የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ፍንጮች፣ ምስሎች፣ ምሳሌዎች፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ማጥኛ መንገድ



2ኛ ሩብ ዓመት 2025


ሚያዝያ 25 - ግንቦት 1

6ኛ ትምህርት

May 3 - 9




መሥዋዕትን ማስተዋል



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 1:2–15፣ ዕብ. 10:3–10፣ ዘፀ. 12:1–11፣ 1ቆሮ. 5:7፣ ሐጌ 2:7–9፣ ኢሳ. 6:1–5፣ ራእ. 4:7–11።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤ ‘መጽሐፉን ልትወስድ፣ ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል፤ በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።’ ” (ራእ. 5፡9)።

የሱስ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ ሲመጣ፣ “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ. 1፡29) ሲል መጥምቁ አወጀ። ይህ እንስሳት በመሥዋዕትነት ለሚቀርቡበት ጽንሰ ሃሳብ የማያሻማ ማጣቀሻ ሲሆን፣ ሁሉም ያመለክቱ የነበረው የክርስቶስን ለመላው የሰው ዘር ምትክ ሆኖ መሞት ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ በጉልህ ከቀረበው የእንስሳት መሥዋዕት ጭብጥ ማምለጥ አንችልም። በመላው የመጽሐፉ ገጾች እንደ ቀይ ፈትል በማለፍ፣ ዮሐንስ ወደ አምላካዊው ዙፋን ቅጥር ወደሚወሰድበት በራእይ መጽሐፍ ታላቅ ትዕይንት ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል (ራእ. 4 እና 5)። የሱስ በዚህ ወሳኝ ትዕይንት የታረደ የሚመስል በግ ሆኖ መታየቱ (ራእ. 5፡6)፣ ትንቢታዊውን ምዕራፍ በሙሉ ልቅም አድርጎ ለማስተዋል የሚያስችለን ቁልፍ ክስተት ሆኖ እናገኘዋለን።

በዚህ ሳምንት የዙፋኑ ክፍል ዋንኛ ተዋናይ ስለሆነው፣ ስለ ታረደው በግ፣ ስለ የሱስ ባለን ግንዛቤ ላይ መረጃ የሚሆኑንን አንዳንድ የመሥዋዕቱን ጭብጦች እንመለከታለን። ለማንም ያልተቻለውን፣ የእርሱ መሥዋዕትነት ብቻ የተገባ ሆኖ ተቀባይነት ማግኘቱ፣ ጌታ በዚያ የመሥዋዕት ስርዓት እያደረገ ስለነበረው ነገር እጅግ ብዙ ይናገራል። የመጨረሻውን መሥዋዕት የከፈለ ፍጻሜ የሌለው ፍቅር ባለቤት የሆነ አምላክ ተደርጎ የተገለጸበት መንገድ፣ እኛም ሆንን ሌሎች በአጽናፈ ዓለም ያሉ ያልወደቁ ባለ ብሩህ አእምሮ ፍጥረታት ለዘላለም ስንገረምና ስንደነቅ የምንኖርበት ይሆናል።

ሚያዝያ 26
May 4

ከንቱ መሥዋዕቶች?


አንዳንዴ ሁለት ሐሳቦችን ማነጻጸር በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

እግዚአብሔር ሕዝቡ ያቀረበውን መሥዋዕት አልቀበልም ካለበት ነጥብ አኳያ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊው የመሥዋዕት ስርዓት በርካታ ትምህርቶችን ማግኘት ይቻላል። ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ኢሳ. 1:2–15፣ ኢሳ. 56:6-7፣ መዝ. 51:17።

መሥዋዕትን አስመልክቶ የቀረቡ ወሳኝ ትምህርቶች ምንድን ናቸው?



በእስራኤል ታሪክ በተፈጸመው በዚህ አሳዛኝ ምዕራፍ፣ እግዚአብሔር የቀረበውን መሥዋዕት አልቀበልም ሲል የመጀመሪያው አልነበረም። በደኅንነት ታሪክ መጀመሪያ አካባቢ ተመሳሳይ ነገር ተከስቶ የነበረ ሲሆን፣ ይኸውም የአቤል መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ሲያገኝ፣ የቃየን ግን ሳያገኝ የቀረበት ሁኔታ በተፈጠረበት ወቅት ነበር። ያ የቀደመ ክፍል፣ ተቀባይነት ያላቸውን እና የሌላቸውን መሥዋዕቶች ለማነፃጸር ተጨማሪ ዕድል ይሰጠናል። (ዘፍ. 4:3–7፣ ዕብ. 11:4)።

በኢሳይያስ ዘመን እስራኤላውያን ኃይማኖት ነክ ጉዳዮችን ከአእምሮአቸው ጓዳ በአንደኛው ክፍል ብቻ አኑረው፣ እንዳሻቸው እየተመላለሱ፣ እግዚአብሔርን ለማስደሰት ብቻ የታይታ ሥርዓት ይፈጽሙ ነበር። ያቀርቡ የነበረው መሥዋዕት ልክ እንደ ቃየን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንጂ፣ ማንነታቸውን ለእርሱ የመስጠትና የማስገዛት እሳቤን ያማከለ አልነበረም።

የዚህን ዓለም መንግሥታት እየዘወረ ያለው ይኸው ከእኔ በቀር ላሳር ዓይነት መንፈስ ነው። ቃየን ልቡን ደስ ባለው መንገድ እየኖረ በራሱ መንገድና አኳኋን ለእግዚአብሔር የአምልኮ ሥርዓት መፈጸሙን ተከትሎ፣ ምናልባት አንድ ሰው—እግዚአብሔር ምቾት እንደነሣውና የገዛ ራሱን መንገድ እንዳይቀይስ እንደ ተጋረጠበት፣ ነገር ግን ይህን መንገዱን ተከትሎ እንዳይሄድ እግዚአብሔርን እንደፈራ አድርጎ ሊያስብ ይችላል።

አቤል ግን እግዚአብሔር የጠየቀውን፣ ይኸውም እግዚአብሔር ወደፊት ስለሚመጣው መሲህ የገባውን ቃል ኪዳን የሚያሳይ መሥዋዕት አቀረበ (ዘፍ. 3፡15)። መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው በግ የክርስቶስን በቀራኒዮ የማዳን ሥራ የሚያመለክት ነበር።

“አቤል ከፍ ያሉትን የመዋጀት መርኅዎች አስተውሎ ነበር። እራሱን እንደ ኃጢአተኛ ይመለከት የነበረው አቤል ኃጢአትና የኃጢአት መቀጮ የሆነው ሞት በነፍሱና ለእግዚአብሔር በሚያቀርበው አምልኮ መሃል እንደቆመ ይመለከት ነበር።

አቤል ሕጉ ከተላላፊው የሚጠይቀውን በማመን ለበደል መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበውን የሚታረድ ጠቦት ይዞ መጣ። በፈሰሰው ደም ውስጥ ወደፊት መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበውን፣ በቀራኒዮ መስቀል ላይ የሚሞተውን ክርስቶስ ተመለከተ። በዚያ ለኃጢአት ሥርየት ሆኖ የቀረበውን አዳኝ ለማመኑና ለጻድቅነቱ ተቀባይነት ያገኘው በመሥዋዕቱ ምስክርነት ነበር።” (የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት ገጽ 72)። በገዛ ራስ ስሜት ከመነዳት፣ ራስን መጠበቅ እንዴት ወሳኝ ነው! እያንዳንዳችን፣ የመዳን ብቸኛ ተስፋችን በሆነው በየሱስ ሞት ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን ምን ማለት እንደሆነ እንዴት መለማመድ እንችላለን?

ሚያዝያ 27
May 5

የኮርማዎች እና የፍየሎች ደም


አንዳንዶች የመሥዋዕቱን ሥርዓት ጽንሰ ሀሳብ—በጭካኔ የተሞላ፣ ርኅራኄ የጎደለው እና ፍትሐዊ ያልሆነ እያሉ ሲተቹት ይስተዋላል። ሆኖም ቁም ነገሩ ያለው እዚሁ ላይ ነው። የክርስቶስ ሞት—በጭካኔ የተሞላ፣ ርኅራኄ የጎደለው እና ጥፋት ሳይኖርበት ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ስለ ኃጢአተኞች መሥዋዕት የሆነ አልነበረምን? እነሆ የኃጢአትን ችግር ለመፍታት ያስኬደው ርቀት እስከዚያ ዘለቀ።

እነዚያ ሁሉ በጭካኔ የተሞሉ፣ ርኅራኄ የጎደላቸውና ፍትሐዊ ያልሆኑ መሥዋዕቶች የክርስቶስን ሞት ሲያመላክቱ ኖሩ። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 10፡3። በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ያቀርቡ ስለ ነበረው መሥዋዕት ጥቅሶቹ ምን ያስተምሩናል? ኃጢአተኞች በእነርሱ መዳን እስካልቻሉ ድረስ ለምን መሥዋዕት ያደርጓቸዋል?



በጎች እና ሌሎች በመሥዋዕትነት ይቀርቡ የነበሩ እንስሳት የእግዚአብሔርን በግ የሥርየት መሥዋዕትነት የሚያመላክቱ ምሳሌዎች ብቻ ነበሩ። መሥዋዕቶቹ ኃጢአተኞች መሲህ ወደፊት መጥቶ በሚሠራው ሥራ ላይ ያላቸውን እምነት በተጨባጭ የሚገልጹባቸው መንገዶች ነበሩ። ብዙውን ጊዜ እንደነዚህ ዓይነቶቹን ምሳሌዎች ቀደም ብሎ እንደተገለጸ የአንድ ነገር ገጽታ ወይም ክስተት አድርገን እንጠቅሳቸዋለን። እንደውም አንዳንዶች እነዚያን መሥዋዕቶች የየሱስን የመስቀል ላይ ሞት አስቀድመው ያሳዩ “ትናንሽ ትንቢቶች” ሲሉ ይገልጹአቸዋል።

ከመሥዋዕት ጋር ትስስር የነበራቸው የአምልኮ ሥርዓቶች በትንሹም ቢሆን ለአንድ ጉዞ ከመክፈል ጋር ይመሳሰላሉ። የባቡር፣ የአውቶቡስ፣ ወይም የአውሮፕላን ቲኬት ሲቆርጡ ለከፈሉበት ጉዞ ወዲውኑ አገልግሎት አያገኙም።

ይልቁንም የጉዞ ማረጋገጫ ወይም ምልክት የሆነ ደረሰኝ ወይም የማለፊያ ወረቀት ይሰጥዎታል። በዚያ ወረቀት ላይ የፈለጉትን ያህል ቢቀመጡ ወደ የትኛውም መዳረሻ ሊወስዶት አይችልም። አንዴ ከተሳፈሩና ጉዞው ከጀመረ በኋላ ግን፣ ለዚያ ለከፈሉበት አገልግሎት እያገኙ በመሆኑ ትኬቱ አላስፈላጊ ይሆናል።

ለመሥዋዕት ይቀርቡ የነበሩት እንስሳትም እንዲሁ ነበሩ። እንስሳቱ የሚጫወቱት ትልቅ ሚና የነበራቸው ሲሆን፣ ነገር ግን እውነተኛ የሆነው እርሱ መሥዋዕት ከሆነ በኋላ ትርጉም የለሽ ሆኑ። ይህ ደግሞ የሱስ በሞተበት ወቅት በቅዱሱ ስፍራና በቅድስተ ቅዱሳን መካከል ያለው መጋረጃ ሲቀደድ የታየ እውነታ ነው። “የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ” (ማር. 15፡ 38)። መላው የመሥዋዕት ሥርዓት፣ ቤተ መቅደሱም ሆነ ሁሉም አገልግሎቶች የየሱስን የመስቀል ላይ ሞት አመላክተዋል። የሱስ የገባውን ቃል በመስቀል ላይ ከፈጸመና በድል አድራጊነት ከሞት ከተነሣ በኋላ ምሳሌዎቹ አላስፈላጊ ሆኑ። ሥጋ የለበሰው ቃል (ዮሐ. 1፡1-3፣14) ይኸውም የየሱስ ሞት ብቻ ሊያስተሰርየው የቻለው ኃጢአት ምን ያህል የከፋ እንደሆነ አሰብ ያድርጉ።

ለኃጢአት ያለን አመለካከት ምን መሆን እንዳለበት አስመልክቶ ይህ ምን ሊነግረን ይገባል?

ሚያዝያ 28
May 6

የፋሲካው በግ


የራእይ መጽሐፍ የሱስን ወደ ሠላሳ ጊዜ ገደማ “በጉ” በማለት ይጠራዋል። በደኅንነት ዕቅድ፣ ከጥንት ዘመን አንስቶ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወደፊት የሚመጣውን መሲሕ ለማመላከት የበግ ጠቦቶችን ሲጠቀሙ ኖረዋል።

አቤል “ከበጎቹ በኵራት” (ዘፍ. 4፡4) መካከል ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ያመሩ ዘንድ ከግብፅ ከውጣታቸው አስቀድመው ከሰውም ከእንስሳም የተወለደውን እያንዳንዱን የበኩር ልጅ አንድ ዓመት በሞላው ተባዕት ጠቦት ይዋጁ ዘንድ መመሪያ ተሰጥቶአቸው ነበር (ዘፀ. 12፡5)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 12፡1-11፣ ኢሳ. 53፡7-8፣ 1ቆሮ. 5፡7፣ ራእ. 5፡6።

ጥቅሶቹ ስለ የሱስ የፋሲካ መሥዋዕትነት ምን ያስተምሩናል? ይህ ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም አለው?



የክርስቶስ ሞት፣ ትንሣኤና ዕርገት ፍጻሜ ካገኘ ከዓመታት በኋላ ጴጥሮስ ስለተፈጸመው ነገር በማሰላሰል እንዲህ ሲል ጽፏል፡ “ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው።” (1ጴጥ. 1፡18-19)።

የሱስ የእግዚአብሔርን ቅድስና የሚያረካ ሰብዓዊ ሕይወት የኖረ ሲሆን፣ እኛ የተቀረነው ግን ኃጢአት ሠራን። ኃጢአተኛውን ሕይወት የምንመራበት የአኗኗር ዘይቤአችንም ስለ ፈጠረን አምላክ በተጨባጭ የሚዋሽ ሆነ።

እነሆ፣ የሱስ ግን “የኋለኛው አዳም” (1ቆሮ. 15፡45) ሆነ። እኛ ወደቅን፣ እርሱ ግን ፍጹም ሕይወት ኖረ። ሰብዓዊውን ሥጋ የለበሰ ሰው እንደመሆኑ፣ ሰብዓዊው ዘር ላይ የሚደርስ ማንኛውም ነገር ደረሰበት። ሆኖም የእግዚአብሔርን ክብር ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባረቀ። የሱስ “እኔን ያየ አብን አይቷል” (ዮሐ. 14፡9) ሲል ለፊልጶስ እንደነገረው ልብ ይሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሱስ በፋሲካ በዓል ላይ ተሰቀለ። ይህም እርሱ—ምሳሌ የነበረው የፋሲካ በግ እውነተኛ መሥዋዕት መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

በዮሐ. 18፡19-20 የሱስ ኃይማኖታዊ አስተምህሮውን “በግልጽ” እንደተናገረ መጻፉን እናነባለን። በተመሳሳይም በዘፀ. 12፡ 5-6 ስለ ፋሲካ በግ በተገለጸው መሰረት፣ የእስራኤል ልጆች ለፋሲካ በዓል የሚሆን ጠቦት እንዲመርጡና የሚታረድበት ቀን እስኪደርስ ድረስ በግልጽ እየታየ፣ እየጠበቁ "እንዲያቆዩ" ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር።

ሊቀ ካህናቱ የሱስን ስለ ትምህርቶቹ በጠየቀው ጊዜ፣ በስውር ሳይሆን ለሁሉም ሰው በግልጽ እየታየ ማስተማሩን በማጣቀስ ተናግሯል። ሕይወቱ፣ ሥራዎቹና አስተምህሮዎቹ በሙሉ እውነተኛ ማንነቱን ፍንትው አድርገው ያሳዩ ነበሩ። እርሱ የእግዚአብሔርን ጽድቅ እና ክብር እጅግ ብርቱ በሆነ መንገድ የገለጸ—ነውር የሌለበት በግ ነው! በሕይወታችን ውስጥ የየሱስን ፍጹም ባሕሪ በተሻለ መንገድ የምናንጸባርቅባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ሚያዝያ 29
May 7

የሱስ በቤተ መቅደስ


በመላው የደኅንነት ታሪክ ውስጥ ውጥረት አለ። እግዚአብሔር በአንድ ወቅት ከእርሱ ጋር የነበረን አንድነት ወደ ቀደመ ንጽህናው እንዲመለስና ወደ እኛ ለመቅረብ ይመኛል። ነገር ግን ኃጢአተኞችን ወደ እርሱ ሐልዎት ማምጣት ፍጹም እንዲጠፉ ያደርጋቸዋል። መዝሙረኛው እንዲህ ሲል ጽፏል፡ “አንተ በክፋት ደስ የምትሰኝ አምላክ አይደለህም፤ ክፉም ከአንተ ጋር አያድርም” (መዝ. 5፡4)።

ወረድ ብሎ ደግሞ እንዲህ ይላል፡ “እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ አንተንም በመፍራት፣ ወደ ተቀደሰው መቅደስህ እሰግዳለሁ።” (መዝ. 5፡7)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐጌ 2፡7-9። ሁለተኛው ቤተ መቅደስ እየተገነባ እያለ ነቢዩ ሐጌ አስደናቂ የተስፋ ቃል ሰጠ፡ አዲሱ ቤተ መቅደስ ከቀድሞው ይበልጥ በክብር የተሞላ ይሆናል። ይህ ትንቢት ምን ትርጉም ነበረው?



የመጀመሪያው ቤተ መቅደስ በሰለሞን አማካይነት ለአገልግሎት እንዲውል ሲመረቅ፣ የእስራኤል ልጆች ወደ ከነዓን ሲጓዙ አብሯቸው የነበረው ሸኪና— የእግዚአብሔር ሐልዎት ክብር ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ስለነበር፣ ካህናቱ በደመናው ምክንያት አገልግሎታቸውን ማከናወን አልቻሉም ነበር (1ነገሥ. 8፡10-11)።

ሁለተኛው ቤተ መቅደስ ሲመረቅ የእግዚአብሔርን ዙፋን ይወክል የነበረው የቃል ኪዳኑ ታቦት በስፍራው አልነበረም። ለዚህ ምክንያቱ፣ በኤርምያስ ተደብቆ ስለነበር ነው። በወቀውቱ ቤተ መቅደሱ በእግዚአብሔር እውነተኛ ሐልዎት አልተሞላም ነበር።

ጉዳዩ ልብ የሚሰብር ሆኖ ሳለ፣ የሐጌ ትንቢት እውን መሆን የሚችለው እንዴት ነው?

በሥጋ የተገለጠ አምላክ የሆነው የሱስ፣ ሥጋና ደም ለብሶ የተገለጠው በሁለተኛው ቤተ መቅደስ ውስጥ ነበር። እግዚአብሔር ራሱ ከመጋረጃው ጀርባ ወጥቶ ከእኛ እንደ አንዱ በመሆን በዚህ በወደቀ ዓለም ሊገናኘን መጣ።

የእግዚአብሔር ልጅ አሁን የሰው ልጅ በመሆኑ ፊቱን ማየት፣ ድምፁን መስማትና— ለአብነት ያህል ርኩስ የነበረውን ለምጻም ነክቶ ሲያነጻው ምስክር መሆን ቻልን (ማቴ. 8፡3)። እግዚአብሔር እኛን በእርሱ ትእዛዝ ወደ ራሱ አቅጣጫ ከማቅረብ ይልቅ፣ በእኛ አቅጣጫ በመጓዝ ወደ ራሱ አቀረበን። እርሱ በአካል ወደ እኛ ወረደ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ የሱስ እንዲህ ማለቱ ብዙም የሚገርም አይሆንም፡ “እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ይሉታል፤ ትርጕሙም፣ ‘እግዚአብሔር ከእኛ ጋር’ ማለት ነው” (ማቴ. 1፡23)። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ያስቡ። የዩኒቨርስ ፈጣሪ በመካከላችን ለመኖር ብቻ ሳይሆን ለእኛ ሲል ሊሞት ወረደ!! መስቀሉ የእግዚአብሔር ፍቅር እጅግ በላቀ መንገድ የተገለጸበት ትእይንት ነው።

የእግዚአብሔርን ፍቅር በተጨባጭ ማየት እና መለማመድ የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ሚያዝያ 30
May 8

ሁሉ ነገር በአንተ ተፈጥሯል!


በጣት በሚቆጠሩ ውስን አጋጣሚዎች ነቢያት የእግዚአብሔርን ዙፋን እንዲያዩ ተፈቅዶላቸው በራእይ ወደ እርሱ እንዲቀርቡ ተደርገዋል። ሕዝቅኤል በላይ ካለው ከጠፈር ከፍ ብሎ ተመልክቷል (ሕዝ. 1፡26)፣ ኢሳይያስ ሰማያዊውን ቤተ መቅደስ ጎብኝቷል (ኢሳ. 6፡1)፤ ስለ ሰማያዊው ዙፋን እጅግ ግልጽ መግለጫ ከሚሰጡን መልእክቶች ውስጥ አንዱ፣ በራእ. 4 እና 5 ዮሐንስ ወደዚያው በራእይ ተወስዶ የነበረበት ሁናቴ ነው። በቤተ መቅደሱ አገልግሎት ውስጥ የነበሩት የብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች ሰብዓዊው ፍጡር ወደ እግዚአብሔር ሐልዎት መግባት የሚችልበት መንገድ አንድ ብቻ—ይኸውም በክርስቶስ ደም እንደነበረ አመልክተዋል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 6፡1-5 እና ራእ. 4፡7-11። እነዚህን ሁለት ራእዮች የሚያመሳስሏቸው አላባዎች ምንድን ናቸው? ለክስተቶች ቅደም ተከተል ትኩረት ይስጡ፤ በመጀመሪያ የሚቀርበው የትኛው ርዕሰ ጉዳይ ነው? የሚከተለውስ? በእነዚህ ራእዮች እግዚአብሔርን አስመልክቶ አጽንኦት የተሰጠው እውነት የትኛው ነው?



በእነዚህ በእያንዳንዳቸው የዙፋኑ ቅጥር ራእዮች የሚስተዋለው የመጀመሪያው ክስተት፣ የሰማያዊ ፍጡራን ለእግዚአብሔር ቅድስና አጽንኦት የመስጠት ጉዳይ ነው። በኢሳይያስ ራእይ የሚታየው ትዕይንት በእጅጉ አስደናቂ ነው፡ ሱራፌል የእግዚአብሔርን ቅድስና ሲያውጁ “የመድረኩ መሠረት ተናወጠ፤ ቤተ መቅደሱም በጢስ ተሞላ።” ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ኪሩቤል “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” በማለት ተመሳሳይ እወጃ ሲያቀርቡ ይስተዋላል። (ኪሩቤል ተብለው ስለተገለጹት ሕያዋን ፍጥረታት የሚከተሉትን ጥቅሶች ይመልከቱ፡ ሕዝ. 10፡14-15)። እያንዳንዱ ነቢይ አንጸባራቂውን አምላካዊ ክብር እንዲያይ ተደርጎው ነበር።

ከዚያም ነቢያቱ በተመለከቱት ነገር የነበራቸውን ምላሽ እንመለከታለን።

ኢሳይያስ ከንፈሮቹ የረከሱበት ሰው መሆኑን በመናገር ወዮልኝ ብሎ ሲጮኽ ይስተዋላል (ኢሳ. 6፡5)። ዮሐንስ ደግሞ ማንም የተገባው ሊገኝ ካለመቻሉ አሳዛኝ እውነታ ጋር በመጋፈጡ አለቀሰ (ራእ. 5፡4)። በእግዚአብሔር የከበረ ማንነት ፊት በቀጥታ እንድንገኝ ስንደረግ፣ ሰብዓዊው ማንነት የሚገኝበትን ሁኔታ መረዳት ስለምንጀምር፣ ብቁ ላልሆንነው ለእኛ ቤዛችን ክርስቶስ እንደሚያስፈልገን እናምናለን።

ሰይጣን በእግዚአብሔር ላይ በርካታ ክሶች በማቅረብ—አምባገነን፣ ራስ ወዳድ እና ጨካኝ ነው ቢልም፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዙፋን እጅግ አጭር የተባለው ጊዜ እንኳ ሳይቀር የሰይጣንን ሐሰተኝነት የሚያጋልጥ ሆኖ እናገኘዋለን።

በዚህም “ ‘የታረደው በግ’ ” (ራእ. 5፡12) የሆነውን የክርስቶስን እውነተኛ ማንነትን መመልከታችን የአብን እውነተኛ ማንነት ያሳየናል። የሱስን በማየታችን አብ ምን እንደሚመስል መገንዘብ መቻላችን ምንኛ አጽናኝ ነው! (ዮሐ. 14፡ 9)። የሱስ በመስቀል ላይ ስለ እኛ ሲሞት የታየው ትዕይንት አብ የተገለጠበት ግዙፍ መንገድ ነው።

እንግዲህ መስቀሉ ሁለት ነገሮችን ሊያሳየን ይገባል፡ አንደኛ እግዚአብሔር ይህን ሲያደርግ፣ ማለትም ራሱን ለእኛ መሥዋዕት አድርጎ ሲሰጥ ምን ያህል ቢወደን እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ መዳን የምንችለው በመስቀሉና በመስቀሉ ብቻ መሆኑ ምን ያህል ኃጢአተኞች እና የወደቅን እንደሆንን ግልጽ ሊያደርግልን ይገባል።

ግንቦት 1
May 9


ተጨማሪ ሀሳብ


ቅዱሳት መጻሕፍት ደኅንነታችንን እውን ለማረግ የተገባው ክርስቶስ ብቻ እንደሆነ በግልጽ ያሳዩናል። ኃጢአት ዐልባ ሰብዓዊ ሕይወት የኖረው እርሱ፣ ለአብ ክብር ፍጹም የሆነ እርካታ ያስገኘ ብቸኛው የሰብዓዊው ሕይወት ምሳሌ ነው። ነውርና እንከን የሌለበት የእግዚአብሔር በግ የሆነው እርሱ፣ እንደ ዘላለማዊ የደኅንነት ዋስትናችን ስለ ለሰብዓዊው ዘር ግንባር ቀደም ሆኖ ቆሟል።

በሌላ በኩል እግዚአብሔር ለእርክስና ምላሽ የሚሰጠውን ፍትሐዊ ፍርድ ለማርካት እነሆ በደላችንን በራሱ ላይ አኖረ። ዮሐንስ በእግዚአብሔር ዙፋን ዙሪያ የተሰበሰቡ፣ አስደናቂውን የሰማያዊ ፍጥረታት ትዕይንት ሲመለከት፣ “አታልቅስ፤ እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር ድል ነሥቷል” (ራእ. 5፡5) ተባለ።

በተጨማሪ የኃጢአትን ችግር ለመፍታት በቂ ሊሆን የቻለው የየሱስ ሞት ብቻ፣ ይኸውም ራሱ እግዚአብሔር መሥዋዕት መሆኑ፣ ስለ ኃጢአት አስከፊነትና በኃጢአት የወደቀው ሰብዓዊ ዘር ስለሚገኝበት ሁናቴ ለማሰብ ይሞክሩ።

እግዚአብሔር የመለኮታዊ መንግሥቱን መርኅዎች ሳይጥስ እኛን ሊያድን የሚችልበት ሌላ መንገድ ቢኖር ኖሮ በእርግጥ ያደርገው ነበር።

“የተጣሰው አምላካዊ ሕግ የተላላፊውን ኃጢአተኛ ህይወት ይጠይቅ ነበር።

በዩኒቨርስ ካሉት ሁሉ አንዱ ብቻ ስለ ሰው ልጅ በመቆም ሕጉ የጠየቀውን ማሟላት ይችል ነበር። መለኮታዊው ሕግ ልክ እንደ ሕግ አውጪው አምላክ ቅዱስ እንደመሆኑ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሆነው አንዱ ብቻ ለሰብዓዊው ፍጡር መተላለፍ ስርየት ማምጣት ይችል ነበር። በኃጢአት የወደቀውን ሰብዓዊ ዘር ከሕጉ እርግማን በመዋጀት ዳግመኛ ከሰማይ ጋር ህብረት እንዲኖረው ሊያደርግ ይችል የነበረው አንዱ ክርስቶስ ብቻ ነበር። ክርስቶስ እንደ በደለኛ ተቆጥሮ የኃጢአትን ውርደት መቀበል ነበረበት። ለቅዱሱ አምላክ በእጅጉ አጸያፊ የሆነው ኃጢአት--አብን ከወልድ የግድ መለየት ነበረበት። ክርስቶስ የጠፋውን ዘር ለማዳን ጥልቅ በሆነ ሐዘንና እንግልት ማለፉ የግድ ነበር።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ፡ 59)


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ዮሐንስ ወደ ዙፋኑ ቅጥር ሲገባ “የታረደ” የሚመስል በግ ይመለከታል። ዮሐንስ ወደ ዙፋኑ ቅጥር ሲገባ “የታረደ” የሚመስል በግ ይመለከታል። የሱስ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የታረደው በግ እንደሆነ ራእ. 13፡8 ላይ ይነግረናል። የደኅንነት ዕቅድ ለእኛ ከማስፈለጉ አስቀድሞ ገቢራዊ ከመደረጉ አኳያ ስለ እግዚአብሔር ምን ትህርት ማግኘት እንችላለን?

2. አምላክ የለሽ የሆኑ በርካታ ሰዎች ቀዝቃዛ በሆነው ጽንፈ ዓለም ውስጥ አምላክ የለሽ የሆኑ በርካታ ሰዎች ቀዝቃዛ በሆነው ጽንፈ ዓለም ውስጥ ብቻችንን እንደምንኖር አድርገው ያምናሉ። በአንጻሩ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር የሚናገር ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን እርሱ ይህችን ምድር አብልጦ ከመውደዱ የተነሣ ወደ እርስዋ እንደ ወረደና አልፎ ተርፎም ስለ እርሷ መሥዕት እንደሆነ ይናገራል። በእግዚአብሔር ከማያምኑት በተቃራኒ ለዓለምና እኛ በውስጧ ስላለን ስፍራ ምን ያህል የተለየ አመለካከት ሊኖረን ይገባል? በሌላ አነጋገር፣ የመስቀሉ እውነታ በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ላይ ምን ተጽእኖ ሊያሳድር ይገባል?

3. የሰው ዘር መዳን የሚችልበት ብቸኛው መንገድ የክርስቶስ ሕይወት፣ የሰው ዘር መዳን የሚችልበት ብቸኛው መንገድ የክርስቶስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ የተከፈለ ውድ ዋጋ ኃጢአት በእርግጥም እጅግ የከፋ እንደሆነ አስመልክቶ ምን ያስተምረናል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL