዳት ነበር።

እግዚአብሔር በፈርዖን ልብ ውስጥ አዲስ ክፋት አልፈጠረም፤ ከዚያ ይልቅ፣ ፈርዖንን ለራሱ የክፋት ስሜቶች አሳልፎ ሰጠው። የሚቆጣጠረው የእግዚአብሔር ፀጋ ስለተወዉ የራሱ ኃጢአተኝነት (ክፋት) እንዲቆጣጠረው ተተወ (ሮሜ 1:24–32ን ይመለከቱ)።

ፈርዖን ነጻ ፈቃድ ነበረው። እግዚአብሔርን ለመቃወም ወይም ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን መምረጥ ይችል ነበር። እርሱ ግን እግዚአብሔርን መቃወምን መረጠ።

ትምህርቶቹ ግልጽ ናቸው። ትክክል በሆነውና ስህተት በሆነው፣ በመልካምና በክፉ፣ በመታዘዝና ባለመታዘዝ መካከል እንድንመርጥ ችሎታ ተሰጥቶናል። በሰማይ ከነበረው ሉሲፈር፣ በኤደን ከነበሩት አዳምና ሔዋን፣ በግብጽ ከነበረው ፈርዖን እና ዛሬ እስካለን እስከ እኛ ድረስ፣ የትም ብንኖር፣ ሕይወትን ወይም ሞትን እንመርጣለን (ዘዳ. 30:19)።

ለንጽጽር ያህል፡- ቅቤንና ሸክላን የሚመታውን የጸሐይ ብርሐን ያስቡ።

ቅቤ ሲቀልጥ ሸክላ ግን ይጠነክራል። በሁለቱም ላይ ያረፈው የጸሐይ ሙቀት ያው ነው፣ ነገር ግን ለሙቀቱ ከሁለቱም የተሰጠው ምላሽ የተለያየ ነው፣ የተገኘው ውጤትም የተለያየ ነው። ውጤቱ የሚደገፈው በቁሱ ላይ ነው።

ፈርዖንን በተመለከተ ውጤቱ የተደገፈው ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ ባለው የልቡ አመለካከት ላይ ነው ማለት ይቻላል። በቀጣዩ ቀን ወይም በሌላ ምን ዓይነት ነጻ የፈቃድ ምርጫ (ምርጫዎች) ሊያደርጉ ነው? ትክክለኛው ምርጫ ምን እንደሆነ ካወቁ፣ ያንን ምርጫ ለማድረግ ራስዎን ማዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው?

ሐምሌ 15
Jul 22

የመጀመሪያዎቹ ሶስት መቅሰፍቶች


በግብጽ ላይ የወረዱት አስር መቅሰፍቶች የታለሙት በግብጽ ሕዝብ ላይ ሳይሆን በአማልክቶቻቸው ላይ ነበር። እያንዳንዱ መቅሰፍት ቢያንስ አንዳቸውን መትቷል። ዘጸ. 7:14–8:19ን ያንብቡ። በእነዚህ መቅሰፍቶች የሆነው ምን ነበር?



ከፈርዖን ጋር የሚደረገው ክርክር ከባድና የማይቻል እንደሚሆን እግዚአብሔር ለሙሴ መመሪያ ሰጠው (ዘጸ. 7:14)። ነገር ግን እግዚአብሔር ለፈርዖንና ለግብጻውያን ራሱን መግለጥ ፈለገ። ስለዚህ እነርሱ ሊያስተውሉ በሚችሉበት መንገድ ሊያነጋግራቸው ወሰነ። ደግሞ ከዚህ ፍጥጫ ዕብራውያን ስለ አምላካቸው ብዙ ስለሚማሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የመጀመሪያው መቅሰፍት የታለመው የአባይ አምላክ በነበረው ሃፒ ላይ ነበር (ዘጸ. 7:17–25)። በግብጽ ሕይወት ሙሉ በሙሉ የሚደገፈው ከአባይ ወንዝ በሚገኘው ውኃ ነበር። ውኃው በነበረበት ሕይወት ነበር። ውኃ የሕይወት ምንጭ ነበር፣ ከዚህ የተነሣ ሃፒ የተባለ የራሳቸውን አምላክ ፈልስፈው ለሕይወት የሚያስፈልገውን ነገር እንደሚሰጥ አምላክ አድርገው ይሰግዱለት ነበር።

በርግጥ የሕይወት ምንጭ፣ ውኃንና ምግብን ጨምሮ፣ የሁሉም ነገር ፈጣሪ የሆነው ሕያው እግዚአብሔር ብቻ ነው (ዘፍ. 1:1፣ 2፣ 20– 22፤ መዝ. 104:27፣ 28፤ መዝ. 136:25፤ ዮሐንስ 11:25፤ ዮሐንስ 14:6)። ውኃን ወደ ደም መለወጥ ሕይወትን ወደ ሞት መለወጥን ያመለክታል። ሃፒ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን መስጠትም ሆነ ሕይወትን ከአደጋ መጠበቅ አይችልም። እነዚህ ነገሮች ሊከናወኑ የሚችሉት በእግዚአብሔር ኃይል ብቻ ነው።

ከዚያም እግዚአብሔር ለፈርዖን ሌላ ዕድል ይሰጠዋል። በዚህን ጊዜ ፍጥጫው ቀጥታ ሄቄት ከሚባል ጓጉንቸር አምላክ ጋር ነበር (ዘጸ. 8:1– 15)። አባይ በሕይወት ፋንታ ግብጻውያን የሚፈሩአቸውን፣ የሚጠሉአቸውንና የሚጸያፉአቸውን ጓጉንቸሮች አወጣ። ጓጉንቸሮቹን ሊያስወግዱአቸው ፈለጉ።

እነዚህ መቅሰፍቶች የተወገዱበት ትክከለኛው ጊዜ ከዚህ መቅሰፍት በስተጀርባ ያለውም እግዚአብሔር መሆኑን አሳየ።

ሶስተኛው መቅሰፍት ከሌሎቹ ሁሉ አጭር የሆነ መግለጫ ተሰጥቶታል (ዘጸ. 8:16–19)። በዚህ ቦታ የተጠቀሰው (በዕብራይስጥ ኪኒም/kinnim) የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የተባለው የነፍሳት ዓይነት ግልጽ አይደለም (ተናዳፊ ዝንብ፣ የወባ ትንኝ፣ መዥገር፣ ቅማል?)። ይህ መቅሰፍት ያነጣጠረው የግብጻውያን የምድር አምላክ በሆነው ጌብ ላይ ነበር። ከምድር አቧራ (የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ታሪክን ያስተጋባል) በመላው ምድር ላይ የተሰራጨውን ቅማል አወጣ። አስማተኞቹ ይህንን ተዓምር መስራት ስላልቻሉ (ሕይወትን መፍጠር የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው) እንዲህ በማለት ተናገሩ፡-“ይህ የእግዚአብሔር ጣት ነው” (ዘጸ. 8:19)። ነገር ግን ፈርዖን አሁንም ውሳኔውን መለወጥ እምቢ አለ። የፈርዖን ልብ ምን ያህል ጠንካራ እንደነበር ያስቡ። ለውሳኔ የሚገፋፉ የእግዚአብሔርን ተደጋጋሚ እርምጃዎች አለመቀበል ሁኔታው የበለጠውን እንዲከፋ አደረገው። እግዚአብሔር በተደጋጋሚ የሚያቀርብልንን ተማጽእኖዎች አለመቀበል ምን እንደሚያስከትል ከዚህ ምን ትምህርቶች ይገኛሉ?

ሐምሌ 16
Jul 23

ዝንቦች፣ ከብት፣ እና ቁስል (እባጭ)


ዘጸ. 8:20–9:12ን ያንብቡ። ይህ ታሪክ የእግዚአብሔር ኃይልና ክብር መገለጥ ምንም ያህል ታላቅ ቢሆንም፣ ሰብአዊ ዘር አሁንም እርሱን ያለመቀበል ነጻነት እንዳለው ምን ያስተምረናል?



ኡቺት የተባለች የግብጻውያን አማልክት በራሪ አማልክትና የረግረጋማ ቦታዎች እመቤት ነበረች። ክሄፕሪ (የምትወጣው ፀሐይ፣ የፍጥረት እና እንደገና የመወለድ) የተባለው አምላክ ደግሞ በዝንብ ራስ ተመልክቷል።

እነዚህ “አማልክት” በእግዚአብሔር ተሸንፈዋል። በዚህ ዘገባ ውስጥ (ዘጸ. 8:20–24)፣ ግብጻውያን እየተሰቃዩ ሳሉ ለዕብራውያን ግን ጥበቃ ተደርጎላቸዋል። እንዲያውም፣ ቀጥለው የመጡ ተtጨማሪ መቅሰፍቶችም እነርሱን አልነኳቸውም ነበር።

በድጋሚ፣ ይህ ሁሉ ጥረት የተደረገው እግዚአብሔር ለፈርዖን ራሱን “በምድር መካከል እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ” እወቅ ለማለት ነበር(ዘጸ. 8:22)።

ከዚህ የተነሳ ፈርዖን መወያየት (መከራከር) ጀመረ። ጫናው ከፍ እያለ ስለመምጣቱ ምንም ጥርጥር የለውም። እሥራኤላውያን አምላካቸውን እንዲያመልኩና መስዋዕት እንዲያቀርቡለት ለመፍቀድ ፈቃደኛ ሆነ፣ ነገር ግን ይህን ማድረግ የሚችሉት በግብጽ ምድር ብቻ ነው (ዘጸ. 8:25)።

በግብጽ እንስሳት እንደ ቅዱስ ስለሚቆጠሩ እና እነርሱን መሰዋት በዕብራውያን ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ስለሚያደርግ ፈርዖን ያቀረበው ሁኔታ ተፈጻሚ ሊሆን አይችልም። እግዚአብሔር ለእሥራኤላውያን ያለው ዕቅድም ይህ አልነበረም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ቀጣዩ መቅሰፍት (ዘጸ. 9:1–7) በቤት እንስሳት ላይ ወረደ.። ሃጾር የተባለች የግብጻውያን የፍቅርና የጥበቃ አምላክ በላም ራስ ተመልክታለች። አፒስ የተባለ የበሬ አምላክም በጥንቷ ግብጽ እጅግ ዝነኛና ከፍተኛ አክብሮት የሚሰጠው ነበር። በመሆኑም፣ በዚህ አምስተኛው መቅሰፍት፣ የግብጻውያን የቤት እንስሳት በሞቱ ጊዜ ተጨማሪ አቢይ አማልክት ተሸንፈዋል።

በስድስተኛው መቅሰፍት (ዘጸ. 9:8–12)፣ ኢሲስ የምትባለው የመድኃኒት፣ የአስመት እና የጥበብ አምላክ ሙሉ በሙሉ መሸነፏ ተገልጧል።

እንደ ሴክህመት (የጦርነትና የወረርሽኝ አምላክ) እና እንደ ኢምሆቴፕ (የመድሃኒትና የፈውስ አምላክ) ያሉ አማልክትንም መሸነፍ እንመለከታለን።

ምጸታዊ በሆነ ሁኔታ፣ አሁን አስማተኞችና ጠንቋዮች እንኳን ቸነፈሩ ስላገኛቸው በቤተ መንግሥት መገኘት አይችሉም። ይህ የሚያመለክተው የሰማይና የምድር ፈጣሪን በመቃወም ባደረጉት ነገር ረዳተ-ቢስ መሆናቸውን ነው።

ስለ አስሩ መቅሰፍቶች በሚናገረው ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅሱ “እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና” ይላል (ዘጸ. 9:12)።

ይህ ገጽ ምንም ያህል ግራ የሚያጋባ ቢሆንም፣ በሙሉ አውድ ሲስተዋል፣ በቀጣይነት እግዚአብሔርን ለመቀበል ፈቃደኛ ያለመሆናችንን ውጤቶች እንድናጭድ እርሱ እንደሚተወን በድጋሚ ይገልጻል። የፈርዖን ችግር የእውቀት ማጣት ችግር አልነበረም፣ ትክክለኛ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችለው በቂ ምክንያታዊ ማስረጃ ነበረው። የእርሱ ችግር የልብ ችግር ነበር። ልባችንን መጠበቅ እንዳለብን ይህ ምን ሊነግረን ይገባል? የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

ሐምሌ 17
Jul 24

በረዶ፣ አንበጣ፣ እና ጨለማ


ዘጸ. 9:13–10:29ን ያንብቡ። እነዚህ መቅሰፍቶች ፈርዖን አእምሮውን እንዲለውጥ በማድረግ ረገድ ምን ያህል ስኬታማ ናቸው?



ኑት የግብጻውያን የሰማይና የሰማያት አምላክ ስትሆን ከሰማይ በታችና በምድር ላይ የሚሆኑ ነገሮችን እንደምትቆጣጠር ተደርጋ ተቀምጣለች። ኦሲሪስ ደግሞ የአዝርዕትና የልምላሜ አምላክ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በረዶ ብዙ ጊዜ ከእግዚአብሔር ፍርድ ጋር ተገናኝቷል (ኢሳ 28:2፣ 17፤ ሕዝ. 13:11–13)። በዚህ መቅሰፍት ወቅት ንብረታቸውን አደጋ በማይደርስበት ቦታ የደበቁ ሰዎች ብቻ ይጠበቃሉ (ዘጸ. 9:20፣ 21)። አሁን ሁሉም ተፈትኗል፡ -የእግዚአብሔርን ቃል በመታዘዝ እንደ ቃሉ ያደርጋሉ ወይስ ሳያደርጉ ይቀራሉ?

ፈርዖን በሕይወት እንዲኖር የመፍቀዱ ዓላማ መላው ምድር እርሱን እንዲያውቅ ለማድረግ እንደሆነ እግዚአብሔር አሳወቀ (ዘጸ. 9:16)። አሁን የግብጽ ንጉሥ ኃጢአት ሰርቻለሁ ብሎ ተናዝዟል፣ ነገር ግን ቆይቶ ሀሳቡን ለወጠ።

የግብጻውያን የማዕበል፣ የጦርነት እና የሥርዓት አልበኝነት አምላክ ሴት ይባላል። ከኢሲስ ጋር በመሆን የግብርና አማልክት ተደርገው ይታያሉ። ሹ የከባቢ አየር አምላክ ነበር። ሴራፒስ መለኮታዊ ግርማን፣ ልምላሜን፣ ፈውስን እና ከሞት በኋላ ያለውን ሕይወት ይወክላል። ጣኦታት ምናምንቴ ስለሆኑ (ኢሳ 44:9፣ 10፣ 12–17) ከግብጻውያን አማልክት መካከል አንድም የእግዚአብሔርን ፍርዶች ማቆም አይችልም (ዘጸ. 10:4–20)።

የፈርዖን ባሪያዎች እሥራኤልን እንዲለቅ ንጉሡን ገፋፉት፣ ነገር ግን በድጋሚ እምቢ አለ። ፈርዖን ሴቶችንና ሕጻናትን ትተው ወንዶች ብቻ ሄደው መስዋዕት እንዲያቀርቡ መደራደሪያ ያቀረበ ሲሆን ሴቶችና ልጆች ሊነጠሉ የማይችሉ የአምልኮና የእምነት ማህበረሰብ አካል ስለሆኑ ሙሴ የድርድር ሀሳቡን እንደማይቀበል በቀጥታ አሳወቀ።

በመጨረሻ፣ ራ የግብጻውያን ዋና አምላክ፣ የፀሐይ አምላክ ነበር።

ቶት የጨረቃ አምላክ ነበር። ከእነዚህ አንዳቸውም ቢሆኑ ብርሐን መስጠት አልቻሉም ነበር። ፈርዖን በድጋሚ ለመደራደር ሞከረ፣ ነገር ግን ሙከራው ፍሬ ቢስ ነበር። ግብጽ ለሶስት ቀናት በጨለማ ተመታች፣ ነገር ግን እሥራኤላውያን በሚኖሩበት ብርሐን ነበር። መለያው ከዚህ የበለጠ አስደናቂ ሊሆን አይችልም።

ሆኖም፣ አገሩ እየደረሰበት ያለው ምት ምንም ቢሆን ፈርዖን ጦርነቱን ለመመከት እንጂ ወደ ኋላ ላለማለት ወሰነ። በውስጡ የነበሩ ሀሳቦችን (የማነሳሻ ምክንያቶችን) ባናውቅም፣ በሆነ ነጥብ ላይ ሙሉ በሙሉ ክብሩን የመጠበቅ ጉዳይ ነበር። ማስረጃው ምንም ያህል ኃይለኛ እና እየሆነ ያለው ነገርም ምንም ያህል ግልጽ ቢሆንም (የራሱ ባሪያዎች እንኳን፣ “ይህ ሰው እስከ መቼ ዕንቅፋት ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ሰዎችን ልቀቅ፤ ግብፅስ እንደ ጠፋች ገና አታውቅምን?” [ዘጸ. 10:7]) ብለው ቢናገሩም፣ ትክክለኛ ምርጫ የማድረግ ዕድሉ በፊቱ ቢሆንም፣ ለአፍታ ካመነታ በኋላ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ለመሸነፍና ሕዝቡን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ።

ይህ “ትዕቢት ጥፋትን፥ ኵሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል” (ምሳሌ 16:18) ለሚሉ ቃላት እንዴት ያለ አስደናቂ ምሳሌ ነው።

ሐምሌ 18
Jul 25


ተጨማሪ ሀሳብ


“የግብጽ መቅሰፍቶች” የሚለውን ርዕስ ኤለን ጂ ኋይት ከጻፈችው አባቶችና ነቢያት ከሚለው መጽሐፍ ገጽ 265–272 ላይ ያንብቡ። “የእርሱ [የእግዚአብሔር] ሕዝብ የጣዖት አምልኮን እጅግ አዋራጅ ተጽእኖ በተመለከተ እንዳይታለሉ ሲባል የሚያደቅቀውን የግብጻውያንን ጭካኔ እንዲለማመዱ ተፈቅዷል። እግዚአብሔር ከፈርዖን ጋር ባደረገው ግንኙነት ለጣዖት ያለውን ጥላቻ እና ጭካኔንና ጭቆናን ለመቅጣት ያለውን ቁርጠኝነት አሳየ።… የንጉሡን ልብ ለማደንደን መለኮታዊ ኃይል ሥራ ላይ አልዋለም። እግዚአብሔር ለፈርዖን እጅግ አስደናቂ የሆነ መለኮታዊ ኃይልን ማስረጃ ሰጠው፣ ነገር ግን ንጉሡ የተሰጠውን ብርሐን ከትዕቢት የተነnሣ መቀበል እምቢ አለ። እያንዳንዱ ዘላለማዊ ኃይልን መገለጥ አልቀበልም ማለት የበለጠውን በአመጽ ለመቀጠል የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት ቁርጠኛ እንዲሆን አደረገው። እርሱ የመጀመሪያውን ተዓምር አልቀበልም በማለት የዘራቸው የአመጽ ዘሮች ፍሬ አፈሩ (ለመከር ደረሱ)።”—Ellen G. White፣ Patriarchs and Prophets፣ p. 268.

“ግብጻውያን ጨረቃንና ፀሐይን ያመልኩ ነበር፤ በዚህ ምስጢራዊ ጨለማ አማካይነት፣ በባርነት ይገዛ የነበረውን ሕዝብ ጉዳይ ሀላፊነት በወሰደው ኃይል፣ ሕዝቡና አማልክቶቻቸው ተመትተዋል። ይህ ፍርድ አስፈሪነቱ እንዳለ ቢሆንም፣ የእግዚአብሔር ርኅራኄና ለማጥፋት ፈቃደኛ ያለመሆን ማስረጃ ነበር። በሕዝቡ ላይ የመጨረሻዎቹንና እጅግ አሰቃቂ የሆኑ መቅሰፍቶችን ከማምጣቱ በፊት እንዲያሰላስሉና ንስሃ እንዲገቡ ጊዜ ይሰጣል።”—Patriarchs and Prophets፣ p. 272.


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ፈርዖን ሕዝቡን በመልቀቅ ግልጽና ትክክለኛ የሆነ ምርጫ ማድረግ ፈርዖን ሕዝቡን በመልቀቅ ግልጽና ትክክለኛ የሆነ ምርጫ ማድረግ ሲችል እንዲሄዱ ባለመፍቀድ ለምን ራሱን ለድንዳኔ አሳልፎ ሰጠ በሚለው ጥያቄ ላይ ያሰላስሉ። ሰው እስከዚህ ድረስ ለምን ራሱን ያታልላል? ትክክለኛ ውሳኔ እና ትክክለኛ መንገድ ሁልጊዜ በፊታችን እያለ በኃጢአት በመጽናት አጥፊ የሆኑ ውሳኔዎችን ማድረግ ስለምንችልበት ሁኔታ ከዚህ ለራሳችን ምን ዓይነት ማስጠንቀቂያዎችን መውሰድ አለብን? ተመሳሳይ የሆነ ስህተት የፈጸሙ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ-ባህሪያት እነማን ናቸው? ለምሳሌ፣ ይሁዳን ያስቡ።

2. ፈርዖን በአገሩና በሕዝቡ ላይ ባመጣው ጥፋት መካከል፣ በሆነ ፈርዖን በአገሩና በሕዝቡ ላይ ባመጣው ጥፋት መካከል፣ በሆነ ነጥብ ላይ፣ እንዲህ አለ፡- “በዚህ ጊዜ በደልሁ፤ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፥ እኔና ሕዝቤም ኃጢያተኞች ነን” (ዘጸ. 9:27)። ይህ ድንቅ የሆነ የኃጢአት ኑዛዜ ቢሆንም እውነተኛ ኑዛዜ አለመሆኑን የምናውቀው እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL