የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ፍንጮች፣ ምስሎች፣ ምሳሌዎች፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ማጥኛ መንገድ



2ኛ ሩብ ዓመት 2025


ግንቦት 9 - 15

8ኛ ትምህርት

May 17 - 23




በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ፡ ክፍል 1



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዕብ. 9:11–15፣ መዝ. 122፣ መዝ. 15፣ መዝ. 24፣ ዘፀ. 33:18–23፣ መዝ. 5፣ መዝ. 51:7–15።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆ፤ በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የእርሱ ስምና የአባቱ ስም በግንባራቸው ላይ የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራቱ ሺሕ ሰዎች ነበሩ።” (ራእ. 14፡1)።

እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ሕዝብ የራእይ መጽሐፍ ምሳሌዎችን ለማስተዋል የሚረዱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ታሪኮችን ስንፈትሽ ኖረናል። ምንም እንኳ እነዚህ ታሪኮች ከብቸኛው መልካም ምንጭ የራቁ ቢሆኑም፣ ነገር ግን ሁሉም በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ይገኛሉ።

አብልጠው በመረጃ ከበለጸጉ ምንጮች መሃል አንዱ የሆነው የመዝሙር መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ በርካታ ሰብዓዊ ተሞክሮዎችን እና ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖሩ ስለሚችሉ ግንኙነቶች የሚዳስሱ ቅዱስ ይዘት ያላቸው የቅኔዎችና ሥነ ግጥም መድብሎችን አካቷል። በኃጢአት ላይ ተስፋ ከመቁረጥ እና ከስቃይ—በእርሱ ሐልዎት እስከሚገኝ ገደብ የለሽ ደስታ—ይቅር ስለመባል ብሎም የደኅንነት ባለቤት ስለመሆን በተደጋጋሚ የተሰጡ ተስፋዎች—የመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ አካል ሆነው እናገኛቸዋለን።

መዝሙረ ዳዊትን በጥንቃቄ ማንበብ የራእይ መጽሐፍ ሕያው እንዲሆን የሚያደርጉ ዝርዝሮችን ይሰጣል። በተለይ ራእይ 14 በምድር ላይ ያለችው ትሩፋኗ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን የምታከናውነውን የመጨረሻ ሥራ ይገልጻል።

የእግዚአብሔር የመጨረሻው ዘመን ሕዝብ እንደ ጥንት እስራኤላውያን ሁሉ ተመሳሳይ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። እኛ ለሕዝቦች ሁሉ ብርሃን መሆን ይጠበቅብናል።

ይህ ደግሞ ሰዎች ሁሉ ፈጣሪያቸውን ያመልኩና ይታዘዙ ዘንድ የመጨረሻው የምህረት ጥሪ ነው።

በአምላካዊው የመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች በምድር ታሪክ የመጨረሻዎቹ ጊዜያቶች ውስጥ ያለንን ድርሻ ለመረዳትና ተገቢውን ዋጋ ለመስጠት የሚያስችሉ አዳዲስ መንገዶች ይከፍቱልናል።

ግንቦት 10
May 18

ሊቀ ካህናችን


ሙሴ የማደሪያ ድንኳኑን የሥራ ሂደት ይቆጣጠር በነበረበት ወቅት እርሱ የፈለገውን ንድፍ ጥቅም ላይ ያውል ዘንድ አልተፈቀደለትም ነበር። እግዚአብሔር አምላክ ሊከተለው የሚገባውን ንድፍ ሰጠው። “ ‘በተራራው ላይ ባሳየሁህ ዕቅድ መሠረት መሥራትህን ልብ በል’ ” (ዘፀ. 25፡40)። ከዕብራውያን መጽሐፍ እንደምናነበው፣ ለመገናኛ ድንኳኑ ሥራ ጥቅም ላይ የዋለው ንድፍ ከፍ ያለውን እውነታ ማለትም ሰማያዊውን ቤተ መቅደስ መሰረት ያደረገ እንደሆነ እንገነዘባለን። ክርስቶስ በሰማያዊው መቅደስ ሊቀ ካህናችን መሆኑን አስመልክቶ የቀረቡትን እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዕብ. 9፡11-15። እርሱ ለእኛ እያደረገ ስላለው ነገር ምን ያስተምረናል?



ምድራዊው ቤተ መቅደስ ከካህኑና ከመሥዋዕቱ ጀምሮ እስከ ንዋየ ቅዱሳቱና ሌሎች የንድፍ ዝርዝሮች ድረስ በሚያስደንቅ ሁኔታ የየሱስ ማሳያ ጥላ ነበር። በዚያ የነበረው ሁሉም ነገር ስለ የሱስ ይናገር ነበር።

የራዕይ መጽሐፍ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይገኙ በነበሩ ምሳሌያዊ ገጽታዎች የተሞላ መሆኑ እሙን ነው። የመቅደሱን መቅረዝ በጥቅሶቹ መክፈቻ የምናገኝ ሲሆን፣ በምዕራፍ አራት ላይ በግልጽ የተጠቀሰውን የቃል ኪዳኑን ታቦት እንዲሁም ስለ ቤተ መቅደሱ የተነገሩ ሌሎች በርካታ ማጣቀሻዎችን እናገኛለን። ስለ ብሉይ ኪዳኑ ቤተ መቅደስ ተገቢው መረዳት ሳይኖር ዮሐንስ በራእይ የተመለከታቸውን፣ መነሾአቸውን ከዚያ ያደረጉትን መግለጫዎች ለማስተዋል መሞከር አዳጋች ይሆናል። ጳውሎስ የእስራኤልን ተሞክሮ አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡ “ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በእነርሱ ላይ ደረሰ፤ የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም ተጻፈ” (1ቆሮ. 10፡11)።

ከቤተ መቅደሱ ዝርዝር ጉዳዮች ጥናት ልንማራቸው የምንችላቸው በርካታ ነገሮች አሉ። በመጽሐፈ መዝሙር ከእነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹን ይኸውም የእግዚአብሔር ሕዝቦች በየግላቸው ከቤተ መቅደሱ ጋር እንዴት ትስስር እንደሚፈጥሩ ለመረዳት የሚያስችል ጠቃሚ ሐሳብ እናገኛለን። ዳዊት ከቤተ መቅደሱና ከአገልግሎቱ ጋር እንዴት ትስስር ፈጥሮ እንደነበር በውልብታም ቢሆን የምንመለከት ሲሆን፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች መሲሑ ለሚያደርግላቸው ነገር የሰጡትንም ልባዊ ምላሽ እናያለን። የሱስን እንድናየው የሚረዱን በምሳሌነት የቀረቡ ነገሮች ብቻ አይደሉም። ይልቁንም እግዚአብሔር በቤተ መቅደሱ አማካኝነት እያስተማረን ያለውን ትምህርት የተረዱ ወገኖችን የግል ተሞክሮ በመመርመር፣ ለራሳችንና ከእግዚአብሔር ጋር ለሚኖረን ተሞክሮ ትምህርት መቅሰም የምንችልበትን መንገድ መቀየስ እንችላለን።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 122። ምንም እንኳ ዛሬ ወደ ብሉይ ኪዳኑ “የእግዚአብሔር ቤት” መሄድ ባንችልም (አሁን ስለሌለ፤ ምናልባት በዚያው ቦታ ተመሳሳዩ ቢሠራ እንኳ ትርጉም የለሽ ይሆናል) በዚህ የመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ክፍል ክርስቶስ ለእኛ ስላደረገው ነገር ሊያበረታቱን የሚችሉ ምን ዓይነት ነገሮችን እናገኛለን? እዚህ ላይ በሰላም፣ በደኅንነት፣ በምስጋና እና በፍርድ ጭብጦች ዙሪያ የሚነሱ ሃሳቦችን ልብ ይሏል።

ግንቦት 11
May 19

በጽዮን ተራራ ላይ


በራእ. 14—የእግዚአብሔር ሕዝቦች በጽዮን ተራራ ላይ ቆመው እንመለከታለን። ቀደምቱ የጽዮን ተራራ የሚገኘው ከጥንታዊቷ የሩሳሌም ከተማ በስተ ምዕራብ በኩል ሲሆን፣ ስፍራው እንደ እግዚአብሔር ዙፋን መቀመጫ ወይም እርሱ በሕዝቡ መካከል የሚገኝበት ስፍራ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ከጊዜ በኋላ፣ የሞሪያ ተራራው መቅደስ እንደ ጽዮን ተራራ መታወቅ ጀመረ።

በሌላ አነጋገር ከሌሎች የራእይ መጽሐፍ እጅግ ቁልፍ ትዕይንቶች ጋር በመሆን፣ ይህ በቤተ መቅደሱ ቋንቋ የቀረበ ወሳኝ መግለጫ የእግዚአብሔርን የመጨረሻ ዘመን ትሩፋን ለማመላከት ጥቅም ላይ ውሏል። ለበጉ ምስጋና ይግባውና የእግዚአብሔር ሕዝቦች በተቀደሰ ተራራው ላይ ይገኛሉ! ዳዊት “በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?” (1962 ትርጉም) በማለት የሚያነሣውን ሁሌም ወሳኝ የሆነ ጥያቄ በመዝ. ምዕ. 15 እና 24 ይመልከቱ።

እርሱ የሰጠውን መልስ በራእ. 14፡1-5 በጽዮን ተራራ ላይ ከቆሙት ሕዝቦች መግለጫ ጋር ያስተያዩ። እንዴት ይመሳሰላሉ? የዚህ ስብስብ አካል መሆን የሚቻለው እንዴት ነው? የአብ ስም በግምባራቸው ላይ የመጻፉ አንደምታ ምንድን ነው? (ራእ. 14፡1)።





በእግዚአብሔር ሐልዎት ፊት መቅረብ እንዲሆንላቸው ፈቃድ ያገኙ ወገኖችን አስመልክቶ በመዝሙረ ዳዊት የቀረበው መግለጫ፣ ኃጢአተኞች ይፈጽሙት ዘንድ የሚጠበቅባቸውን በጣም ረጅም ትእዛዝ ይዟል። ሁሌም በንጽህና ተጉዘናል ብሎ ከመካከላችን በሐቅ መናገር የሚችል ሰው ማን ነው? ወይም ሰርክ እውነትን ከልባችን እንናገራለን የሚልስ? (መዝ. 15፡2)። ኃጢአት ሠርተን አናውቅም የምንል ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው በውስጣችን እውነት የለም (1ዮሐ. 1፡8)።

በጽዮን ተራራ ላይ እንድንቆም የሚያስችለን ከበጉ በቀር ሌላ ማንም የለም ከሚለው ውጪ የተለየ መደምደሚያ ላይ መድረስ አንችልም። በጉ በዳዊት መዝሙር ውስጥ ባይጠቀስም፣ በራእይ 14 ላይ በቀረበው መግለጫ ግን በድንገት ብቅ ሲል ይታያል።

በመሆኑም ራእ. 14 ለዳዊት ጥያቄ መልስ እየሰጠ ይመስላል። አሁን የእግዚአብሔር በግ በጽዮን ተራራ፣ በመቅደሱ መኖሪያውን ስላደረገ እነሆ እኛም በእምነት በተሰጠን ፍጹም በሆነው በእርሱ ጽድቅ በዚያ መገኘት እንችላለን። “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በኢየሱስ ደም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ድፍረት አግኝተናል፤ ይኸውም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል በከፈተልን አዲስና ሕያው መንገድ ነው” (ዕብ. 10፡19-20)። ያለ እርሱ ደም ሌላ ምን ተስፋ ይኖረን ነበር?—ምንም! በኃጢአት ላይ ድል መቀዳጀት እንደምንችል አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለተሰጡን የተስፋ ቃሎች አሰብ ያድርጉ። እነዚህ ሁሉ የተስፋ ቃሎች ተሰጥተውንም እንኳ፣ የሱስ ከተወልን ፍጹም ምሳሌ ሳንደርስ ተሰናክለን ራሳችንን የምናገኘው ለምን ይሆን? ፍጹም የሆነውን የእርሱን ሕይወት እንደ እኛ ምትክ መቁጠር የሚኖርብን ለምንድን ነው?

ግንቦት 12
May 20

ሕግ—በልባችን ውስጥ


በጽዮን ተራራ የተሰበሰቡት ትሩፋን በግንባሮቻቸው ላይ የተጻፈ ስም አለ— የአብ እና የበጉ ስም። በቅዱሳት መጻሕፍት "ስም" የሚለው ቃል ሰዎች እርስ በርስ ከሚጠራሩበት ባሻገር ባህሪንም ይወክላል። ዛሬም ድረስ በብዙ ባሕሎች በተለይም በአገራችን ኢትዮጵያ የአንዳንዶች መልካም ባሕሪ ከስማቸው ጋር ሲገጥም “ስምን መልአክ ያወጣል” ይባል የለ? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 33፡18-23፣ ዘፀ. 34፡1-7፣ መዝ. 119፡55። ሙሴ የእግዚአብሔርን ክብር ለማየት በጠየቀ ጊዜ እግዚአብሔር ምን አሳይሃለሁ ሲል ቃል ገባለት? እግዚአብሔር ስሙን በሙሴ ፊት ባወጀ ጊዜ (ዘፀ. 34፡5) ምን ተከተለ?





አንዳንዶች የእግዚአብሔርን ክብር የማይቀረብ፣ በብሩህና አንጸባረቂ ብርሃን የተሞላ አድርገው ይስሉታል፤ በእርግጥ ይህ ትክክለኛ መግለጫ ነው። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ክብር በዓይን ብቻ ከሚታየው ባሻገር ነው፤ የእርሱ ክብር ባህሪው ነው። ጉዳዩ የእግዚአብሔርንም ስም አስመልክቶ ተመሳሳይ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ስም በግንባራቸው ላይ እንደተጻፈባቸው አድርጎ ትሩፋኑን መግለጹ፣ ቃላቶቹ በግንባሮቻቸው ላይ በግልጽ ይነበባሉ ማለቱ አይደለም። ይልቁንም ጉዳዩ ያለው የእግዚአብሔር ባህሪ በአእምሮና በልባችን ውስጥ መቀረጹ ላይ ነው። ይህ ሲሆን በዚህ ምድራዊ ሕይወታችን የእግዚአብሔርን ፍቅር እና ባሕሪ እናንጸባርቃለን። በፍቅሩ ገመድ ተስበው ወደ እግዚአብሔር ሐልዎት በመቅረብዎ፣ ስለ እርሱነቱ እና ለእርስዎ ስላደረገው ነገር ይህን አምላክ ይወዱታል!

እግዚአብሔር ራሱን ለሙሴ ሲገልጽ፣ ሙሴ ሌላውን የአስርቱን ትእዛዛት ቅጂ ከመቀበሉ ጋር በማጣመር ማስኬዱ፣ አንዱ ትኩረት የሚስብ፣ ብሎም ልብ የሚያሞቅ የባሕሪው ግልባጭ ሆኖ እናገኛዋለን። በተመሳሳይ በራእ. 14 የእግዚአብሔርን “ስም” የያዙ ወገኖች፣ “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁ” ተብለው ተገልጸዋል። አሁን ደግሞ በዕብራውያን መጽሐፍ የቀረቡትን እነዚህን ቃላት እንመለከት፡ “ ‘ከዚያም በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤ በአእምሯቸውም እጽፈዋለሁ።’ ደግሞም፣ ‘ኀጢአታቸውንና ዐመፃቸውን፣ ከእንግዲህ አላስብም’ ” (ዕብ. 10፡16- 17)። ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ሕግ በሕይወታችን ውስጥ ቢንጸባረቅም፣ ኃጢአታችሁን “ከእንግዲህ አላስብም” በተሰኘው አገላለጽ ወንጌል እንዴት ውብ ሆኖ ቀርቧል!

የእግዚአብሔር ስም መገለጫ ባህሪው ነው። አስርቱ ትእዛዛት የባሕሪው ግልባጭ ናቸው። እናም በመጨረሻዎቹ ቀናት በእግዚአብሔር ቅዱስ ኮረብታ ላይ የሚሰበሰቡ—ሕጉን በመታዘዝ በሚገለጥ ይኸውም ለእርሱ ባላቸው ፍቅር የተሞሉ ናቸው። የዳንነው ሕጉን በመጠበቅ ሳይሆን በእምነት ከሆነ ዘንዳ፣ የአምላካዊው ሕግ አስፈላጊነት ፋይዳው ምንድን ነው? (1ዮሐ. 5፡3)።

ግንቦት 13
May 21

መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 5


መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ አምስትን ያንብቡ። ባለ መዝሙሩ ዳዊት በዚህ መልእክቱ በጠፉት እና በተዋጁት መካከል ያለውን ልዩነት አሳይቷል። ይህን ክፍል ራእይ 14፡ 1-12 ከቀረበበት ቋንቋ ጋር ያስተያዩ። በመካከላቸው ያሉ መመሳሰሎች ምን ይመስላሉ? እነዚህ መመሳሰሎች የእግዚአብሔር የመጨረሻው ዘመን ትሩፋን አካል ስለ መሆን ባሎት ግንዛቤ ላይ እንዴት ተጨማሪ መረጃ ያስጨብጦታል?



ዳዊት ክፉ “ከአንተ ጋር አያድርም” (መዝ. 5፡4) በማለት አበክሮ መናገሩን ማጤን ተገቢ ነው። የማደሪያው ድንኳን አንደምታ የእግዚአብሔርን በሕዝቡ መካከል ማደር እውን ማድረግ እንደሆነ ሁሉ፣ በክርስቶስ መንግሥትም እንዲሁ ይሆናል (ራእ. 21፡3)። ወደ እግዚአብሔር ዙፋን የሚቀርቡ ሁሉ የተዋጁ መሆን ይኖርባቸዋል።

በተጨማሪም ዳዊት በመዝ. 5፡7 ላይ የታላቁ ተጋድሎ ወሳኝ ጉዳይ የሆነውን አምልኮ የገለጸበት መንገድ የሚደንቅ ነው። በራእ. 13 “አምልኮ” ወይም “ስግደት” ስድስት ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በሦስቱ መላእክት መልእክት ለፈጣሪ “ስገዱ” የሚል ጥሪ ለዓለም ቀርቧል። ዳዊት “አንተን በመፍራት” በፊትህ እሰግዳለሁ ሲል እንደነገረን ሁሉ፣ ትሩፋኑ ለዓለም የሚያቀርቡትም ጥሪ፡ “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሷል” (ራእ. 14፡7) የሚል ነው።

በተጨማሪ የራእ. 14 የተዋጁ ወገኖች፣ በአፋቸው ምንም ዓይነት “ውሸት”(ራእ. 14፡5) አልተገኘም መባላቸውን ልብ ይሏል። እነዚህ ወገኖች ንግግራቸውም ሆነ ተግባራቸው የእግዚአብሔርን ጻድቅ ባሕሪ የሚያንጸባርቅ— እውነትና እውነት ብቻ ተናጋሪዎች ናቸው። ክፉዎች ግን፣ ዳዊት እንደተናገረው፡ “በንግግራቸው ውስጥ እውነት የለም” (መዝ. 5፡9)።

ዮሐንስ በዚህ የራእይ ቁልፍ ክፍል የገለጸው አስደናቂ የሆነ ትዕይንት ነው፡ ኃጢአተኞች ከሞት ወደ ሕይወት በመምጣት በእግዚአብሔር ፊት የመቆም የልዩ መብትና ጥቅም ተጋሪ ሆነዋል። ይህን መብት የተቀዳጁት በራሳቸው ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር በግ የሆነው ጻድቁ የሰው ልጅ ከእነርሱ ጋር በመቆሙ ነው። ይቅር ተብለዋል፣ ተዋጅተዋልም። በመሆኑም፣ ከዚህ በኋላ የገዛ በደላቸውን መሸከም የለባቸውም (መዝ. 5፡10)። ምክንያቱም የእግዚአብሔር በግ የእነርሱን በደል ተሸክሞላቸዋልና (ኢሳ. 53፡12፣ 2ቆሮ. 5፡21)።

የእግዚአብሔር ስም አንዴ በልብዎ ማኅደር ከተጻፈ በኋላ እውነትን ሳያጋሩ ዝም ብሎ መቅረት—ከባድ ነው! የእግዚአብሔር ሕዝቦች የመጨረሻውን የምሕረት ግብዣ “በታላቅ ድምፅ” (ራእ. 14፡7) ያቀርባሉ። “አንተን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ግን ደስ ይበላቸው፤ ዘላለም በደስታ ይዘምሩ፤ ስምህን የሚወድዱ በአንተ ደስ እንዲላቸው፣ ተከላካይ ሁንላቸው” (መዝ. 5፡11)። እርስዎ ቅዱስ እና ፍጹም በሆነው አምላክ ፊት ለፍርድ ቆመው ያደረጓቸው ቅንነት የጎደላቸው ተግባራት አንድም ሳይቀሩ በገሃድ በፈጣሪ ፊት የሚቀርብበትን ትዕይነት በዓይነ ሕሊናዎ ይመልከቱ። ይህ ምናባዊ ሥዕል ስለ ክርስቶስ ጽድቅ አስፈላጊነት ምን ያህል ይነግሮታል?

ግንቦት 14
May 22

ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራቸው


በኢሳ. 6፡ 1–8 እንደተጻፈው፣ ጌታ በዙፋኑ ክፍል ውስጥ ለኢሳይያስ ከተገለጠለትና ኢሳይያስ “በደልህ ተወግዶልሃል፤ ኀጢአትህም ተሰርዮልሃል” ተብሎ ከተነገረው በኋላ ነቢዩ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” (ኢሳ. 6፡8) ሲል ይደመጣል። ይህ ማለት በእግዚአብሔር ፊት በጽድቅ መቆሙን አንዴ ከተገነዘበና ከተረዳ በኋላ፣ እንከኖች እንዳሉበት ቢያውቅም፣ ለጌታ ለመሥራት ግን ዝግጁ ነበር።

የእኛስ ጉዳይ ከዚህ ጋር አንድ አይደለምን? እኛ ራሳችን የደኅንነት ባለቤት ሳንሆን እንዴት ለሌሎች ማወጅ እንችላለን? በየሱስ በማመን እና እርሱ ለእኛ ባደረገው ነገር የደኅንነት ባለቤት መሆን እንችላለን። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 51፡7-15። ዳዊት ይቅር ከተባለና ከኃጢአቱ ከነጻ በኋላ ምን ለማድረግ ቃል ገባ?



ወደ እግዚአብሔር ሐልዎት መጠራት ማለት ወደ ሌሎች ለመድረስ መላክ ነው። እግዚአብሔር በጥበቡ የተዋጁቱ ለወደቀው ዓለም የእርሱ ተቀዳሚ ድምፆች ሆነው ያገለግሉ ዘንድ ተልዕኮ ሰጥቷቸዋል። በምድር ያሉ ሕዝቦቹ ተጽእኖ ብርቱ ኃይል ዙሪያ ገባውን የሚሰማ ይሆናል። እርሱ ለወደቀችው ዓለም የሚያቀርበው የመጨረሻ ተማጽኖአዊ ጥሪ መላውን ዓለም በብርሃን የሚሞላ ይሆናል።

“አንድ ሰው ወደ ክርስቶስ ከመጣ በኋላ፣ ውሎም ሳያድር በየሱስ ያገኘውን የከበረ ወዳጅ ለሌሎች የማሳወቅ ብርቱ ምኞት በልቡ ጓዳ ይጠነሰሳል።

የሚያድነውና የሚቀደሰው እውነት በልቡ ውስጥ ዝም ብሎ መቀመጥ አይችልም። የክርስቶስን ጽድቅ ለብሰን በእኛ ውስጥ በሚኖረው በመንፈሱ ደስታ ከተሞላን፣ በውስጣችን ያለውን ሰላም ለራሳችን ብቻ ይዘን መቀመጥ አይሆንልንም። የጌታን መልካምነት አንዴ ከቀመስንና ካየን፣ የምንናገረው ነገር ይኖረናል። ፊልጶስ አዳኙን ሲያገኝ እንዳደረገው ሁሉ፣ እኛም ሌሎችን ወደ እርሱ መገኘት እንጋብዛለን።”— Ellen G. White, Steps to Christ, p. 78

በራአ. 14 የቀረቡት የሦስቱ መላእክት መልእክቶች የተመሰረቱት በ “ዘላለማዊው ወንጌል” (ራእ. 14፡6) ላይ ነው። ይህ ማለት “ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው” (ራእ. 14፡7) መስገድ እንደሚገባ ከመታወጁ አስቀድሞ ወይም ስለ ባቢሎን መውደቅ (ራእ. 14፡8) አልያም “ለአውሬው እና ለምስሉ” (ራእ. 14፡9) ስለ መስገድ ከመነገሩ በፊት— የወንጌል መሰረት የሆነው በየሱስ መዳን ታውጇል። ለዚህ መንስኤው እነዚህን መልእክቶች የሚያውጁ ወገኖች የሱስ ከሰጣቸው ተስፋና ቃል ኪዳን እንዲሁም በእርሱ ከተደረገላቸው ነገር ውጪ—የሦስቱ መላእክት ማስጠንቀቂያዎችና መልእክቶች ምንም ትርጉም ስለሌላቸው ነው። ከ “ዘላለማዊው ወንጌል” ሌላ ለዓለም የምንናገረው አንዳችም ዋጋ ያለው ነገር አይኖረንም። የሦስቱ መላእክት መልእክቶች መታወጅ ከመጀመራቸው በፊትም እንኳ፣ ወደ “ዘላለማዊው ወንጌል” የተመላከትን በመሆናችን ጭብጥ ዙሪያ ምልከታ ያድርጉ። ይህ እውነት ለእኛ ለምናምን ሁሉ መሰረታዊ መሆኑን አስመልክቶ ይህ ምን ሊነግረን ይገባል?

ግንቦት 15
May 23


ተጨማሪ ሀሳብ


“የዳዊት መዝሙር ሰዎች እያወቁ ከሚፈጽሙት ጥልቅ በደል አንስቶ እራስን እስከ መውቀስና ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እስከሚያስችል ግዙፍ እምነት ድረስ ያለውን አጠቃላይ የሕይወት ተሞክሮ ይዳስሳል።

ኃጢአት ሐፍረትና መከራ ብቻ እንደሚያመጣ የዳዊት ሕይወት ታሪክ ይነግረናል። እጅግ ጥልቅ የሆነው የእግዚአብሔር ፍቅርና ምህረት ግን የተጸጸተችውን ነፍስ ቀና በማድረግ የእግዚአብሔር ልጅነትን ማእረግ ያጎናጽፋታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከቀረቡት ጠንካራ አምላካዊ ማረጋገጫዎች አንዱ የሆነው ይህ ክፍል በታማኝነት፣ በፍትሕና በአምላካዊው ምህረት ኪዳን ዙሪያ ምስክርነቶችን ይዞአል።

“ለባርያዬ ለዳዊት ምያለሁ… እጄ ይደግፈዋል፣ ክንዴም ያበረታዋል… ታማኝነቴና ምህረቴ ከእርሱ ጋር ይሆናል፤ በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል። እጁን በባህር ላይ፣ ቀኝ እጁንም በወንዞች ላይ አኖራለሁ። እርሱም ‘አንተ አባቴ ነህ፣ አምላኬና መዳኛ ዐለቴም ነህ’ ብሎ ይጠራኛል። እኔም ደግሞ በኩሬ አደርገዋለሁ፤ ከምድር ነገሥታትም በላይ ከፍ ይላል። ምህረቴንም ለዘላለም ለእርሱ እጠብቃለሁ፤ ከእርሱ ጋር የገባሁት ኪዳንም ጸንቶ ይኖራል” (መዝ. 89፡ 3-28)።

(የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት ቅጽ 2 ገጽ )


የመወያያ ጥያቄዎች




1. እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እስከ ፍጻሜ ጠብቆ በመጓዝ ረገድ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እስከ ፍጻሜ ጠብቆ በመጓዝ ረገድ ሰብዓዊው ዘር አሳዛኝ ውድቀት አስተናግዷል። ለእግዚአብሔር “እንደ ልቡ የሚሆንለት ሰው” ተብሎ የተጠራው ዳዊት፣ ከባባድ ስህተቶችን ቢሠራም እንኳ፣ የመዳናችንን ጉዳዮች ለእኛ ለማስተላለፍ በብርቱ ተጠቅሞበታል። የእግዚአብሔርን ኪዳን ስለ እኛ ፍጹም በሆነ መንገድ የጠበቀውን የሱስ— ዳዊት ጥላ በመሆን ያሳየው በምን መልኩ ነበር? የሱስ ለእኛ ሲል ያደረገው ነገር ብቸኛው ተስፋችን የሆነው ለምንድን ነው?

2. በመዝሙረ ዳዊት መልእክቶች፣ እርስዎ በግል ያለፉባቸውን ተሞክሮዎች በመዝሙረ ዳዊት መልእክቶች፣ እርስዎ በግል ያለፉባቸውን ተሞክሮዎች የሚያንጸባርቁ ጠቃሚ ወይም ትርጉም አዘል ምን ነገሮችን አግኝተዋል?

3. የመዝሙር መጽሐፍ ስለ ቤተ መቅደሱ በተደጋጋሚ የሚጠቅሰው ለምንድን የመዝሙር መጽሐፍ ስለ ቤተ መቅደሱ በተደጋጋሚ የሚጠቅሰው ለምንድን ነው? ዳዊት ለቤተ መቅደሱ ካለው ፍቅር ምን እንማራለን? ሰማያዊው ሊቀ ካኅናችን “በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ” እየሰጠ ስላለው “ምልጃ” (ሮሜ 8፡34) ማመስገንና ማድነቅ እንድንችል እንዴት ይረዳናል? እንደ ተዋጀ ሕዝብም እንኳ፣ የክርስቶስ ሰማያዊ ምልጃ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

4. ከላይ በተጠቀሰው ኤለን ጂ ዋይት መልእከት መሰረት፡ “የተጸጸተችውን ከላይ በተጠቀሰው ኤለን ጂ ዋይት መልእከት መሰረት፡ “የተጸጸተችውን ነፍስ ቀና በማድረግ የእግዚአብሔር ልጅነትን ማእረግ ያጎናጽፋታል” በሚለው አነጋገር ዙሪያ “ኃጢአት ሐፍረትና መከራ ብቻ ከማምጣቱ” አኳያ የእርስዎ የግል ተሞክሮ ምን ይመስላል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL