የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኤር. 29:23-24፣ መዝ. 139:1–6፣ ዳን. 12:4፣ ራእ. 22:10፣ 2ጢሞቴ. 3:15–17፣ ዕብ. 4:12።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ ‘የሚመካ ግን፣ እኔእግዚአብሔር
እንደ ሆንሁ በማወቁና፣ በምድር ላይ ምሕረትን፣ ፍትሕንና
ጽድቅን የማደርግ መሆኔን በመረዳቱ፣ በዚህ ይመካ፤ እኔ በእነዚህ
ነገሮች እደሰታለሁና፤’ ይላል እግዚአብሔር” (ኤር. 9፡24)።
ክርስቲያኖች እንደ ሌሎቹ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ሁሉ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን
ትንቢት ለመፍታት መሞከር ጊዜ ከማጥፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም በሚል
እሳቤ በትንቢት ዙሪያም እንዲሁ ስምምነት የላቸውም። ለነገሩ ክርስቲያኖች
በእያንዳንዱ ትንቢት ነክ ነቁጥ ብሎም ርዕሰ ነጥብ ዙሪያ የሚፋለሙ ከሆነ፣ ቃሉ እንዴት
ተገቢና ጽኑ መሆን ይችላል? እንደ አለመታደል ሆኖ፣ በርካታ አማኞች እንደ ራእይ ያሉ
አንዳንድ መጽሐፎችን ሰው ያስተውለው ዘንድ የማይቻለው ብለው ፈርጀዋቸዋል።
አንዳን’ዴ ትንቢትን ማጥናት ከሚያስገኘው መፍትሔ ይልቅ የባሰ ችግር ያስከትላል
ብሎ የሚያስብ አንድ ፓስተር ጆሮአቸውን በሚኮረኩር ድምጸት የተናገረውን ቃል
መሰረት በማድረግ፣ መልእክቶቹን ከማንበብ ይልቅ ገሸሽ ያደርጓቸዋል።
ሆኖም ነገሩ ሁሌም ከላይ የቀረበውን ሀሳብ የሚጋራ አልሆነም። በክርስትና
ታሪክ አሥራ ስምንተኛው መቶ ከፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች
በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ዙሪያ አዎንታዊ አቋም መያዛቸውን ተከትሎ፣ ቁልፍ በሆኑ
ትንቢታዊ መልእክቶች ዙሪያ አስገራሚ የስምምነት ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር።
የእግዚአብሔር ዓላማም ይኸው ነው፡ “ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ መለያየት
እንዳይኖር፣ አንድ ልብ፣ አንድ ሐሳብ እንዲኖራችሁ፣ እርስ በርሳችሁም እንድትስማሙ
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።” (1ቆሮ. 1፡10)።
በዚህ ሳምንት ወጥ ባሕሪ የተላበሱና አስተማማኝ ግንዛቤ የሚሰጡ አንዳንድ የትንቢት መርሆዎችን እንመረምራለን።
እስቲ ወደ የትኛውም የክርስቲያን የመጻሕፍት መደብር ጎራ ብለው
በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ዙሪያ የተጻፉ ርዕሶችን ቃኘት ለማድረግ ይሞክሩ። ብዙም
ሳይቆዩ ለማሰብ የሚከብዱና የተወሳሰቡ፣ በዓይነታቸው የተለያዩ አመለካከትና
ፍቺዎች መኖራቸውን መመልከት ሲጀምሩ፣ እንደ ራእይ ያሉ መጽሐፎች የሚናገሩትን
ማንም ቢሆን በእውነት ማስተዋል አይችልም ብለው ወደማመኑ ሊፈተኑ ይችላሉ።
ለምሳሌ አንድ ደራሲ—የክርስቶስ ተቃዋሚ ከዘይቤአዊ አነጋገር የዘለለ ፋይዳ የለውም
ሲል፣ ሌላው ደግሞ ወደፊት መገለጡ አይቀሬ ነው ይላል። የክርስቶስ ተቃዋሚ ስለ
አንድ ነገር የተሰጠ ማጣቀሻ ወይም በአረማዊው ሮም ዘመነ መንግሥት የነበረ አንድ
ግለሰብ ነው—ይላል ሌላው ተንታኝ። አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ሰባኪ እንደተናገሩት፡
“ምናልባት መጽሐፍ ቅዱስ ቆየት ያለ ዕድሜ እንዳለው ቫዮሊን ነው፤ ማንኛውንም
የምትፈልገውን ዜማ ልትጫወትበት ትችላለህ።”
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ እንዲህ ያለውን አመለካከትም
ሆነ አስተሳሰብ አያጋራም። ይልቁንም እግዚአብሔር እየተናገረ ያለው በከንቱ
እንዳልሆነና በቃሉ የሚናገረውን እውነት ማወቅ እንደምንችል ከግንዛቤ በማስገባት
እናነበው ዘንድ ይጋብዘናል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 24:15፣ ራእ. 1:3፣ ማቴ. 11:29፣ ኤር.
9:23, 24። የእግዚአብሔር ማንነት በሌሎች ይስተዋል ዘንድ ዓላማና ፍላጎቱ
ስለመሆኑ ጥቅሶቹ ምን ይጠቁማሉ?
በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች መጽሐፍ ቅዱስን በሥነ ጽሑፍ ወይም ተመሳሳይነት
ባላቸው ኮርሶች ይሰጣሉ። አንድ ሰው የአረማውያንን አፈ ታሪክ በሚያወሳበት
ተመሳሳይ ድምጸት ፕሮፌሰሩ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቡን ለማስተዋል ሲባል ብቻ—
ስፍር ቁጥር በሌላቸው የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች ቁጭ ብሎ ቃላቶቹን መስማት
በእርግጥም አማኙን ሊያስገርም ይችላል። ሐሳቡ በታሪኮቹ ውስጥ አንኳር የሞራል
“እውነት” ሊኖር ይችላል የሚል ሲሆን፣ ደግሞም አንድ ሰው የፈለገውን ዓይነት ታሪክ
ፈጥሮ መጻፍ ይችላል የሚል እሳቤን ይዟል። ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በእግዚአብሔር
መንፈስ አነሳሽነት ነው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በመምህራኑ ዘንድ እንደ ፌዝ ይቆጠራል።
በመሆኑም መምህሩ መጽሐፍ ቅዱስን ያነባል እንጂ የእግዚአብሔርን
ድምጽ አይሰማም። ሌሎች ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጋር ፍጹም የሚጋጭ
መደምደሚያ ላይ ሲደርሱ ይታያሉ። ለጌታ እጃቸውን ሳይሰጡና እውነትን ለመማር
የሚያስችል የተከፈተ ልብ ሳይኖራቸው መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎች፣
መልእክቱን መሳት ብቻ ሳይሆን በገጾቹ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፍቅር እና
ቅዱስ ባሕሪ በተሳሳተ መንገድ ማስተዋላቸው አይቀሬ ነው። በመሆኑም በመንፈስ
ቅዱስ ምሪት ስር የዋሉ ትክክለኛዎቹ መሣሪያዎችና ቀና የሆነው አመለካከት ሳይኖር
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ብቻውን ጎጂ ሊሆን ይችላል።
አንድ በኃይማኖተኝነቱ የማይታወቅ ግለሰብ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ ሰዎች
ያዩታል። ምን እያደረገ እንደሆነ ሲጠየቅ፡ “ማምለጫ ቀዳዳዎችን እየተመለከትኩ”
ሲል ይመልሳል። እንዲህ ያለውን አመለካከት ይዞ የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ
የተሳሳተ አካሄድ የሆነው ለምንድን ነው?
የአገሩን ቋንቋ መናገር በማይችሉበት ባዕድ አገር ሆነው፣ ክሊኒክ ወይም
መድኃኒት ቤት የሚያስኬድ አጣዳፊ ጉዳይ ቢገጥሞትና ሐሳብዎን ማስረዳት ሳይችሉ
ሲቀሩ—ከዚህ በላይ ሊረብሽ የሚችል ነገር ላይኖር ይችላል። ምን ለማለት እንደፈለጉ
ቢያውቁም፣ ነገር ግን ያን ለመግለጽ የሚያስችል በቂ ቃላት የሎትም።
እግዚአብሔር እየተቸገረበት ያለው ነገር፣ ሌላ ነው። “ ‘ሰማያት ከምድር
ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ
ነው።’ ” (ኢሳ. 55፡9)። ችግሩ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ለመነጋገር የሚያስችል
በቂ ቃላት ስለሌለው ሳይሆን፣ እኛ እርሱን ለመረዳት የሚያስችል የቃላት ወይም
የዕውቀት ብቃት የሚጎድለን መሆኑ ነው።
ከዚህ በታች የቀረቡት ጥቅሶች የእግዚአብሔርን ማስተዋል ከእኛ ጋር እያነጻጸሩ
የሚሰጡት አስተያየት ምን ይመስላል?
መዝ. 139:1–6
መዝ. 147:5
ሮሜ 11:33
1ዮሐ. 3:20
የነገሩ እውነታ—እግዚአብሔር ወሰን የሌለው እና ሁሉን የሚያውቅ አምላክ
እንደመሆኑ የእርሱን አእምሮ ፈጽሞ ልንረዳ አንችልም። ደግሞስ ስለ ፍጥረት
ላመል ያህል ዕውቀት ይዘን ስናበቃ የፍጥረት ባለቤት የሆነውን ፈጣሪ አምላክ
ሙሉ በሙሉ መረዳት የምንችለው እንዴት ነው? አንችልም!
ምንም እንኳን ሁሉንም ነገር መረዳት ባንችልም ለመዳን የሚያስፈልገንን
ነገር ግን መረዳት እንችላለን (2ጢሞ. 3 14-15)። ሐዋርያት ወንጌልን
ለአድማጮቻቸው ያብራሩ በነበረበት ወቅት ፍጻሜ ያገኙ ትንቢቶችን በተደጋጋሚ
ይጠቅሱ ነበር። ከዚህ አኳያ ከትንቢት ቁልፍ ዓላማዎች አንዱ የደኅንነትን እቅድ
በጉልህ ማሳየት ነው ብለን መውሰድ እንችላለን። በእርግጥ፣ ውሎ አድሮ፣ የመጽሐፍ
ቅዱስ ትንቢቶች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ፣ ወደ የሱስ እና እርሱ ለሰው ልጆች
ሁሉ ወደሚሰጠው የደኅንነት ተስፋ ሊመሩን ግድ ይላል።
ለነገሩ ሁሉም ነገር በእርሱ የተፈጠረ (ቆለ. 1፡16፣ ዮሐ. 1፡1-3) ሆኖ
ሳለ፣ ይህ ጌታ ወደዚህ ምድር ወርዶ እጅግ ምስኪንና ጎስቋላ ለሆነው ሰው ሳይቀር ስለ
እያንዳንዱ የሰው ልጅ ኃጢአት ራሱን በመስቀል ላይ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ይህ
ደግሞ እግዚአብሔር ምን ያህል ሁላችንንም እንደሚወደን ያሳያል። ጌታ ይህን ሁሉ
ለእኛ ካደረገ በኋላ፣ ልባቸው የተሰበረ ምስኪኖችን ጨምሮ፣ በየሱስ የሰጠንን ነገር
እያንዳንዱ ሰው ያውቅ ዘንድ አጥብቆ ይፈልጋል። ትንቢት፣ ይህን ማድረግ ይችላል።
ምንም እንኳን በርካታ የማናውቃቸው ነገሮች ቢኖሩም፣ በእነዚህ በማናውቃቸው
ነገሮች ላይ ከመብሰልሰል በተቃራኒ አሁን በምናውቀው ነገር ላይ ማተኮርና
የምናውቀውን ነገር መከተል ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዳን. 12:4። ጌታ ዳንኤልን ምን እያለው ነበር? (ከ ራእ. 22:10 ጋር ያነጻጽሩ)
ሰባኪዎች ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት አስቀድሞ በዳን. 12፡4 የቀረበውን
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ግስጋሴ ትንቢት ሲጠቅሱ መስማት የተለመደ ነው።
በተጨማሪም ብዙዎች ባለፈው ምዕተ ዓመት ወይም ከዚያ ጥቂት ቀደም ብሎ
በነበሩት ጊዜያቶች የተስተዋለውን ፈጣን የዕድገት ግስጋሴ ለመግለጽ ይጠቀሙበታል።
አብዛኞቹ መጻሕፍቶቻችንም ይህንኑ አካሄድ ተከትለው የተቃኙ ናቸው። ምንም
እንኳ አመክኖአዊ ትንታኔ መስጠታቸው እሙን ቢሆንም፣ ሌላ ሊሉ የፈለጉት ነገር
ሊኖርም ይችላል።
ጥቅሱን እንደገና ያንብቡ። መልአኩ ለዳንኤል የሰጠው መመሪያ
የሚጀምረው “የመጽሐፉን ቃል ዝጋ፤ አትመውም” የሚል ትእዛዝ በመስጠት
ነው። የመነጋገሪያው ርዕሰ ጉዳይ ራሱ የዳንኤል መጽሐፍ ነው። ምናልባት በዘመኑ
ፍጻሜ ላይ በድንገት የሚከሰተው የዕውቀት መብዛት ራሱን የዳንኤልን መጽሐፍ
ማወቅና ማስተዋል ይሆን?
ይህም የዳንኤልን መጽሐፍ ከዮሐንስ ራዕይ የተለየ የሚያደርገው ሲሆን፣
ዮሐንስ የጻፈውን መጽሐፍ በማኅተም አንዳይዘጋው ተነግሮታል (ራዕ. 22፡
10)። ሲጀመር፣ የራእይ መጽሐፍ “ ‘ጊዜው ስለደረሰ’ ” እንዲስተዋል ሆኖ
የተዘጋጀ ነው። በአንጻሩ የዳንኤል መጽሐፍ ከብዙ ዘመናት በኋላ ሲታይ በተወሰነ
ደረጃ ይበልጥ ግልጽ ሆኖ የሚስተዋል ዓይነት መልእክት ይዟል።
ባለፉት ምዕተ ዓመታት በርካታ ክርስቲያን ምሑራን የዳንኤልን መጽሐፍ
ለማብራራት የሞከሩ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም ታላቅ የሚባል ዓይነት የግንዛቤ እመርታ
አስመዝግበዋል። በዚህም የዳንኤል መጽሐፍ ግንዛቤ በፍጥነት እየጨመረ ሄደ።
ይሁን እንጂ በ1798 ዓ.ም. ፍጻሜ ያገኘው የ1,260 ዓመታት ትንቢት ካበቃ
በኋላ፣ በርከት ያሉ የመጽሐፉ መርማሪዎች በ1843 አካባቢ አንድ አስደናቂ
ነገር ይፈጸማል ወደሚል ድምዳሜ ደረሱ። ታዲያ ከእነዚህ መካከል ዋነኛው
ዊልያም ሚለር ነበር። የእርሱ ስብከት የአሥራ ዘጠነኛውን መቶ ክፍለ ዘመን
የታላቁን የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተጠባባቂዎች እንቅስቃሴ ወደ ሥራ በማስገባት
ለ“ትሩፋኗ” ቤተ ክርስቲያን መወለድ መንስኤ የሆኑ ተያያዥ ክስተቶች ገቢራዊ
ሆኑ። በተጨማሪም የሦስቱ መላእክት መልእክት በግልጽ መስተዋል ጀመረ።
በሌላ አነጋገር የእኛ ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ መወለድ ዳንኤል በ “ፍጻሜው
ዘመን” “ዕውቀትም ይበዛል” በማለት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ነው።
በሰዎች ደኅንነት ላይ ፍርድ ሳይሰጡ ነገሩን በአንጻራዊ በመመልከት
ብቻ በርካታ ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ስላጠላው “ጨለማ” አሰብ ያድርጉ።
በኤደን የተቋቋመው እንደ ሰባተኛው ቀን ሰንበት ያለ መሠረታዊ ሥርዓት ችላ
ተብሎ፣ አልፎ ተርፎም ውድቅ ተደርጎ በሮም አረማዊ ሥርዓት ሥር እንዲሰድ
የተደረገው የእሁድ ቀን አምልኮ እንዲተካ ተደርጓል። ወይም ደግሞ አብዛኛው
ሕዝበ ክርስቲያን ሰው ሲሞት ወዲያውኑ ወደ ሌላ ሕያው ተፈጥሮ ተቀይሮ መኖር
ይቀጥልና አንዳንዶች ለዘላለም በሚነድ የገሃነም እሳት እየተቃጠሉ ይኖራሉ—
በሚለው አረማዊ አስተሳሰብ ስለሚያምን ሞትን አስመልክቶ ምን ያህል ፍጹም
በሆነ አለማወቅ ውስጥ እየተመላለሰ እንደሆነ ልብ ይሏል።
በአንጻሩ እኛ እውነትን ማስተዋል በመቻላችን በእጅጉ አመስጋኞችና
ትሑታን መሆን ይገባናል።
ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ለማስተዋላቸው
ዊልያም ሚለር ጉልህ ስፍራ አለው። ምንም እንኳ በአንዳድ ቁልፍ ጥቅሶች (ዳን.
8፡14) ዙሪያ የነበረው ግንዛቤ ፍጹም ባይሆንም ሚለር ጥቅም ላይ ያዋለው ዘዴ
በእጅጉ ወሳኝ ነበር። ይህን ተከትሎ ለመጨረሻው ዘመን ትሩፋን ሕዝቦች እንቅስቃሴ
መወለድ መንገድ መጥረግ ችሏል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 5:18፣ 2ጢሞቴ. 3:15–17፣ ሉቃ፣ 24:27።
ጥቅሶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በምን ዓይነት ዘዴ መመርመር እንዳለብን
አስመልክቶ ምን ያስተምሩናል?
አንዳንዴ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የተለያዩ ቁርጥራጭ ምስሎችን አንድ
ላይ በማጋጠም እንደሚገኝ ትልቅ ሥዕል ነው። ሁለት ወይም ሦስት ቁርጥራጭ
ምስሎችን ብቻ አንድ ላይ ደርድሮ ሙሉውን ምስል ማግኘት አይቻልም። ምናልባት
በእነዚያ ሁለት ወይም ሦስት ቁርጥራጮች ላይ የፈረስ ምስል መመልከት
በመቻልዎ ብቻ እየገጣጠምኩ ያለሁት የፈረስ ሥዕል ነው ወደሚል ድምዳሜ
ይደርሱ ይሆናል። ይሁን እንጂ በሌሎች ጥቂት ተጨማሪ ቁርጥራጮች ላይ የዶሮ
እንዲሁም የላም ምስል መኖሩን ይመለከታሉ። ከዚያም እነዚያን ምናልባትም
በመቶዎች የሚቆጠሩ ቁርጥራጭ ምስሎች በአንድ ላይ ካጋጠሙ በኋላ በመጨረሻ—
ከተማ፣ የእርሻ ቦታና በተለያየ ርቀት የሚታዩ ተራሮችን ያካተተ መልክአ ምድራዊ
አቀማመጥ አገጣጥመው እየሠሩ እንደሆነ ይመለከታሉ።
አንዳንድ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ ከሚሠሯቸው አበይት
ስህተቶች መሃል—ጥቅሶቹን ለሆነ ክስተት ወይም ሁኔታ ገጣሚ አድርገው ለመጠቀም
የሚያስችሏቸው አድርገው ከመመልከት ባለፈ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ጥብቅ ቁርኝት
እንደሌላቸው ስብስቦች ወይም ምሳሌያዊ አነጋገሮች አድርገው መመልከታቸው
ነው። አንዳንዶች ጌዴዎን በሚል ስያሜ በሚታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ቀዳሚ
ገጾች ወደሚገኘው ቀለል ያለ የጥናት መምሪያ ይገልጣሉ። ከዚያም በበርካታ
ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳብ የሚሰጡ ጠቃሚ ጥቅሶችን በቅደም ተከተል የያዘውን
ክፍል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የሚያስተምራቸውን ትምህርቶች
በአጠቃላይ እንደሚወክል አድርገው ይወስዳሉ።
የሚያሳዝነው ትንቢትንም አስመልክቶ ተመሳሳይ አካሄድ ይጠቀማሉ።
በዚህም አንድን ጥቅስ ከዐውደ ሀሳቡ ነጥለው በመውሰድ ከተቀረው የመጽሐፍ
ቅዱስ ክፍል ጋር ሳይሆን ከወቅታዊ ክስተቶች አኳያ ያነጻጽሩታል። በዚህም በትንቢት
ዙሪያ የተጻፉ የዘመኑ ሥራዎች ያለማቋረጥ በየጊዜው እየተከለሱ እንዲጻፉ ምክንያት
ሆኗል። ለዚህ መንስዔው ይሆናል ብለው የጻፉት ሳይሆን እየቀረ መቸገራቸው ነው።
በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የተጻፉ የተወሰኑ ጥቅሶችን መምረጥ ብቻ
ሳይሆን፣ ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ በነዚህ ነጥቦች ዙሪያ የሚናገረውን በጥንቃቄ
ማጥናትና የተናገረበትን ዐውድ ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። አንድን
ጥቅስ ከዐውዱ ነጥለን በማውጣት የምንፈልገውን እንዲናገር ማድረግ በጣም
ቀላል ነው።
የተወሰኑ ጥቅሶችን ብቻ በመምረጥ የሚፈልጉትን ለማለት የሚሞክሩ ሰዎችን
አስመልክቶ የእርስዎ ተሞክሮ ምን ይመስላል—ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ወይም
ስለ ሰንበት? ምላሽ ለመስጠት ከሁሉ የተሻለው መንገድ የቱ ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አጥኚዎች ሊጋፈጧቸው ከሚችሉ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ቋንቋ እንዴት መወሰድ ይኖርበታል—እንደ ወረደ (ቃል በቃል) ወይስ በተምሳሌታዊነት—የሚለውን መወሰን ነው። ጸሐፊው ተምሳሌታዊ መንገድ ተጠቅሞ እንደሆነና እንዳልሆነ የሚወሰነው እንዴት ነው? ተምሳሌቶቹ የሚወክሉት ምን እንደሆነስ እንዴት ማወቅ ይቻላል? ይህን ለማድረግ ወሳኙ መንገድ የተጠቀሰው አሃዝም ሆነ ምልክት በዘመናችን አንዴት ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ ከማየት በተቃራኒ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ መመልከት ነው። ለምሳሌ፣ አንዳንዶች በዳንኤል 7 የተጠቀሰው የድብ ምስል ሩሲያን እንደሚያመለክት አድርገው ያስባሉ። ለዚህ መንስኤው ይህ ምስል ዛሬ የሩሲያ ምልክት ሆኖ እያገለገለ በመሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ እንዲገልጥ የሚፈቅዱትን የሚከተሉትን ጥቅሶች ይመልከቱ። በሁሉም ጥቅሶች ላይ የሚገኝ ትንቢታዊ ምልክት ምንድን ነው? ምልክቱ የሚወክለውን አስመልክቶ መጽሐፍ ምን ይላል? ዳን. 7:7፣ ዳን. 8:3፣ ዳን. 7:24
ራእ. 1:16፣ ኤፌ. 6:17፣ ዕብ. 4:12
ራእ. 12:1፣ ራእ. 21:2፣ ኤፌ. 5:31-32፣ ኤር. 6:2
መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ እንዲፈታ መፈቀድ ይኖርበታል የሚለውን
ቀለል ያለ ሕግ በመከተል፣ ከትንቢታዊው ተምሳሌታዊ አገላለጾች በስተጀርባ ያሉ
የተሰወሩ ነገሮች በቀላሉ ይወገዳሉ። ለምሳሌ ቀንድ የፖለቲካ ሥልጣንን ወይም
አገርን ሊያመለክት እንደሚችል እንመለከታለን። ሰይፍ የእግዚአብሔርን ቃል፣ ሴት
ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ልትወክል ትችላለች። በዚህ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን
በራሱ ሲያብራራ በግልጽ መመልከት እንችላለን።
እግዚአብሔር በግልጽ ከመናገር ይልቅ በተምሳሌታዊ መንገድ የተናገረው ለምን
ነበር? ለአብነት ያህል በ 1ጴጥ. 5፡13 ላይ ሐዋርያው የሮም ከተማን ባቢሎን
በሚል ምስጢራዊ አገላለጽ የሚጠራው ለምንድነው?
እግዚአብሔር ትንቢትን በተምሳሌታዊ መንገድ ለመናገር የመረጠበት
በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ የአዲስ ኪዳኗን ቤተ ክርስቲያን
ብንወስድ፣ ሮም ያን ሁሉ ክፉ ድርጊትና ግፍ ታደርሳለች ብሎ የራእይ መጽሐፍ
በግለጽ ቢናገር ኖሮ፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰችው አስከፊና መጠነ ሰፊ ስደት
በእጅጉ የከፋ ሊሆን በቻለ ነበር። ምክንያቱ የቱንም ዓይነት ሊሆን ቢችል እንኳ፣
ተምሳሌታዊዎቹ አነጋገሮች የያዙትን ፍቺ እንረዳ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ
መሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
ምናልባት አንዳንድ ምልክቶችና ትንቢቶች ምሥጢር እንደሆኑ ቢቀሩ እንኳ፣
በተረዳነው ነገር ላይ ማተኮር እምነታችንን የሚያጠናክረው እንዴት ነው?
“አሜሪካዊ ተሐድሶ አራማጅ” ታላቁ ተጋድሎ ከገጽ፡
366-394።
“አገልጋዮችና ሕዝቡ የዳንኤልና የራእይ የትንቢት መጻሕፍት ለመረዳት
የማይቻሉ ምስጢራት እንደሆኑ አወጁ። ሆኖም ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር
በዘመናቸው ሊፈፀሙ ስላሉ ክስተቶች የነብዩን የዳንኤልን ቃላት እንዲመለከቱ
ሲመራቸው ነበር፤ እንዲህም አለ፦ “አንባቢው ያስተውል” [ማቴ 24÷15]።
ራዕይ መጽሐፍ ምስጢር እንደሆነና ለመረዳት የማይቻል ነው ብሎ መፈረጅ
ከመጽሐፉ ርዕስ ጋር የሚቃረን ነው [ርዕሱ መገለጥ /Revelation ነው]፤
“የየሱስ ክርስቶስ ራዕይ እግዚአብሔር የሰጠው ፈጥኖ የሚሆነውን ለባርያዎቹ
ይገልጥ ዘንድ….ምስጋና ይገባዋል [የተባረከ ነው]፣ ለሚያነብ የዚህንም ትንቢት
ነገር [ቃል] ለሚሰሙ በእርሱ የተጻፈውንም ለሚጠብቁ _ ዘመኑ ቀርቦአልና"
[ራዕይ 1÷1-3)…
“ሰዎች የመንፈስን ምስክርነት እያዩ፣ ራአይ ምስጢር ነው፤ ከፍጡራን
ማስተዋል በላይ ነው፤ ብለው ለማስተማር እንዴት ደፈሩ? የተገለጠ ምስጢር፣
የተከፈተ መጽሐፍ ነውና። የራእይ ጥናት የሰዎችን አዕምሮ ወደ ዳንኤል ትንቢቶች
የሚያመላክት፣ ሁሉንም በዚህ ዓለም ታሪክ መደምደሚያ ሊከናወኑ ያላቸውን
ክስተቶች በተመለከተ ለሰዎች ከእግዚአብሔር የተሰጠውን እጅግ አስፈላጊ
ትምህርት የሚገለጽ ነው።
“ለዮሐንስ ጥልቅና አጓጊ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ተሞክሮ ትዕይንቶች
ተገለጡለት። እርሱ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ደረጃ (አቋም)፣ አደጋዎች፣
ግጭቶችና የመጨረሻውን መዳን አይቷል። ለሰማያዊው ጎተራ ነዶ፣ ወይም ለጥፋት
አሳት ገለባ አድርገው የዓለምን መከር የሚያደርሱትን የመደምደሚያ መልእክቶች
ዘግቧል። በተለይም ለመጨረሻዋ ቤተ ክርስቲያን ብሎ ከስህተት ወደ እውነት
ለሚመለሱ ለእነርሱ በፊታቸው ስላሉት አደጋዎችና ጦርነቶች ያውቁ ዘንድ መጠነ
ሰፊ አስፈላጊነት ያላቸው ጉዳዮች ለእርሱ ተገልጸውለታል። በምድር ላይ ሊመጣ
ያለውን በተመለከተ ማንም በድንግዝግዝ ውስጥ መሆን አይገባውም።” (ታላቁ
ተጋድሎ፡ ገጽ፡ 392-393)።
1. የትንቢት ጥናት እምነትዎን በእጅጉ ሊያሳድግልዎ የሚችልባቸው መንገዶች
የትንቢት ጥናት እምነትዎን በእጅጉ ሊያሳድግልዎ የሚችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለዎት እምነት እንዲጨምርና ከሁሉም
በላይ ደግሞ በመንፈሱ አነሳሽነት እንዲጻፍ ባደረገው በእግዚአብሔር አምላክ
ላይ ያሎት እምነት እንዲጎለብት ምክንያት ከሆኑ—በሺህዎች ከሚቆጠሩ
ዓመታት በፊት ተጽፈው በመቶዎች በሚቆጠሩ ዓመታት ወይም በሺህ
ዓመታት ክንውን ያገኙ አንዳንድ ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው? ለምሳሌ ዳን. 2
እግዚአብሔር ስለ መኖሩ ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን እንደሚያውቅ እንተማመን
ዘንድ ኃይለኛ እና አመክኖአዊ የሆኑ ምክንያቶችን የሚሰጠን እንዴት ነው?
2. አንዳንዴ ከገዛ ቤተ ክርስቲያናችን ሳይቀር፣ ትንቢቶችን ለመተርጎም ከሚደረጉ
አንዳንዴ ከገዛ ቤተ ክርስቲያናችን ሳይቀር፣ ትንቢቶችን ለመተርጎም ከሚደረጉ
በርካታ ባዕድ እና ግምታዊ ሙከራዎች ራሳችንን ልንጠብቅ የምንችልባቸው
ምርጥ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? “ነገር ግን ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካም
የሆነውን ያዙ” (1ተሰ. 5፡21) የሚለውን መልእክት ተግባራዊ ስናደርግ
ጥንቃቄ እንዳይለየን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?