የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ዘጸአት



3ኛ ሩብ ዓመት 2025


መስከረም 3 - 9

12ኛ ትምህርት

Sep 13 - 19




“እባክህን ክብርህን አሳየኝ”



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ: ዘጸ. 33:7– 34:35፤ ዘዳ. 18:15፣ 18፤ ዮሐንስ 17:3፤ ሮሜ 2:4፤ ዮሐንስ 3:16፤ 2ኛ ቆሮ 3:18።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “እግዚአብሔርም በፊቱ አልፎ፦ እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው ሲል አወጀ” (ዘጸ. 34:6፣ 7)።

ከእግዚአብሔር ጋር በምናደርገው ጉዞ ሁላችንም ማደግ ያስፈልገናል። የማናድግ ከሆነ ሙታን ነን። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፡- “ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም እስከ ዘላለምም ቀን ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን” (2ኛ ጴጥ. 3:18)። ለማደግ ፈቃደኞች መሆን አለብን። በየቀኑ ምርቃት በሌለበት ግን የማያቋርጥ የመማር ሂደት ባለበት የእግዚአብሔር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነን። በክርስቶስ እንድትሆኑ ወደ ጠራችሁ ሰውነት እንዲቀርጻችሁ ከፈቀዳችሁ በእያንዳንዱ የእድገት ደረጃ ፍጹም መሆን ትችላላችሁ።

ትምህርት ቤትን አስቡ። የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ማንበብንና እስከ መቶ መቁጠርን ከተማሩ እውቀታቸው በዚያ ደረጃና በዚያ የእድገት መመዘኛ ፍጹም ስለሆነ የማለፊያ ውጤት ይሰጣቸዋል። ነገር ግን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ተመሳሳይ የሆነ የእውቀት ደረጃ ብቻ የሚያሳይ ከሆነ በግለሰቡ/ቧ እውቀት ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድቀት መኖሩን ያሳያል። በእግዚአብሔር ጸጋና እውቀት በሚኖረን የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት እድገትም እንዲሁ ነው። በዕድገታችን በእያንዳንዱ ደረጃ ክርስቶስ በራሱ ክበብ ፍጹም እንደነበረ ሁሉ እኛም በክበባችን ፍጹማን መሆን እንችላለን።

በዚህ ሳምንት ሙሴ የእግዚአብሔርን መመሪያዎች በማወቁና በመከተሉ ከጌታ ጋር በነበረው ጉዞ እንዴት ያድግ እንደነበር እንማራለን። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለመስከረም 10 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ

መስከረም 4
Sep 14

የመገናኛ ድንኳን


ዘጸ. 33:7–11ን ያንብቡ። ሙሴ የመገናኛ ድንኳን እንዲሰራ እግዚአብሔር ለምን ጠየቀው?



ከእሥራኤል መኖሪያ ሰፈር (ካምፕ) ውጭ የተገነባውን “የመገናኛ ድንኳን” ኋላ ከተገነባውና በካምፑ መካከል ከተቀመጠው ቤተ መቅደስ ጋር ማምታታት የለብንም። ሙሴ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር ምን ያህል ጊዜ እንደመከረ አናውቅም። ነገር ግን በእርግጠኝነት የምናውቀው አንድ ነገር ቢኖር ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት በመካከላቸው የቀረበ ወዳጅነት መፍጠሩን ነው። “እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር” (ዘጸ. 33:11)። ወዳጅ ማለት የነገርነውን ነገር ለማንም እንደማይገልጥ ስለምንተማመንበት ማማከርና ማንኛውንም ነገር በግልጽ መንገር የምንችለው ሰው ነው። ወዳጅ ሊኖሩን ከሚገቡ ነገሮች ሁሉ የተሻለና ከሰዎች ሁሉ ተሽሎ መገኘት ያለበት ሰው ነው።

በዘጸአት 19–34 ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የሙሴ ታሪክ እግዚአብሔር ሕይወታችንን እንዴት እንደሚለውጥ እጅግ የሚያስተምር ነው።

እግዚአብሔር ከእነዚህ ታዋቂ መሪዎች ጋር ግንኙነት የፈጠረው እንዴት ነበር? የሙሴን ሕይወት ማጥናት በእግዚአብሔር ኃይል እውቀት ብቻ ሳይሆን የእርሱን ፍቅርና ባህርይ በማወቅም እንዴት እንዳደገ ያሳያል። ይህ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት የመፍጠር ወሳኝ ክፍል ነው።

ሙሴ ወደ ሲና ተራራ ከመድረሱ በፊት፣ ገና ልዩ ለሆነው የመሪነት ሚና እየተዘጋጀ ሳለ፣ እግዚአብሔር በኃይል ተጠቅሞበታል። በምድያን ምድር በጎችን እየጠበቀ ሳለ እግዚአብሔር ሁለት መጻሕፍትን፣ ኢዮብንና ዘፍጥረትን፣ እንዲጽፍ አነሳሰው። ከዚያም በሚነድደው ቁጥቋጦ ትዕይንታዊ ክስተት እስራኤልን ከግብጽ እንዲያወጣ እግዚአብሔር ጠራው። በቀይ ባህር የግብጻውያንን አማልክትና ብርቱ ሰራዊት ሽንፈት ተመለከተ። እግዚአብሔር እሥራኤልን ከግብጽ ወደ ሲና እንዴት እንደመራ ለብዙ ሳምንታት ተመለከተ። ፊቱ እንዲያንጸባርቅ ካደረገው ልምምድ በኋላ ለሌላ 39 ዓመታት እሥራኤላውያንን እስከ ተስፋይቱ ምድር ጫፍ ድረስ መራ። ሙሴ ታማኝ የእግዚአብሔር ባሪያ እንደነበር የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች ይናገራሉ (ዘዳ. 34:5፣ ኢያሱ 1:1)፣ በጨለማ ያልተሸፈነ ብርሃን እና ሌሎች ሊለኩ የሚችሉበት ምሳሌ መሆን የቻለ ነብይ ነበር (ዘዳ. 18:15፣ 18)። ምንም እንኳን ሰዎች መመሪያዎቹንና ቃላቶቹን ሁሌ ባይከተሉም እርሱ የለውጥ ወኪል ነበር።

መመሪያዎቹንና ቃላቶቹን በተከተሉ ጊዜ ተከናውኖላቸው ነበር። እግዚአብሔር እንዲለውጠን ስንፈቅድለት በሕይወታችን ምን ማድረግ እንደሚችል ልዩ ከሆነው የሙሴ የሕይወት ታሪክ እንማራለን። እግዚአብሔር በሕይወትዎ በኃይል መስራቱን ከተገነዘቡባቸው ከሕይወትዎ እጥፋቶች መካከል አንዳንዶቹ ምን ነበሩ?

መስከረም 5
Sep 15

አንተን እንዳውቅ


ዘጸ. 33:12–17ን ያንብቡ። ሙሴ እግዚአብሔርን የጠየቀው ምን እንዲያስተምረው ነበር? የእግዚአብሔር ሀልዎት (መገኘት) እንዲመራው የጠየቀው ለምን ነበር?



ሙሴ በጌታ የነበረው እድገት ቀጣይነት የነበረው ነበር። ወደ እግዚአብሔር የበለጠውን በመቅረብ ራሱን በእግዚአብሔር አምሳል ለመቅረጽ ፈለገ። አንድ ቀን ሙሴ በመገናኛው ድንኳን ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገረ ሳለ እርሱን እንደማያውቀው በድንገት በመገንዘብ እንዲህ የሚል ጸሎት ጸለየ፡ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት - “አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ አውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ” (ዘጸ. 33:13)። ሙሴ እግዚአብሔርን በአዲስ ደረጃ የመረዳት ጥልቅ አስፈላጊነት እንዳለ ተረዳ።

እግዚአብሔርን በተሻለ ሁኔታ ሲያውቀው ከዚህ በፊት እንደማያውቀው ተረዳ። ምን እንደሚያስፈልገው አወቀና ከሙሉ ልቡ እርሱን ለማወቅ ፈለገ።

እግዚአብሔርም የሙሴን ፍላጎት በሙሉ ፈቃደኝነት ሰጠው።

እስካሁን ያሉ የሙሴ ልምምዶችን በመመልከት ከእግዚአብሔር ጋር ጥልቅና የቀረበ ግንኙነት ወደመፍጠር እንዴት እንደተሳበና በመንፈሳዊነት እንዴት እንዳደገ ማየት እንችላለን።

በመጀመሪያ፣ ሙሴ ወደ ተራራው በመውጣት “ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ” (ዘጸ. 19:3)። ከዚያም “ወደ ተራራው ራስ ወጣ” (ዘጸ. 19:20)፣ በኋለም እግዚአብሔር ወደሚኖርበት “ድቅድቅ ጨለማ” ወዳለበት ወደ ደመናው ቀረበ (ዘጸ. 20:21)።

በሌላ አጋጣሚ፣ ሙሴ እግዚአብሔር ወዳለበት “ወደ ደመናው ገባ።” በዚያም 40 ቀንና 40 ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ቆየ (ዘጸ. 24:18)። በእነዚህ 40 ቀናት እግዚአብሔር ለሙሴ ሁለት ውድ ስጦታዎችን ሰጠ፡- (1) እግዚአብሔር በገዛ እጁ ጠርቦ ባዘጋጃቸው ሁለት ጽላቶች ላይ የጻፋቸውን የአሥርቱን ትዕዛዛት ሥጦታ (ዘጸ. 24:12)፣ እና (2) ቤተ መቅደሱን እንዴት መስራትና ማስዋብ እንዳለበት የሚገልጹ መመሪያዎችን (ዘጸ. 25–31ን ይመልከቱ)።

ከዚያም ሙሴ ለኃጢአተኞች በማማለድ ሌላ 40 ቀንና 40 ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር አሳለፈ (ዘጸ. 32:30–32፣ ዘዳ. 9:18)።

ከዚህ ሁሉ በኋላ እንኳን ሙሴ የእግዚአብሔርን ባህርይ ተጨባጭ በሆነ ሁኔታ ለማወቅ ተመኘ፤ እግዚአብሔር እርሱ ማን እንደሆነ እንዲረዳ የተለየ ማስተዋልን ሰጠው። ሙሴ ለማግኘት የተመኘው ይህ እውቀት እግዚአብሔርን ዝም ብሎ በአእምሮ መረዳት ሳይሆን ስለ እርሱ ማንነት ተግባራዊ የሆነ እውቀት ማግኘት ነበር።

ኢየሱስ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” (ዮሐንስ 17:3) ማለቱ አያስገርምም። እግዚአብሔር ሰው ከመሆን የበለጠ ራሱን ለሰዎች የሚያስተዋውቅበት ሌላ ምን መንገድ ይገኛል? እግዚአብሔርን ያውቁታል ወይስ ዝም ብለው ስለ እርሱ ያውቃሉ? በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ምንድር ነው?

መስከረም 6
Sep 16

“እባክህ፣ ክብርህን አሳየኝ”


ከወርቅ ጥጃው ክህደት በኋላ ሙሴ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በማማለድ እግዚአብሔር እስከ ተስፋይቱ ምድር መምራቱን እንደሚቀጥል እርግጠኛ መሆን ፈለገ። በውስጡም እግዚአብሔርን በተሻለ ሁኔታ ለማወቅ ፈለገ። ዘጸ. 33:18–23ን ያንብቡ። ሙሴ ክብሩን ለማየት የጠየቀውን ጥያቄ እግዚአብሔር የመለሰለት እንዴት ነበር?



ሙሴ “እባክህ፣ ክብርህን አሳየኝ” በማለት እግዚአብሔርን ጠየቀው።

እግዚአብሔር በምህረቱ ክብሩን ገለጠለት። ነገር ግን የሙሴን ጥያቄ ሲመልስለት እግዚአብሔር “መልካምነቱን” ለማሳየት ቃል ገባለት። የእግዚአብሔር ክብር መልካምነቱ፣ ያውም ባህሪዩ እንደሆነ ከዚህ መደምደም ይቻላል። (ደግሞ ኤለን ጂ ኋይት ከጻፈቻቸው መጻሕፍት The Acts of the Apostles፣ p. 576፤ Christ’s Object Lessons፣ pp. 414፣ 415፤ Prophets and Kings፣ p. 313ን ያንብቡ)።

“እግዚአብሔር መልካምነቱን ለልጆቹ መስጠቱ የእግዚአብሔር ክብር ነው። ወንዶችና ሴቶች እጅግ ከፍ ወዳለው መስፈርት ደርሰው ለማየት ይናፍቃል።”—Ellen G. White፣ The Acts of the Apostles፣ p. 530። የእርሱ ክብር ተናዛዥ ኃጢአተኞችን ማቀፍ (Prophets and Kings፣ p. 668ን ይመልከቱ) እና እነርሱን ለመለወጥ የሚያስፈለገውን ነገር ሁሉ መስጠት ነው። በዚያው ልክ በሕይወታችን የእርሱን ባህሪይ መግለጥና ለሌሎች እንዲታወቅ ማድረግ የእኛ “ክብር” ነው። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

ይህ በእግዚአብሔር ባህርይ፣ መልካምነት፣ ቸርነት እና ፍቅር ላይ የሚደረግ ማሰላሰል በተግባሮቻችን መታየት አለበት። በዚህ መንገድ ለዓለም በረከት የመሆን ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለሚጠበቀው ዩኒቨርስም የሚያንጸባርቅ ብርሐን የመሆን ዕድል አለን። ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- “ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናልና፤ እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች እንዳደረገን ይመስለኛልና” (1ኛ ቆሮ. 4:9)። ይህ ዓለም አቀፋዊ እይታ ለሕይወታችንና ለአገልግሎታችን ከምናስበው በላይ የሆነ ትርጉምና ዓላማ ይሰጣል።

ጳውሎስ በሮሜ 2:4 ላይ “የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሃ ይመራል” ይላል። ይህ ማለት ሰዎች ኃጢአተኛ መሆናቸውንና ድነት እንደሚያስፈልጋቸው የሚያሳምነው የእግዚአብሔር መልካምነት (ቸርነት) ነው ማለት ነው።

በርግጥ መስቀልን ስንመለከትና በዚያ ቦታ የነበረው ማን እንደሆነ ስናውቅ (ጌታ ራሱ) እና እርሱ በዚያ ቦታ ለምን እንደነበር ስናውቅ (ስለወደደን እና ሊያድነን የሚችለው ብቸኛው መንገድ ይህ ብቻ ስለነበር) ስለ እግዚአብሔር መልካምነትና ባህርይ ሊኖረን የሚችለው ከሁሉ የሚበልጥ መገለጥ ይኖረናል። በመስቀልና እርሱ ስለ እግዚአብሔር ባህርይ በሚነግርዎት ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ ምን ያህል ጊዜ ያሳልፋሉ?

መስከረም 7
Sep 17

የእግዚአብሔር ራሱን መግለጥ


ዘጸ. 34:1–28ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ለሙሴ ክብሩን የገለጠው እንዴት ነበር? እንዴት ነበር?



ሙሴ መጀመሪያ የሰበራቸውን የሚመስሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ይዞ መሄድ ነበረበት (ዘጸ. 32:19)። በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ለሰባተኛ ጊዜ ሊገናኝ እየሄደ ነበር። ወደ ተራራ የወጣባቸው ክቡር አጋጣሚዎች በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ ተጠቅሰዋል፡- (1) ዘጸ. 19:3፣ 7፤ (2) ዘጸ. 19:8፣ 14፤ (3) ዘጸ. 19:20፣ 25፤ (4) ዘጸ. 20:21፣ ዘጸ. 24:3፤ (5) ዘጸ. 24:9፣ 12–18፤ ዘጸ. 32:15፤ (6) ዘጸ. 32:30፣ 31። ሙሴ ወደ ተራራው መውጣት የጀመረው በማለዳ ነበር።

አሁን ሙሴ ባለ ግርማውን የእግዚአብሔርን ባህርይ ለመረዳት ተዘጋጅቷል። የእግዚአብሔር ባህርይ ውበት እግዚአብሔር ራሱን በገለጠበት በዚህ የሚያምር መገለጥ በደንብ ተብራርቷል። እግዚአብሔር ማን እንደሆነ የሚገልጽ እጅግ ወሳኝ የሆነ መግለጫ ሲሆን በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ድርና ማግ የተሸመነ ወርቃማ ክር ነው (ዘሁ. 14:18፣ ነህምያ 9:17፣ መዝ. 103:8፣ ኢዮኤል 2:13፣ ዮናስ 4:2)።

እግዚአብሔር በዚህ ቦታ ያወጀው አዋጅ የብሉይ ኪዳን ዮሐንስ 3:16 ነው። የእግዚአብሔርን ባህርይ በትክክል መረዳት አስፈላጊ ስለሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ወሳኝ በሆኑ ቦታዎች ሕያው አምላክ ስለ ራሱ የተናገረውን ይህን ነገር ሥራ ላይ ያውላሉ፣ ይደግሙታል ወይም ያስፋፉታል።

ሙሴ ያልተለመደ፣ ተደርጎ የማይታወቅና ተወዳዳሪ የሌለውን የእግዚአብሔርን ስም ማብራሪያ በተቀበለ ጊዜ በግምባሩ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ። የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ጸጋ፣ ርኅራኄ፣ መልካምነት፣ ታማኝነት፣ ይቅርታ፣ ቅድስና እና ፍትሃዊነት ጭላንጭል ስናገኝ እኛም ደግሞ ወደ እርሱ እንሳባለን።

እኛም እርሱን ለማገልገልና ለመታዘዝ ፍላጎት እንዲኖረን በሚያደርግ ፍቅር እርሱን መውደድ የምንጀምረው የእርሱን ያልተለመዱ ብቃቶች ስናይና ስናደንቅ ነው። እርሱ ስለወደደን እኛም እንወደዋለን (1 ዮሐንስ 4:19)።

እግዚአብሔር ራሱን በገለጠበት በዚህ መገለጥ ለሕዝቡ አስደናቂ ተግባራትን ለመፈጸምና ወደ ተስፋይቱ ምድር ለማስገባት ለሙሴ ማረጋገጫ ሰጠ።

ሌሎች ሕዝቦች የእርሱን ግርማና አስደናቂ ሥራ እንደሚያዩ ተስፋ በመስጠት ቃል ኪዳኑን ያድስላቸዋል። “እነሆ እኔ ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ በምድር ሁሉ፥ በአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እንደ እርሱ ያለ ከቶ ያልተደረገውን ተአምራት በሕዝብህ ሁሉ ፊት አደርጋለሁ፤ እኔም በአንተ ዘንድ የምሠራው ነገር የሚያስፈራ ነውና አንተ ያለህበት ይህ ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ ያያል” (ዘጸ. 34:10)።

ነገር ግን እሥራኤላውያን ብልጽግናቸውን ለመጠበቅ እግዚአብሔርን መታዘዝና ግልጽ የሆኑ አሥርቱን ትዕዛዛት መከተል ያስፈልግ ነበር። ከዚያም አስቀድሞ የተጣሰውን የዚያን ቃል ኪዳን ይዘት እንዲጽፍ እግዚአብሔር ሙሴን ጠየቀው (ዘጸ. 34:27፣ 28).። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

መስከረም 8
Sep 18

የሚያንጸባርቀው (የሚያበራው) የሙሴ ፊት


ዘጸ. 34:29–35ን ያንብቡ። የሙሴ ፊት እንዲያንጸባርቅ ያደረገው ነገር ምን ነበር?



እግዚአብሔር የፍቅር ባህርዩን ለሙሴ ከገለጠለት በኋላ ሙሴ ፊቱ እያንጸባረቀ ከተራራው በመውረድ ወደ እሥራኤላውያን ሰፈር መጣ። ሙሴ ፊቱ እያበራ መሆኑን በመጀመሪያው ያውቅ ነበር? በፍጹም አያውቅም ነበር።

አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር እየቀረበ ሲሄድና ከእግዚአብሔር ቅድስና ጋር ሲነጻጸር የራሱን ፍጹም አለመሆን አብልጦ ይረዳል።

የሙሴ ፊት እንዲበራ ያደረገው የመለወጡ ምክንያት ምን ነበር? ሙሴ ከዚህ በፊት ለበርካታ ጊዜያቶች ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ቢፈጥርም በእነዚያ ጊዜያቶች ፊቱ ስላላበራ በዚህ አጋጣሚ ፊቱ የበራበት ምክንያትም በእግዚአብሔር ሀልዎት (መገኘት) ፊት ስለነበረ ብቻ አይደለም። ሆኖም በእግዚአብሔር ሀልዎት ውስጥ ባይሆን ኖሮ ፊቱ በፍጹም አይበራም ነበር።

ሙሴ የተለወጠውና ፊቱ የበራው የእግዚአብሔርን መልካምናትና ቸርነት በማስተዋሉና ከእግዚአብሔር የባህርይ ውበት የተነሣ ሙሉ በሙሉ ራሱን ለእግዚአብሔር ክፍት በማድረጉ ነበር። ራሳችንን ለእግዚአብሔር አሳልፈን ስንሰጥና እርሱ የሕይወታችን ጌታና ንጉሥ እንዲሆን ስንፈቅድ ልባችንና አእምሮአችን ለውጥን ይለማመዳሉ። 2ኛ ቆሮንቶስ 3:18ን ያንብቡ። ኢየሱስ ቀስ በቀስ ወደ ራሱ ምስል ሊለውጥዎት የሚችለው እንዴት ነው?



ጳውሎስ የሙሴን ፊት መብራት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያነጻጸረ ሲሆን የእግዚአብሔር ሕግና ጸጋ በአካል የተገለጡበት የኢየሱስ ክብር ከሙሴ ጋር ያለውን ሕግ ክብር ይበልጣል። ክርስቶስ ከሕጉ ጋር በባህርያችን ውስጥ ሊቀረጽ የሚችለው ዓይናችንን በኢየሱስ ላይ ስንተክል (ዕብ. 3:1፣ ዕብ. 12:2) እና በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ብቻ ነው (2ኛ ቆሮ 3:12–18)።

እግዚአብሔር ባህርያችንን እንዲለውጥና በመለኮታዊ ምስሉ እንዲቀርጸን ስንፈቅድለት እግዚአብሔር ምን ማድረግ እንደሚችል በማሳየት ሙሴ ምሳሌያችን ነው። ጳውሎስ “በአዲስ ሕይወት” ስለመመላለስ ሲናገር ይህን ማለቱ ነው (ሮሜ 6:4)። የእግዚአብሔርን ባህርይ በተሻለ ሁኔታ ማንጸባረቅ ያለባቸው የባህርይዎ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? ምናልባት ሁሉም አካባቢዎች ሊሆኑ ይችላሉ፣ አይደለም? ነገር ግን በመስቀል ላይ ማተኮርና የዚያ ትርጉም ማደፋፈሪያና የድነት መተማመኛ ሊሰጥ የሚችለው እንዴት ነው?

መስከረም 9
Sep 19


ተጨማሪ ሀሳብ


“ጣዖት አምልኮ በሲና” የሚለውን ርዕስ ኤለን ጂ ኋይት ከጻፈችው አባቶችና ነቢያት ከሚለው መጽሐፍ ከገጽ 327–330 ላይ በጥንቃቄ ያንብቡ። በአንድ ጨለምለም ያለ ቀን አባትና ልጅ አንድ ትልቅ ደብር (ካቴድራል) ጎበኙ። የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ገለጻዎች ያሉባቸውን ቀለም የተቀቡ መስታወቶች እየተመለከቱ ሳሉ ጸሐይ በድንገት በመስታወቱ ላይ በተሳሉ ሰዎች ላይ ስሜትን በሚይዝ ብሩህነት እያበራ ማንጸባረቅ ጀመረ።

ትንሹ ልጅ አባቱን እንዲህ በማለት ጠየቀው፡- “አባባ፣ እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” አባትየው ስለ ክርስትና፣ ስለ ክርስቶስ ወይም ስለ ደቀ መዛሙርቱ እስከዚህም አያውቅም ነበር። ነገር ግን እንዲህ በማለት በፍጥነት መለሰለት፡ - “እነዚህ ሰዎች ክርስቲያኖች ናቸው።” ይህ ብሩህ ስዕል በልጁ አእምሮ ውስጥ ቆየ። አንድ ቀን የልጁ መምህር ክፍሉን እንዲህ በማለት ጠየቀ፡- “ልጆች፣ ክርስቲያኖች እነማን እንደሆኑ ታውቃላችሁ?” ትንሹ ልጅ በደብሩ የነበረውን ብሩህ ስዕል አስታውሶ እንዲህ በማለት መለሰ፡- “አዎን አውቃለሁ፤ ክርስቲያኖች የሚያበሩ ሰዎች ናቸው።” በተመሳሳይ ሁኔታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፡- “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማቴ. 5:16)። የለውጥ ወኪሎች መሆን የሚችሉት የሚያበሩ ሰዎች ብቻ ናቸው። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት


የመወያያ ጥያቄዎች




1. “በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን ካዋረድንና ቸርና ትሁት እንዲሁም “በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን ካዋረድንና ቸርና ትሁት እንዲሁም ገርና አዛኝ ከሆንን፣ ዛሬ አንድ ነፍስ ብቻ በሚለወጥበት ቦታ አንድ መቶ ሰዎች እውነትን በመቀበል ይለወጣሉ።”—Ellen G. White፣ Testimonies for the Church፣ vol. 9፣ p. 189። ባህርያችን፣ ተግባራችንና አመለካከታችን በምስክርነታችን ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ስለመሆናቸው እዚህ ላይ እንዴት ያለ ኃይለኛ መልእክት ለሁላችንም ተቀምጦልናል?

2. ዘጸ. 34:6፣ 7 በትክክል የብሉይ ኪዳን ዮሐንስ 3:16 ነው ዘጸ. 34:6፣ 7 በትክክል የብሉይ ኪዳን ዮሐንስ 3:16 ነው ተብሏል። ለምን?

3. እግዚአብሔር በዘጸአት 34፡6 እና 7 ላይ ራሱን በገለጠበት እግዚአብሔር በዘጸአት 34፡6 እና 7 ላይ ራሱን በገለጠበት መገለጥ ላይ በመመስረት አምላክዎ ማን እንደሆነ ለሚጠይቁ ሰዎች የእግዚአብሔርን ባህርይ ውበት እንዴት ማብራራት ይችላሉ?

4. ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ባህርይና ተግባር በአካሄዳቸው ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ባህርይና ተግባር በአካሄዳቸው (በአኗኗራቸው) ላይ እንዴት ተጽእኖ እንደሚፈጥር በክፍልዎ ውስጥ ተወያዩ። በራስዎ ልምምድ ደግ፣ ቸር፣ ትሁትና ይቅር ባይ የሆኑ ሰዎች ተጽእኖ ምን ነበር? በተመሳሳይ መልኩ ክፉ፣ ይቅር የማይሉና ጥጋበኛ የሆኑ “ክርስቲያኖች” ከእግዚአብሔር ጋር በነበረዎ አካሄድ ላይ ተጽእኖ ያሳደሩት እንዴት ነበር?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL