የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ዘጸአት



3ኛ ሩብ ዓመት 2025


መስከረም 10 - 16

13ኛ ትምህርት

Sep 20 - 26




ቤተ መቅደሱ



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ዘጸ. 35:1–36:7፤ ዘፍ. 1:1፤ ዘጸ. 36:8–39:31፤ ዕብ. 7:25፤ ዘጸ. 40:1–38፤ ዮሐንስ 1:14።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ደመናውም የመገናኛውን ድንኳን ከደነ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላ።…በመንገዳቸውም ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የእግዚአብሔር ደመና በማደሪያው ላይ በቀን ነበረና፥ እሳትም በሌሊት በዚያ ላይ ነበረና” (ዘጸ. 40:34፣ 38)።

በብሉይ ኪዳን ዘመን (እና ዛሬም ለእኛ) የእግዚአብሔር ሕዝብ ዋና ስራ ከእግዚአብሔር ጋር የቅርብ ግንኙነት ፈጥሮ መኖር፣ እርሱን ማምለክ፣ ማገልገል እና የእግዚአብሔርን ትክክለኛ ምስል ለሌሎች ማሳየት ነው (ዘዳ. 4:5–8)። በኤደን የአትክልት ቦታ አዳምና ሔዋን ኃጢአታቸው እግዚአብሔርን እንዲፈሩ ስላደረጋቸው ከእርሱ ተደበቁ። ኃጢአተኛነት ተፈጥሮአዊ በሆነ ሁኔታ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲፈሩ ያደርጋቸዋል፤ ይህ ፍርሃት ስለ ባህርዩ ያለንን አመለካከት ያጣምማል። መልካሙ ዜና ይህንን ክፍተት ለመድፈን እግዚአብሔር የመጀመሪያውን እርምጃ የወሰደ ሲሆን በራሱ ተነሳሽነት የተፈጠረውን ክፍተት በመዝጋት የተቋረጠውን ግንኙነት ይጠግናል። ኃጢአተኛን “የት ነህ?” (ዘፍ. 3:9) በማለት ወደ እርሱ እንዲመለስ ይጠራዋል።

ስለዚህ ቀዳሚው ተልዕኮአችን ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን ባህርይ እና የፍቅርና የጽድቅ ሥራዎቹን በዙሪያችን ላሉት ማቅረብ ነው። ሰዎች ወደ እግዚአበሔር ሲሳቡና ለእነርሱ ያለው ፍቅር ከራስ ወዳድነት የጸዳ መሆኑን ሲያምኑ ሕይወታቸውን ለእርሱ ይሰጣሉ፤ እንዲፈጽሙ የሚነግራቸው ነገርም ለጥቅማቸው እንደሆነ ስለሚያውቁ ይታዘዙታል። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

ቤተ መቅደሱ እግዚአብሔር ከሰብአዊ ዘር ጋር ያለውን ቅርበት በማሳየት ወደ እርሱ በእምነት የሚመጡትን እንዴት እንደሚያድናቸው የሚያሳውቁትን ታላላቅ እውነቶች ገለጠ። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለመስከረም 17 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ

መስከረም 11
Sep 21

የእግዚአብሔር ሰንበት


ሰባተኛውን ቀን ሰንበትን የሚቃወሙ ሰዎች ሰንበት የተሰጠው ለአይሁዶች ብቻ ነው በማለት ምንም ያህል በውሸት ቢከራከሩም (ሰባተኛው ቀን የተለየውና የተቀደሰው በኤደን ነበር [ዘፍ. 2:1–3ን ይመልከቱ])፤ ወይም አይሁዶች ስለ ሰንበት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት በሲና ነው ብለው በውሸት ቢከራከሩም (አይሁዶች ከሲና በፊት ሰንበትን ይጠብቁ ነበር [ዘጸ. 16:22–29ን ይመልከቱ])—ሰንበት ከመጀመሪያው ጀምሮ የዕብራውያን ሕዝብ የሕይወታቸው ክፍል ለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። ዘጸ. 35:1–3ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ቤተ መቅደሱን ከመገንባት አውድ ለሕዝቡ በተደጋጋሚ የተነገረው እውነት ምን ነበር?



ሰንበትና እርሱ የሚያስተላልፈው መልእክት ከዚህ በፊትም ሆነ አሁን ሁልጊዜም ስለ እግዚአብሔር ሲሆን እግዚአብሔር ማን እንደሆነና የእርሱ ኃይለኛ ሥራዎች ምን እንደሆኑ የሚያሳይ ነው። ሰንበት የእግዚአብሔርን የመፍጠርና የማዳን ተግባር በማስታወስ ከሕዝቡ ጋር መኖር በሚፈልገው በእርሱ ላይ ትኩረታችንን ያደርጋል። በዚህ መንገድ ሰንበትና ቤተ መቅደስ ወደ አንድ አቅጣጫ ያመለክታሉ፣ ያውም የእግዚአብሔር በሕይወታችን መገኘት ነው። የብሉይ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ሰንበት የተለያዩ መልእክቶችን ያስተላልፋል።

እነዚህን የሚያስተላልፋቸውን መልእክቶች በአምስት ወሳኝ ነጥቦች አጠቃልሎ ማቅረብ ይቻላል፡-
1. እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው፡- መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ አስደናቂና የማዕዘን ድንጋይ በሆነ አዋጅ ይጀምራል (ዘፍ. 1:1)። ሰንበት የእግዚአብሔር ፍጥረት ግልጽ መታሰቢያ ነው (ዘፍ. 2:2፣ 3፤ ዘጸ. 20:8– 11)። እግዚአብሔር ፈጣሪያችን መሆኑን ከሚገልጸው ከዚህ እውነት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ሁሉ ይፈልቃሉ።
2. መሲሁ ይመጣል፣ ይህ ተስፋ እባቡን (ሰይጣንን) በማሸነፍ ክፉን ድል እንደሚያደርግ እግዚአብሔር ቃል በገባው ዘር ዙሪያ ማዕከል ያደርጋል።
3. እግዚአብሔር መንግሥቱን ይመሰርታል፣ ሰንበት የዚያ መንግሥት ቅምሻ ነው።
4. ድነት የሚመጣው ከእግዚአብሔር ነው ፣ እግዚአብሔር አዳኛቸውና ተቤዥያቸው መሆኑን እና ድነት የሚመጣው ከጸጋውና ከጸጋው ብቻ መሆኑን የእግዚአብሔር ሕዝብ ይመሰክራሉ።
5. እግዚአብሔር የሁሉም ሕዝብ የመጨረሻው ፈራጅ ነው። እርሱን በቀጣይነት የሚቃወሙና የሚክዱ የወደፊት ተስፋ የላቸውም፣ ነገር ግን እርሱን ለሚከተሉት ዘላለማዊ ሕይወትን በነጻ ይሰጣቸዋል። አይሁዶች እንዲህ የሚል አባባል አላቸው፡- እሥራኤላውያን ሰንበትን ከጠበቁት ይልቅ ሰንበት እሥራኤላውያንን ጠብቆአቸዋል። እኛ አድቬንቲስቶች እንደመሆናችን በዚህ መልክ ባንገልጸውም ሰንበት በቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ምን ወሳኝ ሚና ይኖረዋል?

መስከረም 12
Sep 22

ሥጦታዎችና መንፈሱ


ዘጸ. 35:4–36:7ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ዛሬ ለእኛ ምን ወሳኝ ትምህርት አለ?



ቤተ መቅደሱን ለመገንባት እጅግ ብዙ የከበሩ (ውድ) ነገሮች ያስፈልጉ ስለነበር ለሥራው የሚያስፈልጉ ነገሮች የተገኙት ከልባቸው፣ በፈቃደኝነትና በደስታ ከሰጡ የእግዚአብሔር ሕዝብ የልግስና ሥጦታዎች ነበር። ሕዝቡ ወርቅ፣ ብር፣ ነሃስ፣ ቀጭን የተልባ እግር፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ የተለዩ አልባሳት፣ የግራር እንጨት፣ የወይራ ዘይት፣ ቅመማ ቅመም፣ እና ሌሎች የሚያስፈልጉ ብዙ ነገሮችን ሰጡ። ድንኳኑ ወይም በድንኳኑ ውስጥ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት ያሉ ልዩ የሆኑ ብዙ ዕቃዎች በእነርሱ የእጅ ሙያ ጥበብና ትጋት መሰራት ስለነበረባቸው ሰዎቹ ጉልበታቸውንም ጭምር ሰጡ። ደግሞ ልብስ ሰፊዎች በቤተ መቅደስ ለሚያገለግሉ ካህናት ልብስን እና የደረት ኪስንና መጠምጠሚያን የሚያካትቱትን እጅግ ረቂቅ የሆኑ የሊቀ ካህኑን ልብሶች መስፋት ነበረባቸው።

እሥራኤላውን ግብጽን ለቀው ሲወጡ ግብጻውያን በሰጡአቸው ስጦታዎች እግዚአብሔር እሥራኤላውያንን እጅግ ባርኳቸው ነበር። አሁን ደግሞ ምህረት ለተሞላበትና ኃይለኛ ለሆነው የእግዚአብሔር አመራር የምሥጋና ሥጦታዎችን ለመስጠት ለእነርሱ መልካም አጋጣሚ ስለነበር ይህን ሥራ ለእርሱ ክብር ለመፈጸም ልባቸው ተነሳሳ።

ሕዝቡ በደስታና በልግስና ይሰጡ ስለነበር እንዲህ ተብሎ ለሙሴ ተነገረው፡- “እግዚአብሔር ለማገልገያ ሥራ ይደረግ ዘንድ ላዘዘው ከሚበቃ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ሕዝቡ አመጡ” (ዘጸ. 36:5)። ስለዚህ “ያመጡትም ነገር ሥራን ሁሉ ለመፈጸም በቅቶ ገና ይተርፍ ስለ ነበረ” ሕዝቡ የሚሰጡትን ስጦታ ሙሴ ማስቆም ነበረበት (ዘጸ. 36:7)።

በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን በትክክል መስራት እንዲችሉ እግዚአብሔር አስታጠቃቸው፣ ኃይልም ሰጣቸው። ባስልኤል፣ ኤልያብና ሌሎችም “በእግዚአብሔር መንፈስ ተሞልተው ነበር” (ዘጸ. 35:31)፣ ይህ ማለት ሥራውን ሁሉ በትክክል መስራት እንዲችሉ ክህሎትና ጥበብ ተሰጥቶአቸው ነበር ማለት ነው። ፕሮጀክቱ ግዙፍ ስለነበር እግዚአብሔር ለሙሴ ባሳየው ምሳሌ በትክክል መሰራት ነበረበት።

ቤተ መቅደሱን ለመገንባት ጥቅም ላይ መዋል ያለበት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ከሰዎች ችሎታና ክህሎት ጋር የተገናኘ መሆኑ ወሳኝ ነው። በመንፈስ መሞላት አስማታዊ ሂደት አይደለም፣ የተለዩ መንፈሳዊ ኃይሎች በሰው ውስጥ ይሆናሉ ማለትም አይደለም። እግዚአብሔር ሥራው ወደ ፊት እንዲሄድና ተልዕኮው ተፈጻሚ እንዲሆን ለማድረግ ተከታዮቹ ዓላማውን እንዲፈጽሙና በደንብ እንዲሰሩ ኃይል ይሰጣቸዋል። እርስዎ በመንፈስ ቅዱስ በተሞሉ ጊዜ ምን መንፈሳዊ ሥጦታዎችን ተቀበሉ? መንፈሳዊ ሥጦታዎች ጥሩ ሆነው የሚያድጉት በሕይወትዎ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን በደንብ ሲንከባከቡ ነው (ገላ. 5:22፣ 23)።

መስከረም 13
Sep 23

የተገነባው ቤተ መቅደስ


ዘጸ. 36:8–39:31ን በፍጥነት ያንብቡ። የዚህ ዓይነት ግልጽ መመሪያዎች የተሰጡት ለምን ይመስሎታል? እግዚአብሔር ለሁሉም ዝርዝር ነገሮች ግድ የሚለው ስለመሆኑ ይህ ምን ያስተምራል?



ሙሴ ቤተ መቅደሱን በጥንቃቄ የገነባው ሲሆን በሲና ተራራ ላይ የተቀበላቸው መመሪያዎች በጥንቃቄ ተተግብረዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የሚከተሉትን ነገሮች ይዘረዝራል፡- (1) ቤተ መቅደሱን ከተለያዩ አልባሳት፣ መጋረጃዎች እና ክፍሎች ጋር (ዘጸ. 36:8–38)፤ (2) ታቦቱን (ዘጸ. 37:1–9)፤ (3) የህብስት ጠረጴዛን (ዘጸ. 37:10–16)፤ (4) መቅረዙን (ዘጸ. 37:17–24)፤ (5) የዕጣን መሰዊያውን (ዘጸ. 37:25–29)፤ (6) የሚቃጠል መስዋዕት የሚቀርብበትን መሰዊያ (ዘጸ. 38:1–7)፤ (7) የመታጠቢያ ገበታ (ሳህን) (ዘጸ. 38:8)፤ (8) የጉባኤ ቦታ (ዘጸ. 38:9–20)፤ እና(9) ለቤተ መቅደሱ ሥራ ጥቅም ላይ የሚውሉ ነገሮችን (ዘጸ. 38:21–31)። ዘጸ. 39 ኤፉድን፣ የደረት ሳጥንን እና ሌሎች የካህናት ልብሶችን በመግለጽ ይቀጥላል።

የቤተ መቅደስ አገልግሎቶች መላውን የእግዚአብሔርን የድነት እቅድ የሚያሳዩ በዓይን የሚታዩ ተጨባጭ የወንጌል ትምህርቶች ናቸው። የተለያዩ ሥርዓቶቹ የሚከተሉትን ነገሮች ያሳያሉ፡- (1) እግዚአብሔር ለኃጢአት ያለውን ጥላቻ ፣ (2) ንስሃ የገቡ ሰዎችን እንዴት እንደሚያድን ፣ (3) የኃጢአተኞች ዕጣ ፋንታቸው ምን እንደሆነ ፣ እና (4) ክፋት የሌለበትን ባለ ግርማ የሆነ መጪ ጊዜን እንዴት እንደሚያረጋግጥ።

በቤተ መቅደስ ውስጥ በዓመት ሁለት የተለያዩ ግን በቅርበት የተገናኙ አገልግሎቶች ይፈጸሙ ነበር። እነርሱም ዕለታዊውና ዓመታዊው አገልግሎቶች ናቸው። ይህ ሁለት ክፍል ያለው አገልግሎት እግዚአብሔር ኃጢአትን እንዴት እንደሚይዝና ኃጢአተኞችን እንዴት እንደሚያድን ያሳያል። በዕለታዊው የቤተ መቅደስ አገልግሎት አማካይነት እግዚአብሔር ንስሃ ለገቡት ኃጢአታቸውን ይቅር የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት እንዳላቸውና ድነትን በቸርነቱ እንደሰጣቸው አረጋገጠላቸው። ይህን የድነት ሥጦታ ለመቀበል መስዋዕት መቅረብ የነበረበት ሲሆን የእነዚህ መስዋዕቶች ደም “ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻውን” (1 ዮሐንስ 1:7) የመሲሁን ሞት ያመለክት ነበር። ኃጢአትን መናዘዝና የክርስቶስን የጽድቅ ልብስ መቀበል በዚህ ሥጦታ ማዕከል ውስጥ ነበር (መዝ. 32:1፣ 2)። በዚህ መንገድ ተናዛዡ ኃጢአተኛ ይቅርታ ስለ ማግኘቱ ማረጋገጫ የተሰጠው ሲሆነ በድነቱም መደሰት ይችላል።

በስርየት ቀን የሚከናወነው ዓመታዊው አገልግሎት እግዚአብሔር ኃጢአትን እንዴት እንደሚያስወግድ፣ የኃጢአትን ችግር እንዴት እንደሚፈታና ኃጢአት የሌለበትን መጪ ጊዜ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ያሳያል (ዘሌ. 16፣ ዮሐንስ 1:29)። አሁን ክርስቶስ በሰማያዊው ቤተ መቅደስ እያከናወነ ያለው ሁለት ዓይነት አገልግሎት እግዚአብሔር ለእኛ እየሰራ ያለው ሥራ ሌላ መግለጫ ስለሆነ (ዕብ. 7:25) ለክፋት ችግር የመጨረሻውን መፍትሄ ያመጣል (ዳን. 7:13፣ 14፣ 22፣ 27፤ ዳን. 8:14፤ ራዕይ. 21:4)።

ቤተ መቅደሱ እግዚአብሔር የሚመለክበት፣ የሚወደስበትና ለእርሱ ምስጋና የሚቀርብበት ቦታ ነበር። አምልኮ አማኞችን ከእርሱ ጋር ሕብረት እንዲፈጥሩ ከሚጋብዘው ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን ጠብቆ ማቆየትን የሚገልጽ ነው።

መስከረም 14
Sep 24

በቤተ መቅደሱ ውስጥ የእግዚአብሔር መገኘት


ዘጸ. 40:1–38ን ያንብቡ። እሥራኤላውያን የእግዚአብሔርን መገኘት ለይተው ያውቁ የነበሩት እንዴት ነበር?



የኦሪት ዘጸአት የመጨረሻው መጽሐፍ (ዘጸ. 40) የቤተ መቅደሱን ምርቃትና የአሥርቱን ትዕዛዛት ስጦታ ይገልጻል። የቤተ መቅደሱ ምረቃ እሥራኤላውያን በሲና የነበራቸው ቆይታ የመጨረሻው ክስተት ነበር።

የእግዚአብሔር ክብር ቅድስናው፣ ባህርዩ እና የፍቅር መገኘቱ ሲሆን ይህ ራሱ መልካምነት ነው ዘጸ. 3:5፤ ዘጸ. 33:18፣ 19)። የእርሱ መገኘት ቤተ መቅደሱን በመሙላት እንደ ደመና፣ የሼክና ክብር ታይቷል። የዘጸአት መጽሐፍ በቀን በደመና በሌሊት በእሳት አምድ በመራው የእግዚአብሔር መገኘት ምሪት ላይ አጽንዖት በመስጠት ይጠናቀቃል። እጅግ ግልጽና ኃይለኛ በሆነ መንገድ ዕብራውያን የእግዚአብሔርን ተጨባጭነት ብቻ ሳይሆን እነርሱን ሲመራ የነበረበትን ቅርበቱንና በመካከላቸው መገኘቱንም መለማመድ ነበረባቸው።

ሙሴ በሁለተኛው ዓመት የመጀመሪያ ወር የመጀመሪያው ቀን ቤተ መቅደሱን አቆመ (ዘጸ. 40:2፣ 17)። አሮንና ልጆቹን ለክህነት መለየትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ዘይት በመቀባት ቀደሰ (ዘጸ. 40:9፣ 13–15)። ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር እየቀደሰ በቅድስተ ቅዱሳን፣ በቅዱስ ቦታና በጉባኤ ቦታ ውስጥ አለፈ። በዚህ ሂደት አማካይነት የመላው ቤተ መቅደስ አገልግሎቶችን መርቆ አስጀመረ (ደግሞ ዘሁ. 7:1ን ይመልከቱ)። ሙሴ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የቻለው በምረቃው ጊዜ ብቻ ሲሆን ከዚያ በኋላ በዚያ ቦታ በዓመት አንድ ጊዜ፣ በስርየት ቀን፣ ማገልገል የሚችለው ሊቀ ካህኑ ብቻ ነበር (ዘሌ. 16:2፣ 17)።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሥራው መጠናቀቁን በሶስት አጋጠሚዎች ይናገራል፡- (1) በፍጥረት ሳምንት መጨረሻ ላይ እግዚአብሔር የመፍጠር ሥራውን ማጠናቀቁን አስምሮበታል (ዘፍ. 2:1–3)፤ (2) የቤተ መቅደሱ ሥራ መጠናቀቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንዲህ ይገልጸዋል፡- “እንዲሁም ሙሴ ሥራውን ፈጸመ” (ዘጸ. 40:33)፤ እና (3) ሰለሞን ቤተ መቅደሱን ሰርቶ በጨረሰ ጊዜም በዚህ መልክ ተገልጾአል (1ኛ መሳፍንት 7:51)።

ይህ በፍጥረትና በእሥራኤል ቤተ መቅደስ መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ ይዘት፣ ጌታ ከዳኑት ጋር በአድሲቱ ምድር በምትኖረው “የእግዚአብሔር መቅደስ” በሆነችው አዲሲቷ ኢየሩሳሌም (ራዕይ. 21:2፣ 3ን ከራዕይ. 22:1–4 ጋር ያነጻጽሩ) የሚያድርበትን ጊዜ ያመለክታል።

እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱን በመገኘቱ መሙላቱ (ዘጸ. 40:34)፣ ከሙሴ መወለድ በመጀመር በአሥሩ መቅሰፍቶች ጊዜ የግብጻውያን አማልክት በመሸነፋቸው፣ ሕዝቡ ከግብጽ በማምለጣቸው፣ የግብጻውያን ሰራዊት በመሸነፉ እና በመጨረሻም እግዚአብሔር በሲና ተራራ በመገለጡ የቀጠሉ ክስተቶች በግርማ የተሞላ ፍጻሜ ነው።

እርስዎ አሁን እንኳን የእግዚአብሔርን መገኘት መለማመድ የሚችሉባቸው መንገዶች ምንድር ናቸው? እንዲህ ማድረግዎ ወሳኝ የሚሆነው ለምንድር ነው? የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

መስከረም 15
Sep 25

ኢየሱስ ሰብአዊ ዘርን ማደሪያው


(ቤተ መቅደሱ) አደረገ ዮሐንስ 1:14ን ያንብቡ። የክርስቶስ ሥጋ መልበስ ከቤተ መቅደሱ ጋር የተነጻጸረው እንዴት ነው?



የኢየሱስ ሥጋ መልበስ ምስጢርና የዳኑት ለዘላለም የሚያጠኑት ብቸኛ ሳይንስ ነው። ክርስቶስ የእኛን ሥጋ በመልበስ ከእኛ ጋር ተጨባጭ በሆነ መንገድ እንደሚኖር ሐዋርያው ዮሐንስ ገልጦአል። በዚህ ቦታ ኢየሱስ ሥጋን መልበሱ እሥራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲጓዙ ሳሉ በሲና እና በምድረ በዳ በነበረው ቤተ መቅደስ ከእነርሱ ጋር ካደረበት ጋር ይመሳሰላል።

ኢየሱስ ሥጋ በለበሰ ጊዜ ከሰብአዊ ዘር ጋር አደረ። እንዴት ያለ ከአእምሮ በላይ የሆነ ራስን ዝቅ ለማድረግ መስማማት ነው! ዘላለማዊው አምላክ እውነትም “አማኑኤል፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” መሆኑን ለማረጋገጥ ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖ ወደ እኛ ወረደ።

ማቴዎስ 18:20 ላይ ኢየሱስ ሁለት ወይም ሶስት ሆነው በስሜ በተሰበሰቡበት በመካከላቸው እገኛለሁ ብሏል። ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ መገኘት አማካይነት ከሕዝቡ ጋር ነው። ክርስቶስ ከእርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲኖራቸው ተከታዮቹን እንዲህ በማለት ይጋብዛቸዋል፡- “ እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” (ራዕይ. 3:20)። ራዕይ 21:1–3ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ የቀረበልን ነገር ምንድር ነው?



አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ወደ ምድር ስትወርድ የሚሆነውን ነገር ዮሐንስ እንዲህ በማለት ያውጃል፡- “እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል” (ራዕይ. 21:3)። ከተማዋ በሙሉ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስለሆነች በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም መቅደስ የለም (ራዕይ. 21:22)። በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበረው ቅድስተ ቅዱሳን ስድስት ጎን ያለው ሆኖ ሁሉም ጎኖቹ እኩል እንደሆነው (ኩብ) ሁሉ የከተማይቱ ርዝመት፣ ስፋትና ወርድ እኩል ነው (ራዕይ. 21:16)። ኃጢአት፣ ሞት ወይም ስቃይ በሌለበት ዓለም አምላካችን ባለበት ለዘላለም እንኖራለን። ኢየሱስ ቃል የገባልንን ነገር በመመልከት እስከ መጨረሻው መታገስን መማር የምንችለው እንዴት ነው?

መስከረም 16
Sep 26


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ ኋይት አባቶችና ነቢያት በሚለው መጽሐፏ ከጻፈችው “ቤተ መቅደሱና አገልግሎቶቹ” የሚለውን ርዕስ ከገጽ 353–358 ያንብቡ።

“መለኮታዊ የማዳን ተግባር፣ ማለትም እሥራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ ማውጣት፣ የቤተ መቅደሱን ግንባታ ቀድሞታል። ይህን ደግሞ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ቋሚ የሆነ የቃል ኪዳን ግንኙነት ለመፍጠር ፈቃደኛ መሆን ተከትሎታል። እርሱ አምላካቸው እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ (ዘጸ. 6:7)። ከእርሱና ከእርስ በርሳቸው ጋር የሚገናኙበት መንገድ በቃል ኪዳን ሕጉ ተደንግጓል። በርግጥ ቤተ መቅደሱ ሰውና እግዚአብሔር የሚገናኙበት የመገናኛ ቦታ ነበር። ሕዝቡ በማደሪያው ወዳለው እግዚአብሔር መድረስ የሚችሉት ከዳኑና ከእግዚአብሔር ጋር በቃል ኪዳን አማካይነት ቋሚ ግንኙነት ከፈጠሩ በኋላ ብቻ ነበር።”—Andrews Bible Commentary: Old Testament፣ “ዘጸ.” (Berrien Springs፣ MI: Andrews University Press፣ 2020)፣ p. 226.

ኤለን ጂ ኋይት የቤተ መቅደስ አገልግሎቶችን ዓላማ እንዲህ በማለት ትገልጻለች፡- “ስለዚህ በቤተ አምልኮው አገልግሎትና ኋላ ቦታውን በወሰደው ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሕዝቡ ከክርስቶስ ሞትና አገልግሎት ጋር የተዛመዱ ታላላቅ እውነቶችን በየዕለቱ ይማሩ ነበር። እንዲሁም በዓመት አንድ ጊዜ የሕዝቡ አእምሮዎች የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት በክርስቶስና በሰይጣን መካከል ወደሚደረገው ታላቁ ተጋድሎ፣ በመጨረሻ ዩኒቨርስን ከኃጢአትና ከኃጢአተኞች ወደሚያነጻው የመዝጊያ ክስተቶች ይመራ ነበር።”— Patriarchs and Prophets፣ p. 358.


የመወያያ ጥያቄዎች




1. የቤተ መቅደስ አገልግሎቶች ማዕከል የነበረው ደም ማፍሰስ የቤተ መቅደስ አገልግሎቶች ማዕከል የነበረው ደም ማፍሰስ ነበር። የተለያዩ ዓይነት እንስሳቶች እየተሰዉ ደማቸው በሁሉም የቤተ መቅደስ ሥርዓቶች ውስጥ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። ደሙ ምንን ይወክል ነበር? እነዚህ መስዋዕቶች በሙሉ በመጨረሻ ምንን ያመለክቱ ነበር?

2. የዩኒቨርስ ፈጣሪ የሆነው አምላክ በሕዝቡ መካከል በቤተ የዩኒቨርስ ፈጣሪ የሆነው አምላክ በሕዝቡ መካከል በቤተ መቅደስ ማደሩ አስደናቂ ቢሆንም ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖ ሰብአዊ ፍጡር በመሆን በመካከላችን ለማደር መምጣቱ ምንኛ የበለጠውን ያስደንቅ ይሆን። ይህ ራሱ አስደናቂ የሆነ የፍቅር መግለጫ መሆን ይችል ነበር። ነገር ግን ራሱን የኃጢአት መስዋዕት አድርጎ ማቅረብ፣ ማለትም በእኛ ፋንታ መሞትስ? ይህ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ምን ያስተምረናል? ደግሞ እግዚአብሔር በዘላለማዊ መንግሥቱ ድነን ለማየት ምን ያህል እንደሚፈልግ ይህ ምን ያስተምረናል?

3. ዕብራውያን 8:1–6ን ያንብቡ። ኢየሱስ አሁን በሰማያዊው ዕብራውያን 8:1–6ን ያንብቡ። ኢየሱስ አሁን በሰማያዊው ቤተ መቅደስ ስለ እኛ እያደረገ ያለውን ነገር ምድራዊው ቤተ መቅደስ እንዴት እንዳንጸባረቀ ይህ ምን ይነግረናል?



የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ለሚፈልጉ የተደራጁ ቤተከርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎትድርጅቶች የተሠጠ

ማሳሰቢያ


የትንቢት መንፈስ(Spirit of Prophecy - SOP )መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡

እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ የተደራጀ ቤተከርስቲያንም ሆነ በዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ ያለው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን በበላይነት በሚያስተዳድራቸው ሰበካዎችና ኮንፍራንስ የጽሁፍ ከፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ አንዲያስተረጉም ፈቃድ ይሰጠዋል ትርጉሙም ሲጠናቀቅ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጽ በታተመ ወረቀትና ሙሉውን መጽሐፍ በሲዲ ካስረከበ በኋላ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ ሥራውን መፈፀም ይቻላል።

በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገለግሎት ድርጅቶች በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡

ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ ከርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ ማስራጨት፤ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡

ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕከት መልዕከት ለማዳረስ እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡

ድርጅቱ




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL