የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ፍንጮች፣ ምስሎች፣ ምሳሌዎች፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ማጥኛ መንገድ



2ኛ ሩብ ዓመት 2025


ሚያዝያ 18 - 24

5ኛ ትምህርት

Apr 26 - May 2




ሕዝቦች፡ ክፍል 2



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 2:9–17፣ ዳን. 2:31–35፣ ኢሳ. 17:12-13፣ ዳን. 7:1–3፣ ሮሜ. 3:10–19፣ ራእ. 12:15-16. ራእ. 10:1–11።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ ዕወቁ፤ በሕዝቦች ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፤ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።” (መዝ. 46፡10)።

ባለፉት ምዕተ ዓመታት አንዳንዶች እግዚአብሔር የሰውን ውድቀት ይፈልግ ነበር ይሉና—የሰዎች ወደ ኃጢአትና ሞት ቁልቁለት መውረድ የእርሱ ዕቅድ አካል እንደሆነ፤ ከዚያም ራሱን በየሱስ ማንነት ገልጦ ወደ መስቀሉ እንዳመራ ሲሞግቱ ተደምጠዋል። ለነገሩ እርሱ ለሰዎች ሲል በመስቀል ላይ በመሞት ለሰብዓዊው ፍጡር ያለውን ጥልቅ ፍቅር ኃያል በሆነ መንገድ ከመግለጽ ውጪ ምን ማድረግ ይችል ነበር? ባጭሩ በዚህ አስተሳሰብ መሰረት፡ እግዚአብሔር የሰብዓዊውን ውድቀት ይሻ ነበር።

ይህ በእጅጉ አሰቃቂ እና አሳዛኝ አቋም ነው። የሰይጣንም ሆነ የሰብዓዊው ፍጡር ውድቀት የእግዚአብሔር ዕቅድም ሆነ ዓላማ አልነበረም። በመጀሪያ የሰይጣን በመቀጠል ደግሞ የሰብዓዊው ፍጡር አመጻ መጠነ ሰፊ መዘዝ ያስከተለ አሳዛኝ ክስተት ነበር። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ባይወድቁ ኖሮ፣ በእርሱ ያለን ደስታ ፍጹም እንደሆነ ይቀጥል ነበር።

በዚህ ሣምንት ውድቀት ያስከተላቸውን ችግሮች እና ከእግዚአብሔር አስተዳደር በተቃራኒ የቆመውን የሰው መንግሥት ምኞትና ፍላጎት መመልከታችንን እንቀጥላለን። እነዚህ እውነቶች በዳንኤል መጽሐፍ ብርቱ በሆነ መንገድ የተገለጹ ሲሆን፣ ይኸውም ሰዎች ከእግዚአብሔር ገዢነት አፈንግጠው ምድራዊ ልዑላንን ሲመርጡ ሊከሰት ስለሚችለው ነገር ከሰጣቸው ማስጠንቂቂያ አኳያ እርሱ ትክክል እንደ ነበር ያሳያሉ። በትክክል ያገኙት ነገር ቢኖር፡ በሰማያዊው ፋንታ ምድራዊ ልዑላን እና በኃጢአተኞች ላይ የሚሰለጥኑ ኃጢአተኛ ጌቶች!!

ሚያዝያ 19
Apr 27

የመጀመሪያው ትእዛዝ


ኤደን ገነት የመጀመሪያዎቹ የእግዚአብሔር ሰዎች ከፍጥረት ጋር ባላቸው መስተጋብር ያማያቋርጥ ትምህርት የሚቀስሙበት እና የአብራካቸው ፍሬዎችም ቢሆኑ አብልጠው ስለ ፈጣሪ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነበር። “ቅዱሳኑ ጥንዶች በእግዚአብሔር አባታዊ ጥበቃ ስር ብቻ አልነበሩም ነገር ግን ዕውቀቱ የማይመረመረው አምላክ ተማሪዎች ጭምር ነበሩ። … በዐይን የሚታየው ምስጢሩ የዩኒቨርስ ክፍል ‘በእውቀቱ ፍጹም የሆነውን የእርሱን ድንቅ ሥራ’ (ኢዮብ 37፡16) ሳይታክት የሚገልጽና የሚያስተምር የደስታ ምንጭ ሆኖላቸው ነበር።” (የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፡ ገጽ 43)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 2፡9-17። እግዚአብሔር ለሰብዓዊው ፍጡር የሰጠው የመጀሪያ ትእዛዝ (ክልከላ) ምን ነበር—ደግሞስ ያን ያህል ለምን አስፈላጊ ሆነ?



እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠው “ማዘዝ”tswh የተሰኘው ግስ ሥርወ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው በዘፍ. 2፡16 ላይ ሲሆን፣ ትእዛዙ የተሰጠው መልካም እና ክፉ ከሚያሳውቀው ዛፍ እንዳይበሉ በተነገራቸው ጊዜ ነበር። ለመሆኑ አንዳንድ ዕውቀት ሊከለከል የሚችለው እንዴት ነው? ሁሌም ቢሆን ተጨማሪ ተሞክሮ ማግኘት ብሎም የማወቅን አድማስ ማስፋት ጠቃሚ አይደለምን?

እግዚአብሔር አንዳንድ እውቀት ሊያስከትል ከሚችለው የረዥም ጊዜ ሥቃይ ሕዝቡን እየታደገ በጥንቃቄ ለማስተማር አስቦ የነበረ ሲሆን፣ ለአብነት ያህል ሰዎች በራሱ በጌታ ከመገዛት ይልቅ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ሲመርጡ መዘዝ መከተሉ አይቀሬ ነበር—ሲሉ አንዳንዶች ይሞግታሉ።

ከሺህ ዓመታት በኋላ፣ እስራኤል ንጉሥ እንዲሰጣት በጠየቀች ጊዜ፣ ጌታ ሊከተሉ የሚችሉ መዘዞችን ፍንትው አድርጎ አስቀምጦላቸዋል (ባለፈው ሣምንት እንደተመለከትነው)። ከእርሱ ቀጥተኛ አገዛዝ የመውጣታቸው ውሳኔ እስከ ዘመን ፍጻሜ ድረስ እንደሚዘልቅ ለሕዝቡ አሳውቆአል።

የእስራኤል ነገሥታት ከጊዜ ወደ ጊዜ እርክስናቸው ይበልጥ እየተንሰራፋ ሄደ። ይህን ተከትሎ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝቦችም አብልጠው ወደ ዓለማዊነት አዘነበሉ። ምንም እንኳ እርሱ የፈለጉትን ሰብዓዊ መንግሥት ቢሰጣቸውም፣ እስራኤላውያን ግን እንደ ሕዝብ ከታለመላቸው ዓላማ አፈነገጡ።

ይህን የኋላ ታሪክ በአእምሮአችን ይዘን የዳንኤልን መጽሐፍ መግለጣችን በመልእክቶቹ ላይ ብርሃን እንዲፈነጥቅልን ይረዳናል። በመጽሐፉ ላይ በራእይ የተገለጠው ረጅሙ የመንግሥታት መለዋወጥ ጉዞ የአረማውያን “የሕዝቦች” ለውጥ ብቻ ሳይሆን፣ እስራኤላውያን የእርሱን ትእዛዛት ለመከተል አሻፈረኝ ማለታቸውን የሚያሳይ ለውጥ ጭምር ነው። በመጀመሪያ ላይ በኤደን ከተሰጠው ነጻነት በተጻራሪ ለበርካታ መቶ ዓመታት በዘለቀው ሰብዓዊውን ፍጡር በቁጥጥር ሥር የማዋል—በዚህ ዓለም መንግሥታት ባህሪ እና በእግዚአብሔር መንግሥት መካከል ስላለው አስገራሚ ልዩነት ፈቃደኛ ልቦች ምስክር ሊሆኑ የሚችሉባቸው አዲስ የትምህርት ዘርፍ መሆን ይችላል። ስለ እንደነዚህ ዓይነት ዕውቀቶች አሰብ ያድርጉ። ይህ በኤደን ተከልክሎ የነበረውን ነገር መረዳት እንድንችል እንዴት ይረዳናል?

ሚያዝያ 20
Apr 28

ዳንኤል ምዕራፍ፡ 2


እግዚአብሔር በእርሱ ሕዝብ እና በዚህ ዓለም መንግሥታት መካከል ስላለው ግንኙነት እጅግ አሳማኝ መግለጫዎችን በዳንኤል አማካይነት ያቀረበው በባቢሎን ምርኮ ወቅት ነበር። ሕዝቡ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ሁኔታ ማክተሙን ተከትሎ አሁን በምርጫቸው የዘሩትን ማጨድ ግዴታቸው ሆነ። (ምናልባት ከእነርሱ መማር ይኖርብን ይሆን?) እስከ ዓለም ፍጻሜ ለሚዘልቀው የምድር ታሪክ ሰፊ ዕይታ የሚሰጡንን እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዳን. 2፡31-35። ከዚህ አስደናቂ ትንቢት ምን ጠቃሚ እውነቶችን እንማራለን?



በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ብዙዎች ለሰው ልጅ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግስጋሴ አዲስ ዓይነት መተማመን እያሳዩ ነበር። ለአብነት ያህል የፓሪስ ኤግዚቢሽን (1900) ሰዎች ስለ ወደፊቱ ብሩህ ተስፋ እንዲሰንቁ መንስዔ የሆነ አስደናቂ ትዕይነት ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ሰብዓዊው ፍጡር በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ግስጋሴ የተቀዳጃቸው ድሎች መጠነ ሰፊ የሚባሉ የከፉ የሰው ልጅ ችግሮችን የቀረፉ ናቸው! የሰው ልጅ ወደ ሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን በገባበት ወቅት፣ የዕድገት ግስጋሴ ጽንሰ ሀሳቦች የሰውን ልጅ ወደ ፍጽምና እንዲያመራና የጥልቅ እሳቤ ባለቤት እንዲሆን በማድረግ—ለሰዎች በዓይነቱ አስደናቂ የሆነ አዲስ ዘመን እንዲከሰት መንስዔ ይሆናሉ የሚል ብሩህ ተስፋ በበርካታ ምሑራን ዘንድ ይንጸባረቅ ነበር።

ይሁን እንጂ አንደኛው የዓለም ጦርነት እነዚህን ሕልሞች በብርሃን ፍጥነት በማጨለም፤ በሃያኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ከ200 ሚሊዮን የሚልቁ ወገኖቻችንን የጦርነት ወላፈን በላቸው። በቴክኖሎጂ ረገድ አዎንታዊ ግስጋሴ ቢመዘገብም፣ በሥነ ምግባር ግን ጉዞው የኋልዮሽ ከመሆን ፈቅ አላላም።

ዕውቁ የጥቁሮች መብት ተሟጋች ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር የተናገሩትን በአጭሩ ለመጥቀስ ያህል—የማይከሽፉ ሚሳኤሎችን እንጂ ሰዎችን አልሠራንም ብለዋል። ይህ ደግሞ እጅግ አስፈሪ ነው።

በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ተማሪዎች በዳን. 2 ንጉሡ የተመለከተው ምስል ከከበረ ማዕድን አንስቶ እጅግ ዝቅ እስካለው የሚሸፍን፣ ይኸውም፡ ከወርቅ ወደ ብር፣ ከብር ወደ ነሐስ፣ ከነሐስ ወደ ብረት ከዚያም ወደ ብረትና ሸክላ ቅልቅል ዝቅ እያለ መሄዱን ተገንዝበዋል።

ቻርልስ ዳርዊን፣ ካርል ማርክስና ሌሎች የአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ምጡቅ አእምሮ ባለቤቶች፣ የሰው ልጅ በሥነ ሕይወትም ሆነ በማኅበራዊ— እየተመነደገ ይሄዳል በማለት ሊያሳምኑን ሞክረዋል። ምንም እንኳ በአንዳንድ መንገዶች የሰው ልጅ ሕይወት (ቢያንስ በአካላዊ ደረጃ) መሻሻል ቢያሳይም፣ ዛሬ እየተገዛና እየተዳደረ ካለበት ሁኔታ አኳያ የዚህን ዓለም የወደፊት ዕጣ ፈንታ ስንመለከት—ስለ ሰላም፣ ደኅንነትና ብልጽግና ብሩህ አመለካከት እንድንሰንቅ የሚያደርግ ነውን? የሱስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቆናል፡ “ ‘ስለ ጦርነትና ጦርነትን የሚያናፍስ ወሬ ትሰማላችሁ… ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በተለያየ ስፍራም ራብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል’ ” (ማቴ. 24:6- 7)። እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ቢሰጡንም፣ ስለ እነርሱ አስቀድመን ማወቃችን እንዴት ያጽናናናል?

ሚያዝያ 21
Apr 29

ዳንኤል ምዕራፍ፡ 7


የዳንኤል ምዕ. 2 ሕልም በመጀመሪያ የተሰጠው ለባቢሎናዊው ንጉሥ ነበር። በተቃራኒው የዳን. 7 ራእይ የተሰጠው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሕዝብ አካል ለነበረው ዕብራዊ ነቢይ ነበር።

ዳንኤል ከናቡከደነጾር ሕልም ጋር ተመሳሳይ ርዕሰ ነጥብ የሚጋራ ራእይ ቢያይም፣ ነገር ግን እርሱ ያየበት መንገድ የተለየ ነበር። በሕልሙ ምስል ምትክ፣ ተከታታይነት ያላቸው መንግሥታት ከባሕር ውስጥ መውጣታቸውንና ነፋሳትም ውሃውን ሲያናውጡ ተመልክቷል። እነዚህ መንግሥታት በማያቋርጥ ግጭት ውስጥ መኖራቸው፣ በመካከላቸው ጽኑ የሥልጣን መቀያየር እንዲከሰት መንስኤ ነበር።

የሚከተሉት ጥቅሶች በመንግሥታት መሃል የሚነሡ ሁከቶችን ለማሳየት ጎርፍ እና ማዕበልን ጥቅም ላይ ሲያውሉ ይስተዋላል፡ መዝ. 65:5–8፣ ኢሳ. 17:12- 13፣ ኤር. 46:7-8።

በአንጻሩ፣ የተስፋይቱ ምድር በአሕዛብ መንግሥታት መሃል ብትሆንም እንኳ፣ ይህች ጽኑ በሆነው የእግዚአብሔር መንግሥት መሠረት ላይ የተገነባች ቅዱስ አገር፣ ዙሪያዋን ከከበቧት ዓመፀኛ ብሔራት በተቃራኒ የሰላምና የደህንነት ደሴት ሆና ቢያንስ ለተወሱ ዘመናት ኖራለች። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዳን. 7፡1-3። በዚህ ትዕይነት ውስጥ በርካታ እንቅስቃሴዎች ገቢራዊ ሆነዋል። በመጀመሪያ ከባሕር እንደ ተነሣው አውሬ ካሉ ሥዕላዊ መግለጫዎች የምናገኛቸው ትምህርቶች ምንድን ናቸው?



ዳንኤል የአሕዛብን ጦርነት ትርምስ ከባሕሩ ዳርቻ እየተመለከተ እያለ አራዊቱ በድንገት ወደ ምድሪቱ ይኸውም ወደ እርሱ ግዛት መምጣት ጀመሩ! የአህዛብ ችግሮች አሁን የገዛ ሕዝቡ ችግሮች ሆነዋል። እንደ አሕዛብ መኖርን ስለመረጡ፣ አሁን እንደ አሕዛብ (እና ከእነርሱ በታች) ይኖራሉ። ከባቢሎን አገዛዝ አንስቶ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ ፍጹም የተሟላ ወይም ለረጅም ዘመን የሚዘልቅ የራስ ገዝ አስተዳደር ዳግም አግኝቶ አያውቅም።

ዛሬ የእግዚአብሔር የሕዝብ ያጣው የራስ ገዝ አስተዳደር፣ ክርስቶስ በመጨረሻ ወደ ቀደመ ማዕረጉ ተመልሶ ንጉሣችን እስከሚሆን ድረስ ይቀጥላል።

በአዲስ ኪዳን፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የአረማዊው ሮም ተተኪ በሆነው በትንሹ ቀንድ ስደትና መከራ መቀበላቸውን ቀጠሉ።

ምንም እንኳ ከታሪክ እንደምንመለከተው፣ አንዳንድ ሕዝቦች ከሌሎች የተሻሉ፣ አንዳንድ ዘመናት ደግሞ አብልጠው ሰላም የሰፈነባቸው ሆነው ቢያልፉም፣ ግዙፍ ዘመናትን ያካተተው የአገሮች፣ የሕዝቦች እና የመንግሥታት ታሪክ—እሸት ቀጠፍክ ጎመን ቀነጠስክ ብሎ አሳር ከሚያሳየው ከአንደኛው ዘግናኝ ሥርዓት ወደ ሌላኛው፣ ከአምባ ገነኑ ወደ ጨቋኙ—የሚገላበጥ ሆኖ እናገኘዋለን። የሚገርመው ይህ ብዙውን ጊዜ የሚፈጸመው ለገዛ ሕዝባቸው የተሻለ ራእይ እንዳላቸው በሚናገሩ ገዢዎች መሆኑ ነው። ሕዝቡ እግዚአብሔርን ንጉሡ አድርጎ ቢመርጠው፣ ለእነርሱ የነበረው ሀሳብ ምንኛ የተለየ ነበር! ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 3፡10-19። እነዚህ ጥቅሶች ስለ ዓለማችን አስፈላጊውን ማብራሪያ እንድናገኝ እንዴት ይረዱናል? በተለይ ቁ. 19 ወንጌል በሕይወታችን እጅግ ወሳኝ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

ሚያዝያ 22
Apr 30

በምድር እና በባሕር መካከል


በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በተለይ ትንቢት ነክ መልእክቶች ላይ የየብስ ወይም የደረቁ ምድር እና የባሕር በተምሳሌትነት መጠቀስ አስተማሪነት አለው። በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ልዩነታቸው በጉልህ የሚታየውን የምድር እና የባሕር ተምሳሌቶች ልብ ብለው ይመልከቱ።

“በተምሳሌታዊው አቀራረብ፣ ምድር እና ባሕር ጎን ለጎን ሲቀመጡ፣ ምድር ብዙውን ጊዜ በሥርዓት የሚመራውን ዓለም ወይም የእስራኤልን ምድር ይወክላል። ባሕር በየብስ ላይ አደጋ እንዳያስከትል ስጋት እንደሆነ ሁሉ፣ ስጋት የሆኑትን የአሕዛብ መንግሥታት ይወክላል።”—Beatrice S. Neall, “Sealed Saints and the Tribulation,” in Symposium on Revelation, Book 1, ed. Frank B. Holbrook, (Silver Spring, MD: Biblical Research Institute, General Conference of Seventh-day Adventists, 1992), p. 260.

በዚህ እሳቤ፣ ምድር በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ የተመሠረተ የመረጋጋት ስፍራ ሲሆን፣ ባሕሩ በሰው ትምክህት ላይ የተመሰረቱትን የመንግሥታት አለመረጋጋትና ሁከት ያሳያል። ከላይ ለተገለጸው ሀሳብ መነሻ የሚሆኑንን የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 12፡15-16፣ 13፡1፣11። የምድርን እና የባሕርን ጎን ለጎን አቀማመጥ ልብ ይበሉ። እንዴት ነው ጥቅም ላይ የዋሉት? ትንቢትን እንዴት መረዳት እንደምንችል አስመልክቶ ምን ያስተምሩናል?



ዘንዶው ሴቲቱን (ቤተ ክርስቲያንን) ለማሳደድ ውኃ እንደሚጠቀም ልብ ይሏል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ ከትንቢት አኳያ ውኃ ብዙውን ጊዜ ዓለማዊ መንግሥታትንና እነርሱን በተደጋጋሚ የሚጎበኛቸውን ሁከትና ብጥብጥ ይወክላል።

በአብዛኛው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሰይጣን ብዙሃኑን ተጠቅሞ በገዛ መሪዎቻቸው ገፋፊነት እንዴት የእግዚአብሔርን ሕዝቦች እንዳሳደደ መመልከት እንችላለን።

በተጨማሪ ራእ. 12፡16 አማኞች አዲስ ወደ ተገኘው አህጉር በስደት ስለ መፍለሳቸው እንደሚናገር ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች አስተውለዋል። ስለ የብስ እና ባህር ያለን ግንዛቤ ትክክል ከሆነ፣ ይህ ስለ አሜሪካ ሪፐብሊክ መመሥረት ምን ይላል?

“የተስፋይቱ ምድር” ለእግዚአብሔር ሕዝቦች የተለየች ስፍራ እንደነበረች ሁሉ፣ በጥቅሱ የቀረበውን “ምድር” በተመሳሳይ መውሰድ እንችል ይሆን? ከምድር የወጣው አውሬ መጀመሪያ ላይ እንደ በግ ይመስል የነበረው ለዚህ ይሆን? ምንም እንኳ አንዳንድ ቀደምት የአሜሪካ መስራቾች ምድሪቱ እንደ “አዲሲቱ እስራኤል” ተደርጋ እንድትታይ የነበራቸው ምኞት ሳይሰምር ቢቀርም፣ ነገር ግን ለረጅም ዘመናት የኃይማኖት ጭቆና እና ወከባ ሲደርስባቸው ለኖሩ በሚልዮን ለሚቆጠሩ የዓለማችን ሕዝቦች የኃይማኖት ነጻነት የሚከበርባት ምድር ሆና ቆይታለች።

የሚያሳዝነው፣ ይህ እንደ በግ የሚመስል አውሬ አንድ ቀን “እንደ ዘንዶ” ይናገራል (ራእ. 13፡11)። የኃይማኖት ስደት ሲደርስባቸው ለኖሩ ወገኖች የነፃነት ችቦ ሆና የኖረችው ዩናይትድ ስቴትስ፣ ቀንደኛዋ የኃይማኖት አሳዳጅ ትሆናለች! ይህ ሰብዓዊው ዘር እግዚአብሔር ንጉሡ ሆኖ እንዲገዛው ከመምረጥ ይልቅ ራሱን በራሱ ለመግዛት ሲመርጥ ሊከሰት የሚችለውን የሚያሳይ ሌላው ምሳሌ ነው።

ሚያዝያ 23
May 1

እንደገና ትንቢት መናገር


በአስራ ሰባተኛው እና በአሥራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የኃይማኖት ነጻነት ለማግኘት አጥብቀው ይሹ የነበሩ በርካቶች የሚኖሩበትን አገር እየጣሉ ወደ አዲሱ ምድር ተሰደዱ። ትሩፋኗ ቤተ ክርስቲያን የተወለደችው በዚሁ በአዲሱ ምድር ነበር። በሌሎች ስፍራዎች ከተስተዋሉ የረጅም ዘመን ኃይማኖታዊና ፖለቲካዊ መሰናክሎች አንፃር ይህ በአዲሱ ምድር ወይም ኋላ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ በመባል በምትታወቀው አገር የተደረገ እንቅስቃሴ በሌላ አካባቢ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲህ እንደሚታየው ፈጣን ወይም ብርቱ ሆኖ ባልወጣ ነበር። ስለ ንቅናቄው መወለድ የሚገልጹትን የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 10፡ 1-11። ቀደም ሲል ያጠናናቸውን እንደ “ሕዝቦች” ምድር እና ባሕር ያሉ የጉዳዩን አላባዎች በጥቅሶቹ ይፈልጉ። በዘገባው ምን ዓይነት ብርቱ ግንዛቤዎችን መጨበጥ ይችላሉ?



እንደ ራእይ 14 የሦስቱ መላእክት መልእክት እና በራእይ 18 እንደ ቀረበው መልአክ ሁሉ፣ እዚህም ላይ መልአኩ በታላቅ ድምጽ ይናገራል። ይህ ትሩፋኗ ቤተ ክርስቲያን በታሪክ “ስለ ብዙ ሕዝቦች፣ ወገኖች፣ ቋንቋዎችና ነገሥታት” (ራእ. 10፡11) ሲባል እንድትሠራ የተቋቋመችበት አስቸኳይ እንቅስቃሴ ነው።

መልአኩ የዳንኤል መጽሐፍ ሊሆን እንደሚችል የሚታሰብ ትንሽ ጥቅልል “መጽሐፍ” (ዳን. 12፡4) የያዘ ሲሆን፣ መጽሐፉ የተከፈተው ከአያሌ ትውልድ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። አንደኛው እግሩ በባሕር ላይ ሌላኛው ደግሞ በምድር ላይ ቆመው ነበር። ይህ ደግሞ—መልእክቱ አሮጌውንም ሆነ አዲሱን ዓለም ይሸፍናል የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ አመላካች ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ይህ መልእክት ለሕዝቦች ሁሉ ማለትም በምድር ላይ እና በ “አሕዛብ” ባሕር ውስጥ ለሚኖሩ— የሚለውን ሐሳብ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

በመጨረሻ ምድርም ሁሉ ከእግዚአብሔር ክብር የተነሣ ታበራለች፣ የፍጻሜው መልእክት የሆነው ራእ. 14 ወደ እያንዳንዱ ሰው ይደርሳል። ከእስራኤል በተመሳሳይ፣ እኛም እንደ ቤተ ክርስቲያን ባለን ኃላፊነት ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን የመንግሥትን ወንጌል ለዓለም ሁሉ እንሰብካለን ከዚያም መጨረሻው ይመጣል (ማቴ. 24፡14)።

እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ታሪክ—ወደ ሰብዓዊው ፍጡር የግዛት ዘመን ፍጻሜ እና ዘላለማዊው የክርስቶስ ንግሥና እየገፋው ይገኛል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዳን. 2፡34-35፣44-45። ምድራዊ መንግሥታት፣ አስቀያሚ ቅርሶቻቸው ሳይቀሩ እንደሚወገዱና ኃጢአት፣ መከራ፣ በሽታ፣ ክፋትና ሞት ዳግመኛ በማይነሣበት በእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት እንደሚተኩ መጽሐፍ ቅዱስ በማያሻማ መልኩ ፍጹም ግልጽ አድርጎ ያስቀምጥልናል። የዳንኤል 2 እና 7 ትንቢቶች፣ ስለ ዓለም መንግሥታት መነሣት እና መውደቅ ምን ያህል በትክክል እንደተነበዩ ይመልከቱ። የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈበትን ዘመን ስናስብ የመልእክቱ ፍጹም ትክክለኛነት የሚያስደንቀንና በመጨረሻው ዘላለማዊ የእግዚአብሔር መንግሥት ተስፋ ላይ እንድንታመን የሚረዳን ለምንድን ነው?

ሚያዝያ 24
May 2


ተጨማሪ ሀሳብ


“የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት” በሚል ርዕስ ከተተረጎመው የኤለን ጂ. ኋይት መጽሐፍ “የባቤል ግንብ” (ገጽ፡ 125-132) የተሰኘውን ምዕራፍ ያንብቡ ።

“ ‘ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያዪቱ ምድር ዐልፈዋልና’ ” (ራእ. 21፡1)። ኃጥአንን የሚበላው እሳት ምድርን ያነጻታል። እያንዳንዱ የእርግማን ርዝራዥ ሳይቀር ይወገዳል። የተዋጁትን በአስፈሪው የኃጢአት መዘዝ በፍርሐት እያራደ የሚኖር ለዘላለም የሚነድ እሳት የለም።

“አንድ ማስታወሻ ብቻ ይቀራል፦ አዳኛችን ለዘላለም የስቅላቱን ጠባሳ እንደያዘ ይኖራል። በቆሰለው ራሱ፣ በጎኑ፣ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ብቻ ኃጢአት ያመጣው ጨካኝ ሥራ ምልክት ይቀራል። ክርስቶስን በክብሩ ሲመለከት ሳለ ነብዩ እንዲህ አለ፦ “ፀዳሉ እንደ ብርሃን ነው፤ ጨረር ከእጁ ወጥቶአል፤ ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል” [እንባ 3÷4]። ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀው ቀዩ ጅረት የወጣበት ያ የቆሰለ ጎን- የአዳኙ ክብር እዚያ ነው። “ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል።" "ለማዳን የበረታ’ው [ኢሳ 63፥1]፤ በመዋጀት መስዋዕት አማካኝነት የእግዚአብሔርን ምሕረት ባቃለሉት ላይ ፍርድን ይተገብር ዘንድ ብርቱ ሆነ። የመዋረዱ ምልክቶችም የእርሱ የክብሩ ከፍታ ጥግ ናቸው፤ ወደፊት ባሉት የዘላለም ዘመናት የቀራንዮ ቁስሎች | ምስጋናውን ይገልጣሉ፤ ኃይሉንም ያውጃሉ።” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ፡ 769)


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ማንኛውም ምድራዊ ስኬት የቱንም ያህል ታላቅ፣ አስደናቂ ወይም እጅን ማንኛውም ምድራዊ ስኬት የቱንም ያህል ታላቅ፣ አስደናቂ ወይም እጅን በአፍ የሚያስጭን ሊሆን ቢችል እንኳ—ወደ አፈር ብሎም ወደ አመድነት ይለወጣል። ውሎ አድሮ ፍጻሜው ለዘላለም በድል መነሣት ይሆናል። ይህ ደግሞ እርስዎ ያከናወኗቸውን ወይም እያከናወኑ የሚገኙትን ማንኛውንም ታላቅም ሆነ የከበረ ምድራዊ ነገር ያካትታል። ሁሌም ቢሆን ይህን አመለካከት ማስታወስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ አተያይ ቅድሚያ ሊሰጧቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጡ ዘንድ እንዴት ይረዳዎታል?

2. በራእ. 13፡1-10 ከባሕር ስለ ወጣው አውሬ የቀረበውን መልእክት በራእ. 13፡1-10 ከባሕር ስለ ወጣው አውሬ የቀረበውን መልእክት በጥንቃቄ ይመልከቱ። ይህ አውሬ የባቤል እሳቤ ተፈጥሮአዊ መዘዝ የሆነው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ከባቢሎን አንስቶ እስከ ትንሹ ቀንድ ኃይል ያሉት ሰብዓዊ "መንግሥታት" አጠቃላይ ድምር መሆኑ ግልጽ ነው። ለዘመናት በቀጠለው የእያንዳንዱ መንግሥት ባህሪ ምን ታዝበዋል? ለአብነት ያህል ዓለም ዛሬም ቢሆን፣ የባቢሎንን ወይም የሮምን እሴቶች በየትኞቹ መንገዶች እያንጸባረቀች ትገኛለች?

3. እኛ እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ሕዝብ፣ ጌታን በመከተል እኛ እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ሕዝብ፣ ጌታን በመከተል እና የምንኖርበትን የትኛውንም አገር ወይም መንግሥት ሕግጋት በመታዘዝ መካከል ያለውን ትክክለኛ ሚዛን ጠብቀን መጓዝ የምንችለው እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL