የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ
ፍንጮች፣ ምስሎች፣ ምሳሌዎች፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ማጥኛ መንገድ
2ኛ ሩብ ዓመት 2025
ሚያዝያ፣ ግንቦት፣ ሰኔ 2017 ዓ.ም.
መደበኛ እትም
Mar 29 - Jun 27
አዘጋጅ : ሾውን ቡንስትራ
ትርጉም : ዘላለም አስረስ
ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው
የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ-ክርስቲያን ዋና መሥሪያ ቤት በሆነው በጀነራል
ኮንፈረንስ ሥር መምሪያውን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያው የሚዘጋጀው
በሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ሲሆን፣ ቦርዱ የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ
ንዑስ ኮሚቴና የመምሪያው አሳታሚ ነው። መምሪያው ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና
ኮሚቴ ሐሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ፣
የአዘጋጁን ሐሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም። በዚህ ሰንበት ትምህርት መምሪያ
ውስጥ የሚገኙት ጥቅሶች የተወሰዱት በ1954 ዓ.ም በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ
ማኅበር ከታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
2ኛ ሩብ ዓመት
ከመጋቢት 20 እስከ ሰኔ 20/ 2017
በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ
ትንቢት ገላጭ
ፍንጮች
በዓይነቱ የመጀመሪያ በነበረው የባሕረ ሰላጤው ጦርነት (1983 ዓ.ም.) አንድ
ታዋቂ የፕሮቴስታንት እምነት ጸሐፊ እና ሰባኪ፣ የራእይ መጽሐፍ ይህን ግጭት በትንቢት
ለመናገሩ እርግጠኛ ነበሩ። መሞገቻ ነጥባቸው የጦርነቱ አካል ከነበሩት ሄሊኮፕተሮች
መካከል አንዳንዶቹ በራእ. 9 የተገለጹትን አንበጦች ይመስላሉ የሚል ነበር። “ጥልቁን
ጕድጓድ በከፈተውም ጊዜ፣ ከውስጡ ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ያለ ጢስ ወጣ።
ከጕድጓዱም በወጣው ጢስ ፀሓይና ሰማይ ጨለሙ።ከጢሱም አንበጦች ወጥተው
በምድር ላይ ወረዱ፤ እንደ ምድር ጊንጦች ሥልጣን ያለ ሥልጣን ተሰጣቸው” (ራእ. 9፡2-3)።
መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትንቢት ለመተርጎም ይህ የተሻለ አካሄድ ነው ለማለት
ይቻላል? ለነገሩ እንዲህ ያሉ የአተረጓጎም ስልቶች በእጅጉ የተለመዱ ናቸው። ባለፉት
አሥርተ ዓመታት ትንቢትን መሰረት አድርገው የተዘጋጁ ተከታታይነት ያላቸው መጻሕፍት፣
መጣጥፎች፣ ቪዲዮዎች፣ አሁን ደግሞ አዳዲስ ድረ-ገጾች በስፋት ሲሰራጩ ይስተዋላል።
እነዚህን ወደ ሕዝብ የመድረሻ ዘዴዎች በመጠቀም በርካታ ትንበያዎች የቀረቡ ሲሆን፣
በመጨረሻዎቹ ቀናት ክስተቶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑት—ባብዛኛው የመካከለኛውን
ምሥራቅ ጦርነቶች ወይም ሁከቶች ማዕከል ያደረጉ፣ አልፎ ተርፎም ቀን እስከ
መወሰን የደረሱ ናቸው። የሚገርመው በዚህም አሉ በዚያ፣ ከትንበያዎቹ አንዳቸውም
እንደተባለው ሳይሰምሩ ቀርተዋል። ይህ ደግሞ ጉዳዩን የድንገቴዎች ሁሉ ድንገቴ አድርጎታል።
እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ሕዝብ፣ በመካከለኛው
ምሥራቅ በሚገኝ አንድ መልክአ ምድራዊ ቦታና በዚያ በሚፈጠር ማንኛውም
ዓይነት ወታደራዊ ግጭት ላይ አጽንኦት የሚሰጥ ትንቢት ማክተሙን በመገንዘብ፣
የምንከተለው የትንቢት አፈታት ስልት ከዚህ የተለየ ማለትም ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ
ነው። በመሆኑም ትንቢቶቹን የምንመለከተው በክርስቶስ እና በሰይጣን መካከል
እየተካሄደ ባለው ታላቁ ተጋድሎ መነጽር ነው። ዓለምን ዳር እስከ ዳር የሚያናውጠው
መንፈሳዊ ግብግብ፣ አይሁድ እና አሕዛብ የእግዚአብሔር ሕዝቦች (ራእ. 12፡7፣ ራእ. 14፡
12) ከአውሬውና ከምስሉ በተቃራኒ ለፈጣሪ አምልኮ ማቅረብን ማዕከል ያደረገውን
(ራእ. 14፡7) የመጨረሻውን ቀውስ ሲጋፈጡ፣ መንፈሳዊ ትግሉ ጡዘት ላይ ይደርሳል።
እነዚህን ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የተነገሩ ትንቢቶች ለማስተዋል የሚረዳን ቁልፍ
መልእክት በዳን. ምዕ. 2 የሚገኝ ሲሆን፣ ምዕራፉ የትንቢቶቹን ታሪካዊ ይዘት ብቻ
ሳይሆን ትርጉማቸውንም ለመተርተር የሚያስችል የትንቢት መፍቻ ቁልፍ ይዟል።
ዳንኤል ምዕራፍ 2 አራቱን የዓለም ልዕለ ኃያላን መንግሥታት—ባቢሎን፣
ሜዶንና ፋርስ፣ ግሪክ እና ሮም በቅደም ተከተል ካሳየን በኋላ፣ እነርሱን ተከትሎ
በእግዚአብሔር የሚመሰረተውን ዘላለማዊ መንግሥት ያቀርብልናል፡ “ ‘በእነዚያ
ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ
መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ እስከ መጨረሻውም
ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።’ ” (ዳን. 2፡44)።
በዳን. 7 እና 8 የቀረቡት ተመሳሳይ ትንቢቶች የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት
እስኪመሰረት ድረስ ያለማሰለስ የሚቀጥለውን የእነዚህን ምድራዊ መንግሥታት
መነሣትና መውደቅ መሰረታዊ መግለጫዎች ይዘዋል።
በዳንኤል ምዕራፍ 7 የመልአኩ ትርጓሜ ምልአተ ቃል እንደሚከተለው
ቀርቧል፡ “ ‘ “አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ መንግሥታት ናቸው፤ነገር ግን
የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፤ ለዘላለምም ይይዙታል፤ አዎን፤ ለዘላለም
ይይዙታል።” ’ ” (ዳን. 7፡17-18)። የሱስ ዳግም ተገልጦ እግዚአብሔር ዘላማዊ
መንግሥቱን እስኪመሰርት ድረስ እነዚህ አራት የዓለም ልዕለ ኃያላን መንግሥታት
(ባቢሎን፣ ሜዶንና ፋርስ፣ ግሪክ እና ሮም) ያለ አንዳች መፋለስ ቅደም ተከተላቸውን
እንደጠበቁ ይዘልቃሉ።
ክርስቶስ ዳግም እስኪገለጥ እነሆ ዛሬ፣ በአራተኛው እና በመጨረሻው
የዓለም ልዕለ ኃያል ሮም ስር የመኖራችን ነገር እሙን ነው።
ትንቢቶችን ለመረዳት ቁልፍ የሆነውን ይህን ታሪክን መሰረት ያደረገ አመለካከት
ጥቅም ላይ በማዋል የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች እንዴት እንደሚተረጎሙ—በተለይ
ደግሞ አንዳንድ ፍንጮችን፣ ታሪኮችን፣ ምስሎችን እና የመጨረሻዎቹን ክስተቶች
ከፍተው የሚያሳዩንን ዘይቤአዊ አቀራረቦች በዚህ ሩብ ዓመት እናጠናለን።
ከኦሪት ዘፍጥረት የፍጥረተ ታሪክ መነሾአችንን አድርገን—ታሪክን ብቻ ሳይሆን
ያን ተከትሎ የሚመጣውን ለማስተዋል አስፈላጊ ከሆነው፣ በተለይ ከመስቀሉ እና
ከየሱስ የሥርየት ሞት—እስከ ባቤል ግንብ፣ የቤተ መቅደሱ አገልግሎት፣ መዝሙረ
ዳዊት አልፎ ተርፎም እስከ ብሉይ ኪዳን ጋብቻዎች እንዘልቃለን። በእነዚህ ሁሉ እና
ከዚያ በላይ ደግሞ በጸሎት፣ በትህትና እና በታዛዥ መንፈስ ስናጠና (አመጸኛ ልብ
ይዘን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ የምናመራ ከሆነ፣ ጊዜያችንን በከንቱ ከማጥፋት በቀር
የምናገኘው አንዳች ጥቅም አይኖርም) የመጨረሻዎቹን ጊዜያቶች አስመልክቶ
የቀረቡት ምስሎች፣ ምሳሌዎች እና ዘይቤአዊ አቀራረቦች በተለይ ደግሞ የራእይ
መጽሐፍ ፍንትው ይልልናል።
ትንቢታዊውን እውነት ገልጦ ለመመልከት የሚረዱ ሁሉንም ታሪኮች እና
ምስሎች ለማጥናት ሳይሆን—ጥናቱን ለመጀመር እንኳ የሦስት ወር የሰንበት
ትምህርት ጥናታችን በእርግጠኝነት በቂ አይደለም። ማን ያውቃል—ለዚህ ዘላለማዊነት
ሊያስፈልግ ይችላል! እስከዚያው ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የምንችለውን እናጠናለን።
ሾውን ቡንስትራ (Shawn Boonstra) የትንቢት ድምጽ አገልግሎት ተናጋሪ እና
ዳይሬክተር ናቸው። ዩቲውብን ጨምሮ የእርሳቸው ስርጭቶች እና መጻሕፍት በዓለም
ዙሪያ የመነቃቃት ምንጮች ለመሆን የቻሉ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት ከአንታርክቲካ
በስተቀር በሁሉም አህጉራት የወንጌል ቀጥታ ስርጭታቸውን አቅርበዋል።
Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL