የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ፍንጮች፣ ምስሎች፣ ምሳሌዎች፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ማጥኛ መንገድ



2ኛ ሩብ ዓመት 2025


መጋቢት 27 - ሚያዝያ 3

2ኛ ትምህርት

Apr 5 - 11




ዘፍጥረታዊው መሠረት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 40:7-8፣ ዘፍ. 22:1–13፣ ዮሐ. 3:16፣ ራእ. 5:5–10፣ 1ቆሮ. 15:15–19፣ ራእ. 12:1–9።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ዮሐንስ በማግስቱም፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ. 1፡29)።

በዚህ ዘመን እንደ ራእይ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በመፍታት ረገድ ከሚስተዋሉ ቁልፍ ችግሮች አንዱ የመጽሐፉን ዕድሜ ጠገብ ምንጮች መገንዘብ አለመቻል ነው። ጸሐፊው ስለ ብሉይ ኪዳን የካበተ ዕውቀት ያለው ከመሆኑ አኳያ፣ በአንባቢዎቹ ዘንድ በአግባቡ ሊታወቁ የሚችሉ ጽንሰ ሐሳቦችን ጥቅም ላይ ሲያውል ይስተዋላል። በራእይ መጽሐፍ ለማጥናት ከምንፈልጋቸው ክፍሎች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን ጥቅሶች ለማግኘት መላውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች ማሰስ ጠቃሚ ቢሆንም፣ አንዳንድ ጥቅሶች ሊሰጡ ከሚችሏቸው ጥቅሞች በተሻለ መጽሐፉን ለመረዳት የሚያስችሉ ዋና ዋና ክፍሎች መኖራቸውን ማስተዋል ጠቃሚ ነው። ይህ በተለይ የዘፍጥረት መጽሐፍ ሐቅ ነው።

ምክንያቱም መጽሐፉ ዓለማችን ወደ ኃጢአተኛ ሥርዓተ አልበኝነት ትርምስ ውስጥ ሰተት ብላ መግባቷን ገና ከጅምሩ ዘግቦታል። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ቁልፍ ጽንሰ-ሐሳቦች በሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተጠቅሰዋል።

በዚህ ሣምንት ከራእይ መጽሐፍ አንኳር ጽንሰ ሀሳቦች መሃል እፍኝ ያህሉን ዘገን አድርገን እናጠናለን። መጽሐፉን የሚያጠና ተማሪ ከራእይ ጀርባ ያሉትን ጥንታዊ መሰረቶች መረዳቱ፣ በጥቅሶቹ ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን በቀላሉ የማይለዩ የትርጉም ልዩነቶች እንዲያይ ያስችለዋል—የሚለውን ወሳኝ ነጥብ ለመግለጽ፣ ከበርካታዎቹ መሃል በጣም ጥቂቶቹን እንመርጣለን። ከእነዚህም ውስጥ እያንዳንዳቸው ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ፣ ስለ እግዚአብሔር እና በአጽናፈ ሰማይ ብሎም በህይወታችን እየተካሄደ ስላለው ግጭት ጠቃሚ ትምህርቶች ሊሰጡ ይችላሉ።

መጋቢት 28
Apr 6

“በመጀመሪያ የተጠቀሰ”—መርኅን መከተል


አብዛኛዎቹ የአካዳሚክ መርኅ ግብሮች የሚጀምሩት በአጠቃላይ የዳሰሳ ኮርስ ("101") ነው። ይህ ኮርስ ሰፊ እና መሰረታዊ መርኅዎችን የሚሸፍን እንደመሆኑ፣ ትምህርቱን በጥልቀት ለመመርመር በሚደረግ እንቅስቃሴ ለ

ተጨማሪ ሀሳብ


መሰረት ይሆናል። በተመሳሳይ አንድ ሰው መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ፣ እግዚአብሔር በዘፍጥረት መጽሐፍ አጠቃላይ የዳሰሳ ኮርስ ማስቀመጡንና በዚህም በተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ በጥልቀት የሚመረመሩ ሐሳቦችን ማስተዋወቁን ብዙም ሳይቆይ ይገነዘባል።

በጥቅሉ ሲታይ፣ አንድ ጽንሰ ሐሳብ ወይም ተምሳሌት በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጠቀስና ይህም የተስተዋለው በተለይ በዘፍጥረት የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ከሆነ፣ ኋላ ላይ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል ለማስተዋል የሚረዳዎትን የጽንሰ ሀሳቡን ጠቅለል ያለ መረዳት አግኝተዋል ማለት ነው።

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህን ዘዴ “በመጀመሪያ የተጠቀሰ— ሕገ ደንብ" በማለት ይጠሩታል። ሆኖም ከሕገ ደንብ ይልቅ—መርኅ ይበልጥ በአግባቡ ይገልጸዋል። ምክንያቱም ከሕገ ደንብ አኳያ ሊቆጠሩ የማይችሉ አያሌ ጉዳዮች በመኖራቸው ነው። አጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የትንቢት ጥናት በምናደርግበት ወቅት የምናገኘው ንድፍ—እግዚአብሔር ከመሠረታዊው ጽንስ ሀሳብ በመጀመር በጊዜ ሂደት፣ በተገቢው መረጃ ልጆቹን በዝግታ እየመገበ፣ ዓመታት ብሎም ምዕተ ዓመታት በተጨመሩ ቁጥር ደግሞ ደጋግሞ እያሳደገና እያስፋፋ እንደሄደ ያሳያል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 40:7-8፣ ሚልክ. 3:6፣ ዕብ. 13:8። በትንቢት ዙሪያ የሚያደርጉትን ጥናት በትክክል ማጠናከር ይችሉ ዘንድ ከጥቅሶቹ ማግኘት የሚችሉት መሠረታዊ መርኅ ምንድን ነው?





አብዛኛው ዘመናዊው ዓለም ስለ “እውነት” ከመናገር ይልቅ “የግዴታ እውነት ባይሆንም እንኳ እውነተኛ መስሎ ስለ መታየት ወይም ስለ መምሰል” መናገር ይቀናዋል። ምክንያቱም “እውነት” በጊዜ ሂደት ሊለወጥ የሚችልና በቀላሉ ተጽእኖ ላይ የሚወድቅ ተደርጎ ይቆጠራል። ወይም ደግሞ፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ ራሱ የ“እውነት” ጽንሰ-ሐሳብ ከተጠርጣሪነት ጎራ ስለሚመደብ ነው።

ሆኖም እውነትን ያጸናው እግዚአብሔር አምላክ ሐሳቡን ሲለውጥ አይታይም። እርሱ ሕዝቡን አንዴ እውነት ማስተማር ከጀመረ በኋላ ተመሳሳይነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መርኅዎች ወይም ርዕሰ ጉዳዮች ተደጋግመው መቅረባቸው ትርጉሙን አይቀይረውም። እንደውም በተቃራኒው በፍቺው ላይ ተጨማሪ ብርሃን ለመፈንጠቁ መተማመን እንችላለን። ይህ ደግሞ ትንቢትን ለማጥናት ለሚደረግ ጥረት ፋይዳ ያለው ትርጉም ይሰጣል። ስለዚህ በርካታ ቁልፍ ጽንሰ ሀሳቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ተገልጸው በሚመለከቱበት በዘፍጥረት መጽሐፍ ግንዛቤ ላይ የተሻለ ማስተዋል ያገኙ ዘንድ፣ የተቀረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲመረምሩ ያን መጀመሪያ የተረዱበትን መሰረት ጥቅም ላይ ከማዋል ወደ ኋላ አይበሉ። ማንም ሰው ወይም ማንኛውም ነገር የቱንም ያህል ልዝብ ወይም ምክንያታዊ ሊሆን ቢችል እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ እና ይኸው ቃሉ በሚያስተምራቸው የማይሳሳቱ እውነቶች ላይ ያለንን እምነት እንዲያዳክምብን አለመፍቀዳችን በእጅጉ ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ መዳከም ሊከሰት የሚችልባቸው ስውር መንገዶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

መጋቢት 29
Apr 7

የእግዚአብሔርን ፍቅር መረዳት


ኃጢአተኛውን ተፈጥሮ መውረስ ማለት ስለ ዩኒቨርስ ያለን አመለካት ለራስ ወዳድነትና መታበይ ባለን ዝንባሌ ተበክሏል እንደ ማለት ነው። ዓለምን የምንመለከተው ሁሉን አዋቂ ከሆነው አምላክ አኳያ ሳይሆን ከገዛ ራሳችን ውሱን አይታ አንጻር ነው። ምናልባት ኃጢአተኛው ሰብዓዊ ዘር “ፍቅር” ላይ የያዘው ዓይነት የተዛባ አመለካከት በሌላ በየትኛውም ጽንሰ ሀሳብ ላይ አላደረሰ ይሆናል።

በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ባሕል ለሌሎች ሳይሆን—በገዛ ራሳችን እርካታ ላይ ያነጣጠረ የፍቅር ግንዛቤን ለማስፋፋት ሲጥር ይስተዋላል። ይህ ራስ ወዳድነትን ያማከለ አመለካከት እግዚአብሔር በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት ለመረዳት አስቸጋሪ ያደርግብናል።

የፍቅርን ተፈጥሮአዊ ባህሪ መረዳት የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ለማስተዋል የሚረዳ ቁልፍ መሣሪያ ነው። በታላቁ ተጋድሎ ከተነሡ አበይት ጭብጦች አንዱ በእግዚአብሔር ባሕሪ ዙሪያ የተሳሳተ ግንዛቤ መያዝ ነው። ኤለን ጂ. ኋይት ታላቁ ተጋድሎ በመባል በሚታወቀው መጽሐፏ ማጠቃለያ ላይ የሚከተለውን ጽፋለች፡ “ታላቁ ተጋድሎ (ተቃርኖ) አብቅቷል። ኃጢአትና ኃጢአተኞች ከእንግዲህ የሉም። መላው ዩኒቨርስ ንፁህ ነው። አንድ የመስማማትና የደስታ ትርታ በሰፊው ፍጥረት ሁሉ ይመታል።

ወሰን በሌለው ህዋ ዳርቻዎች ሁሉ ሕይወት፣ ብርሃንና ደስታ ሁሉን ከፈጠረ ከእርሱ ዘንድ ይፈሳሉ። እጅግ ደቃቅ ከሆነችው ክፍለ-ቁስ (atom) እስከ ግዙፉ ዓለም፣ ሕይወት ያለውም ሆነ ሕይወት የሌለው፣ ባልደበዘዘ ውበታቸውና ፍፁም ደስታቸው፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነው ብለው ያውጃሉ።” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ፡ 774)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 22፡1-13። በመጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር” የተሰኘው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በዘፍ. 22፡2 ላይ ነው። ታሪኩ አምላካዊውን የፍቅር ባህሪ አስመልክቶ ምን ያስተምረናል?



አንድ ጽንሰ ሀሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጽፎ ለመጀመሪያ ጊዜ ከማግኘት በተጨማሪ፣ ያው ተመሳሳይ ጽንሰ ሀሳብ በተለይ በወንጌል መጻሕፍት ተጠቅሶ መመልከት ጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ አለ። ማቴ. 3:17፣ ማር. 1:11፣ ሉቃ. 3:22፣ ዮሐ. 3:16—“ፍቅር” ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰባቸውን ስፍራዎች ናቸው።

ለአብነት ያህል “ፍቅር” በዮሐ. 3፡16 ለመጀመሪያ ጊዜ መጠቀሱ የእውቀት ብርሃን በመፈንጠቅ፣ በመሰዊያው ላይ ተንጋሎ የተገለጸውን የይስሐቅን ታሪክ የሚያመለክትይመስላል። አብርሃም በእግዚአብሔር ላይ የነበረው እምነት በፍጹም መተማመን ላይ የተመሰረተ ስለነበር ልጁ መሥዋዕት ቢሆን እንኳ ሊያስነሣው እንደሚችል ማመንን መረጠ (ዕብ. 11፡19)። ይህም እግዚአብሔር ለሰብዓዊው ዘር ያለውን ፍቅር ያሳየ ጥላ ነበር። እግዚአብሔር እኛን የወደደን “የሚወድደውን… ልጁን፣ ያውም አንዱን ልጁን” (ዘፍ. 22፡2፣12፣16) እስከ መስጠት ነው። ከዚያም ከሞት አስነሣው። በመሆኑም፣ እግዚአብሔር ራሱን መሥዋዕት አድርጎ እስከ መስጠት የደረሰውን ለአኛ ያለውን ይህን ፍቅር ገለጠልን። እግዚአብሔር ለእኛ የገለጸውን ራስን መሥዋዕት አድርጎ የሰጠ ዓይነት ፍቅር ለሌሎች ማሳየት የምንጀምረው እንዴት ነው? እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በብዙዎቻችን ዘንድ እንደ መሠረታዊ ጉዳይ የማይታየው ለምንድን ነው?

መጋቢት 30
Apr 8



የይስሐቅ ጥያቄ፡ የመሥዋዕቱ በግ ወዴት ነው?


መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሴህ (በዕብራይስጥ፡ በግ) ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅሶ የምንመለከተው—ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ፍቅር በተጠቀሰበት የዘፍ. 22 ታሪክ ውስጥ ነው። እርግጥ ነው፣ ይህ ጠቦት—የሱስ ከሃያ ጊዜ በላይ “በጉ" ተብሎ በተጠራበት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙ ያለማቋረጥ ከተጠቀሱ ምልክቶች መሃል አንዱ ነው። በራዕይ ዮሐንስ እጅግ ብርቱ ከሆኑ ትዕይንቶች መካከል አንዱ በሆነውና ዮሐንስ የእግዚአብሔርን ዙፋን በጎበኘበት ምዕ. 4 እና 5 በጉ ማዕከላዊውን ሚና ይጫወታል። ጥቅሶቹን ያነብቡ፡ ዘፍ. 22፡7-8፣ ዘጸ. 12:3–13፣ ራእ. 5:5–10።

ይስሐቅ መሥዋዕት ከመሆን ለጥቂት የተረፈበት ታሪክ ጠቦቶች ምሳሌ በመሆን ጥቅም ላይ መዋላቸውን መገንዘብ እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው? ይህ ታሪክ ዮሐንስ በራእ. ምዕ. 5 ከተመለከተው ጋር እንዴት ይያያዛል?



በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሴህ (በግ) ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው፡ “የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት ነው?” በሚለው የይስሐቅ ጥያቄ ነበር (ዘፍ. 22፡7)። የሚገርመው፣ የተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለዚህ ጥያቄ በዝርዝር መልስ ሰጥቷል። የተቀሩት 38 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከፋሲካ ሥርዓቶች እስከ ዳዊት ቀደምት ንግሥና እና ከዚያም በኋላ ያሉትን በማካተት፣ የይስሐቅ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ መልስ ወደሚያገኝበት ዝርዝር እና ታዳጊ ቅደም ተከተሎች አንባቢውን ይመራሉ። መላው ታሪክ ይስሐቅ ላቀረበው ጥያቄ ምላሹን አሻግረው በሚያዩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መሲሐዊ ትንቢቶች የተሞላ ነው። ከዚያም በአዲስ ኪዳን— የሱስ በሥጋና በደም ሲገለጥ፣ በሕዝቡ መካከል ሆኖ ሲያገለግልና በመጨረሻም በመስቀል ላይ ሕይወቱን ሲሠዋ ጥያቄው መልስ ያገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዮሐንስ ወንጌል ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ በግ የተጠቀሰውን ይመልከቱ ዮሐ. 1 29–34። ከሁኔታው እንደምንገነዘበው መጥምቁ ዮሐንስ ይስሐቅ ለጠየቀው ጥያቄ በግል መልስ እየሰጠው ይመስላል።

ኃጢአተኞች ንስሐ ገብተው በጥምቀት በጥልቅ ውሃ ውስጥ መቀበራቸው፣ የኃጢአተኛውን ሞት እና የአዲስ ሕይወት ጅማሮ ያመለክታል። በዚሁ ዐውድ፣ የእግዚአብሔር በግ የሆነው የሱስ በድንገት ተገልጦ በማቴዎስ ዘገባ መሠረት፡ “እነሆ፤ ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።” (ማቴ. 3፡17)። ለአብርሃም እና ይስሐቅ ችግር መፍትሔ ይሆን ዘንድ እነሆ ይህን ከሰማይ የታወጀ ድምፅ ልብ ይሏል (ዘፍ. 22፡11-14)።

እንደ ጥሩ ሸማኔ እያንዳንዱን ድር ከማግ እያጋጠሙ ሁሉንም ሸምነው ሲጨርሱ፣ የእግዚአብሔር በግ የሆነው የሱስ የእኛ ምትክ መሆኑ ግልጽ ሆኖ ይወጣል። ይህ ደግሞ በዮሐንስ ራእይ የታረደው በግ ባለን ግንዛቤ ላይ ብርቱ ብርሃን ይፈነጥቅልናል። የሱስ በእኛ ምትክ መሥዋዕት መሆኑን ማወቃችን የመዳናችን ብርቱ መሠረት የሆነው ለምንድን ነው? ያለ እርሱ ምትክ መሥዋዕትነት በተለይ በፍርድ ቀን ምን ተስፋ ይኖርዎት ነበር?

ሚያዝያ 1
Apr 9

ሞትን መጋፈጥ


ምናልባት ከፈጣሪው በተነጠለ ዓለም ውስጥ የመኖር እጅግ አስከፊው ገጽታ፣ ሞት በማንኛውም ጊዜ ሰብዓዊውን ፍጡር ለመምታት ዝግጁ ሆኖ እያደባ በእያንዳንዱ ሕይወት ተሰውሮ የተቀመጠበት መንገድ ሳይሆን አይቀርም። “የኃጢአት ደሞዝ”— በአጽናፈ ዓለም ከሚገኝ ብቸኛው የሕይወት ምንጭ ማለትለም ከፈጣሪ አምላክ በመለየታችን የምንከፈለው ቅጣት ነው። ይህ ተጨባጭ እውነታ ከመሆኑ አንጻር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ መፍትሔው የሚገኘው በየሱስ ይኸውም በሞቱና ትንሣኤው ብቻ እንደመሆኑ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሞት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጹት ነገሮችም ሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመበት ሁኔታ በትንቢታዊው አበይት ጭብጥ ላይ በርካታ ብርሃን በመፈንጠቅ የኃጢአትን ችግር ከባድነት እንድንገነዘብ ይረዳናል።

እንዲሁም እግዚአብሔር ለችግሩ የሰጠውን መፍትሔ ለመረዳት የሚያስችሉ ዓይነተኛ መሣሪያዎች ይሰጠናል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 2፡15–17፣ ዘፍ. 4፡8–15፣ 1ቆሮ. 15፡15–19፣ ራእ. 1፡18። ሞት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበትንና የተከሰተበትን ጉዳይ የሚያካትቱት እነዚህ ጥቅሶች ሰዎች ለምን እንደሚሞቱ፣ እግዚአብሔር ሞትን እንዴት እንደሚመለከተውና እርሱ ለችግሮቻችን ስላለው መፍትሔ ምን ይነግሩናል?





ብዙውን ጊዜ “ሞት አንዱ የሕይወት ክፍል ነው” ብለን ስንናገር አንደመጣለን። ሆኖም ይህ ሐሰት ነው። ሞት የሕይወት ተቃራኒ ነው—የሕይወት መቀልበስ! ሞት የእኛ ተሞክሮ አካል ይሆን ዘንድ ፈጽሞ ያልታሰበ ሰርጎ ገብ ወራሪ ነው። ምንም እንኳ ሞትን የተለማመድን ቢመስልም፣ ሞት በራሱ አንድ መሠረታዊ የሆነ ችግር እንዳለው ሰብዓዊው ዘር በጋራ የተገነዘበ ይመስል ከፊታችን በተጋረጠ ቁጥር ልባችን በጽኑ ይቃወመዋል። ሞት አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም፣ ሮጦ ያልጠገበ ሕፃን ላይ ሲደርስ ግን እጅግ ልብ ሰባሪ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

በአብዛኛው፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በሞት ይቀድማሉ ብለን እንጠብቃለን። ያን ክስተት እንደ መደበኛ የነገሮች ቅደም ተከተል ተቀብለነዋል።

ሆኖም በቅዱሳት መጻሕፍት የተዘገበው የመጀመሪያው ሞት፣ የሚጠበቀውን የተለመደ ሁኔታ የሚቃረን ሆኖ እናገኘዋለን። ወላጅ የሆኑት አዳምና ሔዋን እርጅና ተጫጭኗቸው ሳያርፉ፣ ገና በሕይወት እያሉ ጻድቁ ልጃቸው በዓመጸኛ ወንድሙ የመገደሉ አሳዛኝ ክስተት ሐዘናቸውን መሪር አደረገው። በእርግጥም የአቤል አሟሟት ኢፍትሐዊ ነበር።

እንደ አቤል ሁሉ በዓመፀኞች የተገደለውን ጻድቁን የሱስም እንዲሁ አሰብ ያድርጉ። ለመሆኑ ከክርስቶስ የበለጠ ኢፍትሐዊ የሚባል አሟሟት የየትኛው ነው? በአቤል እና በክርስቶስ የመሥቀል ላይ ሞት መካከል ሌላ ምን ተመሳሳይ ነገሮችን ማግኘት ይቻላል? የአቤል ሞት ሁኔታ የሱስ ”የሞትና የሲኦል መክፈቻ” ቁልፍ እንዳለው ማስተዋል እንድንችል እንዴት ይረዳናል? የሞት ችግር እስካልተፈታ ድረስ ሕይወታችን ውሎ አድሮ ከንቱ፣ ትርጉም ዐልባና ረብ የለሽ የሚሆነው ለምንድን ነው? የሱስ ላደረገልን ነገር ምን ያህል አመስጋኞች መሆን እንዳለብን አ መሆን እንዳለብን አስመልክቶ ይህ እውነታ ምን ያስተምረናል? ስመልክቶ ይህ እውነታ ምን ያስተምረናል?

ሚያዝያ 2
Apr 10

እባቡ


የአምልኮ ጉዳይ በራእይ መጽሐፍ ቁልፍ ስፍራ ይዞ ይገኛል። “ዘንዶ” (ራእ. 13፡2-4) በሚል ስያሜ የተገለጸው ክፉ አድራጊና የሐሰት አምልኮ ሥርዓት አስፈጻሚ የሆነው የወደቀ ጠባቂ መልአክ፣ ይህን እባባዊ መገለጫ (መጠሪያ) በድንገት አልወሰደም። ይልቁንም እባብ ወደ አትክልቱ ስፍራ ገብቶ አዳምና ሔዋን እርሱን ተከትለው በፈጣሪ ላይ እንዲያምጹ ያሳመነበትን የኤደን ገነት ክስተት ግልጽ በሆነ አኳኋን ይጠቁመናል። ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዘፍ. 3፡1-5 እና ራእ. 12፡1-9። በእያንዳንዱ ዘገባ የምናገኛቸው የጋራ ባህሪ ያላቸው ጭብጦች የትኞቹ ናቸው? በዘፍጥረት መጽሐፍ መግቢያ እባቡን አስመልክቶ የቀረቡት ዝርዝር ጉዳዮች፣ ቀደም ሲል በራእይ መጽሐፍ የተገለጹትን በሰማይ ጦርነት ያስከተሉ አንዳንድ ጉዳዮች እንድንገነዘብ እንዴት ይረዱናል?



ሰይጣን መላውን ዓለም እንደሚያስት የተወሳባቸው ሁለት ዘገባዎች በቅዱሳት መጻሕፍት ተጠቅሰው እናገኛለን። በምድር ላይ ሁለት ሰዎች ብቻ ይኖሩ በነበረበት ዘመነ—ዘፍጥረት እና ሰይጣን “ዓለምን ሁሉ የሚያስተው” (ራእ. 12፡ 9) በሚል በተጠቀሰባቸው-ራእ. 12 እና 13፣ ለአውሬው ኀይል ታላቅ ሥልጣን በመስጠት “ዓለም በሙሉ” (ራእ. 13፡2-3) እንዲከተለው በሚያደርበት ስፍራ ላይ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ ከሚገኙት ጭብጦች አንዱ የታላቁ ተጋድሎ የማይለወጥ ባሕሪ ነው። የእግዚአብሔር ባሕሪ እና ቃል እንደማይለወጥ ሁሉ የሰይጣን ዕኩይ ምኞትም አይለወጥም።

ደግነቱ የታላቁ ተጋድሎ ባሕሪ ስለማይለወጥና በቅዱሳት መጻሕፍት ትንቢቶች ግልጽ የሆኑ የማመሳከሪያ ነጥቦች ስላሉን፣ ክርስቲያኖች አንዳድ አዝማሚያዎችን እየለዩና እየመረመሩ መንፈሳዊ ወጥመዶች የተጠመዱባቸውን ፈንጂ ወረዳዎች ለይተው ማወቅ ይችላሉ። እግዚአብሔር ሁሌም የማይለወጥ አምላክ እንደመሆኑ፣ የሰይጣን ባህሪም ይለወጣል ብሎ ማሰብ ተላላነት ነው። ሰይጣን አንድ ሺህ አንድ ካባ ሊደርብ ቢችልም፣ የሺዎቹ ዓመታት የወደቀው ሰብዓዊ ፍጡር ታሪክ—በራእይ ከተሳለው ትንቢታዊ ታሪክ ጋር ተዳምሮ በኤደን ሥራ ላይ ካዋለው የጨዋታ ሕግ ፈጽሞ ፍንክች እንደማይል ያሳያሉ። እግዚአብሔር ጥበብና ማስተዋል እንደሚሰጠን (ያዕ. 1፡5) እንዲሁም እውነት በሆነው ቃሉ እንደሚያስታጥቀን የገባልንን ቃል እናስታውስ እንጂ በዲያብሎስ የሐሰት ጋጋታ ተሰናክለን አንውደቅ። የሚያሳዝነው ብዙዎች በእነዚህ የሐሰት ቃላት ተሰናክለው ወድቀዋል። ወደፊትም በርካቶች እንደውም አብላጫው ሕዝበ ክርስቲያን የዚሁ እኩይ ማታለያ ሰለባ እንደሚሆን ይጠበቃል። ባህል በጊዜ ሂደት እንዴት ሊለዋወጥ እንደሚችል ልብ ማለት ተገቢ ነው።

የማኀበራዊ መስተጋብሮች መለዋወጥ ሲከሰት በአንድ ወቅት ተቀባይነት የነበራቸው ነገሮች በተቃራኒው ተቀባይነት የሚያጡ ይሆናሉ። የታላቁ ተጋድሎ መሠረታዊ ርዕሰ ጉዳዮችና ተዋናዮች የማይለዋወጡ ከመሆናቸው አንጻር፣ አንድ ክርስቲያን እየተቀየረ ያለውን የባህል ገጽታ ሲመረምር ምን ዓይነት ነገሮችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል? ለአብነት ያህል ዲያቢሎስ እንደማይሞቱ ይልቁንም እንደ እግዚአብሔር እንደሚሆኑ የተናገራቸው ዓይነት ያሉ የቀደሙ ውሸቶች ዛሬ በባህላችሁ ሲነገሩ ከወዴት ማድመጥ ይችላሉ?

ሚያዝያ 3
Apr 11


ተጨማሪ ሀሳብ


“The Revelation,” pp. 578–581 in The Acts of the Apostles.

የበርካታ ዓለም አቀፍ ኃይማኖቶች ቁርኝት ከጽንሰ ሀሳቦች ጋር ብቻ ሲሆን፣ በተቃራኒው በክርስትና ኃይማኖት ውስጥ የሚገኙ ጽንስ ሐሳቦች በታሪክ ክንውኖች ላይ ጠንካራ መሠረት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በዘመናት ከሰው ልጆች ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚገልጽ ታሪክ የያዘ ሰነድ ሲሆን፣ እነዚህን በሺዎች የሚቆጠሩ ዘመናት የፈጁ መስተጋብሮች በማጥናት ስለ እግዚአብሔር ጽኑ ባህሪ ብዙ መማር እንችላለን።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ነገር መስማት እየሰለቻቸው እንደሆነ በመግለጽ ሲያማርሩ ይደመጣሉ። አልፎ አልፎ በዓይነቱ ልዩ የሆነው ትንቢታዊ መልእክታችን በይፋ ሲሰበክ፣ ቀደም ሲል እንደ ሰማነውና ልንማር የምንችለው አዲስ ነገር እንደሌለ አድርገን እናስባለን።

መልእክታችን ዘወትር ቋሚና የማይለወጥ ነው ማለት ጉዳዩ ቀላል ወይም ፈታኝ አይደለም የሚል አንደምታ የለውም። እንደውም ከዚህ በተቃራኒ ነው። ከማይወሰነው አምላክ አእምሮ ወደ እኛ የተላለፉ መረጃዎችን በሚያጠኑ ጊዜ፣ የአንድን ርእሰ ጉዳይ መጨረሻ ሊደርሱበት እንደማይችሉ ለመገንዘብ ምንም ያህል ጊዜ አይወስድቦትም።

ኤለን ጂ ኋይት የራእይ መጽሐፍን ለመጻፍ ምክንያት እንደሆነ ከገለጸችባቸው መንስኤዎች አንዱ ቤተ ክርስቲያንን በታሪካዊ መልእክቶቿ መልሕቅ በዘመናት ሁሉ ተጠብቃ ትኖር ዘንድ ነው። “አንዳንድ ወጣት የወንጌል ሠራተኞች [በወቅቱ የነበሩ]... በተደጋጋሚ ይቀርቡ በነበሩ እውነቶች መሰላቸት ይታይባቸው ነበር። አዳዲስ እና አስገራሚ ክስተቶችን ለማግኘት ከነበራቸው ጽኑ ፍላጎት አኳያ አዳዲስ ኃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን ለማስተዋወቅ ሞከሩ።”—The Acts of the Apostles, p. 580. ስለዚህ የራእይ መጽሐፍ በዚያ መጠን ስለ ወደፊቱ ብቻ የሚናገር መጽሐፍ አይደለም። በተጨማሪም መሰረታችንን ፍለጋ ስንባዝን እንዳንስት—በቀደመው የእምነታችን ታሪክ ላይ ሥር እንድንሰድ ታስቦ የተዘጋጀ ስለ ቀደመው ዘመን የሚገልጽ መጽሐፍ ነው።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ቅዱሳን መጻሕፍት አዳዲስ መረጃዎችንና ግንዛቤዎችን ከመስጠት ወደኋላ ቅዱሳን መጻሕፍት አዳዲስ መረጃዎችንና ግንዛቤዎችን ከመስጠት ወደኋላ አይሉም። አንድ ሰው አዲስ ነገር ለመማር ያለውን ፍላጎት ቀድሞውኑ በተሰጡ የእውነት መልሕቆች ላይ ጸንቶ የመቆየት አስፈላጊነት ጋር ሚዛናዊ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?

2. ቤተ ክርስቲያን ለአዳዲስ የትንቢት ትርጓሜዎች እንዴት ምላሽ መስጠት ቤተ ክርስቲያን ለአዳዲስ የትንቢት ትርጓሜዎች እንዴት ምላሽ መስጠት ይኖርባታል? ምንም እንኳ ሁሌም ገና ብዙ የምንማረው ነገር እንዳለ ብናውቅም፣ አዲሱ ብርሃን የግድ አስፈላጊ መሆን አለመሆኑን ወይም የጊዜው ፋሽን (ወረት) አልፎ ተርፎም ስህተት መሆኑን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

3. በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በፓሲፊክ ውቂያኖስ ላይ ይሰፍ የነበረ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በፓሲፊክ ውቂያኖስ ላይ ይሰፍ የነበረ አንድ መርከበኛ ሊሞት በተቃረበበት ወቅት “እኔ ወላጅ የሌለኝ ብቸኛ ሰው ነኝ። ለመሆኑ ስሞት ማን ያስታውሰኛል?" ሲል አጠገቡ የነበረውን ሐኪም ጠየቀው። ሐኪሙም “እኔ ሁሌም አስታውስሃለሁ” ብሎ መለሰለት። ምንም እንኳ የሐኪሙ ቃላት መልካም ቢሆኑም፣ ውሎ አድሮ ሐኪሙም ሆነ የወላጅ አልባው መርከበኛ ትውስታ ይሸኛሉ። በስተመጨረሻ ሞት የሁሉም ነገር መደምደሚያ ከሆነ፣ ይህ ዘገባ መላው ሕይወታችን ከንቱና ትርጉም የለሽ መሆኑን እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL