የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ፍንጮች፣ ምስሎች፣ ምሳሌዎች፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ማጥኛ መንገድ



2ኛ ሩብ ዓመት 2025


ግንቦት 2 - 8

7ኛ ትምህርት

May 10 - 16




ለትንቢት መሠረቶች



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 6:6–8፣ ዘፍ. 3:21–24፣ ሕዝ. 1:4–14፣ ራእ. 4:1–11፣ ዘኁ. 2:3–25፣ ኢሳ. 14:12–14።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ከዚያም የጌታ ድምፅ፣ ‘ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?’ ሲል ሰማሁት። እኔም፣ ‘እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ’ አልሁ።” ኢሳ. 6፡8)።

እግዚአብሔር የሁሉም ፈጣሪ የመሆኑ መሠረት፣ በዩኒቨርስ ላይ ሥልጣን እንዲኖረውና ጽንፈ ዓለምን እንዲገዛ ባለ መብት አድርጎታል (ራእ. 4፡ 11)። የእግዚአብሔርን ጻድቅ ባህሪ መረዳት ስንችል፣ በኃጢአት የወደቁ ሰብዓዊ ፍጡራን ከእግዚአብሔር ክብር እንዴት እና ለምን በአጭር እንደሚስተጓጎሎ ማስተዋል እንጀምራለን (ሮሜ 3፡23)።

በዚህ ሳምንት ወደ አምላካዊው ዙፋን ቅጥር ራእይ ይበልጥ ቀረብ ብለን፣ ሰብዓዊው ዘር እንዴት ቅዱስ ከሆነው አምላክ ጋር እንደሚዛመድ፣ የክርስቶስ መሥዋዕት እንዴት አድርጎ ወደ ቀደመው ንጽህና እንደሚመልሰንና ወደ ዙፋኑ እንደሚያቀርበን እንመለከታለን። የእግዚአብሔር እቅድ እኛን እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በአጠቃላይ እንደ ሰብዓዊ ዘር ወደ ቀደመው ንጽህና መመለስ ሲሆን፣ ይኸውም ዳግም የእርሱን ክብር ለተቀረው ፍጥረት እንገልጥ ዘንድ ነው።

እግዚአብሔር ለእኛ ይቅር ለተባልነው እና ለተዋጀነው ኃጢአተኞች ያቀረበውን ከፍ ያለ ጥሪ ማስተዋልና ማድነቅ እንድንጀምር የሚያስችሉንን ጠቃሚ ፍንጮች፣ የተቀረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በመመርመር ማግኘት እንችላለን።

ሰብዓዊ ዐመጽ ውሎ አድሮ እነሆ ለዘላለም ያከትማል። ሆኖም ከዚያ በላይ— የእግዚአብሔር አፍቃሪ፣ ራስን የካደና መሥዋዕት ያደረገ ባህሪው፣ ለሰብዓዊው ፍጡር ከነበረው የቀደመ ንድፍ የበለጠ ደማቅ ብሎም አንጸባራቂ ይሆናል። ምንም እንኳ የሰው ልጆች ይወድቁ ዘንድ የእግዚአብሔር እቅድ ሆኖ ባያውቅም፣ በመስቀሉ አማካይነት የእግዚአብሔር የፍቅር ባህሪ አስገራሚ ሆኖ ተገለጠ!

ግንቦት 3
May 11

እነሆ እኔን ላከኝ


ከዓመታት በፊት አንድ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞ የነበረውን አሮጌና ጊዜው ያለፈበትን ምድር ቤት በአዲስ ለማደስ ወሰነ። በመጀመሪያ ካደረጓቸው ነገሮች አንዱ የአምልኮ ስፍራውን ይበልጥ ያስውባል ብለው ያመኑበትን አዲዲስ መብራቶች መግጠም ነበር። ይሁን እንጂ መብራቶቹ አንዴ ከተገጠሙ በኋላ፣ መሰብሰቢያ ስፍራው ይበልጥ የከፋ መልክ የያዘ መሰለ። ለዚህ መንስዔው ደማቆቹ መብራቶች እንከኖችን ልቅም አድርገው ማሳየታቸው ነበር።

ኢሳይያስ ስለ እግዚአብሔር ዙፋን የተመለከተው አስደናቂ ራእይ የነበሩትን እንከኖች በሐዘን እንዲገነዘብ አስችሎታል። “እኔም፣‘ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ነኝ፤ የምኖረውም ከንፈሮቹ በረከሱበት ሕዝብ መካከል ነው፤ ዐይኖቼም ንጉሡን፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አይተዋልና ጠፍቻለሁ፣ ወዮልኝ!’ አልሁ።” (ኢሳ፣ 6፡5)። እኛም በድንገት ወደ ጌታ ሐልዎት ብንወሰድ ተመሳሳይ ስሜት መጋራታችን አይቀሬ ነው። የብርሃኑ ነጸብራቅ ሁሉንም ሰበቦች ለማስወገድ በቂ ነው። በእግዚአብሔር ሐልዎት ፊት ስንቀርብ እንደጠፋን ሆኖ ይሰማናል። ኢሳይያስ የገጠመው በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ይሆናል ብሎ ያልጠበቀው ነገር ነበር። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 6፡6-8። ኢሳይያስ ኃጢአት ማለት “መጥፋት” እንደሆነ ያውቅ ነበር። የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው። ነገር ግን እኛን ለኃጢአት መዘዝ ከመተው ይልቅ፣ የፍቅር አምላክ ወደ ራሱ ይስበናል። የዚህ (የኢሳይያስና የእግዚአብሔር) መገናኘት ውጤቱ ምን ነበር? ለምንስ አስፈላጊ ሆነ?



ከዚያም ከሱራፌል አንዱ ከመሠዊያው ላይ የእሳት ፍም በጕጠት ወስዶ አፉን በእሳቱ ነካው። ይህ ስለ እግዚአብሔር ሕዝቦች ምልጃ የሚቀርብበት የዕጣኑ መሠዊያ (ራእ. 8፡3-4) ሳይሆን አይቀርም። አሁን ኃጢአቱ ይቅር ስለተባለ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም ብቁ ሆኖ ተቆጥሯል። ሆኖም ከዚያ በላይ ግን እግዚአብሔርን በዓለም ላይ እንዲወክል ተልዕኮ ተሰጥቶት ነበር።

“ሱራፌል” የሚለው ቃል “የሚነደው” የሚል ትርጉም ያለው መሆኑ ትኩረታችንን ይስበዋል። እዚህ ላይ የሱስ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት የተናገረውን ልብ ማለት ተገቢ ነው፡ “ዮሐንስ እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በብርሃኑ ደስ ልትሰኙ ወደዳችሁ” (ዮሐ. 5፡35)።

እርግጥ ነው፣ ዮሐንስ ራሱ ጸጋና ድነት የሚያስፈልገው ኃጢአተኛ ቢሆንም፣ አገልግሎቱ ጸጋ እና ድነትን በብቸኝነት ሊያመጣ ወደሚችለው ወደ እርሱ (የሱስ) የጠቆመ ነበር።

የሱስ የአብን ክብር ፍጹም አድርጎ በመወከል የመጣ ሲሆን፣ እግዚአብሔርም ልክ እንደ ሰማያዊው ሱራፌል ሁሉ፣ ተመሳሳይ ኃላፊነትን ለኃጢአተኛው ነቢይ ሰጥቶ ላከው። ኢሳይያስ ከኃጢአቱ እንደነጻ ካወቀ በኋላ ነበር—እነሆ እኔን ላክ ያለው።

ከኃጢአታችን በየሱስ ደም የነጻን እኛ እያንዳንዳችን እንዴት እንደ ኢሳይያስ ምላሽ መስጠት እንችላለን?

ግንቦት 4
May 12

ሁለቱ ኪሩቤሎች


የቀደሙት ወላጆቻችን ከኤደን የአትክልት ስፍራ እንደተባረሩ እግዚአብሔር የመሲሑን ተስፋ ሰጠ (ዘፍ. 3፡15)። ከዚያም በገነት ደጆች ግዙፍ ምሳሌ አቆመ፡ ሁለቱን ኪሩቤል እና በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሠይፍ። ይህ ትዕይንት የእግዚአብሔር የዙፋኑ ምልክት ከሆነው የቃል ኪዳኑ ታቦት (ዘፀ. 25፡ 18) ጋር በቅርብ የሚመሳሰል መሆኑ ሊሰወርብን አይገባም። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡21-24። ለኪሩቤል የተሰጠው የሥራ ኃላፊነት ምን ነበር -ለምን?



ኃጢአተኞች ወደ ሕይወት ዛፍ እንዳይደርሱ የመጠበቅ ኃላፊነት ለኪሩቤል መሰጠቱ እርግጥ ቢሆንም (ዘፍ. 3፡22)፣ አንድ ቀን፣ ሰብዓዊ ፍጡራን አጥተውት ወደ ነበረው የኤደን ገነት እንደሚመለሱ የሚያመላክት ተስፋና ቃል ኪዳንም ጭምር ነበር። “ሰብዓዊው ፍጡር አስደሳች ከሆነው የዔደን ገነት ከተባረረ በኋላ በምድር ላይ ለረጅም ጊዜ ይታይ ነበር። የመግቢያ በሩ በመላእክት የተጠበቀ ነበር። ወደ ህይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ እግዚአብሔር ኪሩቤልንና በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሰይፍ አኖረ። በዚያ መለኮታዊው ክብር ተገልጦ ይታይ ነበር። አዳም እና ልጆቹ እግዚአብሔርን ለማምለክ ወደዚህ ስፍራ በመቅረብ በመተላለፋቸው ምክንያት አሁን በዐይን ብቻ ከሚያዩት ዔደን ገነት ያስወጣቸውን ሕግ ለመጠበቅ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ገቡ። ኋላ ላይ የምግባረ ብልሹነት ማዕበል ዓለምን ሲመታና የሰዎች በጥፋት ውሃ መውደም ሲወሰን ዔደን ገነትን ያስቀመጠው አምላክ ከምድር ላይ አነሣው። ነገር ግን በመጨረሻው ቀን “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” (ራዕይ 21፡1) ሲገለጥ፤ መጀመሪያ ከነበረው ሞገስ በላይ እጥፍ ድርብ ሞገስ ይዞ ዳግመኛ ይመጣል።” (የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት ገጽ 57-58)።

በዘፍጥረት 3፡24 ላይ የሚስተዋለው የቃላት አገባብም እንዲሁ ትኩረትን የሚስብ ነው፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ኪሩቤልን ከኤደን በስተ ምሥራቅ “አኖረው” ሲል የሚያመለክት ሲሆን፣ በቀደመው የዕብራይስጥ ቃል ሻካን፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል የሚያድርበት የቅዱሱ “ማደሪያ ድንኳን” ሥርወ ቃል ነው (ዘፀ. 25፡9፣ ዘኁ. 3፡26)። ምንም እንኳ የእግዚአብሔርን መገኘት የሚያመለክተው ሸኪናህ የተሰኘው የተለመደ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም፣ ይኽም ቃል ብዙውን ጊዜ "የማደሪያ ድንኳን" ተብሎ በተተረጎመው በዚሁ ቃል ላይ የተመሠረተ ነው። ሻካን ቃል በቃል ሲተረጎም፡ “እግዚአብሔር ከዔደን ገነት በስተ ምሥራቅ በመገናኛ ድንኳኑ ኪሩቤልን አኖረ” የሚለውን ፍቺ ይሰጣል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ኪሩቤል ከእግዚአብሔር ሐልዎት ጋር የተያያዘ ነው— በተለይም ስሙ በሚታወጅበት ዙፋኑ ባለበት ስፍራ (1ዜና፡ 13፡6፣ መዝ. 80፡ 1፣ ኢሳ. 37፡16)። በራእ. 4 እና 5 በእግዚአብሔር ዙፋን ቅጥር ሆነው ለእርሱ የምስጋና መዝሙር እያቀረቡና ሁሉን የፈጠረ አምላክ እርሱ ይገዛ ዘንድ ባለ መብት መሆኑን የሚያውጁትን ሃያ አራቱን ሽማግሌዎች መዘንጋት የለብንም (ራእ. 4፡11)። ይህ የዙፋን ክፍል ትዕይንት እና ይቅር እንደተባሉ ኃጢአተኞች ከፈጣሪያችን ጋር ሊኖረን ስለሚገባን የግንኙነት ሚና እንድናስተውል ይረዳናል።

ግንቦት 5
May 13

እንደሚነድ የከሰል ፍም


ኪሩቤል እንደ ሕያዋን ፍጥረታት (ሕዝ. 10፡8) ወይም እነርሱን እንደሚወክሉ የወርቅ ምሳሌዎች (ዘፀ. 25፡18) ሆነው በመላው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ይታያሉ። ብዙውን ጊዜ ከእግዚአብሔር ዙፋን አጠገብ እንደሚገኙና የእርሱን ክብር ለዩኒቨርስ እንደሚያንጸባርቁ ሆነው ተገልጸዋል። እንዲሁም የኪሩቤል ምስል ከቅድስተ ቅዱሳኑ በፊት ባለው በመጋረጃው ላይ ተጠልፏል (ዘፀ. 26፡ 1)። በፍጥረት ላይ ሉዐላዊ የሆነው የእግዚአብሔር ኃይል በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ እንደ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ እንደ መጠቀ አምላክ ሆኖ በመዝሙረ ዳዊት ቀርቧል። በስርየት መክደኛው ዳርና ዳር ላይ ከወርቅ የተቀረጹ ሁለት ኪሩቤል እንዲሠሩና ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ዘርግተው እርስ በርሳቸው ትይዩ እንዲሆኑ እግዚአብሔር አዝዞ ነበር (ዘፀ. 25፡18-20)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሕዝ. 1፡4-14። በእነዚህ ጥቅሶች እና—ኢሳ. 6፡1-6፣ ራእ. 4፡1-11 ጥቅሶችና ትዕይንቶች ጋር ምን ተመሳሳይነት ያገኛሉ?



ሕዝቅኤል የእግዚአብሔርን ኃይል አስደናቂ በሆነ መንገድ አሳይቷል።

ሆኖም የተመረጠው ሕዝብ በተስፋይቱ ምድር ሳይሆን በባቢሎናውያን ምርኮ ሥር ከመገኘቱ አኳያ—ትዕይንቱ በወቅቱ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይኖሩ ከነበረበት አስቸጋሪ ሁኔታ ጋር የማይጣጣምና ግራ የሚያጋባ ዓይነት ነበር። ሕዝቅኤል በፊቱ የቀረበውን ትዕይነት እያጠና እያለ፣ ቀና ሲል ከፍ ብሎ የተሰየመውን የእግዚአብሔር ዙፋን ተመለከተ።

ከሌሎች የ “ዙፋኑ” ራእዮች ጋር ያለውን ወሳኝ መመሳሰል ልብ ብለው ያጢኑ። ሕዝቅኤል የተመለከተው የሕያዋን ፍጡር ገጽታ ዮሐንስ በራእይ ከተመለከተው፡ የአንበሳ፣ የንስር፣ የበሬ እና የሰው ምስል ጋር ተመሳሳይ ነው።

አራት መልክ ያላቸው ምስጢራዊ ፍጡራን በሕዝቅኤል የመጀመሪያ መግለጫ ላይ በቀጥታ አልተሰየሙም። ኋላ ላይ ግን በሌላኛው የዙፋን ክፍል ትዕይንት (ሕዝ. 10፥1–21)፣ “ኪሩቤል” ተብለው ተጠርተዋል። እንዲሁም ኢሳይያስ ስለ ሱራፌል ባየው ራእይ—የሚነድ የከሰል ፍም እናገኛለን።

እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር ይገናኝበት በነበረው በምሳሌያዊው የቃል ኪዳኑ ታቦት (ዘፀ. 25፡22) ወይም በአስደናቂዎቹ የነቢያቱ ራእይ የእግዚአብሔርን ዙፋን ባየን ቁጥር ኬሩቤል ሁሌም በዚያ አሉ። ከእግዚአብሔር ዙፋን ጋር በቅርበት የተሳሰሩ ናቸው። በእርሱ አምሳል ስለተሠራው ሰብዓዊው ዘር ወይም በአንጸባራቂ ክብር ከተሞላው ዙፋኑ አጠገብ ስለሚገኙ መላእክት ብናወራ—ሁሉም የእግዚአብሔር ፍጥረታት የእርሱን ክብር እንዲያንጸባርቁ ሆነው ነው የተነደፉት። ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ። ሕዝቅኤል በዚህ ስፍራ በሰጠው የቅድስና ምስክርነት፣ መልካምነቱን እንዴት ያነጻጽሩታል? ወንጌል ለእርስዎ ወሳኝ ስለመሆኑ መልስዎ ምን ይነግሮታል?

ግንቦት 6
May 14

እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር


እግዚአብሔር በደና ዐምድ ተገልጦ ለእስራኤላውያን ይሰጥ የነበረውን ምሪት ተከትሎ፣ በመሃል ወደ ተስፋይቱ ምድር ያደርጉ የነበረውን ጉዞ ገታ ያደርጉና ከምስክሩ ድንኳን ትይዩ ዙሪያውን ጥቂት ራቅ ብለው—በአንድ በኩል ሦስት ነገዶች እየሆኑ በየነገዱ ምልክት ስር ይሰፍሩ ነበር። የእግዚአብሔር ሐልዎት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይወርድና በሕዝቡ መካከል ያድራል። የምስክሩ ድንኳን ካረፈበት ከአራቱም አቅጣጫዎች ከሌሎቹ ልቀው የሚታዩ ነገዶች ነበሩ። በዘኁ. ምዕ. 2 ዘገባ መሰረት እነዚህ አራት ነገዶች እነማን ነበሩ? ዘኁ. 2:3 (ምሥራቅ):



ዘኁ. 2:10 (ደቡብ):



ዘኁ. 2:18 (ምዕራብ):



ዘኁ. 2:25 (ሰሜን):



ከእነዚህ ከሌሎቹ ልቀው ይታዩ የነበሩ አራት ነገዶች እያንዳንዳቸው ማንነታቸውን የሚገልጽ የየራሳቸውን ምድብ “ዐርማ” ያውለበልቡ ነበር።

ቅዱሳን መጻሕፍት በእነዚህ በእያንዳዳቸው ዐርማዎች ላይ የነበረውን ነገር በግልጽ ባያስቀምጡም፣ በዘፍጥረት 49 እና ዘዳግም 33 ላይ የተገለጹት ነገዶች ባሕርያት፣ እነዚህን በአራቱም አቅጣጫዎች ያሉ ምድቦች—የእያንዳንዳቸውን ምስል በገደምዳሜ ማመላከታቸው ትኩረት የሚስብ ልማድ ሆኖ እናገኘዋለን።

“በአይሁድ ወግና ልማድ መሰረት የይሁዳ ነገድ ምልክት የአንበሳ ምስል፣ የሮቤል ነገድ የሰው ምስል ወይም የሰው ራስ፣ የኤፍሬም የበሬ ምስል፣ የዳን ደግሞ የንስር ናቸው። ይህን ተከትሎ በሕዝቅኤል በተገለጹት ኪሩቤል ቅርጽ ሕብረት ፈጥረው የቀረቡት አራቱ ሕያዋን ፍጡሮች በእነዚህ አራት ምድቦች ተወክለዋል።”— Carl Friedrich Keil and Franz Delitzsch, Commentary on the Old Testament, vol. 1 (Peabody, MA: Hendrickson, 2011), p. 660.

ስለ ወግና ልማድ የተጻፉ መልእክቶችን እያነበቡ ብዙ ዘልቆ መሄድ የሚቻል ቢሆንም፣ ነገር ግን ይህን ጥንታዊ ወግ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አዲሲቷ የሩሳሌም ከሚሰጠው መግለጫ አኳያ ማወዳደር፣ ጉዳዩ ትኩረት እንዲስብ ያደርገዋል። በዚህ መሃል አንድ ልብ የሚያሞቅ ምስል ከፊት ለፊት ድቅን ይላል—በአራቱም የከተማዋ አቅጣጫዎች ሦስት፣ ሦስት ነገዶችን የሚወክሉ በራፎች መኖራቸው ነው (ራእ. 21፡12-13)።

ስለ እስራኤል አሰፋፈር እና ስለ አዲሲቱ የሩሳሌም የቀረቡት ሁለቱም መግለጫዎች ለአንድ ወሳኝ እውነት አጽንኦት ይሰጣሉ፡ እግዚአብሔር ሰብዓዊውን ዘር ወደ ዙፋኑ ለመሳብ ፈቃዱ ስለመሆኑ! የራእይ መጽሐፍ እንደሚያስተምረን፡ “ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክና በጉ መቅደሷ” ናቸው (ራእ. 21፡22)። እርግጥ ነው በእስራኤል ሰፈር ውስጥ እየኖርን አይደለም። ሆኖም ዛሬ በሕይወታችን ወደ አምላክ ሐልዎት መቅረብ የምንችልባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?

ግንቦት 7
May 15

የሉሲፈር ውድቀት


ሉሲፈር በአንድ ወቅት ከእግዚአብሔር ዙፋን ቀጥሎ የነበረው ጠባቂ ኪሩብ ሥልጣን በኃላፊነት ተሰጥቶት እንደነበር ሰው ያስተውለው ዘንድ የማይቻል ይመስላል። የእርሱ ሕልውና የእግዚአብሔርን ክብር ለአጽናፈ ዓለም በመግለጥ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው ጥርጥር የለውም። ሆኖም የፈጣሪውን ሳይሆን የገዛ ራሱን ክብር ማየት ጀመረ፤ ወይም፣ በትክክል ለመናገር—ለእርሱ የሚገባው ክብር እንዳልተሰጠው አድርጎ ማሰላሰሉን ተያያዘው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሕዝ. 28፡11-17፣ ኢሳ. 14፡12-14። ሉሲፈርን ለውድቀት የገፋፋው ምን ነበር? እነዚህን ጥቅሶች ከራእ. 14፡1-12 ጋር ያስተያዩ። በሉሲፈር ውድቀት እና ሰብዓዊው ፍጡር በክርስቶስ ባገኘው ከፍ ያለ ስፍራ መካከል ያለው ንጽጽር፣ በራእ. 14 ስለሆነው ነገር ባሎት ግንዛቤ ላይ ምን ገጽታ ይሰጦታል?



የተዋጁት ከእግዚአብሔር በግ ጋር በጽዮን ተራራ ላይ ሲቆሙ፣ ሉሲፈር ከቅዱሱ ተራራ እንዴት እንደተወገደ ልብ ይበሉ። ሉሲፈር በአንድ ወቅት በእግዚአብሔር የአትክልት ቦታ፣ በኤደን እንደነበረ ቃሉ የሚነግረን ሲሆን፣ ሰብዓዊ ፍጡራንም እንዲሁ በዚያ ነበሩ። ነገር ግን ከሰይጣን መጻኢ ቀናት በተቃራኒ፣ ሰብዓዊ ፍጡራን በክርስቶስ በኩል ወደ ኤደን እንዲመለሱ ሆኑ (ራእ. 22፡1-3)።

“ሰማይ ድል ይቀዳጃል፣ በሰይጣን እና መላእክቱ ውደቀት ክፍት ሆኖ የኖረው ስፍራም እነሆ በጌታ በተዋጁ ወገኖች ይሞላል።”—The Advent Review and Sabbath Herald, May 29, 1900.

የዳኑ ወገኖች በዚያ፣ ማለትም በሰማይ ሊገኙ የቻሉበት ምስጢር አንድ ብቻ ሲሆን ይኸውም ወንጌል ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የደኅንነት ወንጌል ጭብጥ በራእ. 4 እና 5 የዙፋኑ ክፍል ሥዕላዊ ገለጻ ቁልጭ ብሎ ቀርቧል። “ ‘ “መጽሐፉን ልትወስድ፣ ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል፤ በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።”” ’ ” (ራእ. 5፡9)። የሱስ ሰብዓዊውን ፍጡር ለመዋጀት መሞቱን የሚያሳይ እንዴት ያለ ወንጌልን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ሥዕላዊ አገላለጽ ነው!

በተጨማሪ ቋንቋው የመጀመሪያውን መልአክ መልእክት ምን ያህል እንደሚያንጸባርቅ ልብ ይበሉ፡ “እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር” (ራእ. 14፡ 6)። ክርስቶስ ለዓለም ያደረገውን በሙላት የሚያሳይ እንዴት ያለ ብርቱ መግለጫ ነው! የምድር ታሪክ ተጀምሮ እስኪያበቃ በምድር የተመላለሰ ክርስቶስ ያልሞተለት አንድም ሰው የለም። ስለ እርሱ መማርና መምረጥ የግለሰቡ ፋንታ ይሆናል። ሰዎች ክርስቶስ ስላደረገላቸው ነገር ያውቁ ዘንድ፣ እንደ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ እንደ ግለሰብ ምን ሚና አለን?

ግንቦት 8
May 16


ተጨማሪ ሀሳብ


“ተጋድሎው አበቃ” ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 756- 774 በአንድ ወቅት ጠባቂ ኪሩብ የነበረው ሰይጣን በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ የነበረውን እምነት ለማጥፋት ተነሣ። እግዚአብሔር የወደቁ መላእክት በአመፃቸው እንዲቀጥሉ የፈቀደላቸው ራስን ከፍ ከፍ በማድረግ የሚመጣውን የክፋት ጥልቀት ለመላው ዩኒቨርስ ለማሳየት ነው። ሰይጣን የሰውን ዘር በማታለል ከእግዚአብሔር ጋር እያደረገ ባለው ጦርነት ከጎኑ ለማሰለፍ ቢጥርም፣ ክርስቶስ ግን በመስቀል ላይ ሙሉ በሙሉ ድል በመንሣት በአንድ ወቅት በወደቁ መላእክት ተይዞ የነበረውን ስፍራ ለተዋጁት ሰብዓዊ ፍጡራን አደረገው። በክርስቶስ የዳኑ ኃጢአተኞች ሉሲፈር በሚያነሣው ሀሳብ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት፣ በይፋ ይገልጻሉ። የመጨረሻው ትዕይንት፣ በአንዳንድ መንገዶች—የእግዚአብሔርን መልካምነት እና ፍቅር ከሉሲፈር ውድቀት በፊት ከነበረው ሁኔታ የበለጠ የሚገልጥ ይሆናል። ምንም እንኳ ክፋት ይከሰት ዘንድ ፈጽሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ ባይሆንም፣ ያስከተለውም ዘላለማዊ መዘዝ አብልጦ አሳዛኝና ልብ ሰባሪ ቢሆንም፣ ማንኛውም ክፋትም ሆነ የክፋት ስር ከተወገደ በኋላ የሚገለጠው የእግዚአብሔር መልካምነትና የፍቅሩ ጥልቀት—ያ ባይሆን ፈጽሞ ለፍጡራኑ መታየት ባልቻለ ነበር።

ክርስቶስ “የተዋጁትን ወደራሱ አምሳል ተለውጠው፤ እያንዳዱ ልብ የመለኮትን ፍጹም ማኅተም ተሸክሞ፣ እያንዳንዱ የፊት ገጽታ የንጉሣቸውን አምሳያ እያንጸባረቀ ተመለከታቸው። የነፍሱን ጭንቀት ውጤት በእነርሱ ውስጥ አየ፣ እረካም። ከዚያም ወደ ተሰባሰቡት እልፍ አዕላፋት ፃድቃንና ኃጢአን በሚደርስ ድምጽ እንዲህ አለ፦ “እነሆ በደሜ የተገዙ ከእኔ ጋር ለዘላለም ይኖሩ ዘንድ ለእነዚህ ተሰቃየሁ፤ ለእነዚህ ሞትሁ። የምስጋና መዝሙርም በዙፋኑ ዙሪያ ባሉ፣ ነጭ ከለበሱ ወጣ፣ ‘የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል’ (ራእ. 5፡ 12)።” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ766)


የመወያያ ጥያቄዎች




1. እያንዳንዱ ሰብዓዊ ኅፀፅ፣ የባሕሪ እንከን፣ የተሳሳተ ድርጊት፣ የተሳሳተ እያንዳንዱ ሰብዓዊ ኅፀፅ፣ የባሕሪ እንከን፣ የተሳሳተ ድርጊት፣ የተሳሳተ አስተሳሰብ እና ተነሳሽነት በእግዚአብሔር ፊት ወለል ብሎ ሲገለጥ በህሊናዎ ያስቡ! ለእርስዎ የሚገባው ሕጋዊና ፍትሐዊ ፍርድ ምን ነበር? ይህ ከሆነ ዘንዳ፣ ብቸኛው ተስፋዎ ምንድን ነው? “እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ” (ሮሜ 3፡ 22 /1962 ትርጉም/)፣ አጥበቀን በምንሻው፣ ዛሬ እና በፍርዱ ቀን ይሽፍነን ይሆን? በአጭሩ ወንጌል ለምን ያስፈልገናል?

2. እስካሁን እንደተመለከትነው መጥምቁ ዮሐንስ እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ እስካሁን እንደተመለከትነው መጥምቁ ዮሐንስ እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ መብራት (ዮሐ. 5፡35) በመሆን የሱራፌልን ሚና ተጫውቷል። እርሱ በእርግጥ ከመሲሑ የመጀሪያ መገለጥ አስቀድሞ በመላክ የክርስቶስን መንገድ የጠረገ ነበር። የእግዚአብሔር የመጨረሻው ዘመን ሕዝቦች ተመሳሳይ ትንቢታዊ ሚና የሚጫወቱት እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL